Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የጎሣ ዘረኝነት (ክልላዊነት) በኢትዮጵያ

$
0
0

ፕ/ር አለማየሁ ገብረማርያም (ትርጉም፣ ነጻነት ለሀገሬ)

Ethnic apartheid in Ethiopia. የጎሣ ዘረኝነት (ክልላዊነት) በኢትዮጵያ

የጸሐፊው ማስታወሻ፡- ይህ “የጎሣ ዘረኝነት/አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ መደበኛ በሆነ መልኩ እያዘጋጀሁ የማወጣው ተከታታይ ትችት ሁለተኛው ክፍል ነው። የዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ጥንድ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ) በአሁኑ ጊዜ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ–ህወሓት) አድራጊ ፈጣሪነት ተመስርቶ እየተቀነቀነ ያለው አውዳሚ የፖለቲካ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሰፊው የጥቁሮች ህዝብ የበላይ አገዛዝ ሥርዓት ከመፈጠሩ በፊት በጥቂት ነጮች የዘረኝነት የበላይ አገዛዝ ከነበረው የአፓርታይድ ዘረኛ አገዛዝ ተሞክሮ ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ከምንም ጥርጣሬ በላይ ለማመላከት እና

2ኛ) ጥልቀት እና ስፋት ያለው ክርክር እና ውይይት በማካሄድ ከጎሣ ዘረኝነት የጸዳች አዲሲቷን ኢትዮጵያ የመገንባቱን አስፈላጊነት ለመፍጠር እንዲቻል የኢትዮጵያን የአቦ ሸማኔ ወጣት ትውልድ ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ነው።


በዚህ “የጎሣ አፓርታይድ በኢትዮጵያ“ በሚል ርዕስ ተቀናብሮ በሚቀርበው ተከታታይ ጽሑፍ የፖለቲካ እና የሕግ ትንተና፣ የምሁራን እና የአካዳሚክ ሁኔታን ከመመርመር ባለፈ ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በዘ-ህወሓት አገዛዝ ስር ወድቃ በምትገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ አጠቃላይ ሁኔታ መዳሰስን ዓላማ ያደረገ ነው። በእርግጥ በዚህ ተከታታይ ጽሑፍ ዓላማ አድርጌ የተነሳሁት ለኢትዮጵያ አቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ ጥሩምባ በመንፋት እንዲህ የሚል ጥሪ ለማቅረብ ነው፡ “ኢትዮጵያ በእናንተ መዳፍ ዉስጥ ናት። ጣቶቻችሁን በማስተባባር፣ በማጠንከር እና እንደ እንቁ ኢትዮጵያን በእጃችሁ መዳፍ ላይ የማድረግ ምርጫው አላችሁ። እንደዚሁም ሁሉ የእጅ ጣቶቻችሁን በማዛል እና ጥንካሪያቸውን በማልፈስፈስ ኢትዮጵያን ከእጅ መዳፋችሁ ላይ አሽቀንጥራችሁ በመጣል እንደብርጭቆ እንክትክት ብላ እንድትሰበር የማድረግ ምርጫው በእናንተው እጅ ላይ የወደቀ ነው። እያንዳንዳችሁ እጅ ለእጅ በመያያዝ እና መዳፎቻችሁን አጠንክራችሁ በመያዝ በአንድነት የመጓዝ ምርጫው የእናንተ ነው። መዳፎቻችሁን በመጨበጥ ጠንካራ ቡጢ በመፍጠር በቁጣ እና በወኔ በመነሳሳት ሀገራችሁን ከአውዳሚ አደጋ የመጠበቅ፣ ክብሯን እና ዝናዋን የማስመለስ ምርጫው በእናንተ እጅ ላይ የወደቀ ነው። የእኔ የጥሩንባ ጥሪ ኢትዮጵያ በእጃችሁ ላይ ናት፣ ሆኖም ግን “ኢትዮጵያ ኦጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘርጋለች“ የሚል ነው።

ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ትውልድ የማቀርበው ጥያቄ፣

መጀመሪያ ባቀረብኩት ትችቴ በዓለም አቀፍ የአሸባሪዎች ስም ዝርዝር የመረጃ ቋት ውስጥ ስሙ በአሸባሪነት ተመዝግቦ በሚገኘው እና በአሁኑ ጊዜ አሸባሪ ቡድን እየተባለ በሚጠራው በዘ-ህወሓት ወሮበላ አምባገነናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ ተጭኖ የሚገኘው “የጎሣ ፌዴራሊዝም” ትርጉም ምን ማለት እንደሆነ የሚሞግት ስልታዊ እና ወሳኝ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ወጣቶች በማቅረብ ጀምሬ ነበር። በጎሣ ፌዴራሊዝም ላይ ያሉኝን የእኔን የመጀመሪያ የክርክር ጭብጦች አንጥሬ በማውጣት ለኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ በማቅረብ ወጣቱ የጎሣ ፌዴራሊዝሙን ሙሉ በሙሉ በመቃወም ወደ የታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ እንዲጥለው ተማጽዕኖ አቅርቤ ነበር።

በዚህ በአሁኑ ትችቴ ላይ ደግሞ በዘ-ህወሓት “የጎሣ ዘረኝነት” ወይም ደግሞ “ክልላዊነት” በማለት ሀገሪቱን በዘጠኝ ክልሎች ወይም ክልላዊ መንግሥታት ከፋፍሎ ባስቀመጠው ከፋፋይ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የትግል መንፈሳቸውን ለማጎልበት እንዲቻል የሕግ ማስረጃ እንዲኖራቸው በማገዝ ትግሌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ።

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ችግር የጎሰኝነት አገዛዝ ሥርዓት እንደሆነ አምናለሁ። ይህ የጎሣ አገዛዝ ሥርዓት ተጸንሶ ያደገው በዘ-ህወሓት ማህጸን ውስጥ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ውድመትን እና ጥፋትን ለማምጣት በኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሰውነት ላይ ተወልዷል።

የጎሣ ክፍፍል እና የጎሰኝነት ችግሮች ለኢትዮጵያ ወይም ለአፍሪካ አዲስ አይደሉም። ዋልተር ሮድነይ በአፍሪካ አህጉር የጎሣ ልዩነቶች ቢኖሩም ቅሉ የግድ የፖለቲካ ልዩነቶችን የሚያመላክቱ አልነበሩም በማለት የክርክር ጭብጣቸውን አቅርበዋል። ሆኖም ግን የጎሣ መስመርን በሚከተሉ እና ሥልጣንን ጨምድደው በመያዝ እና የሀገሪቱን ሀብት ለግል እና ለተባባሪዎቻቸው ጥቅም ማጋበስ በሚፈልጉ በተወሰኑ የአፍሪካ ልሂቃን ተብዬዎች አማካይነት የጎሣ ልዩነቶች የፖለቲካ መልክ እንዲይዙ ተደርገዋል።

ዘ-ህወሓት ሥልጣንን በብቸኝነት ጨምድዶ ለመያዝ እና የሀገሪቱን ሀብት እርሱ እና ተባባሪዎቹ ብቻ ማግበስበስ እንዲችሉ በማሰብ የጎሣ ሥርዓት መስመርን ዘርግቷል። አዲስ ነገር ነው ተብሎ ሊታይ የሚችለው ነገር ቢኖር የደቡብ አፍሪካን ህዝብ በዘር እና በጎሣ በመከፋፈል የፖለቲካ ሥርዓቱን በበላይነት ተቆጣጥሮ ብዙኀኑን የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች ሲጨቁን እና የመሬትን ባለቤትነት፣ ተደራሽነት እና ጥቅም ሁሉ ሙሉ በሙሉ ይዞ ሲበዘብዝ ከነበረው ከጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይነት አገዛዝ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ዘ-ህወሓትም የጎሣ መስመሩን የመከተሉ ጉዳይ ነው።

በደቡብ አፍሪካ እንደነበረው እንደ ጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ሁሉ ዘ-ህወሓትም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉንም መሬት ሰብስቦ በመያዝ (የዘ-ህወሓትን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ልብ ይሏል) የእራሱን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይሉን መስርቶ ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ሥልጣኑን ተቆጣጥሮ (እ.ኤ.አ ግንቦት 2015 ተደረገ የተባለውን የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ 100 በመቶ አሸነፍኩ በማለት እና አረመኔውን አገዛዙን በጠብመንጃ ኃይል አጠናክሮ የሚገኝ መሆኑን ያጤኗል)፣ እንደዚሁም ደግሞ የግል ዘርፉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ (ዘ-ህወሓት በእራሱ የንግድ ድርጅቶች/ኮርፖሬሽኖቹ አማካይነት ሙሉ በሙሉ ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ ልብ ይሏል) እና የስራ ዕድል፣ የትምህርት እና ሌሎች ዕድሎችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ለፖለቲካ ደጋፊዎቹ እና ለታዛዥ ሎሌዎቹ በመስጠት ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ አግልሎ በድህነት እና በስቃይ እንዲዘፈቅ አድርጎት ይገኛል።

እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የዘ-ህወሓት የበላይነት፣ የጭቆና አገዛዝ እና ጎሰኝነትን በፖለቲካ መሳሪያነት በመጠቀም ብዙኀኑን ህዝብ በመበዝበዝ እራሱን የሁሉም ነገሮች ፈውስ አድርጎ በማቅረብ ከእራሱ የፖለቲካ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ማዕከልነት ወደተሻለ ነገር መሻገር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

መሬት እና የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት የሕግ መሰረት፣

የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ/የጎሣ አፓርታይድ ሥርዓት መሰረቱ መሬት ነበር። የመሬት ባለቤትነት። መሬትን የመጠቀም መብት። መሬትን የመያዝ መብት። መሬትን የመቆጣጠር መብት። መሬትን ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ የማከፋፈል መብት። ወደ 90 በመቶ አካባቢ የሚሆነውን መሬት በጥቂት አናሳ ነጭ ገበሬዎች እንዲያዝ የማድረግ መብት። በነጮች የመሬት ነጠቃ እና ብዙኀኑን ጥቀር ህዝቦች ከይዞታቸው የማፈናቀል መብት። ሕገወጥ በሆነ መልኩ ለተወሰደው መሬት የሚሰጥ ካሳን በጣም አሳንሶ የማቅረብ መብት። ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከቀደምቶቻቸው ጀምሮ ይዘውት ከኖሩት መሬታቸው እና እርስታቸው የማፈናቀል መብት። ይኸ ሁሉ ሕገወጥ መብት/ድርጊት በጥቂት አናሳ ዘረኛ የነጮች አገዛዝ የተሰጠ ነበር። ስለሆነም በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ የነጮች አገዛዝ የመሰረት ድንጋይ እና ምሰሶ ሆኖ ሲያገለግል የነበረውን ሕግ በሕገወጥ መልክ በመሳሪያነት በመጠቀም ፍትሐዊ ያልሆነው የመሬት ክፍፍል እና ብዙኀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውን ንብረት የለሽ እንዲሆኑ በማድረግ የኢኮኖሚ ኃይልን ማዳከም ማደህዬት ነበር።

የአፓርታይድ መሰረት የተጣለው “የተወላጆች መሬት ድንጋጌ፣ 1913 (አዋጅ ቁጥር 27/1913)“ ከሚለው እና ከአስርት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1948 በይፋ ከመውጣቱ በፊት ነበር። የመሬት አዋጁ በጥቂት ዘረኛ የነጮች አገዛዝ ቁጥጥር የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የመሬት ባለቤትነት መብት ለማሳጣት የተዘየደ ዋና የሕግ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። ድንጋጌው በተከታታይነት በወጡት ሕጎች እየታገዘ ብዙኀኑ ጥቁር አፍሪካውያን የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን በእጅጉ በመገደብ ከተወላጆች መሬት በደቡብ አፍሪካ ውስጥ 14 በመቶ ብቻ የሚሸፍነውን ለጥቁር አፍሪካውያኖች በመስጠት 87 በመቶ የሚሆነውን መሬት አናሳዎቹ ነጮች ብቻ እንዲይዙት ተደርጓል።

የ1950 የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act በኋላ በቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act 36/1966 ተጠናክሮ በደቡብ አፍሪካ ኗሪዎች በዘር አድልኦ ላይ ተጠናክሮ ወጥቷል። ይህ ድንጋጌ አናሳዎቹን የነጮች ዘረኛ አገዛዝ የገጠር እና የከተማ መሬትን ለነጮች፣ ለፉንጋ ጥቁሮች/colored እና ለሕንዶች የብቸኝነት የመሬት ባለቤትነት መብትን አጎናጽፏል፣ ሆኖም ግን ብዙኀኑ ጥቁር አፍሪካውያን የመሬት ባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው ወይም ደግሞ በብቸኝነት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ አልተደረገም። ሆኖም ግን ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ለሌሎች አካባቢዎች ቡድኖች ተብለው ከተከለሉት አካባቢዎች በተለይ መሬት ለመያዝ ወይም ደግሞ የመሬት ባለቤትነት መብት እንዳይኖራቸው ክልከላ ተደርጓል።

እ.ኤ.አ. በ1950 የወጣው የደቡበ አፍሪካ የህዝብ ምዝገባ ድንጋጌ (ሕምድ)/Population Registration Act (PRA) በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ኗሪ እንደ ዘር እና እንደ ጎሣ ቡድኑ እንዲመደብ እና እንዲመዘገብ አስፈላጊነቱን ይፋ አድርጓል። ያ ሕምድ/PRA በብዙኀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እና ነጭ ያልሆኑ ዜጎችን ለመከፋፈል እና የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አድልኦን በማንሰራፋት የአፓርታይድ ሥርዓትን በማፋጠን በመሳሪያነት በማገልገል ዋና መሰረት ሆኗል። (“አፓርታይድ” የሚለው የአፍሪካ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “መለያየት“ ማለት ሲሆን ከደች/ኔዘርላንድ ቋንቋ “መለየት” ሲደመር “ጎረቤት” ከሚሉት ተጣምረው ሲነበቡ “ከጎረቤት መለየት” የሚለውን የሀረግ ትርጉም ይሰጣሉ። በሕምዳ የአመዘጋገብ ሥርዓት መሰረት ግለሰቦች እንደ ዜጋ፣ ፉንጋ ጥቁሮች፣ ኢሲያዊ ወይም ደግሞ ነጭ በማለት ይመደባሉ። የማንነት ማስረጃ ሰነዶች ፍጹም የሆነውን የዘረኝነት አድልኦ እና ጭቆና ለማስፈጸም በዋናነት የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ነበሩ።

የ1951 የባንቱ ባለሥልጣኖች ድንጋጌ (ባባድ)/Bantu Authorities Act of 1951 (BAA) (የድንጋጌ ቁጥር 68/1951) የባባድን ድንጋጌ ወዲያውኑ የጥቁሮች ባለስልኖች ድንጋጌ (ጥባድ)/Black Authorities Act በሚል ስያሜ ተቀየረ። ጥባድ “የጥቁር አካባቢዎች”፣ “አለቆች”፣ “የጎሣ ባለሥልጣኖች” የሚል ትርጉምን በመስጠት የሥልጣን ኃላፊነታቸውን፣ ስራቸውን፣ የስራ ኃላፊነታቸውን እና የሕግ ማዕቀፎቻቸውን ትርጉም በግልጽ ያስቀምጣል። ጥባድ በርካታዎቹን የጎሣ እና ቋንቋን መሰረት ባደረገ መልኩ የተደራጁትን ጎሣዎች ወደ ባህላዊ የአካባቢ ኗሪነት በመፈረጅ የጎሣ፣ የክልል እና የአካባቢ ባለሥልጣኖችን ፈጠረ። የ1951ዱ የባንቱ ባለሥልጣኖች ድንጋጌ (የ1951 የጥቁር ባለሥልጣኖች ድንጋጌ) ጥቁሮችን ወደተመደቡላቸው ቦታዎች እንዲጋዙ በማድረግ የጎሣ፣ የክልል እና የአካባቢ ባለሥልጣኖችን ፈጠረ።

የ1950ው የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act (በ1966 እንደጸደቀው የቡድን አካባቢዎች ድንጋጌ/Group Areas Act) ሁሉ ደቡብ አፍሪካን ለነጮች እና ለጥቁሮች በሚል በመከፋፈል ህዝቦች ካልተመደቡበት አካባቢ በተለይም ከዘራቸው እና ከጎሣቸው ውጭ መኖር እንደማይችሉ ለማባረር እንዲችል ለአገዛዙ ሥልጣን ሰጠው። በዚህ ድንጋጌ መሰረት ማንም ቢሆን ባልተመደበበት “ስህተት” ቦታ ላይ የሚኖር ዜጋ ሁሉ ወደ ጎሣው/ሳዋ መኖሪያ አካባቢ ይጋዛል/ትጋዛለች። ከዚህም በተጨማሪ ሕጉ አፍሪካውያን ህዝቦች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በማንኛውም ቦታ መሬት የመያዝ መብት የሌላቸው እንደሆኑ እና ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ እንዲታቀቡ የሚል የሕግ ክልከላ ተጥሏል። በዚህ ሕግ መሰረት ጥቁር አፍሪካውያን በግዳጅ ይጋዙ እና እንደ ከብት በበረት ውስጥ በባንቱስታንስ የጎሣ ቡድን ይታጎሩ ስለነበር 3.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወቶች ጠፍተዋል።

እ.ኤ.አ በ1959 የወጣው የባንቱ እራስን በእራስ ማስተዳደር ማበልጸግ ድንጋጌ 1959/Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959 (PBSA) (የድንጋጌ ቁጥር 46) 8 (ቆይቶም ወደ 10 ከፍ እንዲሉ የተደረጉ) በአሁኑ ጊዜ ካሉት እያንዳንዳቸው እራሳቸውን በእራሳቸው በምስለኔዎች፣ በአለቆች፣ በዋና አለቆች፣ እና በጥቁር አካባቢዎች ያሉ የክልል አስተዳዳሪዎች መሰረት ማስተዳደር እንዲችሉ በመፍቀድ ልዩ የሆኑ የባንቱ ክልሎችን ፈጥረዋል። የአካባቢዎች መንግሥታት ውሱን የሆኑ የግብር አሰባሰብ፣ የህዝብ ስራዎች ቁጥጥር፣ የፈቃድ አሰጣጥ ጉዳዮችን እና ውዝግቦችን በሕጋዊ መንገድ የመፍታት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። የPBSA ዋና ዓላማ ለአካባቢ አስተዳደሮች የመጨረሻ ሥልጣን ለመስጠት፣ ከደቡብ አፍሪካ ዜግነት ለማስወገድ እና ለጥቂቶቹ የነጭ ዘረኛ ህዝቦች የብዙሀን ሥልጣንን ጠቅልለው እንዲይዙ ለማስቻል ነበር። እ.ኤ.አ የ971 የባንቱ አስተዳደር ሕገ መንግሥት ድንጋጌ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግሥት በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ለጥቂት ነጭ የበላይነት አገዛዝ ለማንኛውም አስተዳደር አካባቢ ነጻ ሥልጣን ሰጥቷል። የድንጋጌው ዓላማ ግልጽ እና እንዲህ የሚል ነበር፡ “እያንዳንዱ የአካባቢ መንግሥት እራሱን በእራሱ እንዲመራ እና የእራሱ መንግሥት እና ነጻነት ያለው መሆኑ የመንግሥት ጽኑ አቋም እና ሊቀለበስ የማይችል ዓላማ ነው።“ በሌላ አባባል የአካባቢ አስተዳደሮች ድንጋጌ የተለመደውን ተፈጥሯዊ የጎሣ መሬቶች የእራስን ዕድል በእራስ መወሰን በሚል ለባንቱስታንስ መንግሥታት ሙሉ ነጻነት ይሰጣል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት በመጨረሻ ነጻነት እ.ኤ.አ በ1976 እና 1981 ለትራንስኬይ፣ ለቦፉታትስዋና፣ ለቬንዳ እና ለሲስኬይ የአካባቢ መንግሥታት ተሰጥቷል።

ጨካኙ የደቡብ አፍሪካ ነጮች ዘረኛ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሄንድሪክ ቬርወርድ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የህዝብ ምዝገባ ድንጋጌ (ሕምድ)/Population Registration Act (PRA)ን በመጠቀም “የተናጠል ልማት” እየተባለ የሚጠራ ፖሊሲ ነድፎ በስራ ላይ አውሏል። አፓርታይድ የፖሊሲው ዋና ካርታ ሆኖ በመቅረብ የባንቱ የአስተዳደር አካባቢዎች የእየራሳቸው መንግሥታት ወይም ባንቱስታን ለመሆን በቅተዋል። አናሳው የጥቂት ነጮች አገዛዝ የብዙኀኑን ጥቁር ህዝቦች ባንቱስታናዊ የማድረግ እንዲህ የሚል የፖለቲካ ስልት ዓላማ ነበረው።

1ኛ) በዙሀኑን ጥቁር አፍሪካዊ በትንናንሽ የህዝብ ስብስብ የመከፋፈል ስሌትን በመጠቀም የከፋፍለህ ግዛን ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ።

2ኛ) በባንቱስታናዊ ቅኝት የተዘጋጀ የጎሣ ማንነትን ተግባራዊ በማድረጉ ጥረት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን እርስ በእርሳቸው ፍቅር የማይኖራቸው መሆናቸውን በማየት ስኬታማ መሆን መቻላቸውን ካረጋገጡ ማንኛውንም የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን አንድነት በተጨባጭ ለማጥፋት እንደሚችሉ ያምናሉ።

ባንቱስታናዊ ከማድረግም የተነሳ አናሳው የጥቀቲ ነጮች የበላይ አገዛዝ ቀደ 14 በመቶ የሚሆን የባንቱስታንን የአስተዳደር አካባቢ ለብዙኀኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካ ህዝቦች በመስጠት ሌላውን ለሙን፣ የማዕድን ክምችት ያለበትን እና የከተማ ቦታዎችን በሙሉ ለነጮች ይዞታ አደረገ። ወደ 90 በመቶ ያህል የሚሆነው የደቡብ አፍሪካን የንግድ የእርሻ መሬት በሙሉ ለ50,000 ነጭ ገበሬዎች ወይም ደግሞ መንግሥት ተሰጠ። በፖለቲካዊ አካሄድ ባንቱስታናዊነት ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ህዝቦች የእራስ አስተዳደር መብት እና ነጻነት ይሰጣል፣ ሆኖም ግን ለእነርሱ ከተከለለላቸው አካባቢ ውጭ እንደሌላ እንደ ባዕድ ዜጋ ነበር የሚታዩት። ደቡብ አፍሪካውያን በእራሱ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የእኩልነት መብት ይከላከላሉ፣ የእራሳቸው የአካባቢ መንግሥት የጎሣ ዜጋ ከሆኑ የዚያው የአካባቢያቸው መንግሥት ዜጋ እንጅ እንደ ደቡብ አፍሪካ ሬፐብሊክ ዜጋ አይቆጠሩም።

የደቡብ አፍሪካ ዘረኛ/የጎሣ አፓርታይድ ሥርዓት የጥቂት ነጮች ዘረኛ አገዛዝ ውሳኔ የተመሰረተው መሬትን በብቸኝነት ለመቆጣጠር እና መሬትን ተቆጣጥሮ በመያዝ በዚያ ስር የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ማንነት፣ ዜግነት፣ ኗሪነት፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና የኢኮኖሚ መብቶችን በመሉ ለመቆጣጠር ነበር። የደቡብ አፍሪካውያን ማንነት በዋናነት የሚወሰነው ከመሬት ጋር ባላቸው ግንኙነት ነበር። ጥቂቶቹ ነጮች ሁሉንም ምርታማ የሆነ ለም መሬት ተቆጣጥረው ሲይዙ ብዙሀኖቹ ጥቁር አፍሪካውያን ህዝቦች ግን በእርግጠኝነት ምንም ዓይነት መሬት አልነበራቸውም።

መሬት እና የዘ–ህወሓት የጎሣ አፓርታይድ ሥርዓት የሕግ መሰረት፣

የዘ-ህወሓት ልዩ የሆነው ጉብዝናው እ.ኤ.አ በ1995 በጸደቀው ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የጥቂት ነጮች የበላይ አገዛዝ ለበርካታ አስርት ዓመታት ያጸደቋቸውን ሁሉንም የአፓርታይድ ሕጎች እና ፖሊሲዎች ልቅም አድርገው በመውሰድ በእነርሱ ሕገ መንግሥት ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማስገባት የጎሣ የአፓርታይድ ሥርዓት ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ነው።

እ.ኤ.አ በ1995 በጸደቀው የዘ-ህወሓት ሕገ መንግሥት የሕገ መንግሥት አርቃቂዎቹ መሬትን እና ጎሣን በአንድ ላይ በማጣመር የደቡብ አፍሪካን ባንቱስታንስ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የባህል ስብጥር ባህሪያትን እንዳለ በመኮረጅ ወስደው ክልሎችን ለመፍጠር ተጠቅመውበታል። የዘ-ህወሓት ሕገ መንግሥት በመግቢያው መንደርደሪያ ላይ እንዲህ በማለት አውጇል፣ “ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ መብቶቻቸውን እና ነጻነቶቻቸውን ሙሉ በመሉ ለመጠቀም፣ እስከ መገንጠል…“ ይላል። በአንቀጽ 8 (1) የዘ-ሕወሀት ሕገ መንግሥት እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል።“ የዘ-ህወሓት አንቀጽ 39 እንዲህ የሚል መብትን ያጎናጽፋል፣ “እያንዳንዱ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና የኢትዮጵያ ህዝብ የእራሱን ዕድል በእራሱ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል“ ተሰጥቶታል። አንቀጽ 42 (2) እንዲህ የሚል መብትን አጎናጽፏል፣ “ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዚህ አንቀጽ በንኡስ አንቀጽ 1 በግልጽ በተመለከተው መሰረት በማናቸውም ጊዜ የእራሳቸውን መንግሥት የማቋቋም መብት አላቸው።“

የሚያስገርመው ነገር የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት ድንጋጌ 110/1983 እንዲህ የሚል ተመሳሳይ ዓላማን ያነገበ ድንጋጌን አጎናጽፎ ነበር፣ “ቡድኖች እና ህዝቦች የእራሳቸውን ዕድል እራሳቸው እንዲወስኑ ውሳኒያቸውን ለማክበር፣ ለማጠናከር እና ለመጠበቅ“ ይላል።

እንደ ደቡብ አፍሪካ የ1959 የBantu Self-Government Act of 1959 (PBSA) ድንጋጌ ሁሉ መጀመሪያ 8 (ቆይቶም በማስፋት 10) ባንቱስታንስ (የጥቁር ህዝቦች መኖሪያ መንደሮች) እንደፈጠሩ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የዘ-ህወሓት ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 46 (2) የአኗኗር ዘይቤዎችን፣ ቋንቋን፣ ማንነትን እና የሚመለከተውን ህዝብ ስምምነት ከግንዛቤ በማስገባት ክሎችን ይፈጥራል ይላል። አንቀጽ 47 የአኗኗር ዘይቤዎችን፣ ቋንቋን፣ ማንነትን እና የሚመለከተውን ህዝብ ስምምነት መሰረት በማድረግ 9 ክልላዊ መንግሥታትን (ክልሎችን) መስርቷል።

ለደቡብ አፍሪካ ጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ በአጠቃላይ መሬትን መቆጣጠር እንዳስቻለው እንደ ደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ ሕገ መንግሥት እና ሌሎች ሕጎች ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ የዘ-ህወሓት ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 40 (3) ሁሉም የመሬት የባለቤትነት መብት በዘ-ህወሓት እና በዘ-ህወሓት ታዛዥ ሎሌዎች፣ ተባባሪዎች እና በክልል ያሉ ግብረ አበሮች አማካይነት መሬትን በብቸኝነት ለመቀራመት እና ለመቆጣጠር እንዲህ የሚል መብትን አጎናጽፏል፣ “የገጠር እና የከተማ መሬት እንዲሁም ሁሉም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶች የመንግሥት እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው። መሬት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና የኢትዮጵያ ህዝቦች ንብረት ነው። እናም አይሸጥም ወይም ደግሞ አይለወጥም“ ይላል። ሆኖም ግን ዘ-ህወሓት በክልሎች የሚገኘውን በመቶዎች እና በሺዎች ሄክታሮች የሚቆጠረውን አንጡራ የሀገሪቱን ለም መሬት ድብቅ ለሁኑት ሸፍጠኛ የቢዝነስ ሰዎች እየቸበቸበ በማቀራመት ላይ ይገኛል። ከጥቂት ወራት በፊት ካሩቱሪ የተባለው የሕንድ ኢንቨስተር በመሬት ቅርምቱ ያገኘውን መሬት እና የዌልስን ግዛት የሚያህለውን እና በምዕራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ዘ-ህወሓት የሚነካበት ከሆነ የሕንድን ኃያልነት እንደሚያሳየው ድፍረትን በተላበሰ መልኩ ለህወሓት የዘራፊ ቡድን ስብስብ ነግሮታል። ወይ የካርቱርሪ በእራስ መተማመን ድፍረት እንነጋር!

ኢትዮጵያን ክልላዊ በማድረግ የዘ-ህወሓት አገዛዝ እና ታዛዥ ሎሌዎቹ በኢትዮጵያ ብዙሀን ህዝብ ላይ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይ ጌቶች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። የደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች የበላይ የአፓርታይድ አገዛዝ በርካታ አስርት ዓመታትን የወሰደበት ድርጊት ዘ-ህወሓት ግን በ25 ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ችሏል። ዘ-ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝቦች ክፍት በሆነ ከባቢ አየር ውስጥ አስሮ እና እንደ ከብት በበረት አጉሮ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መብት ገፍፎ ሀገሪቱን በክልላዊነት በጥጣሶ በማተራመስ ላይ ይገኛል።

ሁልጊዜ እንደማቀርበው የክርክር ጭብጥ ሁሉ የጎሣ ክላልዊነት ዋና መሀንዲስ የነበረው እና አሁን በሕይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አካባቢ የደቡብ አፍሪካው የጥቂት ነጮች ዘረኛ የበላይ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ሄንድርክ ቬርወርድ እንዳደረገው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ የጎሣ ክፍፍልን መሰረት ባደረገ ራዕይ በመገፋፋት ሀገሪቱን በጎሣ ከፋፍሎ በስቃይ ውስጥ እንድትሆን እና ለከፍተኛ አደጋ እንድትዳረግ አድርጓታል። አምባገነኑ መለስ ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ያህል የኢትዮጵያን ህዝቦች የግንኙነት ክር ለመበጠስ እና በዘር፣ በጎሣ፣ በቋንቋ እና በክልል እንድትቀነበብ ያለ የሌለ ጥረቱን አድርጎ ነበር በተፈጥሮ ትዕዛዝ ተቀደመ እንጅ። አምባገነኑ መለስ ሙሉ በሙሉ በጎሣ እና በዘር ግንኙነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ድርጅት አዋቅሯል።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ጥቂት የነጮች ዘረኛ አገዛዝ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን ከአንድ የትወልድ ቦታ ወደ ሌላ ሲያዘዋውር እንደነበረው ሁሉ ዘ-ህወሓትም አንድ ዓይነት እርምጃ በመውሰድ እና የ”አማራ” ጎሣ ቡድን አባላትን ከደቡብ ክልል (ከ9 ክልሎች አንዱ ከሆነው) በኃይል በማፈናቀል የጎሣ ማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል። አሁን በሕይወት የሌለው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከደቡብ ክልል በኃይል ላፈናቀላቸው የአማራ ብሄረሰብ ዜጎች የሰጠው ማሳመኛ እንዲህ የሚል ነበር፣ “…በታሪክ አጋጣሚ ላለፉት አስርት ዓመታት ከምስራቅ ጎጃም የመጡ በርካታ ህዝቦች ወደ 30,000 የሚጠጉ ሰፋሪዎች በቤንች ማጅ ዞን (በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፍረው ይኖሩ ነበር። በጉራ ፈርዳ ወረዳ ከ24,000 በላይ ሰፋሪዎች አሉ“ ብሎ ነበር። በሰፈራ ፕሮግራም በዘለቄታዊ መንገድ ለዘመናት ቀደምቶቻቸው ሲኖሩበት ከነበረው አካባቢ ከጋምቤላ፣ ከቤንሻንጉል እና ከኦሞ ወንዝ ሸለቆ በኃይል በማፈናቀል መሬቶቻቸው በጫረታ አማካይነት ለሆዳም ስግብግብ ብዙሀን የግብርና ቢዝነስ ለሚያካሂዱ ድርጅቶች ተሰጥቷል።

በዘ-ህወሓት ስቃይ እና ለመቋቋም የማይቻል ክልላዊ ደባን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የግጭቶች አስወጋጅ ቡድን/International Crises Group (ICG) በተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት አስደማሚ ጥናት ተመዝግቦ ይገኛል። “ኢትዮጵያ፡ የጎሣ ፌዴራሊዝም እና ቅሬታዎቹ“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ጥናቱ ICG በጎሣ ፌዴሪያሊዝም (በክልላዊነት) ምክንያት ዜጋዊነት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ማንነት በጎሣ መሰረት ላይ የሚሰጥ የመሆኑን ችግር ይፋ አድርጓል። ጥናቱ እንዲህ የሚል የክርክር ጭብጥ ያቀርባል፣ “የጎሣ ፌዴራሊዝም በሀገሪቱ መካከለኛው ከፍተኛ አካባቢዎች በሚኖሩት እና ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ኦሮሚያ እና አማራ በጣም ትንሽ የሆነ የህዝብ ብዛት ካላቸው እንደ ጋምቤላ እና ሶማሊ ካሉት ጋር የማይመሳሰል ፌዴሬሽን በእኩል ተሰጥቶ ይገኛል። ከዚህም በተጨማሪ የጎሣ ፌዴራሊዝም ጥቂት ቡድኖችን በማጠናከር ደካማ ክልላዊ መንግሥታትን በመፍጠር የብሄራዊነት ጥያቄን መመለስ ተስኖታል። በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ውይይት እና እርቀ ሰላም ለማውረድ የመለስ አምባገነናዊ አመራር ሊቀበል ባለመቻሉ ምክንያት በአሁኑ ወቅት እየታዬ ያለውን ሁኔታ እንዲባባስ በማድረግ ቅሬታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በመሄድ የኢህአዴግ የጎሣ ፖለቲካ ለሥልጣን ስስ መሆን በቀጣይነት የጎሣ ግጭት ለመከሰት የሚያስችል ፍርሀትን አንግሶ ይገኛል።“ የICG ዘገባ ግልጽ እንዳደረገው በረዥሙ የጊዜ እይታ የጎሣ ፌዴራሊዝም የኢትዮጵያን ህዝብ ወደ መበተታተን እና መለያየት ሊያመራው ይችላል። አሁን ብሄራዊነት የሌለው ሀሰተኛው መሲህ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ሥልጣን ሲይዝ ሀገሪቱ ወደ መበታተን አደጋ ላይ ወድቃ እንደነበር ጉራውን ቸርችሮ ነበር። እንዲህ በማለት የክርክር ጭብጡን አቅርቦ ነበር፣ “ማንም ትንታኔ የሚያቀርብ ባለሙያ እንደሚገምተው ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ እና ሶቪዬት ህብረት እንደሄዱበት ባለ መንገድ ላይ ልትጓዝ ትችላለች“ በማለት መተንበይ ይችላል ብሎ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ግን ኢትዮጵያ እንደነ ዩጎዝላቪያ፣ ሶማሌ፣ ኮንጎ ወይም ደግሞ ኤርትራ እንደሆነችው እንኳ ስትሆን አልታየም።

ሀሰተኛው መሲህ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው መለስ ሁልጊዜ እራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል። ሕዝቡን በማስፈራራት ከእግሩ ስር ለማንበርከክ እንዲችል ማንኛውንም አስፈሪ የሆነ ነገረ ሁሉ እየቃረመ ያስፈራራል። እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ሲታይ ግን የጎሣ መለያየት፣ መበታተን፣ መከፋፈል እና ጽንፈኝነት የመለስ አገዛዝ በሥልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመኖር እና አንጡራ የህዝብን ሀብት እየዘረፉ ለመኖር እንዲመቻቸው የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎቻቸው ናቸው። በእውነተኛ የፌዴሪያሊዝም ሥርዓት ብሄራዊው መንግሥት የክልል መንግሥታት ውጤት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ክልላዊ መንግሥታት የብሄራዊው መንግሥት ፍጡሮች እና በዘ-ህወሓት እጅ ተጠፍጥፈው የተሰሩ መንግሥታት ናቸው። በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ብሄራዊ መንግሥት ውሱን የሆኑ እና የተቆጠሩ ሥልጣኖች ተሰጥተውት የክልል መንግሥታት የጋራ የሆኑ ነገሮችን ማስፈጸም ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የዘ-ህወሓት ሥልጣን ሰፊ እና ያልተገደበ ነው። እናም በክልሎች ላይ ጣልቃ ለሚያስገባው ሥልጣኑ ምንም ዓይነት ገደብ የሌለው በመሆኑ እንደፈለገው በማተራመስ ላይ ይገኛል። በዘ-ህወሓት ክልላዊ ሥርዓት ዘ-ህወሓት እና ግብረ አበር ክልሎቹ በህዝቦች መብቶች እና ነጻነቶች ረገጣ እና ለሚያደርጉት ጣለልቃገብነት ክልከላ ዘብ የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል የለም። በቀላል አገላለጽ የዘ-ህወሓት ክልላዊ ፖሊሲ የዘ-ህወሓት አምባገነናዊ አገዛዝ ቀጥተኛ ቅጅ ነው። ክልላዊነት በየራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል በሚል በማስፈራሪያነት ተወሽቆ ይገኛል።

በደቡብ አፍሪካው በጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ አፓርታይድ እና በዘ-ህወሓት የጎሣ ፌዴራሊዝም አፓርታይድ መካከል ያሉት ተመሳሳይነቶች ለመመዝገብ ከሚያስቸግር በላይ በርካታ ናቸው። ዘ-ህወሓት ሙሉ በሙሉ የፖለቲካ ሥልጣኑን፣ ውክልናውን እና የውሳኔ ሰጭነት ተግባሩን እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ አፓርታይድ ብሄራዊ ፓርቲ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ተቆጣጥሮ በመተግበር ላይ ይገኛል። ዘ-ህወሓት በክልላዊ ፖሊሲው የአማራ ብሄረተኞች (ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ ወታደሮች እያለ የሚጠራቸው) የድሮውን ሥርዓት በማምጣት በብሄረሰቦች ላይ የአማራን አገዛዝ ሊጭኑባችሁ ነው በማለት በእርሱ ክልላዊ ፖሊሲ ላይ ትችት የሚያቀርቡትን ጸጥ ለማድረግ ይጠቀምበታል። ዘ-ህወሓት ሌሎችን ተቃዋሚዎች ጽንፈኛ አክራሪዎች እና እንደ ሩዋንዳ የኢንተር ሀሞይ እልቂትን ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው በማለት ይፈርጃቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ተቃዋሚዎቹን “የኮሙኒስት አሸባረዎች” ናቸው በማለት ይጠራቸው ነበር።

ዘ-ህወሓት በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ያደርጋሉ። የዘ-ህወሓት መንግሥት በመንግሥት ላይ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን ያሳልፋል። አምባገነኑ መለስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ በመንግሥት ላይ መንግሥት የሚለው ሸፍጣቸው ገና ከጫካ በነበሩበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረ እና ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ታማኞቹን እና እሺ የሚሉ ሰዎችን ብቻ ከገንዘብ ገንዳው ውስጥ የሚያሳትፍ ሥርዓትን ዘርግቷል። እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች አፓርታይድ አገዛዝ ሁሉ በክልሎች ስማዊ የነጻ ውሳኔ ሰጭነትን ይፈቅዳል። ሆኖም ግን እውነታው ሁሉም ውሳኔዎች በማዕከል ተሰባስበው የተያዙ እና በዘ-ህወሓት በመንግሥት ላይ መንግሥት ውሳኔ የሚሰጥባቸው ናቸው። የዘ-ህወሓት የደህንነት እና የስለላ ኃላፊዎች በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንሶች ላይ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ላይ በመንግሥት ላይ መንግሥት እየሰለሉ ወሬ በማነፍነፍ ለዘ-ህወሓት አመራሮች የሚያቀብሉ ናቸው።

በደቡብ አፍሪካ የጥቂት ዘረኛ ነጮች የበላይ አገዛዝ በባንቱስታንሶች ላይ ያደርግ እንደነበረው ሁሉ ዘ-ህወሓትም እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ ለመሬት ቅርምቱ እና ለሌላው ሀብት እና ዘ-ህወሓትን ለመገዳደር ችሎታው ለሌላቸው እና በዘ-ህወሓት ላይ ጥገኛ የሆኑትን ክልሎችን ለመቆጣጠር እገዛና እና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ።

የዘ-ህወሓት የደህንነት መዋቅር በክልል ውስጥ ያሉ ባለሥልጣኖችን ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠሯቸዋል። በእርግጥ የፖለቲካ መረጋጋት አይታይበትም በሚባል አካባቢ የዘ-ህወሓት የደህንነት እና ወታደራዊ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ባንቱስታንስ አፓርታይድ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ ከክልል ባለሥልጣኖች ነጻ በሆነ መልኩ ይሰራሉ። የዘ-ህወሓት ባለሥልጣኖች የደህንነት እና የወታደራዊ ኃይሉን እንቅስቃሴ በክልሎች ይመራሉ። ማንም የክልል ባለሥልጣን ለዘ-ህወሓት መስመር የማያጎበድድ ከሆነ ከሥልጣኑ እንዲባረር ይደረግ እና የሙስና ክስ እንዲመሰረትበት ይደረጋል።

እንደ ደቡብ አፍሪካው የጥቂት ዘረኛ ነጮች አገዛዝ አፓርታይድ በባንቱስታንሶች ላይ ያደርጉት እንደነበረው ጥብቅ ቁጥጥር ሁሉ ዘ-ህወሓትም በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ላይ በርካታ ስልቶችን በመቀየስ ጥብቅ ቁጥጥር ያካሂዳል። ዘ-ህወሓት ፖሊሲዎቹን ሽፋን ለመስጠት፣ ለማስመሰል እና ለማስፈጸም ኢህአዴግ የሚባለውን የይስሙላ የፓርቲ ስብስብ በማስመሰያነት ይጠቀማል። ክልሎች ለበጀት እና ለሌሎች ድጋፎችም በዘ-ህወሓት ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ምክንያት ዘ-ህወሓት ክልሎቹ እና ሌሎች በእርሱ መስመር አጎብዳጅ ሆነው እንዲኖሩ ሥልጣኑን ለቁጥጥር ይጠቀምበታል።

እንደአፓርታይድ ጓደኞቻቸው ሁሉ ዘ-ህወሀቶችም በተመሳሳይ መልኩ የፈጠሯቸው የጎሣ-ቋንቋ ቡድኖች አንድ ዓይነት እና ተመሳሳይ ናቸው። ሆኖም ግን አንድ ዓይነት ያልነበሩ እና ቀላል በሆነ መልኩ በአኗኗ ዘይቢያቸው፣ በቋንቋ፣ በማንነት መፈረጅ እና መወሰን አልነበረባቸውም። የኢትዮጵያ ህዝቦች በውልደት የተዋኸደ፣ ተመሳሳይ ባህል እና ማንነት ያላቸው ናቸው። ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ልብወለድ ስታሊኒናዊ ዘ-ህወሀቶች ጥሩ ሊመስል ይችላል፣ ሆኖም ግን እውነተኛውን እና ታሪካዊውን የጎሣ ልዩነቶችን እና አንድነቶችን አያንጸባርቅም። የዘ-ህወሓት የጎሣ ሀሳብ ከታሪካዊ እውነታ ጋር የሚጣረስ እና ምንም ዓይነት ወጥነት የሌለው ድልዱም አስተሳሰብ ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ንጉሳዊ አገዛዝ እስከወደቀበት እ.ኤ.አ እስከ 1974 ድረስ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ገዥ የነበሩት ልዑል መንገሻ ስዩም በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዘ-ህወሓትን ክልላዊ መዋቅር የውሸት መሆኑን አሰተባብለዋል። ልዑል መንገሻ ወልቃይት ጠገዴ ከአማራ ይዞታነት ተነስቶ ወደ ትግራይ መካለሉን አስመልከቶ ወደ ትግራይ እንዲካለል የተደረገውን የዘ-ህወሓትን ውሳኔ በጽኑ ተቃውመውታል። በሌላ አባባል በወልቃይት ጠገዴ ወደ ተግራይ መካለል ዘ-ህወሓት አኗኗር ዘይቤ፣ በቋንቋ በማንነት እና ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው ህዝቦች የሚለውን የእራሱን ሕገ መንግሥት እንኳ የጣሰ እና በሸፍጥ የእራሱ ግዛት ለማድረግ ያደረገው እኩይ ምግባር ነው።

የኢትዮጵያ ክልላዊነት አከላል ኢትዮጵያውያንን በጎሣ መስመር በመከፋፈል ለዘ-ህወሓት አገዛዝ እንዲመቸው ዓላማ ያደረገ እና የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም የተቀየሰ የዘ-ህወሓት የጥፋት ዕቅድ ነው። ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ቴደ ቬስተል “የሰብአዊ መብቶች ረገጣ በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፡ መንግሥት አቀፍ የጎሣ ጥላቻ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፋቸው እንዲህ በማለት የዘ-ህወሓትን የዘ-ህወሓትን ክልላዊ ስልት ጨምቀው አቅርበዋል፣

“የኢህአዴግ ሌላው ገጽታው [የብዙሀነት ቅርጽ ያለው ለማስመሰል በህወሓት የተፈጠረው የሸፍጥ ድርጅት] ዋና ስልት የብሄሮችን፣ ብሄረሰቦችን እና ህዝቦችን መብት ትኩረት በሰጠ መልኩ የተዋቀረ የጎሣ ፌዴራሊዝም ሥርዓት አስተዳደርን ለመመስረት ነው። ሆኖም ግን ይህ ትልቅ የሚመስል መርህ ከሌኒን የተኮረጀው ከውሶኒያን ይልቅ የማኪያቬሊንን ሸፍጥ የተላበሰ ነው። እነዚህ ብዙ መስለው የሚታዩት እና ኢህአዴግ/ኢፌዴሪን የሚዘውሩት ትግራውያን ሌሎችን የጎሣ ቡድኖች እየከፋፈሉ እና በጥልቅ የጎሣ ጥላቻ እርስ በእርሳቸው እንዲናቆሩ በማድረግ ወይም ደግሞ እነርሱ ባለቻቸው ትንሽ እውቀት ላይ በመመስረት ትናንሽ ግዛቶቻቸውን በማስተዳደር ተግባር ላይ ተጠምደው ባሉበት ሁኔታ ታላቁ የአገር ጉዳይ በአንድ ፓርቲ መንግሥት እንዲካሄድ ይደረጋል። ስለሆነም ኢህአዴግ ታላቋ ኢትዮጵያ እያለ የሚያሰራጨው የውሸት የብሄራዊ ፕሮፓጋንዳ በቁጥጥር ስር ይውል እና የእርሱ ተቃዋሚዎች እንዲከፋፈሉ እና እንዲሸነፉ ያደርጋል።“

የኢትዮጵያ የአቦ ሸማኔው ወጣት ትውልድ፡ “ኢትዮጵያ በእናንተ እጅ ላያ ናት።”

ከአሜሪካ የሕግ ዳኞች አንዱ እና እጅግ በጣም ታዋቂ የሆኑት ጌሪ ስፔንስ በአንድ ወቅት በወንጀል ጉዳይ ላይ ያደረጉት የመዝጊያ ንግግር ውስጣዊ ስሜቴን እና ቀልቤን ስለገዛው እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምን ማድረግ እንደሚችሉ እና ለእራሳቸው እና ለሀገራቸውስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ታላቅ ትምህርት ይሆናል በማለት ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። ስፔንስ እንዲህ በማለት ሞግተዋል፤¨

“ክቡራት እና ክቡራን፣ ከእናንተ ልለይ ነው፣ ሆኖም ግን ከእናንተ ከመለየቴ በፊት ስለአንድ ብልህ ሽማግሌ እና ስለአንድ አጭበርባሪ ልጅ ታሪክ ልነግራችሁ እወዳለሁ። አጭበርባሪው ልጅ ሽማግሌው ምን ያህል ሞኝ እንደሆኑ ለማሳት ዕቅድ ነበረው። አጭበርባሪው ልጅ ከጫካ ውስጥ አንዲት ወፍ ያዘ። እርሷንም በእጆቹ ያዛት። የትንሿ ወፍ ጅራት ከጁ አልፋ ትታይ ነበር ። በእጆቹ ላይ ያለችው ወፍ በሕይወት ነበረች። ዕቅዱ እንዲህ የሚል ነበር፡ ወደ ሽማግሌው እያመላከተ “ሽማግሌው በእጆቼ ላይ ምንድን ነው ያለው?“ ሽማግሌው ሰው እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል።“ ከዚያም ልጁ እንዲህ ይላል፣ “ሽማግሌው ወፏ በሕይወት አለች ወይስ በሕይወት የለችም?“ ሽማግለው ወፏ በሕይወት የለችም ሞታለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ ልጁ እጆቹን ግራና ቀኝ በመክፈት ወፏ በነጻነት እንድትበር ሆኖ በዛፍ ላይ ታርፍ እና በደስታ መኖር ትጀምራለች። ሆኖም ግን ሽማግሌው ሰው ወፏ በሕይወት አለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ አጭበርባሪው ልጅ በእጆቹ መካከል ወፏን አጣብቆ እና ደፍጥጦ እንድትሞት በማድረግ “ሽማግሌው ይመልከቱ ወፏ ሞታለች“ ይላል። በዚህም መሰረት ልጁ ወደ ሽማግሌው በመሄድ ቀረበ እና እንዲህ አለ፣ “ሽማግሌው በእጆቼ ላይ ምን ይዣለሁ?“ ሽማግሌው እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል።“ ልጁ እንዲህ አለ፣ “ሽማግሌው ወፏ በሕይወት አለች ወይስ ደግሞ በሕይወት የለችም?“ ሽማግሌው ምናቸው ሞኝ እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፏ በእጅህ ላይ ናት“ አሉ።

እኔም ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኢትዮጵያ በእጃችሁ ላይ ናት እላቸዋለሁ። በሕይወት ያለች ወይም በሕይወት የሌለች ወይም ደግሞ ወደፊት የምትኖር ወይም የምትሞት ብቻ ከሆነ እናንተው ብቻ የምታውቁት ይሆናል። ኢትዮጵያ ለዘላለም የምትኖር መሆኗን ግን አረጋግጡ!

ይቀጥላል … (እንደትግሉ)

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles