ባፈው ሃሙስ በሃዋሳ ከተማ ከተማ ልዩ ስሙ ታቦር ት/ቤት በሚባል አካባቢ ፖሊስ በሦስት ጥይት አንድ ሰው መግደሉ በዕለቱ ወዲያውኑ ከሥፍራው መረጃ ቢደርሰንም እስካሁን ተጨማሪ መረጃዎችን ስናሰባስብ ቆይተናል፡፡
የጎልጉል እማኝ ዘጋቢ (ireporter) የላኩልን በምስል የተደገፈ መረጃ እንደሚያመለክተው ድርጊቱ የተከሰተው ግለሰቡ ለቤ/ክ ወደተከራየ ጊቢ ለመግባት በር ላይ በተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ዘጋቢያችን ጠቁመዋል፡፡
ቤቱ ለቤተክርስቲያንነት ቢከራይም የቤተሰቦቹ የሆነውን ቤት እሱ ሳያውቅ የተከራ በመሆኑ እንዲለቁለት ተከራዮቹን በተደጋጋሚ ሲጠይቅ እንደነበር መረጃ አቀባያችን ያስረዳሉ፡፡ እንደተለመደው በዕለቱም ይህንኑ ጥያቄውን ለማቅረብና ወደ ጊቢው ለመግባት በሚሞክርበት ጊዜ ተከራዮቹና ሌሎች ውስጥ የነበሩ ተባባሪዎቻቸው ፖሊስ መጥራታቸውን ዘጋቢያችን በላኩልን መረጃ ጠቁመዋል፡፡
በእጁ ላይ ስለት ይዞ እንደነበር የተገለጸው ግለሰብ ስለቱ ግን ሆን ተብሎ የተቀነባበረበት ስለመሆኑ መረጃ እንዳለ ተነግሯል፡፡ የጎልጉል እማኝ ዘጋቢ እንደሚሉት ከሆነ “ስለቱ ለማስመሰል (ሆን ተብሎ) የተዘጋጀ እንጂ በእርግጥ ግለሰቡ ይዞት የነበረ ለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ” የለም፡፡ “ከዚያም የመጣው ፖሊስ (ግለሰቡን) ይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መውሰድ ሲገባው አይኑ ላይ በጥይት ደበደበው።” ከመረጃው ለመረዳት እንደተቻለው ክላሽንኮቭ ያነገበው የኢህአዴግ ታጣቂ በሶስት ጥይት ግለሰቡን እንደገደለው የመረጃው አቀባይ ያስረዳሉ፡፡
ግለሰቡ የተገደለ ጊዜ ፎቶግራፍ ማንሳት የተቻለ በመሆኑ ድርጊቱ በፎቶ ማስረጃ የተደገፈ ሲሆን መሳሪያ አንጋቢው ግድያውን ከፈጸመ በኋላ ሲሸሽ “በወቅቱ ከኅብረተሰቡ ጋር ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ በመጨረሻም በአስለቃሽ ጭስና በኃይል” አስከሬኑ መነሳቱን እማኝ ዘጋቢያችን ያስረዳሉ፡፡
“አስከሬኑም የት እንዳለ ከፖሊስ ውጭ የሚያውቅ የለም” ያሉት መረጃ አቀባያችን “ገዳዩን ፖሊስ ለማዳን ሁሉም ነገር ሚስጥር ተደርጓል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጎልጉል ከሚመለከታቸው አካላትም ሆነ ከሌላ ሦስተኛ ወገን ሁኔታውን በተመለከተ ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ (ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ)
<!–
–>