Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የግዕዝ ፊደል የዩናይትድ ስቴትስ የባለቤትነት መብት አገኘ

$
0
0

Geezedit. ግዕዝኤዲት

ዋና መሥሪያ ቤቱ ብራይተን ኮሎራዶ የሆነው የኢትዮጵያ ኮምፕዩተሮችና ሶፍትዌር ቁጥሩ ዘጠኝ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ኃምሳ ሰባት የሆነ የዩናይትድ ስቴትስ የባለቤትነት መታወቂያ (ፓተንት) መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. (አፕሪል 7 ቀን 2016 እ.ኤ.አ.) ማግኘቱን አስታወቀ። ፓተንቱ የተሰጠው ለፈጠራውና የኩባንያው ባለቤት ለዶ/ር አበራ ሞላ ሲሆን፤ ኩባንያው የእርሳቸውንና የባለቤታቸው የወ/ሮ ሠናይት ከተማ ነው።


“አብሻ” ሥርዓት በመባል በታወቀው አዲስ ዘዴ፤ መጀመሪያ መርገጫ ላይ ያሉት ቀለሞች የሚከተቡት እያንዳንዳቸው በአንድ መርገጫ ሲሆን፣ ሌሎቹ በሁለት መርገጫዎች ብቻ ነው። ይህ ኮምፕዩተሮች፣ የእጅ ስልኮችና ተመሳሳይ መሣሪያዎች ውስጥ የእንግሊዝኛ ፊደላት ከሚከተቡበት አንዳንድ ዘዴዎች ጋር የተቀራረበ ነው። በተጨማሪም ቁጥሩ 20090179778 የሆነውን የፈጠራውን ገለጻ የአሜሪካ መንግሥት ከአተመበት ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. ወዲህ የዶክተሩን ጽሑፍ የጠቀሱ ስድስት አዳዲስ የአሜሪካ ፓተንቶች ለሌሎች ተሰጥተዋል።

የእነዚሁ (Ethiopic Character Entry) የባለቤትነት መታወቂያ ቁጥሩ ET/P/2009/111 የሆነ ከኢትዮጵያ ለዶክተር አበራ ሞላ እንደሚሰጥ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. (September 9, 2015) ለጠበቃዎቻቸው ተጽፏል።

ግዕዝ ከዓለም ጥንታዊ ፊደላት አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ከሺ ዘመናት በላይ ተጠቅመውበታል። የማተሚያ መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ በ፲፱፻፬ ዓ.ም. ገደማ እስከገባበት ድረስ ፊደሉ የሚከተበው በእጅ ጽሑፍ ብቻ ነበር። በኮምፕዩተር ቴክኖሎጂ መፈጠር የተነሳ፤ ዶ/ር አበራ የግዕዝን ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፕዩተራይዝ ሲያደርጉ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች እንዲከተብ በ፲፱፻፹ ዓ.ም. አቅርበው በግዕዝ ፊደል በኮምፕዩተር መጠቀም በግዙፍ ተስፋፍቷል። ከእዚያም ወዲህ ብዛቱ ወደ ፭፻ የሚጠጋው የግዕዝ ቀለም እያንዳንዱ የራሱ ቁጥር እንዲኖረው ለተቋቋመ ዩኒኮድ (Unicode) የሚባል ድርጅት ቀርቦ፤ በዓለም ደረጃ ዕውቅና አግኝቷል። ትክክለኛዎቹና ሁሉም የግዕዝ ቀለሞች የዩኒኮድ መደብ ውስጥ እንዲገቡ ዶክተሩ ትልቅ አስተዋጽዖም አድርገዋል። 

አስቸጋሪ ሆኖ የቆየው ግን በኮምፕዩተር መርገጫዎች ቍጥር ማነስ የተነሳ ቀለሞቹን ከሁለት መርገጫዎች በአነሰ በኮምፕዩተር የመክተብ ከባድነት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች የሚከተቡበትን እናሻሽላለን ብለው ሌሎች ከአቀረቧቸው ዘዴዎች መካከል በማውስ ቀስት መልቀም፣ አንዳንዶቹን ቀለሞች ከሦስት እስከ ስምንት መርገጫዎችን በመጠቀም ለመክተብ መዘጋጀት፣ ባዶ ስፍራ ቃል መካከል መጨመር፣ የግዕዝን ፊደል በላቲን ፊደል አጻጻፍ ለመክተብ ስፔሊንግ መማር፣ የማይጽፏቸው ቃላት መኖርና ፊደል መቀነስ ይገኙበታል። አዲሱ ፈጠራ ኢትዮጵያውያንን ከእነዚህ ችግሮችና በአድልዎ ከመከፋፈልና መዳከምም አላቋል። በፓተንት ማመልከቻው እንደተጠቀሰው የፈጠራው አስፈላጊነት ግዕዝን በቀላሉና በቀለጠፈ ዘዴ መክተብ የሚያስችል ዘዴ ስለአልነበረ ነው።

የአማርኛ ቀለሞችን በብዙ መርገጫዎች መክተብ የተጀመረው እንግሊዝኛ ለቃላቱ የሚጠቀምበትን የስፔሊንግ ዘዴ ለአማርኛ ፊደል መክተቢያ እንዲሆን አንዳንዶቹ ስለፈለጉና ስለአልተሳካም ነው። እንግሊዝኛ ቃላትን እንጂ ቀለሞቹን በስፔሊንግ አይከትብም። ግዕዝ ድምጻዊ ፊደል ስለሆነና እንደ እንግሊዝኛው ዓይነት የስፔሊንግ ችግር ስለሌለው ተገልጋዩ አሠራሩን በግሉ ተምሮ መጠቀም ይችላል። ፈጠራው ቀላልና ትክክለኛ ስለሆነ መረዳት ከአለማስቸገሩም ሌላ፤ አማርኛ በብዛት የሚጠቀምባቸው ሳድሳን ቀለማት የሚከተቡት በአንድ መርገጫ ነው። በእዚህ አዲስ የፈጠራ ግኝት የተነሳ አንድን ሃሳብ በአማርኛ ወይም ሌሎች የግዕዝ ፊደል ተጠቃሚ ቋንቋዎች በቀላሉ ማቅረብ ተችሏል። ምክንያቱም የአብሻ ሥርዓት ኮምፕዩተር ለእንግሊዝኛ ቀለሞች ከሰጠው ኃይል የበለጠና የረቀቀ በመሆኑ፤ ግዕዝ አዲስ ኃይል ስለአገኘ ነው።

የመርገጫዎቹ ቁልፎች አመዳደብ የተመረኰዘው የእንግሊዝኛው ላይ ስለሆነ የግዕዝ ተጠቃሚው አከታተብ በቀላሉ በመማር ከአንድ ገበታ መክተብ ይችላል። ግዕዙን በአንድና ሁለት መርገጫዎች በግዕዝ ፊደል የመክተብ አስፈላጊነት የግዕዝና ላቲን አከታተቦች ግንኙነት ስለሌላቸው ነው። ስለዚህ ማንኛውንም የግዕዝ ቀለም በሦስት መርገጫዎች መክተብ ጊዜና ጉልበት ማባከን ነው። የተሳሳቱ አከታተቦችና ቀለሞች መጠቀም ተለምደው መቸገርና ማስቸገርንም ያስቀራል። የግዕዝና የላቲን ፊደሎችን ቀላቅሎ መሥራትና መፈለግ ይቻላል። የእንግሊዝኛው የጽሕፈት መሣሪያና ኮምፕዩተር ብዙ ፓተንቶች ሲኖሩት፤ ይህ ፓተንት ለግዕዝ ፊደል የመጀመሪያው ነው።

በግዕዝ ፊደል በየራሳቸውና በሚጋሯቸው ቀለሞች ከሚከተቡ ቋንቋዎች መካከል ቢለን፣ ቤንች፣ ሙርሲ፣ ምኢን፣ ሱሪ፣ ቅማንት፣ ቋራ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ግዕዝ፣ ካይላ፣ ኩንፈል፣ አውንጂ፣ ኦሮሚፋ፣ አማርኛ እና ጫምታንግ ይገኙበታል።

ዶ/ር አበራ ለግዕዝ ፊደል ፈር-ቀዳጅ ተመራማሪ ብቻ ሳይሆኑ፤ ለግዕዝ አስፈላጊ ናቸው ብለው ከሠሯቸው አዳዲስ ቀለሞች መካከል የግዕዝ አልቦ፣ ብር፣ ሣንቲም፣ መብት፣ ንግድ፣ የተመዝግቧል፣ ማጥበቂያና ሌሎች ምልክቶች አሉ። የኮምፕዩተሩን የላቲን ምልክቶች ለግዕዝ ጥቅም አውለውና ከተዘርዘሩት ቋንቋዎች ቀለሞች ጥቅም አልፈው መርገጫዎቹ ተርፈዋል። የዶክተሩ የግዕዝ ፊደል ተመጣጣኝ የሆነ የራሱ የእንግሊዝኛ ፊደልን ያካትታል።

ፓተንት እየተጠበቀ ነው በሚል ማስጠንቀቂያ ኩባንያው ከግዕዝኤዲት ዶት ኮም (http://www.geezedit.com) ድረገጽ ግዕዝኤዲት ክፍል ሁለትን ለጥቂት ዓመታት ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል። ኢንተርኔት ላይ ነፃ የአማርኛ መክተቢያ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ ለዊንዶውስና ማክ ኮምፕዩተሮች አቅርቧል። (http://freetyping.geezedit.com) በ፳፻፮ ዓ.ም. አፕል የአይኦኤስ 8 ሥርዓቱን በመክፈት ሌሎች መክተቢያዎቻቸውንና ፊደሎቻቸውን እንዲያስገቡ ስለፈቀደ ኩባንያው የግዕዝኤዲትን (GeezEdit App) ቁስ (አፕ) ለአይፎን 6 እና አይፓድ አቅርቧል። የአይፎን 4 ኤስ እና 5 ሥርዓት ወደ አይኦኤስ 8 ከተሻሻለ በግዕዝኤዲት ቁስ መሥራት ይቻላል። ቁሱ የአማርኛ ቀለሞችን በአንድና ሁለት መርገጫዎች እንደሚከትበው ዓይነት የሌሎች ቋንቋዎች መክተቢያዎችም ወደፊት ይከፈታሉ። ነፃው ግዕዝኤዲት፣ ለዊንዶውስ የሚሸጠውና ግዕዝኤዲት ቁስ ሦስቱም የሚከተቡት በፓተንትና እየተጠበቁ በአሉ ፓተንቶች በተጠበቁ የአከታተብ ዘዴዎች ነው።

ቁሱ ከሚያስከትብባቸው ፕሮግራሞች መካከል ቴክስት፣ ኢ.ሜይል፣ ሜሴጅስ፣ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኖትስ፣ ማይክሮሶፍት ወርድ፣ ኦፊስ ስዊት፣ ፔጅስ፣ ጉግል፣ ያሁ፣ ቢንግ፣ ዊኪፒዲያና ዋትስአፕ ይገኙበታል። የአማርኛው ቁስ አጠቃቀሙን ከእንግሊዝኛው ሥርዓት ጋር ስለሚጋራ በሁለቱም ፊደላት መሥራት ያስችላል። የስማርት (ረቂቅ) ስልኩ በአማርኛ ቋንቋ እንዲሠራ መምረጥ ይቻላል። አማርኛ አብዛኛው ህዝብ የሚጠቀምበት የኢትዮጵያ ፊደል ሲሆን፣ ፈጠራው የአናሳ ቋንቋዎች ቀለሞች በብዙ መርገጫዎች እንዲከተቡ የሚደረገውን ግፊትና ፊደል ስለበዛ መጻፍ እንዳያስቸግሩ ይቀነሱ የሚባለውን አስተሳሰብ ሊያስቀር ይችላል። የግዕዝኤዲት ቁስ ለማግኘት እዚህ ይጫኑ! 

ግዕዝ ድምጻዊ ፊደል ስለሆነ አንድን ሃሳብ በጥቂት ቀለማትና ስፍራ በጥራት የማቅረብ ችሎታ ሲኖረው፤ ፈጠራው ተጨማሪ ኃይል ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል በፈጠራው ጥቅም የተነሳ በአማርኛ “ዘ ክዊክ ብራውን ፎክስ ጀምፕስ ኦቨር ዘ ሌይዚ ዶግ።” የሚለውን በእንግሊዝኛ “The quick brown fox jumps over the lazy dog.” እንደሚጻፈው ሁለት ገበታዎች አያስፈልጉትም። እንዲሁም “ሐመር ኋይት ሃውስ ሦስት ቋንቋ ትዕግሥት ጨካኝ” ምሳሌ 23 የአማርኛ ቀለሞች በአብሻ ሥርዓት የሚከተቡት በ32 እስከ 34 መርገጫዎች ሲሆን፣ እንደ ሌሎቹ ከ50 በላይ የአማርኛ መርገጫዎችን መጠቀም አያስፈልግም። በተጨማሪም የአማርኛውን ኃምስ “ጬ” በአራትና አምስት መርገጫዎች መክተብ የጉራጌኛ ወይም የጉሙዝ “ጬ”ዎች በእንግሊዝኛ ስፔሊንግ መክተብ እስከ ሰባትና ስምንት መርገጫዎችን መጠቀም ስለሚያስከትል፤ የአናሳ ቋንቋዎች ተጠቃሚዎች እንዳይቀየሙ ፈጠራው ይረዳል። ምክንያቱም በፈጠራው የተነሳ ማንኛውንም የግዕዝ ቀለም በአንድና ሁለት መርገጫዎች መክተብ ስለተቻለ ነው።

በላቲን አከታተብ ሥርዓት 26ቱ መርገጫዎች የተመደቡት ለእያንዳንዱ ቀለም ሲሆን፣ ለ37ቱ የግዕዝ ቀለሞችም ዶክተሩ ግዕዝን ዲጂታይዝ (Digitize) ሲያደርጉ፣ ለእያንዳንዱ ቁልፍ ተመድቦላቸዋል። ግዕዝ በላቲን 26 መርገጫዎች ካልተጻፈ ብለው ጥቂቶቹ የቁልፍ እጥረት ከፈጠሩ በኋላ ይኸንኑ ችግር የዝቅ (ሺፍት) ገበታ ላይ በመድገም ግዕዝ የማያውቀውን የስፔሊንግ ችግር መፍጠር የሚፈልጉም አሉ። ግዕዝ ኮምፕዩተራይዝ ሲደረግ ፓተንቱ አሁንም ስለአልተሰጠ የተለያዩ መክተቢያዎች ቀርበው ህዝቡ ሲበሳጭ የነበረውን አዲሶቹ ፓተንቶች እንዲያስቀሩ ማስተዋልና መጠንቀቅ አስፈላጊዎች ናቸው። የፓተንቶቹ መኖር ኢትዮጵያውያን አዳዲስ የግዕዝ ቴክኖሎጅዎችን ፈጥረው እንዲገነቡቧቸውና ፓተንቶች እንዲያገኙ የሚረዱ የጥበቡ መጀመሪያ መሠረቶች ናቸው። ይኸን ተረድቶና መከተል ከትውልዱ ይጠበቃል።

ዶክተሩ ግዕዝ በኮምፕዩተር እንዲሠራ ሲፈጥሩ ሁለት መርገጫዎችን በመጠቀም መክተብ የሚቻለው ስድስት ቀለሞችን ብቻ ሲሆን፣ አዲሱ ፈጠራ ይኸንኑ ወደ 14 ቀለሞች ከፍ አድርጎታል። ስለዚህ ቃላት ይመስል የግዕዝ ቀለሞችን በእንግሊዝኛ ፊደል ስፔሊንግ መክተብ ወይም የእንግሊዝኛ አክሰንቶች እንደሚከትቡት መንፏቀቅ አያስፈልግም። ምክንያቱም የዝቅ መርገጫን መጠቀም ሳያስፈልግ ሁሉንም የግዕዝ ቀለሞች ከአንድ ሰሌዳ ብቻ መጠቀም ስለተቻለ የምሁራን የፓተንትን ጥቅም ማወቅና ማሳወቅ የራሳቸውንና የሀገሪቱን መብቶች ለመጠበቅ ስለሚረዳ ነው። ዶክተሩ በምርምራቸው በመራቀቅ አዳዲስ ፈጠራዎቻቸውን በማቅረቡ ቀጥለውበታል። 

የዶክተሩ ሙያ እንስሳት ሕክምና ሲሆን፣ በመስኩም ትላልቅ አስተዋጽዖዎች ከማድረግ ሌላ ፓተንቶችም አሏቸው። ለተጨማሪ መረጃ ኢ.ሜይሉ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles