አቶ ማሞ፣ የዘመናይና የእስከዳር አባት፣ የወ/ሮ ከልካይ ባለቤት፣ አንድ ወፍጮ ቤት አላቸው። እህልም ይነግዳሉ። ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ እዚያው ገዝተው እዚያው የሚያስፈጩ ደምበኞች ሞልተዋል። አቶ ማሞ በሰፈሩ ተወዳጅ ናቸው። ተወዳጅ ያደረጋቸው ደግሞ ምርቃታቸው ነው። ምርቃቶቹ በቄንጥ የተደረደሩ ቃላት ሳይሆኑ 50 ኪሎ ጤፍ ላይ ሁለት ወይም ሶስት ኪሎ መጨመራቸው ነው።
“እጅ አጠረኝ …” ላለ ጎረቤት ደግሞ መልሳቸው፤
“ምን ችግር አለ! ሲያገኙ ይከፍላሉ …” ነው። የተበጠሰ ቺንጋ እየቀየሩ፤ መፋቂያ የተሰኩባቸውን ጉራማይሌ ጥርሶቻቸውን በፈገግታ ብልጭ እያደረጉ።
አቶ ማሞ ሃብታም አይደሉም። ድሃም አይደሉም። የሚያገኙት ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ይበቃቸዋል። ያቶ ማሞ መኖሪያ ቤትና ወፍጮ ቤት የተያያዘ ነው። አጥር ነው የሚለየው። ሌሊት ወፍጮ ቤቱ ሲዘጋ እንዳይላሉ የሚባለው፤ ቀኑን ሙሉ ታሥሮ የሚውለው ውሻቸው፤ ከመኖሪያ ግቢያቸው ይለቀቅና የወፍጮ ቤቱ በረንዳ ላይ ተኝቶ ሲጠብቅ ያድራል።
የሰፈሩን አቧራ ነፋስ በሚያቦንበት አንድ ሾዳዳ ቀን አቶ ማሞ ደብዳቤ ደረሳቸው። ትዕዛዙ የተንዛዛ መግቢያ አለው። መደምደሚያው ግን አጭር ነው።
“መኖሪያ ቤትዎን ለቀው እንዲወጡ እናሳስባለን። በወፍጮ ቤቱ ውስጥ ያለውን፤ ማንኛውንም ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት እንዲያወጡና ወደ ሚዘጋጅሎት ሥፍራ እንዲያዛውሩ በጥብቅ እናሳስባለን። መኖሪያ ቤትዎና ወፍጮ ቤቱ የሚይዙትን ሥፍራ የባቡር ሃዲድ ይዘረጋበታል፤ ባቡርም ይሄድበታልና።”
የሚዘጋጅላቸው ሥፍራ መቼ እና የት እንደሆነ አልተጠቀሰም ነበር። ከደብዳቤው ግርጌ ፊርማ አለ። ከፊርማው ግርጌ፣
“ልማትና እድገት እንደ ሰደድ እሳት ናቸው። የሚገታቸው ሃይል የለም!” የሚል ይነበባል።
ከጥቂት ወራት በኋላ ያቶ ማሞ የመኖሪያ ቤትና ወፍጮ ቤት ላይ ግሬደር ሄደበት። ሃዲዱ ሲዘረጋና ባቡር ሲሄድበት ሳይታይ ግን አምሥት አመታት አለፉ። ሃዲዱ በሌላ መሥመር ተዘረጋ። በቻይናዊ የሚነዳም ባቡር ይሄድበት ጀመር።
ዛሬ እንዳይላሉ ግሬደር ያፈረሰው ቦታ፤ ድሮ ወፍጮ ቤት ቆሞበት የነበረው ሥፍራ፤ እየሄደ ያድራል። ቀኑን ሰፈር ውስጥ ሲዞር ውሎ። ወ/ሮ ከልካይ በየሃብታሙ ቤት እየሄዱ እንጀራ ይጋግራሉ። ዘመናይና እስከዳር ቦሌ አካባቢ ዘመናዊ ካፌዎች ውስጥ ያስተናግዳሉ። አቶ ማሞ ደግሞ ቻይናዊ የሚነዳውን ባቡር እያዩ ብቻቸውን ሲያወሩ ይውላሉ።
“ልማትና እድገት እንደ ሰደድ እሳት ናቸው። ይፋጃሉ!” ያሾፋሉ። “እኔና የምንሊክ ሃውልት የትም ወድቀን መቅረታችን ነው?” ያክሉበታል።
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
<!–
–>
The post “ባቡር ይሄድበታል” appeared first on Medrek.