ተደጋግመው ከሚነሱትና መቋጫ ካላገኙት ያገሪቱ አውራ ችግሮች መካከል የብሄረሰቦች መብት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ ሶስት ገጽታዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ አንዳንዶች ብሄረሰብ የሚለውንም ስያሜ ለመቀበል አይሹም፡፡ ለነሱ “ጎሳ”፣ወይም “ነገድ” የሚሉት ይጥሟቸዋል፡፡ ባገሪቱ “ብሄረሰቦች” አለመኖራቸውን ይሞግቱና ለጥፋት ማለትም አገሪቱን ለመከፋፈል ተብሎ የተፈጠረ “ቃል” አድርገው ያቀርቡታል፡፡ በነሱ አስተሳሳብ ኢትዮጵያውያን አንድ ህዝብ ሆነው በውስጣቸው ልዩ ልዩ ጎሳዎች እንዳሉ ይተርካሉ፡፡ (አልሸሹም ዞር አሉ የሚሉት አይነት፡፡) ሌሎች ደግሞ ብሄረሰቦች የሚባል ነገር መኖሩን ከተቀበሉ በኋላ መብታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ወደዱም ጠሉ ተቃቅፈው መኖር ብቻ እንደሆነ ያትታሉ፡፡ ከጥንት ጀምሮ አብረን የኖርን ህዝብ ስለሆን ዛሬ በኢትዮጵያዊነት ስለተሰባሰብን ከዚያ የወጣ ምንም ነገር አንቀበልም ባይ ናቸው፡፡ በነዚህ ወገኖች እይታ ብሄረሶቦች መብት ቢኖራቸውም “መገንጠል” የሚባለውን ማካተት የለበትም ባይ ናቸው፡፡ ማለትም ብሄረሰቦች ይደርሱባቸው የነበሩትን ጭቆናዎች በራስ አገዛዝ ስርአት ማስተካከል ይቻላቸዋልና መገንጠል የማይገባ ነው ይላሉ፡፡ ሶስተኛው ገጽታ ብሄረሰቦች እድላቸውን ለመወሰን መብት ያላቸው በመሆኑ ያለምንም ገድብ እስከመገንጠልና የራሳቸውን አገዛዝ እስከመመስረት መዝለቅ ይችላሉ ብለው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህን ሶስት አመለካከቶች ለመፈተሽ ነው የዚህ ከፍል አላማ፡፡ ካሁን በፊት በተለያዩ መድረኮች በእንግሊዝኛ የጻፍነውን ጭምር እዚህ ክፍል ውስጥ መልሰን ሳናስገባ ፍሬ ነገሩን ብቻ ለመመርመር እንሞክራለን፡፡
ከሁሉ አስቀድሞ በተደጋጋሚ እየተነሳ አሁንም ከመነጋገሪያ ይልቅ መደናቆሪያ የሆነውን “ጎሳ” ወይም “ነገድ” እንጅ “ብሄረሰብ” የለም የሚለውን ክርክር እንመልከት፡፡ ኢትዮጵያ እንደአብዛኞች የአፍሪካ አገሮች በህዝቦችዋ መርመስመስ፣ መዘዋወርና መፍለስ ብሎም መዋዋጥና መቀላቀል የትዥጎረጎረች ለመሆኗ አንድም ተቃዋሚ የሚኖር አይመስለንም፡፡ የቋንቋዎች መብዛት፣ የገጽታዎች መለያየት፣ የባህላዊ ዝብርቅርቆች መነሻቸው የተለያዩ የሰዎች ስብስቦች (አካሎች) ከመኖራቸው እንጅ ካንድነት የመነጩ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አስቀድሞ “ጎሳዎች” ና “ነገዶች” (የኋለኛው ጠቅለል ያለ፣ የፊተኛው የነገድ ክፍልፋዮቹን ይዞ) በሁሉም የአለም አካባቢዎች ይኖሩ እንደነበር፣ በጥንታዊ ስነጽሁፍም ሳይቀር እንደተወሱና እንደተጠቃቀሱ ማን ይስታል; በተለያዩ ምክንያቶች (ጦርነት፣ ፍልሰት ወዘተ) የጎሳዎችና ነገዶች መደበላለቅና መዋዋጥ የፈጠራቸው ስለሆነም የዘር ወጥነት የሌላቸው ስብስቦች ቀስ በቀስ እየበዙ ሄደው ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገለባበጥ ጋር (በተለይ በአውሮፓ) የቋንቋና የስነልቡና አንድነት አግኝተው “ብሄር” መሰኘታቸውንስ ያልሰማ ይኖራል;
በኢትዮጵያ ያፍም ሆነ የስነጽሁፍ ትረካ ውስጥ ከማህበራዊ ስብስቦች መሃል “ጎሳ”ና “ነገድ” እንደነበሩና እንዳሉ የሚክድ እስከዛሬ አልተሰማም፡፡ እንዲያውም ብዙ ያገራችን ጸሃፊዎች ህብረተሰባችን ከነዚህ ማህበራዊ ክፍልፋዮች አላለፈም (ማለት ምንም ለውጥ አልታየበትም፣ ጥንት እንደተፈጠረ ቆሞ ቀርቷል) በሚል ሙግት “ብሄር”፣ “ብሄረሰብ” ወይም ሌላ ቃል ወይም ጽንሰ ሃሳብ አይቀበሉም፤ ክፉኛም ይቃወማሉ፡፡ ማህበራዊ ለውጥ የታየው በአውሮፓ ብቻ ስለሆነ በአፍሪካና ሌሎች አካባቢዎች ያው የጥንቱ የጎሳና የነገድ ስርአት ቀጥሏል በሚል የቅኝ ገዥዎችና የውጭ ጸሃፊዎች የተረኩትን በመከተል እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አፍሪካዊ አገሮች ውስጥም ይኸው አባባል ይናፈሳል፡፡ ለምሳሌ የኬንያና የኡጋንዳን እለታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጦች ያካባቢያቸውን የማህበረሰባዊ ክፍፍሎች ምንም ሳያፍሩ “ነገድ” ወይም “ጎሳ” በሚል ይገልጻሉ፡፡ ቃሎቹ በቀጥታ ሲተረጎሙ አሁንም የማይለወጥና የማይንቀሳቀስ፣ በኋላ ቀርነት ከስልጣኔ ውጭ የሚኖር ህዝብ ያለ መሆኑን ለመጠቆም እንደሚያገለግል አወቁም አላወቁም፡፡
በርግጥ “ጎሳ ወይም ነገድ” እንጅ ሌላ የማህበራዊ ስብስብ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የለም የሚሉት የውጭ (በተለይ የቅኝ ገዢነት አራጋቢ የነበሩትና የሆኑት) ምሁራን የቃሎቹን አጸያፊ ትርጓሜ ለመሸሽ ሲሉ ቁጥራቸው እየቀነሰ ሄዷል፡፡ ዛሬ በይበልጥ በእንግሊዝኛ ስነጽሁፍም ጭምር “የትውልድ ቡድን” (ለምሳሌ የሶማሌ የትውልድ ቡድን፣ የአገው የትውልድ ቡድን እንደሚሉት) የሚሰኘው አጠራር እየተስፋፋ ነው፡፡ ቀዳሚዎቹ የማህብረሰቦች ክፍፍል አጥኚ የነበሩ የ19ኛው መቶ አመት የኦስትሪያ ምሁራን (በተለይ ባወር) ግን በአውሮፓ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ለውጦች እየተስፋፉና ጥልቀት እያበጁ በመሄዳቸው ከጎሳና ነገድ ወጥተው ወደ”ብሄር” እየተሸጋገሩ መሆናቸውን በማመልከት አዲስ ምእራፍ ከፍተዋል፡፡ የዚህ አንድምታ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ህብረተሰቦች ከጎሳና ከነገድ አልፈው ወደብሄርነት መዝለቅ እንደሚችሉ፣ የዚህ ስያሜም ፍቺ ከላይ እንደጠቀስነው የቋንቋና የስነልቡና ውሁድነት የተቀዳጁትን የሚያጠቃልል አዲስ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን ምሁራኑ አስተምረውናል፡፡
ያልሰሙ ካሉ ሁሉም ህብረተሰቦች ባንዴ ዘለው ከጎሳነት ወይም ነገድነት ወደብሄርነት መሸጋገር (መለወጥ) አይቻላቸውም፡፡ ከባላባታዊ ስልተምርት (ግብርና) ወደካፒታሊዝም (ኢንዱስትሪያዊ ስርአት) ለመዝለቅ ብዙ ውጣ ውረድ ስላለው ከሱው ጋር ህብረተሰቡ ከተራ፣ ማይም፣ የጎጥ ወይም መንደር ኗሪነት ወደሃገራዊ ዜጋ ለማደግ ጊዜ ይፈጅበታል፡፡ ባንድ አካባቢ የመኖርን ጉዳይ እንተወውና የብሄርነት ደረጃ ለመጎናጸፍ የሚጠበቀው የንቃት፣ የስነልቡና አንድነት መንፈስ እስኪሰፍን ብዙ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ ፈረንሳዮች በብሄርነት ራሳቸውን ችለው ለመውጣት ሲራወጡ አብዮት ባካሄዱበት ወቅት እንኳን ቋንቋቸው ገና በየሰፈሩና በየጎጡ የተቆራረጠና ርስ በርስ ለመግባባት የማያስችል ነበር፡፡ ስለሆነም የዚህ አይነቱን የመሸጋገሪያ ማህበራዊ ቁርኝት “ብሄረሰብ” በሚል ጽንሰ ሃሳብ መግለጽ አስፈላጊ ሆነ፡፡ በያገሩም ይህ ቃል በየቋንቋዎቻቸው እየተተረጎመ ስራ ላይ ዋለ፡፡
ከ1966 አብዮት በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የጎሳና ነገድ ስያሜዎች የህብረተሰቡን አካሎች በሚገባ አለመግለጻቸውን በመረዳት የሽግግሩን ዘመን የሚያቅፍ አጠራር በአማርኛ ለማውጣት ግዴታ ነበር፡፡ በርግጥ በህብረተሰቡ ውስጥ አዲስ ክስተት መኖሩን በመገንዘብ በታሪካችን ያልነበረውን ስም ማውጣቱ የማይቀርና ተገቢ ነበር፡፡ ይሁንና የእንግሊዝኛውን ስያሜ በመከተልና በመተርጎም ለሙሉው ሽግግር “ብሄር”፣ ለረዥሙ ጉዞ ደግሞ “ብሄረሰብ” የሚለውን (አማርኛው ትክክል ይሁን አይሁን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ የግእዝ ምንጩም ብዙ መመራመር ሳይደረግበት) መጠቀም ተያዘ፡፡ እነዚያ ስያሜዎች ደርግ ስልጣን ከወጣ ወዲህ በየጓዳውና ሻይ ቤቱ ሁሉ ተነዙ፡፡ ዛሬ ማንም፣ የትም ያለ ዜጋ ሁሉ ብሄርና ብሄረሰብን እንደቋሚ መገልገያዎች አድርጓቸዋል፡፡ (አናውቅም፣ አልሰማንም፣ አንቀበልም፣ አሻፈረን ከሚሉት በጣም አነስተኛ ክፍሎች በስተቀር፡፡)
አስገራሚው ነገር የህብረተሰቦች መገለባበጥ ለአውሮፓውያን ብቻ የተሰጠ ጸጋ አስመስለው የሚያወሩ ቀደም ሲል የቅኝ ገዥዎች የመንፈስ አሽከሮች የነበሩ በየዩኒቨርሰቲዎችና በ”ሳይንሳዊ” ስራዎች ጭምር የነዙትን ጨምድደው ይዘው ያዙን ልቀቁን የሚሉ ዛሬም አለመጥፋታቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አቻዎቻቸው በይበልጥ ከዱሮው ገዥ መደቦች ጋር በመንፈሳቸው የመሸጉ ስለሆኑ ያንን አለም እያደር እየተወውና እየጣለው ያለውን የጎሳና የነገድ ስያሜ እኝኝ ብለው አንለቅም ብለዋል፡፡ በዚህ የእምቢታ ማህበር ውስጥ የተኮለኮሉ ብዙ ቢሆኑም ኢትዮጵያ በለውጥ ማእበል በምትናጥበት በ1960ዎች ውስጥ ከዳር ተቀምጠው፣ አንዳችም አበሳ ሳያዩ፣ ነፍሳቸውን ለማዳን ተሸሽገው የኖሩት ጥቂት የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ መምህራንና መሰሎቻቸው በግንባር ቀደም ተሟጋችነት ተሰልፈዋል፡፡ (ጌታቸው ሃይሌ ቢያንስ ቢያንስ የደርግ “ቋሚ ተጠሪ” በስህተት ቤቱን ደርምሶበት በደረሰበት ያካል ጉዳትና መጉላላት ለ”ትግሉ” አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡)
ወደመሰረታዊ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ውጥንቅር በተለይ የብሄረሰባዊ ክፍፍል ባለም ላይ የተለየና አስቸጋሪ ተደርጎ ይናፈሳል፡፡ የትም አገር የሌለና ለውድቀቷ የሚያመቻቻት ነው ብለው የሚያምኑ በርካታ ናቸው፡፡ ነገር ግን የብሄረሰቦች ህልውና ሰዎች በአሻቸው መልክ የሚፈጥሩት፣ ቀጥቅጠው የሚሰሩት ክስተት አይደለም፡፡ ህልውናቸው ከውልደታቸው (ተፈጥሮዋቸው) የተገኘ፣ በታሪካዊ አመጣጣቸው እየተለዋወጠ የመጣ ገጽታቸው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባንድ መጣጥፍ (ቁጥር 2.15 ሆኖ “ታሪክና ኦሮሞነት” በሚል በኢትዮጵያ ዛሬና ነገ መጽሃፍ የገባ) ላይ አንስተን እንዳልነው አንድ ሰው ኩናማ ነው፣ ሌላው አፋር ነው ወዘተ ብሎ ማመልከት በሬ ቀንድ አለው፣ ላም ጡት አላት፣ ሰዎች ባብዛኛው ሁለት እጅ አላቸው ከሚሰኘው ትረካ የሚለይ አይለይም፡፡
ሰዎች ከጥንት ጀምሮ በቡድን በቡድን እንዲለያዩ ካደረጓቸው ገጽታዎች ውስጥ ቋንቋ አቢይ ድርሻ አለው፡፡ ነገዶች ሆነ ብሄረሰቦች ትልቁ መለያቸው ቋንቋቸው ነው፡፡ የየቋንቋው ባለቤቶች ዱሮም ቢሆን ልዩነታቸውንና ተመሳሳይነታቸውን እንዲያውቁ በተለምዶ በያካባቢያቸው የሚገፋፏቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ከተሞች በያቅጣጫው ሲፈልቁ ለንግድ የሚንቀሳቀሱት በተለይ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር የሚገናኙበትና የእራሳቸውን ይዞታ የሚያነጻጽሩበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸው “እኛና እነሱ” የሚለው አነጋገር ሆነ አስተሳሰብ እየበዛ ሄደ፡፡ በዛሬው ኢትዮጵያ ሰዎች ሁሉ ማንነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲችሉ ሁኔታው አመችቷቸዋል፣ አስገድዷቸዋልም፡፡ ያመቻቸው በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች የራሳቸውን የቡድን አለማ ማሳኪያ ይሆናል ብለው የተነሱበትን የብሄረሰቦች መብት ጉዳይ በህገ መንግስት ላይ ስላወጁላቸው ነው፡፡ ግዳጁ ግን ከህገ መንግስት ድንጋጌው በኋላ ሁሉም ሲራወጥና ማነነቱን ለማረጋገጥ ሲጣጣር ዝም ብሎ መቀመጥ ስላልተቻለ ነው፡፡ በቅርቡ የቅማንት ህዝብ ራሴን ችየ ልቋቋም ብሎ በጎንደር አካባቢ ሲውተረተር ካካባቢው ሌላ ህዝብ ጋር የተፈጠረው ውዝግብ የዚህ ተምሳሌት ነው፡፡
ይሁንና የማንነት መብት መሰረቱ በህግ ወይም በይፋ ስለታወጀ ነው የሚሉ አልታጡም፡፡ ማንነቱ በተፈጥሮ ከተገኘ ክስተት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ሰዎች በቃላት ስም ስላወጡለት የተወለደ አድርገው ያዩታል፡፡ መፍትሄ አድርገውም የሚሰነዝሩት ስሙ ሳይነሳ ልክ እንደሌለ ቆጥሮ ወይም ጉዳቱ ያመዝናልና እንርሳው ተብሎ መገኘት ነው፡፡ የአጼ ቴዎድሮስ ዝርያዎች የሆኑት ቅማንቶች ጠፉ፣ አማራው ውስጥ ገብተው ቀለጡ ከተባለ ከስንት አመታት በኋላ እንደገና ለማንሰራራት መሞከራቸውን ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ባለስልጣኖች እኩይ ቁስቆሳ የተነሳ እድርገው የጥያቄያቸውን ተገቢነት ለመቀበል አሻፈረን ያሉት በርካታ ናቸው፡፡ ባለስልጣኖቹ ቆሰቆሱ አልቆሰቆሱ ቅማንትነታቸውን መነሻ አድርገው የራሳቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና አስተዳደር በጃችን እናስገባለን ቢሉ ምንድን ነው ጥፋቱ; ይባስ ብለው ከቅማንትነት አልፈው የአገው ዝርያዎች በመሆናቸው ሁሉንም አገዎች (በምስራቅ ኽምራን በምእራብ አዊን ይዘው) አስተባብረን ባንድነት እንቋቋም ቢሉስ አያስኬዳቸውም; በዚያውም እስራኤል ድረስ ከተዘራው የአገው (የ”ፈላሻ”) ክፍሎች ጋር ቁርኝት እንፍጠር ማለትስ; (በተግባር ለማዋል ይቻላቸዋል አይቻላቸውም የሚለው ጥያቄ ሌላ ጉዳይ ሆኖ፡፡)
የመብቱን መኖር የሚቃወሙት ክፍሎች በብሄረሰብነት መፈረጅን እንደጎጂ፣ ለርስ በርስ መፋጠጥ እንደመነሻ አድርገው የሚያዩት ብሄረሰቦች ለረዢም ዘመናት ስለባህላቸው፣ ቋንቋቸውና እምነታቸው መተንፈሻ አጥተው ስለነበሩና ዛሬ መነቃቃት ስለጀመሩ ልኩን ባለማወቅ ከሚያሳዩት “ፍጹምነት”፣ “ጭፍንነት” ጋር ሲያስተያዩት እየተምታታባቸው ይመስላል፡፡ መነሻ ምክንያትንና ውጤትን አንድ ላይ ጨፍልቀውም መብቱ እንዳይኖር ወይም ከኖረም በተግባር ሳይተረጎም በከንቱ እንዲቀር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ታዲያ ወደመፍትሄ ሳይሆን ወደባሰ ውጥንቅጥ ሁኔታ ያስገባል፡፡
የብሄረሰቦች መብት መታወቅ የመጀመሪያ እርምጃ እንጂ የመጨረሻ ሊሆን እንደማይችል ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ የመብቱ መገለጽና በህግ መቀረጽ ፋይዳ ገና ዳዴ የሚለውን የየብሄረሰበቡን የማንነት መረጋገጥና የሰብእና እድገት ጎዳና መክፈት ነው፡፡ ከዚያ አልፎ የመብቱን ተግባራዊነት ለማሳካትና ለማረጋገጥ መደረግ ያለባቸውን ማወቅም እጅግ አስፈላጊ እንዲያውም አስገዳጅ ያደርገዋል፡፡ የመብቱ መኖር መገለጽ ለብቻው የትም አያደርስምና!
በየብሄረሰቡ ውስጥ ራስን ከሌሎች ለይቶ ከማወቅና ከማቋቋም ጋር የሚፈጠር አላስፈላጊ አዝማሚያ ሊኖር ይችላል፡፡ ከሁሉም በላይ “ራሴን በማናቸውም መስክ እችላለሁ፣ ታሪኬንም ለእኔ በሚጥመኝ መልክ እንደገና እሰራዋለሁ” የሚሉት ነጥረው ይወጣሉ፡፡ እነዚህ ሲመነዘሩ ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር የነበሩትን ያለፉ ግጭቶችና በጦር ሜዳም መሰላለፎች ልክ አዲስ እንደተፈጸሙ አድርጎ “መልሰን እንዋጋና ይዋጣልን” አይነት መንፈስ እየተሰራጨ የመናናቅና የመበቃቀል እይታዎች ይራገባሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ለምን ተከሰቱ ማለቱ አይበጅም፡፡ መከሰታቸው የማይቀር ነውና፡፡ ይልቁንም የራስን ማንነት የመሳሉና የመገንባቱ ጎዳና የዱሮውንም መመርመር አስገዳጅ ያደርገዋል፡፡ ዱሮ ተዋግተን፣ ተዳምተን፣ ተላልቀን ነበርና እሱ ዛሬ ስለማይጠቅመን እንተወው የሚል አስተሳሰብ እስኪስፋፋ ድረስ የመጀመሪያውን የመብት ማወቅ ርምጃ ተከትለው የሚወጡት “አላስፈላጊዎቹ” እይታዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አነዚህ እይታዎች በብሄረሰቦች መካከል ዱሮ የሰፈነውንና ዛሬም ሙሉ በሙሉ ያልታረመውን የበላይና የበታች ግንኙነት ለማስተካከል በመፍትሄነት እንዲያግዙ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሄዶ ሄዶም እይታዎቹ የማይቀሩ ስለሆኑ የዛሬውን ብሎም የነገውን የእኩልነት፣ የመተጋገዝና በሰለም አብሮ የመኖር ጎዳና ለመቀየስ የትናንትናውንና የትናንት በስቲያውን ማደፋፈኑ አይቻልምም፣ አይጠቅምም፡፡
የአኖሌ ሃውልትና መሰሎቹ ለብዙዎች ግፍ ተሰራብን ለሚሉ መጠነኛ ማስታገሻና “ካሳ” አይነት ግልጋሎት አላቸው፡፡ “ግፍ” የተባለው ለመፈጸሙ ማስረጃ አለ; የለም; የሚለው ንትርክ እንደተጠበቀ ሆኖ ጡት መቁረጥ ባይኖር እጅ፣ ቋንጃ፣ እግር መቁረጥና ሌላ ሌላም የተፈጸመበት ህዝብ በዳኝነት የሚቆመው ራሱ እንጅ በታሪክ ተጠያቂው ወይም አሸናፊው ወገን ስላልሆነ በሃውልቱ መኖር ዙሪያ ብስጭትና ሙግት መፍጠሩ ርባና የለውም፡፡ የተመዘገቡትና መድረሳቸው የተረጋገጡት ግፎች በምን መልክ ይዘከሩ የሚለው ጥያቄ የግፉ ቀማሽ ህዝብ ጉዳይ ስለሆነ፡፡ በርግጥ የሃውልቱ መቆም ትርጓሜ ላይ የተበታተኑ ሃሳቦች ሊቀርቡ ይችላሉ፤ ይገባልም፡፡ የአኖሌ ሃውልት ሆነ የጨለንቆ ብሎም በአዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ በቆመው የምኒልክ ምስል ላይ ያስተሳሰብ መጋጨት መፈጠሩ ከህብረተሰባችን ዝብርቅርቅነትና ከእውቀት አለመዳበር ጋር የተቆራኘ ስለሆነ መፍትሄው ግልጽ ንግግርና ክርክር አንዲካሄድ መፍቀድ እንጅ ሃውልት ማፍረስ ወይም መናድ ሊሆን አይችልም፡፡
ያገሪቱ እድገት በተለያዩ መንገዶች ተተብትቦ ባለበት ዘመን ለችግሮቻችን ዘላቂው መፍትሄ በአስተሳሰብ መናቆርና መዋደቅ እንዳልሆነ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ያስተሳሰብ ጥራት የፈለገውን ያህል ቢሆን የህዝቡን ኑሮ ቁሳዊ መሰረት ለመለወጥ እስካልተቻለ ድረስ መልሶ መልሶ በችግሮች እሽክርክሪት እንድንላሽቅ ተደርገን እያለን ወደእድገትና መሻሻል አለመድረሳችን ሊያስገርም አይችልም፡፡ የጋራ መቻቻል፣ መተሳሰብ፣ አብሮ የመኖር ባህል ማዳበር የመሳሰሉት ምንም ያህል ጊዜ ተደጋግመው ተሰበኩ መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እንዳልነው የህዝቡ የኑሮ ቁሳዊ መሰረት ሲቀየር ነው፡፡
በግለሰብ ደረጃ ሆነ በብሄረሰብነት “ጠባብነት” የሚገለጸው ከድንቁርና ጋር እንደተያያዘ አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ አንዳንዶችማ ጭራሽ እንደበሽታ የሚይዝ ወይም የሚጥል አስመስለው መድሃኒቱ ያንን ህዝብ ካላጠፋን እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ባለታሪክ ጥላሁን ይልማ የሚባል ሳይንቲስት “ኢትዮጵያ ከኤርትራና ከትግራይ ትገንጠል” የሚል ሃሳብ በጥር-የካቲት 1989 የኢትዮጵያ ዳሰሳ በሚል ጋዜጣ ላይ (ርእሱ “አዲስ ካርታ ለኢትዮጵያ” የሆነ) ሲያቀርብ “ትግሮች ለመገንጠል ተዋግተው ስልጣን ላይ ሲወጡ ያንኑ ህገ መንግስታቸው ውስጥ አስገቡት፡፡ ሰው ወደማይኖርበት ክልላቸው ሄደው በርሃብ ቢያልቁ ይሻላል፡፡” ብሎ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ እንደጥላሁን ይልማ አባባል “አዲሱ የኢትዮጵያ ካርታ የትግሬ ዘረኞችን ባንድ ላይ ሰብስቦ በማስቀመጥ የብሄር መከፋፈል አስተሳሰባቸው ወደሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዳይዛመት ማድረግ ያስችላል፡፡” በተጨማሪም “አገራችን በሻእቢያ/ህወሃት እጅ ፈጽማ እንዳትፈርስ ለማዳን አሁኑኑ እነዚህን አጥፊ ወገኖች ከህብረተሰባችን ማስወገድ አለብን፡፡” እያለ ሰብኳል፡፡
ሌሎች በበኩላቸው “ጠባብነት” በአስተሳሰብ ደረጃ ብቻ ያለ፣ ምንም የሚቆምበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ መሰረት እንደሌለው ብሎም በአንዳንድ “ክፉ” ግለሰቦች የሚራገብ አድርገው ያዩታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ አስተሳሰብ ዙሪያ የሚኮለኮሉ የተቋውሞና የድጋፍ ሰፈሮች መደማመጥንና ምክንታዊነትን ባለመያዝና ባለመቀበል ጩኸታቸውን ከፍ በማድረግ ብቻ የሚያሸንፉ ይመስላቸዋል፡፡ አስተሳሰቦች ባጠቃላይ ማሸነፍ የሚችሉት ወይም የሚወድቁት ነባራዊውን አለምና ክስተቶችን በጥሞና መርምረው ሲገኙ ወይም ሳይገኙ ብሎም የሚቀበላቸውና የሚጋፋቸው ህዝብ ሲኖር ነው፡፡
በብሄረሰብነት መጠራትን የ”ዘር ፖለቲካ” ብለው ከሚመድቡት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚቀርበው አንዱ ትልቅ ክርክር ጣልያን ተክሎብን የሄደ የመከፋፈያ መርዝ ነው ይሰኛል፡፡ ጣልያን ላገዛዙ እንዲያመቸው ኢትዮጵያን በታትኖ በየዘሮች እንደከፋፈላት ጠቅሰው በተለይ ከኢትዮጵያ ተባሮ የወጣው ኦስተሪያዊው ባሮን ሮማን ፕሮቻሽካ በዘረኝነት የተሞላውን መጽሃፉን ለፋሽሽቶች በማበርከቱ እንደጠቀማቸው ያንኑም አስተሳሰብ ዛሬ ህወሃት/ኢህአዴግ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነ ይዘረዝራሉ፡፡
ይህን አይነት አስተሳሰብ ካላቸው ውስጥ አንዱ አሁን በህይወት የሌለው አለሜ እሸቴ ይገኝበታል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዘር መለወስ ምንጭ፤ ከፋሺዝም እስከፋሺዝም በሚለው የ1995 አም መጣጥፉ እላይ የተወሳውን ኦስተሪያዊ መሰረታዊ አስተሳሰብ ይጠቅሰዋል፡፡ እንዲህ ብሎ “የራስን እድል የመወሰን መብት ተስጥቷቸው ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ አገዛዝ ስር የሚኖሩት በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት ሃበሻን ከሚገዙት አናሳ ክፍሎች የሚለያዩት በርካታ ህዘዝቦችና ነገዶች ያበሻን ቀንበር ከዘመናት በፊት አሽቀንጥረው በጣሉት ነበር፡፡…የተባበረ ያበሻ ህዝብ የሚባል ነገር የለም፡፡ በሃበሻ የሚኖሩት ክርስቲያን ያልሆኑት ነገዶች አብዛኞቻቸው ከአማሮች ጭቆና ነጻ ከመሆን የበለጠ አንገብጋቢ ፍላጎት የላቸውም… ነጻ ድምጽ መስጠት ቢችሉ ኖሮ ከዳር እስከዳር ከሚጠሉ ዘራፊዎቸችና ጉልበት መጣጮች ይልቅ በአውሮፓውያን ስር ተጠልለው መኖርን ይመርጡ ነበር፡፡ ይህች አገር በመገጣጠሚያዎቿ ሁሉ እየተንቋቋች ነው፣ እስከ ዛሬም አንድ ላይ ሆና የቆየችው ጭካኔ በተመላበት ሃይል ብቻ ነው፡፡”
እንደአለሜ እሸቴ ከሆነ ፕሮቻሽካ “የራስን እድል መወሰን” የሚባለውን ለኢትዮጵያ አገዛዝ መገነጣጠል ፍቱን መሳሪያ አድርጎ ሲያቀርብ የመጀመሪያው ነበር፡፡ በዚህም ያሜሪካው የስለላ ድርጅት ሳይቀር ይህንን መብት ሲያስተጋቡ ኢትዮጵያን በነገድ እንድትሰነጣጠቅ የሚሻውን የፕሮቻሽካን አስተሳሰብ ቃል በቃል እንደተቀበሉ ይከራከራል፡፡ ማስረጃ አድርጎ የሚጠቀመውም ጣልያን ኢትዮጵያን በ1928 አም አሸንፋ የቀድሞ አውራጃዎችና አካባቢዎችን ገነጣጥላ የቅኝ ግዛት ክፍሎች አድርጋ ማወጇን ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባን እንደልዩ ግዛት ትቶ ነገድን እየተከተለ ኤርትራ (ትግራይን ጨምሮ)፣ አማራ፣ ሃረር፣ ጋላና ሲዳማ እንዲሁም ሶማሌ ብሎ 5 ቅኝ ግዛቶችን እንዳዋቀረ ያትታል፡፡ እያንዳንዱ አካባቢ የራሱን ቋንቋና ጽሁፍ እንዲሁም እስልምናን እንዲጠቀም በተለይ ደግሞ የላቲንና አረብ ፊደሎችን እንዲገለገል ግፊት እንደነበር ይጠቅሳል፡፡ “አማርኛ ከይፋ ቋንቋነት ተነስቶ አረብኛ፣ ጋልኛና ካፍኛ በትምህርት ቤት እንዲሰጡ” በተጨማሪም እያንዳንዱ ቅኝ ግዛት ራሱን ችሎ እንዲተዳደር ከሮማው ማእከላዊ መንግስት ጋርም ግነኙነት እንዲያደርግ ይፈቀድለት እንደነበር ህጉን እያያያዘ አስፍርል፡፡
የፋሺስት ጣልያን አላማ አገሪቱን ካሸነፈ በኋላ ያለተቃውሞ ለመግዛት እንዲያስችለው ባገኘው መንገድ ሁሉ መከፋፈሉና መቆራረጡ ምንም የሚደንቅ አይሆንም፡፡ የኦስተሪያውን ዘረኛ ስብከትም ተከትሎ የተደረገ ነው የሚያሰኝበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያውን አገዛዝ ዋና ምልክቶች ማለትም አማርኛንና ኦርቶዶክስ እምነትን ሸርሽሮ በሌሎች ለመተካት መምረጡ ከእቅዱ ጋር የሚሄድ ስለሆነ እንጅ ልዩ ተልእኮ እንዳበጀ የሚያስተች አይደለም፡፡ የፋሺስት ጣልያን ስርወ መንግስት ባፍሪካ ላይ እንዲያንሰራፋ የግድ ጥንካሬ አብጅተው ያሉ ባህሎችንና ስብስቦችን መበተኑ ከዚያም በፋሺስቱ ስርአት ውስጥ በሌላ አኳኋን እንዲሰባሰቡ መደረጉ ያገዛዝ ስልት እንጅ በተለይ “የራስን እድል መወሰን” ከሚለው መርህ ጋር የተቆራኘ አይደለም፡፡ አለሜ ራሱ የጠቀሰው አንድ የፋሺስት ስርአቱ ለፋፊ እንዳለው “የቅኝ ግዛቶቹ ወሰኖች አበጃጅ የፋሺስት ህግ አውጭዎች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ፣ የተለያዩትን ህዝቦች ዝንባሌዎችና ባለፈው መቶ አመት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተከሰቱትን ድርጊቶች ምን ያህል በጥንቃቄና በትኩረት እንደተከታተሉት ህያው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሸዋው መንግስት የዳርቻ አካባቢዎችን ህዝቦች ጥቅሞች እየጣሱ ወደመሃል የማጠቃለል ስራዎቻቸውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡” በሱ አስተሳሰብ ያዲሱ አደረጃጀት አላማ የሸዋው ገዥዎች በየዳር አገሩ ሁሉ የፈጠሯቸውን ፍራቻዎችና የመገለል ስሜት ለመምታት እንደነበረ ነው፡፡
ሄዶ ሄዶ የጣልያን አገዛዝ የተባበረ የቅኝ አገዛዝን የሚቃወም እንቅስቃሴ ባገሪቱ አንዳይስፋፋ ህዝቦችን በየጎጣቸው አሰልፎ መጠነኛ ጉርሻ ለመስጠት ነበር፡፡ በኤርትራ ያገኘውን መረገጫ ምድር ተጠቅሞ ለወታደራዊ ዘመቻው ሃይል ከካባቢው ተወላጆች መመልመል (በሊቢያም ጭምር ለማሰማራት) እንደቻለ ሁሉ በተከፋፈለች ኢትዮጵያም ያንኑ ለማግኘትና ለሌላም ሌላም እቅድ ለማዋል ምኞት ነበረው፡፡ ለመሆኑ ጀርመኖች እንግሊዝን አሸንፈው ቢይዙና በአፍሪካ ያለው የእንግሊዝ ጦር ቢመታ ኖሮ የጣልያን ይዞታ ሙሉ በሙሉ ተለውጦ የኢትዮጵያ ህዝቦችም ለሚከተለው የጦርነት ስምሪት ማገዶ ሊሆኑ ይችል አልነበረም;
ሌሎች ተሟጋቾችን እንመልከት፡፡ ፍስሃ ጽዮን መንግስቱና ተባባሪዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የማያቋርጥ እብደት በሚል ርእስ በአዲስ መንበር ጋዜጣ ጥቅምት 8 ቀን 1992 ላይ ይህንን ደርድረው ነበር፡፡ “ባለፉት ሰላሳ አመታት አላስፈላጊ የሆኑ መከፋፈሎች፣ ጦርነትና ስቃይ ከፈጠሩት ዋና የርእዮታለምና የፖለቲካ ምክንያቶች መካከል አንዱ በጣም የጎደፈው ‘የብሄሮች እስከመንገንጠል የሚደርስ የራስን እድል የመወሰን መብት’ ነው፡፡ ይኸው ጉዳይ የኤርትራን መገንጠልና የኢትዮጵያን ፖለቲካ በብሄረተኝነት መቀባት አስከትሎ ይህ ነው የማይባል መዘዝ ለኢትዮጵያውያንም ለኤርትራውያንም ዳርጓል፡፡” ተሟጋቾቹ አለም በመጠቃለል ሂደት ላይ በመግባቷና ኩባንያዎች እየተዋዋጡ የአለም ታላላቆቹ 3 የገበያና የገንዘብ ምድቦች (ዶላር፣ ዩሮ ና የን) እያየሉ በመምጣታቸው አገሮች የአለም ኢኮኖሚ አካል እንዲሆኑና “የገበያዎችን መከፋፈልና መገንጠልን ፍጹም ትርጉም እንዲያጡ” አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡
አክለውም “እንደኛ ባሉ ብዝሃነት በሰፈነባቸው ድሃ፣ ኋላ ቀር አገሮች ውስጥ ‘የመገንጠል መብትን’ መቀበል ከጥቅሞቹና አገልግሎቶቹ ይልቅ እጅግ የበዛ ጉዳትና አሉታዊ ውጤቶች አሉት፡፡ እንደዚህ አይነት መመሪያዎች ለብሄራዊ ደህንነት፣ አንድነትና ለወደፊቱ ህልውናችን በጣም አስጊ ናቸው፡፡ በቀላሉ ለመግለጽ፣ እነዚህን የእብደት፣ ርስበርስ የመጨራረስና አንዱ ሌላውን የማግለል መመሪያዎች መከተል ከቀጠልን ምንም ብሩህ እድል አይኖረንም፡፡” ይላሉ፡፡ እንደነሱ አስተሳሰብ በተለይ የእምቅ ሃብቶች ባለንብረትነት በየብሄረሰቡ ከተከፋፈለና እያንዳንዱ ክልል ሌሎችን አናስገባም ወደሚል መመሪያ ካዘነበለ ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ልትቀጥል አትችልም፡፡ ስለሆነም አንቀጽ 39 መሻሻል ይገባዋል ይላሉ (ከሌሎች የህወሃት/ኢህአዴግ መመሪያዎች ጋር)፡፡
ሲጠቃለል የተከራካሪዎች ዋና ነጥብ የብሄረሰቦች ማንነት ተከብሮ፣ የመገንጠል መብት ቀርቶ፣ በጋራ ህብረተሰቡን ወደተሻለ እድገት ለማሸጋገር ያገሪቱ ሃብት በተወሰነ ብሄረሰብ እጅ መያዝ እንዲቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያገሪቱ ሃብት ባለቤት መሆን እንደሚገባቸውና “እራሱን የኢትዮጵያ መንግስት ብሎ የሚጠራው መንግስት የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብቶች ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ ለአንድ የተለየ ብሄረሰብ እንዳይሆን የማድረግ ተቀዳሚ ግዴታ አለባቸው” ይላሉ፡፡
የተከራካሪዎች እይታ ባለም ላይ ከደረሱት ርስበርስ ጦርነቶች (ዩጎስላቪያ) መማር እንደሚያስፈለግ በሚለው ትንታኔ ይደገፍ እንጅ ለዘመናት አንድ ላይ ታጅሎ በንጉሳዊና ወታደራዊ አገዛዝ ተቀጥቅጦ የኖረን ህዝብ በምን ተአምር ስለማንነቱና ምን አይነት አስተዳደር እንደሚሻ የሚፈቅድለትን መብት ሸራርፎ ይህች ብቻ ትበቃሃለች እንደሚባል ግልጽ አይደለም፡፡ ወይስ ህዝቡ ለመወሰን መብት አይኖረውም; መብቱም በወረቀት ከሰፈረ በኋላ ባዶ ሆኖ እንዲቀመጥ ማን እንደገና ሊወስንለት ነው; ዴሞክራሲ ህዝቡ ባለመብት የሚሆንበት ስርአት አይደልም እንዴ; ስለሆነም ፍስሃ ጽዮን መንግስቱና ተባባሪዎቹ የዱሮውን ስርአቶች ሙጭጭ ብለን ይዘን እንድንቆይ ነው የሚወተውቱን; ደግሞስ ስለመሬት ባለቤትነትና አጠቃቀም በጅምላ ያገሪቱ ሃብት መሆን ይኖርበታልን ከየት አመጡት; ያለውን ስርአት በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲቀጥልበት ለመገፋፋት ነው;
ፍስሃ ጽዮን መንግስቱና ተባባሪዎቹ እንደበርካታ ሌሎች የመገንጠል መብት ተቃዋሚዎች አንድ መሰረታዊ ግድፈት አለባቸው፡፡ ብሄረተኝነትንና የራስን እድል የመወሰን መብትን አንድ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ወይም የመብቱ መኖር ለብሄረተኝነት በር ይከፍታል ባይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከነጭረሹ መብቱን መሸበብ የተገባ መመሪያ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ወደባሰ አቅጣጫ ይወስዳቸዋል፡፡ መጀመሪያ ነገር መብቱ ምንም ዳር ድንበር ሳይበጅለት በህዝቡ ተግባራዊ ካልተደረገ መብቱ ሙሉ ሊባል አይችልም፡፡ ለሰሚያቸው ማሳመኛ ያገኙ እየመሰላቸው የመብቱን መዳረሻ “መገንጠል” ብቻ አድርገው ሲያቀርቡ ለመብቱ መሸራረፍ በቂ መከራከሪያ እንዳበጁ ይቆጥሩታል፡፡ ነገር ግን ሁለት ወዶ አይሆንም፡፡ መብቱ በልቅነት ስራ ላይ ከዋለ ወይም ገደብ ካልተበጀለት ወደመገነጣጠል ያመራል በሚል ተሸራርፎ እንዲቀር ሲወተውቱ ወደዴሞክራሲ መግባት እንደማይቻል መመስከራቸው ነው፡፡ ወደዴሞክራሲ ለመግባት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ካላቸው ደግሞ ምንም ሆነ ምን ውጤት ካለ ያንን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡
የብሄረተኝነት መነሻ ባብዛኛው የዚህን አይነት የተምታታ አስተሳሰብ ለመቃረን ከሚፈልጉ መሃል ነው፡፡ መብታችንን አያውቁልንምና ራሳችንን ችለን ካለንበት ፖለቲካዊ አስተዳደር ውጭ እንኖራለን በሚል ይጠነሰስና ስልጣን ላይ ካሉት ጋር በሚከተለው ግጭት ሳቢያ እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ የብሄርና ብሄረሰብን ለብቻ የማቋቋም ወይም ከሌሎች ተገንጥሎ የመኖር እንቅስቃሴ ስር መሰረቱ የመብት ጥሰት እንጅ የአጉል ምኞት አይደለም፡፡ ሁሉም ህዝቦች በእኩልነትና በመከባበር የሚኖሩበት ስርአት ከተበጀ ማናቸውም ወገን ተነስቶ አልተመቸንምና እንውጣ የሚል ስብከት ቢያሰራጭ ብዙ ተከታይ አያገኝም፡፡ በካናዳ በኪዩቤክና በብሪትን በሰኮትላንድ በተለያዩ ጊዜያት የታዩት እነዚህን ያረጋግጣሉ፡፡
በርግጥ ከመብት አለመከበር ጋር የሚዳመሩና የብሄርተኝነት ችግሩን የሚያባብሱ ሌሎችም ገጽታዎች አሉ፡፡ ከአገዛዙ አወቃቀርና የስልጣን አከፋፈል ጋር የብሄርና ብሄረሰብ ይዞታዎች፣ የቁጥር ልዩነቶች፣ የአንጡራ ሃብት ክምችትና ስርጭት፣ የታሪክ ጠባሳዎች እንዲሁም የባህላዊና ስነልቡናዊ ትስስሮች መዳበር አለመዳበር ችግሩን ሊያባብሱት ወይም ሊገቱት ይችላሉ፡፡
ለምሳሌ አድርገን በስፋት የሚወራውን የአማራን ህዝብ ብሄርተኛ አለመሆን ጉዳይ እናንሳ፡፡ (አማራው ብሄርተኛ ካልሆነ ታዲያ ማነው ሌላ ብሄርተኛ; ወይስ ባገሪቱ በሙሉ ብሄርተኞች የሉም;) ብርሃኑ አበጋዝ “የኢትዮጵያ አገዛዝ ስልትና እንቆቅልሽ የተሞላበት አማራ” በሚል ጽሁፍ ይህንን የአማራ “ጸጋ” ከጠቀሰ በኋላ እስከዛሬ “የአማራ ዘርን መነሻ ያደረገ ፓርቲ ለመመስረት የነበረው ተቃውሞ እየቀረ ለራስ-መከላከያ ድርጅቶች እንዲያም ብሎ የተገንጣይነት ስሜት ያላቸው ብቅ እያሉ ነው፡፡” ይላል፡፡ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው ብሎ ራሱን ከጠየቀ በኋላ የሚሰጠው መልስ ባንድ በኩል “ያንድ ቡድን በአጋጣሚም ሆነ በእቅድ በመንግስት መመሪያ ሲጠቃ፣ የባህላዊ ንቃቱ ቀስ በቀስ ራስን ከሌላው ወደመነጠል ይሸጋገራል፡፡” ይልና በሌላ በኩል ደግሞ “አማሮች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ለየት የሚሉበት ከዘር ስብስብነት አልፈው ባንድ ህብረብሄር አገዛዝ ስር ወደብሄርነት መሸጋገራቸውን የጨረሱ መሆናቸው ነው፡፡”ይላል፡፡ በሱ አስተሳሰብ አማሮች በብሄርተኛነት የማይታሙ ስለሆነና በህብረብሄርነት መጠቃለልን ስለሚሹ፣ ከዘር ስብስብነት ወደብሄርነት ስለተሸጋገሩም አማራጩ ወይ ዘመናዊ ኢትዮጵያዊ የህብረብሄር አገዛዝን አጠናክሮ ማቆም አለበለዚያም በአንቀጽ 39 ድንጋጌ ተገፋፍተው ሁሉም የየራሳቸውን መንገድ አዘጋጅተው ሲሄዱ አማሮችም ራሳቸውን ለማዳንና የራሳቸውን አገዛዝ ለማቋቋም መዘጋጀት አለባቸው፡፡
በብርሃኑ አበጋዝ አመለካከት የአንቀጽ 39 መኖር ራሱ በኢትዮጵያ አገዛዝ ላይ ወደኃላ መሽቀንጠርን አስከትሏል፡፡ ታዲያ እሱ እንደሚለው አማራው እንኳን ታድሏል (ሽግግሩን ጨርሷልና) ሌሎች አብረውት በህብረብሄራዊ ጎዳና ለመሄድ ምን መተማመኛ፣ ምን መመሪያ ሊይዙ ነው; ኢትዮጵያ ከነበረችበት “የብሄረሰቦች እስር ቤትነት” ወደ ህብረብሄራዊ አገዛዝና ወደ ዴሞክራሲ ለመሻገር እንዴት ትቻል; ህዳጣን ስብስቦች ሆኑ ብሄረሰቦች ህልውናቸውን፣ ባህላቸውን ሆነ ጥቅማቸውን በቀጥታ የሚያስጠብቅላቸው ምን ተቋምና መዋቅር ይኖራል ወይስ ምንም አያስፈልግም?
በነገራችን ላይ አማራው ራሱ ሆነ ሌሎችም ከዘር ስብስብነት ወደብሄርነት ገና አልተሸጋገሩም፡፡ (ስለዚህም ነው ብሄረሰብ የተባሉት፣ ብሄር ወደመሆን ገና የሚያመሩ ለማለት) አማራው በተለይ የብዙ ዘሮችና ትውልዶች ድብልቅ ስለሆነና ካንድ ቁርጥ ጎሳ ወይም ነገድ ብቻ ስላልመጣ (ባብዛኛው ከአገዎችና መሰል ህዘቦች ተውጣጥቶ አዲስ በተፈጠረው ጉራማይሌ ቋንቋ ዙሪያ ስለተወለደ) ወደብሄር የሚያሸጋግረውን መንገድ ለማቋረጥ ገና ብዙ ገና ይቀረዋል፡፡ በአማራው ህዝብ መሃል የስነልቡና ውሁድነት ገና ለመገንባት ካለመቻሉ ሌላ በቋንቋውና በባህሉ የተፈላቀቀ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ አንድ ቀበሌ፣ ጎጥ፣ ወረዳ፣ አውራጃ ከሌላው አቻው ጋር እየተፎካከረ፣ እንደተለያየ አገር ከሚተያዩበት አስተሳሰብና ልምድ ገና ለመውጣት ያንን “ጠባብነት” የሚያጠፋ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ (ትምህርታዊ) ሽግግር ይጠብቃል፡፡
የትግራይ ትግርኚት ብሄረሰብማ በባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደገባ ነው፡፡ ባንድ በኩል የሸዋ ነገስታት በውስጡ የቀበሩበት ርስበርሱ የመናናቅና የመናቆር ስሜት በሁለት መንግስታት ስር እንዲወድቅ አድርገውታል፡፡ አጋመ የሚባለውን ህዝብ ጨፍልቀው ምንም ሳያስተርፉ እራሳቸው ጋር እንደቀላቀሉት ሁሉ ጭራሽ የዘለፋ ቃል አድርገው አንደኛው ሌላውን ይተችበታል፡፡ በሌላ በኩል ቋንቋውና ባህሉ አብሮ እንዲራመድ ለህዝቡም ውህደት እንዲያግዝ ከመርዳት ይልቅ በፖለቲካ ብጥብጣቸው አማካይነት የህዝብና ህዝብ መቃቃርን እያሰፉት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኤርትራ ያሉት ወገኖቻችን ወደመሃል አገር እንዲመለሱ፣ በስራም በትምህርትም እንዲጠቀሙ መደረጉ ቀና አስተሳሰብና ርምጃ ቢሆንም በሁለት አገዛዞች ስር ወድቆ የሚገኘውን ህዝብ በአንድ ላይ ለማቋቋም ከሚያስፈልገው ጥረት አኳያ ውሃ የመውቀጥ ያህል ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ የተከፋፈለው ህዝብ ይበልጥ እየተራራቀ መሄዱ አይገታም፤ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተጨምሮበት አንዱ ለሌላው ባይተዋር ሆኖ መኖሩን መቀጠሉ ዘለቄታዊ የሆነ አስከፊ ውጤት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የኤርትራ ህዝብ በቀን በቀን እየተበተነ በስዴትና በችጋር እየተቆላ የራሱ ቁራሽ የሆነው ከመረብ ምላሽ ያለው ህዝብ ግን መፍትሄ ለማብጀት አለመሞከሩ ደግሞ አስተዛዛቢ በቻ ሳይሆን አሳዛኝ ነው፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ የትግራይ ትግርኚት ወዳንድ ብሄር መጠቃለሉ ቀርቶ በሁለት ደካማ ብሄረሰቦች ተሸንሽኖ መቆየቱ አይቀሬ ነው፡፡
ወደመሰረተ ውይየታችን እንመለስ፡፡ ብሄርነት ከኢንዱስትሪያዊ ህብረተሰብ ምስረታ ጋር የተቆራኘ ማህበራዊ ክስተት ለመሆኑ በስፋት የታወቀና በአለም ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ሆኖም ይህንን ቀላል ጽንሰ ሃሳብና ክስተት በኛም አገር ለመረዳት እንዲቻል አልታደልንም፡፡ እስከገጠር መንደሮች ድረስ የተስፋፋው የብሄር/ብሄረሰብ አነጋገር ከነገድ ያለፈ ትርጓሜ ሳያበጅ የዘር ስብስብነትን ተሻግረው የወጡ አሉ (አማሮች!) በሚል የተሳሳተ ግምገማ መታጀባችን አሳዛኝ ነው፡፡ በርግጥም አገራችን የቁሳዊ ሀብት አለመዳበር ብቻ አይደልም የሚጠናወታት የአስተሳሰብ (የህልናዊ) ሀብትም ጭምር እንጅ፡፡
በቀለም ቀመሱና በዴሞክራሲያዊ ሃይሎች መካከል የሚፈለገው የዘር ልዩነቶች የሉብንም፣ ጎሳና ነገድ የሚባል ዱሮ የቀረ ነው፣ ብሄረሰብ ማናምን የሚሉት ከፋፋይ አስተሳሰብ ነው የሚሉትን እጅግ ኋላ ቀርና መጨበጫ የሌላቸው ሀተታዎች ወደጎን ትተው በተፈጥሮ የተወለደውን ማህበራዊ ስብስብ መቀበልና በመብትነት የተቀረጸውን ህጋዊና ፖለቲካዊ ፈር መፍትሄነቱ ምን ያህል እንደሆነ (እንደሚገባው) ሰፋ ያለ ውይይት ማካሄድ ነው፡፡ የዋለልኝ መኮንን መጣጥፍ ከወጣ ከ45 አመታት በኋላ እንኳን ስለማህበራዊ ስብስቡ ምንነትና ስለመብቱ ስፋትና ጥልቀት ስምምነት ለማብጀት አለመቻሉ ብቻውን ምን ያህል አገሪቱን ለመምራት የሚበቁ ሃይሎች እንዳላፈራች ያረጋግጣል፡፡