ይህ የእኔ የግል እምነቴ ነው ብል ይሻለኛል፡፡ ምክነያቱም ብዙ ነጻ ነን የሚሉ ሰዎች እንኳን ምንም ሳይከብዳቸው ኦሮሞዎች፣ አማሮች፣ ትግሬዎች ወዘተ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ልብ በሏቸው ቃላቶቹ ምንን እንደሚያመለክቱ፡፡ ኦሮሞዎቹ ወይም አማሮቹ ወይም ሌላ ሲል አንድ ሰው ለእኔ እኔ የለሁበትም እያለ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድነት የለም፡፡ አንድነት ቢባልም ለይስሙላ ነው የሚመስለኝ፡፡ እንዲህ ያለ አነጋገር ደግሞ ሕዝብ እያደነቃቸው ካሉ የፖለቲካ መሪዎችም ሲወጣ ይደመጣል፡፡ ለእኔ በጣም የሚሻክሩ ቃላቶች ናቸው፡፡ ብዙ ሰው የማያሰተውለው ነገር ማንነቱን እንኳን ጠንቅቆ ሳያውቅ ራሱን የሆነ ብሔረሰብ አባል አድርጎ ሌላውን እንትናዎቹ ማለትን ይጀምራል፡፡ አሳዛኝ ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ደግሞ አክራሪ ኦሮሞ ነኝ የሚለው ጎጃሜ ሆኖ ሊገኝ ይችላል አክራሪ አማራ ነኝ የሚለው በተቃራኒው ሜጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙዎች ራሳችንን መርመመርመር ስንጀምር ታሪካችን የሚያበቃው እንደዛ ነው፡፡ አንድ ደብረማርቆስ ተወልዶ ያደገ የገዛ ጓደኛዬ ቅልጥ ያለው ጎጃሜ ሆኖ ራሱን አማራ አደርጓል፡፡ የሚገርመው ግን የቤተሰቡን የዘር ሀረግ ከጉደር አካባቢ ከሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ እንደሆነ ያውቃል፡፡ አክራሪ አማራ ነገር ስለነበር ምን ሆነህ ነው ታዲያ እንደዚህ አክራሪ አማራ ነገር የምትሆነው ስለው በራሱ ተገርሞ የሰጠኝ መልስ እውነት ምን ሆኜ ነው የምል ነበር፡፡ እሱስ ስለሚያውቀው እውነት ምን ሆኜ ነው አለ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከእነ አካቴው ራሳቸውን ጠንቅቀው ሳያውቁ ዋና የሆነ ብሔረሰብ አሳቢና ተቆርቋሪ ሆነው ይገኛሉ፡፡
ብዙ ጊዜ እኔ ኦሮምኛ ተናጋሪ፣ አማራ የሚባለው ምናምን እያልኩ የምጽፈው ወድጄ አደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቋንቋና እራስን የሆነ ብሔር አድርጎ ከማሳመን ያለፈ በቂ መረጃ ኖሮት በእርግጠኝነት እኔ የዚህ ብሔረሰብ አባል ነኝ ሊል የሚችል ሰው ካለ አንድ ከመቶ አይሆንም፡፡ ሁሉም ብቻ በስሜትና በወከባ ራሱን የሆነ ጎሳ አባል አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ከ25 ዓመት ወዲህ አደገኛ ልክፍት ሆኗል፡፡ በእርግጠኝነት የምናውቀው ግን አንድ ዘር ሀረግ ያለው አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ ምናምን የሚባል ሕዝብ እንደሌለ ነው፡፡ ኦሮሞ የሚባለውን ሕዝብ ባለፈው አንስቼ ነበር፡፡ በጠቂቱ ለማስታወስ ላንሳ፡፡ ዛሬ የኦሮምኛ ተናጋሪ ሕዝብ የሆነው የተለያየ ዘር ሀረግ ያለውና የኦሮሞ እንቅስቃሴ ከሚባለው ከዛሬ 450ዓመት በኋላ ብዙ የተልያዩ ሕዝቦች ወደ ኦሮምኛ ተናጋሪነት በመቀየራቸው የተፈጠረ ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህ በዝዋይ ሀይቅ የሚኖረው የዜይ ሕዝብ በኦሮምኛ ተናጋሪዎች ተጽኖ ብዙም ስላልነበረበት ለምልክት ይሆነን ዘንድ ዛሬም ድረስ እንዳለ እናሰተውል፡፡ ከ450 ዓመት በፊት ዛሬ ኦሮምኛ በሚነገርባቸው አካባቢዎች ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ነበር፡፡ አማራን ስናይ ብዙ ቦታዎች በተለይ በሰሜን አማርኛ የመሳፍንት ቋንቋ ስለነበር ብዙ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች አማርኛ ተናጋሪ ሆነው ዛሬ አማራ በሚል ተጨፍለቀዋል፡፡ ዛሬ ጎንደር አካባቢ ቅማንት ነን የሚሉት ሕዝቦችም የዚሁ አንዱ መገለጫ ናቸው፡፡ እኛ እንኳን ስናውቅ ወይጦ የሚባል ሕዝብ በጎጃም ይኖር ነበር፡፡ አሁን ያ ሕዝብ ፍጹም ተቀይሮ አማራ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለቤት የሆነው አገው ሳይቀር አፋፍ ላይ ነው ያለው፡፡ ትግርኛንም ስናይ ወልቃይቶች ትግርኛ ተናጋሪ እንጂ በዘር ከተከዜ ማዶ ካሉት አይገናኙም፡፡ አላማጣ ቆቦ ራያ ድሮ ኦሮምኛ ተናጋሪ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ዛሬም ለምልክት አለ፡፡ ወሎ የጁ፣ ቦረና ኦሮምኛ ተናጋሪ ነበር ዛሬ አማራ ነው፡፡ እነዚህን ሶስት ብሔረሰቦች ለምሳሌ ነው ያነሳሁት፡፡ ሌላውም እንደዛው ነው፡፡
ዘር ከተባለ ኢትዮጵያ ከጥንትም ጀምሮ ሰዎች ተደበላልቀው የሚኖሩባት፣ የሚዋለዱባት፣ አበሻ (ሐበሻ) ተብለው በአንድነት የሚጠሩባት ሕዝቦች አገር ነች፡፡ ዛሬም ቢሆን ይህ የጋብቻና የዘር ቅልቅሉ እንኳንስ ቋንቋን እምነትን (ሀይማኖትን) እንኳን ጥሶ አንዱ ከሌላው ሲጋባና ሲዋለድ ሌላ ትውልድ ሲፈጥር እናያለን፡፡ ለዚህ ማስተዋል ዝግ የሆንን እኛ ዛሬ ራሳችንን መነዘርንና ማንነታችንንም፣ ነጻነታችንንም የጠላቶቻችን መገልገያ አደርገን ሰጠን፡፡ ያሳዝናል፡፡ ኢትዮጵያ የአለም ሕዝቦች ሁሉ ዘር ሀረግ ያለባት አገር እንደሆነች ዛሬ ሳይንስ ሳይቀር እየመሰከረ ነው፡፡ በቅርቡ ታዋቂው ሳይንስ የተባለው የሳይንስ ምርምር የሚቀርብበት መጽሔት ይሄንኑ ነው የሚያረጋግጠው፡፡ በተመሳሳይ ሌላ ተናጥል እትም የሳይንስዊ መጽሔት ጥንታውያኑ ግብጾች ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ይመሰክራል፡፡ ዓለም በሰው ዘር ዝርያ ሀረግ ምርምር ኢትዮጵያ ውስጥ ይርመሰመሳል፡፡ የእኛ ሳይንቲስት ተብዬዎች በጎሳ ልክፍት መክነው ስልቀበሌ ያወራሉ፡፡ http://science.sciencemag.org/content/350/6262/820 እንድታነቡት ከምጋብዛችሁ አንዱ ነው፡፡ ብዙ ነው፡፡ የሐበሻ ምድር የሚባለው በእርግጥ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሱዳንን፣ ኤርትራን፣ ሶማሌን፣ የመንን የሚጨምር ነው፡፡ አስኳሏ ግን ኢትዮጵያ ነች፡፡ እውነታው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ በእነዚህ አገራት ሁሉ የሚኖሩ የዘር ሀረግ መጠላልፍ አለ፡፡ በቋንቋ የሚለያዩ በድንበር የሚዋሰኑ የኢትዮጵያ ዛሬ ብሔረሰብ የምንላቸው ሕዝቦች የዘር ቅርርብ ከምናስበው በላይ ነው፡፡ እውነትን መናገር ግድ ስለሆነብኝ እንጂ አንድነት የሚባለውን ለመስበክ አይደለም፡፡ አሁን አሁን እንደውም ተለያይትን ብንሞክረው እያልኩ ነኝ፡፡ ለምሳሌ ኦሮምኛ ተናጋሪው ከኢትዮጵያ ውጭ ለዓመት አብሮ መኖር የማይችል ዘጠኝ ትንንሽ የሚሆን ሕዝብ ነው፡፡ አይደለም ባሌና ወለጋ ሐረቶና ሻመቡ ተለያይተው ነው የምናገኛቸው፡፡ አማራም እንደዛው፣ ትግሬም ተብዬው እንደዛው፡፡ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት እንጂ አንድ የሆኑት በብሔረሰብ እንዳልሆነ መጀመሪያ እንወቅ፡፡ ማስተዋል የጎደለው ትውልድ ሆነናል፡፡ አስናለሁ! ለእኛ ዛሬ ላለንው ትውልድ የሚከተለውን ግጥም ጋብዣችኋለሁ፡፡
የነጠፈው የኢትዮጵያ ማህጸን!?
ሀ ብሎ ሲጀምር ጥበብን የጠራ፣
አክሱም ላሊበላን በእጆቹ የሠራ፣
ያንን ምጡቅ ትውልድ ሲያፈራ የኖረ፣
ወላድን በድባብ ከድኖ ያከበረ፣
ምን ሆኖ ደረቀ/ነጠፈ ያ ለምለም ማህፀን፣
ምክነያቱ ጠፋኝ ግራ ገባኝ እኔን፡፡
በእግዚአብሔር አምላክ ፊት ሲቦርቅ አይተሽው፣
ምን አልባት ዳዊትን በልብሽ ንቀሽው፣
የሳዖል ልጅ ሜልኮል የደረሳት ዕጣ፣
ያ የእግዚአብሔር በትር ያ የእግዚአብሔር ቁጣ፣
ዘላለም እንዳትወልጅ ዳግም በአንቺ መጣ?
ነገሩን ሳስበው የአንቺ ከእሷ ባሰ፣
መዘጋት መድረቁ ደግሞ ባላነሰ፣
አራሙቻ አብቅሎ አገር አረከሰ፡፡
ምንኛ ቢከፋ ታዲያ የአንቺ ኃጥያት፣
እንዳልተባለልሽ የጠቢባን እናት፣
ያ ለም ማህጸንሽ የተዘመረለት፣
መንጠፉ ሳያንሰው አረም በቀለበት!?
ኃጥያትሽ በዝቶ እንደሁ ተስፋ ሳትቆርጪ፣
አጥቦ ያፀዳሽ ዘንድ እምባሽን አመንጪ፣
በአፍኝሽ ሙይና እርጪው ወደ ሰማይ፣
መስዋዕት ይሁንሽ በአምላክሽ ፊት ይታይ፡፡
በፀፀትሽ ብዛት አስቦ ታሪክሽን፣
ዳግም እንድከፍተው ለምለም ማህፀንሽን፡፡
ስቃይዋ ቢበዛ ብታጣ ልጆቿን፣
መጽናናት ቢሳናት ልቧ ገብቶ ሐዘን፣
ስቅስቅ ብላ አልቅሳ አውጥታ የአንጀቷን፣
ብሶቷን አሳፍራ ብትልክ አምባዋን፣
እግዚአብሔር ስለእሷ ሕዝቡን መመልከቱን፣
ያቺን የሐዘን እናት አስቢ ራሄልን!!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! አሜን!