ትግራይ፣ ትግራይ ( የህዋህት ደጋፊ)
ኦሮሞ፣ ኦሮሞ ( ኦሮሞ ፈርስት፣ ኦቦ ጁሀር)
አማራ፣ አማራ ( ቤተ አማራ ፣ ሞረሽ )
የአነዚህን አንድ ኢትዮጵያን ፈታኝ የሆነ መንገድ ላይ የጣለ የዘር የገመድ ጉተታ ለመፍታት ኢትዮጵያን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለማቆየት የሚሹ ብዙ ሀገር ወዳዶች ተው! የዘር ጥምጥም ገመድ ለአንድ ሀገር ውድቀት ፣ ለውጭ ወራሪ በር የሚከፍት ነው እያሉ ስሚ እንኳ ባያገኙ ስለ ኢትዮጵያ ሲቃትቱ አመታት ተቆጥረዋል።
አንዳንዴ ደግሞ የአንድነት ሀይሉደጋፊ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ፍርደ ገምድልነት ሲሄድ የእነ እከሌ አጃቢ የነገር ጁራፍ ይገርፈኛል ብሎ ማለፍ ህልናዮ አይቀበለውም። ጎንደር የሚገኙ የነጻነት ተፋላሚዎች የገዳይ ወያኔ አፈሙዝ እያጓራባቼው ለነጻነት ሲዋደቁ እኔ የማንንም ደጋፊ ተቃውሞ ፈርቼ ዝም ልል አይቻለኝም።
ወደ ዋናው ሀሳቤ ልግባ ፣ ትናንት በስፋት በሁለት ወገን ተቧድኖ ሲወዛገብ ያየሁት ጉዳይ አንድ አማራ በ በጉራጌ ዞን ውልቂጤ አንዲት ሴት ተገድላለች በሚል ሰበብ ወንጄሉን ፈጻሚው እርሱ መሆኑ በህግ ፊት ቀርቦ ሳይጣራ በቀቤና ጉራጌዎች ከፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት ወጥቶ ልክ እንደ ሳውዝ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን በግፍ በገጄራ ተከትክቶ ያለ ገላጋይ የመገደሉ ዜና ነው። እዚህ ላይ ሟቹ ተጋሩ፣ ኦሮሞ ቢሆን ይህ የግፍ ዜና እንዴት በጦዘ የእዮዮው እንቢልታ አለምን ባዳረሰ። ደግነቱ በዚህ ዘመን ለሞት የተፈጠረ በሚመስለው በአማራ መሆኑ ለሟች በግፍ መገደል ምንም ሳይታዘን የገዳይ ዘር የ ቀቤና ጉራጌ ለምን ተወሳ በማለት ልብሳቼውን አውልቀው ያበዱ የሚመስሉ ፀሀፊ እና ደጋፊዎችን አስተዋልኩ ። ዜናውን የዘገበውን ጋዜጠኛ ሙሉቀንንም ይባዝቱት ጄመር። ዳኛ አልባዋ፣ ሁሉም ሊቅ እና ዜና ዘጋቢ ጋዜጠኛ የሆነባት ፌስ ቡክ ቀውጢ ሆነች። ጉራጌ እኮ እነ እከሌ የወጡበት ማህበረ ሰብ ነው ተብሎም ተደሰኮረ።
አቤት ጉድ! ማስተዋላችንን ማን ወሰደው እረ? እኛ እያነስን ሄድን እንጂ ከየትኛውም ብሔረሰብ በተለያዩ ዘመን ጄግና ያልወጣበት ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ እኮ የለም። ክብር የነፈግካት አንተ ፣ ኡትዮጵያ ሁሌም የጄግና መብቀያ መሬት ነች።
አንተም አማራ፣ አማራ የምትለው ወገን ፣ግድያውን አስፈጻሚው መግደያ ገጄራ አቀባዪ ወያኔ እንጂ ጉራጌ እማ እንደ አማራ በድህነት እንዲማቅቅ የተፈረደበት ማህበረሰብ መሆኑን ለምን አታስተውልም?
የእብድ ገላጋይ በመሆን ፍርድን በመገምደልሳይሆን ይልቁን የነጻነት ትግሉን ተባብረን ዳር ማድረስ እንድንችል ሁል ጊዜ በደል ለሚደርስበት ብቻ ለመጮህ እንንቀሳቀስ። የዘር ፖለቲካ ወያነያዊ ጥርጊያ መንገድ ነው ፣ ግቡም መፈራረስ እና መለያየት ነው።
በመጨረሻም እጁ በካቴና እያለ ከስር ቤት በግፍ ወጥቶ በገጄራ የተከተከተውን መስፍን አዳነ ኢሰብአዊ ግደያ አምርሬ አወግዛለሁ።
ፍትህ ለሟች ቤተሰብ እንዲሰጥ እጮሀለሁ።
ጨረስኩ!
ልያ ፋንታ
The post የዘር መቧደንን ትግል፣ ፍርድ በመገምደል አንታገል! (ልያ ፋንታ) appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.