Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

‹‹ሀሳብ ስጋት የሆነበት መንግስት ሀገር መምራት አይችልም›› (ጋዜጠኛ ጸደይ ለማ)

$
0
0

‹ሀሳብ ስጋት የሆነበት መንግስት ሀገር መምራት አይችልም››
‹‹መንግስት ሀሳብን ፈርቶ መኖር አይችልም››
‹‹ሕገ-መንግስቱን ሳያከብር ‹መንግስት ሆኜ እቀጥላለሁ› ካለ የዋህነት ነው››

ወደጋዜጠኝነት ሞያ ከተቀላለቀች 16 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ በሆነችው ‹‹አዲስ ትሪቡን›› ላይ ጋዜጠኝነትን አንድ ብላ ጀመረች፡፡ ‹‹ኢንተርፕርነር›› እና ‹‹ዴይሊ ሞኒተር›› በተሰኙ እንግሊዘኛ ጋዜጦች ላይም ሰርታለች – ጋዜጠኛ ጸደይ ለማ፡፡

ጸደይ፣ በድረ-ገጽ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚጻፉ ጽሁፎችን ያትም በነበረው ‹‹Europian news agency›› ላይም ትጽፍ ነበር፡፡ በሺኖዋ የዜና አገልግልት ላይም የጋዜጠኝነት አበርክቶ ነበራት፡፡ በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ፣ በሚዲያ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ዙሪያ ለአራት ዓመታት በአማካሪነትም ሰርታለች፡፡ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ ወርሃዊ የእንግሊዘኛ መጽሄት የሆነችውን ‹‹አዲስ ስታንዳርድ›› መጽሄትን ከመሰረቱት ሰዎች መካከል አንዷ የሆነችው ፀደይ፣በአሁኑ ወቅትም የመጽሔቷ ዋና አዘጋጅ ሆና በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ መብት አኳያ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ኤልያስ ገብሩ ከጋዜጠኛ ጸደይ ለማ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንዴት ታይዋለሽ?

ከባድ ጥያቄ ነው፡- ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ መቻል ሁለት የተለያዩ ገፅታዎች ናቸው – በኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሁለት ነው የምለው …የምትገልጸው ሀሳብ በተለይ መንግስት የሚያቀነቅንባቸው ወይም የመንግስትን እሳቤ የሚያቀነቅኑ ከሆኑ ችግር የለብህም፡፡ እስከፈለህ ድረስ መግለፅ ትችላለህ፡፡ ሌሎችን እስከማስፈራራት የሚደርሱ ሀሳቦችን ጭምር እስከመግለጽ ድረስ መሄድምትችላለህ፤ መብቱ አለህ፡፡

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሲባል ግን፤ በነፃነት ለአንተ የሚሰማህንና የምትፈልገውን ሀሳብ መግለጽመቻል ማለት ነው፡፡ የምትፈልገውን ሀሳብስትገልጽ ብዙ ጊዜ ከመንግስት ጋር የማይጣጣም ከሆነ ከባድ ይሆናል፡፡

ለምሳሌ፣ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆነው ዮናታን ተስፋዬ ላይ ሰሞኑን የቀረበበት የሽብር ክስን ማየት ይቻላል፡፡ የዮናታን ሀሳብ ከመንግስት ጋር የማይጣጣም ስለነበረ ለሽብርተኝነት የሚያደርስ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡

በእንደዚህ አይነት ሁኔታውስጥ ነው እንግዲህ እንደጋዜጠኝነት ሀሳብን የምታንሸራሽረው፡፡ ሀሳብን ለመግለጽ ስትፈልግ ‹‹ምንድን ነው የምገልጸው?›› ብለህ ቆመህ አስበህ፣ ‹‹ብገልጸውስ ችግር ሊያመጣብኝ ይችላል ወይስ አይችልም?›› ብለህ ብዙ ጊዜ በማሰብ ነው የምትገልጸው፡፡ከዚህ አኳያ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በኢትዮጵያ ብዙ ችግር እንዳለው እገነዘባለሁ፡፡

ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሕገ-መንግስታዊ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮ የሰጠን ሰብዓዊ መብትም ጭምር ነው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ፣ ይሄ መብት በምን ደረጃ ላይ አለ ብሎ መናገር ይቻላል?

እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እያደገ የመጣ አይደለም፡፡ ሲጀመር፣ የገለጽከው ሀሳብ ውጤቱ በአንተ ላይ አደጋየሚያመጣ ከሆነ፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ውስጥ ላትገባ ትችላለህ፡፡

መንግስትም በሚያሳዝን ሁኔታ እንዳያድግ ካደረጋቸው እና እንዳያድጉም ከሚፈልጋቸው በርካታ ነገሮች መካከል አንዱ የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡ ለዚህ ብዙ ማመላከቻዎች አሉ፡፡ መንግስት የሚከተላቸው የሚዲያ ሕጎች፣ የሚዲያ ተቋማትቁጥርና ተደራሽነትታቸው ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ ምን ያህል ለህዝቡ ተደራሽ ናቸው? ህዝቡስየፈለገውን መረጃ ለማግኘት እና እነዚህን የሚዲያ ተቋማት ለመጠቀም ምንያህል መብት አግኝቷል? ብለህ ስትመለከት እጅግ የተገደበ ነው፡፡

 ጋዜጠኛ ጸደይ ለማ /የ‹‹አዲስ ስታንዳርድ›› መጽሄት ዋና አዘጋጅ/
ጋዜጠኛ ጸደይ ለማ /የ‹‹አዲስ ስታንዳርድ›› መጽሄት ዋና አዘጋጅ/

ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ በነፃነት የሚገለጹ ሀሳቦችንም ጭምር ያለፍርሃትተደራሽነት ማድረግንምጭምር ያጠቃልላል፡፡ በእኔ እምነት፣‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ሀሳቡን ለመግለጽም ሆነ በነፃነት የተገለጹ ሀሳቦችን ለማዳመት፣ ለማየትና ለማንበብ ይችላል ወይ?››ብለህ ብትጠይቅ፣ከ90 ሚሊየን ህዝብ በላይ በሚኖርባት ሀገር እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ ከላይ ከጠቆምኩት ነገር ተገልሎ ይገኛል፡፡ ከሀሳብ ውይይት በጣም ተነጥሎ ያለ ህዝብ ነው፡፡ እድገቱ እያደገ ሳይሆን ይበልጥ እየቀጨጨ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
ከነፃ ሀሳብና ከሀሳብ ብዝሃነት ተቆጥቦ መኖሩም ጉዳት ነው፡፡ ሚዲያው እየተመረጠ (በመንግስት) የሚሰጥ ኢንዱስትሪ ሆኗል፡፡ ‹‹እያደገ ነው›› ብሎ ለመናገር በጣም ይከብዳል፡፡ በሚያስደነግጥ ሁኔታ፣የኢትዮጵያ ህዝብ የተጋለጠው ለመንግስት ሀሳቦች ብቻ ነው፡፡3 በመቶ የማይሞላየኢንተርኔት ተጠቃሚውን እንኳን ትተህ ሌላውን ብትመለከት፤ ለየትኛው ሀሳብ ነው ህዝቡ የተጋለጠው?ህዝቡ የተጋለጠውና ተደራሽነት ያለው መንግስት መጥኖ ‹‹የሚሆንህ ይሄ ነው›› ብሎ ለሚሰጠው መረጃ ነው፡፡
ስለዚህ ሀሳብን በነጻነትየመግለጽና በድፍረት የተገለጹ ሀሳቦችን የማግኘት ጽንሰ-ሀሳብበእጅጉን እየቀነሰ ነው፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፡፡
በወርሃዊነት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ታትማ አንባቢን ዘንድ የምትደርሰዋን “አዲስ ስታንዳርድ” መፅሄትን በዋና አዘጋጅነት እያሳተምሽ ትገኛለሽ፡፡ በስራችሁ ላይ በተግባር የገጠሟችሁ ተግዳሮቶች ምን ምንድን ናቸው?

ብዙ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ አንደኛው ደፍረን እንደምንሠራቸው ስራዎች፣ በብዙ ስራዎች ላይ ራስን ማቀብ (Self-censorship) አለ፡፡ በኤዲቶያል ስብሰባ ላይ ሀሳቦች ሲነሱ እንኳን ‹‹ይሄንን ሀሳብ ለምን አንሰራበትም? ይሄንን ነገር ለምን አንመረምረውም?›› ብለን ስናስብ ‹‹ይሄ የሚነካ ነው፣ ይሄ ደግሞ የማይነካ ነው›› ብለን እንነጋገራለን፡፡ በገደብ ውስጥ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ከኤዲቶሪያል ሕግ አኳያ ትልቅ ተግዳሮ ነው፡፡
ለምሳሌ፣ስለትላልቅ ሙስናዎች ይነሳል፡፡ መንግስት ራሱ የሙስናውን ችግር እየተነገረ ጉዳዩን አንስተህ መመርመር ትችላለህ ወይ? የትኛውም ጋዜጠኛ አደጋውን ተጋፍጦ ሊገባበት የማይፈልገው አካባቢ ነው፡፡ ይሄ ራሱን የቻለ የጋዜጠኝነት ስራ ላይ ገደብ የጣለ ትልቁ ተግዳሮታችን ነው፡፡
ሌላኛው ጋዜጠኞች ወይም ጦማርያን ብለህ ስትገልጽ፣ እስራቱንና ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ስታስብ በስራህ ላይ ምንም አይነት መተማመን እንዳይኖር ያደርግሃል፡፡ መቼ እዚያየእስርና አደጋ ወጥመድ ውስጥ እንደምትገባ አታውቀውም፡፡ ራስህን ገድበህ ‹‹ይሄንን እናድርግ፣ ያንን አናድርግ›› ብለህ ነው የምትጀምረው፡፡ ይሄም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡
ሌላው የግል ሚዲያ እንደመሆናችን መጠን፣ ከመንግስት የምናገኘው ነገር የለም፡፡ ራሱን በማስታወቂያ ማስተዳደር ያለበት የህትመት ውጤቱ ነው፡፡ ብዙ ማስታወቂያ ሊሰጡ የሚችሉ፣ በመንግስት ሚዲያ ላይ ግንበነጻነት ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ድርጅቶች እና ተቋማት እኛጋር ሲመጡ ይፈራሉ፡፡ እኛ መንግስትን በመተቸት ነው የምንታወቀው፡፡ ተቺ መፅሄት መሆን በራሱ መብት ነው፤ መሆንም አለበት፡፡ ግን እንደእድል የሚታይ ስራ ነው፡፡ እኛም እድላችንን እየሞከርን ያለበት ነፍቀ ክበብ ነው፡፡ ሌሎች እኛ ጋር ማስታወቂያ ሲያስነግሩ የሚችሉ ድርጅቶችእኛ ጋር ለመታየት ፍርሃት አለባቸው፡፡ አንዳንዴም ከምንጽፈው ነገር ተነስተው ማስታወቂያ የሚሰጡን ድርጅቶች ይገባሉ ይወጣሉ፡፡ ‹‹ለምን ይሄንን ፃፋችሁ?›› ይሉናል፡፡ ይሄ ከባድ ነው፤ የገንዘብ አቅማችንን ይፈታተናል፡፡ የፋይናንስ አቅምህ ከተፈተነ ደግሞ አታድግም፤ የምትፈልገውም ቦታ መድረስ አትችልም፡፡ ይሄ በአስተዳደር በኩል ያለብን ተግዳሮት ነው፡፡ ማስታወቂያ አስተዋዋቂዎችም መተማመኑ የላቸውም፡፡ ይሄ ከመንግስት ከራሱ ባህሪ የመነጨ ነው፡፡
መረጃን የማግኘት ችግርም አንዱ ተግዳሮታችን ነው፡፡ መረጃን ለማግኘት ትልቅ አድልዎ አለ፡፡ መረጃና ታሪክ ያላቸው ግለሰብ ሰዎች ጭምርእኛ ጋር መጥተው ለመናገር ይፈራሉ፡፡ እኛ ደግሞ የመረጃውን ተአማኒነት ለመጨመር የሰዎቹን ስም(መረጃ የሰጡንን) መጥቀስና የመረጃውን ምንጭ ማውጣት አለብን፡፡ ሠዎቹ ግን ‹‹ለሌላ ነገር ይዳርገናል›› ብለው ስለሚሰጉ መረጃዎችንያቅቡብሃል፡፡ ከመንግስትም በኩል መረጃ አታገኝም፡፡ ከመንግስት የምናገኘው መረጃ የተመጠነ ነው፡፡ እኛን የሚያካትቱበትና የማያካትቱን ጊዜ አለ፡፡ ለመረጃ ተደራሽ መሆን (Access to information) ትልቁ ተግዳሮታችን ነው፡፡ ያለ እርሱ ደግሞ የግል ሀሳቦች ላይ ብቻ ትቀራለህ፡፡ በመላ ምት ነው የምትሰራው፡፡…ለመረጃ ተደራሽ አለመሆን፣ የማስታወቂያ አስተዋዋቂዎች ስጋት፣ ፍርሃትና አለመተማመን፣ እንዲሁም ራስን ማቀብ ዋነኞቹ ተግዳሮቶቻችን ናቸው፡፡
ባለፈው ሳምንት የአለም የፕሬስ ቀን በመላው አለም ተከብሮ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም “የሚዲያ ብዝሃነት የተረጋገጠባት ሀገር – ኢትዮጵያ” በሚል መርህ ቃል በዓሉን ማክበሩ ታውቋል፡፡ እውነት በኢትዮጵያ የሚዲያ ብዝሃነት ተረጋግጧል?
ይሄ የአመቱ ምርጥ ቀልድአድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ ብዝሃነት ሲባል የአማርኛ ትርጉሙ ካልከዳን በስተቀር “Diversity” የሚለው የእንግሊዘኛ አቻ ትርጉም ይገልጸዋል፡፡ ከ80 በላይ ብሄር ብሔረሰብ፣ ከ90 ሚሊየን በላይ ህዝብ ባለባት ሀገር፣ ያለውን የሚዲያ ብዝሃነት ስትመለከት አግላይ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያ ሆነው በአማርኛ በዛ ያሉ፤ በእንግሊዘኛ የተወሰኑ፣በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በአፋርኛ…በተወሰኑ ከአራት ወይም ከአምስት በማይበልጡ ቋንቋዎችነው መንግስት ሚዲያውን እየተጠቀመበት ያለው፡፡ በመንግስትም ይሁን በግል የሚበዛው በአማርኛ ቋንቋ የሚቀርቡት ናቸው፡፡
ይሄንን የሚያክል ህዝብ ለሚዲያ ያለው ተደራሽነት በጣም ውስን ነው፡፡ አማርኛ ብሄራዊ ቋንቋ ከመሆኑ አኳያ ይበዛል፤ ሌላው ውስንና በጣት የሚቆጠር ነው፡፡ ‹‹የሚዲያ ብዝሃነት ተረጋግጧል›› ስትል ራስንም ማታለል ነው፡፡ ካለው የሀገሪቷ ነባራዊ ሃቅ ጋር በፍጹም አይገናኝም፡፡ እንደ መርህ ቃልም መመረጥ አልነበረበትም፡፡
ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ሰብዓዊና ሕገ-መንግስታዊ መብት በበቂ ተደራሽነት እና በተግባር እንዴት በሀገራችን እውን ሊሆን ይችላል ብለሽ ታምኚአለሽ?
ሕገ-መንግስታችንን ስትመለከት፣ በአንቀጽ 29 ላይ ሀሳብንበነጻነት የመግለጽ መብትን አረጋግጧል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን እንደ ሰው ልጅ መብት አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡ ሆኖምበራሱ በመንግስት ሰለባ ሆኗል፡፡ አሁን ያለውን ሕገ-መንግስት አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የተቀረጸው ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም የእነሱ ሌጋሲ ነው፡፡ ራሳቸው አምጥተውት ራሳቸው አጥቅተውታል፡፡ የወለድከውን ልጅ እንደማጥቃት ማለት ነው፡፡ ግን በሕገ-መንግስቱ ላይ ከተጠቀሰው በተጻራሪ የወንጀል ሕጉ የሚዲያንና የጋዜጠኞችን ሥራ በተለያዩ ጊዜያቶች፣ በተለያዩ ጋዜጠኞች ላይ ወንጀል ሲያደርገው ታያለህ፡፡በዚህ ማንም አይስማማበትም፤ እኔም አልስማበትም፡፡
ሕገ-መንግስቱ ሀሳብን በነፃነት ከመግለጽ አኳያ ችግር የለበትም፤ ወርቃማ ሕገ-መንግስት ነው፡፡ ችግሩ ግን ራሳቸው በፈጠሩት፣ ስልጣን ላይ ባለው አካል የተጠቃ መሆኑ ላይ ነው፡፡መብቱ ወረቀት ላይ የሚገኝ ነገር ነው፡፡
‹‹ወደፊት ምን ሊሆን ይችላል?›› የሚለው ነገር በህዝቡ ንቃተ ህሊና ላይ የተመረኮዘ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ሕገ-መንግስት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ጦርነት ውስጥ ሳትገባ፣ መንግስትን ተጠያቂ እንዲሆነ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ሕገ-መንግስት ነው፤ ሕገ-መንግስቱም ይሄንን መብት ሰጥቷል፡፡ ይሄ መብት በተግባር እንዲከበርለት ሕዝቡ መታገል አለበት፡፡ ወደፊት ሕገ-መንግስቱን ማስጠበቅ ይጠበቅበታል ፡፡
ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ-መንግስታዊ መብት በእጃችን ላይ አለ፡፡ በተለያየ መንገድም ህዝቡ ከመንግስት ጋር እየታገለ ይገኛል፡፡ ይሄንን ማስጠበቅ የእኛ የሚዲያና የህዝብም ግዴታ ነው፡፡ መዋቅሩ አለ፤ ቆፍረን የምናወጣው ነገር አይደለምና ታግሎ ማስከበር እንደሚቻል ተስፋ ይታየኛል፡፡ ህዝቡ ከመንግስት ነጥቆ መብቱን በምንም አይነት ሁኔታ ማስጠበቅ አለበት፡፡ ሌላው መንግስትም ቢሆን ይሄን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ሕገ-መንግስቱን ሳያከብር ‹መንግስት ሆኜ እቀጥላለሁ› ካለ የዋህነት ነው፡፡ እስከ አሁን የታየው ይሄ ነው፡፡ ምን ላይ ድክመታቸው እንዳለ ቆም ብለው ማሰብ ያለባቸው ጊዜ ላይ የደረሱ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ የሠሩትን ሀገር ማፍረስ ብቻ አይደለም፤ በመቶ ዓመት ወደኋላ የመጎተት ዝንባሌ በድርጊት ሊገለጽ ይችላል፡፡ ራሳቸውም ቢሆን ለራሳቸውም ሲሉ ሕገ-መንግስቱን መጠበቅ አለባቸው፡፡ እነዚህ ይፈጠራሉ፣ በሕገ-መንግስቱ በተሰፈረው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ምንም ችግር የለብኝም፡፡ ግን በማንኛውም ዋጋ ሕገ-መንግስቱ መከበር አለበት፤ ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለመንግስት ሲባል፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ዕቅድ “ቢ” የለም፡፡
በኢትዮጵያ ብዙ ጋዜጠኞች ይሰደዳሉ፣ ይታሠራሉ፣ ይከሳሳሉ፣ ይፈረድባቸዋል -በወንጀል እና በሽብር ወንጀል፡፡ አሁንም ድረስ የሚታሠሩና የሚከሰሱም አሉ፡፡ የነገረ-ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውንና ዮናታን ተስፋዬን (ፌስ ቡክ ላይ በጻፋቸው ጽሁፎች) ማንሳት ይቻላል፡፡አንቺ እንዳልሽውም በዚህ ሞያ ውስጥ ተኹኖ ምን እንደሚከሰትና እንደሚፈጠር አይታወቅም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት መጓዝ ይቻላል? መፍትሄውስ?
በእንደዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡ በመሳሪያ ኃይል መቀጠል ትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሀገርን አንድ ሀገር የማድረጊያ መንገድ አይደለም፡፡ መንግስት ሀሳብን ፈርቶ መኖር አይችልም፡፡ ሀሳቦች ናቸው ነገሮችን የሚወስኑት፡፡ የእኛ ትውልድ ደግሞ አሁን ላይ በስልጣን ላይ እንዳሉት ኃይሎች ጠብ መንጃ ይዞ ወደጫካ የሚገባ አይደለም፡፡ ይሄንን ትውልድ ራሳቸው ገንብተውታል፡፡ በሀሳብ የሚያምንና የሚከራከር ትውልድ ተገንብቷል፡፡ ሶሻል ሚዲያውም ይሄንን በአዲስ መልክ ቀይሮታል፡፡ በአሁን ሰዓት መቀየር ያለበት መንግስት ነው፡፡ መንግስት ሀሳብን ፈርቶ ‹አስተዳድራለሁ› ማለት የዋህነት ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው፣ በጋዜጠኞች ላይ እየደረሠ ያለው ወከባና ጫና በፍርድ ቤት በሚመላለሱት እና በታሠሩት ላይም(እነእስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ተመስገን ደሳለኝ፣…)፣ ከሀገር የተሰደዱትንም ስትመለከት ጠብመንጃ ይዘው ሳይሆን ብዕር ይዘው ሲፅፉ ነው፡፡ ይሄ ተቃርኖሽ ነው፡፡
የፍርድ ቤት ዘገባዎቻቸውን እንመለከታለን፤ መንግስት በአንድ በኩል ‹‹በፃፉት ጽሑፍ የታሰሩ፣ የተከሰሱ የሉም›› ይላል፡፡ አቃቤ ሕግ ደግሞ የፃፉትን ማስረጃ ክርክር አድርጎ ያቀርባል -በፍ/ቤት፡፡ ይሄ ያለውን ክፍተትና ያለውን እውነት ያሳይሃል፡፡ ይሄ የሚያሳይህ፣ ለዚህ መንግስት ትልቁ ስጋት ሀሳብ ነው፡፡ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ሀሳብ ስጋት የሆነበት መንግስት ደግሞ ሀገር መምራት አይችልም፡፡ ሀገር መምራት የሚችለው (ኢህአዴግ) በአንድ መንገድ ብቻ ነው – በመሳሪያ፡፡ ማሰር የሚችሉትን ያስራሉ፤ የሚያሳድዱትን ያሳድዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ አዋጪ አይደለም፡፡ አንድና ሁለት ዓመት ሊያስቀጥል ይችል ይሆናል፤ ግን ቀጣይነት ሊኖረው እንደማይችል ግን መተንበይ የግድ አይደለም፡፡
መንግስት የሠውን ልጅ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትንፈርቶ ሀገርን አስተዳድራለሁ ካለ የዋህነት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በግሉ ሚዲያ ውስጥ የሴቶች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ደፍረው መንግስትን የሚተቹ ሴት ፀኃፊያንም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡አንቺም‹‹አዲስ ስታንዳር›› መጽሄትን ከመሰረቱት መካከል ነሽ፡፡ ሴትን ያላሳተፈና የሴቶች ተሳትፎ አናሳ በሆነበት መድረክ ደግሞ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እጅግ አዳጋች ነው፡፡ ሀገርንም በተሻለ መልኩ ለመንገንባት ሴቶች ትልቅ ሚና አላቸውና ሴቶች ቁጥራቸው ለምን አነሠ? እንዲበዙስ ምን ይደረግ?
በሚዲያ የሴቶች ተሳትፎ አነስተኛ መሆን ከሌሎች መስኮች ለይቼ አላየውም፡፡ ይሄ የአንድ ተግዳሮት ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ‹‹ሴት ታጋዮች የት ሄዱ? ብለህ ብትል፣ የምታገኘው መልስ ሚዲያ ላይ ‹‹ለምን አይሳተፉም?›› ብለህ ከምታገኘው መልስ ብዙ የተለየ አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ጫና፣ ፖለቲካዊ ማግለል አለ፡፡ ንቀትም አለ፡፡ በማኅበረሰቡ፣ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በሃይማኖቱ …ሴቶችን ዝቅ የማድረግ ነገር አለ፡፡
ሴቶች ኃላፊነት አለብን፡፡ ለምሳሌ እኔን ‹‹የልጅ እናት ሆነሽ እንዴት እንደዚህ አይነት ስራ ላይ ትሠማሪያለሽ?›› የሚሉኝ አሉ፡፡ ይከብዳቸዋል፡፡ ሴት በተፈጥሮ የቤተሰብ ኃላፊነት የመውሰድ ተፈጥሯዊ ኃላፊነት አለብን፡፡ ሚዲያ ደግሞ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ዕድሉ እንኳን ቢኖርያ አደጋ ውስጥ ለመግባት ብዙዎቹ አይመርጡትም፡፡ አንድ ነገር የምትሰራው ውስጥህ መነቃቃቱ ሲኖር ነው፤ ግን የሚዲያ ምህዳሩ የሚያበረታታ አይደለም፣ አትገባበትም፡፡ መግባት አይደለም የምትበረታታበትም አይደለም፡፡ ካለው ስጋት አንፃር ቀላል አይደለም፤ አንተም ታውቀዋለህ፡፡ አድረህ ትሠራለህ፡፡ የቤተሰብ ኃላፊነትን ሴት ላይ በጣለ ማኅበረሰብ ውስጥ ሌሊት ለሥራ ማደር፣ የስራ ዕቃዎችህን ጭነህ ወደ አንዱ ቦታ መሄድና መስራት የማይሞከር ነው፡፡ያለ እነርሱ እንዲሁ ማደግ ይቻላል? አይቻልም! ምክንያቱም አንዴ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ የሆኑት ዴላሚን ዙማእንዲህ በማለት ተናግረው ነበር፡- ‹‹ሴቶች የሚወክሉት የአለማችንን 50 በመቶ ሳይሆን የተቃረውንም 50 በመቶ ጭምር ነው››
የኢትዮጵያ ሴቶች የሀገሪቷን 40 ወይም 50 በመቶ ብቻ አይደለም የሚወክሉት፡፡ በሙሉ የሚወክሉት እነርሱ ናቸው፤ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የእነርሱ አስተዋጽኦ ውስጡ ባይኖርሊያድግ የሚችል ነገር የለም፡፡ ፖለቲካውም፣ ኃይማኖቱም፣ ሚዲያውም….. ሌላውም ሁሉም፡፡ ስለዚህ ይሄንን ችግር እንዲፈታ ማድረግ አለብን፡፡ መንግስትም የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለሴቶች መስጠት ያለበት ይመስለኛል – ለሴት ፀሐፊያንና ባለሙያዎች፡፡
በሌላ በኩል ሲቪክ ማኅበር የለም፡፡ የሴት ጋዜጠኞችና ፀሐፊያን ማኅበር ግን አለ፡፡ ማኅበሩ ባለው የሲቪል ማኅበራት አላማ መሠረት ሴቶችን ሊያወጣና ሊያበረታታ ቀርቶ የራሱም ህልውና አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ወይም በመንግስት የተነካ ድርጅት ሆኗል፡፡ እንደዚህ ኖሮ እንኳን፣ ሴቶችን እንዳይደግፍ፣ ምንም ማድረግ ሳይችል የቀረ ድርጅት ነው፡፡ ከሁለት ወይምሶስት ሰዎች በቀር በውስጡ ማንም እየተንቀሳቀሰበት አይደለም፡፡ ይሄ ለሴቶች ደጋፊ ሀይል ነበር፡፡ እንደሴት ሆነህ መደራጀት በራሱ ለዚህ መንግስት ፍርሃት ነው፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች ባሉበት መስክ የሴቶችን ተሳትፎ መጨመር ከባድ ነው፡፡ ያለ እነርሱ ደግሞ ኢንዱስትሪው ያድጋል ማለትም ከባድ ነው፡፡
ዘርዘርአድርገሽ ያነሳሻቸው ተግዳሮች እንዳሉ ሆነው፣ በሴቶች በኩልስ ችግር የለም? መፍራት፣ የተመቸ ህይወትን መፈለግ …
እኔ ፌሚኒስት አይደለሁም፡፡ እንዲህ ብሎ ማሰቡ ትንሽ የሚያናድድ ይመስለኛል፡፡ ለምን? ሴቶች አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ዕድል ኖሮ፣ ‹‹እኔ ምቾት ነው የሚሻለኝ›› ብላ የምትቀመጥ ሴት አለች ብሎ ማሰቡ በጣም ነው የሚከብደኝ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ሴቶች ከየዲፓርትመንቱ ተመርቀው ለመውጣት ያለባቸው ተግዳሮች በራሱ አለ፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተቀረፉበት፣ ሴቶችአስተዋጽኦ አለማድረጋቸው ለእኔ ብዙ ይቸግረኛል፡፡
ለቃለ-ምልልስ ስሄድ የማገኛቸው ብዙ ጎበዝ ሴቶች አሉ፡፡በጣም ጎበዝ ሴቶችን አገኛለሁ፡፡ ግን ዕድሉ ስለሌላቸው፣ ባለው ነገር ውስጥ ለመግባት ፍርሃቱ ስለሚበዛ አይታዩም፡፡ ችግሮች ከተስተካከሉ ግን …
ከተመረቁ በኋላ እንኳን ሌላ የማይሆን ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ይሄ ያሳዝናል፡፡ ጋዜጠኛ መሆን ለእነርሱ ከባድ ነው፡፡ካልነው ነገር አኳያ ስትናገራቸው ግን እየሰሩበት አይደለም፡፡ ከችግሮች አንጻር እንጂ ከራሳቸው ፍርሃት ነው ብዬ መግለጹ ይከብደኛል፡፡
በመጨረሻ …ከተነሱት ሀሳቦች በመነሳት እንደመፍትሄ የምታነሺው …
መንግስት ሚዲያው ላይ ያለውን አመለካከት መቀየር አለበት፡፡ ይሄ ለህዝቡ ሲል ብቻ ሳይሆን ለራሱም ሲል መሆን አለበት፡፡ ሚዲያው በተለይም የግሉ በገለልተኝነት እንዲሰሩ ለማስቻል ያለውን አቋም መቀየር አለበት፡፡ በእርሱ ቁጥጥር ስር ያሉና ለእርሱ አዘኔታ ያላቸውን ሚዲያዎች መኖራቸው በራሱ ችግር የለውም፡፡ ግን ጋዜጠኞች በነፃነት እንዲሰሩ ማድረግ ጥቅሙ ለመንግስትም ጭምር ነው፡፡
ሚዲያ ማለት፡- ሰው ከሰው፣ ተቋም ከተቋም፣ ህዝብ ከህዝብ፣ ህዝብ ከመንግስት …የሚገናኝበት መድረክ ነው፡፡ ህዝቡ እንዲያውቅ ከፈለገ ሚዲያው በነፃነት እንዲሰራ መፍቀድ አለበት፡፡ የራሱ ሚዲያዎችም በነፃነትና ያለገደብ ህዝቡ ውስጥ ገብተው የህዝቡን ብሶት እንዲያወጡ፣ ብሎም ያለውን ነገር እንዲለኩ መፍቀድ አለበት፡፡ ይሄ ጥቅሙ ለራሱ ነው፡፡
ባለፉት አምስትወራት በኦሮሚያ ክልል ህዝቡ ጎዳና ላይ የወጣበት ምክንያት ከመንግስት ጋር ለመነጋገር ስለፈለገ ነው፡፡ ግን በዚህ መልክ አይደለም ከመንግስት ጋር ለመነጋገርየሚቻለው፡፡ ጥል ድረስ መደረስ የለበትም፡፡ ለግሉ ሚዲያ በነፃነት እንዲሰራ ፈቅዶ ቢሆን ኖሮ ችግሩ ያን ያህል ደረጃ ባልደረሰ ነበር፡፡ በዚህ ራሱ ትልቅ ትምህርት መውሰድ አለበት፡፡ መድረኩ ወይም ሚዲያው (የመንግስት) በነፃነት መስራት አለበት፡፡ ገና ለገና ችግሩ ይወጣብኛል ብሎ ፈርቶ ከሆነ ችግር ነው፡፡
መንግስት መንቃት አለበት፡፡ ነፃ ሚዲያውን እንደመሳሪያ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ በብዙ ነገር ይጠቀማል እኮ! የህዝቡን ሙቀት በነፃው ሚዲያ መለካት ይችላል፡፡ ለመንግስት አይንና ጆሮ ነው መሆን ያለበት፡፡ መንግስት ሊያይ የማይችለውን ነገር ሊያሳየው ይችላል፡፡ ነገሮችን አደገኛ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ነፃው ሚዲያው ችግሩን መርምሮ እንዲያወጣ መፍቀድይኖርበታል፡፡ አብሮ መስራትም አለበት፡፡ ችግሮቹን ነቅሶ ለማውጣት እንዲህ ካላደረገ ለራሱ ህልውና ራሱ አስጊ ይሆንበታል፡፡ አሊያ የራሱን መቀበሪያ ጉድጓድ እያቀረበው ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን መንግስትን የሚያናግርበት መድረክ መፍጠር አለበት፣ ያ መድረክ ደግሞ ሚዲያ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሚዲያ አራተኛው የመንግስት አካል የሚባለው፡፡ ያን ያህል ኃይል አለው፡፡ ለህዝብ የሚዲያ በሩን ስትዘጋበት ኦሮሚያ ላይ እንደሆነው ጎዳና ላይ ወጥቶ ያወራሃል፣ ይሄ ደግሞ መርዛማ ይሆናል፡፡ መንግስት ሚዲያውን መደገፍ ይኖርበታል፡፡
ጨርሻለሁ፡፡
እኔም አመሰግናለሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles