Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ከተማርኩት ቁጥር 2

$
0
0

አንዳንድ ጊዜ ሳስበው ምን ከምን እንደሚሰራ የማያውቅ ሰው ምንም የሚሰራ አይመስለኝም። እውነት ይሆን? አዎ!

እውነት ሳይሆን አይቀርም። እስቲ አሁን ምርጥ ሾርባ እንዴት እንደሚጠጣ እንጂ ከምንና እንዴት  እንደሚዘጋጅ የማያውቀውን የኔን ብጤ ሾርባ ስራልኝ ብትሉት ምን ይውጠዋል? ለሾርባ የሚሆን ቁሳቁስ በሙሉ በቤት ውስ ቢኖር እንኳን ሾርባ እንዴት እንደሚሰራ ካልታወቀ እዚያ ቤት ውስጥ መቼም ቢሆን ሾርባ አይኖርም። ምክንያቱም ጥሬ እቃው እንጂ ጥበቡ አልተገኘማ!

እናም እስኪ እንጠይቅ። ሀገር የሚሰራው ከምንድነው? በተለይ ታላቅ ሀገር? እንደዱሮዋ ኢትዮጵያና እንደዛሬዋ አሜሪካ ያለ ማለቴ ነው።

ባለፈው ፅሁፌ አሜሪካኖች ካካሄዱት የርእስ በርእስ ጦርነት ሰላምን፣ ፍትህንና ልማትን መፍጠራቸውን ጠቁሜ ያገሬ ሰዎችም ባለፈ የጦርነት ታሪክ መቆዘምና መራገምን ትተው ከጥፋትና ስህተታችን ልማት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ፍትህና እድገትን ይማሩ ዘንድ ምኞቴን ገልጬ ነበር። ዛሬም በዚሁ መስመር ልቀጥል።

የዛሬው ፅሁፌ ማጠንጠኛ ሃሳብ ላወቀበት ከልዩነት ሀያልነትን መፍጠር ይቻላል የሚል ነው። እናም እንግዲህ ካሜሪካኖች የተማርኩ የመሰለኝ ሌላው ቁም ነገር በልዩነት ታላቅ ሀገር መፍጠር እንደሚቻል ነው። ያሜሪካ ህዝብ ዛሬም ሆነ ዱሮ በባህል፣ በቋንቋ፣ ባስተሳሰብ፣ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በመልክ፣ ወዘተ የተለያየ ነው። ልባድርጉልኝ! ልዩነቱ በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ያለውን ያህል ልዩነት ያህል ጠባብ አይደለም። ባሜሪካ ህዝብ መካከል ያለው ልዩነት በተለያዩ ሀገር ህዝቦች መካከል ያለ ልዩነት ያህል ነው። ሰፊና ፈርጀ-ብዙ።

አሜሪካ የተመሰረተችው ባመዛኙ በሀገሬው ተወላጂ አይደለም። ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ሀገሮች በተሰባሰቡና ዥንጉርጉር ማንነት ይዘው በመጡ ያለም ህዝቦች ነው። ምናለፋችሁ አሜሪካ ያለም ህዝብ ቅጂ ማለት ናት።

ታዲያ ይህ ከነውጥንቅጥ ተፈጥሮው በዚህ ምድር የሰፈረው ህዝብ ኑሮ ሲጀምር በቋንቋ፣ በባህልና በስነልቡና በማይመስለው ሌላ ቡድን ላይ ጦርነት አልጀመረም። ቋንቋዬን ስለማትናገር የኔ አይደለህምና አትጠጋኝ አላለም። እንደየማንነታችን እንከለልም አላለም። የግዛት ክፍሉም በቋንቋ ወይም በዘር አልነበረም። እኔ እስከተረዳሁት ድረስ በዚህ ሀገር የእስፔን ክልል፣ የጀርመን ክልል፣ የኢራን ክልል፣ የኢትዮጵያ ክልል፣ የናይጄሪያ ክልል ወዘተ የሚል ግዛት የለም።

በሌላ አነጋገር በልዩነታቸው ልዩነትን አልፈጠሩም። ይልቁንም ልዩነታቸውን ሳይረሱ ትኩረታቸውን ህብረትና አብሮ መኖር ላይ አደረጉት። ምኞትና ፍላጎታቸውን አጥብበው ጠባብ ጎሬ ከመፈለግ ይልቅ የጋራ ፍላጎታቸውን የሚያረካ ሰፊ ሀገርና ስርአት መሰረቱ። እያንዳንዱን ህዝብ በየዘሩ በመለየት ለእያንዳንዱ እንደየአመሉ ተለይቶ የሚገባባቸውን ጥቃቅን ጎጆዎችን በመስራት ጊዜያቸውን አላጠፉም። ይልቁንም ለሁሉም ፍላጎት የሚመች ስርአት በመፍጠር ከየሀገሩ የመጣውን ልዩልዩ ስልጣኔ አንድ ላይ በማድረግ በለፀጉበት። ግዛታቸውንም ከምስራቅ ወደምእራብ በማስፋት የጋራ ምድራቸውን አግዝፈው አቀኑት።

እናም አሜሪካኖች ዛሬ በሀምሳ የማይነቃነቁ የብረት ምሰሶዎች በሰሩት ማማ ላይ ተቀምጠው አለምን ቁልቁል ይመለከታሉ። በልዩነት ታላቅነትን መፍጠር ማለት ይህ ነው። የልዩነት ቤት ጠባብ ነው። የህብረት ግን ሰፊ። ለእያንዳንዱ ህዝብ ደካማ ጎጆዎችን ከመቀለስ ይልቅ ለሁሉም የሚሆን ጠንካራ ቤት ሰሩ። አሁንም ልዩነታቸው በሁለት የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መካከል ያለውን ያህል የጠበበ እንዳልነበረ አስተውሉልኝ። ባባትም በናትም የማይገናኙ ያለም ህዝቦች በአንድ ምድር ተሰብስበው ያለጠብ ታላቅ ሀገር ፈጠሩ። አያስቀናም?

ይህን ስታዘብ ታዲያ ኢትዮጵያን አሰብኳት። በዘርማንዘር የማይገኙ ፍጡራን ከየማእዘኑ ተሰባስበው ግዙፍ ሀገር በመመስረት በየሄዱበት አንቱ ተብለው ሲኖሩ ወንድማማቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ልዩነቱን እያሰላ ቁልቁል ሲኳትን ስመለከት ልቤ አዘነ። አንዱ ለሌላው ባእድ የሆነው ያሜሪካ ህዝብ ድምፁ ሳይሰማ አዲስና ታላቅ ሀገር ሲገነባ ሊበጠስ በማይችል የዝምድና ገመድ የተሳሰርነው እኛ ግን ተንጫጥተን እንኳን ነባሩን ክብራችንን ለማስጠበቅ ያለመቻላችን እንቆቅልሽ ሆነብኝ።

ላሜሪካውያን ልዩነት መታደል ሆኖላቸው መታፈርንና መከበርን ሲያስገኝ ለኛ እርግማን ሆኖ ለውርደትና ሀፍረት ሊዳርገን የበቃበት ሚስጢር አልፈታልህ አለኝና ተቸገርኩ። በማይገናኝ ባህልና አስተሳሰብ አለምን የገዛ ህብረት መፍጠር መቻሉን በተጨባጭ ስመለከት ባአባትና እናቶቻችን ህብረት የተላለፈልንን ክብርና ታላቅነት መሸከም አቅቶን በመንገዳገድ በልዩነት ታናሽነትን ለመግዛት የምንማስንበት ምክንያት አልገለፅልህ ይለኛል።

በተለይ አንዳንድ ወገኖች (በብዛት ተምረናል የሚሉትን ይመለከታል) ልዩነት ታላቅነትን ሊፈጥር በሚችል ጎዳና እንዲሄድ ከመምራት ይልቅ ከውነተኛ ተፈጥሮው በላይ ተደምሮ በመስጠት መስመሩን ሲያስቱት መመልከት ረፍት ይነሳል። ነባር ታሪክ ያላትን ሀገር በጎደለው ሞልቶ በጋራ ታላቅ ለመሆን ከመድከም ይልቅ ለልዩነት የሚዘምቱበት ምክንያት የተከሰተላቸው ሰዎች ካሉ እድለኞች ናቸው። ለኔ ግን እንደአሜሪካኖች በልዩነት ከመበልፀግ ይልቅ በልዩነት መቆርቆዝ የጤና አይመስለኝም። ከህዝብ ተፈጥሯዊ ልዩነት ሀያል የሆነ ሀገራዊ ማንነት እንደሚገኝ ካላወቅን ወይም ካልፈለግን ምን እንደምንሰራ ልናውቅ አንችልም። ምን ከምን እንደሚሰራ የማያውቅ ሰው ምንም ሊሰራ አይችልምና።

እናም ወገኖቼ፣ የኔ ምኞት የኢትዮጵያን ህዝብ ልዩነት ጉልበት መሆኑን በማመን ያፍሪካ ኮከብ በነበረችው ሀገር ፍትህ በማንገስ ልጆቿ ከዳር እስከዳር ባዲስ ጉልበትና ፍቅር ተነስተው ባጭር ጊዜ ያጣችውን ክብርና ሞገስ በማስመለስ ታምር ሲሰሩ ማየት ነው። ያ ጊዜም የደረሰ ይመስለኛል።

እናየው ዘንድ እድሜውን ያድለን።

ሰላም ሁኑልኝ።

ህሩይ ደምሴ


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles