ሰሞኑን የኤስቢኤስ ራዲዮ አማርኛው ክፍል አዘጋጅና አቅራቢ የሆነው ተወዳጁ ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሄድንባቸውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሂደቶችን እያስታወሰ በተከታታይ ሂደቱን ከሚያውቁና በሂደቱም ጉልህ ተሳታፊ ከነበሩ ምሁራን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ከምሁራኖቹ ብዙ ያላስተዋልናቸውን ጉዳዮች እንድንረዳ እረድቶናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በሰከነና ለማንም ባላዳላ ሕዝብንና አገርን ትኩረት ያደረጉ ጉዳዮችን ከምሁራኖቹ ወደ እኛ (ሕዝቡ) እያደረሰን ላለው ጋዜጠኛ ካሳሁን ከፍተኛ ምስጋና ሊቸረው ይገባል፡፡ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው እንግዶቹም ለበሳልና እውነትን መሠረት ያደረገ መረጃዎቻቸው አመሰግናለውሁ፡፡
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታን መሠረት አድርጎ ታሪካዊ አመጣጡን ካሳሁን ለታዳሚዎቹ ያነሳቸው ጉዳዮች ይበልጥ አደማጭን ስበዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔን የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስቅና የፕሮፌሰር አለም ሀብቱ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ አስመልክቶ፤ የአቶ አሰፋ ጫቦና ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በዋናነት የፖለቲካውን ሂደት አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ይበልጥ ትኩረቴን ስበውታል፡፡
ኤፍሬም ይስሀቅ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የሰሜን አሜሪካ መሥራችና የመጀመሪያው የማህበሩ ሊቀመንበር ማሕበራቸው ከመጀመሪያው የነበረውን ዓላማ ትቶ በፈረንጆቹ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ እሳቸው ወዳልፈለጉት አመጽ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ለውጥን መከተሉ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከእሳቸው በኋላ ማህበሩን የመሩት አለም ሀብቱ እንዴትና ለምን ማህበሩ የሥልጣን ጥማት በነበራቸው ግለሰቦች እንደተዘወረ አንስተዋል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አለም የኤርትራን ሕዝብ ጥያቄ መመለስ በሚል ሽፋን ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ከዛም በላይ ዛሬ ኢሕአዴግ በሕገመንግስቱ ጭምር አካቶት ያለው የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚለው የኢሕአዴግ ሳይሆን ከጅምሩ የተማሪዎቹ ሀሳብ እንደሆነ ጠቁመውናል፡፡ ይህን ከአለም ሀብቱ ስሰማ እንደመደንገጥ ጭምር ስሜት ጭሮብጫል፡፡ እነ አለምም ድብቅ አላማ ባላቸው ኤርትራውያን ዛሬ የሆነውን እውነት ለማምጣት የዘወሩት እንደሆነ አሰብኩ፡፡ በአንድ ወቅት የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ቤት ሥራ ሰጥቻታለሁ ማለታቸውንም እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ አለም መረጃውን ከመሥጠት ባሻገር በደንብ ለሕዝብ አሰረግጠው ቢገልጹትና እራሳቸውም ለዚህ በአለማወቅም ቢሆን የተፈጸመ ስህተት በግላቸው ይቅርታ መጠየቅ ቢችሉ አሁን ያለው ትውልድ እንዲነቃና ወደራሱም እንዲመለስ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ይህ ታሪክ እሳቸው የተሳተፉበት ስለሆነ እሳቸውም ዛሬ ላለው የብሔራዊ ስሜት መደብዘዝና ዘውጋዊ አመለካከት መጠንከር በዛው ልክ የአገር ሕልውና ፈተና አስተዋጾ ነበር ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላለው ፖለቲካ ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አሁን ሥርዓት የእነ አለም ትውልድ ፍልስፍናዎች ነጻ እንዳልሆነም እረዳለሁ፡፡ ስለዚህ እነ አለምና መሰሎቻቸውም አሁን ማድረግ የሚችሉት ከአላቸውም ልምድ እነጻር ድክመቶችንና የነበሩ በጎ ልምዶችን በመለየት ትውልዱን በብሔራዊ ስሜትና ሕዝባዊነት ማነጽ ቢሞክሩ ጥሩ ነው ባይ ነኝ፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦና ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ከዳዕማት እስከ ኢሕአዴግ በሚል አብይ ተከታታይ መወያያ ርዕስ መሠረት አድርጎ ታሪካዊ ፖለቲካዊ ሂደቶች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎች ነበሩ የቀረቡላቸው፡፡ አሰፋ የደርግን በጎ ነገሮችን ያጎላ አስተያየት ሲሰጡ በብዛት የዘውዳዊ አገዛዙን ይወቅሳሉ፡፡ አሁን ስላለው መንግስት ብዙም አልተናገሩም፡፡ ከአሰፋ ከሚሉት ጋር በብዙ አንጻር ብንስማማም ኃ/ሥላሴ የ20ኛው ዘመን ሰው አልነበሩም የሚለውን ልቀበለው አልወደድኩም፡፡ አሰፋ ወደ ደርግ ያደላ አመለካከት ስላላቸው እንጂ ኃ/ሥላሴ የደርግም መንግስት ከነበሩት ባለስልጣኖች ለዚህ ትውልድ የቀረበ አመለካከት እንደነበራቸው አንክድም፡፡ አሰፋ የምኒሊክንም ሥርዓት ከዚሁ አንጻር እንደሚያዩት ጠቁመዋል፡፡ አሰፋ ያላስተዋሉት ነገስታቱ ከምንም ወደ አንድ ትልቅ ሕዝብና መሪ መሆን የቻሉ፡፡ ለአገርም እሳቸው ከሚያወድሱት ደርግ በብዙ እጥፍ ጉልህ ሚና ያበረከቱ መሆኑን አለማስተዋላቸው ነው፡፡ የዛን ዘመን አለም ዓቀፍ ሂደቶችም የነገስታቱን የሚመስሉ እንደነበሩ ሳይዘነጋ፡፡ ከአለም እኩሉ ንጉሱ ይራመዱ እንደነበር የሚያሳየው ደግሞ ንጉሱ በአለም መድረክ የነበራቸው ተደማጭነትና ያበረከቱትም አስተዋጽዖ ነው፡፡ ዘረኝነትን ቅኝ ገዥነትን መዋጋት፣ አልፎም አፍሪካ በአሕጉር ደረጃ የሚወክላት ድርጅት ማቋቋምን የመሰሉ የንጉሱ ጉሊህ ሚና የሆኑትን ሂደቶች ከ20ኛው ዘመንም ወደፊት ቀድመው የሄዱ እንደሆኑ አሰፋ የዘነጉት ይመስላል፡፡ በአገርም ውስጥ ቢሆን ትምህርትና ዘመናዊ ልማቶች እንዲፋጠኑ ንጉሱ የበኩላቸውን ብዙ ጥረት እንዳደረጉ የሚካድ አይደልም፡፡ አገር መምራት እንደ ቀላል ነገር የግለሰብ ብቻ ጥረት ሊያሳካው የሚችል ግን አይደለም፡፡ ንጉሱ ብዙ መልካም ሀሳብና ምኞት ቢኖራቸውም በሥራቸው ያሉት መሳፍንቱና መኳንነቱ እንዲሁም አሰፋም እንደጠቆሙት የእምነት አባቶች ተጽኖ እንዲህ ቀላል ፈተና አልነበረም፡፡ ይህ ፈተና ቀደም ብለው ከነበሩት ከሚኒሊክ አንጻር ሲታይ የኃ/ሥላሴ ቀለል ብሎ ቢታይም ከደርግ ፈተናዎች ያልተናነሰ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ስለዚህ አሰፋ ኃ/ሥላሴን ከ20ኛው ዘመን ጋር የማይሄድ አስተሳሰብ ያላቸው ማለታቸው ትክክል አይደለም ባይ ነኝ፡፡ በአንጻሩ አሰፋ የደርግን በጎ ገጽ አጉልተው አሉታዊ ጎኑን ለመከላከል የሞከሩ ይመስላል፡፡ ሆኖም ግን ደርግን በጨፍጫፊነቱ፣ ባልተማሩ ሰዎች የሚመራ እንደሆነ ለምናስበው ደርግን ወደጨፍጫፊነት የገፉትን ነባራዊ ምክነያቶችና እንደተባለውም ባልተማሩ ሰዎች ብቻ የሚመራ ሳይሆን የተማሩም እንደነበሩበት ሆኖም ግን ጥፋቱ ጊዜ የወለደው እንጂ ከመሀይምነት ጋር እነዳልተያያዘ አሳውቀውናል፡፡ እንዲህ ያለው መረጃ ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ ምክነያቱ ደግሞ በጭፍኑ ያለመረጃ እየተነዳን እኛ የመሪነቱ እድል ቢገጠምን ሊመጡ የሚችሉትን ተግዳሮቶች ለማስተዋል ይረዳል ባይ ነኝ፡፡ በእርግጥ ቀደም ብዬም እንደተረዳሁት የደርግ ግፈኝነት ይልቁንም ተማርን የሚሉ በወቅቱ ኢሀፓና ምናምን የሚሏቸው ፓርቲ አባል የነበሩ ሰዎች ቀድመው የተከተሉትን ተቃዋሚህን ሁሉ አጥፋ የሚል ልክፍትና ይህንንም በተግባር በመከተላቸው ለዚያ ምላሽ ለመስጠት የሆነ ግፍ መሆኑን እንረዳለን፡፡ እስከዛሬም ድረስ ሥልጣን ላይ ያሉ የዛ ትውልድ ባሕርያት ስናይ ተቃዋሚህን አጥፋ የሚለው ፍልስፍና ይንጸባረቅባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ እንደተባለውም አልተማሩም ከሚባሉት የደረግ ባለስልጣናት ይልቅ በተማሩት ብሶ ስናየው ችግሩ ቀለም ከመቁጠር ያለፈ መማሩ ለሕይወት ፍልስፍናና ነጻነት ያላቸውን ዕውቀት የረዳቸው ነገር እንደሌለ እንያለን፡፡ ሰው ቀለም ስለቆጠረ ብቻ ፍትሐዊነትን ያውቃል ማለት ራሱ አለማወቅ ነው፡፡ ፍትሀዊነት ከጠለቀ የአእምሮ ብስለትና ተፈጥሮን ለማስተዋል የሚቻል ጥበብ የሚመጣ ስለሆነ፡፡ አገርን ለመምራትም ይህን ፍልስፍናና ጥበብ ቢጠየቅም ብዙዎች በጉልበትና በጠበበች አእምሮአቸው ሲመሩ ጥፋቱ የገዘፈ ነው፡፡ ምኒሊክ ዩኒቨርሲቲ ገብተው አልተማሩም ግን አውቃለሁ የሚል መሪ እሳቸውን ይተካል የምል እምነት የለኝም፡፡ በጥንት አባቶቻችን በታሪክ የምናውቅ ከሳውዲ የተሰደዱ እስላሞችን በስብዕናቸው የማስተናገድ ብስለት እንዲህ ካለ ጥበብ እንጂ የዩኒቨረሲቲ ዲግሪ የደረደረ ጠባብ አክራሪ አእምሮ ሊታሰብ አይችልም፡፡
ሌላው ተጠያቂ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ሰፋ ያለ ጊዜም የተሰጣቸው ሲሆን ሁሉንም በጎ ጎናቸውንም ደካማ ጎናቸውንም በስፋት ተንትነውታል፡፡ ዋነኛ ትኩረት ያደረጉት ንጉሱን፣ የደርግንና ኢሕአዴግን ሥርዓት ቢሆንም ዘለግ ብለው ከቴዎድሮስ ጊዜ ጀምሮ የነበረውን በጨረፍታም ቢሆን ሊነካኩት ሞክረዋል፡፡ ከሁሉም ግን ደርግንና ኢሕአዴግን ከሞላጎደል ሚዛናዊ በሆነ ምሁራዊ ትችት አስደምጠውናል፡፡ አሰፋም ገብሩም የኤርትራንና የሶማሌን ጉዳይ የኃ/ሥላሴ ሥርዓት የፈጠረው እንጂ ደርግ ችግሩን ከመውረስ ያለፈ የችግሩ ፈጣሪ እንዳልነበረ ጠቁመዋል፡፡ ገብሩ አሁን ያለውን ሥርዓት በጎ ጎኑን ከልማት አንጻር አንስተው ተንትነዋል፡፡ እዚህ ጋር ከእኔ ጋር አንለያይም፡፡ መንገድ ተሰርቷል፤የትምህርትና ጤና ተቋማት ተገንብተዋልና የመሳሰሉት እውነትነቱ በገሀድ የሚታይ ስለሆነ አያከራክርም፡፡ ሆኖም እሳቸው ደጋግመው ያወደሷቸው የደርግ የመሬት አዋጅና የኢሕአዴግ ፌደራሊዝም ብዙም ሚዛን ሊደፋልኝ አልቻለም፡፡ የደርግን የመሬት አዋጅ ደርግ እንደሄደበት ካልሆነ ማን ይደፍረው ነበር ተብሎ ከታሰበ መልካም፡፡ ሆኖም የደርግ የመሬት አዋጅ ዛሬም ድረስ አጨቃጫቂና የመሬት ባለቤትነትን መብት መንግስት ለራሱ ይዞ ሕዝብን የሚገዛበት መሣሪያ ሆኗል ተብሎ በብዙ ይተቻል፡፡ እውንም መሬት የአምባገነኖች መሳሪያ ሆኖ እናየዋለን፡፡ እኔ መሬት ይሸጥ ይለወጥ ከሚሉ አደለሁም፡፡ ግን በመሬቱ ላይ በተለይ ገበሬው ሙሉ ዋስትና የሚሰጥ ባለቤትነት አለው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በከተማ የሊዙ አዋች እስከወጣ ድረስ ባለይዞታዎች ሙሉ መብት ነበራቸው፡፡ ሌላው ገብሩ ኢሕአዴግን ያወደሱበት ፌደራሊዝም እኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አደገኛ ከሚባሉ ስህተቶች እንደ አንዱ የማየውን ነው፡፡ ኢሕአዴግን እኔ በሁለት ነገሮች በታሪክ ተወቃሽ አደርገዋለሁ፡፡ ሀገሪቱን ያለወደብ ማስቀረቱና የቤሔር ፖለቲካን ማስፈኑ፡፡ እንግዲህ ገብሩ ያወደሱት ፌደራሊዝም ጎሰኝነትን መሠረት ያደረገውን አገሪቱን መከፋፈል ነው፡፡ እዚህ ላይ በየትኛውም አመክኒዮ ገብሩ ሚዛን የሚደፋ ማሳመኛ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ፌደራሊዝም እንደ ፌደራሊዝምነቱ በጎ ነገር ሊኖረው ይችላል፡፡ የኢትዮጵያው አይነት ፌደራሊዝም ግን ዛሬ የአገር ስሜቱ የደበዘዘና በጎሰኝነት ጉሮኖ ውስጥ ራሱን የከረቸመ ትውልድ እንዲያፈራ ከማድረጉም በላይ የአስተዳደራዊ ምቹነት የሌለው ነው፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ መዋቅር ፌደራላዊ ወይም ማዕከላዊ መሆኑ ብዙም ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ ምንአልባትም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትልቁን የልማት እንቅስቃሴዎች ማዕከላዊ መንግስቱ የሚያከናውንባቸው አገራት ማዕከላዊነቱ ይበልጥ ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዝ ብዙዎቹ አካባቢዎች ዕድሉ ቢሰጣቸው እንኳን የአቅም ውስንነቱ እንዳለ የማይካድ ነው፡፡ እውነታውም ይሄንን ያሳያል፡፡ ሕዝብ ፍትሕንና መልካም አስተዳደርን እንጂ ፌደራል ሆነ ማዕከላዊ የዛን ያህል ቁብ የሚሰጠው አይደም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይልቁንም ተማርን የሚሉት ሕዝብንና አገርን ሳይሆን በየትኛው አጋጣሚ መጠቀም እንደሚችሉ እያሰሉ ያለፍቃዳችን የሚያቀርቡልን አማራጮች ይመስሉኛል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ብሔረሰብን መሠረት ያደረገው ፌደራሊዝም ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ወደፊትም ብዙ ያስከፍለናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምንአልባትም የኢሳያስ የመቶ አመት ቤት ሥራን ለማከናወን እንጂ ለኢትዮጵያ አደጋ እንደሆነ ለመረዳት ብዙ መመራመርና መማር የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ገብሩን ተሳስተዋል እላለሁ፡፡
ሌላው ገብሩ የፌደራል ሥርዓቱን አለመተግበር ኢሕአዴግን ራሱን በራሱ እያጠፋው እንደሆነ ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ እኔን ግን ጉዳዩ አሁንም ከፌደራል ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ ያለ የጎሰኝነት እንጂ ሥርዓቱን በመተግበርና አለመተግበር የመጣ ችግር የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኢሕአዴግን የመሪው የመለስንም ብዙ ድክመቶች ገብሩ ጥሩና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ የገለጽዋቸው ቢሆንም አንድን ቁልፍ ጉዳይ በትልቅ ፌደራሊዝም ካባ ጀቡነውት አልፈዋል፡፡ የሄውም የኢሕአዴግ መንግስት ባለስልጣናት ውክልና ነው፡፡ ገብሩ እንደ ትግራይ ተወላጅነታቸው ይሄንን ጉዳይ ይፋ አድርገውት ቢሆን ምንኛ ሚዛናዊነት ባላበሳቸው ነበር፡፡ ገብሩ ወደ ፌደራሊዝም ትግበራ ድክመት የጎተቱት ዋነኛው የኢሕአዴግ መንግስት ችግር ግን ከአንድ አካባቢ በመጡ ግለሰቦች የአገሪቱን ዋሳኝ የስልጣን ቦታዎች ማስያዝ ነው፡፡ ይሄውም ከትግራይ የመጡ ምን አልባትም ከትግራይም ከተወሰነ ቦታ ብቻ የተሰባሰቡ ግለሰቦች ሁሉንም ወሳኝ የሚባ የመንግስት መዋቅር መያዛቸው አደገኛውና አሁንም በተለያየ ቦታ ለተነሳው ችግር ምክነያት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ገብሩንም ይሄ ነገር ጠፍቷቸው ወይም ዘንግተውት አይመስለኝም፡፡ የእነዚህ ባለስልጣናት ከአንድ አካባቢ መሠባሰብ ብቻም አልበቃቸውም፡፡ የሕዝብና የአገር ሐብትም እንዲሁ ከዚሁ አካባቢ ለመጡ ፍትሐዊ ባልሆነ ሁኔታ እንደሚሠጥ ይታወቃል፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ ያነሳው ተቃውሞም በግልጽ እንዲህ ላሉ ፍትሐዊነት ለጎደላቸው የሐበት ክፍፍል ነው፡፡ የተባለው እኮ መሬቱ ከእኛ እየተወሰደ ለትግራይ ተወላጆች ይሰጣል ነው፡፡ እንዲህ እንነጋገረው በሚል እንጂ እንደ እውነቱ ለእኔ የትግራይ ተወላጅ ዘመዴ እንጂ ሌላ ወገን እነዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ገብሩ ይሄንን የሚያህል ችግር ዘልለውታል፡፡ የስልጣን ውክልናውን ስናይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአገር መከላከያ፣ የአገር ደህንነትና መረጃ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ጉዳዮች እነዚህ ከሁሉም ቦታዎች ቁልፍ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የተያዙት ከትግራይ ምንአልባትም ከእንድ አካባቢ በመጡ ግለሰቦች አንደሆነ ይታያል፡፡ በላይ ባሉ መዋቅሮች ብቻም ሳይሆን በእነዚህ መዋቅሮች እስከታች ድረስ ይሄው ይንጸባረቅባቸዋል፡፡ ይሄንን መቀበልና ፍትሐዊ ማድረግ ሲቻል ስህተትም ካለ አሁን እንደሆነው አይነት ሳይሆን በቀላሉ የሚታረም ነው፡፡ የኦሮምያም በሉት የሌላው አመጽ ከፌደራሊዝም ጋር ይያያዛል ከተባለ የጎሰኝነቱ ጉዳይ ነው፡፡ የአመጹ መሠረታዊ ጥያቄዎች ግን የፍትሀዊነትና ከአንደ አካባቢ በመጡ ግለሰቦች አገሪቱ እየተመራች መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከትግራይ በመቀጠል ከኦሮምያ ምስራቅ ወለጋና አርሲ፣ ከአማራ ከሚባለው ክልል ከጎጃም የመጡ ባለስልጣናት በኢሕአዴግ መዋቅር ውስጥ በዝተው ይገኛሉ፡፡ ሌላው አካባቢ ያለው ውክልና ሊያውም ካለ መታየት የሚችል አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ራሳቸው ዋናዎቹ ለስልጣናቸው መቆየት የሄዱበት እውነት ነው፡፡ ፌደራል ወይም ማዕከላዊ መሆኑ የሚኖረው ፋይዳ እምብዛም አይደለም ባይ ነኝ፡፡ ያነሳሁት ከአንድ አካባቢ በመጡ ባለስልጣናት አገር እንድትመራና ወሳኝ መዋቀሮቿም መያዝ አደጋ የጋበዘው እሱ ነው ባይ ነኝ፡፡ ከኦሮምያ ሰው ጠፍቶ ነው ወይስ ከሌላ ክልል፡፡ ሌላ ቀርቶ አሁን የሉት የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ወሳኝ ሚና ቢኖራቸው የኦሮምያ ሕዝብ አሁን የምናየውን ተቃውሞ ያደርጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሕዝቡ እኮ ክልሉን በሚመሩትም አያምነም፡፡ ምክነያቱም እነሱም ተገዥና ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ወሳኝ አይደሉም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ማዕከላዊ ውክልናውን ሕዝቡ ይፈልገዋል፡፡ ስለዚህ ገብሩን በብዙ መልኩ ወድጃቸው ይሄንን ነገር ስለዘለሉት ቅር ብሎኛል፡፡ ደግሜ እላለሁ እነድ ትግራይ ተወላጅነታቸው እሳቸው ይህንን ቢተቹት ምንኛ ባማረ፡፡
ከዚህ በተረፈ ኢሕአዴግ የሠራቸው ልማቶች እውነትም ለውጥ ያመጡ መሆናቸው የማይካድ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ከዋጋቸው በላይ አገሪቱን ዋጋ እየጠየቁ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ሜትር መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት የሚወጣው ወጭ ከሌሎች አገሮች አንጻር ሲታይ ብዙ ይበልጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲያ ባይሆን አሁን ከተሰራው ልማት ብዙ እጥፍ ማልማት በተቻለም ነበር፡፡ ይሄን ገብሩም ጠቀሰውታል፡፡ የሳቸው ያምራል ሙስና ብቻም ሳይሆን የተወሳሰብ አስተዳደራዊ ግድፈት እንደሆነ ዘረዝረውታል፡፡ ደላሎቹን በግልጽ ስላነሷቸው እኔ አልበረዘውም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢሕአዴግ ሥራዎቹ የዘመቻና ሥራውንም የሚሰራው ለአገርና ሕዝብ እንደሆነ ሳይሆን ሠራሁላችሁ ለማለት ያስመስልበታል፡፡ ትንሹን ነገር ትልቅ ሚደያ ይሰራበታል፡፡ ሕዳሴ ግድብ፣ ሕዳሴ ድልድይ ምናምን ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚያነስሱበት እንጂ እንደ ትልቅ ነገር ጠዋት ማታ የሚነገሩለት ልማቶች አይደሉም፡፡ ይልቁንስ ኢሕአዴግ ብዙ አስፋልት መንገድ እንደማሰራቱ ብዙ ስለዚህ አላወራም፡፡ የጎተራን መሳለጫ ግን እንደ ትልቅ ነገር በቴሌቨዥን ሲያሳየን ስንት እድሜአችንን ፈጀው፡፡ ምን አልባትም ብርቅ የሆነባቸው ጋዜጠኞቻችንም ይሆናሉ፡፡ ይሄንን ብዙ ጊዜም አየዋለሁና፡፡ ጋዜጠኞቻችን በቃ ነገር አለሙን ሁሉ ረስተውት መጀመሪያ መፍጠር ከዛም እሱኑ ማጋነን ልምዳቸው ነው፡፡
ሌላው እንደ ተፈጥሮአዊ ክስተቱ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ተከሰተ የተባለው ድርቅ ተጽኖ ከሥርዓቱ ችግር ጋር ይያያዛል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እዚህ ጋር ተቃዋሚዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡ እነሱም ቢሆኑ ከዚህ የተሻለ ነገር የኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢሕአዴግ የገጠሩን ልማት ለማሳካት ብዙ መጣሩ አይካድም፡፡ ይልቁንም ጥረቱ ሁሉ የዘመቻና የሆያሆዬ ስለሆነ በሚሊየን ዋጋ ያፈሰሰባቸው ፕሮጀክቶች ራሳቸው ጥቅም ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ዋናው ምክነያቱ ኢሕአዴግ በመዋቅሩ ሁሉ ይዞ ያለው የሚያወሩለትን እንጂ የሚሰሩ ሰዎችን አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ፕሮፌሰር (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የሚመሩት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ አንዱ የሌለ ቁጥር እየጠቀሰ የየተከለ ችግኝ ብዛት ያወራል፡፡ ሰውዮው ባለሙያ ከሚባሉት ነው፡፡ የሚያወራውም ለባለሙያዎች ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በጣም ተናደው ·[ እባካችሁ እንዲህ የሌለ ቁጥር እያወራን እኮ አገርንና ሕዝብን እያጠፋን ነው እዚህ እንኳን እውነቱን ማውራት ብንችል ሲሉ ሰውየው ፕሮፌሰር ምን ላድርግ ግብርናዎች እኮ እንደዚያ ነው የሚያቀርቡት የእኛ ከእነሱ ሲያነስ ደስ እይለኝም ብሉ ተሰበሳቢውን ለሳቅ ጋብዞታል፡፡ አብዛኛዎቹ የገጠሩ ልማት ፕሮጀክቶች ይሄንን ይመስላሉ፡፡ ከዚህ በላይም ነገሮች በእቅድና ትክክለኛ ስልት ተነድፎላቸው ሳይሆን የሚሰሩት በዘመቻና በኮታ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ውሃ ማቆር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሶበት ጠብ ያለ ነገር ሳይኖረው መክኖ ቀርቷል፡፡ በወቅቱ ኮታ ለመሙላት እየተባለ የማያስፈልጉ ጉድጓዶች በየቦታው ተቆፍረው በኋላ ጭራሽ የወባ መራቢያ ሆነው ትልቅ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ሆኖም ውሃ ማቆር እንደ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብዙ ቦታዎች የሚያሰፈልግ ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ የተፋሰስ ልማት በሚል የሚያስፈልገውም የማያስፈልገውም ቦታ በኮታ እርከን ሥሩ ተብሎ ብዙ ችግር ተፈጥሯል፡፡ በዚሁ ወቅት ወደ ሀረር ለሥራ ተጉዘን የሀረር ገበሬ ድሮውንም ልምዱ የሆነው እርከን እሱ በሚፈልገው መሬቱን ስለሰራ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ሁሉም በእኔ መሬት ላይ እይሰራም ስላለ ኮታውን ለመሙላት በሚል አንድ የተደላደለ መሬት የትምህርት ቤት ግብ ሲቆፍሩ ሰዎችን አግኝተን እዚህ ላይ እንዴት እርከን ትሰራላችሁ ብንላቸው፡፡ ምን እናድርግ ተገደን እንጂ ጉልበት ተርፎን መሰላችሁ አሉን፡፡ ባለሙያዎቹንም ስንጠይቅ እንደዛው ነበር መልሳቸው፡፡ በዛው ወቅት ድሬዳዋም ለጥ ያለውን ሚዳቸውን እርከን ሲሰሩለት ነበር፡፡ ምን አለ ያን ጉልበት ወደ ድንገጎ እንኳን አምጥተው ውጤት ቢኖረው፡፡ በአገሪቱ ትላልቅ የተባሉ የመስኖ ሥራዎችም ተከናውነዋል መጨረሻቸው ግን በብዙ ውስብስብ ጉዳዮች ምክነያት ወጤታማ አይደሉም፡፡ ይሄን ለማብራራት እዚህ ቦታ ስለማይበቃ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ጥረቱ ጠፍቶ ሳይሆን እንዲህ ውጤት የሌላቸው በዘመቻና በግብታዊነት አንዳንዴም የፕለቲካ ጥቅም ለማግኘት ብቻ በሚወጠኑ የልማት አሰራሮች አገሪቱ የአንድ መከር ዝናብ መዛበትን እንኳን የሚቋቋም ምርት ማምረት አልቻለችም፡፡ በእቅድና በትክክል በሚነደፉ ስልቶች ቢሰራ ግን አገሪቱ ከራሷ አልፋ ሌሎችን ለመመገብ አቅሙ አላት፡፡ እኔ እነደባለሙያም ይሄንን ለማሳካት የሚባለውን ያህል ከባድ ሆኖ አላየውም፡፡ እድሉና አጋጣሚው ከእነሙሉ ኃላፊነቱ ቢሰጥ አገሪቱ በጥቂት አመታት ውስጥ ከራሷ በላይ ብዙ ትርፍ አምራች ማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎች አሉ፡፡ እንዴት ለሚለው ለመተንተን ይህ ቦታው አይደለም፡፡ ከሌሎች አገሮች አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ተከሰተ ማለት ያዳግታል፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር አላግባብም ቢሆን ከኢትዮጵያው ድርቅ ጋር ለንጽጽር ያነሷቸው የእነ ካሊፎርኒያ፣ አውስትራሊያ፣ እስራኤል የመሳሰሉት ድርቆች አያድርግብን እንጂ እጅግ የከፉ ናቸው፡፡ ተጽኖአቸው ግን የሰውን ሕይወት አያስከፍልም፡፡ ይልቁንም እነዚህ አገራት ትርፍ አምራችና፣ ከዛም በላይ የተመረጠ ምርት ለአለም ገበያ የሚያቀረቡ ናቸው፡፡ የእኛው ግን ችግር ችግርን ለመፍታት የታቀደ ሥራን አለመሥራት ነው፡፡ በዚህ ኢህአዴግን ብቻውን ልወቅስ አልፈልግም፡፡ ሌላውም ቢመጣ የተሻለ ነገር ይሆረዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኛ ስለድርቅና ረሀብ ብዙ ጊዜ አወራን ሌሎች አንዴ ተከሰተባቸው ከዚያ በቁጭት እስከመጨረሻው አሸነፉት፡፡ አሊያማ ጥንት ሕንድን የመታ ድርቅ ዛሬም በሕንድ እኮ አለ፡፡ ሌላውም አገር ድርቁ ወቅቱን እየጠበቀ ይከሰታል፡፡ እንደእኛ ግን ለረሀብና ሞት አይዳርግም፡፡ ይህን እድል በሙያው ለሰለጠኑ ባለሙያዎች ከነሙሉ ኃላፊነቱ ቢሰጥ የኢትዮጵያ አይነቱ ድርቅ መቼም ቢሆን አግሪቱን ሊፈታተናት በማይችል መልኩ ማስወገድ እንደሚቻል አምናለሁ፡፡
በመጨረሻም ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ ብዙ የአገርና የሕዝብ ጎዳዮችን እያነሳ ምሁራኑንና የሚመለከታቸውን በመጠየቁ ብዙ ያላወቅናቸውን ጉዳዮች እንድናውቃቸውና ወደፊትም ምን መሆን እንዳለበት ማሰብ እንድንችል ጥሩ ግንዛቤ ፈጥሮልናል፡፡ አሁንም ካሳሁንን አንድ ነገር እንዲህ በተከታታይ እንዲያደርገው እመኛለሁ፡፡ እስካሁን በብዛት ትኩረቱ የታለፈባቸው ታሪካዊ ኩነታት ላይ ነበር፡፡ አሁን ካሳሁንን የምጠይቀው ታሪካዊ ኩነታቶቹ እንደመነሻ ሆነው ብዙ ትኩረት ወደፊት መፍትሄ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ እንደሁ ምሁራኖችንና የሚመለከታቸውን በመጋበዝ ሌላ ግንዛቤ መፍጠር እንዲያስችለን ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይሄን እርስ በእርስ የሚያሻኩት ጥላቻ የበዛበት፣ ብሔራዊ ስሜት የደበዘዘበት፣ የግል ጥቅም የጎላበት ፖለቲካ ተወግዶ ዜጎች ሁሉ አገሬ የሚሏትን ኢትዮጵያን ወደመገንባት የሚወስዱንን የአገርና ሕዝብን አንኳር ጉዳዮችን የሚዳስሱ ውይይቶችን ቢያዘጋጅልን ተጽኖ ፈጣሪ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሁሉም ሥርዓቶች ድክመትም በጎም ነገር አይተናል፡፡ ካሳሁን እጅግ ጠቃሚ የሚሆኑ ድምጾችን አሰምቶናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዝ ካሳሁንን የምጠይቀው ቢቻል የፖለቲካ ድርጅቶችን ለመካሰስ ሳይሆን መወቃቀስ የሚያስችሉ፣ ትንታኔና የየረሳቸውን ፍልስፍና ሳይሆን ሁሉም በአንድ የአገርና ሕዝብን ጉዳይ ሊነጋገሩባቸው የሚችሉ መድረኮችን ብትፈጥር እላለሁ፡፡ ለዚህ ቃለ መጠይቅ ያደረክላቸው እንደ ኤፍሬም ይሳቅ የመሳሰሉ ሰዎች በፖለቲካ ባላንጣዎቹ መካከል ሆነው ሊያግዙህ ይችላሉ ይሚል እምነት አለኝ፡፡ በድጋሜ ካሳሁንና ባልደረቦቹ እያደረጉ ስላለው አስተዋፅኦ እያመሰገንሁ ይበል ወደፊትም በርቱ እላለሁ፡፡
ሁላችንም የአገርና ሕዝብ ጉዳይ ይቆጨን ሁላችንም አጥፍተናል አውቀንም ሳናውቅም በጥፋታችንም እነኳን ያበረከትነው አለ፡፡ አንዱ በሌላው ጣት መቀሰሩ ይብቃ፡፡ አንዱ የሰራውን በጎ ነገር ሌላው አያውድመው፡፡ የሰራውን በማመስገን ያልሰራውን ለመሙላት ይሁን፡፡ ሁላችንም እኛው ነን፡፡ ያጠፋንም እኛ የጠፋንም እኛ… እኛው ነን ጌትነት እንየው በትክክል ገልጾታል፡፡
እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ! አሜን!
ሰርጸ ደስታ