[የክቡር ሚኒስትሩ ፊት ጠቋቁሮ አማካሪያቸው አገኛቸው]
– ምነው ክቡር ሚኒስትር?
– ምነው?
– ፊትዎት ጠቋቁሯል፡፡
– ትዝ ብሎኝ ነዋ፡፡
– ምኑ ክቡር ሚኒስትር?
– ዊኬንድ ኳስ አላየህም እንዴ?
– የማንን ክቡር ሚኒስትር?
– የእነባርሳን ነዋ፡፡
– በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
– እኔማ ስቃጠል ነበር ሰሞኑን፡፡
– ለምን ክቡር ሚኒስትር?
– ባርሳ እኮ አሸናፊ ቡድን ነው፡፡
– እኔ ግን በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
– ለምንድን ነው ደስ ያለህ?
– ሁሌ አንድ ዓይነት ቡድን ሲያሸንፍ ያስጠላላ፡፡
– ከቻለ ምን ታደርገዋለህ?
– አይ ግን ያው ሁሌ ፉክክር ሲኖር ጥሩ ነው፡፡
– የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ሲባል አልሰማህም?
– ግን ክቡር ሚኒስትር ኳስ ላይ ፉክክር ከሌለ ያስጠላል፡፡
– እኔ ግን ፉክክር ያለበት ነገር ደስ አይለኝም፡፡
– ግን አንድ ነገር ልንገርዎት፡፡
– ምን?
– እስቲ የአገራችንን ፖለቲካ ይመልከቱት፡፡
– ምን ሆነ?
– ፉክክር የለበትም፡፡
– በጣም ደስ ይላላ፡፡
– ምን ደስ ይላል ያሰለቻል እንጂ?
– ምኑ ነው የሚያሰለቸው?
– ሁሌ አንድ ዓይነት ቡድን የበላይነቱን ሲወስድ፡፡
– እኛ እንግዲህ ተፎካካሪ አናመጣ፡፡
– ፅድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፡፡
– እንዴት ማለት?
– ተፎካካሪ ማስመጣቱ ቀርቶባችሁ ያሉትን ባታንኮታኩቷቸው ጥሩ ነበር፡፡
– ጥሩ ተፎካካሪ መቼ አለ?
– እናንተ እንዲኖር መቼ ትፈልጋላችሁ?
– አንተ ግን ከፀረ ልማት ኃይሎች ጋር መዋል ጀመርክ እንዴ?
– ምነው ክቡር ሚኒስትር?
– ተፎካካሪ ምናምን አበዛህ፡፡
– ያው ሁሌም አንድ ቡድን የበላይ ሲሆን ይሰለቻል ብዬ ነው፡፡
– እና ኢሕአዴግ ተሰልችቷል እያልከኝ ነው?
– እሱን እርስዎ አሉ፡፡
– እኔን ግን ያሳሰበኝ ምኑ እንደሆነ ታውቃለህ?
– ምንድን ነው ያሳሰብዎት?
– ባርሳ በመሸነፉ ብዙ ሰዎች እጅግ ደስተኞች ናቸው፡፡
– እንዳልኩዎት ሁሌም አንድ ቡድን ብቻ ሲያሸንፍ ይሰለቻል፡፡
– እንደዚህ ከሆነ የእኛን ሽንፈት በጉጉት የሚጠባበቁ ሞልተዋል ማለት ነው፡፡
– የማንን ሽንፈት?
– የኢሕአዴግን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከመሥሪያ ቤታቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጠዋል]
– ዛሬ ለምን እንደተሰበሰብን ታውቃላችሁ?
– አናውቅም፡፡
– በመሥሪያ ቤታችን ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ፡፡
– እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ለዚህ ችግር አፋጣኝ መፍትሔ ማምጣት አለብን፡፡
– ደስ ይለናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ከሰው ኃይል አስተዳደር እንጀምራለን፡፡
– እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ሰዎች የሚቀጠሩት በወንዝ ብቻ ነው፡፡
– እ…
– መሥሪያ ቤታችንን በአብዛኛው የሞሉት የአንድ ብሔር ሰዎች ናቸው፡፡
– ምን ላድርግ ክቡር ሚኒስትር?
– በአገራችን ብዙኃነትን እናሰፍናለን እያልን ይህ መደረጉ ከፍተኛ ስህተት ነው፡፡
– አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ይህ ችግርህ ደግሞ በተደጋጋሚ ተነግሮሃል፡፡
– ወድጄ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እንዴት ማለት?
– የወንዝ ነገር በአንዴ አይለቅም፡፡
– የወንዝ ነገር እንዲለቅህ ወንዝ ይዞህ ሊሄድ ይገባል ማለት ነው?
– እንደዛ ማለቴ አይደለም፡፡
– ለማንኛውም ዕርምጃ ይወሰድብሃል፡፡
– ኧረ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– በቃ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የIT ክፍል ኃላፊውን መገምገም ጀመሩ]
– የአንተ ችግር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
– ምንድን ነው ክቡር ሚኒስትር?
– ኔትወርካችን እንደማይሠራ ታውቃለህ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ኔትወርኩ መቆራረጥ አለበት ስላሉኝ እኮ ነው፡፡
– እኔ ያልኩህ የሙስና ኔትወርኩን ነው፡፡
– እ…
– በዛ ላይ መሥሪያ ቤታችን ያሉት ኮምፒዩተሮች አንድ ዓይነት ብቻ ናቸው፡፡
– ዴል ኮምፒዩተር ይገዛ ስላሉኝ ነው፡፡
– ከዴል ውጪ ግን ቶሺባ ወይም HP ለምን አይገዛም?
– እሱ ጥሩ ነው ብዬ ነው፡፡
– የለም፣ ችግርህ በብዝኃነት ስለማታምን ነው፡፡
– እንዴት ማለት?
– ከዴል ውጪ ቶሺባ ወይም HP መጠቀም አትፈልግማ፡፡
– ይኼ ከብዝኃነት ጋር ምን ያገናኘዋል?
– በደንብ ይገናኛል፡፡
– እ…
– በዛ ላይ ዴል ለምን እንደምትገዛ አውቃለሁ፡፡
– ለምንድን ነው?
– ደልደል ያለ ገንዘብ ስለምታገኝ ነዋ፡፡
– ምን አሉኝ?
– ለማንኛውም ዕርምጃ ይወሰድብሃል፡፡
– ኧረ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ይቅርታ መፍትሔ አይደለም፡፡
– ምንድን ነው መፍትሔው?
– ቅጣት!
[ክቡር ሚኒስትሩ የፋይናንስ ኃላፊውን መገምገም ጀመሩ]
– አጅሬው፡፡
– አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ዕቃ መቼ ነው በጨረታ የሚገዛው?
– ራስዎት ጨረታ ይቅር ስላሉኝ እኮ ነው፡፡
– ከእኔ ውጪ ያለጨረታ የምትገዛው ዕቃ ስንት ነው?
– እ…
– እና አንተ ሚኒስትር ነህ?
– ኧረ በምን ዕድሌ?
– ሳትሆን ማን ነው ያለጨረታ ዕቃ እንድትገዛ የፈቀደልህ?
– ስህተት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ስለዚህ አንተም ዕርምጃ ይወሰድብሃል፡፡
– ኧረ ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– የይቅርታ ጊዜ አልፏል፡፡
– እና ምን ሊያደርጉ?
– አንተ ቦታ ትቀየራለህ፡፡
– ወዴት ክቡር ሚኒስትር?
– የIT ክፍል ኃላፊ ትሆናለህ፡፡
– ኧረ እኔ ሙያውን አላውቀውም፡፡
– ሒሳብ በፒችትሪ አይደለ እንዴ የምትሠራው?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ስለዚህ የIT ክፍልን ለመምራት ቅርቡ አንተ ነህ፡፡
– ምንም ሳላውቅ ክፍሉን ልመራ?
– ስላላባረርኩህ ነው እንዴ እንደዚህ የምትጨቃጨቀው?
– እሱስ እውነትዎትን ነው፡፡ ከባድ ቅጣት ነው፡፡
– የIT ክፍል ኃላፊው ደግሞ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ ሆነሃል፡፡
– እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
– ኮምፒዩተር በአግባቡ ማስተዳደር ስላልቻልክ ሰዎችን ማስተዳደር ትጀምራለህ፡፡
– ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
– ከመባረር አይሻልም?
– ለነገሩ ልክ ብለዋል፡፡
– የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊው ደግሞ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ ሆነህ ትሠራለህ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ምንም እኮ አላውቅም፡፡
– ስለገንዘብ የማያውቅ ማን አለ?
– እ…
– የወንዝ ፖለቲካ ይዞህ ከሚሄድ…
– የገንዘብ ወንዝ ይዞኝ ይሂድ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ አንድ ከውጭ የመጣ ባለሀብት ገባ]
– ምን ልርዳህ?
– አዲስ ሐሳብ ይዤ መጥቼ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
– የምን አዲስ ሐሳብ?
– በዘመናዊ መንገድ ቤቶች የመሥራት ሐሳብ ይዤ መጥቻለሁ፡፡
– በጣም ደስ ይላል፡፡
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ ለእርስዎም በዛው ሐሳቡን ልንገርዎት ብዬ ነው፡፡
– ምንድን ነው ሐሳቡ?
– በአዲሱ ቴክኖሎጂ በርካታ ቤቶችን በቀላሉ በአንዴ መገንባት ይቻላል፡፡
– ይህማ ስንፈልገው የነበረ ነገር ነው፡፡
– የበርካታ ዜጐችን የቤት ጥያቄ መመለስ እንችላለን፡፡
– ኧረ ለመሥሪያ ቤታችን ሠራተኞች ራሱ ቤቶች ትሠራልኛለህ፡፡
– በደስታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ደወለ]
– አቤት ወዳጄ፡፡
– ሰሙ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
– ምኑን?
– አንድ የውጭ ባለሀብት አገር ውስጥ ገብቷል አሉ፡፡
– የምን ባለሀብት?
– ቤቶችን በአዲስ ቴክኖሎጂ እሠራለሁ ነው የሚለው፡፡
– እሱንማ አግኝቼው ነበር፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ሥራችንን እኮ ዜሮ ነው የሚያስገባው፡፡
– እ…
– እንደዛ ከሆነ ደግሞ የእርስዎም ጥቅም ተቋረጠ ማለት ነው፡፡
– ምን ላድርግ ታዲያ?
– ከቻሉ በአስቸኳይ ያስቁሙት፡፡
– ተወው በቃ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የውጭ ባለሀብቱ ጋ ደወሉ]
– አቤት ክቡር ሚኒስትር?
– ያመጣኸው ቴክኖሎጂ ብዙም ለአገራችን የሚሠራ አይመስለኝም፡፡
– ለምን ክቡር ሚኒስትር?
– ከባህላችን ጋር አይሄድም፡፡
– የአገሪቱ ባህል ምንድን ነው?
– የጭቃ ቤት፡፡
– እ…
– እና ፕሮጀክትህ መቋረጥ አለበት፡፡
– በዚህ ምክንያት?
– አዎ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የሚፈሩዋቸው ሌላ ሚኒስትር ደወሉ]
– ክቡር ሚኒስትር ምን እያደረጉ ነው?
– ምን አደረኩህ?
– ከውጭ የመጣውን ባለሀብት ምንድን ነው ያሉት?
– ፕሮጀክቱን እንዲያቆመው ነግሬዋለሁ፡፡
– እኮ ለምን ሲባል?
– ከባህላችን ጋር አይሄድማ፡፡
– የምን ባህል?
– ባህላችን እኮ ጭቃ ቤት ነው፡፡
– አሁንም አላቆሙም ማለት ነው፡፡
– ምን?
– ማቡካት ነዋ፡፡
– ምንድን ነው የማቦካው?
– ጭቃ!
↧
ክቡር ሚኒስትር – በጋዜጣው ሪፖርተር
↧