በዚህ የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስትር አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በአገሪቱ የመምህራንን ተጠቃሚነት በማሳደግ የትምህርት ጥራትን አሁን ካለበት ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋግራል ብሎ መንግስት እየተገበራቸው እና የሚተገብራቸውን ማሻሻያዎች ይፋ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለፁት፥ ቀደም ሲል ከሁለት እርከን ይጀመር የነበረው የመምህራን ደሞዝ ከሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በ10 እርከን የሚጀመር ይሆናል።
ከደሞዝ ማሻሻያው በተጨማሪ በአዲስ አበባ ለሚገኙ መምህራን 5 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።
ሌሎች 19 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችም ለአዲስ አበባ መምህራን በመገንባት ላይ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
በሌሎች አከባቢዎች እና በተለይም በገጠር አከባቢዎች የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ የመኖሪያ ቤት መስሪያ መሬት በቀላሉ እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት አቶ ሽፈራው፥ በተጨማሪም ቤት ተገንብቶ እንዲሰጣቸው ይደረጋል ነው ያሉት።
ዛሬ በአፍሪካ ህብረት እየተካሄደ ባለው የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ከአዲስ አበባ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተመረጡ 128 መምህራን ተሸላሚ ሆነዋል።
በስራ አፈጻጸማቸው ውጤታማ ለሆኑት መምህራን ሽልማት መበርከቱ ለቀጣይ ትውልድን የማነጽ ስራ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ።
“ክብርና ምስጋና ለህዳሴው ትውልድ አናጺ መምህራን” በሚል መሪ ቃል ነው የሽልማት ስነ ስርዓት እየተካሄደ ያለው።