Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

የኢትዮዽያ ድንበር ጉዳይ ምስጢራዊነትና ስጋት አረብቦበታል

$
0
0

ኢትዮጵያ ከድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ አራት ጊዜ ያህል ከጎረቤቶቿ ጋር ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ከ1983 ዓ.ም ወዲህም የባህር በር አልባ ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ሲንከባለል የቆየውን የድንበር ማካለል ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱ እየተነገረ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎም በአዋሳኝ ድንበሩ አካባቢ የፀጥታው ሁኔታ ማሽቆልቆሉ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያና ኬንያ በጋራ ድንበራቸው በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የፀጥታ ችግር ይቀርፋል የተባለ የጋራ የተቀናጀ የልማትሃሳብ የጋራ ድንበሮችን እንደ መዝጋት ሳይሆን በህጋዊ መንገድ በመክፈት ለውህደትና ትብብር በር ከፋች እንደሆነ እርምጃ መታየት እንዳለበት የዘርፉ ምሁራን ያሰምሩበታል፡፡

ከመቶ ዓመት በፊት ከሱዳን ቅኝ ገዢ እንግሊዝ ጋር የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርን ለማካለል ውል የተፈረመ ቢሆንም ከበርካታ ዓመታት ውይይት በኋላ በያዝነው ዓመት በመሬት ላይ ማካለል እንደሚጀመር መነገር የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ የኢትየጵያ መንግስት ግን የድንበር ማካለሉን ዝርዝር ይዘት ይፋ ማድረግ ባለመፈለጉ ከፍተኛ ጥርጣሬና ተቃውሞ እያሰሙ ያሉት ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

ምንም አስተማማኝ ማረጋገጫ ባይገኝለትም የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት በተለምዶ “የጉዬን መስመር” የሚባለውን እና ተቀባይነት የሌለውን በአንድ እንግሊዛዊ የተሰመረውን ድንበር መሰረት በማድረግ የሀገሪቱን ግዛት ያላግባብ ለሱዳን ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት ሰፍኗል፡፡ በአዋሳኝ ድንበሩ አካባቢም ከሁለት ወራት በፊት በሱዳን ሚሊሻዎችና በኢትዮጵያዊያን ታጣቂ ገበሬዎች መካከል ግጭት እንደተከሰተና የፀጥታው ሁኔታም ማሽቆልቆሉን የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከኬንያ ቅኝ ገዢ እንግሊዝ ጋር ሲያወዛግባት የነበረው የጋራ ድንበር ግን በ1962 ዓ.ም እንደገና የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በማሻሻል በመሬት ላይ ተካሏል፤ ምንም እንኳ የተተከሉት ችካሎች በጊዜ ብዛት ቢጠፉም እስካሁን ፀንቶ ይኖራል፡፡

የኬንያው “ዴይሊ ኔሽን” ጋዜጣ በቅርቡ እንደዘገበው ኬንያና ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ወዳጅነትና ትብብር ያላቸው ቢሆኑም ከመጋቢት እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ ጦር በኬንያ የመሸጉ ያላቸውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጣቂዎችን ለማጥቃት አምስት ጊዜ ድንበር ጥሶ በመግባት የመንግስት ድንበር ጠባቂ ፖሊሶችን እስከመግደል ደርሷል፡፡

የአዋሳኝ ድንበሩን ፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ኢትዮጵያና ኬንያ በቅርቡ ለአምስት ዓመታት የሚዘልቅ የተቀናጀ፣ ሁሉን ዓቀፍና ዘላቂ የጋራ ልማትና ፀጥታ መርሃ ግብር በኢትዮጵያው ቦረና ዞን እና በአጎራባቹ የኬንያዋ ሜርሳቢት አውራጃ ላይ ለመተግበር ስምምነት ላይ የደረሱት በቅርቡ ነበር፡፡ ከኢጋድ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር የሚተገበረው ይኸው መርሃ ግብር 200 ሚሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ የተነገረለት ሲሆን በማዕድን፣ እንስሳት ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ስራ ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንትና ኢነርጂ ልማት ዘርፎችን በጋራ በማልማት የስራ እድሎችን ለመፍጠርና የገቢ ምንጮችን ለማስፋት ያለመ ነው፡፡

በተለይ ተስፋፊዋ ሱማሊያ በኦጋዴን ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቷ ሦስት ጊዜ (1961፣ 1963፣ 1977/78) ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በጦርነቶቹ ያጣችው ግዛት የለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከአስር ዓመት በፊት ጦሩን ወደ ሱማሊያ ማስገባቱም በከፊል የድንበር ውዝግቡ መዘዝ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ታዛቢዎች ይገልፃሉ፡፡

ኢትዮጵያን ከሱማሊያ ጋር የሚያዋስነው ድንበር በርዝማኔው ቀዳሚው ሲሆን ለኢትዮጵያም የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ደቅኖ ቆይቷል፡፡ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር እንደ ቀድሞው አሊትሃድ እና የአሁኑ አልሸባብ የመሳሰሉ ሽብርተኛ ድርጅቶች ከሱማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ሰርገው ለመግባት የዚህን ድንበር ክፍተት እንደሚጠቀሙ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡

ምንም እንኳ በቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ማግስት በአፍሪካ አህጉር የድንበር ግጭቶች እጅጉን ቢቀንሱም ኢትዮጵያ ከኤርትራም ገር በድንበር ውዝግብ ሳቢያ ደም አፋሳሽ ጦርነት አካሄዳለች፡፡ በዋነኛነት የቅኝ ግዛት ውሎች መሰረት ተደርገው ድንበሩ ከ13 ዓመታት በፊት በዓለም ዓቀፉ የድንበር ኮሚሽን የመጨረሻ ውሳኔ ቢያገኝም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ውሳኔውን አልቀበልም በማለቱ እስካሁን በመሬት ላይ መካለል አልቻለም፡፡

በአፍሪካ አህጉር ምንም እንኳ የቅኝ ግዛት ድንበሮች እንደገና እንዲፈተሹ ግፊቶች ቢኖሩም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ግን እኤአ በ1964 ከቅኝ ገዥዎች የተወረሱ ድንበሮች በሙሉ በነበሩበት እንዲፀኑ የወሰነው ውሳኔ እስካሁንም እንደፀና ነው፡፡ ሃምሳ አምስት ሉዓላዊ ሀገሮች ያሉባት አፍሪካ በጠቅላላው 109 ዓለም ዓቀፍ ድንበሮች ያሏት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ2/3ተኛ በላይ የሚሆኑት በካርታ ላይ ያልተካለሉ ወይም በመሬት ላይ ያልተሰመሩ እንደሆኑ ከአፍሪካ ህብረት የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከነፃነት ማግስት ጀምሮ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአፍሪካ ሀገሮች ከድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዙ ግጭቶች ሲታመሱ ኖረዋል፡፡ ምንም እንኳ በርካታ የድንበር ውዝግቦች ህጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሄ ቢያገኙም እስካሁንም የፀጥታ ስጋት መንስዔ የሆኑ ድንበሮች አሉ፡፡

በአፍሪካ ከታዩት በርካታ ድንበር ውዝግቦች መካከል የአይቮሪኮስትና ላይቤሪያ፤ የማሊና ሞሪታኒያ ውዝግቦች በቶሎ በድርድርና በሽምግልና ተፈተዋል፡፡ በቱኒሲያና ሊቢያ፤ በቻድና ሊቢያ፣ በጊኒቢሰዋና ሴኔጋል፣ በናጀሪያና ካሜሮን መካከል የተነሱት ውዝግቦች ደግሞ ከብዙ ዓመታት መጓተት በኋላ በዓለም ዓቀፉ የዳኝነት ፍርድ ቤት ውሳኔ ነበር የተፈቱት፡፡

በድንበር ውዝግብ አፈታት በጥሩ ምሳሌነታቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ የናይጀሪያና ካሚሮን ተጠቃሽ እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡ እኤአ ከ1963 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የዘለቀው የሁለቱ ሀገሮች ውዝግብ በዓለም ኣቀፉ ፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኘው እኤአ በ2002 ቢሆንም ናይጀሪያ ግን እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ሳትቀበለው ቆይታለች፡፡ ናይጀሪያ በጠቅላላው ከአጎራባቾቿ ጋር ያላትን ድንበር ውዝግብ የፈታችው ብሄራዊ የድንበር ኮሚሽን በማቋቋም፣ የሚመለከታቸውን ህዝቦች በቀጥታ በማሳተፍና ከጎረቤቶቿ ጋር ክልላዊ ውህደትን ታሳቢ ያደረገ የድንበር ፖሊሲ በመንደፍ እንደሆነ በርካታ ታዛቢዎች ይመሰክሩላታል፡፡

የአፍሪካ ህብረት እኤአ እስከ 2017 ድረስ የአፍሪካን ድንበሮች በመሬት ላይ ተካለው እንዲያልቁ እያገዘ መሆኑን ቢገልፅም ዕቅዱ በታሰበለት ጊዜ እንደማይሳካ አስረጅ እየጠቀሱ የሚናገሩ ታዛቢዎች አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ይካለላል ተብሎ የማይጠበቀው የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ለታዛቢዎች ጥርጣሬ ዓይነተኛ ማስረጃ መሆን ይችላል፡፡

በሉዓላዊ ግዛት እና ድንበር ጉዳይ በኢትዮጵያዊያን ስነልቦና ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ እጅጉን አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ድንበር አያያዝን የሚተቹ በውጭ የሚኖሩ ምሁራንና ሌሎች ጉዳዩ ያሳስበናል የሚሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ጥቂት አይደሉም፡፡ በጠቅላላው የኢትዮጵያና ኬንያ የሰሞኑ ስምምነት እንዲሁም ከሱዳንም ጋር የሚካለለው ድንበር ለግጭትና ድህነት ተጋላጦ በቆየው ጠረፋማ አካባቢ ሁሉም ህዝቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ብሎም ክፍለ-አህጉራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደትን የሚያጠናክሩ መሆን ስለመቻሉ ወደፊት የሚታይ ነው፡፡

 Source:: wazemaradio

The post የኢትዮዽያ ድንበር ጉዳይ ምስጢራዊነትና ስጋት አረብቦበታል appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles