በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ፣ በቤቶች ልማት ኤጀንሲና በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ልማት ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ በርካታ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በሕገወጥ መንገድ ላልተመዘገቡና ዕጣ ላልወጣላቸው ግለሰቦች በመስጠት፣ ለጨረታ የወጣ የሊዝ መሬት ሳይወዳደሩ ያሸነፉ በማስመሰል ለራሳቸው ጥቅም በማዋል የተጠረጠሩ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ተስፋ ሚካኤል ገብረ ማርያም፣ ጌታቸው ተመስገን፣ ዳንኤል ምንዳሴልና ይድነቃቸው ሮሪሳ፣ በአስተዳደሩ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ባለሙያ ሲሆኑ፣ አቶ ሱራፌል ልሳኑ፣ ብርሃኑ ማሞና አንገሶም ገብረ ሩፋኤል ደግሞ ነጋዴዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጥቅም በመመሳጠር፣ በተለይ የአስተዳደሩ የተለያዩ የሥራ ባለሙያዎች የተሰጣቸውን የሥራ ኃላፊነት ወደ ጎን በማለት በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት እንዳመለከተው፣ ተጠርጣሪዎቹ ባልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ስም ካርታና ፕላን በማዘጋጀት፣ አስተዳደሩ የሊዝ መሬት ጨረታ ሲያወጣ ሳይወዳደሩ አሸናፊ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን ገልጿል፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች መረጃ ቋት ላይ በእምነት ተመድበው ሲሠሩ፣ በኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ የደረሳቸውን ሰዎች በሚፈልጉት ቦታ እንዲቀየርላቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸታቸውን፣ ያልተመዘገቡና ዕጣ ያልደረሳቸው ደግሞ በደላላ ሲጠይቋቸው፣ በሕገወጥ መንገድ እንዲያገኙ የማድረግ ተግባር መፈጸማቸውን አስረድቷል፡፡
ኮሚሽኑ ቀሪ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ፣ የምስክሮችን ቃል ለመቀበልና ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጠይቆ በፍርድ ቤቱ ተፈቅዶለታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹም የዋስትና መብት ተከልክለው በፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ለግንቦት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር