Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ሥደት

$
0
0

ቦሳሶ ሶማሊያ

ቦሳሶ በገልፍ ባህረ ሰላጤ ደቡባዊ ክፍል፣ሶማሊያ ጠርዝ ላይ የምትገኘው ከተማ፣ ካርታ ላይ ሲመለከትዋት፣ ያፍሪካ ቀንድ ላይ የተቀመጠች ዝምብ ትመስላለች። አፈ ታሪክ ስለከተማዋ አሰያየም እንዲህ ይላል።

ቦሳሶ የቀድሞ ሥያሜዋን ያገኘችው ካንድ ታዋቂ ነጋዴ ሥም ነበር – ባንዳር ቃሲም ከተባለ ነጋዴ። ቃሲም ከተማ እየተባለች ትታውቅም ነበር። ነጋዴው፣ ባንዳር ቃሲም ደግሞ እጅግ በጣም የሚያፈቅራት ቡሳስ የተባለች ግመል ነበረችው። ሥለዚህ ከተማዋ ከጊዜ በኋላ በቃሲም ተወዳጅ ግመል ቡሳስ ተብላ ተሰየመች። እያደር ከቡሳስነት ወደ ቦሳሶ ተቀየረች።

አለምሰገድና ባለቤቱ ምህረት፣ ምህረትያንድ አመት ልጃቸውን አቅፋ፣ ከቦሳሶ ተነስተው ከሦስት ሰዓት ጉዞ በኋላ ማሬሮ ገብትዋል። ማሬሮ ገደላማ ናት። ካርቶን አንጥፈው የሚቆረቁረው መሬት ላይ ተቀመጡ።

አለምሰገድ ለራሱና ለምህረት 200 ዶላር፤ ለልጃቸው ደግሞ 50 ዶላር ከፍሎ ወደ የመን ለመጓዝ ተነስተዋል። ባለፈው ሳምንት፣ ሶማልያ ውስጥ፣ በአስተናጋጅነት የሚሰራበት ሬስቶራንት ውስጥ ቦምብ ፈንድቶ ሃያ ሁለት ሰዎች ከሞቱ በኋላ አለምሰገድ ወሰነ። ወደ የመን፣ ከዚያ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሄድ ወሰነ። ሬስቶራንቱ ኢትዮጵያውያን የሚያዘወትሩት በመሆኑ ሆን ተብሎ ነው ጥቃት የደረስበት ይባላል። የኢትዮጵያን ወታደሮችን በሞቃዲሹ መኖር በማይወዱ ክፍሎች የተደረገ ድርጊት ነበር ይባላል።

አለምሰገድና ምህረት ሁለት ሊትር ወተትና አንድ ካርቶን ብስኩት ለህጻኑ፤ ለራሳቸው ደግሞ ዳቦ ገዝተዋል።

ወሩ መስከረም ነው። ማሬሮ በመስከረም ወር ወደ የመን ለመሄድ በሚመኙ ሰደተኞች ትጣበባለች። የመስከረም ወር ማዕበሉ ረገብ የሚልበት በመሆኑ አሻጋሪዎች (ስደተኞችን ከሶማልያ ወደ የመን የሚያሻገሩ) ሥራ ይበዛባቸዋል።

ስደተኞቹ ማሬሮ ሆነው የሚወስዳቸው ጀልባ እስኪመጣ ይጠባበቃሉ። ከሁለት ቀን እስከ ሳምንት ያስጠብቃል። የአሻጋሪዎች ጀልባ የምትመጣው ለሊት ሰለሆነ እንቅልፍ በሰላም ማሸለብ አይቻልም።

አለምሰገድን ዛሬ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይዞታል። የጥርጣሬ ድባብ፤ የተስፋ ድባብ። የመሥከረም ተስፋ፤ የመጣበት ከተማ (ጂማ) ትዝታ፤ የጸደይ ወራት የአበቦች ልምላሜ፤ የህጻናት ሆያሆዬና የእንቁጣጣሽ ዜማ፤ አረንጓዴው ሜዳ፤ አረንጓዴው ተራራ በዳ ቡና (የቡና ተራራ) … ለምለሟ ጂማ ከተማ ታወሰችው። ለምለሙና አመቱን በሙሉ አረንጓዴው በዳ ቡና ታወሰው።

ጂማ ተወልዶ፣ ጂማ ነው ያደገው። ጂማ ነው በህጻንነቱ ምላሱን እያወጣ መሳደብ ሲጀምር የጎረቤት ሰው አናቱን በኩርኩም እያናወጠው ሥነ-ምግባር ያስተማረው። ጂማ ነው ጥርሱን እየፋቀ የፓፓያ ጁስ እየጠጣ የጎረመሰው። ጂማ አዌቱ መናፈሻን ተንሸራሽሮበታል። ጂማ አዌቱ መናፈሻ ልጃገረዶችን አሽኮርምሞበታል። ጂማ ነው በደሌ ቢራን ሲኮሞኩም የነበረው፤ ጂማ ነው ቢስን ከነግልባጩ ቢራ እየጠጣ ያመሸበት። በኋላ የ“ብርሃን” ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ አመት የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሳለ ነው ደጋጎ የተባለው ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ፕሬዚደንት “አለምሰገድ ሲፋቅ ሰባት ቦታ ተከፈለ እየተባለ ይጠረጠራል ብሎ ለተማሪዎች ዲኑ ለተሰማ ሪፖርት አድርጎ ሊታሰር ሲል ካገር የወጣው።

“አለምሰገድ ሲፋቅ ሰባት ቦታ ተከፈለ”ማለት አለምሰገድ የግንቦት ሰባት የፖለቲካ ድርጅት አባል ሆነ ማለት ነው።

ከሃገር ለመውጣት መወሰኑን ለምህረት ሲነግራት “አብሬህ የሄድክበት እሄዳለሁ” አለችው፤ እስዋም ከአራተኛ አመት የህክምና ትምህርቷን አቋርጧ።

አለምሰገድ ማሬሮ ተቀምጦ ቆጨ፤ መንትያና ሳር ሰፈርን አስታወሰ። አዌቶ መናፈሻ ከምህረት ጋር ያሳልፉት ቀናትና ምሽቶች ታወሱት።

ሰው ግን እንዴት ከገነት ወደ …(ማያውቀው ሥፍራይሄዳል ሲል አሰበ።

ጂማ ገነት ነው። አረንጓዴ ገነት! ሳውድ አረቢያ ገነት ይሆን?

ጉዞዋቸውን ወደ የመን ለማድረግ በመጠባበቅ ላይ ያሉ ሶማሌዎች፤ ኢትዮጵያውያኖችና ኤርትራውያን ማሬሮን ሞልተዋታል። ማሬሮ መረሬ ጭቃ ወደ ድንጋይ የተለወጠባት፣ ደረቅ፣ ጥቁር ቆርቋሪ መሬት ናት።

ማሬሮ ስትሆን፤ ወደግራ ስታይ መረሬ ድንጋይ፤ ወደቀኝ ስታይ መረሬ ድንጋይ፤ ወደፊት፡ ወደኋላ ስታይ መረሬ ድንጋይ።

መረሬ ድንጋዩን ላለማየት ካድማስ ባሻገር ማየት አለብህ – ተስፋ ያለው ካድማስ ባሻገር ስታይ ነው። ሰማያዊው ውቅያኖስ ሰማያዊ ተስፋ ይሰጥሃል። ማርና ወተት የሚፈሰባትን ሃገር ያመላክታል። ያቺ ማርና ወተት የሚፈስባት ሃገር ትኖር ይሆን?

ያ ሰማያዊ ተስፋ ነው አለምሰገድን እንደባሪያ ሲለፋ ከርሞ፣ ያጠራቀማትን ገንዘብ ለአሻጋሪዎች ከፍሎ፣ ቤተሰቡን ይዞ የመን ለመግባት እንዲሰናዳ እዚህ ማሬሮ አማሮ ያስመጣው።

አሞሮች በባህሩ ላይ ያንዣብባሉ። አንዳንዴ እንደቀስት ይወረወሩና ውቅያኖሱ ውስጥ ጠልቀው ዓሳ ይዘው ይወጣሉ። አንዳንዴ ደግሞ ክንፎቻቸውን ሳያራግቡ አየር ላይ ይንሳፈፋሉ። ነፋሱ ወደወሰዳቸው ይወሰዳሉ። አለምሰገድና ምህረት ይህንን አስተውለው ቆዩና ተያየ። ተያይተውም ዝም አሉ። ነፋሱ ወደሚወስዳቸው ለመወሰድ ዝም አሉ።

አንዲት ጀልባ እየቀረበች ነበር። ርዝመትዋ ቢበዛ ከሰባት ሜትር አይበልጥም። ቢበዛ ወደ ሃያ አምሥት ሰው መያዝ ትችላለች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባህሩ ዳር ከተኮለኮሉት ሰዎች ውስጥ157 ሰዎች ሲጫኑባት አዩ።

አለምሰገድና ምህረት ጀልባዎችን እየተጠባበቁ ሳለ ሁለት ወጣቶች መጡና ተዋወቁዋቸው። ነብዩና (የጁልየት የድሮ ጓደኛ) ጎይቶም መጡና አጠገባቸው ተቀመጡ።

“በዚች አይነት ጀልባ በዚህ አይነት ሁኔታ ነው እንዴ የሚወስዱን?” ሲል ጠየቀ አለምሰገድ።

“ይሆናላ፤ ሌላ ትልቅ ጀልባ ያለ አይመስለኝም። በጣም ያስፈራል ጀልባዋ ሁኔታዋ ሁሉ ልክ እንደሰማነው ይመስላል” ሥትል መልሰችለት ምህረት።

“ቆመን ነው ወይስ ተቀምጠን ነው የምንሄደው? ተቀምጠን መቼም አትበቃንም።”

“ዋ..ይ.. ደራርበው ያስቀምጣሉ እኮ! ባንዱ አናት ላይ አንዱን” አለ ጎይቶም እየሳቀ። ከተዋወቁዋቸው ወጣቶች አንዱ ነው።

ቀልደኛ ነው። እየሞተም ቢሆን ይቀልዳል ጎይቶም።

“አንተ ላይ ሰው ደርበው ካስቀመጡብህ እዚያው እንዳንሶላ ተነጥፈህ ትቀራለህ” አለ ነብዩ ጎይቶምን እያየ። ነብዩ፣ የጁልየት ፍቅረኛ።

ይ አ ነብዩ . . . እንደውም እሱ ይሻላል … ምን ሽግር አለው፤ ከላይ ከሆንኩ ነፋሱ ይወስደኛል…”

“አንዴ ይዞህ ቢሄድ ይሻለሃል አሥሬ ከምትመላለስ” አለው ነብዩ እየሳቀ።

ጎይቶም ከዚህ በፊት፣ ከዚሁ ቦታ ተነስቶ ሳውዲ አረቢያ ሁለቴ ጊዜ ገብቶ ነበር። ሁለቱንም ጊዜ ከሳውዲ አረቢያ አባረሩት። አሁን ለሶስተኛ ጊዜ እድሉን እየሞከረ ነው።

እንዴ … ነብዩ እንደዚህ አይባልም።” ምህረት ነበረች።

“አሁን እዚህ ሆነህ ቀልድ፤ እዚያች ጀልባ ላይ እንኳን መቀለድ፤ መተንፍስ አይፈቀድህም፤ አትችልምም።” ጎይቶም መለሰ። ከዚያም ቀጠለ፣

“እኔ የተፈጠርኩት ከየሃገሩ ለመባረር ነው መሰለኝ። መርካቶ ተወልጄ፤ መርካቶ አድጌ አንድ ቀን ያይንህ ቀለም ደበረን ተብዬ ወደ ኤርትራ ተባረርኩ።

ነብዩ

[1]“አንቺ አዲስ አበባ ማየቱን ተውሽ ወይ

አሳድገሽ ሲጠፉ የታሉ አትይም ወይ?”

የምትለዋን ዘፈን ነብዩ ያፏጭ ጀመር። ጎይቶም እንዳልሰማው ሆኖ ቀጠለ።

“ኢትዮጵያ ወልጄ ኤርትራዊ ተባልኩ። የሚገርመው ዜግነት ምረጡ ሲባል እኔ ኢትዮጵያዊነትን ነበር የመረጥኩት።”

ጎይቶም ቀጠለ፣

“ጦርነት ሲጀመር ደግሞ ኤርትራዊ ተባልኩና ተባረርኩ። ኤርትራ መሄዴን እንኳን አላማርረውም። ምጽዋ አይቼ የማላውቃቸውን ዘመዶቼን አየሁ። የዋና ችሎታዬንም በጣም አሻሻልኩ። እድሜ ለቀይ ባህር!”

[2]“አልፈራም ጨርሶ የባህር ውስጥ አውሬ

እድገቴ ዳህላክ ነው የትውልድ መንደሬ”

ሲል ጀመረ ነብዩ። ጎይቶም እንዳልሰማው ዝም ብሎ ወሬውን ቀጠለ።

“ሳውዲ ደግሞ ሁለቴ አባረረችኝ። እስኪ ተመልከቱት ይህንን መሬት? ይህንን ደረቅ መሬት! እኛ ካገራችን ወጥተን እዚህ መሆን ይገባን ነበር? እ? ሰላምና ፍቅር ተነሳስተን ይኸው በየቦታው እንከራተታለን።”

ጎይቶም መሬቱን እያሳየ፤ መሬቱን እየረጋገጠ በምሬት ተናገረ።

“አቦ አትፈላሰፍ …” ነብዩ አሾፈበት።

ነብዩና ጎይቶም አዲሳበባ ይተዋወቃሉ። ነብዩ የአቦይ ወልደአብና የእማማ ብርሃን የዘመድ ልጅ ያቶ ንብረት ሰፈር ልጅ ነው። ጎይቶም ደግሞ በየሳምንቱ እየመጣ አቦይ ወልደአብና እማማ ብርሃንን የሚጠይቅ ዘመድ ነው።

አለምሰገድ ጎይቶም ‘ሰላምና ፍቅር ተነሳን’ ሲል ከሰማው በኋላ በራሱ አለም ውስጥ ሰምጦ ነበር። ‘እውነትም ሰላምና ፍቅር የሳን ወይም እንድንነሳሳ የተደረግን ህዝቦች’ አለ ለራሱ።

ከሶስት ቀናት በኋላ የነሱ ተራ ደረሰ። አለምሰገድና ምህረት ጀልባዋን ለመሳፈር ቀረቡ። ሁለት አሻጋሪዎች ጀልባዋ ጫፍ ላይ ቆመው መንገደኞቹን የት መቀመጥ እንዳለባቸው እያመናጨቁና እየጋፋፉ ያሳያሉ።

አንደኛው አሻጋሪ በጣም ቀጭን፣ ረጅም ነው። ሁለተኛው አጠር፣ ደንደን ያለ ነው። ሁለቱም አፋቸውን በጫት ወጥረዋል።

ጀልባዋ ውስጥ ሌሎች ሶስት አሻጋሪዎች ይታያሉ። እነዚያም አፋቸውን በጫት ወጥረዋል። ቀጭን ረጅሙ አሻጋሪ አለምሰገድን ወደጀልባዋ ውስጥ እንዲገባ አሳየው።

አለምሰገድ “አንድ ላይ ነን” አለ ምህረትን ይዞ።

ገና ተናግሮ ሳጨርስ ረጅሙና ደንዳናው አሻጋሪዎች ገፋፍትው አንዲት አንድ ሜትር ባንድ ሜትር የሆነች የዓሳ ማስቀመጫ ሥፍራ ሸጎጡት። እዚያች ሳጥን ውስጥ ጎይቶምን ቀደሞ ተሸጉጦ አገኘው። እንደገና ለመናገር አፉን ሲከፍት አናቱን በሽጉጥ ስደፍ ጎድጉዶ አገኘው።

“አንተ አለምስገድ አርፈህ ተቀመጥ ምህረት እዚያው ትሁን ጀልባው ላይ ይሻላታል እዚህኮ መተንፈሥ አይቻልም አለው ጎይቶም

ባለሽጉጡ የጎይቶምንም አናት በሰደፍ ሰረጎደው።

ጎይቶም አናቱን እያሻሸ በሹክሹክታ

“መነጋገርም አይፈቀድም ሰው እላይህ ላይ ሲያስቅምጡብህ በተቻለ መጠን ትከሻህን ሥጠው አናትህ ላይ ከሚቀመጥብህ ይሻለሃል።”

“እዚች ሳጥን ውስጥ ከዚህ በላይ ሰው ይጨመራል? አሁን ራሱ ተጣብቀን አይደለም እንዴ የተቀመጥነው?

“ዝም ብለህ ያልኩህን አድርግ በድጋሚ እንዳልመታ” ጎይቶም ይህንን ከማለቱ ነብዩ ተጨመረ።

ባጭር ጊዜ ውስጥ እዚያች አንድ ሜትር ባንድ ሜትር በሆነች ሳጥን ውስጥ 27 ሰዎች ተጣጥፈውና ተነባብረው ታጨቁ። አለምሰገድና ጎይቶም ጉልበታቸው አገጫቸውን እስኪነካው ድረሥ ተኮራምተዋል። ትከሻቸው ላይ ሌሎችን ተሸክምው።

“ሶማሌዎቹን እንደኛ ሳጥን ውስጥ አይከቷቸውም እኮ እነሱ በሙሉ እላይ ናቸው።” ከማለቱ ነብዩም አናቱ በሽጉጥ ሰደፍ ሰረጎደ።

በመጨረሻ አንዲት ኢትዮጵያዊት ከነብዩ ላይ ተጫነች።

“የኔ እህት ወደ ሳውዲ ነው? ጎይቶም እባላለሁ በሰላም ከደረስን የመጀመሪያዋን ሻይ እንድጋብዝሽ ፍቀጂሊኝ

“አምሳለ እባላለሁ ግብዣውን ተቀብያለሁ። ባንድ አፍ።” ፈገግ አለች።

ችግር የጋረደው ውበት ልክ አፈር ውሥጥ እንደተቀበረ ዘር ነው። የተቀበረው ዘር ትንሽ ውሃ ጠብ ሲልበት አፈሩን ቦዳድሶ ብቅ ይላል። ያብባል።

ትንሽ መልካም ቃላትም የአምሳለን ፈገግታ ብልጭ አስደረጉ፣ ልክ የሚጋርዳት ደመና እንደተገፈፈላት ጸሃይ፣ ጨረሯን ብልጭ እንደምታደርግ ጸሃይ። በዚያች ብልጭታ ውበቷ ታየ። እላይ ቆሞ ይህንን ሲመለከት የነበረው አሻጋሪም ፈገግ አለ። ጥርሱ በልዟል። አረንጓዴ ሆኗል። መጣና አምሳለን ወሰዳት።

“ምነው አፌን በዘጋው” አለ ጎይቶም።

ጎይቶም ከሥር ሥለነበርና በሽጉጥ ሰደፍ ለመምታት ስለማይመች አናቱን በብረት ቱቦ ጫፍ አሻጋሪው ሸነቆረው። መድማት ጀመረ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጀልባዋ ተንቀሳቀሰች። ባህሩ ጸጥ ያለ ነበር። ሊነጋጋ አካባቢ ማዕበሉ ተነሳበት። ጀልባዋ ወደላይ እየጓነች መፍረጥ ጀመረች።

አለምሰገድ ላይ ተቀምጦ የነበረው ሰውየ ማስታወክ ጀመረ። ሳጥኑ ውስጥ ከተጨቀጨቁት ውስጥ ከያቅጣጫው ጩኸት መሰማት ጀመረ። አሻጋሪዎቹ መንገደኞቹን በዱላ፤ በብረት ቱቦና በሰደፍ መቀጥቀጥ ጀመሩ።

“ዝም በል ዝም በይ

ዷ በዱላ፤ ድም በሰደፍ፤ ጧ በጥፊ። ይህንን ሲያዩ ጀልባው ላይ ያሉት ህጻናት የበለጠ ማልቀስ ጀመሩ። ከአሻጋሪዎቹ አንዱ፤ ሃሺሽ እያጨሰ ያለው፤ ተንደርሮ መጣና አንዱን ህጻን ከናቱ መንጭቆ ወስዶ ወደባህሩ ወረወረው። እናትየው ዘላ ልትከተለው ሥትል ሰዎች ተባብረው ያዟት።

“መንጫጫታችሁን ካላቆማችሁ እያንዳንድሽን ወደ ባህር ወረውርሻለሁ።” አለና ሃሺሻሙ አሻጋሪ ከኪሱ ጠርሙስ አውጥቶ አልኮሉን ጨለጠ።

ድብደባው ጋብ ሲል ሌላኛው አሻጋሪ ሳጥን ውሥጥ የተቀመጡትን ቃኛቸው። አንዱ “እባክህን መተንፈሥ አቃተኝ ለትንሽ ጊዜ እላይ ልውጣ” ሲል በደከመ ትንፋሽ ጠየቀው።

“እላይ መውጣት ያስከፍላል። በነጻ አይቻልም። አምስት ዶላር አለህ?

“አዎን” ሲል ሰውየው መለሰ።

አሻጋሪው ሰውየውን ጎትቶ አወጣው።

ሰውየው እየተንገዳገደ ከሸሚዙ በውሥጥ በኩል በእጅ ከተሰፋች ኪሥ ውስጥ አምስት ዶላር አውጥቶ ልክ እንደሰጠው አሻጋሪው በርግጫ ገፍትሮ ወደ ሳጥኑ መልሶ ከተተው። ከዚያም ልክ ጆንያ እንደሚጠቀጥቅ ሰው ወደ ውሥጥ በግሩ አናቱን ይረግጠው ጀመር። ሰውየው ኩርምትምት ብሎ ታጨቀ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ራሱን ሳተ። ብዙም ሳይቆይ ሞተ። አሻጋሪዎቹ መጡና ጀልባ ላይ አውጥተው ኪሱን በርብረው ያገኙትን ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ ሬሳውን ወደ ባህሩ ወረወሩ።

“ዋ …የሰው መጨረሻ! ሚስኪን ሰውየ … ትላንት እኮ አብረን አውርተን ነበር ከወሎ ነው የመጣው። የሁለት ልጆች አባት ነበር። ለቤተሰቦቹ የሚነግራቸው እንኳን የለም። እንደወጡ መቅረት! መኖሩንም መሞቱንም ማንም ሰው አያውቅ!” አለ ጎይቶም።

[3] “በጎራዴ በጦር አርበድበዶ ሥንቱን ጉድ

ያስከበረኝ ልጁ ሥሰደድ

ክቡር ደሙ ገዝቶ እንዳይገታኝ ከመንገዴ

ረሃብ አስቸገሮኝ ባዶ ነበር ሆዴ!

ምሽቱንና ለሊቱን ማዕበሉ ቀለል ብሎ ነበር። ጀልባዋ ላይ ያሉት ተሳፋሪዎች በየተቀመጡበት መጸዳዳት ጀምረው ነበር።

“ይህንን ሁሉ ችለህ ነው ሶሥተኛ ጊዜ የምትሄደው? ሲል አለምሰገድ ጎይቶምን ጠየቀው።

“ምን ላድርግ? ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት።

ጀልባዋ የየመን የጠረፍ ጠባቂ ወታደሮች እንዳያዩዋት ቀጥታ የባህር መሥመሩን ትታ ረጅም መሥመር መከተል ጀመረች። በዚህ መሃል ያቺ ልጇ የተወረወረባት ሴትዮ መጮህ ጀመረች።

“ራበኝ ራበኝ” ትላለች።

አጠገቧ ያሉትን ሰዎች መናከስ ጀመረች። ሰዎቹ ፈርተው ወዳንድ ጎን መሸሽ ሲጀምሩ ጀልባዋ ወደዚያ ጎን ማዘንበል ጀመረች። አጋፋሪዎቹ መጡና የሴትዮዋን እጅና እግሯን ይዘው፤ ዥዋዥዌ አድርገው፤ ወደ ባህሩ ወረወሯት። ጀልባዋ ላይ ያሉት ተደናግጠው መጯጯህ ጀመሩ። በዚህ የተነሳ የምህረት ልጅ ማልቀሥ ጀመረ። ያ ሃሺሻም የአልኮል ጠርሙሱን አንጠልጥሎ መጣ።

“ውሃ ጠምቶት ነው እባክህን ውሃ ካለህ ትንሽ ጠብታ ትንሽ …” ምህረት መማጸን ጀመረች።

“ውሃ ነው? ውሃ? አምጪው” እያለ ቀረባት።

ከዚያም ልጇን ከእጇ መንጭቆ ወሰደውና ወደ ባህሩ ወረወረው።

“አሁን የፈለገውን ያህል መጠጣት ይችላል”

አለና በጫት አረንጓዴ የሆነ ጥርሱን አሳይቷት ጀርባውን ሰጣት። ምህረት ዘላ፣ ልጅዋን ተከትላ ባህሩ ውስጥ ገባች። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አየር የተሞሉ እንክብሎች ባህሩ ላይ መንሳፈፍ ጀመሩ።

ጀልባዋ በሶሥተኛው ለሊት ወደየመን ጠረፍ ተቃረበች። ከጠረፉ ወደ አንድ ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ላይ እያለች አሻጋሪዎቹ መንገደኞቹን እየጎተቱ ወደ ባህሩ ይወረውሩዋቸው ጀመር።

“ምንድነው የሚያደርጉት? ለምን ባህሩ ዳር ድረሥ አይወስዱንም? ነብዩ ከሳጥኑ ወጥቶ መቆም አቅቶት እየተንገዳገደ ጠየቀ።

“የየመን ፖሊሶች እንዳያዩዋቸው ነውወደ ባህሩ ዳር ከወሰዱን የየመን ፖሊሶች ሊያዩዋቸው ይችላሉ። ለዚህ ነው እዚህ የሚወረውሩን። ጠንከር ብለህ ቁም ዋና ትችላለህ አይደለም? የታለ አለምሰገድ?

አለምሰገድ ምህረትን እየፈለገ ነበር። ያን ሃሺሻም አየው።

“የታለች ምህረት? ባለቤቴ? ከትንሽ ልጅ ጋር የነበረችው?”

“እነሱ ቀደም ብለው ነው መዋኘት የጀመሩት” ያንን አረንጓዴ ጥርሱን አሳየው።

አለምሰገድ ቀስ በቀስ ምን ማለቱ እንደሆነ ተገለጸለት። በቦክሥ ያን አረንጓዴ ጥርሱን ሊያረግፈው ሲል ሌላኛው አሻጋሪ ከኋላ በበረት ቱቦ ጀርባውን ሲለው ዥው ብሎ ወደቀ። አንሥተው ወደባህሩ ወረወሩት። እሱን ተከትሎ ጎይቶም እንደቀሥት ተወርውሮ ወደ ባህሩ ጠለቀ።

*********************

ጌቱ ኃይሉ – ይህ ጽሁፍ “ጸሃዮቹ” ከተባለው መጽሃፍ የተወሰደ ነው። ጸሃዮቹ (tsehayochu) መጽሃፍ በ amazon.com ላይ ገበያ ላይ ውሏል

[1]አብዱ ኪያር እንዳዜመው

[2]መልካሙ ተበጀ እንዳዜመው

[3]ተመስገን ታፈሰ ባዜመው ላይ የተመሰረተ


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>

The post ሥደት appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles