አሁን ኢትዮጵያ ለደረሰችበት አሳሳቢ ደረጃ ዋናውና ብቸኛው መፍትሔ ሰላማዊ ዕርቅ መሆኑ በአገር ውስጥና በውጪ ልዩ ትኩረት እየሳበ መሆኑ ተሰማ። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢህአዴግ በራሱ ችግር በየጊዜው ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱን፣ ይህንን ቅራኔ መፍታት ካልቻል መንገዱ የውድቀት እንደሚሆን አስጠነቀቁ። ሕዝብ በአፉና በእጁ እየገፋን ነው አሉ።
ለጎልጉል የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው በቅርቡ የተጀመረውን “የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” ተከትሎ የዕርቅ ሃሳብ አሁን ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ አማራጭ የሌለው እንደሆነ እየተጠቆመ ነው፡፡ በተለይ በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተከታታዮችና ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ጉዳዩ ድጋፋቸውን የሚሰጡበት እንደሆነ መረጃው አመልክቷል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተመሠረተው ምክርቤት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በመጠቆም ስለምክር ቤቱ ዓላማ ከተረዱ በኋላ “አሁን አገሪቱ ለገባችበት ስጋት ብቸኛው መፍትሔ እርቅ እንደሆነ” እንደሚያምኑና ወቅቱን ጠብቀው ድጋፋቸውን በግልጽ እንደሚሰጡ መረጃው አመልክቷል።
“የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” ምሥረታን አስመልክቶ መግለጫ ያሰራጨውን ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ስለ ጉዳዩ የሚያውቀው ካለ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጠይቀን፤ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ይኽው “የኢትዮጵያ የዕርቅና ርትዓዊ ፍትሕ ምክርቤት” መመሥረቱን ጠቁሞ አኢጋን ሰሞኑንን ባሰራጨው መግለጫው ላይ “… በግድያ እና በብቀላ ዑደት ውስጥ ባለችው አገራችን ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ሊያመጣ የሚችል ብቸኛው ተስፋ ከዚህ የብቀላ አዙሪት በመውጣት ይቅርታን፣ ዕርቅንና ርትዓዊ ፍትሕን መፈለግ ሊኬድበት የሚገባ አዲሱ መንገድ መሆኑ በየጊዜው ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ከዚህ ምክርቤት ምሥረታ ጋር አብሮ የሚጠቀስ እውነታ ነው” ሲል ምክር ቤቱ የተወለደበትን ጊዜና ወቅት ትክክለኛነት አውጇል።
መግለጫው አያይዞም “… በዘር በተከፋፈለች አገራችን ተግባብቶ ለመኖር የሚችል ኅብረተሰብ ለመመሥረት የሚቻለው እያንዳንዳችን ከታገትንበት የዘር፣ የጎሣ፣ የነገድ፣ … ሣጥን በመውጣት ሌሎችን እንደራሳችን በመመልከትና ከዘር ወይም ከማንኛውም ልዩነታችን በፊት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ መስጠት የሚያግባባ ሃሳብ የሆነበት ደረጃ ላይ” መደረሱንም አመልክቷል።
“… በአገራችን ዕርቅ፣ የጉዳት ፈውስ፣ ርትዓዊ ፍትሕ በሕዝብ መካከል እስካልተደረገ ድረስ የወደፊቱ ኅልውናችን አሁን ካለንበት እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል” የጠቆመው የአኢጋን መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ “ለመተማመን እንነጋገር” በሚል መሪ መፈክር ያካሄደው ተከታታይ ስብሰባ ለዚህ የምክርቤት ምሥረታ በዋንኛነት የሚጠቀስ ግብዓት እንደሆነ አስረድቷል፡፡ መግለጫው ይህንን ሲያስረዳም “መነጋገር ወደ መደማመጥ፣ መደማመጥ ወደ መተማመን፣ መተማመን ደግሞ ወደ ዕርቅ ይመራናል” በማለት እጅግ ለተወሳሰበው የኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ሁሉም ሊያስተውለው በሚችል መንግድ አስረድቷል፡፡ “ከዚህ አንጻር በዚህ ምክርቤት ውስጥ መካተት የማይችል አይኖርም” ያለው መግለጫ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወደ መተማመን የሚያደርስ ንግግር እንዲጀምር” ምክርቤቱ ለሁሉም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ሰሞኑን ለኢህአዴግ ጉባኤ የስድስት ወር ሪፖርት ያቀረቡት አቶ ሃይለማርያም እርስ በእርሱ በሚጋጨው ዲስኩራቸው ስለመታረቅ ተናግረዋል። እንደሳቸው አባባል በፈተና ውስጥ የማለፍ ልዩ ብቃት ያለው ኢህአዴግ፣ አሁን ያጋጠመውን ፈተና እንደሚሻገረው ሲያስገነዝቡ “ሌላ አካል ላይ ጣታችንን ከመቀሰር ችግሩ የራሳችን መሆኑን አስምረን ማለፍ አለብን” በማለት ነበር። ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ስለማይሰጥ ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባቱን አቶ ሃይለማርያም ሳይሸሽጉ በይፋ ተናግረዋል።
አቶ ሃይለማርያም ለተፈጠሩት ችግሮችና ለተነሳው ተቃውሞ ሌላ ሃላፊነት አለመውሰድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ጠቁመዋል። “… ሌላ ምክንያት መፍጠር ቀዳሚው የውድቀት መንገድ ነው” በማለት የህዝብን ጥያቄ መልሶ ከሕዝብ ጋር መታረቅ የድርጅታቸው ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ አስረድተው፣ ህዝብ ስርዓቱን በአፉና በእጁ እየገፋ መሆኑንን አምነዋል። ከትግራይ እስከ ደቡብ ክልል ጫፍ ተመሳሳይ ችግር እንዳለ አውስተው ችግር ባለበት ችግሩን በመፍታት፣ ችግር ባልተከሰተበት አስቀድሞ ለህዝብ ጥያቄ መልስ በመስጠት ከህዝብ ጋር እርቅ መፍጠር አንገብጋቢ መሆኑንን አመላክተዋል። አቶ ሃይለማርያም ንግግራቸውን ተከተሎ በርካታ ወቀሳ ቢሰነዘርባቸውም፣ “ካሁን በኋላ አርሶ አደሩም ሆነ የከተማው ነዋሪ የነቃ ስለሆነ በትከሻው ላይ ተጣብቆ መኖር አይቻልም” ማለታቸው እንደ እውነት ተወስዷል።
“አቶ ሃይለማርያም ራሳቸውን ሆነው ችግሩን በተረዱበት መጠን አይናገሩም” ሲሉ የሚተቹ አንደበታቸው ነጻ መሪ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ንግግራቸውንም ጉልበት አልባ ይሉታል። ከሕዝብ ጋር መታረቅ ሲሉ ስለ ምን ዓይነት ዕርቅ እንደሚናገሩ ይጠይቃሉ። “ባግባቡ ጥያቄ አቀርቦ አልተመለሰለትም” የሚሉት ሕዝብ ተገድሎና እየተገደለ፣ ታሰሮና እየታሰረ፣ ተደብድቦና አሁንም እየተደበደበ፣ ተስድዶና እየተሰደደ ባለበት ሁኔታ፣ አገሪቱ በወታደራዊ አስተዳደር ሥር ወድቃ፣ እንኳን ተራው ህዝብ እሳቸው ጠ/ሚኒስትር ሆነው በነጻነት ስራቸውን መስራት በማይችሉበት አገር ምን አይነት እርቅ ነው ከህዝብ ጋር የሚደረገው? ሲሉ ኢህአዴግን የሚመራው ህወሃት ስለ እርቅ በቅጡ ሊያስብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ።
ስለ መታረቅ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው። ሹመታቸውና አሿሿማቸው የራሱ ጣጣ ቢኖረውም የኦርቶዶክስ እምነት የበላይ የሆነው ሲኖዶስ “የአገሪቱ ችግር አሳሰበኝ” ሲል ድምጹን አሰምቷል። ከራሱ ከኢህአዴግ ወገኖች የዕርቅ ፍላጎት ያላቸው እንዳሉ ጎልጉል መረጃ አለው። ህወሃት አካሄዱ ያልጣማቸውና በስማቸው ወንጀል የሚፈጸምባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በተመሳሳይ ዕርቅ እንዲወርድ ይወዳሉ። ትልቁ ችግር ያለው በዝርፊያ የከበሩት አካላት ዘንድ ነው። ለነሱ ይመስላል “ይድረስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጉልበት ላላችሁ ሁሉ” በሚል ርዕስ ፕሮፌሰር መስፍን ሰሞኑንን “እግዚር በቀዳዳ ያያል” ሲሉ የልጅነት ወግ አዘል ከባድ መልክት አስተላለፈዋል።
“…የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ዓላማችሁ ምንድን ነው? እስከዛሬ ድረስ በየትም አገር በሰማይ ጠቀስ መቃብር ውስጥ የተጋደመ ባለሥልጣን የለም፤ ደግሞስ ሰማይ ጠቀስ መቃብር ካስፈለገ ለአንድ ባለሥልጣን ከነቤተሰቡ ስንት ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ ስንት ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ያስፈልጉታል … እስር ቤቶችን ሁሉ ዝጉ፤ የዘጋችሁትን አንደበት ሁሉ ልቀቁ፤ ያፈናችሁትን አእምሮ ሁሉ ለነጻነት አብቁት፤ ጭካኔን በርኅራኄ፣ ጉልበትን በእውቀት፣ ዱላን በክርክር፣ ቁጣን በፍትሐዊነት እየለወጣችሁና እያበረዳችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ታረቁ፤ በተለይ ከኢትዮጵያ ወጣት ጋር ልብ ለልብ ተገናኙ፤ ነገ የወጣቱ ነው”፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
<!–
–>