Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ህወሃት በኦሮሚያ ላፈሰሰው ደም 2.4 ቢሊዮን ብር ጉቦ ሰጠ

$
0
0

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ህወሃት) በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ሰላማዊ ተቃውሞ ተከትሎ ላፈሰሰው ደም 2.4 ቢሊዮን ብር ጉቦ በኦህዴድ አማካይነት መስጠቱ ይፋ ሆነ። ገንዘቡ የኦሮሚያ ሥራ አጥ ወጣቶችን ባለሃብት እንደሚያደርግ ሲገለጽ፣ ስራ አጥቶ ግብርና የተመለሰው ኢንጂነር በዳዳ ጋልቻ በህወሃት አንጋቾች የእርሻ ስራውን ጨርሶ ሲመለስ በጥይት ተደብድቦ ተገድሏል።

በዳዳ ገልቻ ማን ነው? ምን ደረሰበት?

በዳዳ እስከ አለፈው ማክሰኞ ድረስ ጉጂ ዞን፣ አዶ ሻኪሶ ወረዳ፣ መጋደር መንደር ነዋሪ ነበር። በምህንድስና ትምህርት ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ስራ ማግኘት ተሳነው። ስራ ፈለጋ ሲታከተው ትውልድ መንደሩ ተመለሶ በራሱ ስራ ፈጥሮ ለመስራት ጥያቄ አቀረበ። ያካባቢው አስተዳደር ጥያቄውን በውል ባልተገለጸ ምክንያት ውድቅ አደረገበት። ዲግሪውንና የስራ እቀዱን ወደ ጎን ትቶ ሙሉ በሙሉ ግብርና ላይ ተሰማራ።

ባለፈው ማክሰኞ ማሳው ላይ ደቦ ነበረው። ለደቦ ከጠራቸው ጋር ሆኖ ሲሰራ ዋለ። ደቦው ተጠናቆ ከማሳው ሲወጡ አወል የተባለ ሰው ወዴት እንደሚሄድ ጠየቀው። እሱም ወደቤት እንደሚሄድ ነገረው። ከዚያም ይህ ሰው ብርሃኑ ከሚባል ደህንነት ጋር ሆኖ መንገድ ላይ ጠበቁት። አጋዚዎችም አብረው ነበሩ። ከበዳዳ ጋር የነበሩት ሰዎች ሲደናገጡ “እናንተን አንነካም። የምንፈልገው ሰው አለ” በማለት በዳዳን “ቁም” አሉትና በጥይት ደበደቡት። ያካባቢው ህብረተሰብ ተኩስ ስምቶ ተሰበሰበ። ደጋገመው በመተኮስ የተሰበሰበውን ህዝብ አጋዚዎች በተኑት። ከዚያም ታርጋ በሌለው መኪና ጭነው አዶላ ሆዬ ሆስፒታል ወሰዱት።

ሆሰፒታል ከደረሰ በኋላ በዚያው ቀን ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ ህይወቱ አለፈ። በዳዳ ኢህአዴግ 100 እጅ አሸነፍኩ ባለበት ምርጫ ኦፌኮን የወከለ እጩ ተወዳዳሪ ነበር። እሱ በተገደለበት ቀን ተቃውሞ አልነበረም። ከወር በፊት የሼኽ መሐመድ ሁሴን አልሙዲ የአኮቴ የወርቅ ፕሮጀክትንና የማስተር ፕላኑን በመቃወም ተካሂዶ የነበረውን ሰልፍ አስተባብሯል በሚል ግን ይጠረጠር ነበር። ቪኦኤ ዳንኤል ቦሩ እና ጋሪ ሱኔ የተባሉ የአይን ምስክሮችን ጠቀሶ አርብ ምሽት ካቀረበው የተወሰደ።

“የተቃውሞው ዋና መንስኤ ስራ አጥነት ነው” ኦህዴድ

የበዳዳን መገደል በጉያው አድርጎ የኦሮሚያን ሥራአጥ ወጣቶች ባለሃብት የሚያደርግ አስቸኳይ ፕሮጀክት መነደፉን ይፋ ያደረገው ኦህዴድ ፕሮጀከቱ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ብሏል። ሪፖርተር የጠቀሳቸው የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ 832 ሺህ ስራ አጦች “የዕድሉ ተጠቃሚ” ይሆናሉ ብለዋል።

ሰላማዊ ጥያቄ በማንሳታቸው በህወሃት ታጣቂዎች ወንድምና እህቶቻቸው የተሰዉባቸው ሥራአጥ የኦሮሚያ ወጣቶች ንጹህ ውሃ ማምረት ይጀምራሉ። የምግብ ማዘጋጃ ፋብሪካ ባለቤት ይሆናሉ። ማዕድን ማምረት ይጀምራሉ። ሪፖርተር እንዳለው ሥራአጥ የነበሩት የኦሮሚያ ወጣቶች “ባለሃብቶች” ይሆናሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ዋና ቁልፍ ችግር ሥራአጥነት መሆኑ በመታወቁ ነው።

ህወሃት ለኦህዴድ ጉቦ?

የኦሮሚያን ሥራአጥ ወጣቶች ባለሃብት የማድረግ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን አስመልክቶ የጎልጉል የአዲስ አበባ መረጃ አቀባይ ወሊሶ፣ ነቀምት፣ አዳማ፣ አለለቱና አርሲ ኮፈሌ የሚገኙ ነዋሪዎችን ትዝብት የማግኘት እድሉ አጋጥሞት እንደነበር ያወሳል። ከ800 በላይ የተለያዩ አመራሮችን ከሃላፊነት ዝቅ ያደረገውና ያሰናበተው ኦህዴድ አሁን ያስቀራቸው ሃይሎች ለህወሃት ታማኝ የሆኑት ብቻ መሆናቸው በስፋት እንደሚነገር ይገልጻል።

አሁን ከህወሃት ጋር የሚቀጥለው የኦህዴድ ታማኝ ክፍል የህዝብ፣ በተለይም የወጣቱን ታማኝነት ለማግኘት ይችል ዘንድ ትግራይ ውስጥ በከፊል ተግባራዊ ተደርጎ የኖረውን አሠራር ተግባራዊ እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል። ህወሃት በክልሉ ሃብታም ያደረጋቸው ታማኝ ወዳጆቹ እንደሚንከባከቡት ሁሉ ኦህዴድም እንደአቅሚቲ ባለሃብት ወጣቶችን እንዲያፈራ ተመከሯል። 2.4 ቢሊዮን ብርም ተመድቦለታል። ፕሮጀከቱ ለቀጣዩ ምርጫ ሩጫም ጭምር እንደሆነም ይተቻል።

የ2.4 ቢሊዮን ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን ተከትሎ “ህወሃት ለኦህዴድ የሰጠው ጉቦ ነው። የህወሃት ታጣቂዎች ላፈሰሱት ደም የተሰጠ ጉቦ ነው። በቀጣይ በወገኖቻቸው ደምና አጥንት ላይ ቆመው ብር የሚቆጥሩ ዜጎችን እናይ ይሆን?…” የሚሉ የመረሩ ተቃውሞዎች ይሰማሉ።

“ከሃጂዎችና ሆዳሞች፣ ከሃጂና ሆዳም ትውልድን ነው የሚፈጠሩት። ህወሃትን ክህደት እንደወለደው ሁሉ ከሃጂዎችን ስብስቦ እዚህ ደረሰ። አሁን ያለው ትውልድ ግንዛቤው በማደጉ ከበላው ማካፈል ግድ ሆነበት። 2.4 ቢሊዮን ብር ፈቅዶ የማካፈል ፖለቲካን ሊጀምር ወሰነ። ይህ ኢምንት ገንዘብ በኦሮሚያ ከፈሰሰው ደምና ከተፈጸመው ግፍ በላይ ገዝፎ የዜና ሚዛን ማግኘቱ ያሳዝናል። አንድ አገር የምትቆመውና ሰላሟ የሚጠበቀው ፍትህ ሲሰፍንባት ብቻ ነው። የሰው ልጆች የማይደበቁት ህሊና አላቸው” ሲሉ ከኦህዴድ አስቀድመው የተሰናበቱ አስተያየት ሰጠተዋል። ኦህዴድ የክህደት መንገዱን እስካላቆመና ኦሮሚያን አስቀድሞ እስካልሰራ ድረስ ችግሩ ሁሌም አለ። አቶ ሃይለማርያም ህዝብ ነቀቷል፤ ካሁን በኋላ በዚህ ህዝብ ጫንቃ ላይ ሆኖ እንዳሻው መጋለብ አይቻልም ሲሉ የተናገሩት ጉዳዩ በውል ገብቷቸው ከሆነ ትክክል የሚሆኑት ራሳቸውንና ሌሎችን ነጻ ባለስልጣን ሲያደርጉ ብቻ ነው – እንደ ኦህዴዱ ሰው!!


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles