(ሳተናው) ኢትዮጵያዊያኑ በህይወትና በሞት መካከል በሚገኘው ቀጭን ክር ላይ ይገኛሉ፡፡ከወዲሁ እንስሳቶች ድርቁ ያስከተለውን ርሃብ መቋቋም ተስኗቸው የሚበዙት በሞት ተሸፍነዋል፡፡
ከበላያ መንደር ስለ ሁኔታው ለአለም የምትናገረው የሚዲያ ሴንተሯ ሶፊ ኮሲንስ ‹‹በቀጣይ የምንሰማቸው ነገሮች የሰዎችን ሞት በብዛት የሚያረዱን ይሆናሉ››ብላለች፡፡
ሶፊ ከምስል ጋር በማቀናበር ባቀረበችው ልብ ሰባሪ ዜናዋ አንዲት በወጣትነት የዕድሜ ክልል የምትገኝ እናት ያቀፈችው የሶስት ዓመት ልጇ ከጡቶቿ ወተት ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ሲጎትታት ቆይቶ የፈለገውን በማጣቱ አምርሮ ሲያለቅስ ይደመጣል፡፡
የ25 ዓመቷ መስከረም ለሶፊ ‹‹ምንም ዝናብ ለረዥም ጊዜያት አላገኘንም ስለዚህም ያለ ምግብ ወደመኝታችን መሄድ ግድ ብሎናል››ብላታለች፡፡
ከአዲስ አበባ የአምስት ሰዓታት የመኪና ጉዞ በኋላ የሚደረስበት ሲሶያታ መንደር በጫካ የተሸፈነ በመሆኑ በአካባቢው ስር የሰደደ የርሃብ ወሬ የሚነገርበት ባይመስልም መስከረም‹‹የምንዘራው ዘር፣አትክልቶችና ለቆጮ የሚያገለግለን እንሰት የለንም››ብላለች፡፡
መጪው ጊዜ ካለፉት ጊዜያቶች የበለጠ እንደሚያስፈራት የምትናገረው መስከረም ‹‹ዝናቡ በጣም በቶሎ የማይመጣልን ከሆነ ለልጆቼና ለእኔ ሁኔታዎች የበለጠ አስፈሪ ይሆናሉ››ማለቷን ሶፊ ዘግባለች፡፡
በኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ አለም አቀፍ ተቋማት የ1.4 ቢልዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያሻ በመጥቀስ ጥያቄያቸውን ካቀረቡ ረዘም ያሉ ወራቶች ቢቆጠሩም የተገኘው ምላሽ ግን የተጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡የቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቼጌ ጉጌ‹‹ለጥሪው እየተሰጠ የሚገኘው ምላሽ በጣም ዘገምተኛ ነው፡፡የእኛ ቀዳሚው ተግባር የኢትዮጵያ መንግስትን በመደገፍ ህይወት ማዳን ቢሆንም ሁሉንም በመድረስ ላይ አንገኝም››ይላሉ፡፡
የአለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ ለጥሪው እየተሰጠ በሚገኘው ዘገምተኛና አነስተኛ ምላሽ የተነሳ ስጋት እንደተደቀነበት በመግለጽ ሁኔታው አስጊ መሆኑን ጠቁሟል‹‹ለወራት አስቸኳይ እርዳታ ስለማግኘት ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ነገር ግን ያገኘነው የጠየቅነውን አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው፡፡በጣም በቅርቡ መሰረታዊ የሚባል ድጋፍ ማግኘት ካልቻልን በቀጣዩ ወር የያዝነውን ምግብ ስለምንጨርስ ፕሮግራማችንን እናቆማለን››ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ፈንታሌ ደግሞ ነገሮች በጣም ተባብሰዋል፡፡ከተማይ በሞት አፋፍ ላይ የምትገኝ መሆኗን የሚጠቅሱት የእርዳታ ሰራተኞች ወንዞቹ ደርቀው የእንስሳት የወዳደቁ የሰውነት ክፍሎች አካባቢውን ሸፍነውትና መሬቱ ተሰነጣጥቆ ከመሬት የሚነሳው ነጭ አቧራ ሞትን ተሸክሞ የተነሳ ይመስል እንደሚያስፈራ ያወሳሉ፡፡
በፈንታሌ በሚገኘው የቻይልድፈንድ ቢሮ የሚሰራው ኢዮኤል ለማ ሁኔታውን ሲገልጽ ‹‹ወንዙ ደርቋል፣እንስሳት ሞተዋል ለእርሻ የሚሆንም ምንም ነገር የለም፡፡እርዳታ እየተደረገ ቢሆንም ሁኔታው ከቀን ወደቀን እየተባባሰ ይገኛል››ብሏል፡፡