ለፍትሕ ፓርመከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ቢሰናበቱም በይግባኝ አቤቱታ ላለፉት ስድስት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ለዴሞክራሲናቲ፣ የአረናና የሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የነበሩት አራት ግለሰቦችና አንድ መምህር ከእስር እንዲፈቱ፣ ዓርብ የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የመፍቻ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ ከአገር እንዳይወጡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዲያውቀው ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የካቲት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ይግባኙን እየመረመረው በሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቀርበው፣ በእስር ላይ በሚገኙበት በፌዴራል ማረሚያ ቤት እየደረሰባቸው ያለው ተፅዕኖ ለሕይወታቸው እንደሚያሠጋቸው ለችሎቱ ከተናገሩ በኋላ፣ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሚ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር፡፡
ይግባኝ ሰሚው ችሎት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በታሳሪዎቹ ስለቀረበው ‹‹ለሕይወታችን ያሠጋናል›› አቤቱታ ምላሽ እንዲሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ እስረኞቹ በዕለቱ ሲቀርቡ የተነገራቸው ‹‹መፍቻ ይጻፍላችሁና ተፈትታችሁ ለቀጣዩ ቀጠሮ ከቤታችሁ ትቀርባላችሁ›› የሚል ነበር፡፡ ችሎቱ ለእስረኞቹ በነገራቸው መሠረት የካቲት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት የመፍቻ ሰነድ ወደ ማረሚያ ቤት መላኩ ተረጋግጧል፡፡ ሪፖርተር ኅትመት እስከገባበት ዓርብ ሌሊት ድረስ ከእስር አለመፈታታቸውን አረጋግጧል፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. የአንድነት አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ አብርሃ ደስታ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋና መምህር አብርሃም ሰለሞን በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊት ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ መስጠቱን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በማግሥቱ በይግባኝ አቤቱታ እንዳይፈቱ ማሳገዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡