Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ኦህዴድ ሳያገግም፤ ብአዴን ሊደገም?

$
0
0

ኢትዮጵያን በተገንጣይ ስም የሚመራው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት፣ የገጠመው ቀውስ እየተለጠጠበት ነው። ኦህዴድ አደረጃጀቱ ሊጠገን በማይችልበት ሁኔታ ተናግቶበታል። ይኽው ወረርሽኝ ወደ ሌሎች ገባር ድርጅቶች መስፋፋቱ የማይቀር ቢሆንም ብአዴን ውስጥ ቀውስ ስለመነሳቱ መረጃዎች ከቀድሞው በላይ ጎልተው እየወጡ ነው።

በ1997 ምርጫ ኢህአዴግን ከውድቀት ጉድጓድ ያወጣው ኦህዴድ፣ ህወሃት በአንጃ ተቧድኖ ሲባላ የመለስን ወገኖች የታደገው ብአዴን አሁን ለህወሃት መከራ ሆነውበታል። አጋር የሚባሉት ድርጅቶችም ውስጥ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳሉ የራሱ የህወሃት መገናኛዎች እየመሰከሩ ነው።

የችግሩ አሳሳቢነት ቀላል ባለመሆኑ ኦሮሚያና ጋምቤላ ተሸንሽነው “በጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር” ሥር ወድቀዋል። ይህንኑ እውነት አሁንም የራሱ የህወሃት ልሳኖች አምነው ይፋ አድርገውታል። አንድ ወጥ አገር በነጻ አውጪ ቡድን፣ በፌዴራል መዋቅር፣ በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር፣ በሱዳን ሚሊሺያ፣ ወዘተ የተዘበራረቀ አመራር ላይ መውደቋ የወደፊቱን የመለስ “ራዕይ” አመላካች ስለመሆኑ አስተያየት እየተሰጠ ነው።

ነገሮች እንደዚህ በጦዙበት ወቅት “የታላቋ ትግራይ” ድንበር ሙሉ የሁመራን ለም ምድር የሚያጠቃልል፣ ጠገዴንና ወልቃይትን የሚውጥ፣ እንዲሁም ኤርትራ ግዛት ጠልቆ የሚገባ መሆኑ ቦታና ስም ተዘርዝሮ ይፋ መሆን ጀምሯል። በሌላ ጎኑ ኦህዴድ ውስጥ “ህዝብ ለምን አመጸ፣ የጸጥታ ሃይሉ እንዴት ከጃችን ወጣ? የታች መዋቅሩ እንዴት ፈረሰ? ድርጅታዊ ሠንሰለቱ እንዴት ተበጠሰ? ታማኝነትና ጠባብነት …” ማለቂያ የሌለው ግምገማ  እየተካሄደ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ  የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚና የኦህዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፣ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኩቹ ለጊዜው ከተመደቡበት ያገለጋይነት ሹመት ተነስትው ቀለበት ውስጥ እንዳሉ ተሰምቷል። ሹም ሸሩ ቀጣይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

በህወሃት አደረጃጀት “ጸጥታ” የሚለው ሹመት የስለላው ምሶሶ ዘርፍ ነው። የኦህዴድ የፀጥታ ሃላፊ ተነሱ ማለት ስለላው ተናግቷል ወይም እንደ ቀድሞ መረጃ አያገኝም ማለት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ አንድ ለአምስት የሚባለው የስለላ መዋቅር ውሃ በለቶታል ማለት ነው። አሁን እንደ አዲስ ቢደራጅ የሚተገበረው ቀድሞ ታች ባሉት አመራሮችና ካድሬዎች ላይ በመሆኑ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም በማለት ስለ አደረጃጀቱና ስለ ወቅቱ ግለት የሚያውቁ እየገለጹ ነው።

በየቀበሌው ድምጻቸውን ያሰሙ ወገኖች ተገልለዋል፤ በሺህ የሚቆጠሩ ታስረዋል። የተሰደዱ፣ ቀያቸውን ጥለው የኮበለሉ፣ ዱር ያሉ፣ ከዚህም በላይ ሃዘን ያደቀቃቸውና የሚጠዘጥዛቸው ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ የወንዝ ልጆች፣ ኦሮሞዎች፣ ኢትዮጵያውያን አዝነዋል። የቂም ቋጠሯቸው ጠብቋል። የፈሰሰው ደም ከሚያንዘፈዝፋቸው  ክፍሎች መካከል የታችኛው ካድሬና አመራር በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፍ ነው። በዚህ መነሻ ህወሃት እነዚሁ ዜጎች ላይ ታዛዥ ሃላፊ ቀይሮ እንደ ቀድሞው ልፈንጭ፣ ለጋልብ፣ ልፍለጥ፣ ልቁረጥ ቢል አይሳካለትም ሲሉ እነዚሁ ክፍሎች ያብራራሉ።

ምሳሌ ሲያነሱ አርሲ የሆነውን ይጠቀሳሉ። የኦሮምያ ፈጥኖ ደራሽ አባል ወገኖቹን ሊገድል የመጣውን የአጋዚ ቅጥረኞችን መሳሪያ አዙሮ ረሸነ። አስራ አንዱን ሲገድል አንዱን አንገቱ ላይ ቆሞ ነው እያቀራራ ጥይት ያዘነበበት። ተቺዎች እንደሚሉት የዚህ ፖሊስ ተግባር መጪውን የሚያመላክት ነው። ህወሃት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በብሄራቸው ላይ የሚፈጸም ግፍ ያማቸዋል። በዝርፊያ የበሰበሱትን ሳይጨምር።

የበታቹ ካድሬ የዝርፊያ ጉዳይ አያሳስበውም። አብዛኛው ደግሞ ይህ የህብረተሰብ ከፍል ነው። ባንድ ግምገማ ላይ አንድ የህወሃት ሰው ስለ ሙስና አንስተው ሲገመግሙ አንድ ከንቲባ ተነስተው “እርስዎ ቤተሰቦችዎን እየላኩ መሬት ይወስዱ አልነበረም” ሲል ሞግተዋቸው እንደነበር የሚያስታውሱ “አሁን የበላዩ የበታቹን ሲገመግም አዳራሹ በሽሙጥ ይሞላል፤ ሌላውን ለመወንጀል ንጹህ ጀርባ ያላቸው ስለሌሉ የሚታየው ሁሉ ከበሰበሰ እንቁላል ጫጩት የመከጀል ያህል ነው” በሚል ህወሃት ብስባሽ ላይ ሆኖ እንደሚወራጭ ያስረዳሉ።

በኦሮሚያ መዋቅር ፈርሶ ሽማግሌዎች መሬት ለተወሰደባቸው ሲያከፋፈሉ ነበር። አጋርፋ አካባቢ ይህ ተፈጽሟል። ይህንን ህዝብ መልሶ ማደራጀት ጅልነት እንደሆነ የሚጠቁሙ ክፍሎች ህወሃት በቅጡ አስቦና መክሮ ወደ ትክክለኛው መፍትሄ ሊመጣ እንደሚገባው ይመክራሉ። አያይዘውም በሌሎች የህብረተሰብ ከፍሎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ አድሮም ቢሆን ዋጋ ስለሚያስከፍል በስማቸው የሚፈጸመው ወንጀል ይቆም ዘንድ የትግራይ ንጹሃን ድምጻቸውን ሊያሰሙ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አማራ ክልልም ቢሆን የተሳከረ ችግር ስለ መኖሩ ህወሃት የማይክድበት ደረጃ ላይ ነው። ባለፈው ሳምንት የትግራይ ክልል ፐሬዚዳንት የአማራ ክልል አስተዳዳሪን ውይይት ላይ “አማራን ትጥቅ አስፈታ” የሚል ትዕዛዝ አዘል ንግግር ሲናግሩ “የምን ትጥቅ ነው የማስፈታው? አንተ ግምጃ ቤት ከፍትህ ለትግራይ ህዝብ መሳሪያ እያደልክ” የሚል መልስ እንደሰጡ በተለይ ለጎልጉል መረጃ የላኩ አስረድተዋል።

የወልቃይትን ጉዳይ ከህወሃት ፍላጎት አንጻር የብአዴን ስራ አስፈጻሚ እንዲቀበልን አቋም እንዲይዝ ትዕዛዝ ቢሰጥም “በቀጥታ ከህዝብ ጋር የምንገናኘው እኛ ነን፤ ይህንን አንቀበልም፤ ልታስፈጁን ነው?” የሚል ምላሽ ከበታች ካድሬዎች ተሰንዝሯል። እንደ ዜናው አቀባዮች ከሆነ ብአዴን ውስጥ ኦህዴድ ላይ የደረሰው የበታች አመራር መንሸራተት እየታየ ነው።

የብአዴን ማዕከላዊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ፣ ከቅማንት ማኅበረሰብ ማንነት ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግርና የግጭት አፈታት ተግባራትን፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በፀገዴ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግርና በሁለቱ ክልሎች የተደረገውን ምክክር፣ በክልሉ በድርቅ የተጠቁ 2.3 ሚሊዮን ዜጎችን በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለሦስት ቀናት መክሯል ሲል ሪፖርተር ዛሬ ዘግቧዋል።

ሰሞኑን በሁለት የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተወሰደው እርምጃ የተጀመረው ኦህዴድን የማጽዳት ተግባር በርካታ የአመራሮች ላይ ሰይፉን እንደሚያሳርፍ ከወዲሁ የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡ ከሁለት ወር ተኩል በፊት ጎልጉል የኦህዴድ ህወሃት/ኢህአዴግን መክዳት አስመልክቶ በጻፈው የዜና ዘገባ ላይ እስካሁን የተሠራው ጥርነፋም ሆነ የህወሃት የበላይነት የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቀርቶ ኦሮሚያን ለከፋ ችግር እንደዳረጋት ተጠቅሶ ነበር፡፡

ይህ የኦህዴድ ችግር ገና መስመር ሳይዝ አሁን ደግሞ ህወሃት ወደ ብአዴን ላይ ለመዞር ማሰቡና “ትጥቅ” ለማስፈታት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጉዞውን ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል የሚለው አስተያየት የበረከተ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ኦህዴድና ብአዴን አብረው ህወሃትን ብቻውን ቢያስቀሩት የፖለቲካውን አሰላለፍም ሆነ የአገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ ባልታሰበ መልኩ ይቀይረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ (ፎቶ: addisfortune)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles