Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

“ለአውሮጳውያን (ስለ ምርጫው ውጤት) ‘ሌክቸር’ አልፈልግም ብዬ ነግሬአቸኋለሁ”

$
0
0

በዑጋንዳ በተካሄደው ምርጫ አገሪቱን ለ30 ዓመት የመሩት ዮዌሪ ሙሰቪኒ ለአምስተኛ ጊዜ “አሸንፈዋል”፡፡ ተቀናቃኛቸው ምርጫው መጭበርበሩንና እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡ አውሮጳውያንና አሜሪካ ምርጫው ዓለምአቀፋዊ ሕግጋትን የጠበቀ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ሙሰቪኒ ዋናው ዓላማቸው እስካሁን ኢትዮጵያን ያላካተተውን የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን መመሥረት እንደሆነና ስለምርጫው ከአውሮጳውያን “ሌክቸር” እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል፡፡

በምዕራባውያን ድለላና ድጋፍ በትጥቅ ትግል ወደ ሥልጣን የመጡት መለስ ዜናዊ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ፖል ካጋሜ እና ዮዌሪ ሙሰቪኒ “አዲስ የአፍሪካ መሪዎች ውልድ (ዘር)” በመባል በቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን እንዳልተሞካሹ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ፍጹም አምባገነኖች ሆነዋል፡፡ መለስ ዜናዊ ሞት ባይቀድማቸው ኖሮ ከሌሎቹ ጋር በመሆን ማቆሚያ የሌለውን ሥልጣናቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ ሌሎቹ ግን ሲያመቻቸው “በምርጫ” ካልሆነም በምርጫና በጠብመንጃ ካልሆነም ምርጫ አልባ በሆነ ስልት አምባገነናዊ አገዛዛቸውን ቀጥለዋል፡፡

uganda museveniቅዳሜ በተደረገው የዑጋንዳ ምርጫ አገሪቱን ለ30 ዓመታት የገዙት የ71ዓመቱ ዮዌሪ ሙሰቪኒ በ61 በመቶ አካባቢ በሆነ ብልጫ “አሸንፈዋል” ተብሎ በአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ተደርጎላቸዋል፡፡ በአገርዓቀፉ ምርጫ ሙሰቪኒ እንደተመረጡ ቢነገርም ከካቢኔያቸው ውስጥ የመከላከያ ሚኒስትራቸውን እና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ጨምሮ 19 ሚኒስትሮቻቸው የፓርላማ መቀመጫቸውን አጥተዋል፡፡ “ለአምስተኛ ጊዜ ተመርጫለሁ” የሚሉት ሙሰቪኒ “በተለይ የገጠሩ ዑጋንዳዊ እኔንና ድርጅቴን ይወዳል” ቢሉም ሕዝቡ በሚደርስበት አፈና እና ጭቆና የምርጫ ትርጉሙንም ሆነ ፍላጎቱን እንዳጣ ይነገራል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ለመመምረጥ ከተመዘገበው 63 በመቶ አካባቢ ለምርጫ እንደወጣ ሲነገር በመዲናዋ ካምፓላ 46በመቶ ያህሉ ብቻ በምርጫው እንደተሳተፈ ተዘግቧል፡፡ የካምፓላ ነዋሪ የሆነውና የሞተር ብስክሌት ታክሲ (ቦዳ) የሚነዳው የ40ዓመቱ ስቲቨን የአስርሺህ ሽልንግ (የሦስት ዶላር) ቤንዚን ቀድቶ ወደ ምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምጽ መስጠት አቅሙ ስላልፈቀደለት ሳይመርጥ እንደቀረ ይናገራል፡፡ በመቀጠልም “(በአጠቃላይ ምርጫው ራሱ) ገንዘብ ማባከን ነው” በማለት መናገሩን ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል፡፡museveni

የሙሰቪኒ የቀድሞ የግል ሃኪም የነበሩትን አሁን ግን ተቀናቃኛቸው በመሆን ለአራተኛ ጊዜ የተወዳደሩት ሐኪም ኪዛ ቤሲግዬ የምርጫውን ውጤት ፈጽሞ እንደማይቀበሉትና ደጋፊዎቻቸውም ይህንኑ አውቀው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የቀድሞውን መሪ ሚልተን ኦቦቴን ከሥልጣን ለማስወገድ በተደረገው ጦርነት የሙሰቪኒ የትግል አጋር የነበሩት የ59ዓመቱ ቤሲግዬ “እኛ እስካልተባበር ድረስ ይህ አገዛዝ መቆየት አይችልም፤ ስለዚህ ይህንን የምርጫ ሌብነት በአንድነት እናውግዝና ከዚህ አገዛዝ ጋር ያለንን ትብብር እናቋርጥ፤ እውቅናም አንስጠው” በማለት ጥሪ አሰምተዋል፡፡Besigye Arrested

የምርጫ ዘመቻ በሚካሄድበት ወቅት ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ የተቀበሉት ሐኪም ባለፈው ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ሦስት ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ሰኞ እለት የምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ ሳለ እንዲሁም ሐሙስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ እንደገና አርብ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ የምርጫው ውጤት ቅዳሜ ይፋ ከመሆኑ በፊት “ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ መድረክ – FDC” የተሰኘው የቤሲግዬ ፓርቲ ጽ/ቤት “የምርጫውን ውጤት ለብቻው ይፋ እንዳያደርግ ለመከላከል” በሚል በፖሊስ ከተወረረ በኋላ ነበር እርሳቸው ለእስር የተዳረጉት፡፡ አሁንም በቁም እስር ይገኛሉ፡፡

ምርጫው ዓለምአቀፋዊ መስፈርቶችን ያሟላ አይደለም በማለት አውሮጳውያንና አሜሪካ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ “(የሙሰቪኒ ተግባር) ሃሳብን በነጻ የመግለጽን ነጻነት ይጻረራል፤ በአገሪቷ ውስጥ የዛቻንና የማስፈራራትን አየር ይፈጥራል” በማለት የአውሮጳ ኅብረት ተናግሯል፡፡ አሜሪካ በበኩሏ የቤሲግዬ መታሰር እንዲሁም በምርጫው የተከሰተው ወከባና እንግልት እንዲሁም ድምጽ የመግዛት ተግባር እንደሚያሳስባት ተናግራለች፡፡ የጋራ ብልጽግና ኅብረት የምርጫ ታዛቢን የመሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ምርጫው “ወሳኝ የዴሞክራሲያዊ መለኪያዎችን እንዳላሟላ” ተናግረዋል፡፡BesigyeArrested demo002

ሙሰቪኒ ለዚህ ሁሉ መልስ ያጠራቸው አይመስሉም፡፡ “(አውሮጳውያን) ተሳስተዋል፤ እንዲያውም ለነዚህ አውሮጳውያን (ምርጫውን በተመለከተ) ከማንም ሌክቸር አልፈልግም ብዬ ነግሬአቸኋለሁ” በማለት የአጸፋ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የአሜሪካ ጉዳይ እንደማያሳስባቸው በአነጋገራቸው እንደምታ የገለጹት ሙሰቪኒ “ሚ/ር ጆን ኬሪ (የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር) ደውለውልኝ ነበር፤ የምርጫን ጉዳይ በተመለከተ ሁሉ ልክ ማስገባቱን እናውቅበታን (ለእኛ ተዉልን) ብያቸዋለሁ” በማለት መናገራቸውን ሬውተር ዘግቧል፡፡

ሙሰቪኒ ለተቀናቃኛቸው የሰጡት ምላሽ ግን ከሁሉም የከረረው ነው፡፡ “ቢሲግዬ ማወቅ የሚኖርበት ነገር ቢኖር ኡጋንዳ ማለት አይቮሪ ኮስት ወይም ኬኒያ ማለት አይደለችም፤ በምርጫ ኮሚሽን ከተካሄደው የድምጽ ቆጠራ ሌላ ትይዩ ቆጠራ እንዲያደርግ አንፈቅድለትም” ካሉ በኋላ ሁኔታው በዚሁ የማያበቃ ከሆነ ቢሲግዬን እስርቤት እንደሚልኩ ዝተዋል፡፡

በቀድሞው የኬኒያ ምርጫ እንደተጭበረበሩ በስፋት የሚነገርላቸው ራይላ ኦዲንጋ በቀጣይ ለሚደረገው አገራዊ የፕሬዚዳንትነት ምርጫ “ትይዩ ቆጠራ” (parallel tallying) ለማድረግ ከጀርመን ኩባንያ ጋር ንግግር እያደረጉ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ በዚህ የትይዩ ቆጠራ አሠራር መሠረት ከሁሉም ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የሚሰጠውን ድምጽ ኩባንያው እየሰበሰበ እና እየቆጠረ ለቀጠረው ተቃዋሚ ፓርቲ መረጃውን ያስተላልፋል፡፡ በዚህም መሠረት ተቃዋሚው ትክክለኛውን ውጤት በሥልጣን ላይ ካለው አገዛዝ እንዳይነጠቅ የሚከላከልበትን በማስረጃ የሚያስደግፍበትን መረጃ የሚያገኝበት ይሆናል፡፡ በአምባገነናዊ አገዛዝ ሕዝባቸውን የሚጨቁኑ ግን “አንድ አገር ሁለት ዳኛ ሊኖራት አይገባም” በማለት አሠራሩን ሲቃወሙ ምርጫ በሕጋዊው የምርጫ ኮሚሽን ብቻ መፈጸም አለበት ይላሉ፡፡eac

እንደ መለስ፣ ኢሳያስ እና ካጋሜ የለውጥ ሃዋሪያ መሆናቸውን አስመስለው በ40ኛው ዕድሜያቸው ወደ ሥልጣን መንበር የመጡት ሙሰቪኒ እንደባልንጀሮቻቸው የተጠናወታቸው አምባገነንነት 30ዓመታት በመግዛት ሊበቃቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም በድጋሚ “በምርጫ” ስም በአምባገነንነቱ ቀጥለውበታል፡፡ ከኡጋንዳ ያለፈ ቀጣናዊ ዕቅድ እንዳላቸው የሚናገሩት ሙሰቪኒ በታኅሳስ 2007ዓም በአዲስ አበባ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን” የመፍጠር ዕቅድ እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

እንደ ሙሰቪኒ አነጋገር ከሆነ ይህ የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን አምስት አገራትን የሚጠቀልልና በድምሩ አንድ ወጥ የሆነ የምስራቅ አፍሪካ ልዕለኃያል አገር መፍጠር እንደሆነ ለኡጋንዳ ሬዲዮ የተናገሩትን ጠቅሶ ኒውስዊክ ዘግቧል፡፡ በዚህ ፌዴሬሽን ውስጥ የተጠቃለሉት አገራት ቡሩንዲ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ የፌዴሬሽኑ ዋና ዓላማ አገራቱን እንደ ቻይና፣ ሕንድ እና እንግሊዝ የመሳሰሉ ልዕለኃያላን እኩይ ምኞት መከላከል እንደሆነ ኢትዮጵያን የማያካትተው ፌዴሬሽን መሐንዲስ ሙሰቪኒ አስረድተዋል፡፡eac-presidents

እነዚህ አምስት አገራት የዛሬ 50ዓመት አካባቢ የተመሠረተው የምስራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ (East African Community – EAC) አባል አገሮች ናቸው፡፡ የዚህ ማኅበረሰብ ሃሳብ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ እንደገና ተነሳስቶ ቀጣናውን ለመቆጣጠር ምኞት ባላቸው አምባገነኖች ብዙ ሲባልበት የኖረ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በአገራት መካከል ትብብር እንዲኖር የሚጥር ሲሆን በአውሮጳውያን ዓመት 2024 በአገራቱ መካከል የሚሠራ አንድ የመገበያያ ገንዘብ ይፋ የማድረግ ዕቅድ አለው፡፡ እኤአ 2010 በአገራቱ መካከል የጋራ ንግድ የተመሠረተ ሲሆን ይህም ሠራተኞችና ዕቃ በአገራቱ ድንበር በነጻ እንዲተላለፍ የሚፈቅድ ሆኗል፡፡ በያዝነው 2016 ዓመት ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ኬኒያ የፖለቲካ ውህደት (ፌዴሬሽን) ለመፍጠር ዕቅድ የያዙ ሲሆን ይህ ሃሳብ ወደፊት በመግፋት በአምስቱ አገራት መካከል የምስራቅ አፍሪካ ፌዴሬሽን እንዲፈጠር የሙሰቪኒ ቀጣይ አጀንዳ ይሆናል፡፡ ዕቅዱ ተሳክቶ ተግባራዊ ከሆነ ሙሰቪኒ የአገራቸው ብቻ ሳይሆን የቀጣናውም አምባገነን ይሆናሉ!


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

<!–

–>


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles