[ክቡር ሚኒስትሩ የሚያስገቡት ዕቃ ኬላ ላይ ተይዞባቸዋል፡፡ ሚስታቸው ደወሉላቸው]
– ሰላም ዋልሽ?
– ምን ሰላም አለ?
– ምን ሆንሽ ደግሞ?
– ምን የማልሆነው ነገር አለ?
– ጠዋት ሰላም አልነበርሽ እንዴ?
– የዚህ አገር ሰላም እኮ እንደ ስቶክ ኤክስቼንጅ ይወጣል ይወርዳል፡፡
– ሴትዮ አትሳሳቺ፡፡
– እንዴት ባክህ?
– በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት አገር የትም የለም፡፡
– አትቀልድ ባክህ፡፡
– እውነቴን ነው፡፡
– አሁን የምነግርህ ዜና ሰላምህን ይነሳህ የለ እንዴ?
– ምንድን ነው እሱ?
– ዕቃው ተወረሰ?
– ልጆቼ እያሉ ማን ነው የሚወርሰኝ?
– መንግሥት ነዋ፡፡
– መንግሥት እኮ እኔ ነኝ፡፡
– ለማንኛውም አሁን ስልክ ተደውሎልኝ ነበር፡፡
– ማን ነው የደወለልሽ?
– ዕቃው ተወረሰ ብለው ነው የደወሉልኝ፡፡
– የትኛው ዕቃ?
– ሳሙናና ዲተርጀንት የጫኑት መኪኖች ተይዘዋል፡፡
– ብረት የጫኑትስ?
– እነሱ አልተያዙም፡፡
– ሞባይል የጫኑትስ?
– እነሱም እስካሁን አልተያዙም፡፡
– እፎይ፡፡
– እፎይ ትላለህ እንዴ?
– እነዚህስ ተይዘው ቢሆን ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር ብዬ ነዋ፡፡
– ቂሊንጦ ነበራ የሚውጥህ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የኬላው ኃላፊ ጋ ደወሉ]
– ማን ልበል?
– ጭራሽ ማን ልበል ትለኛለህ?
– የደወልከው እኮ አንተ ነህ፤ ማን ልበል?
– ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
– ምን አልከኝ?
– ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
– ውይ ውይ በሞትኩት፤ ወሳኝ ሰዓት ላይ ነው የደወሉት ክቡር ሚኒስትር፡፡
– የምን ወሳኝ ሰዓት?
– ይኸው ሁለት አይሱዙ ዕቃ እንደያዝኩ ነው የደወሉት፡፡
– የምን ዕቃ ነው?
– የሌቦች ዕቃ ነዋ፡፡
– እንዴት?
– ይኸው ታክስ ሳይከፍሉ ሊያሳልፉ ሲሉ እኮ ነው የያዝኳቸው፡፡
– ምንድነው የጫኑት ዕቃ?
– ዲተርጀንትና ሳሙና ነው፡፡
– እ…
– ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር ይቅርታ ቅድም ሌላ ሰው መስሎኝ ነው፤ ይኸው ከመቀመጫዬ ተነስቼ ሰላምታ ሰጥቻለሁ፡፡
– ገና ከወንበርህ ለዘለዓለም አነሳሃለሁ፡፡
– ምን አሉኝ?
– ሰምተሃል፡፡
– እኮ ምን አደረግኩ?
– ያደረግከውንማ ታውቃለህ፡፡
– ዲተርጀንትና ሳሙና ስለወረስኩ?
– ለመሆኑ ገላህን ታጥበህ አታውቅም አይደል?
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ይኼን ሁላ ሳሙና እወርሳለሁ ስትል አታፍርም?
– ታክስ እኮ ስላልተከፈለ ነው፡፡
– እኔ ለሁሉም ነገር ታክስ ከፍዬ እችለዋለሁ?
– የእርስዎ ነው እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
– እና የአንተ ነው?
– ላውንደሪ ቤት ከፈቱ እንዴ?
– እሱን ደግሞ ማን ነገረህ?
– አሁን ምን ይሻላል?
– የዘራሃውን ታጭደዋለህ፡፡
– እንዴት ማለት ክቡር ሚኒስትር?
– ዕቃዬን እንዳሰርክ …
– እ…
– አንተም ትታሰራለህ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
– ምነው ክቡር ሚኒስትር የተቆጡ ይመስላሉ?
– ምን ሰይጣን ብቻ የተሰበሰበበት አገር?
– ምን ተፈጠረ?
– ዕቃዬን ይዘውብኝ ነዋ፡፡
– ማን ነው የያዘብዎት?
– ኬላ ላይ ነዋ፡፡
– የምን ዕቃ ነው?
– ዲተርጀንትና ሳሙና፡፡
– የማን ዕቃ ነው?
– የእኔ ነዋ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር የድግስ ዕቃ ያከራዩ ጀመር እንዴ?
– ምን ማለት ነው?
– ኬላ ላይ ከተያዘብዎት በመኪና የሚገባ ነው ብዬ ነዋ፡፡ ያ ሁሉ ሳሙና ምን ያደርግልዎታል?
– መቼም ልታጠብበት ነው አልልህም?
– ለነገሩ እርስዎ ቢታጠቡም አይፀዱም፡፡
– ከምን?
– ከሙስና!
[አንድ ባለሀብት ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
– ሰላም ወዳጄ፡፡
– እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
– አለሁ አንተ እንዴት ነህ?
– ኧረ ክቡር ሚኒስትር እጅግ እኮ እየተማረርኩ ነው፡፡
– ምን አማረረህ?
– ምን የማያማርር ነገር አለ ብለው ነው?
– አንተ እኮ ደረጃ አንድ ግብር ከፋይ ነህ፡፡
– ለዛውም ዋንጫ ተሸላሚ እንጂ፡፡
– በዚህኛውም ዓመት ደግመህ ዋንጫውን ከወሰድከው እኮ ሐትሪክ ነው የምትሠራው፡፡
– ምን ዋጋ አለው ክቡር ሚኒስትር?
– ዋንጫውን ታስቀረዋለሃ፡፡
– አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ሆነሃል?
– እኔ በቃ የመልካም አስተዳደር ችግሩን አልቻልኩትም፡፡
– እንዴት ማለት?
– ሠራተኞቼ አቅተውኛል፡፡
– ምን አደረጉህ?
– ግብር አይከፍልም ብለው ይጠቁማሉ፡፡
– ለምን?
– ምቀኝነት ይዟቸው ነዋ፡፡
– እሺ፡፡
– በዛ በኩል የእናንተ ሰዎች ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ይሉኛል፡፡
– ምቀኞች በላቸው፡፡
– በጐን ሠራተኞቼ ፍርድ ቤት ሲያመላልሱኝ ነው የሚውሉት፡፡
– ምን ሆንኩ ብለው?
– እየተበደልን ነው ብለው ነዋ፡፡
– ወይ ጣጣ፡፡
– እና ክቡር ሚኒስትር እኔ በጣም ተማርሬያለሁ፡፡
– ቆይ ተረጋጋ፡፡
– ፍትሕ አጥቻለሁ ነው የምልዎት፡፡
– መላ አለው ስልህ፡፡
– እኔ ፍርድ ቤትም መመላለስ ሰልችቶኛል፡፡
– እኔ አሪፍ መፍትሔ አለኝ፡፡
– ምን ክቡር ሚኒስትር?
– በራስ ለምን አታቋቁምም?
– ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
– እስር ቤቱንና ፍርድ ቤቱን!
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
– ሰው ይፈልግዎታል፡፡
– የምን ሰው?
– አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ነው ይላል፡፡
– ተራ ሰው አደረግሽኝ እንዴ መንገደኛው ሁሉ የሚያገኘኝ?
– አይ ክቡር ሚኒስትር አጣዳፊ ጉዳይ ገጥሞዎት ነው፡፡
– ሴትዮ ሥራ ላይ ነው ብለሽ አባሪልኝ፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ባለጉዳዩ መግባት እንደማይችል ብትነግረውም አልፏት ገባ]
– ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ፈልገህ ነው?
– መግባት አትችልም ብላኝ ነበር፣ ግን ጉዳዬ አጣዳፊ ስለሆነብኝ ነው፡፡
– በጥበቃ እንዳስወጣህ ፈልገህ ነው ታዲያ?
– አይደለም ክቡር ሚኒስትር አንዴ ያድምጡኝ፡፡
– ምንም አላዳምጥም፡፡
– ችግር እየፈጠረ ያለው እኮ አለማዳመጥዎት ነው፡፡
– እሺ ምንድን ነው ችግርህ?
– እኔ ሳሙና አስመጪ ነኝ፡፡
– አንተ ነሃ ተፎካካሪዬ፡፡
– አንዳንድ ነጋዴዎች ታክስ ሳይከፍሉ እያስገቡ ከገበያ እያስወጡን ነው፡፡
– እና ምን ላድርግልህ እኔ?
– መንግሥት ጣልቃ ይግባልንና ይቆጣጠራ፡፡
– ሰውዬ ታመሃል፡፡
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ይኼ እኮ ነፃ ገበያ ነው፡፡
– እሱንማ አውቃለሁ፡፡
– ስለዚህ መንግሥት ጣልቃ አይገባም፡፡
– ለነገሩ እርስዎ በደንብ ጠልቀው መግባትዎን ሰምቻለሁ፡፡
– ምን ውስጥ?
– ኮንትሮባንዱ ውስጥ!
[የክቡር ሚኒስትሩ የእህት ልጅ ደወለላቸው]
– ሄሎ ጋሼ፡፡
– እንዴት ነህ ታዳጊው ባለሀብት?
– ኧረ ጋሼ አላሠራ አሉኝ እኮ?
– እነማን?
– የእናንተው ሰዎች ናቸዋ፡፡
– ምን አደረጉህ?
– ይኸው ሱቄን አሸጉት፡፡
– ለምን ተብሎ?
– ሕገወጥ ነህ ብለው ነዋ፡፡
– የሱቪኒር ዕቃ መሸጥ ማን ነው ሕገወጥ ያደረገው?
– አይ ያው በጐን ዶላር እሸጥ አይደል?
– ዶላር እጥረት ስላለ አይደል እንዴ የምትሸጠው? ማን ነው እሱንስ ቢሆን ሕገወጥ ያደረገው?
– እሱማ ጋሼ ለባንክ ብቻ የተፈቀደ ሥራ ነው፡፡
– አንተ ካደግህ እኮ ባንክ መሆን የምትችል ልጅ ነህ፡፡
– ብቻ ጋሼ እኔን ያሳሰበኝ የልጆቼ ጉዳይ ነው፡፡
– እነሱማ ምን ይሆናሉ?
– እንዴት አይሆኑ?
– በስማቸው ያስቀመጥክላቸው ገንዘብ እኮ እነሱንም ባንክ መሆን ያስችላቸዋል፡፡
– እ…
– እንደውም ባንኮች መዋሀድ አለባቸው እየተባለ ስለሆነ አንድ ላይ ተዋህዳችሁ ትልቅ ባንክ መመሥረት ነው፡፡
– እዚህ አገር ግን ሠርቶ ማደግ ቀረ ማለት ነው?
– እሱ ቀርቶ እኮ ሌላ ስትራቴጂ መጥቷል፡፡
– ምን የሚሉት?
– ሰብስቦ መጥፋት!
ምንጭ – ሪፖርተር