Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ኦባማ “ልማታዊ” ጎብኚ?!

$
0
0

ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንትና አጃቢዎቻቸው ለሁለት ቀን አዳር ለሆቴል ያወጡት ወጪ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ተገለጸ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት በአንድ ሆቴል ብቻ እንደሚደረግ አስቀድሞ የተነገረ ቢሆንም የአስተዳደራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ አጃቢዎቻቸውና ሌሎች የደኅንነት ሠራተኞች በአራት ሆቴሎች ውስጥ አርፈው እንደነበር Weekly Standard የክፍያ ሰነዶችን በማስደገፍ ይፋ አድርጓል፡፡ አስቀድሞ የተለቀቀው መረጃ እንደሚያመለክተው የኦባማ ቡድን በሒልተን ሆቴል ቆይታ እንደሚያደርግና ወጪውም ብር 8,491,127.81 ወይም በግምት ዶላር $ 412,390.86 መሆኑን የሚያሳይ የኮንትራት ውል መፈረሙን ነበር፡፡

hotels

ከአሜሪካ መንግሥት የተጠያቂነት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የፕሬዚዳንቱ ቡድን ለሁለት ቀናት ያረፉት በአንድ ሆቴል ሳይሆን በአራት የተለያዩ ሆቴሎች ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ለተጠቀሰው የሒልተን ሆቴል ወጪ 1,280 የመኝታ ክፍሎች ተከራይተዋል፡፡ 22 ማዞሪያ ከዋሪት ህንጻ ፊትለፊት በሚገኘው ካፒታል ሆቴልና ስፓ (Capital Hotel and Spa) ለ1,000 ክፍሎች ብር 3,673,950 ወይም በዶላር $178,433.71፤ ካዛንቺስ በሚገኘው ኢሊሊ (Elilly) ሆቴል ለ120 ክፍሎች ብር 5,100,480 ወይም በዶላር $246,877.06፤ እንዲሁም በሸራተን አዲስ ለ1,236 ክፍሎች ብር 10,050,826.13 ወይም በዶላር ግምት $488,141.14 ወጪ መደረጉ ተዘግቧል፡፡ ይህም ለአራቱ ሆቴሎች በድምሩ በዶላር ግምት 1,325,841 ወይም በብር 27,771,383.94 መሆኑ ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡ ክፍያው አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስፈጻሚነት በውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) መከናወኑ መረጃው በግልጽ ያስረዳል፡፡

hilton elilly capital sheraton

ከፕሬዚዳንቱ ቡድን ጋር አብረው የተጓዙ በፍሎሪዳ ጠቅላይግዛት የሚገኙ ነጋዴ ለWeekly Standard እንዳሉት “(በአዲስ አበባ) አብሬአቸው ስሰራ የነበሩ በከተማዋ የሚገኙ አሜሪካውያን እንደነገሩኝ ኦባማ አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ሸራተንን እንዳለ ገዝቶት ነበር”፡፡ ኦባማ በሸራተን ለመቆየታቸው ደግሞ አብሯቸው የተጓዘው ፎቶ አንሺ Pete Souza የምስል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡

ይህ የሆቴል ወጪ ብቻ ሲሆን ከዚህ ሌላ ለእጅ ስልክ ቀፎዎች ግዢ $7,540 ዶላር ወጪcell መደረጉን አብሮ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ ስልኮቹ የተገዙት በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ኩባንያ ከውጪ ድርጅት ጋር ባደረገው ኮንትራት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ ስልኮቹን የሸጠው ኩባንያ ማንነት ተጠይቆ ቤተመንግሥቱ (ኋይት ሃውስ) መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ ስልኮቹን ማን እንደተጠቀመባቸው ከጉብኝቱ በኋላ ደግሞ የት እንደደረሱ አይታወቅም፡፡

ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙ ወቅት የወጣው ይህ ወጪ የሆቴል ኪራይና የስልክ ብቻ ሲሆን ሌላ እጅግ በርካታ የሆነ ከጉብኝቱ ጋር የተደረገ የደኅንነት፣ የጉዞ፣ የግንኙነት፣ የሚሊታሪ፣ ወዘተ ወጪዎችን የሚጠቀልል አይደለም፡፡

በሆቴሉ ወጪ ዙሪያ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንዳሉት “ካንበት ሁኔታ አኳያ ስተረጉመው ኦባማ ልማታዊ ጎብኚ ናቸው፤ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው አንድ ሁለቴ ጉብኝታቸውን ቢደግሙ የባንክ ዕዳችንን ከፍለን ጨርሰን ትርፋማ እንሆን ነበር፤ ሕገመንግሥታቸውን ቀይረው ለሦስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ቢወዳደሩ መቶ በመቶ እደግፋቸዋለሁ፤ መቶ በመቶ እንደሚያሸንፉም እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡ (የገጽ ፎቶ: Pete Souza)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

<!–

–>

The post ኦባማ “ልማታዊ” ጎብኚ?! appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles