Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. Feb. 08, 2016)፡- በኢህአዴግ መንግሥት ሙሉ ቁጥጥር ስር ያለውና ጋዜጦችንና መጽሔቶችን የሚያሳመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድረገጽ “አኖን ፕላስ” (AnonPlus) በተሰኙ ያልታወቁ ወገኖች ከቅዳሜ ጥር 28 ቀን ጀምሮ ተጠለፈ (ሐክ ተደረገ)። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ ድረገጹ እንደማይሠራ ለመገንዘብ ችለናል።
ይኸው የሐከሮች ቡድን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ድረገጽ (http://www.ethpress.gov.et/) በመጠቀም የአኖን ፕላስን አርማ እና ማኒፌስቶውን አውጥቷል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ድረገጽ በአሁኑ ወቅት መጎብኘት እንደማይችል ለማረጋገጥ ችለናል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚያሳትማቸው ጋዜጦች ውስጥ አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች በቀዳሚነት ተጠቃሽ መሆናቸው ይታወቃል።
ህወሓት/ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ላለፉት 24 ዓመታት ለፕሮፓጋንዳ ከሚጠቀምባቸውና በህዝብ ገንዘብ ከሚንቀሳቀሱት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል። ላለፉት ሦስት ቀናት ድረገጹ ተመልሶ ለመጎብኘት ያልቻለ ሲሆን፣ ይኽንኑ የጠለፋ ሥራ የሠራው የአኖን ፕላስ ሙሉ ማኒፌስቶ ከዚህ በታች ቀርቧል።