የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተምን ተከትሎ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት ሃገሮች “ከምር“ . . . የጦርነቱ ቆስቋሽና ድል አድርገናል ባይ ሃገራት ደግሞ “ለፖለቲካ ትርፍ “ ሲሉ፣ ዓመቱን እየቆጠሩ ያከብሩታል። እ.ኤ.አ ባለፈው ሃሙስ ጃንዋሪ 5/2016 ላይ የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ማብቂያ 70ኛውን ዓመት ያከበረችው ቻይና በታላቁ ከተማዋ በቤጂንግ ከ20 በላይ የሃገራት መሪዎች በተገኙበት እለቱን በታላቅ ድምቀትና “እኛ እንዲህ ነን“ በሚል ስሜት ሲሆን በእለቱም ከዚህ ቀደም ለህዝብ እይታ ያልበቁ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን፣ ታንኮች፣ የተለያዩ የአየር ላይ ተወንጫፊዎችና Dongfend-21D የተሰኘ አዲስ ጸረ-መርከብ ባላስቲክ ሚሳኤሎችን ለትእይንተ ህዝብ አቅርባለች።
ከዚህ በዓል አከባበር ጋር ተያይዞም ሁለት ወሳኝ የሚባሉና የአካባቢውንም ሆነ የዓለሙን ፖለቲካ ተንታኞችን “ከልብ ከሆነ እሰይ“ ያሰኙ ክስተቶች በመዲናዋ በቤጂንግ ተከናውነዋል፣ ለትእይንቱ በተሰበሰበው በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ፊት መድረኩን በሞገስ የሞሉት Mr. Xi Jinping . . . በንግግራቸው መሃል የሃገሪቱን ወታደሮች ቁጥር በ300,000 እንደሚቀንሱ ሲገልጹ ጭብጨባውና ፉጨቱ የቤጂንጉን አደባባይ አናውጦት ነበር።
ሃገሪቱ ካላት 2.3 ሚሊዮን የሚጠጋ ወታደር ከ 3መቶ ሺ በላይ የሚጠጋውን ሰራዊት እንቀንሳለን ማለታቸውን ብዙዎች በጥርጣሬ ነበር ያዩት፣ ይልቁንም የዘመናት ባላንጣዋ የሆነችው አሜሪካ፣ ሃገሪቱ የወታደሩን ቁጥር መቀነሷ፣ የጦር ሃይሏን ይበልጥ በቴክኖሎጂ ስላደራጀች ወይም ሜካናይዝድ በማድረጓ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ። ፕሬዚዳንቱ አክለውም “ኢፍትሃዊነት፣ ማግለል፣ ጥላቻና ጦርነት ለሃገራት ቀውስና ህመም ምክንያት ናቸው። በመከባበር ላይ የተመሰረተ አብሮነትን በእኩል ደረጃ መገንባት፣ ሰላምና እድገት እንዲሁም የአብሮ መበልጸግ ፍልስፍናዎችን ማእከል ያደረጉ አስተሳሰቦች ብቻ ለዓለማችን አዋጭ መንገዶች ናቸው“ በማለት ነበር ታሪካዊ የተባለውን ንግግር ያደረጉት።
የኢኮ-ፖለቲካ ባላንጣነት
ከየትኛውም የዓለም ሃገራት ቀድማ ሁሉ-ዓቀፍ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ከቻይና ጋር የጀመረችው አሜሪካ፣ ምንም እንኳ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሰንሰለቱ /ግንኙነቱ/ በብዙ ሺ ማይሎች ርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ጉሽሽማቸው በካርቦን ልቀት ሳቢያ አየሩን አደፈረስሽብኝ ነገር ፍለጋ /ክስ/ በላይ ዘልቆ፣ ወደ ሳይበር /መረጃ መረብ/ ጠለፋና ጥብቅ የሳተላይት ስለላዎች ክስና አቤቱታዎች ተሸጋግሯል። የደቡባዊ ቻይና ሰው ሰራሽ ደሴት ጉዳይም የሁለቱ ሃገራት የሃያልነት ትፍፍግ ሰበቃውን ጨምሮ በሚገኝበት ወቅት የተደረሰበት በመሆኑ የሁለቱን /የምእራብና ሩቅ-ምስራቅ/ ባላንጣ ሃገራትን መተማመን በእጅጉ የሸረሸረው ሆኖአል።
Mr. Xi ባለፈው Sep./2015 ከቤጂንግ ወደ ሲያትል ባቀኑበት ወቅት ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ1979 ዳግም ከታደሰው ግንኙነት ጋር ተያይዞ በጎሪጥ መተያየታቸውን ይቀንሳል ብለው ያሰቡ ብዙዎች ነበሩ፣ ነገር ግን እንደአሜሪካውያኑ አባባል ቻይናውያን . . . “ንግዳቸውን ብቻ ሳይሆን አእምሮአቸውንም ለመልካም ተግባቦት አልከፈቱም “ ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ካረፉበት ከተማ እግራቸውን ሳያነሱ ተችተዋቸዋል። ለዚህም ምክንያቱ በዚሁ ሰሞን በመረጃ መረብ ተለቆ በታየው የሳተላይት ምስል ቻይና በደቡባዊ ግዛቷ በኩል በሚገኘው ምእራባዊ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ ታላቅ ሰው ሰራሽ ደሴት መገንባቷና በደሴቲቱም ላይ እንቅስቃሴዎች መጀመሯ የሁለቱን ሃገራት ፖለቲካዊ ቁርቁስ ግለት መጨመሩ ነው።
የገዢ መሬት ይዞታ እሽቅድድም
ዓለማችን በተለያዩ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች በመጠርነፍ ለግዛት ከማመቻቸት በዘለል በኢኮኖሚ ላቅ ያሉ ሃገራት አካባቢያዊ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን በሚያደርጉት መፈታተሽ ቀድሞ ከነበራት ምእራብና ምስራቅ ከሚል ሃሳባዊ ክፋይ ወጥታ ብዙዎች የየክፍለ ሃገራቱ ደንብ አስከባሪ ለመሆን በሚያደርጉት ፍትጊያ ከፊል የምስራቁ አውሮፓ አካል ሲቀር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ስልታዊም ሆነ ግልጽ ግንኙነት በማድረግ የምድራችንን ጥቂት የማይባለውን ክፍል የያዙ ሲሆን ሩሲያ ደግሞ ጥቂት የምስራቅ አውሮፓ ሃገራትንና የተወሰኑ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን በመያዝ የያዘችውን ገዢ ክፍለ ዓለም ላለመልቀቅና የቀድሞ ይዞታዎቿን ለማስመለስ፣ ከክሬምሊን ቤተ መንግስት ቀጥታ ትእዛዝ እያስተላለፈች ድርሻዋን በማስከበር ላይ ስትገኝ፣ የመካከለኛው ምስራቅን ገዢ መሬት ይዞታን ለመጠቅለል ደግሞ የኢራንና የሳኡዲ አረቢያ የቀጥታም ይሁን የተዘዋዋሪ ፍጭቶች ገና ያልለየላቸው የፖለቲካ ሽሚያዎች ናቸው።
ሩቅ ምስራቁን የቻይናና የህንድ የልሆሳስ እንቅስቃሴዎች፣ ሌሎች ታናናሽ የክፍለ አህጉሩን ሃገራት አንገት አስደፍቶና ፖለቲካው ላይ የለንበትም፣ ስራችንን እንስራበት፣ አትንኩን አይነት ዝምታ ላይ እንዲጸኑ አስገድዷቸዋል። በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ ብቃቷን የምትፈትሸው ሰሜን ኮሪያም የራሷን ግዛታዊ ማንነት ከመጠበቅና ከደቡብ ጎረቤቷ ጋር ከመጎነታተል ባለፈ /ለጊዜው/ በክፍለ አህጉሩ ላይ ለመፍጠር የምትፈልገው ተጽእኖ እምብዛም ነው። በነዚህ ሁሉ ክፍልፋይ የፖለቲካ አውዶች ተወጣጥረው ካሉት የዓለማችን አህጉራት በተለየ ሃገራቱ ባላቸው የውስጥ ፖለቲካ አለመረጋጋትና በዚህም ሳቢያ ያላቸውን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው በየራሳቸው ችግር የተወጠሩት የአህጉረ አፍሪካ ሃገራት ከራሳቸው ውስጣዊ ቅራኔና ለቅራኔው አፈታትም ከሚሰጡት አምባገነናዊ ምላሽ ወጥተው /አልፈው/ የገዛ ህዝባቸው ላይ የሚያከብዱትን ቀንበር ከማጽነን ባሻገር፣ ሃገራቱን በዚህ ውድድር ውስጥ ባለማሳተፋቸው የሌሎች ክፍለ አህጉራት የኢኮኖሚና የጦር የበላይነት ቁርቁስ በዚህችው ድሃ አህጉር ላይ መጥቶ ነበልባሉን መትፋቱን እናያለን። በዚህ የፖለቲካ ቁርቁስ ዳር ሆና በወላፈኑ የምትለበለበው አፍሪካ ላይም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቻይና የኢኮኖሚ የበላይነት መጥቶ ቆብ ከመድፋቱም በላይ አሁን አሁን የምንሰማቸው ዜናዎች ደግሞ ከነጻ የንግድ ቀጣና ግንባታዎች ወደ ወታደራዊ በዓት /ነጻ ቀጣና/ ወይም ምሽግ ቁፈራዎች በማሳለጥ ወታደራዊ ቤዝ /መሰረት/ ለመጣል ደፋ ቀና እያለች እንዳለ በስፋት እየዘገቡ ነው።
ከቤጂንግ እስከ ታጁራ ባህረ ሰላጤ፣ ከዋሽንግተን እስከ አርባ ምንጭ
ከሰሞኑ ቻይና ከኢኮኖሚያዊ ኪራይ ሰብሳቢነት ወጥታ አፍሪካን እንዲሁም መካከለኛውን ምስራቅ አስተቃቅፎ ጥቅሜን ያስጠብቅልኛል ባለችው፣ በህዝብ ቁጥሯ ከመቶ ሺዎች ያልዘለለች ትንሿ የአፍሪካ ቀንድ ሃገር ላይ ትኩረቷን ማድረጓ በቀጣናው የፖለቲካ ንፍቅ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል ሰፊ ጥያቄን ያስነሳል። በኤርትራ፣ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ተከባ ቀይ ባህርን ዳርቻዋ አድርጋ በቀንዱ ላይ የነጥብ ያህል የተቀመጠችው ትንሿ ሃገር ጂቡቲ፣ በገጠራማ አካባቢዎቿ መካከል ከሚገኙ ኮረብታዎቿ አንዱን ለቻይና ወታደራዊ መንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ለቀጣይ 10 ዓመታት ፈርማ አስረክባለች። ቻይናና አሜሪካ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ በመካከላቸው የተነጠፈው የፓሲፊክ ወለል አራርቆ ያስቀመጣቸው የሁለት አህጉር ሃገራት ሲሆኑ በመካከላቸው ያለው እርቀትም ከ11,600 ኪሜ በላይ ነው፣ ሁለቱ ሃገራት አፍሪካ ላይ የጋራም ይሁን የተናጠል ጥቅም አላቸው፣ ሁለቱም በአህጉሩ ቁልፍ ገዢ መሬት እንዲኖራቸው ይሻሉ፣ በዚህም የተነሳ በተለይ በምስራቁ የአህጉሪቱ ክፍል ወሳኝ የሆነ ይዞታ ማግኘት የቅርብም የሩቅም ዓላማቸው ነው።
ከዛሬ 5 ዓመት በፊት በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ መለስ ዘመነ መንግስት ያለምንም ግርግር አሜሪካውያኑ ተረክበው በኢትዮጵያ ደቡባዊ ግዛት አርባ ምንጭ ከተማ ላይ የገነቡት የሰው አልባ ድሮን /አውሮፕላን/ መንደርደሪያና፣ ከሰሞኑ ቻይና ከጂቡቲ የተረከበችው ወታደራዊ ጣቢያ በርቀት ደረጃ ሲታይ ሃገራቱ በመልክዓ ምድራዊ ተፈጥሮ ካላቸው ርቀት በአስር እጥፍ ያነሰ ነው። የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ሰበር ዜና ሆኖ በድንገት የተሰማው የኢትዮጵያ አሜሪካ የወታደራዊ እዝ ጣቢያ /Base/ የልሆሳስ ስምምነት ባለፈው የፈረንጆች አዲስ ዓመት መባቻ ላይ እንዲሁ በልሆሳስ የተጠናቀቀ ሆኖ፣ ከ5 ዓመታት በላይ በደቡባዊ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ ከተማ የነበረው የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ቅኝትና መንደርደሪያ ጣቢያ አገልግሎቱን አብቅቶ ተዘግቶአል።
ምክንያቱን በሁለቱም በኩል ያሉ ባለስልጣናት ሲገልጹ “የአልሸባብ መዳከም“ በወታደራዊ ቤዙ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ እንድናነሳ አድርጎናል፣ እናም አልሸባብ ተዳክሞ ሶማሊያ በራሷ መንግስት እንዲሁም በአሚሶም ከፊል ድጋፍ መተዳደር ስለጀመረች ብለው የነበረ ቢሆንም ይህ ዜና 15 ቀናት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ በሌላ ሰበር ዜና ተሰብሯል።
ባለፈው ዓርብ ጥር 15/2015 የአልሸባብ ወታደሮች በደቡባዊ ምእራብ ሶማሊያ፣ ኬንያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ጣቢያ እንዳጠቁና በመቶዎች የሚቆጠሩ የህብረቱን ወታደሮች በአብዛኛው በሶማሊያ ሰላም ማስከበር የተሰማሩ የኬንያ ወታደሮችን ሲገድሉ፣ የዓለም መገናኛ ብዙሃን ዘጋቢዎችን ትኩረት የሳበ አስደንጋጭ ክስተት ነበረ። ተዳክሞአል የተባለው አልሸባብ እንዲህ ባየለበትና የፖለቲካና ኢኮኖሚ ባላንጣዋ ቻይና በቅርብ እርቀት፣ በታሪኳ የመጀመሪያ /በአፍሪካ/ የሆነውን ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ አፍንጫዋ ስር መጥታ እንደምትተክል መረጃው እያላት፣ አሜሪካ ያላትን ጣቢያ ነቅላ አብቅቻለሁ ማለቷ ምን እንድምታ ይኖረዋል?
የዚህ የፖለቲካ ምህዋር እና ጂኦ-ፖለቲካ አቅጣጫ ቅየራ፣ ወታደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ እዙን በአግባቡ ለመቆጣጠር መሆኑ ግልጽ ሲሆን አሁን በፍጥነት አገልግሎቱን ያቆመው የአርባ ምንጩ የአሜሪካ ሰው አልባ ወታደራዊ አውሮፕላን መንደርደሪያ ጣቢያ ማረፊያውን የት ያደርጋል?
የአስመራው US ኤምባሲ እና የታጁራው የቻይና ወታደራዊ ቤዝ
ሁከት ብጥብጥና የተለያዩ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችን የሚያስተናግደው ምስራቁን የአፍሪካ ቀንድ ከአሸባሪዎች ነጻ አድርጎ ለማቆየት ብሎም የመካከለኛው ምስራቅን የፖለቲካ ሙቀት ለመቆጣጠር፣ ከትንሿ ጂቡቲ እና ሁለት ታላላቅና 124 አነስተኛ ደሴቶችን ጠርንፎ ከያዘው የቀይ ባህሩ ዳህላክ ደሴት ለአሜሪካ ይበልጥ ጠቃሚው የትኛው ነው?
በሳኡዲ አረቢያ አማካይነት /በእጅ አዙር/ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ደጇን የከፈተችው ኤርትራ የዚህ ፖለቲካዊ ምህዋርና የጂኦ- ፖለቲካው አቅጣጫ ቅየራ ስትራቴጂ ቦታ ስለመሆኗ ሰሞኑን እየታዩ ያሉት መጠነኛ የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችና አቋማዊ ልስላሴዎች፣ አሜሪካ በቀንዱ ሃገራት ላይ ያላትን በተለይም አሁን ባለው የኢትዮጵያ መንግስት እምነት ማጣት ሳቢያ ያላትን የፖለቲካ ቅያስ በ360ዲግሪ ጠምዝዞታል። መነሻውን ለአመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ኤምባሲ መክፈት አድርጎ፣ ስጋት ናቸው ተብለው በአሜሪካ የተፈረጁትን የየመን አማጺ ሃይላት ለመውጋት ወታደራዊ ዘመቻን እስከመቀላቀል የዘለቀው ግንኙነት መዳረሻውን ለማወቅ ጥቂት መታገስ ያስፈልግ ይሆናል።
ሌላው ደግሞ ምናልባትም ሰሞኑን በኢትዮጵያ /በተለይም በኦሮሚያ አካባቢዎች/ በተከሰተው ህዝባዊ እንቢተኝነት ምክንያት ካለፉት 25ዓመታት “የአሳስቦኛል“ መግለጫ ባለፈ ይዘቱ ጥቂት ጠጠር ያለ ማሳሰቢያ መሆኑና እንዲሁም ሌሎች ለእይታ ግርድ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ እንሽርቶች፣ የፖለቲካ መልክዓ ምድር ቅየራ ምልክት የሚመስሉ ኩነቶችን እያየን ነው። በመሆኑም የሁለቱ ሃያላን ሃገራት ቁልፍ ገዢ መሬት የመያዝ እሽቅድድም የቀንዱ ሃገራት ፖለቲካዊ ቅቡልነት ህላዌ ላይ ጉልህ የሆነ ተጽእኖ ማሳረፉ አይቀሬ ነው።