በሐይማኖቱ እና በአገሩ የሚደራደር ካለ የምድሩ እና የሰማይ ቤቱን በፍቃዱ ያስነጠቀ ደካማ ብቻ ነው።
ጠላት በራፍህ ላይ ቆሞ ሲያፏጭ ዝም ማለት ነገ ቤትህ የኔ ነውና ውጣ ከማለት እንደማይመለስ ማወቅ ይጠበቅብናል። ለሃይማኖታችን ዘብ ለመቆም የተዋህዶ ልጆች ቆርጠን እንነሳ ያኔ ለጠላታችን የምንፋጅ እሳት ለወዳጆቻችን ጥምን የምናረካ ውሃ እንደሆንን ያውቁናል። የሰማዕቱ የአቡነ ጴጥሮስን ቃል ማስታወስ ግድ ይለናል “አገርን የሚያጠፋ ሐይማኖትህን የሚያስለውጥ ጠላት መቷልና የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ አገርህን ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጥ ሐይማኖትህን ለውጠህ ብትገኝ ደሜ በሰማይ ይፋረዳችኋል እንኳን ሰዉ ምድሪቷም ለጠላት እንዳትገዛ ገዝቻለው”
ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስትያንን በአንድ ወቅት የማየት እድሉ ገጥሞኝ ነበረ። በየገዳሙ ስሄድ እያንዳንዱ ገዳም የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው እናም ደብረ ብርሃን ሥላሴ ለምን ተባለ ብዬ ጠየኩኝ፦ አንድ በእድሜ በሰል ያሉ አባት እንዲህ ሲሉ ያብራሩልኝ ጀመር፦ ደብረ ብርሃን ሥላሴ የሚለውን ስያሜ ከማግኘቱ በፊት ነው ቤተክርስትያኗ የተመሰረተችው። አሁን ያለውን ስም ሊሰየምለት የቻለው ግን በወቅቱ አገሪቷን ይመሩ የነበሩ የንጉሱ ሚስት ለመቁረብ ወደዚች ቤተክርስትያን ይመጣሉ እናም ስጋ ወደሙን ለመቀበል በሚቀርቡበት ሰዓት ጸጉራቸው በወጉ አልሸፈኑም ነበረና ዲያቆኑ እንዲህ መማለት ይናገራቸዋል “እሜቴ ስጋ ወደሙን ሲቀበሉ ጸጉሮን በነጠላ በደንብ ይሸፍኑ” ብሎ ይናገራቸዋል። የንጉሱ ልጅ እንዴት እናቴን አንድ ዲያቆን ይዳፈራል በማለት ቤተ ክርስትያኑ በራፍ ለይ ይገለዋል። ታሪኩን በማሳጠር ነው ያስቀመጥኩት በግዜው የነበሩ ፈራጆች(ዳኞች) ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ዲያቆኑ ጥፋተኛ እንደሆነና የንጉሱ ልጅ ትክክል እንደሆነ ፈረዱ። ዲያቆኑ የተዳፈረው የንጉስን ሚስት ነውና ልጃቸው የወሰደው እርምጃ ትክክል አንደነበረ አስረግጠው ተናገሩ።
ይህ ጉዳይ ንጉሱ ዘንድ ይደርስና ንጉሱ ዳኞችን ጠርተው ህዝቡን ሰብስበው የሆነውን ከሰሙ በኋላ የዳኞችንም ፍርድ ካዳመጡ በኋላ እንዲህ በማለት ለህዝባቸው ይናገራሉ። “እውን ከኔ ሚስት ክብር የክርስቶስ ስጋ ወደሙ ክብር አይበልጥምን? ከኔ ሚስትስ ስም የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም አይበልጥምን? ዲያቆኑ እውነትን በመናገር ለሚበልጠው ክብር ሰጥቷልና ጥፋተኛው ዲያቆኑ ሳይሆን ልጄ ነውና ዲያቆኑ የሞተበት ቦታ ላይ ወስዳችሁ ግደሉት በማለት ንጉሱ ይፈርዳሉ። የዚህን ግዜ እግዚአብሔር የጉሱ ፍርድ ትክክል ነው ሲል ከሰማይ በቀስተደመና አምሳል ብርሃን መጥቶ እዚህ ቦታ ላይ በትንሹ የተገነባች የድንጋይ ምልክት እያሳዩኝ እዚህ ቦታ ላይ መጥቶ ተተከለ ከዛን ግዜ ጀምሮ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ተብሎ ተሰየመ በዚህ ምክንያትም የአካባቢው መጠሪያም ሆነ። ደብረ ብርሃን ከተማ እና ፓሪስ ከተማ እኩል እድሜ እንዳላቸው ይነገራል።
ቤተክርስትያናችን ክብር እንዳልነበራት ሁሉ ዛሬ ግን ቤተክርስትያናችን መድፈርና ማቃለል ከተጀመረ ሰነባብቷል። ቤተክርስትያኗ ላይ ያለውን ችግርና እየመጣ ያለውን አደጋ በሌላ ግዜ እመለስበታለው ነገር ግን ሁሉም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በሙሉ በንቃት ሊጠብቅ እና በቁርጠኝነት ስለ እምነቱና ስለ አገሩ ዘብ ሊቆም የሚገባበት ስዓት እንደሆነ ላስገነዝብ እወዳለው።
ከላይ እንደመደርደሪያ ያነሳሁት ሃሳብ ያመጣሁበት ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ባለቤቱ እስራኤል የሚገኘውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን በመጎብኘት ላይ በነበሩበት ግዜ የቤተ ክርስትያኗ ቀኖና በማይፈቅደው መልኩ ጫማቸውን ተጫምተው ቤተ መቅደስ መግባታቸው የቆምክበት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን አውልቅ የሚለውን ህግ ተላልፈው በመገኘትና ለቤተ ክርስትያኗ ያላቸውን ንቀትና ድፍረት ያሳዩበት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ከፍተኛ ቁጣ ነው የቀሰቀሰው። አንደሚታወቀው አቶ ኃይለማርያም እና ባለቤታቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ እንደሆኑ ይታወቃል የነሱ እምነት ወደ ቸርቻቸው ሲሄዱ ጫማ ማውለቅ ምንም ትርጉም ላይኖረው ይችላል በኛ በኦርቶዶክሶች ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝም ስለሆነ ከምእመኑ እስከ ጳጳስ ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ጫማ ተወልቆ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩም ወደ ተዋህዶ ቤት ነውና የመጡት ስለዚህ የቤተ ክርስትያናችንን ህጓን ሊያከብሩ ይገባዎት ነበር ። እንዲከበሩ።
በአንድ ወቅት ባራክ ኦባማ የእምነት ተቋምን ሲጎበኙ ጫማቸውን አውልቀው ገብተዋል። ጫማ ማውለቁን ኦባማ ባያምንበትም ቅሉ ነገር ግን ለአማኞቹ ያለውን ክብር ያሳየበት በመሆኑ በማህበረሰቡ እንዲከበር ሆኗል። የኛዎቹ ግን በትእቢት እና በንቀት በመወጠር ቤተ መቅደስ ውስጥ ከነጫማቸው ገብተዋል። ምክንያቱም ደግሞ እኛ ኦርቶዶክሶች ስለተኛን ነው። መጽሐፍ እንደሚል አንተ የተኛህ ንቃ ይላልና ያለንበት ግዜ ታግሰን የምናልፍበት ሳይሆን የእምነታችንን ክብርና ሃያልነት ከፍ በማድረግ ከማንኛውም ጥፋትና የድፍረት አሰራር ነጻ የምንወጣው ቆርጠን በመነሳት ነቅተን በመጠበቅ ነውና ማንም ይሁን ማን በምንም ምክንያት ይሁን ተዋህዶ ላይ የስድብ አፉን የሚያላቅቀውን ለአፍታም መታገስ ሳያስፈልግ እምነታችንን እና አገራችንን ማስከበር አለብን እላለው። ይቆየን
ከተማ ዋቅጅራ
06.06.2017
Email- waqjirak@yahoo.com