ኢትዮጲያዊያንን ጨምሮ ለብዙ ሰው ሞት ተጠያቂ የሆነውና የዓለማችን አደገኛው ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪ የተባለው የ35 ዓመቱ ኤሪትሪያዊው መርዕድ መድሃኒ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተረጋግጧል፡፡ ኤሪትሪያዊው መርዕድ መድሃኒ ቁጥራቸው ያልታወቁትን ሳይጨምር በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ወደ ጣልያን ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስመጧና በጀልባዋ ተሳፍረው ሲጓዙ ባህር ውስጥ ገብተው ላለቁ ለ 350 ስደተኞች ሞት ተጠያቂ በመሆኑ ሲፈለግ እንደነበር ዘገባዎች አመልክተዋል፤ ኤሪትሪያዊው ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ መርዕድ መድሃኔ በዚህ ህገ-ወጥ ሰው የማዘዋወር ሥራው በየአገሩ ካሉ አስተላላፊዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበረውና በተለይ በሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ካሉ የአካባቢ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት የነበረው በመሆኑ ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ ለማስተላለፍ ከተለያዩ የአፍሪካ ህገ ወጥ አስተላላፊዎች ጋር በጋራ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለት ነበር ሲል ጣሊያን ውስጥ የሚታተመው ዴላ ሴራ /Della Serra/ የተባለው ጋዜጣ በዛሬው እትሙ አስነብቧል፤ቢቢሲ በበኩሉ Newsday በተሰኘው ፕሮግራሙ ‹‹ ይህ ዓለም አቀፍ ወንጀለኛ በዚህ ህገ ወጥ ሰዎችን የማዘዋወር ስራው በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሳያተርፍ አይቀርም›› ሲል ፡ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ የራሱን ወንጀለኛ ቡድን በማቋቋም ገንዘብ የሌላቸውን ስደተኞች በማገትና አስሮ በማሰቃየት ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በግድ ያስልክ ነበር የሚሉና ልዩ ልዩ የወንጀል ዘገባዎች እየወጡበት ነው ፡፡
ግለሰቡ በበርካታ የወንጀል ክሶች የተጠረጠረ ሲሆን ከዚህ በፊት በአንድ ወቅት ዱባይ ውጥ የባንክ ሂሳብ ለመክፈትና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለማስቀመጥ በሙከራ ላይ እንዳለ የፀረ-ማፊያ መርማሪዎች ደርሰው ምርመራ ሲያደርጉለት ጣሊያን እንደኖረና የገንዘብ ምንጩም ጣሊያን አገር ሰርቶ ያገኘው መሆኑን በማሳወቅ ተጨማሪ ምርመራ ሳይደረግበት እንደቀረ ተገልፃል፤እንግሊዝ ውስጥ የሚታተመው ዴይሊ ሚረር / Daily Mirror/ የተባለው ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ለየት ያለ ነው ግለሰቡ ስደተኞችን ከሊያብያ ወደ ሜዲትራንያን በሚያጓጉዝበት ወቅት ባካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የአይኤስ /ISIS/ አባላት ጋር ግንኙነት ያደርግ እንደነበረና በአይኤስ በታገቱ ፣በታረዱና በተገደሉ አፍሪካዊ ስደተኞች ሞት ውስጥ እጁ አለበት እንዲሁም አፍሪካ ውስጥ እያቆጠቆጠ ላለው የአይኤስ /isis/ ክንፍ የገንዘብ አስተላላፊም ሆኖ ይሰራ ነበር ብሏል ፡፡
መርዕድ መድኃኔ የተለያዩ የአፈሪካ አገሮች በፍጥነት ስለሚዘዋርና በተለይ የሊቢያን አለመረጋጋት በመጠቀም ከአካባቢው ባለስልጣናትም ሚስጥራዊ ከለላ በማግኘቱ ሊያዝ ሳይችል የቆየ ቢሆንም በመጨረሻ ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡