የኢትዮዽያ መንግስት የስልክ ቀፎዎችን የማስመዝገብ ግዴታ በድንበኞቹ ላይ ለመጣል ተዘጋጅቷል። በቫይበርና(Viber) ዋትስ አፕ(WhatsApp) አገልግሎቶች ላይም የተለየ ክፍያ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቋል። በአፋኝነቱ የሚታወቀው መንግስት ወደዚህ አይነቱ እርምጃ የመራኝ “የሞባይል ስልክ ቀፎ ስርቆት” መባባሱ ነው የሚል ምክንያት ያቀርባል። ዳንኤል ድርሻ ስለጉዳዩ ዝርዝር አዘጋጅቷል።
የሞባይል ቀፎ ሳያስመዘግቡ አገልግሎት የሚገኝበት ዘመን ማክተሙን ኢትዮ ቴሌኮም አሳውቋል፡፡ በአዲሱ አሰራር ባለ ሁለት ሲም ካርድ ቀፎ ያላቸው ተገልጋዮች… የሚጠቀሟቸውን ሲም ካርዶች ለድርጅቱ ያስመዘግባሉ፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ሲም በተለያየ ቀፎ ለመገልገል ቀፎዎቹን ቅድሚያ ማሳወቅ የግድ ይላል፡፡ ከውጪ ሃገር በስጦታ የሚገባ የቀፎ መጠንን የሚወስነው መስሪያ ቤቱ ይሆናል፡፡ “ደረጃቸው ወርዷል” ብሎ የፈረጃቸውን አንድ ጊዜ ብቻ ለአገልግሎት ይመዘግባል፡፡
የሞባይል ቀፎን የሚመዝግብና መለያ ቁጥር የሚሰጥ “ኢኪዩፕመንት አይደንቲፊኬሽን ኤንድ ሬጂስተር” የተሰኘ መሳሪያ ወደ ሃገር ማስገባቱን ይፋ አድርጓል። ቴክኖሎጂው የተጠቃሚውን የስልክ ቀፎ ከሲም ካርዱ በማናበብ የቀፎ ስርቆትን ለማስቀረት በመፍትሔነት እንደተመረጠ ነው በድርጅቱ የተገለጸው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ደፈር ብሎ በስም አይጥቀሰው እንጂ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን የሚመዘግበው የሞባይል ቁጥር IMEI (International Mobile Station Equipment Identity) በአጭሩ “አዬሚ” ይባላል፡፡ የሞባይል ስልክዎን ባትሪ አንስተው ከስር ይሕንኑ ቁጥር መመልከት ይቻላል፡፡ አለያ ደግሞ በሞባይልዎ ይሕን ቁጥር ይደውሉ፦ *#06#፡፡ እህሳ… ባለ 13 ወይም 15 ዲጂት ቁጥር ስክሪንዎ ላይ ተመለከቱ?… “አዬሚ” (IMEI) ማለት እሱ ነው፡፡ ቁጥሩ ከቀፎ ቀፎ ይለያያል፤ እንደ እጅ አሻራ አይመሳሰልም፡፡
ለሕግ የሚገዙ መንግስታት ሥርዓት ለማስፈን የ“አዬሚ” መለያን ብሎክ በማድረግ ሌላ አዲስ ቁጥር ይሰጣሉ፡፡ የኢትዮጵያው ቴሌ አሁን ቴክኖሎጂውን እንደ አዲስ ግኝት “አስገባሁት” ቢልም አውስትራሊያ ከ13 ዓመት በፊት ነበር “ኢኪዩፕመንት አይዴንቲፊኬሽን ኤንድ ሬጂስተር”ን (EIR) ሥራ ላይ ያዋለችው፡፡ የተሰረቁና የጠፉ ስልኮችን በማፈላለግ “አዬሚ” ድንቅ ጠቋሚ ነው፤ የስልጡን ሃገራት የፖሊስና የደሕንነት አባላት ተጠርጣሪዎችን ለማደን ይጠቀሙበታል፡፡
በአንጻሩ ኢሕአዴግና መሰል ጉልበተኛ መንግስታት የጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞችን ሞባይል ቀፎ በ“አዬሚ” ቁጥሩ ተጠቅመው ይጠልፋሉ፤ የተጠለፈ መረጃቸውን በሐሰት ለመወንጀልና ወሕኒ ለማጎር ይመነዝሩታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በሃገር ውስጥ የሚከታተላቸውን በIMEI በመሠለል ሳይገደብ ፊንፊሸር የመሳሰሉ የስለላ ሶፍትዌሮችን በኢሜል በመላክ በአሜሪካና በእንግሊዝ የሚኖሩ ሰዎችን ጭምር መሰለሉ ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡
ሞባይል ስልክ የሶስትዮሽ ግንኙነት ጥምረት ውጤት ነው፡፡ ሞባይል ሲበራ በቅድሚያ “አዬሚ” የምንለው የሞባይል ቀፎ መለያ፣ ወደ ቀፎው ከገባው ሲም ካርድ ጋር ይናበባሉ፤ ቀጥሎ በቅርበት ከሚገኝ የቴሌ ማማ (ታወር) ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ይመሠረታል፡፡ በዚህ ሥርዓትና አሠራር መረጃዎች ለአገልግሎት ሠጪው መስሪያ ቤት ይደርሳል፡፡ የንግግሩ ይዘት አይታወቅ እንጂ ከየትኛው ቁጥር እንደተደወለ ቴሌ ያውቃል፤ ከማን ጋር ሜሴጅ እንደተላላኩና ዝርዝሩ፣ በሞባይል ኢንተርኔት ብራውዝ ያደረጉትን (ዩቲዩብ ነው ወይስ ጉግል ወዘተ…)፣ የተጠቀሙት ዳታ ይመዘገባል፤ የት ሥፍራ ሆነው እንደተጠቀሙ በአቅራቢያ ግምት ይታወቃል፡፡ በደሕንነት የሚሠለለው ባለ ሞባይል በ“አዬሚ” ቁጥሩ አማካይነት ልዩ ክትትል ሲደረግበት የሚነጋገረው ይቀረጻል፤ በቀፎው የመዘገበው የሌላ ሰው ስልክ ቁጥር (ኮንታክት ሊስት)፣ ፎቶግራፍና ቪዲዮ በዚያ ወገን ባለው ሠላይ ይታያሉ፤ አንተርኔት የሚጠቀም ከሆነ በሞባይሉ ካሜራ ሳያውቀው ፎቶ ሊነሳም ይችላል፡፡
የእጅ ስልኩ መጠለፉን የሚጠራጠር ሠላማዊ ሰው ሲም ካርዱን ብቻ በማውጣት ከክትትል እንደማይርቅ መረዳት ይገባዋል፤ እንዲህ ዓይነት ሥጋት ሲኖር መፍትሔው ባትሪውን ከቀፎው ማውጣት ነው፡፡ ከክትትልና ጠለፋ ሥጋት ለመራቅ መሞከር ይጠቅማል፤ ሞባይል ስልክን ለሠከንዶች እንኳ ሌላ ሰው እጅ መግባት የለበትም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኢንተርኔት የማይታዩ የስለላ አፕሊኬሽኖች መጫን ከባድ አይደለምና፡፡ ከቴሌ የተቀበሉትን ሲም ካርድ ፓስወርድ መቀየር፣ ቀፎውን በድርብርብ ፓስወርድ መዝጋት፣ የኢንተርኔት ብራውዚንግ ሂስትሪን ማጥፋት፣ በሠላማዊ ትዕይንት ወቅት ቪዲዮና ምስል ሲቀርጹ “ኤሮፕሌን” ሞድን መጠቀም፣ ሎኬሽን “ኦፍ” ማድረግ… ወዘተ የሥጋት መቀነሻዎች ናቸው፡፡
ስልክዎ መጠለፉን ለማወቅ የሚረዱ ምልክቶችን መከታተልም መልካም ነው፡፡
የባትሪ ቆይታ ጊዜን መረዳት፦ በቅድሚየ የባትሪን ቆይታ ጊዜ መረዳት፤ የድምጽና የጽሁፍ መልዕክት በሚላላኩበት ወቅት ባትሪው ከጠለፋ ምንጩ ጋር መተዋወቅ ይጀምራል፡፡ አንድ ሰው በድብቅ ከርቀት የስልክዎን ማይክራፎን ከፍቶ እያዳመጠዎት ከሆነ ባትሪው ይሕንኑ ይረዳል፡፡ እናም ባትሪ ከተለመደው ጊዜ በፍጥነት ማለቅ ከጀመረ፣ አዲስ ባትሪም ተቀይሮ ችግሩ ካልተቀረፈ ስልኩ ተጠልፏል ማለት ነው፡፡
ሙቀቱን ይወቁ፦ የሞባይልዎን ሙቀት ልብ ይበሉ፤ ስልክ አገልግሎት ሲሰጥ ሙቀቱ መጨመሩ የሚጠበቅ ነው፤ እርስዎ ሳይጠቀሙበት ሞባይልዎ የሚሞቅ ከሆነ ከእርስዎ ዕውቅና ውጪ ሌላ ሰው እየተጠቀመበት ነውና መጠለፉን ይገምቱ፡፡
እንግዳ ጉዳዮችን መቆጣጠር፦ ሞባይልዎ በራሱ መብራትና መጥፋት ከጀመረ፣ ለማጥፋት ሲሞክሩ ካስቸገረ ወይም እምቢ አልጠፋም ካለ የሞባይል መጠለፍ ሌላ ምልክት መሆኑን ይረዱ፡፡
መልዕክት ማስተዋል፦ በምልክት የተቀመጡ የጽሑፍ መልዕከቶችን ልብ ብሎ ማስተዋል ያስፈልጋል፤ ወደ ሜሴጅ ቦክስ እና ኢ ሜል በቃላት ፈንታ የማይነበቡ፣ ቁጥር እና ምልክቶች ከተላከልዎ ከእርስዎ የመልዕክት ሳጥን መረጃ ለመውሰድ በሌላ ወገን ያልተሳካ ሙከራ እየተካሄደ መሆኑን ይረዱ፤ ከማያውቁት ቁጥርም ሆነ ላኪ የተሰደደ ሜሴጅ ሊንክን አይክፈቱ፡፡
ያልተለመደ ድምጽ፦ በስልክ ንግግርዎ መሐል የማስተጋባት፣ የእንቅስቃሴ ወይም የሚቅጨለጨል ድምጽ መኖር አለመኖሩን ይከታተሉ፤ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ድምጾች በሞባይልዎ የሚከሰቱት ከጠለፈው ሰው መሳሪያ ስለሚሆን ንግግርን ማቋረጡ ይመረጣል፤ ወጪ፦ በየጊዜው የሚያወጡትን የሞባይል ወጪ ልብ ይበሉ፡፡ በክፍያ ላይ ከፍተኛ ወጪ ከገጠመዎ ይሕም ሌላ የመጠለፍ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡
የመንግስት ቴሌኮም የማይቆጣጠራቸው የሜሴጅና የስልክ ጥሪ አገልግሎቶች (ማለትም እንደ ስካይፕ እና ቫይበር የመሳሰሉት) ያለመጠለፍ ዋስትናቸው እጅግ ደካማ መሆኑን ያጢኑ፡፡ ይሕ ማለት ግን ሌሎች አስተማማኝ የስልክና መልዕክት አገልግሎት የለም ማለት ባለመሆኑ የተሻለ ጥራት ያላቸውን ይምረጡ፡፡
የሞባይል ደንበኞቹ ከ42 ሚሊየን ማለፋቸውን፣ ኢንተርኔት እና ዳታ ተጠቃሚው ደግሞ 12.4 ሚሊየን መድረሱን ያሳወቀው ኢትዮ ቴሌኮም በ2008 ግማሽ ዓመት ያልተጣራ 10.09 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡ የኬንያ የሞባይል ሽፋን ከሕዝቧ 87 %፣ የኡጋንዳ 52 %፣ የታንዛንያ 67 % መሆኑን የገለጸው budde.com ድረ ገጽ በኢትዮጵያ ከ34 % አለመሻገሩን ያሳያል፡፡ ከብዙዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተወዳዳሪ አለመሆኗንም ይጠቁማል፤ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ድረ ገጽ ባለፉት 6 ወራት በ141 ሰዎች ብቻ መጎብኘቱን የሚያሳየው ከኢትዮ ቴሌኮም የተገኘው መረጃ… ስለ ሃገሪቱ ኢንተርኔት አጠቃቀም የሚያስተላልፈው መልዕክት አያጣም፡፡