በአውስትራሊያ ያሉ የኢትዮጲያ ማ/ሰብ አባላት ለ 19 ጊዜያት የስፖርትና የባህል ቶርናመንቶችን በየአመቱ በፈረንጆቹ የመጨረሻ ወር የመጨረሻ ቀናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ከእነዚህ ቶርናመንቶች አብዛኛዎቹ ፈታኝ በሆኑ የመከፋፈል አደጋዎች የታጀቡ ነበሩ። ለተጋረጡባቸው አደጋዎች ሳይበገሩ እስከዚህ ላደረሱን ወገኖቻች የላቀ ክብር ይገባቸዋል
ለተወሰኑ አመታት ከሞላ ጎደል አንድነቱን ጠብቆ የተጓዘው ቶርናመንት በዚህ ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት ማብቂያ ላይ ሌላ የመከፋፈል አደጋ ገጥሞታል። ይህም አደጋ በሜልበርን የኢትዮጲያ ኮሚኒቲና በስሩ በነበረው የስፖርት ፌዴሬሺን መሀል የተፈጠረው ነው። ይህ ክፍፍል ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሮ ሁለት ቶርናመንቶች በተመሳሳይ ወቅት ሜልበርን ውስጥ እንዲካሄዱ ሆኗል። ይህ ከመሆኑ በፊት በሁለቱ አካላት መሀል ከአመት በላይ የቆዬ እሰጥ አገባ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ችግሩን ለመፍታት ተቋቁሞ የነበረው ሸምጋይ ቡድንም ተልእኮውን ለመከወን የቻለውን ያክል ሄዶ ሳይሳካለት ቀርቷል።
ለኔ ይሄ ሶስተኛው ቶርናመንት ሲሆን የዘንድሮውን የታደምኩት እና በሙሉ አቅሜ የተሳተፍኩት ኮሚኒቲው ባዘጋጀው ቶርናመንት ላይ ነበር። እንዲህ አይነት ዝግጅቶች በአመት አንድ ጊዜ፣ ከሳምንት ላነሱ ቀናት ባለንበት ቦታ ኢትዮጲያን በምናብ ፈጥረን በአንድነት ሆነን ባህላችንን ወጋችንንና ታሪካችንን ለልጆቻችን የምናወርስበት ፣ አታካች ከሆነው የፈረንጅ አገር የህይወት ጫና ላፍታ ተነጥለን የሆድ የሆዳችንን ከአገር ልጅ ጋ በአገርኛ የምናወጋበት፣ ትዝታዎቻችንን የምናጣጥምበት፣ የተጠፋፋን የምንገናኝበት ልዩ እና ምትክ የሌለው አጋጣሚ ነው።
የኮሚኒቲው ዋነኛ አላማ ኢትዮጲያውያን በዘር በሀይማኖት እና በፖለቲካ ሳይለያዩ ኢትዮጲያዊ የሚያሰኙን ልዩና ውድ እሴቶቻችን ተጠብቀው አንዲኖሩ ፣ ትውልድም እንዲለማመዳቸውና እንዲረከባቸው ማድረግ ነው። ኮሚኒቲው ኢትዮጲያዊነት በሰፊው የሚናኝበት በቅብብሎሽ የሚተላለፍ ቅርስ ነው። ስለዚህ ማንኛውም የባህል፣ የስፖርትና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች በኮሚኒቲው ስር መሆናቸው በኔ በኩል ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።
በኮሚኒቲው አመራር ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጲያዊያን ቅሬታ እንዳላቸው ግልፅ ነው። እንደማንኛውም ማህበር አመራር ጥንካሬም ድክመትም መኖሩ የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር መገንጠልን እንደመፍትሄ የምንወስድ ከሆነ በፊትም ኮሚቲውን እንደራሳችን ማህበር አልተቀበልነውም ነበር ማለት ነው። ከነችግሩም ቢሆን ከማህበራችን ጋር እየወደቅን እየተነሳን ፣ የተከፋንባቸውን ጉዳዮች ለመቅረፍ የመፍትሄው አካል ሆነን መቀጠል ነው እንጂ የልጆቻችንን የወደፊት የጋራ መሰባሰቢያ ጥላ ለማን ጥለን ነው የምንሄደው? አመራሮች ይመጣሉ አመራሮች ይሄዳሉ። ኮሚኒቲ ቋሚ ነው። የአገር አምሳል ነው። ከዚሁ ጋር አብረን በሰከነ መነፈስ ልናዬው የሚገባው ደግሞ ይችን ክፍፍል በናፍቆት ሲጠባበቁ የነበሩ የአንድነታች ጠላቶች በቅርብ ርቀት ላይ መሆናቸውንና በተጨባጭም ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውን ነው።
የታደምኩበት ዝግጅት በድምቀት ደረጃ ካሳለፍኳቸው ሁለት ቶርናመንቶች በእጅጉ ይበልጣል። በክፍፍሉ ምክንያት ይገኛል ተብሎ ከተገመተው በላይ ህዝብ ተገኝቷል። ይሁን እንጂ በሁለቱም ቶርናመንት የተገኘው ህዝብ ተደምሮ ከአምናው ከግማሽ በላይ ያነሰ መሆኑ አሳዛኙ ውጤት ነው። በርካቶች ሁለቱም ቦታ ላለመገኘት ወስነው በቤታቸው ማሳለፍን መርጠዋል። ወንድማማቾች በተለያዩ ዝግጅቶች ተነጣጥው ተጫውተዋል። አባትና ልጅ የተለያየ ቦታ ነበሩ። ወጣቶች እኛ በፈጠርነው መከፋፈል እዚያ እና እዚህ ሆነው አንዱን ዝግጅት በአካል ሌላውን የሞባይል ቴክኒዎሎጂን እየተጠቀሙ ሲከታተሉ ተስተውሏል ። ልባቸው ከሁለት ተከፍሎ እና መወሰን ተስኗቸው የነበሩ በርካቶች ናቸው። አባቶች በልዩነቱ ዙሪያ ልጆቻቸው ለሚያነሱባቸው ጥያቄዎች የሚመጥን መልስ አጥተው የተቸገሩበት ሁኔታ ታይቷል ።
ጎበዝ የመከፋፈሉን አደጋ ወደ ልጆቻችን እያወረድነው ነው። ይህ ሁኔታ ባስቸኳይ መገታት አለበት። የሀይማኖት አባቶች ፣ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ከአሁኑ ሊመክሩበት ይገባል። ከኮሚኒቲውም የበለጠ ሀላፊነትና ሆደሰፊነት ይጠበቃል። የፌዴሬሽኑ አባላትም ይህ ኮሚኒቲ የናንተም የልጆቻችሁም ነውና ኑና ችግሩን በጋራ እንፍታው። የኮሚኒቲው ሬዲዮም (3R) ችግሩን ለመፍታት ሰፋፊ የውይይት መድረኮችን ሊያዘጋጅ ይገባል። በየቤቱ ምንም ተሳትፎ ሳያረጉ በየፌስቡኩ ሁኔታውን የሚያራግቡ ወገኖቻችንም ወደ መድረኩ በመምጣት የመፍትሄው አካል ሊሆኑ ይገባል።
በዚህ መለያዬት ያሸነፈ የለም። ሁላችንም ተሸንፈናል።ኢትዮጲያዊነት ተሸንፏል።
በአንድነት መቆም ስንችል ያኔ ሁላችንም አሸናፊ እንሆናለን። ለፍቅር ዝቅ ባልን ቁጥር ምንጊዜም አሸናፊ ነን። ነገሮች የበለጠ ሳይከሩ ከአሁኑ እንቅጫቸው።
The post ክፍፍሉ መቆም አለበት – ወንድምአገኘሁ አዲስ (አውስትራሊያ) appeared first on Medrek.