ክተት፡-
“እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትን አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት ለሁሉ ነውና ስለ እኔ ሞት አላዝንም፤ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን የባሕር በር አልፎ መጥቷልና እኔም ያገሬ ከብት ማለቁንና የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልተውህም ማርያምን፤ ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከትተህ ላግኝህ፡፡”
ከድል በኋላ፡-
“(ጥልያኖች) በጥጋባቸው አድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ፡፡ እኔ በድንቁርናቸው ብዛት የእነዚያን ሁሉ ክርስቲን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ “ድል አደረኩዋቸው” ብዬ ደስ አይለኝም” መጋቢት 23፤ 1888 ምኒልክ ለአውሮጳዊው ዲፕሎማት ሙሴ ሸፍኔ ከላኩት፡፡
ምርኮኞችን ሲመልሱ፡-
“… በእጄ ጨብጫቸው፤ በእግሬ ረግጫቸው የነበሩትን እኒህን ምርኮኞች ሳልነካቸው የሰደድኩልህ … በሞኝነት አይደለም፡፡ … ብትታረቁ ድንቅ፤ ጦርነትም ከከጀላችሁ እነዚህንም ጨምራችሁ ኑ፡፡”
ስለዚህ የምኒልክን ውርስ እያስታወስን እንዲህ እንላለን:-
ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ።
በሠራው ወጨፎ ባመጣው እርሳስ
ተፈጠመ ጣሊያን አበሻ እንዳይደርስ።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡