ከተጀመረ ወራትን ያስቆጠረውና ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች በጭካኔ ለመገደላቸው መረጃ የሚቀርብበት ሕዝባዊ ንቅናቄ አሁንም በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ቀጥሎዋል። ኢህአዴግ በአፈቀላጤዎቹ አማካኝነት “ሰልፍ የወጣ የለም፣ ከተማችን ሰላም ነው፣ የተገደለ የለም፣ . . .” በማለት የማስተባበያ ሙከራው በራሱ ሹሞች ሲጨናገፍ በተደጋጋሚ ይስተዋላል። በሌላ በኩል በፌዴራልና በአግአዚ መራር ሰቆቃ እየደረሰበት ያለው ሕዝብ “ባርነት በቃን፣ ግድያው ይቁም፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ . . .” የሚሉ መፈክሮችን እያነገበ ሰላማዊ ተቃውሞውን ቀጥሎዋል። የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ባለፉት ሦስት ቀናት የተከሰተውን ያቀረበው ዘገባ ከዚህ በታች ይገኛል።
ባለፈው ሐምሌ ወር ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ ተወስዶ ታስሮ እንደነበርና ታሞ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና ላይ ሳለ ህይወቱ እንዳለፈ የተነገረው ተማሪ አብደታ ኦላንሳ ቀብር ዛሬ (ረቡዕ) አምቦ ከተማ ተፈጽሟል። በስልክ ያነጋግርናቸው ነዋሪ ትናንት ማታ የወጣቱን አስከሬን ለመቀበል በወጣ ህዝብ ላይ የጸጥታ ሃይሎች ድብደባ አድርሰዋል። ወደ ሰማይ ሲተኩሱም ነበር። አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ ተገድሏል ብለዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአምቦው ነዋሪ አስከትለውም ዛሬ በቀብሩ ላይም እንዲሁ የከተማው ነዋሪ በብዛት ወጥቶ እንዳይቀብረው ለማስተጓጎል ወታደሮች በተለይ ወጣቶችን መኪና ላይ እየጫኑ ወስደዋቸዋል ብለዋል። ወደ ቀብሩ ጉዞ ላይ የነበረ ወጣት በጥይት መገደሉን ገልጸውልናል።
ትናንትና ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርስቲ አዋሮ ግቢ አጠገብ የአንድ ወጣት አስከሬን ተገኝቷል ብለዋል።
የአምቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ሂርኮ አምቦ ውስጥ ተገደሉ የተባለውን አስተባብለዋል።
ባልደረባችን ጃለኔ ገመዳ አነጋግራቸው ነበር ። “ባለው መረጃ አምቦ ውስጥ የተገደለ ሰው የለም አዲስ አበባ ከተማ ታሞ የሞተ ሰው አአስከሬኑ አምቦ ገብቶ ዛሬ ተቀብሯል ። ለበለጠ መረጃ የአምቦ ከተማ ከንቲባውን አነጋግሩ” ሲሉ ቢመሯትም ከንቲባ ዱጋሳ ኦሉማ በእጅ ስልካቸው በተደጋጋሚ ተደውሎ አላነሱትም።
አዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሞቶ ዛሬ ተቀበረ ስለተባለው ወጣት አብደታ ኦላንሳ ጉዳይ ሆስፒታሉ መዝገቡን ተመልክቶ ነገ ማብራሪያ ሊሰጥ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ሶራ ሃለኬ ባገኘው መረጃ ደግሞ ፌደራል ፖሊሶች የተማሪዎች መኝታ ቤቶች እየገቡ ጭካኔ የተመላበት ድብደባ አካሂደዋል ብዙ መቶዎች አስረው ወስደዋል።
ስሜን አትግለጡ ያለው ተማሪ፣ ተማሪዎች ያሉትን ለማጣራት ወደ ከተማዋ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ደውሎ እንዳልተሳካለት ባልደረባችን ሶራ ሃላኬ በዘገባው አመልክቷል።
በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ ደግሞ የከተማው መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው ምክንያት የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ” “ ግድያው ይቁም” በማለት ትናንትናና ዛሬ ሰልፍ ወጥተዋል ሲሉ “ስማችንን እንዳትገልጹብን” ያሉ ተማሪዎች ለባልደረባችን ቱጁቤ ሆራ ገልጸውላታል።
በሰላም ነበር ሰልፉ የሚካሄደው የመንግሥት ሃይሎች በተኑት፣ የተወሰኑ ተማሪዎች ተደበደቡ፣ የታሰሩም አሉ ያለው ተማሪ እኔም ራሴ ከተደበደቡት አንዱ ነኝ ብሏል።
“የሃሮማያ እና የጅማ ተማሪዎች እንዲሁም በአምቦ ተማሪዎች መገደላቸውን በመቃወም፣ ድርጊቱ ይቁም ትግላችን ይቀጥላል ብለን ድምጻችንን ስናሰማ ነበር” ሲል ገልጿል።
የሻሸመኔ ከተማ የአስተዳደር እና ደህንነት ሐላፊ አቶ ስንታየሁ ጥላሁን ግን ሃሰት ነው ይላሉ ።
“ሰልፍ የወጣ የለም። ሰልፍ ማካሄድ ተፈቅዷል፣ ግን የወጣም የለም የታሰረም የለም፣ ተማሪዎች እየተማሩ ናቸው። መማር የፈለገ ይማራል፣ የማይፈልገውን ግን አናስገድድም መብቱ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ስንታየሁ አንዳንድ ጥያቄ ያነሳ ሊኖር ይችላል ብለው ነበርና ቱጁቤ ምን ጥያቄ ነው ያነሱት? ብትል “ማለት የጠየቁት እኮ ነገር የለም ቢሯችን የደረሰው መረጃ የለም ከተማውም ሰላም ነው” እንዳሏት አክላ ጠቅሳለች።
በሌላ በኩል በምእራብ ሃረርጌ በአዳ ቡልቱም ወረዳ በዴሳ ከተማ ከትላንት በስቲያ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ሕብረተሰቡ “ባርነት በቃን” የሚል መፈክር አንግቦ ለተቃዉሞ እንደወጣ መንግስት ጥቃት እንዳያደርስብኝ ሰሜ አይገለጥ ያሉ የሰልፉ ተካፋይ ለአፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።
በቀለ ገርባና በቀለ ነጋ ይፈቱ፣ የታሰሩ ተማሪዎች ሁሉ ይፈቱ ማስተር ፕላን ይሰረዝ የሚል በራሪ ወረቀቶች ይዘዉ ነዉ የወጡት። መንግድ ላይ የከተማዋ ካቤኒ አባል መሃመድ ሰይድ መጥቶ ወረቀቶችን ከእጃቸዉ ነጥቆ ሲበትን ሰልፈኞቹ ደበደቡት። ፌዴራል ፓሊሶችና አዳማ በታኝ ሃይሎች አሁን ያገኙትን ሁሉ እያወከቡና እያሰሩ ነዉ ፣ አግአዚዎችም ገብተዋል።
የባዴሳ ከተማ ካቢኔ አባል አቶ መሃመድ ሰይድ የበኩላቸዉን እንዲገልጹልን ሰልክ ደዉለንላቸዉ ነበር አያነሱም።
በምእራብ ሃረርጌ ሂርና ከተማ ለአንድ ሳምንት ያክል ሲካሄድ የሰነበተዉ ተቃዉሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አድማ በታኞች በወሰዱት እርምጃ ወደ ለየለት ጦርነት ተቀይሯል ይላሉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ በመጠየቅ የኦሮሚኛ ቋንቋ ክፍልን ያነጋገሩ የሰልፉ ተካፋይ።
“ሰላማዊ ሰልፍ ነበር የተጀመረዉ። መከላከያ ሰራዊት አምጥተዉ በሰላም የጀመርነዉ ትግላችንን ወደ ጦርነት ቀየሩት። በጥይትና በእንባ አስመጪ ጋዝ እየደበደቡን ነዉ። አጋአዚ ሁሉ አምጥተዉ ወንድ ሴት ሳይሉ በሒርና ከተማ ያለ ነዋሪ በር ሰብረዉ በመግባት እያሰሩ እየገረፉ ነዉ” ብለዋል።
በዛሬዉ የጸጥታ ሃይሎች ጥቃት ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቅ ሰዎች ቆስለዋል ብለዋል የሰልፉ ተካፋይ ነኝ ያሉት የዓይን እማኝ። ካሁን በፊት በጽኑ የቆሰሉ ሶስት ሰዎች ጭሮ ሆስፒታል እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የሂርና ከተማ ከንቲባ አቶ ከድር አቦዶ በበኩላቸዉ ከተማዋ ሰላም ናት ይላሉ።
“አይ እየታሰሩ ያሉ ሰዎች የሉም። ዉሸት ሊሆን ይችላል፣ እስካሁን የታሰረ ሰዉ የለም ከተማችን እስካሁን ሰላም ናት፥ ይህ ሁሉ ዉሸት ነዉ” ብለዋል።
ትላንት በምእራብ ሃረርጌ የአሰቦት ከተማ ተማሪዎች የከተማዋ ባንክ ቤት ፊት ለፊት ቆመዉ የአዲስ አበባና የፊንኒኔ ዙሪ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተቃዉሞ ማሰማታቸዉን የቪኦኤ የአፋን ኦሮሞ ክፍል ባልደረቦች ሰልፉን የተካፈትን በማነጋገር ዘግቧል።
የከተማዋ ፖሊሶችን ባለስልጣናት ተኩስ በማሰማት ሰልፉን መበተናቸዉም ታዉቋል፣ የቆሰለ ሰዉ ግን የለም። የአፋን ኦሮሞ ክፍልን ያነጋገረ አንዱ ተማሪ በአሰቦት ከሰዓት በሁዋላ ከ6 – 9 ሰዓት ሁለተኛ ዙር በተካሄደ ተቃዉሞ ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች ለገበያ የወጡ አርሶ አደሮች መቀላቀላቸዉን ገልጿል።
“ከዚያ በሁዋላ ሶስት መኪና ሙሉ የመከላከያ አባላት ወደ ከተማዋ ገብተዉ ተኩስ ከፈቱ፥ ተኩስን በመጋፈጥ ተማሪዎቹና ሕዝቡ ድንጋይ በመወርወር ተከላከል በተወረወሩ ድንጋዮች የተጎዱ የመከላከያ አባላት አሉ” በማለት በከተማዋ የነበረዉን ሁኔታ አብራርቷል። ተከትሎም የጸጥታ ሃይሎች ቤቶችን ሰብረዉ ገብተዉ ተማሪዎችን ለቅመዉ አስራዋል ብሏል።
ትናንት በዚሁ በምእራብ ሃረርጌ ጡጢሲ በሚባል ከተማና የዳሮ ገጠር ነዋሮዎች የተቃዉሞ ስልፍ ማከሃዳቸዉን ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የከተማዉ ነዋሪ ገልጿል። ጥያቄአቸዉም “አቶ በቀለ ገርባ እና የታሰሩት ሁሉ ይፈቱልን ኦሮሞ የሃገር ባለቤት ነዉ በማለት ሴት ወንድ ሳይል ነዉ ሁሉም ለተቃዉሞ የወጣዉ። ተማራዎች አልተካፈሉም። አርሶ አደሮች የአገር ሽማግሌዎች ናቸዉ ልጆቻችንን አትሰሩብን” በማለት ለተቃዉሞ የወጡት።
በጡጢሲ ተቃዉሞዉ በሰላም ቢጠናቀቅም፣ ፖሊሶች ብዙዎችን ቁጥጥር ስር እንዳዋሉ ተገልጾል።
የምእራብ ሃረርጌ አስተዳዳሪ አቶ አልይ ኡመር የአሰቦት ከተማ ከንቲባ አቶ ቶፈቅ አልህ እና የከተማዋ ሰላምና መረጋጋት ሃላፊ አቶ አደም ሲራጅን ለማነጋግር የተደረገዉ ሙከራ አልተሳካም።
የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ በኦሮሚያ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተጀመረ፣ ተቃዋሚዎቹ የታጠቁና የመንግስት ባለስልጣናትን፣ መሳሪያ ያልያዙ የጸጥታ ሃይሎችን፣ ገበሬዎችንና፣ ሕዝብን የሚያሸብሩ ናቸዉ ማለታቸዉን ሮይተርስ ባለፈዉ ታህሳስ አራት ዘገባዉ ጠቅሷል።
<!–
–>
The post በኦሮሚያ ከተሞች የሚካሄድ ተቃዉሞ ቀጥሏል appeared first on Medrek.