Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

በውጥረት ላይ ውጥረት መደራረብ ይቁም!

$
0
0

ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በሰሜን ጎንደር የተከሰተው የተቃውሞ ንቅናቄ ሀገሪቱን ውጥረት ውስጥ ከትቷታል፡፡ አመጹ እየተጋጋለ መሄድ እንጂ የመቀዛቀዝ ባህሪ አላሳይ ብሏል፡፡ አሁንም በልዩ ልዩ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡ በአራቱም አቅጣጫዎች ውጥረት ሰፍኗል፡፡ በህይወት ዘመኔ ይህንን ያህል ዘላቂ ሆኖ የቆየ አመጽ አይቼ አላውቅም፡፡ በዚህ አመጽ ለጠፋው ህይወትና ንብረት እናዝናለን፡፡ በየትኛውም ወገን ሆኖ በትርኢቱ ውስጥ የተሳተፈው የኛው ዜጋ በመሆኑ ነፍሱና አካሉ ታሳዝነናለች፡፡

ታዲያ አመጹ የተከተሰው በመንግሥት ሚዲያ እንደሚነገረው “ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ግንቦት ሰባቶችና ኦነጎች በወጠኑት ሴራ ነው” የሚለው ምክንያት መሰረት የለውም፡፡ እንደዚህ ማለት “ህዝቡ አያገናዝብም፤ በማንም ይታለላል” የማለትን ያህል ነው፡፡ በኤርትራ የመሸጉት ድርጅቶችም ሆኑ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚባሉት የማይታወቁ ሃይሎች በዚህ አመጽ ላይ የተለየ ሚና የላቸውም፡፡ ድርጅቶቹ አመጹን ደግፈው መግለጫ መስጠታቸው የአመጹ ቀስቃሽም ሆነ መሪ ሃይል የሚያስብላቸው አይደለም፡፡

አመጹ የተወለደው የህዝብ ብሶቶች እንደ ኩሬ ውሃ እየተጠራቀሙ ከግድባቸው አልፈው መፍሰስ በመጀመራቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዚህ የህዝብ ብሶቶች ተጨባጭና ወቅታዊ ምላሽ እየሰጠ ኩሬውን ማድረቅ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ከህዝብ ከሚነሳው ቅሬታ ይልቅ ካድሬዎቹ በሚጽፉት አማላይ ሪፖርት ስለሚታለል ስለብሶቶቹ የሚያወሳውን ሁሉ እንደ ተቃዋሚ ያይ ነበር፡፡ ትክክለኛ ተቃዋሚዎችን ደግሞ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የቋመጡ ተስፈኞችና ሁከት ፈጣሪዎች ብሎ ከመፈረጅ ውጪ እንደ ተቃዋሚ የማየት ችግር አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች ከሚያነሱት የተቃውሞ ሃሳብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አይገነዘብም፡፡ የነዚህ ሁሉ ግድፈቶች ድምር ነው እንግዲህ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት እያሰለሱ ሲፈነዱ የነበሩትን አመጾች ሲቀሰቅሱ የነበሩት፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት አሁን አመጹን (በርሱ አገላለጽ “ሁከቱ”ን) ተቆጣጥሬአለሁ እያለ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁኔታው ትምህርት ቀስሞ ለህዝብ ጥያቄዎች ተጨባጭ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አሁንም ተመሳሳይ ስህተት ወደ መስራቱ ነው ያዘነበለው፡፡ ለምሳሌ በብዙ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ሰዎች በገፍ እየታሰሩ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ሁለት የኦፌኮ አመራር አባላት እና የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ታስረዋል (አንደኛው በቅርቡ የተለቀቁት አቶ በቀለ ገርባ ናቸው)፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ከስራ ገበታቸው እየተወገዱ ስለመሆናቸውም እየተነገረ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራንም ከትምህርታቸውና ከስራቸው መባረራቸውና መታሰራቸው ተዘግቧል፡፡ ይህ ሁሉ ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ሲደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ህዝቡ ይህንን ፈርቶ ለተቃውሞ እና ለአመጽ ከመውጣት አልታቀበም፡፡ ብሶቱ ሲያንገሸገሽው ለተቃውሞ ይወጣል፡፡ መንግሥት ለወደፊቱ ተመሳሳይ አመጽ እንዳይከሰት ከፈለገ የህዝቡን የልብ ትርታ ነው ማዳመጥ ያለበት፡፡ ዘወትር የሚወቀስበትን ተቃውሞን በጸጥታ ሃይል የመቆጣጠር ስልትን ተከትሎ በውጥረት ላይ ውጥረት መጨመር አይገባውም፡፡
—-

መንግሥት ራሱን አንቅቶ ሀገሪቱን መምራት የሚሻ ከሆነ በሶስት ደረጃዎች የሚተገበሩ እርምጃዎችን መውሰድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከሚፈጸሙት ተግባራት መካከል የመጀመሪያው በቅርቡ የተካሄደው ንቅናቄ “የህዝብ አመጽ” መሆኑን ማመን እና ይህንኑ በየደረጃው ላሉት አባላትና ደጋፊዎቹ የማሳመን ስራ ነው፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ጫፍ ከምትገኘው መንዲ ጀምሮ እስከ ምስራቅ ሀረርጌዋ የኮምቦልቻ ከተማ የሚኖረው ህዝብ የተሳተፈበትን ተቃውሞ “የጥቂት ነውጠኞች” ተቃውሞ እያሉ ማጥላላት አይቻልም፡፡

ንቅናቄው የኢህአዴግ መሪዎች በአድናቆት ከሚያወድሷቸው የራያ (ቀዳማይ ወያነ)፣ የጎጃም እና የባሌ ገበሬዎች አመጽ ጋር እንጂ አይተናነስም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚለው ንቅናቄው የተለኮሰው “ሽብርተኞች፣ ኒዮ-ሊበራሎች፣ ጋኔሎች እና ጋንግስተሮች” ባደረጉት ቅስቀሳም አይደለም፡፡ ስለዚህ ተቃውሞው የህዝብ እንደሆነ ማመን ይገባል፡፡

ከመንግሥት የሚጠበቀው ሁለተኛው ተግባር ደግሞ ተቃውሞው የህገ-መንግሥት ይከበር ጥያቄ መሆኑን ማመንና ማሳመን ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባው ማስተር ፕላን ጉዳይ ላይ የቀረበው ጥያቄ የህገ-መንግሥት ይከበር ጥያቄ ነው፡፡ ህገ-መንግሥቱ “የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ መብት አለው” በማለት ደንግጎ ሳለ ከዚህ ድንጋጌ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ማስተር ፕላን መንደፍ ምን ማለት ነው…? አዲስ አበባ ለኦሮሚያ መስጠት የሚገባውን ልዩ ጥቅም ሳይሰጥ ሃያ ዘጠኝ የኦሮሚያ ከተሞችንና ከሚሊዮን የበለጠ ደሃ ገበሬ የሚኖርበትን መሬት ደረጃ በደረጃ በአዲስ አበባ ውስጥ ለማካለል መሞከር በየትኛው የህገ-መንግሥቱ አንቀጽ ነው የሚፈቀደው? በዚያ ላይ ማስተር ፕላኑ ከሁለት ዓመታት በፊት ደም ያፋሰሰ መሆኑ እየታወቀ እና ለወደፊቱ ይቀራል ተብሎ ለህዝቡ ተነግሮ ሳለ ዘንድሮ ላይ ለተፈጻሚነቱ መንቀሳቀስ ጥቅሙ ለማን ነው….?. ህዝቡ ከህግ አግባብ አልወጣም፡፡ የየማስተር ፕላኑን ጥያቄ ጨምሮ ህዝቡ የተንቀሳቀሰላቸው ሌሎች ታላላቅ ጥያቄዎች ሁሉ ህገ-መንግሥቱን የማስከበር ጥያቄ እንደሆነ ማመንና ለተፈጻሚነታቸው መንቀሳቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

ሶስተኛው ታላቅ ተግባር ደግሞ በመንግሥት የሚሰነዘሩ ሃሳቦችንም ሆነ ፖሊሲዎችን የማይቀበለውን ዜጋና ድርጅት እንደ ሀገር ጠላት አድርጎ የሚፈርጀውን ኮሚኒስታዊ እሳቤ ማቆም ነው፡፡ በተግባር እንደሚታወቀው ኮሚኒስቶች እነርሱን የሚቃወመውን ሁሉ እንደጠላት ነበር የሚፈርጁት፡፡ ይህ ኮሚኒስታዊ አረዳድ በሀገራችን ውስጥ ምን አይነት ጥፋት እንዳስከተለ እናውቃለን፡፡ ለቀይ ሽብር መከሰት ዋነኛው ምክንያት የነበረው በ1966 ዓብዮት ማግስት ባበቡት ድርጅቶች መካከል የነበረው የአቋም ልዩነት ሳይሆን ድርጅቶቹ ከነርሱ የተለየ ርዕዮት ያለውን ዜጋና ቡድን በጅምላ እንደ ጠላት የሚያዩበት ኮሚኒስታዊ (ግራ-ዘመም) ዘይቤአቸው ነው፡፡ ኢህአዴግም የኮሚኒዝም አቀንቃኝ በነበረበት ዘመን ከርሱ የሚለዩትን ሁሉ በጠላትነት ይፈርጅ ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተከታይ ነኝ በሚልበት ዘመን እንኳ ከዚያ የጥንት ልማዱ ሙሉ በሙሉ አልተላቀቀም፡፡ ይህ ልማድ ካልቀረ ደግሞ ለሀገር በትክክል የሚያስበውን ዜጋ ለይቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ለሀገር ተቆርቁሮ በመንግሥት ፖሊሲዎችና የልማት ፕሮግራሞች ላይ ትችት የሚሰነዝረው በሙሉ እንደ ጠላት ስለሚፈረጅ የርሱ ሃሳብ አይደመጥም፡፡ የሚገርመው ደግሞ መንግሥት ብዙ ከተጓዘ በኋላ ከነዚህ ተቆርቋሪ ዜጎች የተሰነዘሩትን ሃሳቦች አምኖ የሚቀበል መሆኑ ነው፡፡ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡

በ1994/95 ሀገራችን ልክ እንደ አሁኑ በከፍተኛ ድርቅ ተመትታ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን የገበሬውን ህይወት ለመለወጥ በሚል መንግሥት በተግባር ላይ ካዋላቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ “ውሃ ማቆር” የሚባለው ነው፡፡ ሃሳቡ በአጭሩ “ገበሬው በክረምትና በበልግ ወራት የሚዘንበውን ዝናብ በጉድጓድ አጠራቅሞ ዝናብ በጠፋበት ወቅት ይጠቀምበት” የሚል ነው፡፡ ይሁንና የተለያዩ የውሃ ኤክስፐርቶች ይህ አሰራር ሀገር አጥፊ መሆኑን ማስረጃ እየጠቀሱ ሞገቱ፡፡ ለምሳሌ “በኩሬ የተጠራቀመው ውሃ ቀስ በቀስ ወደ መሬት እየሰረጎደ ስለሚገባ የገበሬው ልፋት ከንቱ ሆኖ ይቀራል፤ በተጨማሪም በጉድጓዱ ውስጥ ደለል ስለሚገባበት ገበሬው የሚፈልገውን ያህል ውሃ ማጠራቀም አይቻልም” ተብሎ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ውሃው ለወባ መራቢያ አመቺ በመሆኑ በገበሬው ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል” የሚል ስጋት ከውሃ እና ከጤና ኤክስፐርቶች ተነግሯል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዚህ ሃሳቦች ዋጋ በመስጠት ፈንታ “ጠላቶቻችን ልማታችንን ለማደናቀፍ የሰነዘሩት ሃሳብ ነው” እያለ ማጥላላትን ነው የመረጠው፡፡

ይሁንና በሂደት ሁሉም ችግሮች ቀስ በቀስ እየታዩ መከሰት ጀመሩ፡፡ ውሃው ወደ ኩሬ ውስጥ ከገባ በኋላ በኩሬው ውስጥ ከመቆየት ይልቅ ወደ መሬት ውስጥ እየሰረጎደ እንደሚገባ ታወቀ፡፡ መንግሥት ይህንን ለማስቀረት በሚል በኩሬው ውስጥ ፕላስቲክ ይነጠፍ ማለት ጀመረ፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ታላቅ አደጋ ተከሰተ! በዚያ የውሃ ማቆር ዘመቻ ሳቢያ ሀገሪቱ በታሪክ ያላየችው የወባ በሽታ ተጠቂ ሆነች!! መንግሥቱ በድርቅና በወባ ተወጠረ፡፡ አንደኛውን ችግር በአስቸኳይ ማስወገድ ስለነበረበት እንደዚያ የተለፋበትና የፕሮፓጋንዳ ጥሩምባ የተነፋለት የውሃ ማቆር ዘመቻ በ1997 አጋማሽ ላይ ለማንም ሳይነገር ተሰረዘ፡፡ ከዚያ በኋላ ስለርሱ ያወራ የለም፡፡ በቃ “የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ” ሆኖ ቀረ!!!

የኢትዮጵያ መንግሥት ከያኔው ስህተቱ ተምሮ ከምሁራን የሚሰነዘሩ ሃሳቦችን መስማት ነበረበት፡፡ ነገር ግን አሁንም ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ ጆሮውን ለምሁራን ውትወታ ሲከፍት አይታይም፡፡ በዚህ አያያዝ መቀጠል የህዝብ ብሶትን ማጠራቀም ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሃሳብ የሰነዘረን ግለሰብ እና ቡድን አክብሮ ለሃሳቡ ዋጋ መስጠትና መመርመር፣ እንደዚሁም ሃሳቦቹን ጠቅልሎ ከመዘነ በኋላ ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ ይገባል፡፡
—–
በሁለተኛው ደረጃ ላይ የሚከናወኑት ተግባራት ከህዝቡ ህይወት ጋር በቀጥታ ለሚገናኙ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ገበሬው ብሶት የሚያሰማበትን በግዴታ ላይ የተመሰረተ ማዳበሪያ የመጠቀም አሰራር እና ከተሜው ለሚማረርባቸው የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት አፋጣኝ መፍትሄዎችን መሻትን ይጨምራል፡፡ ሁሉም ዜጋ የሚንገሸገሽባቸው የመልካም አስተዳደር እጦትና የሙስና አሰራርም የመንግሥትን ፈጣን እርምጃ ይሻሉ፡፡ ከመደበኛ ነጋዴዎች የተለየ ድጋፍ የሚደረግላቸው ኢንዶውመንት ፈንድስ የሚባሉት ድርጅቶች (ኤፈርት፣ ጥረት፣ አምባሰል፣ ዲንሾ፣ ቱምሳ፣) ትክክለኛውን ህጋዊ መስመር ይዘው እንዲሰሩ መደረግ አለባቸው፡፡

ብዙዎች “የጆሮ ጠቢ ስርዓት” እያሉ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ማስወገድና የወጣቶችና የሴቶች ሊግ አባላት ብቻ እየተመረጡ ተጠቃሚ የሚሆኑበት የጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ፈጠራ ፕሮጀክት ለብዙሃኑ ህዝብ ክፍት ማድረግ ይገባል ፡፡ በዚህ ረገድ የሚሰሙት ብሶቶች ከህዝቡ ህይወት ጋር በቀጥታ የተገናኙ በመሆናቸው ሌላ የህዝብ ቁጣ እንዲነሳ የማድረግ አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ብሶቶቹን በጊዜ ለመቅረፍ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የሚፈጸሙት ስትራቴጂያዊ እቅድ ወጥቶላቸው የሚተገበሩ ስራዎች ናቸው፡፡ ከነዚህም መካከል አንዱ አዲስ የከተሞች ልማት ስትራቴጂ መቅረጽ ነው፡፡ የኢህአዴግ መንግሥት እስከ አሁን ድረስ የሚሰራበት የከተሞች ልማት ስትራቴጂ አዲስ አበባን ወደ ጎን ከመለጠጥ እና አስከፊውን የመሬት ቅርምት ዘመቻ ከማባባስ ውጪ በከተሞቻችን እድገት ላይ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ አነስተኛ ነው፡፡ በአንዳንድ ከተሞች የተወሰኑ ፎቆችንና መለስተኛ ፋብሪካዎችን ለማየት ቢቻልም በከተሞቻችን መካከል ተመጣጣኝ እድገት ማምጣት አልተቻለውም፡፡ የመንግሥቱ ትኩረት በአዲስ አበባ ላይ ብቻ በመሆኑ የክልል ከተሞች ከእንፉቅቅ ጉዞ ሊወጡ አልቻሉም፡፡ አዲስ አበባ እየተለጠጠች በማስተር ፕላን ስም የኦሮሚያ መሬቶችን ለመዋጥ ያሰፈሰፈችው የፌዴራል መንግሥቱ ለከተማዋ የሰጠው ገደብ የለሽ አትኩሮት በርካታ ፍላጎቶችን ስለቀሰቀሰ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ወልጋዳ የከተሞች እድገት ስትራቴጂ ተወግዶ ሁሉም ከተሞቻችን ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አዲስ የከተማ ልማት ስትራቴጂ መቀረጽ ይኖርበታል፡፡

ሌላው ደግሞ ዲሞክራሲን በትክክል የማስፈን ስራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ቢታወጅም ሀገሪቱ በተጨባጭ የምትመራበት ስርዓት ስያሜ በየትኛውም መዝገበ-ቃላት ተፈልጎ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ህገ መንግሥቱ ከአንዳንድ አንቀጾቹ በስተቀር በምዕራቡ ዓለም ያሉትን ህገ-መንግሥቶች ይመስላል (አብዛኛው ክፍሉ ከፈረንሳይ ህገ-መንግሥት የተገለበጠ ነው ይባላል)፡፡ በመሆኑም “ተራማጅ” ሊባል የሚችል ጤናማ ህገ-መንግሥት ነው፡፡ በአንዳንድ አንቀጾቹ ላይ (አንቀጽ 39፤ የመሬት አዋጅ ወዘተ…) የሚሰነዘሩት ጥያቄዎች ሀገሪቷ ወደ እውነተኛ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ እድገት ውስጥ በምትገባበት ጊዜ በሚፈጠረው ብሄራዊ መግባባት ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነቱን ተራማጅ ህገ-መንግሥት አጽድቆ ለርሱ ተገቢውን አትኩሮት የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡ ድርጅቱ ከህገ-መንግሥቱ ይልቅ በፓርቲ ደረጃ ለሚመራባቸውና ለሚያምንባቸው መርሖዎች ከፍተኛ ስፍራ ይሰጣል፡፡ እነዚህ መርሖዎች በአብዛኛው ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የተገለበጡ ነው የሚመስሉት፡፡ እነዚህ የፓርቲው መርሖዎችና ህገ-መንግሥቱ ሰማይና መሬት ናቸው፡፡ ሁለቱ ባልተጣጣሙበት ሁኔታ ትክክለኛ ዲሞክራሲን ማስፈን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፓርቲው መርሖዎቹን እንደገና በህገ-መንግሥቱ አቅጣጫ አስተካክሎ ራሱን ለፉክክር ማዘጋጀትና ሀገሪቱ ከጭምብል ዲሞክራሲ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የምትሸጋገርበትን ስርዓት ለመገንባት ሌት ከቀን መጣር አለበት፡፡
——
ከላይ በግሌ የሰነዘርኳቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ሙሉእ አይደሉም፡፡ የህዝብን ብሶት ለማሻርና እምባውን ለማበስ የሚሰሩት ስራዎች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ እኔ እነኝህን የመፍትሄ ሃሳቦች የጠቀስኳቸው ችግሮችን ዘርዝሬ መፍትሔዎችን ካልጠቆምኩ “ችግር ዘምዛሚ” የሚል ስም እንዳይሰጠኝ በመፍራቴ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና መንግሥት መፍትሔ ሰጪ መሆንን የሚሻ ከሆነ እኔ የጻፍኩትን ባይሆን እንኳ ጉዳዩን ይበልጥ መዘርዘር ከሚችሉ ምሁራንና ተቋማት የሚሰነዘሩትን የምክር ሃሳቦች ይስማ እላለሁ፡፡ በልዩ ልዩ ከተሞች አመጹን ለማስቆም በሚል በጸጥታ ሃይሎች የሚካሄደው ግድያ፣ እስራትና ከስራ መፈናቀል በውጥረት ላይ ውጥረትን እየደራረበ ሀገሪቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ከመውሰድ ውጪ ወደ መፍትሔ አያመሩንም፡፡ ስለዚህ እነርሱን በአስቸኳይ ማቆምና ለህዝብ ጥያቄዎች መፍትሔ የመሻት ስራዎች ላይ መረባረብ ይገባል፡፡ “ህዝቡ መቶ ፐርሰንት መርጦኛል” የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት በእውነትም ለህዝብ ጥቅም የቆመ ህዝባዊ መንግሥት ከሆነ ጆሮውን ከፍቶ ህዝቡን ማዳመጥ አለበት፡፡
—–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 29/2008

ማስታወሻ፡
1. በዚህ ጽሑፍ ላይ አስተያየት ስትሰጡ የማንንም ጎሳና ብሄር ከመሳደብ ልትቆጠቡ ይገባል፤ ሁሉም ህዝብ የኛ ህዝብ ነው ብሎ የማያምን ሰው ወደዚህ ባይመጣብን ይሻላል፡፡

2. አስተያየታችሁ በጹሑፉ እና በሰሞኑ አጀንዳ ላይ ያተኮረ ቢሆን ይመረጣል፡፡


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡

<!–

–>

The post በውጥረት ላይ ውጥረት መደራረብ ይቁም! appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles