ወያኔ ብአዴንና ኦህዴድ የሚባሉ አገልጋዮቸን ፈጥሮ ፣ ኢትዮጵያውያንን በጎሳ አከፋፍሎና ለአገዛዙ እንዲመቸው አድርጎ አደላድሎ ለ17 ዓመታት የተዋጋለትን ዓላማውን ተግባራዊ ከማድረግ አልፎ ሀያ አራ ዓመታት በሥልጣን መቆየት በመቻሉ ሊደነቅ ይገባል፡፡ ለዴሞክራሲ አንታገላለን የሚሉ አንደ ወፍ ዘራሽ በየቦታው በቅለው ሳይለያዩ ተለያይተው፣ ሳይነጋገሩ ተጣልተው፣የቃላት አንጂ የተግባር ሰውነት ርቆአቸው ሀያ አምስት አመታት ስንዝር መራመድ ባልቻሉበት ወያኔ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት አንድነቱን አጥብቆ፣ ገመናውን ደብቆ በሌሎችም ተጠቅሞ መዝለቅ መቻሉን ማድነቅ አለመቻል የራስን ድክመት ለመቀበል አለመፍቀድ ነው፡፡
ነገራችንን ሁሉ አንቆቅልሽ ያደረግነው አኛው መሆናችንን አምኖ አለመቀበል ደግሞ ለበሽታችን መድሀኒት ለችግራችን መፍትሄ አንዳናገኝለት አድርጎናል፡፡ ወያኔ በጎሰኛነት እየከሰስን በተቃራኒው እኛ እሱ የሚዘራውን የዘረኝነት መርዝ ወኃ እያጠጣንና እየኮተኮትን እናሳድጋለን፡፡ አንድነት ያማጣችን ምክንያቱ የመለያየታችን በሽታ ምንጩ ወያኔ ነው እያልን እኛ ግን በጎሳ መለያየቱ አልበቃ ብሎን የሚያቀራርበንን ሳይሆን የሚያለያየን በመፈለግ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትጵያውያን ስለ ፖለቲከኞች አንድ አለመሆን እየተቆጩ እነርሱ ግን የአንድ እምነት ተከታዮች ሆነው ቤተ እምነታችውን ለያይተው ላይገናኙ አጥር አበጅተው ላይደራረሱ ተማምለው ርስ በርስ ይወጋገዛሉ፡፡ ከእንዱ ደብር ሌላው ጋር ሄዶ ምኮት መፈጸምን ወንጀል አለያም ክህደት አድርገው ያያሉ፡፡ ለመሆኑ በዚህ መልክ የተገነባ ቤተ እምነት እንዲህስ እየተሆነየሚደረግ ጸሎት ለምህረት ወይስ ለቅስፈት፡፡
ለወያኔ አገልጋይነት ያደሩት ወገኖች ሀያ አራት ዓመት ሙሉ ሰጥ ለጥ ብለው የመገዛታቸው ምክንያትም ሆነ ተቃዋሚው ይህን ያህል አመት ትንሽ አንኳን ለውጥ አለማምጣቱ ሊያስመርረው ሊስያቆጨውና በእልህ ሊያነሳሳው ያለመቻሉ ነገር (ይህ የማይመለከታቸው ጥቂቶች ቢኖሩም) ለፍቺ ያስቸገረ እንቆቅልሽ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ አበው ማር አንኳን ሲበዛ ይመራል ይላሉ እንኳንስ አገዛዝ፡፡ በዚህ ዘመን ግን ለወያኔ ያደሩት አገልጋዮች ሌላ ሌላው ቢቀር ንቀቱ ውርደቱ የሚሰማቸው አልሆኑም፡፡ ተቀዋሚዎቹም በህዝብ ላይ የሚፈጸመው ግድያ እስራትና ደብደባ፣ በሀገር ላይ የሚፈጸመው ታሪክን ማዛባት ሉአላዊነትን መናድና ዳር ድንበርን መሸራረፍ ብሎም ወዘተ ከማማረር ወደ ማምረር ሊያደርሳቸውና ከቃላት ተቃውሞ አውጥቶ ለተግባራዊ ትግል በአንድነት ሊያሰልፋቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም ዛሬም ዜጎች ይገደላሉ ይታሰራሉ ይሰደዳሉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች ግን እዛው የቃላት ጨዋታቸው ላይ ናቸው ፡፡
ኦህዴድና ብአዴን ብየ ጀምሬ የነገሮች ተያያዥነት እየጎተተ እዛና እዚህ አስረገጠኝ እንጂ በዚህች አስተያየቴ ለማንሳት የፈለግሁት በጠቅላይ ምኒስትሩ ዙሪያ የሁለቱ ድርጅቶች ሰዎች አለመኖር ለአገልጋይነት አንጂ ለቤተ መንግስት የማይፈለጉ ወይንስ የማይመጥኑ ሆነው በሚልስሜቴ ያጫረብኝን ጥያቄ ነው፡፡ በሟቹ ጠቅላይ ምኒስትር ዘመን ያልነበሩ የስልጣን ቦታዎች እየተፈጠሩ የህውኃት ሰዎች በተለያየ የማእረግ ስም ወደ ቤተ መንግስት እየገቡ አቶ ሀለማሪያምን ሲከቡ ከሁለቱ ድርጅቶች አንድም ሰው ወደዛ ቦታ ድርሽ አንዲል አልተደረገም፡፡
ብዙ አሳይቶንና አሰምቶን ባለፈውና በታረክ ውስጥ ልዩ ምእራፍ በያዘው ምርጫ 97 ከተካሄዱ የክርክር መድረኮች በአንዱ ኦህዴድ እወክለዋሁ አንደሚለው የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት ተገቢ የሥልጣን ቦታ አልያዘም፡፡ ለኦሮሞ የሚገባው ምንም ሥልጣን የሌለው የፕሬዝዳንትነት ቦታ ሳይሆን የጠቅላይ ምኒስትርነቱ ቦታ ነበር የሚል ጥያቄ ተነስቶ ጠቅላይ ምኒስትርነቱ የተያዘው በእውቀት በችሎታና በብቃት እንደሆነ የሚገልጽ ምላሽ ነበር የተሰጠው፡፡ ይህ ማለት በጠባቡ ሲታይ ከኦህዴድ በሰፊው ከታየ ደግሞ ከኦሮሞ ለጠቅላይ ምኒስትርነት የሚያበቃ እውቀት ችሎታና ብቃት ያለው የለም የሚል መልእክት ያለው ነው፡፡
መልእክቱ በዚህ ብቻ አይወሰንም ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆነ በአጠቃላይ ከኢትጵያውያን መካከል መለስን የሚተካከል ለጠቅላይ ምኒስትርነት የሚያበቃ እውቀትም ሆነ ችሎታና ብቃት ያለው የለም ፤ እኛ በትግላችን ደርግን ደምስሰን ያመጣንላችን እያጣጣማችሁ አርፋችሁ ተገዙ፤ የማይገባችሁን አትጥያቁ የማይመጥናችሁን አትከጅሉ ያይሆን ነገር አታንሱ ወዘተ ማለት ነው፡፡ ያ ጥያቄ ከአስር አመት በኋላ ዛሬ ቢነሳ የመላሹቹ መልስ ተመሳሳይ ይሆናል ተብሎ መገመት ይቸግራል፡፡ ህውኃት የፈቀደው ምንም ይሁን ማ ጠቅላይ ምኒስትር መሆን ይችላል ሊሉ ይችሉ ይሆናል ብሎ መገመት ግን ይቻላል፡፡ ጥያቄው ቢነሳና ምላሹ የገመትነው ቢሆን ደግሞ ብአዴንና ኦህዴድ በህውኃት የሚፈለጉት ለአገልጋይነት አንጂ ለወሳኝ ቦታ ሹመት አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ በተግባር የሚታየውም ይኸው ነው፡፡ታዲያ ሎሌነትም ልክ አለውና ይህን ለምን ብሎ መጠየቅ የእነርሱ አንጂ የእኛ ድርሻ ሊሆን አይችልም፡፡
በተደጋጋሚ ግዜ ስለ ወታደራዊ ከፍተኛ መኮንኖችም ጥያቄ ተንስቷል፡፡ በተለይ ጀነራሎቹ ህውኃት መሆናቸው መቼም ያማይቆም ጥያቄ ነው፡፡ ታግለን ነው ለሥልጣን የበቃነው የሚሉትን፤ ብዙ ሚሊየን ብሮች ከህዘብ ጉሮሮ እየነጠቁ የምስረታ በአል እያሉ የሚያከብሩት፤ አንባገነኑን የደረግ ስርአት ደምስሰን እያሉ የሚያቅራሩት ብአዴንና ኦህዴድ ግን የጀነራልነቱ ቦታ አንደማይገባቸው አውቀው አቅማቸውን አውቀው የተቀመጡ ነው የሚመስለው፡፡ ከፕሮፓጋንዳው በስተጀርባ ያለውን ለዚህ ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት ያባቃቸው ምክንያት በመጠኑ የሚታወቅ ቢሆን ሀያ አራት አመት ሙሉ ያለምንም ኮሽታ ለማገልገላቸው ይልቁንም በአደባባይ በግልጽ የሚነሱ ጥያቄዎች ( ምሳሌ የጀነራልነቱ) የማይሞቅ የማይበርዳው የሆነበትን ምክንያት የሚያውቁት እነርሱ ናቸው፡፡ ህን ደግሞ ይዘገይ ይሆናል አንጂ ከእነርሱው አንደበት መስማታችን አይቀርም፡፡
የጀነራልነቱ ሥልጣን በአብዛኛው በህውኃት ስለመያዙ ምክንያት ምላሽ ሲሰጥ የሚሰማው ከህውኃት ሰፈር ሲሆን በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ህውኃት በመሆኑ የሚል ነው፡፡ ይህ አባባል ብዙ ነገሮች ያሳያል፡፡ እንደው በትንሹ ቀንጭበን ብናየው የታገልነው ለሥልጣን ነው፤ እናንተንም ለዚህ ያበቃናችሁ እኛ ስለሆንን የሰጠናችሁን መቀበል ነው ያለባቸሁ፤ የህውኃቶች ወታደራዊ አመራር ችሎታና ብቃት በተግባር የተረጋገጠ ሲሆን ሌሎቻችሁ ለዚህ ደረጃ የሚያበቃ በተግባር የተፈተነ ብቃቱ የላችሁም፤ ወዘተ የሚል ነው፡፡ራቁቱን ለተወለደ ልጅ ጥብቆ መች አነሰው አንደሚባለው በህውኃት ትግል በተገኘ ድል በተመሰረተ መንግሥት ውስጥ በችሮታችን የሰጠናችሁ ቢበዛባችሁ አንጂ አያንሳችሁም ነው መልእክቱ፡፡ ሀያ አራት አመት ሙሉ ማመጣጠን ያልተቻለውም በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠ ብቃትን በጦር ትምህርት ቤት የሚገኝ እውቀት ሚዛን ደፍቶ ሊገዳደር ስለማይበቃ ነው፡፡ የብአዴንና የኦህዴድ ሰዎችም ይህንኑ ተቀብለው የህሊናቸው ጉዳይ ባይታወቅም ቁሳዊ ፍላጎታቸውን አርክተው ሆዳቸውን ሞልተው እየኖሩ ነው፡፡
ታዲያ ምን አዲስ ነገር ኖሮ ነው ይህ ጉዳይ አንደ አዲስ መነሳቱ የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያት ሆኖኝ ይህን ያነሳሁት ብአዴንና ኦሀዴድ ለጠቅላይ ምኒስትርነትም ሆነ ለሌሎች ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎች እንዲሁም ለጀነራልት የሚበቃ ሰውም ሆነ ለዚህ አንዲታጩ የሚያበቃቸው ድርጅታዊ ቁመና ባይኖራቸውምና ይህንኑ አምነው ቢቀበሉም ለጠቅላይ ማኒስትሩ አማካሪ የሚሆን ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሰው እንኳን መጥፋቱ አስገርሞኝ ወያኔም የንቀት ደረጃ ጥያቄ ሆኖብኝ ነው፡፡
በአቶ መለስ መልካም ፈቃድ ወደ ቤተመንግሥት የተሳቡትና በህውኃት ፍላጎት ጠቅላይ ምኒስትር የሆኑት አቶ ኃለማሪያም ደሳለኝ ከህውኃት ፍላጎትና ፈቃድ ውጪ አንዲት ጋት አንዳይራመዱ ለማድረግና ኣጋዛዙ በአቶ ሀይለማሪያም ስም ሽፋን በህውኃት መከናወኑ ተጠናክሮ አንዲቀጥል በተለያየ የሥልጣን ሥም የህውኃት ሰዎች ወደ ቤተመንግሥት በመግባት አቶ ሀይለማሪያምን ከበዋቸዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ብአዴንና ኦህዴድ አንዴት ለዚህ ቦታ እንኳን የሚሆን ሰው የላቸውም፡ለምንስ ይሆን ህውኃት ይህን ቦታ እንኳን ሊፈቅድላቸው ያልፈለገው፣ ሎሌነታቸው እስከምን ደረጃ ቢሆን ነው እነርሱስ ይህን ሁሉ አሜን ብለው መቀበላቸው ወዘተ የሚል ጥያቄ ማንሳት አግባብነት ይኖረዋል፡፡
የብአዴንም ሆነ የኦህዴድ ሰዎች በወያኔ የሚደርስባቸውን ንቀቱን ችለው፣ ውርደቱን ተቀብለው አገልጋይነቱ አሜን ብለው፣ የመኖራቸው ምክንያት ከመነሻው ህውኃት ሰራሽ መሆናቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ እነዚህ የራሳቸው ህልውና የሌላቸው በወያኔ ፈቃድ የሚኖሩና በትእዛዝ የሚሰሩና የሚናገሩ ሰዎች የሚመሩዋቸውን ድርጅቶች አንደ ድርጅት ተቀብለው በአባልነት አለያም በደጋፊነት ተሰልፈው በተዋረድ ውርደትን አሜን ብለው ንቀትን ተቀብለው እየኖሩ ያሉ ሰዎች ምክንያትም አጠያያቂ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቁሳዊ ፍላጎቱን ለማርካት እስከዚህ ይደርሳል፡፡አበው ሆዱን የወደደ ማእረጉን ይጥላል የሚሉት አንዲህ አይነቱን አይደል፡፡
ለሁሉም ግዜ አለው እንደሚባለው የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች ሰዎች የተሰጣቸውን እየተቀበሉ የታዘዙትን እየፈጸሙ በሉ የሚባሉትንም እየተናገሩ ሀያ አራት አመታት ቢዘልቁም አሁን ጊዜ ትልቅ ፈተና ጋርጦባቸዋል፡፡ ህውኃት በተካነበት ብልሀትም ጉልበትም ነገሮች አንደስከዛሬው ነገሮችን ዝም ጭጭ ማሰኘት አለመቻሉ ደግሞ የእነርሱን ፈተና አክብዶታል፡፡ ህውኃት በሚያሳያቸው መንገድ እየተጓዙ የህውሀትንም ምክር ይሁን ትዕዛዝ እጠቀበሉ ፈተናውን ሊያልፉት አደጋውን ሊወጡት እንደማይችሉ የተገነዘቡ ሰዎች (ከብአዴንም ከኦህዴድም) ፈተናውን የማለፊያ መንገድ እየፈለጉ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡
የሚባው እውነት ከሆነ ለሁሉም ልክ አለው ብለው የተጫነባቸውን ቀንበር አውልቀው ለመጣል የሚታገሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ ሎሌነት ወይንም ሞት ብለው በመጡበት መንገድ መቀጠልን የሚመርጡ ሌላ የርስ በርስ ትግል ይጀምራሉ፡፡ ይህ ጠርቶና ነጥሮ ከወጣ ሌነት በቃን ያሉት በሕዝብ ሲደገፉ በሎሌነት መቀጠል ምርጫቸው የሆነው የወያኔ ድጋፍ አይለያቸውም፡፡ማን እንደሚያሸንፍ ደግሞ ለሶስት ወራት ያላባራውና ወያኔን ያንበረከከው በኦሮምያ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ይነግረናል፡፡
ሲሆን ሲሆን ብአዴንም ሆነ ኦህዴድ አንደ ድርጅት ሎሌነት በቃን ነጻነት አንሻለን ቢሉ፤ለየግል ጥቅማችን ስንል አንወክለዋለን የምንለውን ህዝብ ማስጠቃቱ ማስናቁ ይበቃል ከእንግዲህ የህውሀትን የሞግዚት አስተዳደር አንሻም በህገ መንግስት ያሰፈርነው የክልሎች ነጻነት ተግባራዊ ይሁን ወዘተ ብለው ቢወስኑ ለሀጢአታቸው ስርየትን ለበደላቸው ይቅርታን ሊያስገኝላቸው ይችላል፡፡
ይህም ካልሆነ በየግል ውሳኔ በቃን ብለው ነጻነታቸውን በመሻት የሚታገሉትንና ታሪክ ለክብር ያጫቸውን በአንጻሩም ሎሌነቱ ተመችቶኛል የማይገባኝን ያገኘሁት በህውኃት ነው ብለው በአገልጋይነታቸው በመቀጠል ከውርደት አትውጡ ያላቸውን ለማየት አንበቃ ይሆናል፡፡