ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች አማራን የማጥፋት የቆረጠ የጥፋት ዓላማና ድርጊት ይዘው መምጣታቸውና ሀገሪቱን ከመቆጣጠራቸው የወሰዱት የተቀናጀ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ጥቃት መፈጸማቸው የአማራ ልኂቃንን አስጨንቆ ሕዝቡን ከወያኔና መሰሎቹ የዘር ማጥፋት ጥቃት የታደጉ፣ የሠወሩ፣ ያዳኑ፣ የከለሉ፣ የተከላከሉ መስሏቸው ሁለት የተለያዩ አቋሞችን ለማራመድ ሲያስገድድ ከአማራው ሕዝብም ቀላል ቁጥር ያልያዘውን ምናልባትም አሁን የአማራ ሕዝብ ተብሎ ከሚገለጸው የሚበዛውን በተለይ በወያኔ አጠራር የአማራ ክልል ተብሎ ከሚጠራው ውጭ ርቆ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን አማራ ነኝ ብሎ ያምን የነበረውን ዜጋም ማንነቱን እንዲቀይር የያለበትን አካባቢ ብሔረሰብ ነኝ ብሎ ማንነቱን እንዲክድ አስገድዷል፡፡ ወያኔ ኦሮሚያ ብሎ ከሚጠራው የሀገራችን ክፍል ብቻ ከ7 እስከ 10 ሚሊዮን (አእላፋት) አማሮች ጥቃትን በመፍራትና ከጥቃት ለመዳን በማሰብ ማንነታቸውን ወደ ኦሮሞነት ለውጠው ኦሮሞ አድርገዋል፡፡
አስገራሚው ነገር ይሄ አይደለም እዛው ወያኔ የአማራ ክልል ብሎ ከሚጠራው የሀገራችን ክፍል ያለው አማራም በዘሩ የተቀላቀለችውን የሌላ ብሔር በተለይም የትግሬን እያሰላ አማራነቱን የካደና ትግሬ ነኝ ያለ መኖሩና አማራ ነኝ የሚለውም ወያኔ ለአማራ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻና የማጥፋት ዓላማ እንዳለው እያወቀም ከወያኔ ጋር ተሰልፎ ይሄንን የወያኔን የጥፋት ዓላማ የሚፈጽምና የሚያስፈጽም መኖሩ ነው፡፡ እነኝህን ግለሰቦች በብዛት “ብአዴን” ተብሎ በሚጠራው የወያኔ አሻንጉሊት ውስጥ ታጉረው ታገኟቸዋላቹህ፡፡ አማራን ይዘልፋሉ ከወያኔ በሚቀበሉት ትእዛዝ ባሕሉን ማንነቱን ታሪኩን አጠቃላይ እሴቶቹን ያጠፋሉ የተለያየ ጥቃት ያደርሳሉ፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱ የልኂቃን ቡድኖች ደግሞ አንደኛው “አማራ የሚባል ብሔረሰብ የለም!” የሚለው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ከዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት መትረፍ የምንፈልግ ከሆነ በቅናትም ይሁን በሌላ ምክንያት ለመጠቃት ምክንያት የሆኑብንን ማንነታችንን፣ እሴቶቻችንን፣ ትውፊታዊ ሀብቶቻችንን፣ ቅርሶቻችንን፣ መለያዎቻችንን፣ ኩራቶቻችንን፣ መብቶቻችንን፣ የሥልጣኔ ፍሬዎቻችንን ወዘተረፈ. አሳልፎ መስጠት፣ መተው፣ መጣል፣ መሠዋት፣ የእኛ መሆኑን አለመጠየቅ አለመናገር አለመመስከር፣ እንደሚገደን እንደሚያገባን አለመናገር፣ አንገታችንን አቀርቅረን መቀመጥ፣ የፈለጉትን ቢያደርጉት ዝም ማለት” ብለው የሚያምኑና ይሄንንም በማድረግ ከሌሎቹ ጋር ለመግባባት የሚሞክሩ ከወያኔና ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጋር ሳይቀር ተባብረው የሚሠሩና ለመሥራት የሚጥሩ ከሀዲያን ናቸው፡፡
“አማራ የሚባል ሕዝብ ወይም ብሔረሰብ የለም!” የሚሉቱ ከመጨነቃቸው የተነሣ ለበጎ አስበው ይሄንን ነገር ቢያደርጉትም ይሄ ድርጊት ወያኔ በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰበት ካለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ባልተናነሰ የከፋና የከበደ አደጋ እንዳለው በወቅቱ ያሰቡት አይመስለኝም፡፡ ይሁን እንጅ እንዳልኩት ይሄንን የሚሉ ወገኖች ስለጨነቃቸው እንጅ በእርግጥም “አማራ የሚባል ብሔረሰብ የለም!” ብለው ስለሚያምኑ ነው ይሄንን ያሉት ብሎ ማለት የዋህነት ነው፡፡ ይህ አባባል ጉዳት ያለው ቢሆንም እነሱ ለክፉ አስበው ስላላደረጉት ሊዘለፉ የሚገባም አይመስለኝም፡፡
እንዳጋጣሚ ሆኖ ይሄንን አመለካከታቸውን ሕዝቡ አልተቀበለውም እንጅ ተቀባይነት አግኝቶ “አማራ የለም!” በሚለው አስተሳሰብ ቢሠራበት ኖሮ ለዚህች ሀገር የጀርባ አጥንት ሆኖ ስንት መሥዋዕትነት የከፈለ ስንት ታሪክ የሠራ ሕዝብ እንዳልነበረ ሆኖ ጠፍቶ ተረስቶ ቀርቶ ነበር፡፡ የተባለው ነገር የዚህን ያህል ጉዳት ባያደርስም ግን ይህ “አማራ የለም!” የሚለው አባባል እራሳቸውን ከጥቃት ለማዳን ማንነታቸውን የካዱትን የአማራ ተወላጆችን እንዲህ ዓይነቱን ክህደት በራሳቸው ላይ እንዲወስዱ ተጨማሪ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ መገመት ይቻላል፡፡ ለአንድ ሕዝብ ከዚህ በላይ ኪሳራና ጉዳት ምንም ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ “የለም!” በመባሉ ጨርሶ የመረሳት የመፋቅ አደጋ ባይደርስበትም አለ በመባሉ ከወያኔ ይደርስበታል ተብሎ ከተፈራው አደጋ የከፋ አደጋና አደገኛ ውጤት በተለያየ መልኩ እየደረሰበት ይገኛል፡፡
ሲጀመር ወያኔ አማራ አለ ብሎ አምኖ በራሱ እምነት “አማራ” ያለውን ወገን እየመነጠረ ለማጥፋት ቆርጦ እስከተነሣና ይሄንንም ተግቶ እስከፈጸመ ጊዜ ድረስ እኛ “አማራ የለም!” ማለታችን ማንነታችንን በገዛ ራሳችን በመካዳችን ለወያኔ ድርብ ድል ይሰጠው እንደሆን ነው እንጅ “የለም!” በማለት ወያኔ የዘመተበትን ሕዝብ ከጥፋት ለመከላከል የማይረዳ መሆኑን አለመገንዘብ የዋህነት፣ እጅ መስጠት፣ ጥቃት ወይም ሽንፈትም ነው፡፡
የወያኔ ችግር አማራ ተብሎ የሚጠራ ሕዝብ መኖሩ እንጅ ያ ሕዝብ አማራ መባሉ ላይ አይደለም፡፡ አማራ አማራ መባሉ ቀርቶ ሌላ ሥያሜም ቢኖረው ኖሮ አማራ ስላልተባለ ከወያኔና መሰሎቹ ጥቃት የሚያድነው አይደለም፡፡ ስለሆነም አባባሉ ጭንቀት የወለደው እንጅ ታስቦበት የተባለና እውነትም ሆኖ የተባለ አይደለም፡፡
እዚሁ ላይ አንድ ግራ የሚገባኝ ነገር ቢኖር “አማራ የለም!” ብለው የሚሉ ወገኖች እራሳቸውን ማን ብለው ነው እየገለጹ ያሉት? ሌላ ብሔረሰብ እየጠሩ ወይስ ብሔረሰብ የሌለኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያሉ? ይህ አባባል ስሕተት የሚሆነው አማራ ብቻ የለም በመባሉ ነው እንጅ ሌሎቹም የሉም ቢባል ስሕተት ባልሆነ ነበር፡፡ ምክንያቱን “ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከጥፋት የሚታደገው ብቸኛው መንገድ!” ከሚለው ጽሑፍ ላይ ይመልከቱ፡፡
ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች አማራን ለማጥፋት የተነሡት የጥፋት ኃይሎች እንደሚያወሩትና የዋሀን የአማራ ተወላጆችና ሌሎችም እንደሚመስላቸው አማራ ግፍ ስለፈጸመ አይደለም ልብ በሉ ይሄንን ስል በሌሎች ሀገራት እንደተፈጸሙት ያለ ግፍ በሀገራችን አልተፈጸመም አልኩ እንጅ የዚህ ወይም የዚያ ዘር ብሔረሰብ አባል በመሆን መናቅ መገፋት አልነበረም እያልኩ አይደለም፡፡ ይሄም ቢሆን ግን “እዬዬም ሲዳላ ነው” እያልን ካልሆነ በስተቀር ይህ ጉዳይ ተጋኖ ጭራሽም ለፖለቲካዊ (ለእምነተ አሥተዳደራዊ) ፍጆታ ውሎ በሀገርና በሕዝብ ህልውናና ደኅንነት ላይ አደጋ እስኪጋርጥ ድረስ ትኩረትና ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ በፍጹም በፍጹም አልነበረም፡፡ ይሄ አለመብሰል ነው፡፡ ምክንያቱም አንዳች ነገርን ምክንያት በማድረግ መናናቅ ያለ የነበረና የሚኖር ሊጠፋም የማይችል በመሆኑ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሰው በመሆናችን ካሉብንና ከውስጣችን ልናጠፋቸው ከማንችላቸው ደካማ ጎኖች ይሄ አንዱ በመሆኑ፡፡
በእርግጠኝነት የምነግራቹህ ነገር ቢኖር “ኦሮሞ በመሆናችን ትግሬ በመሆናችን ወዘተረፈ. እንናቅ እንገፋ ነበር” የሚሉ ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራዊያን) እንዲያው ሌላውን ሁሉ ነገር ተውና እነሱ ዛሬ ከተሜ ሆነው ከተሜነትን እያጣጣሙ ስለሆነ ብቻ በገጠር ዘመዶቻቸው በወንድም በእኅቶቻቸው በእናት በአባቶቻቸው የሚያፍሩ የሚሸማቀቁ ከእነሱ ጋር አብሮ መታየትን የማይፈቅዱ፤ አካለ ስንኩል ወይም የአእምሮ ዘገምተኛ የቤተሰብ አባል ካለም እንዲያ የሆነው ሰው ለተጎዳው ያንን ችግርም በራሱ ላይ ያመጣው ራሱ ተጎጅው ፈልጎ ያመጣው ይመስል ከባድ የሆነ ንቀት ጥላቻ ማግለል ችግሩ ባለበት የቤተሰባቸው አባል ላይ የሚፈጽሙ የእነሱ የቤተሰብ አባል መሆኑም እንዲታወቅ የማይፈልጉ አብረው ለመታየት በፍጹም የማይፈቅዱ ናቸው፡፡ ይሄ የእነሱ ችግር ብቻ ነው እያልኩ አይደለም ይህ ችግር እንደሌለባቸው ሁሉ በመመጻደቃቸው ችግሩ የእነሱም እንደሆነ ለማሳየት እንጅ፡፡
እንግዲህ ይሄ የሚያመለክተው አንዳች ነገርን ምክንያት አድርጎ መናናቅ ተፈጥሯዊ የሆነ ሰው የመሆን ደካማ ጎን መሆኑን ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ደካማነትም ተፈጥሯዊ እንደመሆኑ ሳንፈልግና ሳንፈቅድም ተገደን በሁሉም ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ይንጸባረቅብናል፡፡ ቆንጆ እኅት እራሷን እንደዛ አስውባ የፈጠረችው እሷው እንዳልሆነች እያወቀችም በፉንጋ እኅቷ ታፍራለች ትሸማቀቃለች እኅቷ መሆኗንም መናገር አትፈልግም አብራ መታየት ያሸማቅቃታል ባስ ሲልም እኅቷ መሆኗን ትክዳለች፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ለመናቅ የሚያበቁ ምክንያቶች ሌላው ቀርቶ የአንድ ቤተሰብ አባላትን እንኳን ያስተዛዝባል ግንኙነት ያሻክራል መለያየትን ይፈጥራል፡፡
እንግዲህ ይህ ችግር ድንቁርና የሚሆነው ተፈጥሯዊ መሆኑን ካለመገንዘብና እኛው እራሳችንም በሌላ መልክ በገዛ ቤተሰባችንም የምንፈጽመው በደልና ግፍ መሆኑን ካለመረዳት በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ባሉ ጎሳዎች መሀከል እራሱም አንደኛው በሌላኛው ላይ የሚፈጽመው በደል መሆኑንና የተለየ ነገር እንዳልሆነ ልብ ካለማለት ትግሬ፣ ኦሮሞ ምንትስ በመሆናችን ተናቅን ተገፋን በማለት ለፖለቲካዊ (ለእምነት አሥተዳደራዊ) ጉዳይ ፍጆታ ለማዋል የተነሣን እንደሆነ ነው ለማንም የማይጠቅም ተግባርና ከድንቁርናም ድንቁርና የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ተራው አማራ እራሱም በመሳፍንቱና በመኳንንቱ የተናቀ የተገፋ ለጋብቻ ለዝምድና የማይፈለግ የማይመረጥ የተጠላ የተረገጠ የተጨቆነ ነበርና፡፡
እንዲህ ስል ዘርን ምክንያት አድርጎ የሚፈጸም የመናቅና መገፋት በደል ትክክል ነው ይቀጥል እያልኩ አይደለም ምክንያት እየፈጠሩ መናናቅ ተፈጥሯዊ ቢሆንም በተቻለ መጠንም እንዲቀር መሥራትማ ይገባል፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ችግሩ ሁላችንም የምንፈጽመው ተፈጥሯዊ ችግር ነውና ተፈጽሞ ስናይ አይግረመን ለመጥፎ ዓላማም አንጠቀምበት ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው ጥቁርም የሰው ልጅ ሆኖ ሳለ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ምንም በደል ሳይኖርበት እስከዛሬም ድረስ የሥልጣኔ ጣራ ላይ ደርሰዋል አዋቂዎች ናቸው በምንላቸው በነጮቹ ግፍና በደል እየተፈጸመበት የሚገኘው፡፡ ጥቁሩ ጥቁር ስለሆነም ብቻ አይደለም በነጮቹም መሀከል እርስ በእርሳቸው አንዱ የዚህ ወይም የዚያ ዘር በመሆኑ ብቻ አንዱ ሌላውን ይንቀዋል ያገለዋል ወዘተረፈ.
እና ችግሩ እንዲወገድ መሥራቱ የሚገባ ቢሆንም ቀርፈን በማንቀርፈው ነገር ላይ ለመጥፎ ዓላማ በመጠቀም ጊዜያችንን ገንዘባችንን ሁሉን ነገራችንን ማባከን ኪሳራን እንጅ ትርፍን አያመጣም እንዲያውም ይሄ ችግር ሲነኩት ይብስ እብደሚገማ እንደሚገን አንዳች ነገር በመሆኑ የዚህ መድኃኒቱ ንቆ መተዉና ትኩረት ባለመስጠት እንዲረሳ ለማድረግ ቢጣር ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ንቀን የተውነው እንደሆነ ነው በሁለንተናችን ላይ ችግር የመፍጠር አቅም የሚያጣው፡፡
ወደቀደመው ነገራችን እንመለስና ወያኔ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ታጥቆ ተነሥቶ በግልጽና በስውር ይሄንን ሰይጣናዊ ተግባር እየፈጸመ ያለው በሌሎች ከእኛ ጋራ ተመሳሳይ የመንግሥት አሥተዳደር በተበራቸው ሀገራት ዘርን መሠረት አድርጎ የተፈጸመው ዓይነት ግፍ በደል በትግሬነቱ የተፈጸመበት ኖሮ ያንን ለመበቀል ሳይሆን “አሜን ብሎ የማይገዛልኝና የማይተኛልኝ ቀን ጠብቆ የሚበቀለኝ አማራ ነው!” ብሎ ስለሚያስብ፣ በዚህች ሀገር ላይ በብቸኝነት ነግሦ ለመኖር ካለው አንባገነናዊ ዓላማው አንጻር እና ከበረሀ ጀምሮ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ጠላት ከሆኑ ባዕዳን ከተሰጠው አማራን የማጥፋት ተልዕኮውና ዓላማው የተነሣ ነው፡፡ ስለሆነም “አማራ የለም!” በማለት አማራን ከወያኔ ሰይጣናዊ ጥቃት ልንታደገው አንችልም፡፡
ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንዳነሣሁት ኦሮምኛ በመናገራቸውና “የኦሮሞ” የሚባልን ባሕልና እሴት በመከተላቸው ኦሮሞ ነን እንደሚሉትና እንደተባሉት፤ የትግሬ የጉራጌ ወዘተረፈ. የሚባልን ቋንቋ ባሕልና እሴት በመከተላቸው ትግሬ ነን፣ ጉራጌ ነን ወዘተረፈ. እንደሚሉትና እንደተባሉት ሁሉ አማርኛ በመናገራቸው የአማራ የሚባልን ባሕልና እሴት የሚከተሉ እያሉ “አማራ ሊባሉ አይገባም አማራ የለም!” ማለት እጅግ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሲጀመር ጎሳ ብሔረሰብ ነገድ ሐሳባዊ እንደመሆኑ በዚህ መለኪያ ከሔድን አማራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የለም፡፡ ምክንያቱም አማራም እንደሌሎቹ የሰው ዘሮች ሁሉ የተገኘው ከአዳም ወይም ከሉሲ ስለሆነ አማራ በመሆኑ በተፈጥሮው ከሌሎቹ የተለየ አይደለምና፡፡
የጎሳ የብሔረሰብ የነገድ ህላዌ ሐሳባዊ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እያንዳንዱ ጎሳ ነገድ ብሔረሰብ ከተለያዩ አዳሞች ወይም ሉሲዎች የመጡ ባለመሆናቸው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ በእርግጠኝነት ጠልቆ ለመረመረ ሰውና የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኩነት ለሚያውቅ እያንዳንዱ ሰው ቢያንስ ከሦስት ቢበዛ ደግሞ ካምስትና ከዚያ በላይ የተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ያልተወለደ ዜጋ የለምና የሕዝቡ ስብጥራና ደም እንዲህ የተዋሐደ በሆነበት ሁኔታ ከማንም ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ያልተዋለዱ ያልተዋሐዱ የራሳቸው የብቻቸው አዳም ወይም ሉሲ ያላቸው አባላት ያሉት ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ፈጽሞ በሌለበት ሁኔታ ትግሬ ኦሮሞ ወዘተረፈ. ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ሊኖር ስለማይችል ከነዚህ ከነዚህ አንጻር አማራ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የሉም ሊባል ይችላል፡፡
ከዚህ በመለስ ግን ሳይንሳዊም ባይሆን በዘልማድ እየሠራንበት ነውና ኦሮምኛ ቋንቋ ቋንቋችን ነው ብለው ኦሮምኛ በመናገራቸው የኦሮሞ የተባለን ባሕልና እሴት በመከተላቸው ኦሮሞ የሚባሉ ከሆነ አማርኛ ቋንቋ ቋንቋችን ነው ብለው የአማራ የተባለን ባሕልና እሴት የሚከተሉት አማራ መባል አይገባቸውም የሚል ካለ ይሄ ሲበዛ የዋህና የማያስተውል ነው፡፡
ወደ ኋላም ዐየን ወደ ፊት የአንድን ብሔረሰብ አባላት እንዲህ የሚባሉ ብሔረሰብ ናቸው ለማለት እየተሠራበት ያለው መሥፈርት ቋንቋና ባሕል ከሆነ ይህ መሥፈርት አማራ ላይ ሊሠራ የማይችልበት ምንክያት ምንድን ነው? ብሔረሰቦች የሚፈጠሩት በጊዜ ሒደት አንደኛው ከነበረው እየወጣ የራሱን ቋንቋና ባሕል አዳብሮ ሲገኝ ነው እንጅ ከሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ከተለያየ ምንጭ ተፈጥረው መጥተው ቁጭ ቁጭ ያሉ ኅብረተሰባዊ ቡድኖች አይደሉም፡፡ ሁሉም የተቀዱትና የወጡት ከአንድ የሰው ዘር ምንጭ ነው፡፡
ወደ ሁለተኛው ቡድን ማለትም “አማራ በአማራነቱ ብቻ መጠቃቱ የጨነቃቸውና አማራ ከዚህ ጥቃት መትረፍ የሚፈልግ ከሆነ በቅናትም ይሁን በሌላ ምክንያት ለመጠቃት ምክንያት የሆኑበትን ማንነቱን፣ እሴቶቹን፣ ትውፊታዊ ሀብቱን፣ ቅርሱን፣ መለያውን፣ ኩራቱን፣ የሥልጣኔ ፍሬውን ወዘተረፈ. መተው፣ መጣል፣ አሳልፎ መስጠት፣ መሠዋት ወይም የእሱ መሆኑን አለመናገር አለመመስከር እንዲጠፉ መፍቀድ አለበት” ብለው ወደሚያምኑትና ይሄንንም በማድረግ ከሌሎቹ ጋር ለመግባባት ወደ ሚሞክሩትና ከዚያም አልፈው ከወያኔና ከሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ጋር ተባብረው ወደሚሠሩት ጅሎች፣ ራስ ወዳዶች፣ ፈሪዎች፣ ከሀዲዎችን ስናይ ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ በአንደበታቸው እንዲህ ብለው ሲናገሩ አትሰሟቸውም ይሄንን ብለው እንደሚያስቡና እንደሚያምኑ የምታውቁት በድርጊቶቻቸው ነው፡፡
ከአማራ ውጪ የሆነ ደካማ ዜጋ እንዲህ ብሎ ቢያስብ ቢሠራም ባልገረመኝ አማራ ሆነውና የአማራ ልኂቃን ሆነው እንዲህ የሚያስቡ የሚያደርጉም ዜጎች መኖራቸው ነው እኔን በእጅጉ የሚደንቀኝ፡፡ አማራ ከሌላው የተለየ ፍጥረት ነው ሌላው ከአማራ ያነሰ ነው ማለቴ ሳይሆን አማራ የሆነው የራሱ ለሆነው እሴት ሊገደው ሊቆረቁረው ሊቆጭ ባለአደራነት ሊሰማው ሲገባው ይሄንን ሳያደርግ መቅረቱ በእጅጉ ቢገርመኝ ነው፡፡
መቸስ ወያኔ የተሳካለት ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊያንን ከዳር እስከ ዳር የነበረንን ብሔራዊ መግባባት ድብልቅልቁን ማውጣቱ ደብዛውን ማጥፋቱና በታሪክ በባሕል በማንነት እሴቶቻችን ላይ ልዩነትና አለመግባባት ፈጥረን የኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የአማራ ብቻ እንደሆነ እንዲቆጠር በማድረግ የማንም እንዳይሆን አማራ ነን በሚሉት ሳይቀር የጥፋት ዘመቻ እንዲዘመትበት ማድረጉ ላይ ነው፡፡
እጅግ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር የጥፋት ኃይሎቹ የሚያደርጉትና ጥያቄያቸውን ፍትሐዊና ትክክለኛ እንዳይሆን የሚያደርገው “የኢትዮጵያ ይሄ ብቻ አይደለም (የአማራ ብለው የሚያስቡት) ሌላም አለ እሱ ይጨመር ማለት ሲገባቸው በጥቅሉ ይሄ የነበረው አይደለም እሱ መጥፋት አለበት ይሄ እኛ የምንለው ነው መሆን ያለበት” በማለት ከባድ የጥፋት ዘመቻ ማድረጋቸው ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የተበደልን የተገፋን ነን ብለው እራሳቸውን ከሚገልጹት ወገኖች በኩል ያለው አተያይና አስተሳሰብ ድርጊትም ነው፡፡
ጨቋኝ ገዥ ከተባለው ወገን የሆነውና ታደርሱብን ትፈጽሙብን ነበር ተብሎ እንደተነገረው “የተፈጸመባቸውን ግፍ በደልና መገፋት መገንዘብ መረዳት አለብኝ” ብሎ የሚያስበው ተራማጅ ነኝ ባይ የወያኔ የኦነግና የሌሎች የጥፋት ኃይሎች የጥፋት ሥራቸው ተባባሪዎች ከሀዲያኑ ለዚህ ስሕተት የዳረጋቸው ነገር ቢኖር ስለራሳቸው ስለታሪካቸው ምንም የሚያውቁት ነገር የሌለ መሆኑና በወያኔና በሌሎች የጥፋት ኃይሎች የሚወራው የተቀነባበረ የፈጠራ ስም ማጥፋት እውነት መስሎ የሚታያቸው መሆኑ ነው፡፡
እንዲህ በማሰባቸው ነው ከሀዲያኑን ከወያኔና ከሌሎቹም የጥፋት ኃይሎች ጋር አብሮ በመቆምና በመሰለፍ የአማራ ተብሎ በተፈረጀው በኢትዮጵያ ታሪክ ባሕልና የማንነት እሴቶች ላይ በጥፋት አብረው እንዲዘምቱ እንዲተባበሩ የሚያደርጋቸው፡፡ አሁን አሁን እግጅ አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ቀድሞ የምናደንቃቸው በተቃውሞው ጎራ ያሉ አንዳንድ የአማራ ልኂቃን ሳይቀሩ የዚህ ወያኔ የፈጠረው ምልከታ ሰለባ ሆነው የወያኔና የኦነጋዊያን የጥፋት ሥራና የጥፋት ዓላማ ተባባሪ ሆነው እያየን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እነኝህን ዓይነት ወገኖችን ወያኔን ለመታገል ቆርጠው በተሰለፉ ቡድኖችና ድርጅቶችም ጭምር ታገኟቸዋላቹህ፡፡
ይህ ውድቀትና አደጋ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሣ ችግሩን ከስሩ ማየትና እነኝህ ወገኖችን ያሳሳተውን ብዥታ ማጥራትና ወደ ትክክለኛው አስተሳሰብ ማምጣት አስተላጊ ሆነ በመገኘቱ ይሄ ጽሑፍ ተጽፏል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ ላይ፡-
- አማራ እንዲህ እንዲህ አድርጓል እየተባለ በወያኔና በሌሎች የጥፋት ኃይሎች አማራ እንዲጠላ እየተነዛ ያለው ሁሉ ወሬስ እውነት ትክክል ነው ወይስ ሐሰት?
- ለመሆኑ አማራ እንደ ሕዝብ በዳይ፣ ገፊ፣ ጨቋኝ ሆኖ ያውቃል? ወይስ ተበዳይ፣ ተገፊ፣ ተጨቋኝ?
- እስከአሁን የኢትዮጵያ ተብሎ የሚገለጸው ታሪክ ባሕል እሴቶች የማንነት መለያዎች ሁሉስ የጥፋት ኃይሎች እንደሚሉት እውን የአማራ ብቻ ነው ወይ?
- የአማራ የሆኑትስ አማራ ኢትዮጵያዊ እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ሀብት ሆነው መቆጠር መጠበቅ ይኖርበታል እንጅ የአማራ ስለሆነ ይጥፋ ተብሎ ሊፈረድበት የሚችልበት የሕግ የፍትሕ አግባብ አለ ወይ?
- የፍትሕ የእኩልለት ጥያቄ አለን በማለት የእኛም ታሪክ ባሕል እሴቶች ይታወቅ ይመዝገብ ይዘከር የሚሉ ወገኖችስ የአማራ የሚሉት እንዲጠፋ እንዲወገድ እንዳይታሰብ እንዳይዘከር ቦታ እንዳያገኝ ለማድረግ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለሀገርና ለሕዝብ ህልውና እድገት ሥልጣኔ ጠቃሚ ወይስ አጥፊ፣ መፍትሔ ሰጪ ወይስ ተጨማሪ ችግር ፈጣሪ?
- ሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላቸውን፣ ሥልጣኔያቸውን፣ እሴቶቻቸውን ወዘተረፈ. በእኩል ዕድል ማቅረብ የሚችሉባት ሚዛናዊ መድረክና መስተንግዶ የሚያገኙባት ሀገር መሆን አለባት ሲባልስ ምን ማለት ነው? ትክክለኛና አመክንዮአዊስ ነው ወይ?
እነኝህንና ተያያዥ ነጥቦችን በጥልቀት እናያለን፡፡ ከርእሰ ጉዳዩ ግዝፈት አንጻር ጽሑፉ ረዘም ብሏል ለዚህ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
እነዚህ ወገኖች ይሄንን በማድረጋቸው ሀገርንና ወገንን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል ሁነኛ አኪያሔድ መስሎ ይታያቸዋል፡፡ በእርግጠኝነት ልነግራቸው የምፈልገው ነገር ቢኖር ኢፍትሐዊና አግባብ ያልሆነን ጥያቄ በመቀበልና በማስተናገድ የሚገኝ ሰላምና ደኅንነት ሊኖር የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ሰላምና ደኅንነት በፍትሐዊና ትክክለኛ መሠረት ላይ ካልተመሠረተ የሚገኘው ሰላም አስተማማኝና ዘላቂ አይሆንም፡፡ እውነትን ለድርድር ማቅረብ ትርፉ ኪሳራ እንጅ መልካም ሊሆን አይችልም፡፡ ለሀገርም ለወገንም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት እንዲመጣ ከተፈለገ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእውነት ለአመክንዮ ለእፍትሕ ታማኝ ሆኖ ክብርና ዋጋ ሰጥቶ መቅረብ ግዴታው ነው፡፡
ዳኛው ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ እንደየ ሥራችን ይፈርደናል፡፡ ችግሩ የጥፋት ኃይሎች ዳኛው ታሪክ ከሆነ የጥፋት ዓላማቸው ፍላጎታቸውና ማግኘት የሚፈልጉትን ኢፍትሐዊ ጥቅም ማግኘት እንደማይችሉ አውቀው የሀገርን ታሪክ በመቶ ዓመታት መገደባቸውና ከዚያ በፊት ያለውን በዓይን የሚታይ በእጅ የሚዳሰስ ቅርስ አሻራ ማስረጃና መረጃ ያለውን የሀገሪቱን ታሪክ ሁሉ ተረት ተረት የፈጠራ ወሬ ነው ብለው አቋም መያዛቸውና አንቀበልም ማለታቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ለአመክንዮ ለሞራል (ለቅስም) ለፍትሕ መገዛት በእነዚህ እሴቶች መዳኘት ፈጽሞ ከማይፈልግ አካል ጋር ተግባብቸና ተስማምቸ እሠራለሁ ብሎ ማሰብ እጅግ ቂልነትና ከባድ ዋጋም የሚያስከፍል ስሕተት ነው፡፡
ያለን አማራጭ በጥፋት ዓላማና ፍላጎት ሰክረው የናወዙትን እነኝህን አካላት ወደ ትክክለኛው ተቀባይነት ወዳለው አስተሳሰብ እንዲመጡ ሳይታክቱ ለማግባባት መጣር ነው፡፡ ይህ የማይሆን የማይረዱ የማይገባቸው ከሆኑና አልሆን ካለ ግን ቆርጦና ጨክኖ መፋለም ብቻና ብቻ ነው ለው አማራጭ እንጅ ኢፍትሐዊ ኢአመክንዮአዊ ኢሞራላዊ ጥያቄዎቻቸውን ተቀብሎ ማስተናገዱ አይደለም መፍትሔው ምክንያቱም እንዳልኳቹህ ስሕተት በመሥራት የሚመጣ ሰላምና ደኅንነት የለምና ሰላምና ደኅንነት በአለት ላይ ሲመሠረት እንጅ በድቡሽት ላይ ሲመሠረት ዘላቂ ሊሆን አይችልምና፡፡
ይሄንን ማስጠንቀቂያ ተላልፎ ኢፍትሐዊ ኢአመክንዮአዊ ኢሞራላዊ ኢሰብአዊ ጥያቄዎች ካሏቸው ወገኖች ጋር በነገሮች በቂ ግንዛቤና እውቀት ካለመያዝ በጥፋት ኃይሎች የሚወራው ትክክለኛ እውነት እንደሆነ በመገመት ከእነሱ ጋር የሚሠራ ለሀገርና ለወገን ተቆርቀዋሪ የሚመስለው ወገን ካለ በሀገርና በወገን ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ወያኔና ሌሎቹም የጥፋት ኃይሎች ካደረሱትና ከሚያደርሱት ልተለየ የማይሆን መሆኑን አጥብቄ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ምክንያቱም ሰላምና ደኅንነት ከጥፋት ኃይል ጋር በመሥራት ስለማይመጣ ሰላም በአለት መሠረትላይ እንጅ በድቡሽት ላይ ተመሥርቶ ዘላቂና አስተማማኝ ስለማይሆን፡፡
እነኝህ ወገኖች ስንሰማቸው አንባገነንነትን ጭቆናን አፈናን ተቃዋሚ ታጋይ ኮናኝ ነን እያሉ ሀገርና ሕዝቧ ዕድሜ ዘመናቸውን የፈጁበትን ስንትና ስንት የተደከመበትን የሀገርና የሕዝብ ሥልጣኔ ፍሬ የሆኑትን እሴቶች የጠላት ንብረት አድርገው የአማራ ነው ሊበለጽግ ሊያድግ ሊስፋፋ አይደለም በጭራሽ ልናየው አንፈልግም በማለት ለማጥፋት ወገባቸውን አስረው ሲሠሩ አንባገነንነትን ጭቆናን አፈናን እንቃወማለን እንታገላለን ባዮቹ እነሱ እራሳቸው የወጣላቸው አንባገነን ጨቋኝ አፋኝ አጥፊ እንደሆኑ መገንዘብ የሚችል ጭንቅላት ያላቸው ቡድኖች አይደሉም፡፡
ይሄንን መገንዘብ መረዳት የተሳናቸው ወይም የማይፈልጉ የኢሞራላዊ፣ የኢፍትሐዊ፣ የኢሰብአዊ፣ የኢአመክንዮአዊ አስተሳሰብናና አግባብነት የሌለው በቀል የተሞና ሰብእና ያላቸው አካላት ከዚህ የደነቆረና አጥፊ አስተሳሰባቸው ካልተፈወሱ በስተቀር በምንም መመዘኛ ቢታዩ ለሀገርና ለየትኛውም ሕዝብ የሚጠቅሙ የሚበጁ አይደሉም፡፡ እንኳንና ለሌላ ለየግላቸውም የሚበጁ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ሀገርንና ወገንን የጠቀሙ መስሏቸው ከአጥፊ አስተሳሰባቸው ሳይለወጡ ለመለወጥም ሳይፈልጉ ከነአጥፊ አስተሳሰባቸው ከነሱ ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚሞክሩ ወገኖችን በእርግጠኝነት አብረዋቸው በመሥራታቸው የሚፈልጉትን ውጤት ማምጣት አይችሉም ያልኩት፡፡
የወያኔና እንደ ኦሕዴድ ደሕዴግ ወዘተረፈ. ያሉ የወያኔ አሻንጉሊት ድርጅቶች፣ የኦነግና የሌሎች የጥፋት ኃይሎች ጥፋት ምንድን ነው?
ይህ ጥፋት አማራን “ጠላትና መጥፋት ያለበት!” ብለው ከመደምደማቸው የሚመነጭ የጥፋት ተግባር ነው፡፡ የሚያደርሱትንም ከባባድ የጥፋት ተግባር ለመደገፍ በአማራ ላይ ከባባድ የሆኑ የፈጠራ ክሶችንና የስም ማጥፋቶችን በማናፈስ የጥፋት ተግባራቸውን ለመደገፍ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ከጥፋቶቹ ጥቂቶቹ፡-
- የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ያለው ታሪክ የአማራ ታሪክ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ፈጠራ ነው ተረት ተረት ነው ይወገድ ይጥፋ ተብሎ በ18 (አሁን ጨምሮ ሊሆን ይችላል) ዩኒቨርስቲዎች (መካነ ትምህርቶች) የታሪክ ትምህርት እንዲዘጋ ማድረጋቸው፣ “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ነው” በሚል የደነቆረ ሽፋን የሀገር (እነሱ የአማራ ይሉታል) እሴቶች የነበራቸውን ቦታ እንዲያጡ ብሎም እንዲጠፉ ማድረጋቸው፡፡ ለምሳሌ አማርኛ ዛሬ ብሔራዊ ቋንቋ አይደለም የሥራ ቋንቋ ነው ብለዋል የሥራ ቋንቋ እንደመሆኑ ግን እንደ የሥራ ቋንቋነቱ የመጠናት የመመርመር የመበልጸግ መብቱን ነፍገው በየዩኒቨርስቲው (መካነ ጥምህርቱ) ቀድሞ የነበሩትን የአማርኛን ሥነጽሑፍ ማዕከል ያደረጉ ክፍለ ጥናቶችን (ዲፓርትመንቶችን) እንዲዘጉ ማድረጋቸው ዋና ዋና ዎቹ ናቸው፡፡
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ ሆን ተብሎ የሌሎቹ ተዘንግቶ የአንድ ዘር ብቻ እንዲጻፍ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ በጣም ስሕተት ነበር፡፡ የሚገርመው ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም ቦታ የተጻፈ የሀገራችን ታሪክ አንዱም ቢሆን “የአማራ ታሪክ ነው” ተብሎ የተጻፈ አለመሆኑ ነው፡፡ እስኪ የሩቁን ትተን የቅርቡን የአድዋን ድል እንይ መቸና የትስ ነው የአድዋ ድል የአማራ ታሪክ ነው ተብሎ የሚያውቀው? በዚህ ታሪክ ላይ የሌሎች ብሔረሰቦች ጉልህ ድርሻ አልተጻፈም ወይ? እኒህንና መሰል ጥያቄዎችን እያነሣን ስንጠይቅ የጥፋት ኃይሎቹ የጥፋት ሥራ አግባብነት ከሌለው ጥፋቻ ብቻ የመነጨ እንጅ ተጨባጭነት ያለው ሆኖ አይገኝም፡፡
እርግጥ በታሪክ ላይ አንድ ዓለማቀፋዊ እውነታ አለ፡፡ ሁሌም ታሪክ የሚጻፈው ለገዥዎች ባደላ መልኩ ነው፡፡ ሰፊውን ቦታም የሚይዘው የእነሱ ሕይዎት እንጅ የዝቅተኛው ኅብረተሰብ ክፍል ሕይዎት አይደለም፡፡ ይሕም ቢሆን በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ በወቅቱ የነበረው ኅብረተሰብ ሕይዎት መጠቀሱ አይቀርምና ገዥዎቹም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸውና እንዴት ሆኖ የኢትዮጵያ ሊባል አይገባም ይጥፋ ሊባል እንደሚችል አይገባኝም፡፡ “የዝቅተኛውን ኅብረተሰብ ሕይዎት ያዘለ አይደለምና የተሟላ አይደለም” አንድ ነገር ነው የነበረው የየወቅቱ ዝቅተኛ ኅብረተሰብ ሕይዎት ካለና የሚታወቅ ከሆነ እሱን አምጥቶ ማሟላትም የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ እንዲያው ግን በደፈናው የገዥውን ክፍል ብቻ ነውና የሚያወራው የኢትዮጵያ ታሪክ ሊባል አይገባል እንዴት ሊባል ይችላል? የማን እንበለው ታዲያ? ኢትዮጵያዊያን አይደሉም ወይ? ኢትዮጵያዊያን እንደመሆናቸው ያለው ታሪክ በቂ በሚባል ደረጃ የዝቅተኛውን ኅብረተሰብ ክፍል ሕይዎት የያዘ የገለጸ አለመሆኑ እንዳለ ሆኖ እንዴት ነው የኢትዮጵያ ሊሆን ሊባል የማይችለው? የተሟላ አለመሆኑ ይገለጻል እንጅ እንዴት የኢትዮጵያ አይደለም ሊባል ይችላል? ይሄስ ችግር ዓለማቀፋዊ አይደለም ወይ? ታሪክ ሁሌም የሚጻፈው በአሸናፊዎች እንደመሆኑ አድልኦ ግነትና ውስንነት ቋሚ የታሪክ ሰነዶች ችግሮች አይደሉም ወይ? ይሄ በመሆኑ እንደእናንተ ሁሉ የሀገራችን ታሪክ አይደለም ብሎ ታሪኩን የጣለ ያጠፋ እንዲጠፋ የሚሠራ የሠራ ሀገር ማን አለ? እስኪ ጥቀሱልን?
መቸም በአንዲት ሀገር ላይ ደናቁርት ሥልጣንን ሲቆጣጠሩ አደጋው ይሄው ነው፡፡ በዚያች ሀገር የሚያደርሱት ጥፋት ሊነገር ከሚችለው በላይ ነው፡፡ በኛም ሀገር ላይ የሚታየው ይሄው ነው፡፡
ታሪክ ማለት በሀገሪቱ ያሉ የሁሉንም ብሔረሰቦች እሴቶች “እኩል” ስፍራ ሰጥቶ ማስተናገድ እንደሚጠበቅበት የብሔረሰቦች ሙዚየም (ቤተ መዘክር) ማለት አይደለም፡፡ በቤተ መዘክር እንኳን እራሱ በመርሕ ደረጃ እኩል ስፍራ ይባላል እንጅ ይሄንን አሠራር ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ በየትም ሀገር የለም፡፡ ቅንነት ከማጣት ሳይሆን ካለው ተፈጥሯዊ ገዥ ሕግ አኳያ እንጅ፡፡ ምክንያቱም አንደኛው በርካታ የበለጸጉ የታሪክ የባሕል የመሳሰሉት ቅርሶችና መገለጫዎች እሴቶች ሲኖሩት ሌላኛው ደግሞ የሌላኛውን ያህል የሌለው ይሆናልና፡፡
እናም “የሀገር ታሪክን ድርሻ ለየብሔረሰቡ እኩል እናከፋፍላለን!” ማለት አባባሉ ቀናና ፍትሐዊ ቢመስልም አላዋቂነት የተጫነው ቂልነትና ነባራዊውን ሀቅ ያልተገነዘበ አስተሳሰብ ነው፡፡ ሲጀመር ጀምሮ ዓለም የኢፍትሐዊነት መድረክ ናት፤ የአሸናፊዎች ሀብት ናት፡፡ ታሪክ የሚባለውም ይሄ ነው ሌላ አይደለም፡፡ በዚህች ኢፍትሐዊነት በገነነባት ዓለም ከታሪክ ዳቦ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት አሸናፊዎች እንደሆኑ መገንዘብ አለመቻል እጅግ አለመብሰል ነው፡፡ ባንወደውም እውነታው ይሄው ነው፡፡ እኩል መከፈል አለበት በማለታችንም ልናመጣው የምንችለው ለውጥ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ዘመኑን ወደ ኋላ መልሰን በዚያች ሀገር ያሉ ብሔረሰቦችን በአንድ የጊዜ ስፍር ላይ አስጀምረን አንተ ይሄን አንተኛው ደግሞ ይሄን ሥሩና መጨረሻ ላይ በሀገሪቱ ታሪክ ላይ እኩል ድርሻ ይኖራቹሀል ብለን ማበጃጀት ከቶውንም አንችልምና፡፡ ያለው አማራጭ ተወደደም ተጠላ ያለውን የተገኘውን ይዞ መጓዝ ብቻና ብቻ ነው፡፡
ታሪክ ማለት የሚያስደስተው የሀገርና የሕዝብ ገጽታ ማለት ብቻ ሳይን የማያስደስተውና የሚያስከፋውም አጠቃላይ የሀገርና የሕዝብ ያለፈ የነበረ ሁለንተናዊ መስተጋብር ወይም ገጽታ ማለት ነው፡፡ ይህ ታሪክ እነ እከሌን ስለሚያስከፋ ወይም ስለሚያስቀና ከሀገር ታሪክ ተቆርጦ ይጣል ይወገድ ማለት ድንቁርና ወይም የታሪክን ምንነት አለማወቅ ነው፡፡ ታሪክ አስከፋም አስደሰተ ተጠብቆ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ቀጣዩ ትውልድም ከደካማውና ከጠንካራው ጎኑ ይማርበታል፡፡
ይሄንን እውነታ መገንዘብ መዋጥ የሚከብዳቸው ወገኖች ካሉ ለዚህ ድንቁርና የዳረጋቸው እራሳቸው በራሳቸው ላይ የጫኑት ጠባብና ዘረኛ አስተሳሰባቸው ነውና ይሆነናል ይበጀናል ብለው እስከያዙት ጊዜ ድረስ ከዚህ ደዌያቸው እንዲፈወሱ ልንረዳቸው የምንችለው ነገር ባለመኖሩ እጅግ እናዝናለን፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት እነሱ እራሳቸው የዚህች ሀገር ታሪክ የአማራ ታሪክ ነው አሉ እንጅ በየትኛውም የታሪክ ሰነድ ላይ አማራ የኔ ነው ያለበት ዘመን ኖሮ አያውቅም፡፡ ነገሥታቱ ከአማራ የወጡ ቢሆኑም በአማራ ስም ግን ይህችን ሀገር ለአንድም ቀን ገዝተው አሥተዳድረው አያውቁም፡፡ ሀገሪቱ ለማስተናገድ ትቸገር ወይም አትፈቅድ የነበረው አረማዊ ኢአማኒ በሌላ አጠራር ጋላ (ልብ በሉ ጋላ የብሔረሰብ መጠሪያ አይደለም አረማዊ ወይም አሕዛብ ማለትም ያላመነ ያልተጠመቀ ከሚለው ቃል ጋር በተለዋዋጭነት የሚያገለግል ቃል ነው የቤተክርስቲያን መጻሕፍት ግብጽ ውስጥ አሕዛብ ያፈረሷቸውን አብያተክርስቲያናት “ጋላት” ወይም “ጋሎች አፈረሱት” በማለት ይገልጻሉና) እናም እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይነግሥ ብቻ ነው እንጅ አማኝ እስከሆነ ጊዜ ድረስ የዘሩ ማንነት ቦታ የሚሰጠው አልነበረም በዚህም ምክንያት ነው በጥንታዊት ኢትዮጵያ ከአገው ከትግሬም ከኦሮሞም የተወለዱ ነገሥታት ሊኖሩን የቻሉት፡፡ ንጉሥነት በዘር የሚወረስ መሆኑና የሥልጣን ሽሚያ የነበረ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፡፡ የአማራ የምንትስ የምንትስ የሚል ነገር የመጣብን ደናቁርቱ የጥፋት ኃይሎች ከመጡ በኋላና በእኩይ መነጽራቸው ወደኋላ እየተመለከቱ እኩዩ መነጽራቸው የሚያሳያቸውን እኩይ ነገር መናገር ከጀመሩ ጊዜ በኋላ ነው፡፡
እንዲህ ባለ ስብጥር የተሠራውን የሀገር ታሪክ ዛሬ እኩያኑ በጥቅሉ “የአማራ” ብለው በመፈረጅ “አማራ የራሱን ታሪክ፣ ባሕል፣ አስተሳሰብ፣ ማንነት፣ ሥልጣኔ ወዘተረፈ. በተቀረው ሕዝብ ላይ ሲጭን ቆይቷል እንዲጭን አንፈቅድም! የተጫነውንም እናስወግዳለን” ብለው አረፉት፡፡
ሲጀመር “የኢትዮጵያ” ተብሎ የሚጠራው ባሕል፣ አስተሳሰብ፣ ማንነት፣ እሴት ሥልጣኔ የአማራ ሕዝብ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀው የጥፋት ኃይሎች የአማራ የሚሉት ባሕል፣ አስተሳሰብ፣ ማንነት፣ ሥልጣኔ በራሱ ሒደት ከሌሎቹም ብሔረሰቦች መልካም መልካሙን የተሻለ የተሻለውን የላቀ የላቀውን ተሞክሯቸውን አውጣጥቶ ወስዶ እራሱን የቀረጸ የገነባ እንጅ የአማራን ብቻ እያለ እየለየ እራሱን የቀረጸ አይደለም፡፡ አንደኛው ብሔረሰብ የበለጠ አዋጥቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና መስፈርቱ “የማን?” ሳይሆን “የትኛው የተሻለ የሠለጠነ?” የሚለው ነውና የማንትስ የማንትስ ብለን ጥያቄ ልናነሣ የምንችልበት አግባብ ሊኖር አይገባም፡፡ ነው ወይስ ደናቁርቱ ሊሉን የፈለጉት በዚህ የኢትዮጵያ ተብሎ በሚጠራው የአማራ መካተት አልነበረበትም? ለምን?
ደናቁርት ሆይ! ደዳብት ሆይ! ምንም ነገርን ከማንም ሳይወስድ የራሱን ብቻ ባሕል በሉት አስተሳሰብ ቋንቋ በሉት ሥልጣኔ ይዞ እንደ ደሴት እራሱን ነጥሎ ብቻውን የኖረና የሚኖር የገነባና የሚገነባ ብሔረሰብ ከኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ከመላው ዓለም አንድ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ አንድ ብቻ እንኳን ልትጠቅሱልኝ ትችላላችሁ?
በታሪክ አጋጣሚ ከሞላ ጎደል ያለውን የሀገራችንን ዘመን ከአማራ የወጡ ነገሥታት የመሪነትን ሚና እንደመጫወታቸው ሌሎቹ ወገኖች ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን እንዲተውና የተሻውን፣ የበለጠውን፣ የላቀውን አስተሳሰብ እንዲጨብጡ ማድረጉ፣ መጣሩ፣ ማሠልጠኑ ኩነኔው፣ ኃጢአቱ፣ ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው? ሥልጣኔ እንዴት ሆኖ የተስፋፋ ነው የሚመስላቹህ? ጠቃሚና የተሻሉ አስተሳሰቦችን፣ ተሞክሮዎችን ልምዶችን አንዱ ከሌላው በመውሰድ ያንንም ሥራ ላይ በማዋል አይደለም ወይ?
አየ መለስ ነፍስህን አይማረው የደንቆሮ መጨረሻ፡፡ እሱ ደንቁሮ ግብረአበሮቹንም አደንቁሮ ሀገርን ማጥ ውስጥ ከቷት ሔደ፡፡ እንኳን እዚህ ለዚህ ወገን ለወገን ቀርቶ ስንት ኢትዮጵያዊ እሴት ነው ከእኛ ወጥቶ ለሌላው ዓለም የተረፈው? ሌሎቹ ብልጦቹ ከእኛ ወስደው የተጠቀሙ ስንት እግዳሉ ይታወቅ አይደለም ወይ? ይህች ሀገር የአማራ እሴቶች ያላቹህትን ሁሉ አጥታ ምን ይቀራታል? ታዲያ እነኝህ እሴቶች ጠቃሚ መሆናቸው ከታወቀ ከተመሰከረ፤ እኮ በምን ምክንያት ነው የአማራ ስለሆኑ ብቻ ይጥፉ ይወገዱ የሚባለው? ይሄ ምን ማለት ነው? አማራ ከዚህ በኋላ ለሀገሩ ለወገኑ መሥራት ማዋጣት አይችልም አይኖርበትም ማለት ነው? ከዚህ በኋላ በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ሥልጣን ኃላፊነት መያዝ አይችልም ማለት ነው? አዎ ይሄንን ማለታቹህ እንደሆነ በምትሠሩት ሥራ ሁሉ አረጋገጣቹህ፡፡
ግን በ 21ኛው መቶ ክ/ዘመን እንዲህ ዓይነት የድንጋይ ዘመን የአረማውያን የደዳብት የደናቁርት አስተሳሰብን ሥራ ላይ ለማዋል መሞከር የለየለት እብደትም ነው? ይቻላልስ ወይ? እስከ አሁን እንደቻላቹህ ነገም የምትችሉ ይመስላቹሀል ወይ? እኔ ሆኖ ከማየቴ በፊት ወያኔና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችም የፈለጋቸውን ያህል ሲጠቡ ሲደነቁሩ ሲደድቡ ቢኖሩ የዚህን ያህል ይጠባሉ ይደነቁራሉ ይደድባሉ ብዬ ለማሰብ እጅግ ይቸግረኛል፡፡ እጅግ ያሳዝናል እውነታው ይሄው በመሆኑ፡፡
የሚጠቅም ሆኖ እስከተገኘ ጊዜ ድረስ እምየ ኢትዮጵያና ሕዝቧ አይደለም ከአማራ ባሕር ተሻግራም ከአቦርጁኖችም ቢሆን ትወስዳለች፡፡ እንደመስጠታችንም የወሰድነውም አለ፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠቅም የሠለጠነ የበሰለ አስተሳሰብ ማለት ይሄ ነው፡፡ የእከሌ ነው የእከሌ ነው እያሉ ማጥፋቱ አይደለም እሽ ደናቁርት?
አማራ ምን ባደረገ ነው የዚህን ያህል የሚጠላው? ሌሎቹን ብሔረሰቦች ይዞ መልካም ሥራ የሠራ፣ ለዚህች ሀገር ምኑንም ነገሩን ሳይሰስት የመጨረሻ መሥዋዕትነት እየከፈል ሀገሪቱን በነጻነቷ የኮራች የደመቀች ባለታሪክና የሥልጣኔ መሠረት እንድትሆን ማድረግ የቻለ ሊደነቅ ሊከበር ጎሽ ሊባል ሊመሰገን ይገባል እንጅ እኮ በምን ሒሳብ ነው ስንት የሆነላትን ሀገር ታሪክና እሴት ገደል ከቶ፣ በመቶ ዓመት ተገድቦ፣ ከንቱ አመድ አፋሽ ተደርጎ በገዛ ወገኖቹ እንደጠላት በክፉ ዐይን ሊታይ የሚገባው?
ዛሬ ላይ ወያኔ በሠራው የአማራን ስም የማጠልሸት ሠይጣናዊ የክፋት ሥራው አማራነትና እሴቱን እንኳን በሌላው ብሔረሰብ በገዛ አባላቱ እንኳን አላስፈላጊ የሚጠላና የሚያሳፍርም ማድረግ የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
አንድ ዓለማቀፋዊ እውነታ አለ፡፡ ከአንድ በላይ ብሔረሰቦች ባሉበት ሀገር የአንድ ብሔረሰብ የበላይነት (Domination) የማይቀር ተፈጥሯአዊና የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ የትም ዓለም ያለው ተሞክሮ ከዚህ የተየ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም የተለየች ልትሆን የምትችልበት ተአምር የለም፡፡ እንዲያውም ግፍንና በደልን በተመለከተ ተመሳሳይ የአሥተዳደር ሥርዓት ከነበራቸው ሀገራት እንጻር ሀገራችን ስትታይ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ምስክርነት ከጥንት ጀምሮ ሕዝቧ እግዚአብሐርን አምላኪ ሕዝብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሌሎቹ ሀገራት ሲፈጸሙ የነበሩ የዘር ልዩነትን መሠረት ያደረጉ ግፎችና ኢሰብአዊ ድርጊቶች ፈጽሞ አልነበሩም አልተፈጸሙም፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ላይ በርካታ ብሔረሰቦች አናሳም ሆኑ ምን ሠፍረው ያሉበት ቦታ ለምና አረንጓዴ ሆኖ የምናገኘው፡፡ በዚህች ሀገር የብሔር ጭቆና ፈጽሞ አልነበረም፡፡
“የብሔር ጭቆና አለ! የኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራው ይሄ ይሄ ባሕል የማን ነው? የአማራና የትግሬ አይደለምን? የብሔር እኩልነት ይስፈን!” እያለ ጥያቄውን ያነሣውና ያራገበው ለወያኔና ለሌሎችም የጥፋት ኃይሎች መሠረት የሆነው የአማራ ተወላጁ ዋለልኝ መኮንን መሆኑ ይታወቃል፡፡ እኔ ይሄንን የዋለልኝ አስተሳሰብ የምኮንንበት ምክንያት ዋለልኝ ትግሬን ከጨመረ ለምን ሌሎቹህ እንደተወ ሊገባኝ ስላልቻለ ነው፡፡
ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ከትግሬ ይልቅ የአገው ብሔረሰብ ጉልህ አሻራ አለውና የማስተዋል ችሎታው ደካማ ከመሆኑ የተነሣ ካልሆነ በስተቀር የሌሎቹም አሻራ እንዲሁ በኢትዮጵያ ባሕል ሥልጣኔ ማንነት ነጻነት እሴት ላይ ጉልህ ነው፡፡ እንዲያውም ካለስ ትግርኛ የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ አያውቅም ትግሬ በነበሩት ንጉሥ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመንም እንኳ ንጉሡ ሲሠሩ የነበሩት በአማርኛ ነበር፡፡ መኳንንቶቻቸው ለምን? ብለው ለጠየቋቸው ጥያቄ ሲመልሱ “አማርኛ የአክሱም ነገሥታት ቋንቋ ነው ቤተመንግሥት ቤቱ ነው እኔ ላስወጣው አይገባኝም” ነበር ያሉት፡፡ ኦሮምኛን የወሰድን እንደሆነም ያውም በጎንደር ዘመን ለአጭር ጊዜም ቢሆን የመንግሥት ቋንቋ ለመሆን በቅቶ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉና የተሻለ ተሳትፎ የነበራቸው እያሉ ትግሬ ብሎ ትግሬን ብቻ ጨምሮ ማቆሙ አግባብ አልነበረም፡፡ ከጨመረ ቢያንስ እነኝህን መጨመር ነበረበትና፡፡
በየተራ ግዙ ብሎ እያፈራረቀ የሚሾምና የሚሽር አካል በሌለበት ሁኔታም ሰማንያ ብሔረሰቦች አሉና ተብሎ ሰማንያውም በየተራ መንገሥ ነበረባቸው ብሎ ማሰቡ መቸስ ቂልነት ካልሆነ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህች ስንት ነገር ባለፈባት ዓለም መሆናችንም ተረስቶ ተመሳሳይ የአሥተዳደር ሥርዓት ከነበራቸው ሀገራት እጅግ የተሻልን መሆናችን እየታወቀ ሀገራችን ያለችው ከገነት መሀል ይመስል እንዲያው ኮሽታም እንኳን መኖር አልነበረበትም ብሎ ማሰብ አሁንም እጅግ አለማስተዋልና መግቢያየ ላይ የገለጽኩላቹህን ሰው ከመሆናችን ጋር በተያያዘ ያለብንን ችግር አለማወቅ ነው፡፡
እነ ዋለልኝ ያላስተዋሉትና ድንቁርናቸው የነበረው ችግሩ የነበረባቸውን የምዕራባዊያን ሀገራትን ወቅታዊ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) እንቅስቃሴ ችግሩ ወዳልነበረባት ሀገር እንደ ፋሽን (ዘመንኛ) ነገር ቆጥረውት እንዳለ መቅዳታቸውና ያንንም ማራገባቸው ነው፡፡
ይህ እጅግ ብስለት የጎደለውና በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ የዋለልኝ አስተሳሰብ የተማሪዎችን ዐመፅ ቀስቅሶ ዐፄውን ለውድቀት ዳርጎ ገና ከጅምሩ የሀገሪቱን ውድና አንጋፋ መሪዎች ቅርጥፍ አድርጎ የበላውን ደርግን ለሚያህል ጭራቅና በተመሳሳይ ሰዓትም የበፊቱን የበረሀ አውሬ የዛሬውን አንባገነን ጭራቅ የወያኔን አገዛዝ ሌሎችንም የጥፋት ኃይሎች ፈጥሮብናል፡፡
ዋለልኝና ተከታዮቹ ሐሳባቸው ያልበሰለና እንጭጭ መሆኑን ሳይረዱ ይሄው አሁን ድረስ ላለንበት ውጥንቅጥ እየተወሳሰበ ለሚሔድ ችግር ዳርገውናል፡፡ ከላይ እንደገጽኩላቹህ በእኔ እምነት በእኔ እምነት ብቻም ሳይሆን መሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀው ባሕል፣ ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆኑ ቅርሶች (tangible and intangible Heritages) ፣ እሴቶች ሁሉ የአማራ ብቻ አይደሉም፡፡ እነ ዋለልኝ ሊረዱት ያልቻሉት ይሄንን ሀቅ ነው፡፡
ማንነታችን በራሱ ጊዜ የተሻለ አስተሳሰብ ባሕል እሴት ካለው ብሔረሰብ እየወሰደ የሀገሪቱ አድርጓል፡፡ ሥርዓቶቹ የከፋውንና ኋላ ቀር የሆነውን የማይጠቅመውን ልማድ እያስቀሩ በተሻለው አስተሳሰብ ባሕል እሴት ለመተካት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የአንድ መንግሥት ወይም አስተዳደር ኃላፊነትና ግዴታም ነው ለምሳሌ ያህል አንዱን ልጥቀስ ዕቁብ ወይም ቁቤ ዛሬ ላይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለመደና ያለ ባሕላችን ነው፡፡ የሁላችንም ከመሆኑ በፊት ግን ዕቁብ የጉራጌ ባሕል ነበር፡፡ ልማዱ ባሕሉ አስተሳሰቡ የሠለጠነ የበሰለ ጠቃሚም ስለሆነ ከጉራጌ ተወስዶ የኢትዮጵያ ሆነ፡፡ በዚሁ መልኩ ጠቃሚና የላቁ ባሕላዊ አስተሳሰቦችና ልማዶች ከየብሔረሰቡ እየተለቀሙ ተውጣጥተው ነው የኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀውን ባሕል አስተሳሰብና እሴቶችን ሊቀርጹ ሊገነቡ የቻሉት፡፡ አሁን ላይ ሲታዩ የአንድ ብሔረሰብ ሊመስሉ ይችላሉ ነገር ግን በፍጹም የአንድ ብሔረሰብ ባሕል ማንነት እሴት ብቻ አይደሉም፡፡ በዚህች ሀገር ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ በዚህች ሀገር እንደመኖራቸው ለዚህች ሀገር ለነጻነቷ መሥዋዕትነት ከመክፈል ጀምሮ ከማንነት እስከ ሥልጣኔዋ ድረስ አስተዋጽኦ ላያደርጉ የሚችሉበት ምንም ምክንያት አልነበረም፡፡
ከዚህ ውጭ ግን የሁሉም ብሔረሰቦች ሁሉም እሴቶች እኩል የእውቅና ዕድል መሰጠት ነበረበት ከሆነ ጥያቄያቸው ይሄ ጥያቄ የመብትና የፍትሕ ሳይሆን የአመክንዮ፣ የሥነሥርዓትና የፍላጎት ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መልስ ሊሰጥ የሚችል አካል የለም፡፡ ነገሮች እራሳቸውን የሚያስተናግዱበትን ተለምዷዊና ተፈጥሯዊ አሠራር አላቸው፡፡ ይህ ጉዳይ የሚዳኘው በዚህ አሠራር ነው፡፡ ይሄንን ጥያቄ እንኳን እኛ ከሀብታሞቹ ሀገራት አንዳቸውም እንኳን አልመለሱም፡፡ በሁሉም ሀገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ጎልተው የሚወጡ የተወሰኑ ብሔረሰቦች እሴቶች መሆናቸው ግድ ሆኖ ኖሯል፡፡
እስከማውቀው ድረስ ጎልተው የተዋወቁ እሴቶች ይኖሩ ይሆናል እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሌሎች ብሔረሰብ እሴቶች የኢትዮጵያ አይደለም ተብሎ አያውቅም፡፡ የቀረው የአቅም ጉዳይ ነው የተሻለና ጠቃሚ የሆነው ግን አስቀድሜ እንዳልኩት አናውቀውም እንጅ በራሱ ጊዜና ባለው የተሻለ አቅም እየተመረጠ የሐገሪቱ ሆኗል፡፡ በተረፈ እንዲህ ብለው ማሰባቸው ራሱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እንዲህ ብለን እንድናስብ የሚያደርገን አለመብሰላችን ነው እንጭጭነታችን ነው ጠልቀን አስፍተን ማሰብ አለመቻላችን ነው ድንቁርናችን ነው፡፡ ቋንቋ ባሕላችንን ብናይ የአንደኛው ከሌላኛው የተወራረሰ የተቀላቀለ የተዋዋሰ ነው፡፡ ይሄንን ተፈጥሯዊ ሁኔታ ነው ደናቁርቱ እየኮነኑ ያሉት፡፡
“ጭቆና አልነበረም! እያልከን ነው ወይ?” ካላቹህኝ አልወጣኝም! ነበረ፡፡ የነበረው ጭቆና ግን ፈጽሞ የብሔር ሳይሆን የመደብ ነበር፡፡ ይሄም ቢሆን ግን የጥፋት ኃይሎች ለርካሽ ጥቅማቸው ሲሉ ጭቆናው ነበር ተብሎ እጅግ ተለጥጦና ተጋንኖ ፈጠራም ታክሎበት የሚያወሩትን ያህል አይደለም አልነበረምም፡፡ ሥልጣኑ ይያዝ ይገኝ የነበረው አማራ በመሆን ከማንኛውም የአማራ ተወላጅ ተመርጦ ሳይሆን ከሰሎሞናዊው የዘር ኃረግ ጋር የተሳሰረው ቤተሰብ ተወላጅ በመሆን ብቻ የነበረ በመሆኑ፡፡ ጭቆናው የመደብ እንጅ የብሔር አልነበረም አይደለምም፡፡
በሀገራችን የነበረው ገዥና የሚወራውን ያህል ባይሆንም ግፍ ፈጸመ የሚባለው ማን እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ እያለ አማራን ሲጨቁን ሲረግጥ የኖረ አድርገው ያስባሉ፡፡ እውነታው ግን ይሄ አይደለም፡፡ ለአማራ ያለው የጥላቻ መንፈስ መሠረቱ ቅንነት ማጣት፣ ማየት ማሰብ ካለመቻል የሚመነጭ ድንቁርናና ጠባብነት ነው፡፡ በሀገራችን የመደብ እንጅ የብሔር ጭቆና እንዳልነበረ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዥዎች የተጨቆኑ የተረገጡ ብሔረሰቦች አሉ ከተባለ እጅግ በከፋ ሁኔታ የተጨቆነ የተረገጠ የተበዘበዘና የግፍ ገፈት ተጋቹ የነበረው የአማራ ሕዝብ እንደሆነ ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
እንደምታውቁት በዘውዳዊው ሥርዓት የሀገሪቱ ጦር ወይም ተዋጊዎች ደሞዝ አልነበራቸውም፡፡ ጦሩን የመመገብ የማሥተዳደር ግዴታና ኃላፊነቱ የተጫነው በገበሬው ላይ ነበር፡፡ ገበሬው ለሀገር ጠባቂ ጦር ልጆቹን ከመስጠቱ በተጨማሪ የሀገሪቱን ሠራዊት ተከፋፍሎ የመቀለብ ግዴታ ነበረበት፡፡
ዘውዳዊው ሥርዓት ከአማራው እንደመውጣቱና ከአማራው ሕዝብ መሀል እንደመኖሩ የአማራ ሕዝብ ከሌሎቹ ብሔረሰቦች በተለየ መልኩ ይሄንን ግዴታ የመሸከም ኃላፊነት ነበረበት፡፡ በመሆኑም እነኝህ የሠራዊቱ አባላት ሦስትም ሆነ አምስት በመሆን በአንድ ገበሬ ጎጆ ይመሩ ነበር፡፡ ይህ አሠራር “ተሠሪ” ይባላል በጎጃም “እሬና” ይባላል፡፡ እነኝህ ሀገር ጠባቂ ፋኖዎች በተሠሩበት ገበሬ ቤት ይበላሉ ይጠጣሉ አባወራና ልጆች የሚያገኙት ከነሱ የተረፈውን ነው፡፡ በአንዳንዶቹ ቤት የተሠሩትም ሲያሰኛቸው ያለ ባለቤቶቹ ፈቃድ ጠቦቱን አርደው ይበላሉ ገበሬው ምንም ማለት አይችልም፡፡
ተሠሪዎቹ እንዲህ እንዲህ እያሉ ያች ጎጆ ስትደኸይባቸው ስታጣ ስትነጣባቸው ደሞ ወደ ሌላዋ ይሄዳሉ ደሞ ያችንም በተራዋ ያደኸያሉ፡፡ ዝርዝሩን ቢናገሩት ትንሽ አስቸጋሪ ነው እንዲሁ ልለፈው ባጠቃላይ ግን ለዚህች ሀገር ህልውናና ነጻነት መጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ገበሬው ነው፡፡ አማራ ይሄንን ከባድ መራር ዋጋ ለገዥዎቹ ሳይሆን ለሀገሩ ነጻነትና ህልውና ሲል የሚከፍለው ዋጋ እንደሆነ ተቀብሎ፣ የውዴታ ግጌታው አድርጎ ለሽዎች ዓመታት ሲከፍል የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የአማራ ገበሬ ጥሪት መቋጠር ለልጁ ማውረስ የሚችለው ነገር የሌለውና ኑሮው ከእጅ ለወደ አፍ እንኳን የሚበቃ ያጣ ሊሆን የቻለውና ዛሬም ድረስ ሥር በሰደደ ድህነት ታስሮ የቀረው፡፡
ዛሬ በወያኔ ደናቁርት አንደበት “ለእግሩ ጫማ የማያውቅ” ተብሎ እስከመዘለፍ ላበቃው ድህነት የተዳረገው ለሀገሩ ሲል ሁለንተናውን ሲከፍል በመኖሩ ነው፡፡ ካላቹህ የአማራ ገበሬ ጫማ ብቻ አይደለም እንደምንም አንዲት ጨርቅ ከገዛ እሷኑ እየደራረተ ከገላው ላይ ተበጣጥቃ እስክታልቅ ድረስ ሌላ መቀየሪያ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ገጠሮችን እየተዘዋወራቹህ ስትጎበኙ አንድ የምትታዘቡት ነገር አለ የደቡቦችና የኦሮሞዎች የገበሬዎች ቤቶች አቋም ጠንከር ደርጀት ያሉ ናቸው ወደ አማራው ዞር ስትሉ ደግሞ የገበሬው ጎጆ ደሳሳ ሆኖ ታገኙታላቹህ፡፡ በሌሎች ነገሮች ላይ ያለው የይዘትና የጥራት ልዩነትም እንደዚሁ ነው፡፡ አማራ የገዥዎች ጭሰኛ ሆኖ ነው የኖረው ኑሮውን ቀረብ ብለው ላዩት አንጀት ይበላል፡፡
በታሪክ አጋጣሚዎች ያጣቸውን ነገር ግን የራሱ መሬቶች መሆናቸውን እያወቀም እንኳን ሁኔታው ወደ ነበረበት ቦታው ሲመለስ አስለቅቄ መሬቴን መልሸ ልያዝ ሳይል ለም መሬቶቹን አስረክቦ እሱ ለእርሻም ለምንም በማይመች መሬት ላይ የሚኖር ደግና ቅን ሕዝብ ነው፡፡
ይሄንን መሥዋዕትነት ለማንና ለምን ሲከፍል እንደኖረ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ብቻ ነው ምንም እንዳልሆነ በችጋር እየተጠበሰ ምንም እንዳልጎደለበት ሆኖ የኖረው፡፡ ከዚህች ሀገር የሚበልጥበት ምንም ነገር የለምና ሁለንተናውን ለእናት ሀገሩ ከፍሎታል አውሎታል ሠውቶታል፡፡
የሚያሳዝነው በጠላት ሸፍጥና ሴራ እጁ አመድ አፋሽ መሆኑ ውለታው ሁሉ ገደል ገብቶ ያለስሙ ስም ተሰጥቶት መጠላቱ ነው፡፡ ጭንቅላት ቢኖረን ወደ ኋላም ወደ ፊትም ደወ ግራም ወደ ቀኝም መመልከት ብንችል አርቀን አስፍተን ጠልቀን ማሰብ ብንችል፣ ኢትዮጵያዊነቱ ቢሰማን የሀገራችንንና የሕዝቧንም ህልውና የምንፈልግ የምንመኝ የምንወድ ብንሆን በምንም ተአምር ለአማራ ጥላቻ ሊያድርብን አይችልም፡፡ ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ህልውናና ነጻነት አማራ ለከፈለው ገደብ የለሽ መራራ ዋጋ እናመስግነው ብንል ለምስጋናችን ተስተካካይ ቃል ፈጽሞ ልናገኝለት አለመቻላችንን በሚገባ በተረዳን ነበር፡፡ አማራን ልንጸየፍ ልንጠላ አይደለም ወደነውም ለፍቅራችን የልባችን ባልደረሰ፡፡ ውግዘትና ጥላቻውን ትተን ክብር በሰጠነው በኮራንበትም ነበር፡፡ ለዚህ ነው ለአማራ ያለው የጥላቻ መንፈስ መሠረቱ ድንቁርና ጠባብነት የሀገር ጠላትነትም ነው ያልኩት፡፡
እኔ ግን የምፈራው የሌለ ያልነበረ ነገር እያወራን አማራን ያለስሙ ስም እየሰጠን እያከፋፋን ፊት እየነሳን እያሸማቀቅን የሌለ አውሬ ፈጥረን እያወራን በገዛ እጃችን አውሬውን ፈጥረነው ቁጭ እንዳንል ነው፡፡ አማራን በየሔደበት በክፉ ዓይንና አቀባበል እየተቀበልን በጎሪጥና በጥላቻ ዐይን ዕያየን ሳይወድ በግድ ጥላቻ እንዲያድርበት እያደረግን ከዚህም በኋላ መልካም ምላሽ የምንጠብቅ ካለን እጅግ ተሳስተናልና እንታረም ማለትን እወዳለሁ፡፡ እንደዛ ተሰባብሬ ደቅቄ መራር መሥዋዕትነት ከፍየ ባቆየኋት ሀገር ባልዋልኩበት ከዋልኩ፣ ባልሠራሁት ከታማሁ፣ ስም ከወጣልኝ አይቀር ብሎ የተነሣ እንደሆነ ኋላ ማጣፊያው ይቸግራልና መታረሙ ሳይሻል አይቀርም፡፡
አንድ የውጭ ጋዜጠኛ ነው አሉ የጃንሆይን ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅን “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ይሆናል” ብሎ ቢጠይቃት “ከአምስት መቶ አንበልጥም” ብላ ቁጭ አለች፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ልዕልቲቱ በዘር አማራ እንደሆነች ብታስብም ለእሷ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት የንጉሣዊያን ቤተሰብ ብቻ እንጅ አማራውም እንኳን አይደለም፡፡ የነበረው አስተሳሰብ ሐቅና እውነታ ይሄ ነው፡፡ የንጉሣዊያን ቤተሰብ ያልሆነው የአማራ ሕዝብ በገዥዎቹ ይናቅ ይገፋ ይዋረድ ይጣጣል ነበር እንጅ አማራ በመሆኑ አልተከበረም፡፡ ወያኔና የጥፋት ኃይሎች እንደሆኑ ጥላቻን ለመፍጠር የሕዝብ አንድነትና ዝምድና እንዲፈርስ ለማድረግ ነው ሆን ብለው እውነትን እያዛቡ የማይመስል ፈጠራ እያመጡ ገዥዎችንና አማራን አንድ አድርገው በማየት የኢትዮጵያን ሕዝብ የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲያዝ ለማድረግ እየደከሙ ያሉት፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ አስቀድሜ እንዳልኳቹህ የጥፋት ኃይሎች የገዥዎቻችንን ግፍና በደል አጋነውና ፈጠራ ጨምረው እንደሚያወሩት ያህልም እንኳን ቢሆን በሀገራችን የነበረው አገዛዝ ከጥንት ጀምሮ ሀገሪቱ ሃይማኖተኛ በመሆኗ ምክንያት ተመሳሳይ ዘውዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ከነበራቸው ሀገራት እጅግ የተሻለው ነበር፡፡
አውሮፓና ሌሎች ሀገራት ላይ እንደነበረው የሰው ልጆችን ለመዝናኛነት ከአውሬ ጋር እያታገሉና እያስበሉ መዝናናት ነገሥታቶቻቸው ሲሞቱ ጠባቂ እንዲኗቸው ተብሎ የሰው ልጆችን ከነ ሕይወታቸው አብሮ መቅበር የመሳሰለው ግፍ በሀገራችን አልተፈጸመም፡፡ የሩቁን ብንተወው በናዚ ዘመን በሰው ልጆች የተፈጸመውን ግፍ ማሰብ ይቻላል፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግን የዚህ ወይም የዚያ ዘር በመሆኑ ብቻ ዘግናኝ ግፍ የደረሰበት ዘር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡
የጥፋት ኃይሎች ፋሽስት ጣሊያን “አማሮች ለአገዛዜ እንቅፋቶች ናቸው!” ብሎ በማሰቡ አማራን ጠላት አድርጎ በማቅረብ በሌሎቹ ብሔረሰቦች ለማስጠቃት በማሰብ በእውነተኛ ታሪካዊ ኩነት ላይ ተመሥርቶ ፈጠራ ጨምሮበት በማውራት በወቅቱ በአማራ ላይ ሰፊ ጥቃት እንዲፈጸም ያደረገበትን የሔጦሳንና የጨለንቆን ፈጠራ ዛሬም ወያኔ እና ኦነግ የጥፋት ኃይሎች በሽግግሩ ወቅት አሁንም እየደጸሙት ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመሸፋፈንና ምክንያታዊ ለማስመሰል ጣሊያን ለጥፋት ዓላማው ፈጥሮ ያወራውንና ምንም ዓይነት መረጃ የሌለውን፤ የጦሩ አዝማች ኦሮሞ (ራስ ጎበና ዳጬ) በሆኑበት ሁኔታና እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ጥናትና ምርምር ከዚያ ሠራዊት ከ95 በመቶው በላይ ኦሮሞ በሆነበት ሁኔታ ጣሊያን ፈጥሮ ያወራው ሐሰተኛ ወሬ ይሆናል ይፈጸማል ብሎ ለማሰብም ፈጽሞ በማይቻልበት ሁኔታ ሐሰት መሆኑን እያወቁ የጣሊያንን የጥፋት ፈጣራ ወሬ አንሥተው ለተመሳሳይ የጥፋት ዓላማ ተጠቅመዋል፡፡ ወሬው ግን እንዳልኳቹህ ነጭ ውሸት ነው፡፡
ጦርነቱ ነበረ ወይ ከተባለ አዎ ነበረ፡፡ በዘመነ መሳፍንትና በዋዜማው ማዕከላዊ መንግሥት ተዳክሞ ሀገሪቱ ተፈረካክሳ እነኝህ ዐፄ ምኒሊክ ጦር ያዘመቱባቸው የሀገራችን አካባቢዎች ተረስተው ርቀው ስለነበረና ዐፄ ቴዎድሮስ የጀመሩትን ሀገርን እንደገና የማዋሐድ አንድ የማድረግ ተልእኮ ዐፄ ምኒልክም የማስፈጸም ግዴታ ስለነበረባቸው ያንን አድርገዋል፡፡ የተባለው ግፍ ግን የፋሽስት ፈጣራ ነው፡፡ እንዳልኩት ከጦሩ አባላት ማንነት አንጻር ይሄንን ለመፈጸም የሚያበቃ ክፍተትና አጋጣሚ ፈጽሞ አልነበረምና፡፡
እንኳንና እንዲህ ዓይነት ግፍ ሊፈጸም ዐፄ ምኒሊክ የዚያ አካባቢ ሰው እንቢ ብሎ ጠንክሮ በመዋጋቱ ምክንያት ብዙ ዓማፅያን ማለቃቸው አሳዝኗቸው መኳንንቱ በጦርነቱ ወላጆቻቸው የሞቱባቸውን ልጆች አምጥቶ እንደልጁ አድርጎ እንዲያሳድግ ማዘዛቸውና ይሄም መፈጸሙ ይታወቃል፡፡ ባልቻ አባነብሶና ፊታውራሪ ኃ/ጊዮርጊስ ዲነግዴ ያኔ ወላጆቻቸው በጦርነቱ ከሞቱባቸውና መኳንንቱ አምጥተው እንደልጅ አድርገው ካሳደጓቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት የተሞላበት ሥራ ነው የተሠራው፡፡ በዚህ ሀገርን መልሶ አንድ በማድረጉ ትንቅንቅ ግፍ ተፈጸመ ከተባለ ግፍ የተፈጸመው በመጀመሪያውና የተልእኮው ከባዱ ወቅት በነበረው ዐፄ ቴዎድሮስና መሳፍንቱ ባደረጉት ትንቅንቅ መሳፍንቱ ሕዝቡን እያስገደዱ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ያደርጉ ስለነበር ሕዝቡን ለጥቃት በማጋለጣቸው ሕዝቡ እየተሰበሰበና በቤት ውስት ታጭቆ እየተዘጋበት እንዲቃጠል የተደረገው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተፈጸመው በኦሮሞው ወይም በትግሬው ላይ ሳይሆን በአማራው ያውም በጎንደሬው ላይ ነው፡፡
የጥፋት ኃይሎች ይሄንን ሁሉ አጥተውት አይደለም እንደ የጥፋት ኃይልነታቸው ፋሽስታዊ የጥፋት ሥራ መሥራት ስላለባቸው ከጌታቸው ከፋሽስት ጣሊያንን ፈጠራ ተቀብለው ሐውልት በመሥራት ሕዝብ ለማፋጀትና ያ አካባቢ የኢትዮጵያ እንዳልነበረና ዐፄ ምኒልክ የቀላቀሉት አስመስሎ ለመገንጠል ነው ፈጠራውን የሚያወሩት፡፡ ደናቁርቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ፈጠራ ነው አንቀበልም ካሉ ማየት የሚችል ዓይን መዳሰስ የሚችል እጅ ካላቸው ከከፋ እስከ ሐረር በመላው አካባቢው ከክርስቶስ ልደት በፊት ስድስት መቶ ዓመታት ካስቆጠሩት እስከ ሰባት መቶ ዓመታት ዕድሜ እስካላቸው በዓይን የሚታዩ በእጅ የሚዳሰሱ ገዳማትና ቅርሳቅርሶችን በማየት የሚሉት አካባቢ የኢትዮጵያ አካል መሆኑን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ዳሩ እውነቱ ጠፍቷቸው አይደለም ታሪክን የሚክዱት የጥፋት ዓላማቸውን ለማስፈጸም ታሪክ እውነትን እየመሰከረ አላሠራ ስላላቸው እንጅ፡፡
ዐፄ ምኒልክ (ለነገሩ ያኔ ገና ዐፄ አልሆኑም) በዚህ ተልእኮ ጦራቸውን ወደተባሉት ሥፍራዎች አዝምተው የራቀውን የተረሳውን ባይመልሱ ኖሮ የእነዚህ የሀገራችን ክፍሎች ነዋሪዎች በባለአባቶቻቸውና በጎሳ መሪዎቻቸው ለባርበት ተሸጠው ሊያልቁ ከባድ አደጋ ላይ ነበሩ፡፡ ይህ አደጋ የተገታው ዐፄ ምኒልክ ዐፄ ቴዎድሮስ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ በጸረ የባሪያ ንግድ ላይ የጸና አቋም የያዙ ስለነበሩና እንዲቆም በማድረጋቸው ነው፡፡ እናም እውነቱና የጥፋት ኃይሎቹ የሚያወሩት እጅግ የተራራቀና የማይገናኝ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገንና ሀገራችን ከእንደዚህ ዓይነቱ የዘር ልዩነትን መሠረት ካደረገ ጥፋት የተጠበቀች ነው የነበረችው፡፡ በተለያዩ የጥንት ፈላስፎች መጻሕፍትና የሃይማኖት መጻሕፍት ተጽፎ ያለውም ሀገራችን የፍትሕ ሀገር መሆኗን ነው፡፡
ዛሬ ላይ ግን የሚገርመው እነዚያ ከእኛ እጅግ የከፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የነበረባቸው የአሥተዳደር ሥርዓት የነበራቸው የአውሮፓ ሀገራት ኮሽታ እንኳን የነበረባቸው ሳይመስሉ ተግባብተውና ተስማምተው በመሥራት ለማደግ ለመበልጸግ ሲችሉ ያሳለፉት ዘግናኝና የእርስ በእርስ እልቂት ተስማምተው ተባብረው ከመሥራት ቅንጣት ታክል እንቅፋት እንዲፈጥርባቸው ሳይፈቅዱለት ሲጓዙ እኛ ግን ጭራሽም ያልነበረ የሌለ እየፈጠርን በመናቆር ቁልቁል መሔዳችን ነው፡፡
እንደ ወያኔ ዓይነት ያለ የሌለ እያወራ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማፋጀት ሴራ ላይ የተጠመደ ደንቆሮ ደደብ የማይገባው የማይረዳ አህያ አመራር ሳይሆን ልባም አርቆ አሳቢ በመግባባት በመስማማት በአንድነት በፍቅር መሠረትነት ሕዝብን የሚመራ ኃላፊነት የሚሰማው አመራር ስላላቸውና በዚህ ላይ ተግተው ስለሠሩ ነው፡፡ እኛ ግን እውነቱንም ውሸቱንም እየተጋትን ያን ፈጸሙ የሚባሉት ሰዎች ዛሬ ያሉና እነሱን መፋረድ ይቻል ይመስል እዚህ ግባ የማይባል በደልን እየጠቀስን ያም ቢሆን ገፈቱን የተጋተው አማራ ሆኖ እያለ ልክ በእኛ ብቻ የተፈጸመ እያስመሰልን የጥንት ነገርን እየጎተትን መናቆር መፋጀትን ሥራየ ብለን ይዘነው በየት በኩል አልፈን መቸስ ሠርተን ይለፍልን?
በዚህ አጋጣሚ ጥፋትን መተላለቅን መለያየትን ለምትሰብኩ የጥፋት ልጆች የምለው መልእክት ቢኖረኝ እስኪ ልብ በሉና ቆም በሉና እየሠራቹህት ያላቹህትን ነገር አስቡት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከዚህ እንደማናተርፍ ታውቃላቹህ ወይም ማወቅ ይኖርባቹሀል፡፡ የምታውቁ ከሆነም ታዲያ ምን ነው? ምን ነው? ምን አለ ይሄንን ምስኪን ሕዝብ ያሳለፈው መከራ ችጋር ቢበቃውና ፍቅርን አንድነትን ሰላምን ሰብካቹህለት ተባብሮ ሠርቶ አንገቱን ቀና ቢያደርግ? ችጋሩን ቢያራግፍ ምን አለበት? ይሄንን ብታደርጉ ምን ትሆናላቹህ? ተጠቃሚ ትሆናላቹህ እንጅ ምናቹህ ይጎዳል? እንግዲህ ምሁርነት ማለት ሕዝብን መውደድ ማለት አርቆ አሳቢነት ማለት ዐዋቂነት ማለት ይሄ ነው ሌላ ምን አለ ብላቹህ ታስባላቹህ?
የጥፋት ኃይሎችን ልጠይቅ የምሻው ጉዳዮች ቢኖሩ፡- መሮጥ የቻለ የቻለውን ያህል መሮጥ እንዲችል የውድድር መድረኩ ለሁሉም ክፍት መሆንና ሁሉም ችሎታውና አቅሙ የፈቀደለትን ያህል መሮጥ እንዲችል መደረግ ሲኖርበት “እኩል ዕድልና መድረክ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች” የሚለውን ፍትሐዊ የሚመስል ግን ያልሆነን ፅንሰ ሐሳብን እጅግ በተሳሳተና በደነቆረ አረዳድ በመተርጎም ያለቦታው “አንተ ቀድመህ ከሮጥክ እኛን ጥለኸን ስለምትሔድ፣ በልጠህ ልቀህ ስለምትታይ ቀድመኸን መሮጥ ብትችልም አንፈቅድም ከእኛ ጋራ ነው መሮጥ ያለብህ፤ እኛ ካንተ ጋር እኩል መሮጥ አንችልምና አብረኸን አዝግም! ወይም እስከምንደርስብህ ድረስ ተኛ ካልሆነ ደግሞ ጥፋ!” የሚል አስተሳሰብስ ከ21ኛው መቶ ክ/ዘ ሰዎች ያውም ተምረዋል ከሚባሉት የሚጠበቅ ነው ወይ? አሠራሩስ ድንቁርና የተሞላበት ኢፍትሐዊ አሠራር አይደለም ወይ? ይሄስ ዓይነት አሠራር በየት ሀገር ነው ሥራ ላይ ውሎ ተግባራዊ ሆኖ የሚያውቀው ፍትሐዊስ የሚሆነው?
ሌላው ብሔረሰብ የሚጠና የሥነ ጽሑፍ ሀብት ወይም ሰፊ ታሪክ ከሌለው የበለጸገ የሥነ ጽሑፍ ሀብትና ሰፊ ታሪክ ያለው (የአማራ) መጠናት የለበትም ወይ? ይሄ ጠልፎ መጣል ማሰናከል አይደለም ወይ? “የኔ ዓይን ጠፍቷል ያንተም ይጥፋ!” ማለት አይደለም ወይ? ይሄ ጎትቶ መጣል አይደለም ወይ? ከዚህስ የከፋ ደንቆሮነት አለ ወይ? የሄ እንዴት ሆኖ ነው ፍትሐዊ አሠራር የሚሆነው?
እንዲህ ዓይነት “ተበለጥን ተቀደምን” በማለት ዓይናቸው ደም የሚለብስባቸው የሚቀላባቸው ሰዎች ካሉ ችግሩ በዚህ ሰይጣናዊ ቅናት የተለከፉቱ የእነሱ እንጅ ጠንክረው በመሥራታቸው መቅደም መሠልጠን የቻሉት ወገኖች አይደለምና ወደ ውጪ መመልከታቸውን ትተው ወደ ውስጣቸው ይመልከቱና ለዚህ የኅሊና ደዌያቸው መድኃኒት ይፈልጉ “ያለመበለጥ ያለመቀደም” መፍትሔው ጠልፎ በመጣል የቀደመውን ማስቀረት ማሰናከል ሳይሆን በርትቶ በመሥራት ከተቻለ ለመቅደም ወይም እኩል ለመሮጥ ካልተቻለ ደግሞ አቅምን አውቆ መበለጥን መቀደምን አምኖ በጸጋ መቀበል እንደሆነ መረዳት ነው፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው