ከአሰፋ እንደሻው (ለንደን፣ እንግሊዝ)*
ህብረተሰቡ የሚታነጽባቸው ዋና ዋና መንገዶች በቤተሰብና በማህበረሰቡ፣ በሃይማኖት ተቋሞችና በትምህርት ቤቶች ሆኖ ሳለ ዛሬ በይፋም በውስጥ ለውስጥም የሚነፋው የተሳሳተና የተጣመመ ብሎም ጎጂ አመለካከትና አጉል ልማድ ሁሉ በቀላሉ መወገድ የማይችል እየሆነ ነው፡፡ ትልቁ ምክንያት ለነዚህ አካሎች ሁሉ አመራር ሊሰጥ የሚችል ወገን በመጥፋቱ ነው፡፡ መንግስት ተብየው ለስሙ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ አማካይነት አልፎ አልፎ ማለቃቀስ ቢያሰማም፣ በተለይ ደግሞ ሙጭጭ አድርጎና አፍኖ በያዘው በመገናኛ ብዙሃኑ አማካይነት ምንም ለህብረተሰቡ ጎጂ የሆኑትን አመለካከቶችና አጉል ለማዶች ማስወገጃና ማራከሻ፣ ከውጭ ለሚጎርፉት የባህል ወረራዎች መከላከያ ሊፈጥር ቀርቶ በእውቀታቸውና በሙያቸው ይህንን ተግባር ሊፈጽሙ ለሚችሉት እንቅፋት ሆኖ ይኖራል፡፡
ለምሳሌ በጣም አስቂኝ ከሆነው ነገር ግን ምን ያህል ጠንቀኛ ባህል ሰባሪ መናኛ ድርጊት ተስፋፍቶ ህብረተሰቡን እንደሚበክልና ጤናውን እንደሚያውክ ስለአዲሱ አጎራረስ እናንሳ፡፡ ስንት መወያየት የሚሻ ቁም ነገር ሞልቶ ስለአጎራረስ ደግሞ እንዴት እናወራለን የሚሉ አይጠፉ ይሆናል፡፡ አንድ እንጀራ በሶስት በአራት ከፍሎ እየጠቀለሉ ባንድ አፍታ መጉረስ ለተመልካች ምን ያህል አንደሚያስጠይፍ ተመልክታችኋል? እጁ የሰበሰበውን ወጥና እንጀራ ለመያዝ አልችል ብሎ እየተንቀጠቀጠ ወዲያው አፉን ከስሩ አስገብቶ እንደመደገፊያም እንደተቀባይም ሲያደርግ ይህ ትርኢት የጤንነት ነው ትላላችሁ? ችኮላው ምንድነው; መስገብገቡስ; ጤናማ አበላል አለመሆኑን በደቂቃዎች ውስጥ ወዳንጀቱ አስገብቶ የሚያጭቀው መጠን ይመሰክራል፡፡ ሁለተኛም በዚያ ፍጥነት ሆዱ ውስጥ የሚጎደጎደው ምግብ የሚያስከትልበትን የውስጥ ጭንቀትና በጨጓራው ላይ የሚረጨውን ፈሳሽ መጠን እንዴት እንደሚቋቋመው ባለሙያዎቹ ቢናገሩት ይሻላል፡፡ አየር እንኳን ለመተንፈስ እየታገሉ በጉርሻ ጋጋታ የሚታፈኑ ሰዎች እንዴት ለጤናቸው እክል አይሆኑም?
ሌላ የታዘብነውን እንጨምር፡፡ የመኪና መንገድ አጠቃቀምን በተመለከተ ህብረተሰቡ ራሱን ለአደጋ ማጋለጡ እጅግ የላቀ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ እንደአምቦና የጎጃም ስልጡን ህዝብ በዳርና በዳር ከመሄድ መሃል ገብቶ መኪናው እንዲፈራና በጎማው ስር ሰውን እንዳያስገባ እንዲጠነቀቅ (እንዲጨነቅ) ማድረግ የጀብዱ አይነት ደረጃ ይዟል፡፡ በመሃል ገብተው እየተንጎራደዱ የመኪና ድምጽ ሲሰሙ ምንም ፍንክች የማይሉ፣ ጥሩምባ ሲነፋባቸው ለመሳደብና ለመደባደብ የሚሞክሩ፣ ከብቶቻቸውንና እንሰሳዎቻቸውን መንገድ ውስጥ ላይ ትተው እነሱ ከዳር ቆመው ትርኢት የሚያዩ … ስንቱ አይነት ሁኔታ ይታያል፡፡ አስተማሪም መሪም ጠፍቶ እንጅ የመቶበላ (መኪና) መንገድ የመኪና ብቻ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ሰዎች በአስገዳጅ ምክንያቶች መኪና መንገድ ውስጥ ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የመንገዱ አገልግሎት በጉልበት እየተለወጠ፣ ህጻናት ሳይቀሩ ለጥሩምባ ምንም ደንታ የሌላቸው ሲሆኑ ህብረተሰቡ ምን ያህል መናጋት እየደረሰበት ነው ያስብላል፡፡ ጧት ማታ የአደጋ ብዛትን በመገናኛ ብዙሃን ከማስተላለፍ በላይ የሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን ትምህርት ለህብረተሰቡ መስጠትና የህጉ ተፈጻሚነት ባሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን በመንገደኛውም ላይ እንዲጸና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ሆን ብሎ በመንገዶች አቆራርጦ ለመሄድ የብረት አጥር እየዘለለ ሲሄድ አደጋ ቢደርስበት ባለመኪና ሲጠየቅ በዚያ ድርጊት ላይ ዋናው ተዋናይ ግን እንደተጎጂ መደረጉ መቆም አለበት፡፡ ይሁንና በእግረኛው ደንታቢስነትና የመኪና መንገዶችን ሳይፈራ እንዲያውም እየተሞላቀቀ በመጠቀሙ በሚደርስበት ጉዳት ባለም ላይ እንደሚታየው ምንም ካሳ አለመስጠት በህጉ ጭምር መካተት አለበት፡፡ ገና ለገና ጉዳት የሚደረሰው በመኪናው ስለሆነ ምክንያቱ መጣራት እየቻለና እየታወቀ እግረኛው ምንም ቢሆን ምን የባለአሽከርካሪው እዳ እየተደረገ መቆየቱ ለአደጋዎች መብዛት እንጂ መፍትሄ አልሆነም፡፡ በህግ ረገድ በጣም የተሳሳተ አሰራር ከመሆኑ ሌላ፡፡ (በህግ ለጥፋት ምክንያት የሆነው ሰው ወይም አካል ነው ተጠያቂውም፣ ካሳ ከፋዩም፡፡ ጉዳት የሚደርሰው በመንገደኛው ጥፋት ከሆነ ጎጂው መኪናው መሆኑ ምንም ግምት ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡)
ሌላ አንድ ምሳሌ እንጨምር፡፡ በመንገድ ላይ፣ ባደባባይ፣ በህዝብ መገናኛዎች ውስጥ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ሁሉ የሚተላለፈው ዘለፋና እዚህ ላይ ለመድገም የሚቀፍ አስቀያሚ የስድብ አይነት ብሎም ለሰዎችና ለህብረተሰቡ የሚሰነዘር ንቀትና ያስተሳሰብ ትውከት ምን ልክ አለው; ምንስ አመልካች ነው; አጉራ ዘለል ወጣቶችና ለፍላፊዎች ህዝቡን በየስበቡ ሲያሸማቅቁት፣ በተለይ የፈረደባቸው እናቶች ላይ የሚወረወረው የብልግና ናዳ አየሩን ሲሞላው፣ ከሰው መሃል ብድግ ብሎ ይህንን ማቆም የሚችል እየጠፋ ዘመኑን ብቻ በመርገም ማለፍ እንዴት ይቻላል? መፍትሄውስ ምንድነው;
በመጨረሻም ባዲስነቱ ዘመናዊ እየመሰለ ነገር ግን የህብረተሰቡን መግባቢያ ልሳን ማለትም አማርኛን እየሞረደ ያለውን ክስተት እናንሳ፡፡ ካሁን ቀደም ደጋግመን አማርኛ ላይ ጉራማይሌነት እየተጫነው መምጣቱንና ይህንን አደገኛ አዝማሚያ ማስታገሻ መንገዶች ምን እንደሆኑ በተለይ ደግሞ ቀለም ቀመሱ ክፍል (“ምሁራን” ላለማለት ነው) ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት አውስተናል፡፡ የዛሬው ትዝብትችን ያገራችንን ሳባዊ (ፊኒቃዊ?) ፊደሎች እየተው በላቲን ስለመጠቀም ነው፡፡ ለቋንቋችን የተሻለ አጻጻፍ ይሆነናል ብለው ላቲንን እየሞከሩ ያሉትን ብሄረሰቦች ማለታችን አይደለም፡፡ ከብዙ አመታት በፊት ጀምሮ ደጋግመን በየመድረኩና በዚህ መጽሃፍ ላይ ያነሳነው ነገር ቢሆንም አማርኛ የሚገባቸውና የሚያነቡ ሁሉ ለምን በላቲን ፊደል ውስጥ መሸሸግ እንደሚፈልጉ አስገራሚ ሆኖብናል፡፡ ምናልባት ጥንት ከፊኒቃውያን ብሎም ሳባውያን እየተወራረደ ዛሬ በስህተት የግእዝ ብሎም የአማርኛ ፊደል የሚባለው እያለላቸው የተውሶ ላቲን ስር መንበርከክ ከምን መጣ?
በጣም አስቸጋሪና ጥልፍልፍ ስእል የሚመስል አጻጻፍ ያላቸው ቻይናዎች፣ የታይላንድ ዜጎች እና የመሳሰሉት እንኳን በራሳቸው “ፊደላት” እየተገለገሉ ነው። በራስ ፊደል መጠቀም ጥቅሙ እንደልብ ሃሳብን ለመግለጽ ማስቻል መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በመረጃና መገናኛ አብዮቱ ምክንያት ሁሉም አገሮችና ህዝቦች ከነቋንቋቸውና ባህላቸው ኢንተርኔትን ጨምሮ በተፈጠረው ህዋ (ምህዋር) ውስጥ መግባታቸው የግድ ነው፡፡ ነገር ግን የኛ ወገኖች የሆኑት በመረጃና መገናኛ ጥበብ የተከፈተውን እድል ማለትም ትልልቅ ሀሳቦችና የኪነጥበብ ስራዎችን ለማሰራጨት ሆነ ለመፍጠር በማስቻሉ የኖሩበትንና የለመዱትን እርግፍ አድርገው ጨርቃቸውን ጥለው በውጭ ፊደሎችና ዘየዎች ስር መወተፍ አይኖርባቸውም፡፡ በየድድ ማስጫው ላይ ሃሳብን መለዋወጥ ቀርቶ ፎቶህ ያምራል፣ ፎቶሽ ያምራል እየተባለ በላቲን ከመጻጻፍ የኛ ፊደል ምን አነሰው? ህዝቡ በራስ ባህልና ማንነት እንዲተማመን ማድረግ ስለተሳነ እንጅ።
ኢንትርነት (አለማቀፋዊ መረብ) ላይ የሚጽፉ ሰዎች በግድ በእንግሊዝኛ የተራቀቀ እውቀት ያላቸው ብቻ መሆን አይጠበቅባቸውም። አንድም የእንግሊዝኛ ቃል ባያውቁ አለማቀፉ መረብ ላይ እንዳይሳተፉ ምንም የሚገድባቸው ነገር የለም፡፡ እንደተጠቀሰው ቻይናዎችም፣ ኢራናውያን፣ አረቦችና ሩሲያውያን በየስእላቸው ወይም በየፊደላቸው ነው የሚጠቀሙት፡፡ (የተጠቀሱት ሁሉ የየብቻቸው ስእሎችና ፊደሎች እንዳላቸው ልብ በሉ፡፡) የኛዎችም በሳባዊ ፊደል ቢጽፉ ፋራነት የሚመስላቸው ካሉ በጣም ይሳሳታሉ፡፡ የመረጃና መገናኛ አብዮቱ የፈጠረውን ምህዋር (ህዋ) የሞላው ያለም ህዝብ ሁሉ ከነግሳንግሱ ነውና! በርግጥ ሁሉም አገሮች ህዝባቸው ይህንን ምናባዊ ወይም የፈጠራ ህዋ በሚገባ እንዲጠቀምበት ለየቋንቋዎቻቸው መንጠላጠያ አልሰሩም፡፡ ሃያላኑና ሃብታሞቹ አገሮች አዲሶቹን ግኝቶች በቶሎ ለህዝባቸውና ለኢኮኖሚና መንግስታዊ አውታሮች ለማዳረስ ስለሚተጉ እንደእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ቻይንኛ ያሉ ቋንቋዎች በምናባዊው ህዋ ላይ ገናና ሆነው ተሳፍረዋል፡፡ ከነዚህ በተቃራኒ ያሉት በተለይ አዲሱን ጥበብ ዘግተው ማንም ዜጋ እንዳይጠቀምበትና ስልጣናቸውን እንዳይነጥቃቸው የሚፈሩ ኢትዮጵያና መሰል መንግስታት ላለም አቀፉ መረብ ተስማሚና የተደላደለ አሰራር አልዘረጉም።
ነገር ግን በኢንተርኔት አጠቃቀም ወደኋላ የቀሩትና አፈና የሚደርስባቸው አካባቢዎችም በቅርቡ በጉግልና በማይክሮሶፍት ድርጅቶች በኩል መንገዱ እየተጠረገላቸው ነው፡፡ የያካበቢ ቋንቋዎች ቦታ እንዲኖራቸው፣ ተሳታፊዎች የማይገባቸውን ጽሁፍ ለማስተርጎም የሚያስችል አሰራር እያስገቡ፣ የግልጋሎት መረቡን እያሰፉት ነው፡፡ የአማርኛ አተረጓጎማቸው ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም ከትንሽ ጊዜ በኋላ ማንበብና መጻፍ ለሚችሉ ሁሉ የደራ ገበያ እንደሚሆንላቸው መገመት ይቻላል፡፡ ያገሪቱ መንግስት መስራት የሚገባውን ሌላው አለማቀፋዊ ሃይል ሲወስደው በነጻ እንደማይሆን በይበልጥ ደግሞ የውጭ ተጽእኖን ለማስፈን ከፍተኛ በር እንደሚከፍትላቸው ግን ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ ምን ይደረጋል; ባመዛኙ የመገናኛው አውታር እስከ ገጠሩ መንደር እየተዘረጋ በሄደ ቁጥር ተጽእኖው ቢያድግም በራሱ የሚተማመን፣ ባህሉንና ማንነቱን የሚጠብቅ ህብረተሰብ የመፍጠሩን ስራ ያከብደው እንደሆነ እንጅ ሂደቱ ሊገታ አይችልም፡፡ በሩን መዝጋትም አማራጭ አይሆንም፡፡ እንኳን ለሁልጊዜ ላንድ ሰሞን ሲዘጋ ምን ያህል በነጋዴው ህብረተሰብ፣ በኢኮኖሚው ባጠቃላይ እንዲሁም በውጭ ተወካየች ላይ ጉዳትና መንጫጫት እንደሚፈጥር ሁሉም የታዘበው ስለሆነ ምንም ሀተታ አያስፈልገውም፡፡
በርግጥ እንደቻይና ያሉ ሃያላን ለአለሙ መገናኛ ድር መነጋገሪያ (መዘወሪያ) ቋንቋ ጭምር በራሳቸው እየሰሩ ለህብረተሰባቸውና ለሃገራቸው ልእልና ቁልፍ አብጅተዋል፡፡ የቃሎች ትርጉም ብቻ ሳይሆን “ፊደላቸውን” ቀርጸው ገበታ ላይ አስፍረው ዜጎቻቸውን በቀጥታ ሚሹትን ለማየትና ለመመዝገብ አስችለዋቸዋል፡፡ አቅም የሌለው ሁሉ ግን በስማ በለው የሌሎችን ፊደሎች ሊዘግብ በተሰራው ገበታ ላይ የራሱን ጭኖ (ተውሶ ወይም ተንተርሶ ቢባል ይሻላል) ይንገዳገዳል፡፡ ዛሬ ባለው አሰራር ለምሳሌ ይህን መጽሀፍ ስናዘጋጅ ገበታው በላቲን ለሚጽፉ የተዘጋጀ ላይ ስለሆነ ልክ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ እንደምንጽፍ መስለን ነው የምንታየው፡፡ ያገር ባህል፣ የሃገር ልእልናና የማንነት ተቆርቋሪ መንግስት ቢኖር ይህንን አቢይ ጉዳይ እስከዛሬ ሊተወው አይችልም ነበር፡፡
በምሳሌነት የተጠቀሱትንና መሰል ችግሮችን በማህበራዊ መንገዶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም በተቋቋሙ መንግስታዊ ድርጅቶች አማካይነት ማስወገድ ቢቻልም መንግስታዊ ሆኑ የግል መገናኛዎች እንዲሁም መስሪያ ቤቶች ድርሻቸውን እንዲወጡ አመራር የሚሰጥ አላየንም፡፡ ህብረተሰቡ የመንግስት ፖለቲካ ልፈፋ ያሰለቸው ቢሆንም ያለአንዳች ማህበራዊና ባህላዊ አቅጣጫ ስለሚገላበጥ ያልተጠበቁና ያልተመዘኑ የውጭ ወጎችና ልማዶች፣ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች እየሾለኩ ሲያምሱት፣ ሲበክሉትና ከስር መሰረቱ ዋልጌነትና ማንዘራሽነት ሲተከልበት ዝም ብሎ መመልከት አይገባም፡፡ ዞሮ ዞሮ የዱሮው ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች እየተሻሻሉ መሄዳቸው፣ የሚነቀፉት በትክክል እየተገመገሙ መጣላቸውን ባዳዲስ መተካታቸው የማይቀር ቢሆንም በገፍ ከውጭ ከሚገባው የሸቀጥ እቃ ጋር የሚዥጎደጎደውን የተውሶ ዝባዝንኬ ግን መቋቋም አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ሰዎች ሰብእናቸውን ለማበልጸግ፣ ህብረተሰቡም ወጥ ባህሉንና ማንነቱን ለማነጽ የግድ የአጓጉል ተውሶ ወጎችን፣ አስተሳሰቦችና ዘዬዎችን አጥብቆ መግታት አለባቸው፡፡
ዛሬ አለማቀፉ መረብ ከየትኛውም አለም ክፍል ያሉትን ማናቸውም ወጎች፣ አስተሳሰቦችና ዘዬዎች እያደበላለቀ በመረቡ ላይ ለሚገናኙ ሰዎች ያለምርጫቸው ስለሚተፋቸው በጃቸው በሚገባው ስልክ ወይም የጭን ኮምፒዩተር ያለልፋት ስላገኙት መቀበል ያለባቸው መስሏቸው ለሚታለሉት ድጋፍ ሰጭ ሃይልና የጠራ የኑሮ መመሪያና እውቀት ያስፈልጋል፡፡ የራሳቸው የተጠናከረ የመገምገም ችሎታ ያላቸው ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ፊደል እንኳን በወጉ ያልቆጠሩ በመረቡ ላይ ስለተሰገሰጉ ያገር ባህልንና ገመናን ብሎም ታሪክንና ስነልቡናን አበክሮ በተጠቀሱት መንገዶች ማስጨበጥ፣ ከጥቃትና መሸርሸር ማዳን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
የባህል መሸርሸርን መቃወም የቆየውን ሁሉ እንዳይነካ የመከላከል ተልእኮ አድርገው የሚመለከቱ አይታጡም፡፡ ከጥንቱ ከጧቱ ፈቀቅ ማለት የሌለበት እንደቋሚ ሃውልት ተገትሮ መቅረት እንዳለበት አድርገው የሚሰብኩ እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ህብረተሰቡ በሂደት ለኑሮው እንቅፋት ሆኖበት ያገኘውን ለመለወጥ መነሳሳቱ የማይቀር ነው፡፡ እንኳን እኛው ራሳችን ከውጭ ወዳገሪቱ እየገቡ የሚታዘቡት ብዙ ነገር እንዳለ አመልክተዋል፡፡ አንዳንዴ መስመር የሳተ ሆኖ ቢገኝም፡፡
ስለኢትዮጵያውያን ባህርዮችና ወጎች ከሚቀርቡ ሀተታዎች አንድ ምሳሌ እናቅርብ፡፡ ሰላምታ በሚባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጽሄት ላይ አስተዋጽኦ የሚያደርግ አንድ የውጭ ተመልካች ስለኢትዮጵያውያን ይህን ብሎ ነበር። “ክህደት ሲደርስባቸው ምንም ያህል አይገረሙም፣ የግል መናቆርን ለዘመናት ይዘው መቆየት ይችላሉ። በብዛት ከቡድን ይልቅ በግለኝነት ይንቀሳቀሳሉ፣ ስርአትን እንጅ የውስጣቸውን አይከተሉም፣ ወደወሬው እንጅ ወደፈጠራው አይገቡም።”
ግምገማው ማለፊያ ይመስላል። እንደብዙዎች አጠቃላይ አነጋገሮች ግን የፈረንጁ ግምገማ የሚመስሉና የማይመስሉ ነገሮች አሉት። ኢትዮጵያ ባብዛኛው የግብርና ህብረተሰብ መናኸሪያ ስለሆነች ግለኝነት፣ ምቀኝነት፣ መጠላለፍ፣ መተናነቅ ሞልቷታል። እነዚህ የባላባቱም የባላገሩም ባህርያት ናቸው። ወደግብርናው ያልገቡ አካባቢዎች ይህን ላይጋሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል የሀገሪቱ አገዛዝ ከአክሱም ዘመን አንስቶ እስከ ሃይለስላሴና ደርግ ድረስና ዛሬም በርከኖች የተዋቀረ ወታደራዊ ባህርይ ስለነበረው ተጠንቅቆ በታዛዥነት አለቆችን መከተል እንጅ የፈጠራ ችሎታ ማብጀትና በራስ አነሳሽነት መንቀሳቀስ አልተለመደም። ከ1966 በፊት ዘመናዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ብቅ ማለትና በህዝቡ ውስጥ ሊስፋፉ ያልቻሉት፣ ዛሬም በአናሳ ቡድኖች ተከፋፍለው ከመቶ በላይ ሆነው ርስበርስ እየተጠላለፉ የሚታዩት በዚያው ምክንያት ነው። ድንገተኛ ሁኔታ ተፈጥሮ ለሁሉም የመጥፊያ ስጋት ካላደረባቸው ወይም ሰፊ እድል እፊታቸው ካልተዘረጋላቸው ተበታትነው መኖራቸው አይቀሬ ነው። ለየብቻቸው ፊን ፊን ሲሉ ቆይተው ዘላቂ ይሁን አይሁን ጊዜ የሚፈርደው ቢሆንም በቅርቡ ወደህብረት የመጡት የኦሮሞ “ነጻነት” ድርጅቶች የዚያ ተምሳሌት ናቸው።
ፈረንጁ ካለው ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደውንና ወደአማርኛ የተረጎምነውን መነሻ አድርገን ነው አስተያየት የሰጠነው። እርግጥ ነው ነቀፌታን በጥቅሉ የመጥላት ባህል በቀለም ቀመሱ ውስጥ የተስፋፋ ነው፣ እንኳን በገበሬውና በባላባቱ መሃል። ገበሬው የሚሰማውና የሚቀበለው በስልጣን፣ በእውቀትና በእድሜ የሚበልጠውን ነው። ከነዚህ ውስጥ ይበልጥ ደረጃ ያለው እንደተዘረዘሩት ነው። ወጣት ሆኖ ባለእውቀት ምንም ቢንጫጫ ቦታ አይኖረውም። ከ1966 ወዲህ በነዚህ በሶስቱ ደረጃ በኩል መጠነኛ ለውጥ ቢመጣም የእውቀት ቦታ አሁንም ከስልጣን በታች ነው። እድሜና እውቀት አቻ ሳይሆኑ ይቀራሉ; አንድ ሰሞን ተይዞ ከስር የተፈታው አስመሳዩ ዶ/ር መሃንዲስ ተቀባይነት ማግኘቱና ብዙ ሰው ለማታለል መብቃቱ በህብረተሰቡ ውስጥ የእውቀት ቦታ ከፍ እያለ መምጣቱን ያሳያል። በየከተሞች ውስጥ የማታ ትምህርት ሳይቀር በተልእኮውም በምኑም ሁሉም ወረቀት ነገር ለመጨበጥ የሚያደርገው መፈራገጥ ከዚህ የእውቀት ደረጃ መጨመር ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡ አንድ ሰሞን ዲግሪ የሌላቸው በስራቸው ግን እጅግ የተመሰገኑና ልምዳቸው የዳበሩ የመንግስት ሰራተኞች ሳይቀሩ መባረራቸውና መዋረዳቸውም ለዚህ ሂደት አስተዋጽኦ እንደነበረው መገመት ይቻላል፡፡
ህብረተሰባችን ባጠቃላይ በገበሬ የተሞላ ስለሆነ (በከተማውም የሞተ ከዳ ለባሽ ሞፈር ሰቀል ገበሬ ስለሚበዛ) በጠቀስኳቸው ሶስት ደረጃዎች ካልሆነ ማንም ሰው በአስተሳሰቡ ከኔ ይበልጣል ብሎ አይቀበልም። ለዚህ ነው ነቀፌታን እንደስድብ መቁጠር አሁንም ስር ሰዶ የሚታየው። ጠጅ ቤት ወይንም ባሁኑ ይበልጥ በተስፋፋው ቢራ/ድራፍት ቤት እንዲሁም በእድርና ሰርግ ላይ ተሰሚነት የሚገኘው በጩኸት በመብለጥ፣ በማንጓጠጥ፣ በደጋፊ (ቲፎዞ) ማብዛት (ነገረው! እያሉ እየጮሁ) ነው። ሶስቱን ነገሮች ከሚዛንነት አውጥተን።
ይህ ሁሉ ሲባል አርብቶ አደሩና ክፊል አራሽ የሆኑት እካባቢዋች በመጠኑም ቢሆን ከዚህ ትንታኔ ውጭ ናቸው። ባንድ በኩል እነዚህ አካባቢዎች አኗኗራቸው ከግለኛነት ይልቅ የጋርዮሽነት ባህሪዩ የጎላ ስለሆነ ሰብእናቸውም ያንኑ ይላበሳል፡፡ አብሮ ማለትም ተጋርቶ መብላትና መጠጣት፣ ንብረትንም መካፈል፣ መተጋገዝና መረባረብ ስለሚበዛባቸው እንደሌሎች አካባቢዎች ግለኝነት እስካሁን መረን አልተለቀቀባቸውም፡፡ ሆኖም በከተሞች መስፋፋትና በነሱ ይዞታ ስር አርብቶ አደሩን የማስገበር ሂደት እየተጠናከረ በመሄዱ ያብሮነቱ ብሂል እየሟሸሸ እንደሚሄድ እየታየ ነው፡፡
በርግጥ ባገሪቱ ባጠቃላይ ግለሰብ የምንለው ከህብረተሰቡ ገንጠል ብሎ የሚንቀሳቀስ ብቸኛ ፍጡር ገና የለም ወይም አልወጣም፡፡ አሁንም ድረስ አዛዡ፣ ፈራጁ፣ ሰጭና ነሺው ህብረተሰቡ ነው፡፡ ግለሰቡ የትም ሮጦ፣ ህይወቱን አሸንፎ የመኖር ግዴታ ቢኖበትም በባህርዩና በወጎቹ በኩል ህብረተሰቡ የሰጠውን ይዞ እንጅ እንዳሻው መሆን አይችልም፡፡ ከተሞች እያደጉ፣ ከገጠር ወደነሱ የሚተመው ህዝብ እየበዛ ከህብረተሰቡ ቀጥተኛ ቁጠጥር ስር እየወጡ አንጻራዊ የመንቀሳቀስና በህይወታቸው ላይ የሚሹትን ለማከናወን አቅም ሲያበጁ ከማናቸውም አይነት ጫናና ማህበራዊ መመሪያ መውጣት ይደፍራሉ፡፡ በከተሞች ውስጥ ከገጠሩ ህዝብ ለየት ያሉ ባህርዮች መታየታቸው የዚህን ሂደት የሚያስተጋባ ነው፡፡ ነገር ግን ገና በማደግ አዝማሚያ ደረጃ ላይ ያለ ስለሆነ የግለሰቦች የመንቀሳቀስና የመወሰን ችሎታ የተገደበ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ህብረተሰቡ በጋራ የሚወስናቸውና የሚያከናውናቸው በርካታ የኑሮና የስራ ክፍሎች ስላሉ ግለሰቦችም ከነዚያ ውሳኔዎችና ክንውኖች ዘለው የመውጣት እድላቸው ጠባብ ነው፡፡
ይሁንና የህብረተሰቡ ቁጥጥር በከተሞች ውስጥ የላላ ስለሚሆን በባህርይና በምግባር አቀራረጽ ላይ ከሰፊው ህብረተሰብ ይልቅ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና ቤተ እምነቶች ብሎም የመገናኛ ብዙሃን ድርሻቸው ይጎላል፡፡ በዛሬው ያገሪቱ የትምህርት ስርአት መውደቅ ወጣቱ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ወላጅም የባህርይና የምግባር ግንባታ ያልጎበኘው መሆኑ ስለማይቀር የባህል መሸርሸር መንገድ አግኝቷል፡፡ ስር ሰዷልም፡፡ ስማቸውን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ የዩኒቨርስቲ ምሩቆች መኖራቸው ሲሰማ ቢገርምም ሚዛን የሚደፋ አስተያየት ለመስጠትና ከሚቀናቀናቸው ጋር በጥሞና ለመወያየት አለመቻል በተደጋጋሚ በየመድረኩ ሲከሰት ለባህል መሸርሸር ችግር መፍትሄ ከየት ሊመጣ እንደሚችል ይጠፋናል፡፡ እነዚህ መሳዮች የቤተሰብና የቤተእምነት መሪዎች ሆነው ህብረተሰቡን ሲያተራምሱት ልጆቻቸውና ታዳሚያቸው የሚፈለገውን የባህርና የምግባር ቀረጻ ይጎናጸፋሉ ትላላችሁ;
የባህል መሸርሸርና የሰብእናችን መደብዘዝ ከተገለጠበት አንዱ አገራዊ ገጽታ በሰንደቅአላማ ዙሪያ የሚደርሰው መናፈር ነው፡፡ ባገሪቱ ህገመንግስት ላይ ሳይቀር በተከታታይ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ሆኖ እንደኖረ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ዱሮ በዘውዳዊ ስርአት ዘመንና በደርግ አገዛዝ የአንበሳ ምልክትን እንደአርማነት ሲገለገሉበት በመቆየታቸው አዲሶቹ ገዥዎች ስር ነቀል ለውጥ ያደረጉ መስሏቸው በሁለት የተለያዩ መንገዶች ስራ ላይ የመሆኑን ጉዳይ ሳቱት፡፡ ሁለቱንም ጠቅልለው አንድ ላይ ማስቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን አንበሳውን የት እንዳደረሱት ሳይታወቅ ለህዝቡ ግር የሚል አዲስ ምልክት ፈጠሩ፡፡ ይህን የተመለከተ ዜጋ ግን ዝም አላለም፡፡ የራሱን ሃሳብም በተለያዮ መልኮች ሲያቀረርብ ቆይቷል፡፡ በቃላትም በስእልም፡፡
አንዳንድ ሰው የፈጠራ ችሎታው አስደናቂ ነው። ባለፈው አመት ውስጥ አንዱ የመንግስት ተቃዋሚ የነበረን ባንዲራና ያገሪቱን የቆየ አላማ አዋህዶ ያቀርባል!! አሁን ይህን የሰንደቅአላማ ሽብልቅ ማን ያስበው ነበር? ይሁንና ኢትዮጵያ ትልቅ አገር መሆኗን መዘንጋት አይገባም። በብሄረሰቦች ብዛት ያጌጠች ስለሆነች ሁሉንም (እንደግማለን ሁሉንም) የሚያሰባስብ ሰንደቅአላማ እንጅ የጥቂት ህዝቦች ብቻ ለይቶ ይዞ መነሳት የተሳሳተ ይሆናል። በደቡብና ደቡብ ምእራብ የሚኖረው የህዝብ ስብስብ (ከ57 ብሄረሰቦች በላይ!) አብሮ መካተት አለበት።
ከዚህም በተጨማሪ መጠቆም ያለበት አቢይ ነጥብ አለ። የጣልያን ወረራ ባገራችን ላይ ሲቃጣ የኢትዮጵያን የነጻነት ተጋድሎ ለመደገፍ ባለም ዙሪያ የተንቀሳቀስው በይበልጥ በአሜሪካና በካሪቢያን ቀይ ቢጫ አረንጓዴውን ሰንደቅ አላማ አንግቦ ነበር። የኢትዮጵያ ነጻነት ከተመለሰም በሁዋላ ያንኑ ሰንደቅአላማ በቅኝ ግዛትነት የነበሩት ያፍሪካ አገሮች የነጻነት ትግላቸው አርማ አድርገውት ቆዩ። ብዙዎቹም ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ ያንኑ አርማ ለሰንደቃላማነት ተቀመውበታል። የጋና የሴኔጋል የማሊ ወዘተ ብሄራዊ ሰንደቃላማዎች ቀይ ቢጫ አረንጓዴን ይዘው ቦታውን ግን እያፈራረቁ እንደያዙት ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ገዥዎችና ፖለቲከኞች ራሳቸውን ከአለም ህብረተሰብ ውጭ አድርገው የመመልከቱ ይዞታ ስለተጠናዎታቸውና አሁንም ስለሚጠናዎታቸው የቀይ ቢጫ አረንጓዴው ሰንደቃላማ የጥቁሮች የነጻነት ተጋድሎና አርማ ሆኖ በአፍሪካም ሆነ በአሜሪካና በካሪቢያን ባህልና ፖለቲካ እንደተቀረጸ ሊገባቸው አልቻለም። በእውርነታቸውና ድንቁርነታቸው ይህን አርማ ማንገብ ቢያቅታቸው ከጥቁሮች የነጻነት ተጋድሎ ሰልፍ የሚወጡ መሆኑን እስካሁን መገንዘብ አቅቷቸዋል።
ህወሃት ስልጣን ከመያዙ በፊት ሆነ በሁዋላ አለማቀፍ እውቅናና ተምሳሌነት ያበጀውን ባንዲራ በማጎሳቆል ራሱ ተደናብሮ ሌላው እንዲደናበር ሞከረ። ለማንም ህዝብ ትርጉም የሌለው ባንዲራ አብጅቶ በጉልበት ሲያውለበልብ ኖረ። ከዚህም በላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተሻሽሎ የአፍሪካ ህብረት ሲሰኝ ከአፍሪካ የነጻነት ተጋድሎ ጋር የተሳሰረውን የኢትዮጵያን ባንዲራ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ካልሆነም በመጠኑ ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ አላማ እንዲሆን ምንም ሳይጥር ቀርቶ እዚህ ግባ የማይባል ባንዲራ በነጋዳፊ ተመረጠ። (አማርኛና ኦሮምኛ ከአህጉሩ ህብረት መነጋገሪያ ቋንቋዎች መካከል ከአረብኛና ስዋሂሊ እኩል እንዲገቡ ሳላለማድረጉ ጠቅሰን ብቻ እንለፈው?)
በቅርቡ የተለያዩ ወገኖች በተለይ የጎንደር ህዝብ ምስጋን ይግባቸውና ያንን የጥንቱን የኢትዮጵያና የአለም የጥቁሮች ነጻነት አርማ መልሰው በያሉበት ተክለውት ነፍስ እየዘራ ይገኛል። ምንም ተጫማሪ ነገር ሳያስፈልገው በኒው ዮርክ፣ በለንደን፣ በኪንግስተን ጃሜይካ፣ በእዲስ አበባን ሎሎች አካባቢዎች ህዝቦች የለመዱትንና የወደዱትን ባንዲራ በነጻነት እንዲውለበለብ አድርገውታል። ያው አይነት እርምጃ እልም ድርግም ይበል እንጅ እየቀጠሉ ነው።
ህወሃት ከህብረተሰቡ ጋር የሚጋጭበት ሳያጣ ብዙም ትንታኔና መተማመኛ በማያስፈልገው የባንዲራ ጉዳይ እየተነከሰ ራሱን ለውድቀት እያዘጋጀ ነው፡፡ አገር አቀፉ ባንዲራ ህዝቡ እንደሚፈልገውና በዱሮው መንግስታት ሳይወሰን አለማቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን ስቶ መዳከሩ አላስፈላጊ ነበር፡፡ አሁንም ሲሆን ሲሆን ህገመንግስቱ እንዲስተካከል በሚለው የህዝብ ጥያቄ ስር የሚጠቃለል ጉዳይ ስለሆነ ወደዱሮው እንዲመልሰው እስከዚያው ድረስ ራሱ የነደፈውን ባንዲራ ቤተመንግስቱ ላይ እየተከለ ማለትም የርእሰ ብሄሩ (የፕሬዚዳንቱ) ብቻ አድርጎ ህዝቡ የለመደውንና የሚወደውን ቀይ ቢጫ አረንጓዴ እንዳሻው እንዲጠቀም ይተወው፡፡ ዱሮም ቢሆን በርእሰ ብሄሩ ቢሮ፣ መኖሪያና መንቀሳቀሻ አካባቢ አገልግሎት ላይ የሚውለውና ባገሪቱ ህዝብ ዘንድ የሚታወቁት ሁለት አይነት ሊሆን ይችል የነበረውን በጉልበት አፍርሶ የመጣ ችግር ስለሆነ የሰው መሳቂያ ሆኖ ከመቅረት ልቦና መግዛት ይሻላል ባይ ነን፡፡
- አስተያየት ካለ፡- a_endeshaw@yahoo.co.uk
The post የባህል መሸራረፍና የሰብእና መሰባበር – ከአሰፋ እንደሻው appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.