የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የባለስልጣናት ሌብነትና ድርጅታዊ ዝርፊያ፣ የማንነት ጥያቄ፣ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ አድሏዊ አመለካከት፣ የሰብአዊ መብት አለመከበር፣ የማሰብ፣ የመቃወም፣ የመናገርና የመጻፍ ተፈጥሮአዊ መብቶች መጣስ፣ የዲሞክራሲ መብቶች አለመከበር የፈጠረው ስሜት ተጠራቅሞ እየገነፈለ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የተነከረችበት ከፍተኛ እዳና የተከሰተው ችጋር አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ እንዳያመራት ስጋት አይሏል።
ባለፉት ስድስት ወራቶች ሰላማዊ ጥያቄ ያነሱ ዜጎች በጥይት ተደብድበው ሞተዋል። በዚሁ ሳቢያ ኦሮሚያ በእምባ ነፍራለች። ህጻናትና እናቶች በህወሃት ልዩ ታማኝ ኃይሎች ተገድለዋል። የታሰሩ ዜጎች ቁጥር በሺህ የሚቆጠር ነው። የት እንደ ደረሱ የማይታወቁ ወገኖች ስለመበራከታቸው ቤተሰቦች ስምና አድራሻ ሳይደብቁ እየተናገሩ ነው። አማራ ክልል “በግድ ትግሬ መሆን በቃን” በሚል ጥያቄ ያቀረቡ ወገኖች ታስረዋል፤ ተገርፈዋል፤ የሞቱም አሉ። በተወለዱበት ቀዬ መኖር ተስኗቸው የተሰደዱና ዱር ቤቴ ያሉ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። ይህንኑ ተከተሎ ያኮረፉና የተበሳጩትን ቤት ይቁጠራቸው። በደቡብ ክልልም በተመሳሳይ ችግሩ የተወሳሰበ መሆኑንን ከስፍራው የሚወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ።
ይህ ሁሉ የተቆለለ ችግር ሳያንስ ሲሸፋፈን ቆይቶ የተገለጠው ረሃብ በተለይም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ለሶሰት ተከታታይ ዓመታት የከረመ ድምር እና የክሽፈት ውጤት መሆኑ ይፋ እየሆነ ነው። “መቶ በመቶ የሕዝብ ድጋፍ” አግኝቻለሁ በሚል አገሪቱን በነጻ አውጪ ስም የሚገዛው ህወሃት/ኢህአዴግ፣ ተገድዶ ያመነው ችጋር ያስከተለው ጉዳት ትክክለኛ መረጃ እስካሁን ይፋ ባይሆንም አደጋው ዘግናኝ ስለመሆኑ መከራከር በማይችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። የህወሃት ሹመኞች “ራሳችን እንወጣዋለን” ሲሉ እንዳልነበር ዛሬ የርዳታ ያለህ ጩኸት እያሰሙ ነው።
ጠኔው እየገፋ ሄዶ የአገሪቱን የህወሃት ውላጅ ሚዲያዎች በየቀኑ መንታ ምላስ ባደረገበት ባሁኑ ወቅት፣ “ነጻ” የሚባሉት የወረቀት ሚዲያዎች ጉዳቱ የደረሰበት ስፍራ ሄደው በወጉ ሽፋን አለመስጠታቸው ታሪካዊ ትዝብት ፈጥሯል።
የአውሮፓ ኮሚሽን በድረገጹ እንዳሰፈረው ከ10 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተርቧል ሲል፤ ህጻናትን አድን የተሰኘው ድርጅት ደግሞ ከ6ሚሊዮን በላይ ህጻናት በረሃብ አደጋ ላይ መሆናቸውን ይፋ ያደረጉት አሳሳቢ የተባለው ችግር አለበት ቦታ ድረስ ሄደው ካዩ በኋላ ነው።
እንደ ኮሚሽኑ አተያየት የወቅቱ የኢትዮጵያ ችጋር አምስት አንኳር እውነታዎች የሚከተሉት ናቸው፤
- በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ከተከሰቱት አስከፊው ድርቅ ነው፤
- በድርቁ በጣም በተጎዱት አካባቢዎች ከ50 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ሰብል መና ሆኗል፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ከብቶች አልቀዋል፤
- 100 ሚሊዮን ከሚጠጋው አጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ይሻሉ፤
- ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ ተፈናቅሏል፤ ከምግብ በተጨማሪ መጠለያ፣ ውሃ፣ ንጽህና አጠባበቅና የህክምና ርዳታ እጅግ አንገብጋቢ የሚባሉት ናቸው፤
- የአውሮፓ ኮሚሽን ካለፈው ዓመት ጀምሮ 170 ሚሊዮን ዩሮ ለአስቸኳይ ርዳታ እጁን ዘርግቷል።
ኮሚሽኑ 125.5 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ የገባውን ስጋት ደጋግሞ ጠቁሟል።
በመከረኛው ኢል ኒኞ የሚላከከው ችጋር በሴፈቲ ኔት የታቀፉትን ወገኖች ጨምሮ 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ወገኖችን ተፈታትኗል። በተለይም ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ እረፍት የሚነሳ ሆኗል። “… አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ነው፤ አሁን ማድረግ ያለብንን ፈጥነን ካላደረግን የፈራነው እውን መሆኑ አይቀሬ ነው” ሲሉ ከጉብኝታቸው በኋላ ስጋታቸውን ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የተናገሩት የህጻናት አድን ዋና ኃላፊ ናቸው።
በቅርቡ የምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚክስ) ፕሮፌሰር የሆኑት አለማየሁ ገዳ ይፋ ባደረጉት ጥናታቸው አገሪቱ ከሰላሳ ቢሊዮን ዶላር በላይ እዳ ይጮህባታል። የብድሩ መብዛት ብቻ ሳይሆን አከፋፈሉ እንዲሁም የገቢና የወጪ ንግዱ አለመጣጣም መጪውን ጊዜ አሳሳቢ እንደሚያደርገው አሰገንዘበዋል።
በሌላ በኩል ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ ባወጣው ሪፖርት በ2009 ብቻ ከኢትዮጵያ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተዘርፎ ካገር እንዲወጣ ተደርጓል። ሪፖርቱ እንዳለው በድምሩ ባለፉት ሰባት አመታት ከአገሪቱ ተዘርፎ ወደ ውጭ የወጣው ገንዘብ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ስለመሆኑ ምስክርነቱን መስጠቱ የሚያስታውሱ ወገኖች የተዘረፈውን ዶላር “ይህ ብር ምን ያህል ሰፋፊ የእርሻ ልማት ይገነባበት ነበር” ሲሉ ይጠይቃሉ። በገፍ የተወሰደውን ብድር አስመልክቶ “በሌብነትና በከሸፈ ፖሊሲ ላይ የተበተነ ያገሪቱ የመጪው ትውልድ ቁልል እዳ” ይሉታል። አቶ መለስ አፈር ሳይውጣቸው “መሃይምም ቢሆን የድርጅታችንን ዓላማ እስከተቀበለ ድረስ…” በማለት ራሳቸውን ለማግዘፍ ዙሪያቸውን የዕውቀት ድርቅ ባጠቃቸው በመክበብ ሹመት እየሰጡ ሚኒስትር ማድረጋቸው አሁን እየተከሰተ ላለው ክሽፈት በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ለበርካታ ጊዜያት የሚላስ የሚቀመስ በማጣት የራሳቸውን ሥጋ “እየበሉ” ሲኖሩ የቆዩ ወገኖች መሞት የሚጀምሩት ከወራት በፊት እንደሆነ በኢትዮጵያ ችጋር ላይ ከበቂ በላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ይናገራሉ። ተፈጥሮ ፊቷን በምታዞርበት ጊዜ በችጋር አፋፍ ላይ የሚገኙት ገበሬዎች ወደችጋሩ ገደል መግባት ይጀምራሉ የሚሉት ፕ/ር መስፍን “ችጋር ሕዝብን በጅምላ የሚጨፈጭፍበት ጊዜ ከስድስት እስከ ስምንት ወራት ይፈጃል” ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ በተመለከተ የሚያስከትለውን አስከፊ ሁኔታ ሲያስረዱም “ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ተከሰተ የተባለው ድርቅ ሰዎችን በችጋር መረፍረፍ የሚጀምረው በሚያዝያና በመጋቢት ነው፤ ገበሬዎቹ ከአሁን ጀምሮ እስከ መጋቢት ምንም ሰፊና ትልቅ ዘላቂ እርዳታ ካላገኙ በመጋቢትና በሚያዝያ ሰው እንደቅጠል የሚረግፍበት ጊዜ ይሆናል” በማለት “ስለ ችጋር” በሚል ርዕስ በኅዳር 2008ዓም ባስነበቡት ጦማር ትንታኔ ሰጥተው ነበር።
በነጻ አውጪ ስም ላለፉት 25ዓመታት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ህወሃት “አገር የመምራት ብቃት ፈጽሞውኑ” የሌላቸው ግለሰቦች ስብስብ መሆኑን አስቀድመው እንደተናገሩት እንደ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ የህወሃት/ኢህአዴግ ሰዎች ይህንኑ ትንቢታዊ ንግግር ከ25ዓመታት በኋላ በማያሻማ መልኩ ዕውን አድርገውታል፡፡ ሕዝብ ወድዶን መቶ በመቶ ተመርጠናል ከማለት ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በድርብ አኃዝ እያደገ ዓለምን አስደምሟል በማለት ህወሃት የዕውቀት ጠር በሆኑት ሹሞቹ ሕዝብን ሊያሳምን የጣረው ሁሉ አልሠራ ብሎት ምዕራባውያንን “ብትረዱን ይሻላችኋል” በማለት ትዕዛዛዊ ማስፈራሪያ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ምርጫን መቶ በመቶ አሸነፍኩ፤ ሕዝብ ይወደኛል፤ … ለማስባል ተሸፋፍኖ የከረመው የዓመታት ችጋር አሁን ያለበት ሁኔታ ከሚገመተው በላይ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ በጠኔ ተጠብሰው ከሞት ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡት ወገኖች የመጨረሻውን እስትንፋስ ላለመተንፈስ እየተገዳደሩ ቢሆንም ቀን የከዳቸው ይመስላል፡፡ ሕጻናት ያለ አሳዳጊ፣ ወላጆች ያለ ጧሪ የሚቀሩበት ጊዜ ጀምሯል፡፡ የበርካታ ትውልድ የወደፊት ተስፋ ጽልመት ጋርዶታ፣ የሕይወት መስመር ተቋርጦ አለመኖር በመኖር ላይ እየነገሠ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ አልፎ ለመኖር የሚበቃው ወገን የተስቦ ወረሽኝ ገና ይጠብቀዋል – ድርብ ድርብርብ ክሽፈት! (ፎቶዎቹ ከኢንተርኔት የተገኙ ናቸው)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>