Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

“…የተገፋንበት ማጥ፣ እንኳን ተለያይተን አንድ ሆነንም ከተወጣነው ታላቅ ነገር ነው”

$
0
0

ከ“ህልውና” የተወሰደ፣  1992፣

ዶ/ር ሰለሞን ይርጋ፣

የትግራይ ጉጅሌ በህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል፣ በአንድ አናሳ በሆነ የትግራይ ጎሳ/ነገድ አባላት በሆኑ ጥቂት ሰዎች አማካይነት እየሆነ ያለው ዝርፊያ ቅጥ ማጣት፣ የፍትህ መጥፋት፣ የሌሎቹ የሁሉም ጎሳዎች/ነገዶች ድምር (አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ከንባታ ወዘተ…) አባላት የሆኑ ኢትዮጵያዊያን የገቡበት የድህነት እና የተስፋ መቁረጥ ደረጃ፤ እያንዳንዱ ዘራፊ ባለስልጣን፣ ደህንነቱን የሚመዝነው ባጠራቀመው ገንዘብ/ሃብት እና በስሩ ባሰለፈው አንጃ ብዛት እና (አንጀኞቹ እንደየሚወከሉት ነገድ/ጎሳ/ዘር እና/ወይም የቤተሰብ ዘር ሃረጋቸው እና ስልጣን ደረጃ ልክ ወዘተ…) መሆኑ፤  የአገራችንን ህልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥሏል። ጉጅሌው ለዝርፊያ እና ለአገዛዝ እንዲያመቸው የተከለው የጎሳ/ነገድ ፖለቲካ ዛሬ፣ ዘግይቶም ቢሆን፣ ጎጂነቱን ሁሉም ጎሳ እየተረዳው ይመስላል። ግን ከመረዳት በላይ አንድ እርምጃ ተራምዶ መሄድን የሚጠይቅ ጊዜ ላይ ደርሰናል–አበረታች የሆኑ ጅምሮች ቢኖሩም።

 

ጃዋር ሙሃመድ ከሰሞኑ በኢሳት “… የኦሮሞ ህዝብ በህይወቴ እንደዚህ ተቆጥቶ አይቸው አላውቅም። … ይህን [የኦሮሞ] ቁጣ [የትግራይ ጉጅሌ መንግስት] አሸንፎ ይወጣል ማለት ዘበት ይመስለኛል …” ማለቱን ሰማሁ። እኔ ደግሞ፣ ጉጅሌው ይኸንንም አመጽ አፍኖ ለማስቀረት የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም (ዶ/ር መሳይ፣ ይልማ በቀለ ሌሎቹም በቅርቡ በለቀቁት ጽሁፉ ውስጥ አስቀምጠውታል)። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያኑ የኦሮሞ ጎሳ/ነገድ ተወላጆች ሰልፍ ወጥተው ብቻቸውን ተቃውሞ ሲያሰሙ፣ በትግራይ ጉጅሌ መንግስት ሲገደሉ አሁን የመጀመሪያው አይደለም። ይኸን ያሁኑን አመጽ እና ያስከተለውን ግድያ እንደ አዲስ ነገር አድርጎ ማውራት፣ አምቦ፣ ወለጋ፣ ወዘተ ላይ ከዚህ ቀደም በግፍ የተገደሉ ዜጎቻችንን መስዋዕትነት ዋጋ ማሳጣት ይመስለኛል። የኦሮሞ ጎሳ ብቻ ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ፣ ሲዳማ፣ ከንባታ ወዘተ… ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን አገዛዙን ተቃውመው ሰልፍ ወጥተዋል፣ ተገድለዋል፣ ታስረዋል። ሰልፍ የወጡ በወሎ፣ ሸዋ፣ ጎንደር እና ጎጃም ወዘተ የተለያዩ ጎሳ/ነገድ ኢትዮጵያዊያን ተረሽነዋል።

 

የትግራይ ጉጅሌ እነዚህን ሁሉ የተለያዩ ቁጣዎች፣ በሚዘገንን የግድያ እና እስራት አጸፋ አሸንፎ ወጥቷል (በመሰረቱ እኔ “አሸነፈ” አልልም። በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እና በደል ስብስብ ውጤት፣ ጉጅሌውን እንደ ማዕበል ጠራርቶ እንደሚያስወጣው መገመት አያዳግትም። አስፈሪው ጉዳይ፣ ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥር፣ ማዕበሉ ሁሉንም ጠራርጎ እንዳይወስድ ነው)። ለጊዜውም ቢሆን ግን አፍኖ ማስቀረት የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም (ይህን ጽሁፍ የጀመርኩት ካንድ ሶስት ቀን በፊት ነው፤ በስራ ውጥረት ምክንያት አልተመለስኩበትም ነበር፣ አሁን ይኸው እየሆነ ያለውን እያየን ነው)። አስፈሪው ነገር የጉጅሌው ግድያ፣ እስራት እና የሃገር ሃብት ዘረፋ እየከፋ እና፣ የዜጎች ችግር እና አበሳ እየባሰ በሄደ ቁጥር፣ ሊከተል የሚችለው ምስቅልቅል ነው።

 

ይህን ሁሉ ግፍ እና ወንጀል ለመፈጸም ጉጅሌው ወትሮም ራሱ ብቻውን ሆኖ አይደለም፣ የየጎሳ/ነገዱ የ“ፖለቲካ ነጋዴዎች[1]”ን እጅ ተጠቅሞም ነው። የ“ፖለቲካ ነጋዴዎች” ስል እንደ ኦህዴድ ያሉትን ብቻ ማለቴ አይደለም። እንደ ኦህዴድ እና ኢህዴን አይነቶቹ፣ የለየላቸው ናቸው። አብዛኞቹም የየጎሳው የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ነን ባዮች “የፖለቲካ ነጋዴዎች”፣ ጉጅሌው መዝዞ የሰጣቸውን ብሄር[2]/ብሄረሰብ የሚሉ ካርታ እየመዘዙ ሲጫወቱ ኖረው፣ እነሆ ጃዋር አሁን እንዳልከው፣ “[ጉጅሌው] … ያቺን አገር በታትኗት እርስ በርስ አጫርሶን…” ሊሄድ ነው።

 

“እርስ በርስ አጫርሶን ሊሄድ…” እንደሆነ ባደባባይ መናገር፣ ከሩብ ምዕተ አመት በኋላም ቢሆን፣ እሰየው ነው። በጊዜ በጣም ጠቃሚው ጊዜ “አሁን” ነው። ጃዋር ከተናገረው ውስጥ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ በጥልቀት ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር “ይህ መንግስት ካሁን በኋላ 5 ወይም 10 አመት ከቆየ– እርሳው። ያቺን አገር በታትኗት ህዝቡን አጫርሶ ነው የሚሄደው … ሌላ የሚያስማማ ነገር እንኳን ቢጠፋ፣ ራስን ከመጥፋት ለማዳን መስማማት ያስፈልጋል” ያለው ነው።

 

“… ርሳው”። “ጫወታ ፈረሰ፤ ዳቦ ተቆረሰ” ብለን እንርሳው? እንወክለዋለሁ የምንለው ኦሮሞስ እጣ ፈንታው ምን ይሁን? እርስ በርስ ተጨራርሶ ሲያልቅ እንየው እና … እንርሳው? ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ የለም? ጃዋር፣ እስኪ ራስህን፣ አሁንም ሆነ ከ5 አመት በኋላ አገርቤት እንዳለህ አስበው እና እርስ በርስ እንደሚተላለቀው ህዝብ አንዱ አድርገህ አስበው።

 

እኔ ጃዋርን ብሆን አማራጩን አያለሁ። “… እወክለዋለሁ/እቆረቆርለታለሁ” የምለውን ህዝብ ከጥፋት ለማዳን፣ እስካሁን የሄድኩበት መንገድ ካልሰራ እና በተዘዋዋሪ መንገድም ቢሆን ለህወሃት የጎሳ/ነገድ መንግስት መሳሪያ ሆኖ መጠቀሚያ ከሆነ … “ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው፣ አንድ ህዝብ ነን” ብዬ አውጃለሁ፣ በጋራ ለመስራት ብሄራዊ አጀንዳ ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ጋር ለመነጋገር በሩን እከፍታለሁ፣ ከመዘግየቱ በፊት። አለበለዚያም፣ ፕሮፌሰር እዝቅኤል ጋቢሳ በቅርቡ በOMN እንደተናገሩት “… ዲያስፖራው ተከታይ ነው መሆን ያለበት፣ …በዚያ አገር ያለውን የወደፊት የፖለቲካ ስርዓት፣ ሼፕ ሊያደርጉት የሚችሉት…ወደፊት ሊኖሩበት የሚችሉት ወጣቶች ናቸው… እነሱ ናቸው ዋና ተጋፋጮች፤ ዲያስፖራው የነሱን አመራር እየተከተለ፣ … ቀድሞ ‘እንዲህ መሆን አለበት…’  ከማለት…የድጋፍ ሰጪነትን ሮል (ድርሻ) ነው መስጠት ያለበት… በውስጡ ያለው ዳይናሚክስ አለ… ያንን ቀደም ብለን ማየት መቻል አለብን።… ወዴት እየሄደ ነው? ለውጥ የራሱ አካሄድ አለው፣ ለለውጡ ዲስትራክቲቭ እንዳይሆን (ከጃዋር “…በሜጫ ነው የምንለው…”፣ “Ethiopia out of Oromia… አይነቶቹ አፍራሽ ንግግሮች ማለታቸው ይመስለኛል) ፣… ወደፊት ነው ማየት ያለብን፣ ባለፉት ሞዴሎች ብቻ እንዳንያዝ ማለቴ ነው…”፣ እንዳሉት የህዝቡን ሞት እና መከራ ከማራዘም ይልቅ፣ አገር ቤት መሬት ላይ ያለው ህዝብ ትግሉን በራሱ መንገድ እንዲያስኬድ መተው ነው። ፕሮፌሰሩ “… የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ከሌላው ህዝብ ጥያቄ የተለየ አይደለም..የዲሞክራሲ፣ የልማት እና የሰላም ጥያቄዎች የሰው ልጅ የሆኑ ጥያቄዎች እንደሆኑ በማረጋገጥ ትክክለኛ የሆነ ጥያቄ እንደሆነ መናገር ያስፈልጋል፣… የኦሮሞ መሪዎች ራሳቸው ጥያቄያቸው የሰው ልጅ መብት ጥያቄ እንደሆነ፣ እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ የሰው ልጅ ሁሉ ጥያቄ እንደሆኑ በማረጋገጥ…” መናገር እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት። እውነታቸውን ነው። For every failure, there’s an alternative course of action. You just have to find it. When you come to a roadblock, take a detour. Mary Kay Ash.

 

“Detour” … ለውጥ መንገድ ማየት ያስፈልጋል። ዛሬም ያንኑ የነገድ/ጎሳ ፖለቲካ ከማራመድ፣ እናም ከ5 ዓመት በኋላ የሚሆነውን ነገር እያዩ ከመርሳት የተሻለ አማራጭ አለ፣ የሚያስማማን ነገርም ሞልቷል። ትንሽ ሰብዓዊ እና ቅን መሆንን ብቻ ነው የሚጠይቀው። ትንሽ አሁን ካሉበት ቦታ ወርዶ፣ “ተሳስቼ ነበር” ማለት ብቻ ይበቃል። መንግስት ካሁን በኋላ 5 ወይም 10 አመት እንዳይቆይ እና ከርስ በርስ መጨራረስ ለመዳን፣ “ራስን ከመጥፋት ለማዳን”፣ የጎሳ/ነገድ ፖለቲካ እና/ወይም ሲቪክ ድርጅቶች ተወካዮች እና ተጠሪዎች፣ ከ“መርሳት” የተሻለ ትልቅ ሚና መጫወት ይችላሉ። እንደሚከተለው፦

 

  • ጎሳ/ነገድን መሰረት ያደረገ ስም ያለውን የማናቸውንም የፖለቲካ ድርጅት ቢቻል ኢትዮጵያዊ ስም መስጠት፤ የሲቪክ እና ሜዲያ ድርጅቶች እንደፈለጉ ስም ማውጣት ቢችሉም እንኳን፣ ኢትዮጵያዊ አቋም ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ እና ይህንንም ታዋቂ የሆኑት የየድርጅቱ ተጠሪ ግለ-ሰቦች ተሰባስበው አንድ መግለጫ እንዲያወጡ ማድረግ እና በአለም አቀፍ የሜዲያ ድርጅቶች፣ በተለይም አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደርሡ በሚችሉ ሜድያዎች (ኢሳት፣ ቪኦኤ፣ ጀርመን ድምጽ ሬድዮ፣ አዲስ ድምጽ፣ ኦ.ኤም.ኤን ወዘተ…) በመግለጫ ደረጃ እንዲሰራጭ ማድረግ። እና የየድርጅቱ ተወካዮች እያንዳንዳቸው በመግለጫው ውስጥ ካሁን በኋላ አጀንዳቸው ኢትዮጵያን ከትግራይ ጉጅሌ ነጻ ማውጣት እና ማውጣት ብቻ የሆነ ብሄራዊ አጀንዳ እንደሆነ፣ እስካሁን የተሄደበት መንገድ፣ እንደማያስኬድ መግለጫዎች እንዲሰጡ ማድረግ (ምሉዕነት ባይኖረውም ተጀምሯል። የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር መሪ አቶ ሌንጮ ለታን እና ሌንጮ ባቲ በሩን ገርበብ አድርገውታል። በርግደው መክፈት ያለባቸው ይመስለኛል)፤
  • በትጥቅ ደረጃ ከጉጅሌው ጋር እየተዋደቁ ያሉ ድርጅቶች መሪዎች፣ በመነጋገር አንድ ማእከላዊ አመራር እንዲኖራቸው ማድረግ፤ እና ምንም አይነት የጎሳ/ነገድ ቅጥያ የሌላቸውን፣ ብሄራዊ አጀንዳ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ፣ ነገር ግን ሁሉም ድርጅቶች፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ እና ሂደት፣ የሚያምኑበትን ግለሰብ/ቡድን አመራሩን እንዲይዝ/ዙ ማድረግ።
  • የፖሊቲካ እና የፕሮፓጋዳ ስራው በምንም አይነት አጠቃላዩን የትግራይን ምስኪን ህዝብ የጉጅሌው ደጋፊ አድርጎ ከማየት መቆጠብ ይኖርበታል። እውነታውም ያው ነው። ጉጅሌው በትግራይ ወጣቶችን ለውትድርና እየጠራ እንደሆነ (ጎልጉል ጋዜጣ) እየተነገረ ነው። አያደርግም አይባልም። “የዘራዊነት መጨረሻው እስከ ቤተሰብ ድረስ መሰባሰብ ነው”። የትግራይ ጉጅሌ መሪዎች ዛሬ፣ በትግራይ ህዝብ ስም ተነስተው፣ ኢትዮጵያን በሞላ በቤተሰብ ደረጃ በሚመስል እየዘረፏት ነው። በሚስት እና ልጅ፣ ወንድም እና እህት፣ አክስት እና አጎት እያለ እየወረደ … ያከማቹት ገንዘብ እና ሃብት ያስደነግጣል። ከነሱ የተረፈው ነው ለሌሎቹ እንደነ ኦህዴድ ላሉ የጎሳ/ነገድ መሪ ለሆኑ የ“ፖለቲካ (ደም) ነጋዴዎች” የሚደርሰው። የጉጅሌው መሪዎች ልጆች እና ዘመድ አዝማዶች ዛሬ መሳሪያ አንስተው ቃታ ሊስቡ ቀርቶ፣ እስክሪብቶ የሚጎረብጣቸው ናቸው። የትግራይ ድሃ ልጆች ደግሞ ስለ “ሙስና ሠፈር” እና ባለቤቶቻቸው ብዙ ያውቃሉ። ስለዚህ አብዛኛው የትግራይ ጎሳ እንደሌላው የተገፋ፣ የተገደለ፣ የደኸየ ነው። ይህን ስል በመጠን (ፕሮፖርሽን) ደረጃ፣ የትግራይ ጎሳ/ነገድ ህዝብ ከሌላው ጎሳ/ነገድ ህዝብ በተለየ አልተጠቀመም ማለትም ራስን ማዘናጋት ይሆናል። የጄነራሎቹን ማንነት ማየት ይበቃል። የአማራ፣ ኦሮሞ፣ ከምባታ ወዘተ ጎሳ ተወላጆች በጄኔራልነት ደረጃ ተሰማርተው አገራቸውን እና ራሳቸውን (ከሞራልም ሆነ ከቁስ አኳያ) መጥቀም ይወድላቸዋል። ዛሬ አብዛኛው የመንግስት ቢሮ (ለምሳሌ ኢሚግሬሽን) በአብዛኛው በትግራይ ተወላጆች የተያዘ ነው። መርካቶ ገበያ አዳራሽ ብትገባ እንደቀድሞው በጠንካራ የስራ ባህላቸው የሚታወቁትን ጉራጌዎች አታገኝም። አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ግን አሁንም እየተሰደደና በድህነት ውስጥ ያለ ነው። ሁሉንም የትግራይ ተወላጅ ባንድ ላይ የትግራይ ጉጅሌው አባል እና ጠላት አድርጎ ማየት ትክክል አይደለም፣ ከትግራይ ተወላጆች ውስጥ የሚቃወማቸው የለም ማለትም፣ በጉጅሌው በግፍ የተገደሉትን እነ አረጋዊ እና ሌሎቹንም በርካቶች የተሰዉትን፣ የፖለቲካ ስርዓቱን በመቃወም በየእስር ቤቱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን እንደነ አብርሃም ደስታን እና በስም ያልታወቁ እና በየህቡዕ እስር ቤቱ እየማቀቁ ያሉትን የትግራይ ተወላጆች መርሳት ፍርደ ገምድልነት ነው።

 

“… በኢትዮጵያዊያን መሃል ጠላትነት የለም። ጠላትነትን የሚፈጥሩት የፖለቲካ ተጠቃሚዎች ናቸው። እነዚህ በፖለቲካ ድርጅት የተደራጁት የህዝባችንን አንድነት ለማስተማር እና አብሮ ለማሰለፍ ካልቻሉ የኢትዮጵያ ህዝብን የሚጠሉ ናቸው። በኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ ራሳቸውን ለማሳደግ የሚፈልጉ ናቸው። …” ይህ ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው በኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ የተናገረው ነው። የአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራም መኖሩ ራሱ በጣም የሚያበረታታ ነው። በተለይ “… ጠላትነትን የሚፈጥሩት የፖለቲካ ተጠቃሚዎች ናቸው…በህዝብ ስቃይ ራሳቸውን ለማሳደግ የሚፈልጉ ናቸው” ሲል የጠቀሳቸውን፣ ዶ/ር ሰለሞን ይርጋ ደግሞ “የደም ነጋዴዎች” ይላቸዋል። ሁለቱም ምሁራን፣ የዘር ፖለቲካ አራማጆች፣ በሰው ደም ሃብት እያካበቱ ያሉ መሆናቸውን ለመንገር ነው። በዘር ፖለቲካ ተጠልሎ፣ ህዝብን በዘር እያጋጩ ሃብት ማግበስበስን ከትግራይ ጉጅሌ መሪዎች “ኢንቬስተርነት” ሌላ ምን ማስረጃ ያስፈልጋል?

 

አማራው በጉጅሌው ሲገደል እና ሲጨፈጨፍ፣ ጊሚራው በርቀት እያየ ዝም ያለበት፤ ኦሮሞው ሲታረድ፣ ጋሞው እጁን አጣጥፎ ያየበት፤ ሱማሌው በወንድሙ ገዳይ አዛዥነት የገዛ ወንድሙን ሬሳ እንደ ዲንጋይ “ልቀም” ሲባል፣ ሃረሪው ፊቱን ያዞረበት፣ ቤንሻንጉሌው በጫካ ታርዶ ሲጣል አኝዋኩ ጀርባውን ሲሰጥ (vis versa) … ወዘተ፣ ጉጅሌው ያገሪቱን ሃብት ዘርፎ፣ ያገሪቱን ህዝብ አደህይቶ እንሆ የኢትዮጵያ ህዝብ በመኖር እና ባለመኖር ላይ ይገኛል።

 

ባለፉት 25 አመታት ውስጥ፣ ይህ አሳዛኝ ነገር  እንዲሆን፣ የጉጅሌው መንግስት ባደባባይ አደራጅቶ እና አስታጥቆ ካሰማራቸው የየነገዱ ተወካይ ነን ባዮች እና ታጥቂዎች (ለምሳሌ የኦህዴዱ አባዱላ ገመዳ) ሌላ፣ በየዉጭ ሃገሩ የሚገኙ እና ጎሳችንን እንወክላለን የሚሉት ድርጅቶች ተጠሪዎችም፣ የህዝባችን ድምጽ ነው በሚሉት ሶሻል ሚዲያ ሁሉ፣ ከፍተኛ የአፍራሽነት ሚና ተጫውተዋል።

 

ዶ/ር ጌታቸው “… ያለፉትን ስህተቶች አርሞ የወደፊቱን ብሩህ ጸጋ ሊያጎናጽፈው የሚችለውን ለማየት እንዲችል አብቁት። የፖለቲካ ድርጅቶች … ቶሎ… ቶሎ በአስቸኳይ በመጠራራት፣ በመገናኘት አንድ ጊዜያዊ የመተባበሪያ ሰነድ በማውጣት …መንቀሳቀስ እና የህዝቡን ትግል ማስተባበር ይጠበቅባቸዋል። ይህን የማያደርጉ የፖሊቲካ ድርጅቶች የህዝቡ ጠላቶች ናቸው” ያለውን ማስተዋል እና ባስቸኳይ አቋም ላይ መድረስ እና ያን አቋም ማሰራጨት ያስፈልጋል።

 

የእገሌ ጎሳ የእገሌ ጎሳን ዘረፈ/አልዘረፈም፣ ገደለ/አልገደለም፣ ወዘተ … ለሚል ክርክር አሁን የተረፈ የቅንጦት ጊዜ ያለን አይመስለኝም። አንድ የምለው ነገር ቢኖር ቢያንስ በደርግ ጊዜ፣ የመሬት አዋጅ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ፣ በአንዱ ጎሳ ቋንቋ/ባህል ላይ ሌላው ከማሾፍ እና ከመበሻሸቅ (Bully ከማድረግ፣ ይኸንንም መደገፌ አይደለም፣ በውነት አንዱ በሌላው ዘር/ጎሳ ላይ ማሾፍ እና ራስን ከፍ አድርጎ ማየት እና ሌላም በደል አልደረሰም አይባልም። አሁንስ ቢሆን ቀልደኞቻችን ቀልዶቻቸው ባብዛኛው ባንዱ ጎሳ ቋንቋ እና አነጋገር ዘይቤ መሳቅ መሳለቅ አይደል እንዴ?) ባህር ማዶ ከመጣሁ ሁለት አሰርት ሊሞላኝ ነው። ካገሬው (ያሜሪካ) ሰው የገረመኝ ነገር ቢኖር በእንግሊዝኛዬ ስቆ ወይም አሹፎ የሚያውቅ ሰው የለም። ቋንቋ መግባቢያ ነው። አለቀ!) ባለፈ፣ ዘርን መሰረት ያደረገ ግድያ፣ እስራት እና ዝርፊያ አልሆነም። ቢያንስ በደርግ ጊዜ ይህ አልሆነም።

 

የትግራይ ጉጅሌ ባለስልጣን አባይ ጸሃዬ ይህን አመጽ ልክ እንደተናገሩት “ልክ አስገብተው” ወይም “…እስር ቤት ቢሞላም እንኳን በረት ውስጥ …” እያሰሩ ሊቆጣጠሩት ቢችሉ ችግሩ የማን ነው? (ስልጣን ላይ የሚያቆየው ከሆነ፣ አይደለም ማሰር፣ በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ማለቅ ቢኖርበት እንኳን፣ ጉጅሌው ከመግደል የሚመለስ አይደለም። ሰዎቹ ጭካኔያቸው ወደር የለውም። በ1960ዎቹ መጨረሻ/70ዎቹ መጀመሪያ ላይ በትግራይ በረሃዎች ውስጥ፣ በጎሳ ፖለቲካ እና በመሳሰሉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአሁኖቹ ጉጅሌዎች የተለየ አቋም ይዘው የነበሩ የትግራይ እና ሌሎች ጎሳ ተወላጆችን፣ “… በቴትራ ሳይክሊን ካፕሱል ውስጥ የሳይናይድ መርዝ ሞልተው፣ መድሃኒት አስመስለው ሰጥተው በርካቶችን የገደሉ ሰዎች መሆናቸውን…” ማንበቤ/መስማቴ ትዝ ይለኛል። ህወሃቶች ሰብአዊነት የላቸውም ማለት ብቻውን ጭካኔያቸውን ማሳነስ ይሆናል።

 

ይህ “ህልውና” የሚባል መጽሃፍ “የዘራዊነት መጨረሻው እስከ ቤተሰብ መሰባሰብ ነው…” ይላል። ምሳሌ አደርጎ ያቀረበው ሶማሌን ነው። አንድ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህል ያላቸው ሶማሌዎች፣ እንዲያ አገራቸውን “መንግስት አልባ” አድርገዋት የኖሩት፣ በነገድ እና ጎሳ (የእገሌ ዘር ከእገሌ፣ ማንትስ እገሌን ቢወልድ… በሚል ተሰባስበው እና ተደራጅተው እና ተከፋፍለው) ሲጫረሱ ኖረው፣ መጨረሻ ላይ እስከቤተሰብ ድረስ እንደወረዱ እና አገሪቱን “መንግስት አልባ” እንዳደረጓት ያወሳል። ከሰማንያ በላይ ጎሳ/ነገድ ባለባት እና ቋንቋ በሚነገርባት፣ በርካታ ሃይማኖቶች ባሉባት አገራችን ውስጥ ሊሆን የሚችለውን እያሰቡ ካሁኑ መዘጋጀት እና ጋዜጠኛዋ ርዕዮት እንዳለችው ተባብሮ እና አንድ ላይ ሆኖ “… ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል”–በተቀናጀ እና ሁሉን ጎሳ/ነገድ/ ባካተተ ሁለገብ ትግል።

 

አሊ ጓንጉል

aliguangul@gmail.com

 

[1] እያንዳንዷ [የነገድ “ነጻ አውጪ” ነን ባዮች] የተሰባሰበችው፣ የኔ ዘር ተበደለ፣ ተሰደበ፣ ተበዘበዘ፣ ተናቀ…ዘራችን እንዲህ ሆነ እያሉ…። ዘራችን ተበደለ ሳይል የተሰባሰበ አንድም የዘር ድርጅት የለም። በዚህ ሁሉም አንድ አይነት ናቸው። ከዚህ እንግዲህ ሌላው ዘር በድሎኛል የሚለው ነው። ሁሉም እንዲህ ይላል። ቀጥሎ የኔ ዘር ነው የሚበልጠው ይላሉ። ይህም ሁሉም ጋር ያለ ነው። ጥቂት የተለያዩ የዘር ፓርቲ አፈቀላጤዎችን አነጋግሬ የእነዚህን እውነትነት አረጋግጫለሁ።…አንዱ ስለሱ ዘር ታላቅነት ሲደነፋ፣ አገር የመሰረተ፣ ጥንታዊ ታሪክ የሰራ ዘር ነው ዘሬ ይላል።… ሌላው ደግሞ ይነሳል። እንዴታ፣ ስለዘሩ የቀድሞ ጀግንነት ሌሎቹን እንዴት እንዳራወጣቸው፣ እንደጨፈጨፋቸው፣ የሱ ዘር ሰው እንዴት ሲወለድ ጀምሮ ዲሞክራት ሌሎቹ ግን ከተወለዱ ጀምሮ ጨቋኞች እንደሆኑ ተረቶቹን ይደረድራል። እንደምን ሃብታም የዴሞክራሲ መናኸሪያ የፍትህ አደባባይ የሆነች አገር እንደሚሰራ የተስፋ ማር ወለላውን ምስኪን ህዝብ ላይ ያንጠባጥባል። በተግባር ከድህነት የመውጣት ህልምም የለው። ከቀናው ዲሞክራሲን ለጥይት ያስረክባል። ፍትህን ባደባባይ ያርዳታል። እንደገና የሚገርመው ለዚህም ደጋፊና እርዳታ ሰጪ አይጠፋም። ውጤቱ ግን ያው ጦርነት፣ እልቂት፣ መከራ፣ ረሃብ፣ እናም ድህነት ናቸው። ማን ይጎዳል? ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን። ማን ይጠቀማል? የፖሊቲካ ነጋዴው፣ ህዝቡን ያስጨፈጨፈው የፖለቲካ ነጋዴው።… እኒህ የፖሊቲካ ነጋዴ ያልኳቸውን “የደም ነጋዴ” ማለቱ የበለጠ ይገልጻቸዋል።

 

… ከሩብ ምዕተ አመት በፊት እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ የምናስበው ስለጠቅላላው አገር እድገት እና ስለመላው ህዝብ በነጻነት ሰርቶ መኖር፣ ስለ ዲሞክራሲና ፍትህ መስፈን… ነበር። አሁን ጊዜው በመቶ ዓመታት ስላለፈበት ስለዘርና ዘሮች ሳይናገሩ እነዚያን ጉዳዮች ማንሳቱ የሚረባም አልመሰለኝ። ኢትዮጵያዊ ብቻ በመሆኔ፣ የዘር ፖለቲካ አውራጆች ሲያቀነቅኑ እያዳመጥኩ አለሁ። አዳማጭ ከሆንኩ ተቀባይ እንደማልሆን ግልጽ ነው። በማዳመጤም የአገሬን ህዝብ ስቆቃ እያሰብኩ፣ ታጥቦ ጭቃ በመሆኑ እየተከዝኩ፣ ካስፈለገ የመሳሪያው ሰሪ መሆን የሚገባው ህዝብ መሳሪያ ሊሆን አይገባውም፣ ከሚል መደምደሚያ ጋር ደረስኩ። እናም አውራጆችን የአሳባቸውን ተቃራኒ በማቅረብ እንደምን አንድ ህዝብ እንደሆንን ለመንገር አሰብኩ…”። አንድ ባለ “ትልቅ” ድምጽ አውራጅ፣ በአንድ አጋጣሚ “ለ ‘ሀ’ ህዝብ አንድም እንኳን ጥሩ የሰራ፣ አንድም እንኳ ተበድለዋል ያለ የ ‘ለ’ ዘር ግለሰብ የለም..” በሎ ‘ሲቀድ’ ሰማሁት። እድሉን አላገኘሁም እንጂ “አንተ ውሸታም፣ አንት ሌባ፣ አንት የደም ነጋዴ” ማለት ይገባኝ ነበር። እንደማስረጃም የማቀርበው ‘መሬት ላራሹን’ ነበር። ከጥንስሱ እስከ ፍጻሜው። አሁን ያመጣውን ተረት፣ ‘ዕውነት፣ እርግጥ ነው’ ብሎ ሲተርክ ትናንት የሆነውን የ66ቱን የኢትዮጵያ አብዮት እየካደ መሆኑን እናገር ነበር። የኢትዮጵያ አብዮት የዘር ምልክትም የለው ነበር።…ትከሻ ለትከሻ ተያይዞ የተጓዘ ወንድማማችና እህትማማች፣ ከኢትዮጵያዊነታቸው በስተቀር ምንም ቅጽላቸውን አይተዋወቁም ነበር። ‘የደም ነጋደዴዎች’ በዚያ ጊዜ [የዘር] ማስታወቂያቸውን ቢያቀርቡ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀድዶ ይጥልላቸው ነበር…” (የጸሃፊው ማስታወሻ፦ (አቤት የብስለት እና የሰብዓዊ ሞራሊቲ አስተሳሰብ ልዩነት! የህልውና ደራሲ “[የዘር] ማስታወቂያቸውን ቀድዶ ይጥልላቸው ነበር..” ነው ያለው? “… በሜጫ አንገት አንገቱን …” አላለም) በነገራችን ላይ፣ ልጅ ሆኜ፣ በመሬት ላራሹ አዋጅ ጊዜ፣ አንድ ፊውዳል አምጾ ጫካ ገብቶ ሸፍቶ ሲዋጋ፣ የገበሬ ታጣቂዎች፣ አንገቱን ቆርጠው እንደተመለሱ ሲወራ አስታውሳለሁ። ድርጊቱን አሁን ሳስበው አግባብ እንዳልነበረ ይገባኛል። ይህ የሆነው በ1967/68 ይመስለኛል። ጃዋር ያኔ የተፈጠረ እና በመሬት ላራሹ ማግስት አሁን የሚያራምደውን የዘር እና የሃይማኖት ፖለቲካ ያኔ ቢሞክራት ኖሮ፣ ያደገበት አካባቢ አርሶ አደር ህዝብ ራሱ በሜጫ …።

 

በጣም የሚያሳዝነው ጃዋር ይህን ሁሉ የሚናገረው አሜሪካ አገር ውስጥ ሆኖ ነው። አንዳንዴ የሰዎች የህይወት አላማ (purpose of life) ልዩነት ይገርማል። አቶ በቀለ ገርባ የNPR ሬድዮ ጋዜጠኛ “… አሁን ተመልሰህ ልትሄድ ነው። አትፈራም..?” አይነት ጥያቄ ጠይቆት ነበር። በቀለ…ምን እንደሚጠብቀው እንደማያውቅ፣ ግን ከመሄድ እንደማይቀር ነበር የተናገረው። አቶ በቀለም የኦሮሞ ጎሳን ወክሎ የተደራጀ ነው፣ የትግሉ ፍሬ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ ለሌሎቹ ጎሳ/ነገድ አባል ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ልዕልና ይሆናል ብየ አስባለሁ። በቀለ የሚናገረው እና የሚያደርገው ሁሉ እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ እየደረሰበት ያለውን እስራት፣ ግርፋት፣ ሞትም እንኳን ቢሆን ለመቀበል ቆርጦ ነው ሲሰራ የኖረው እና አሁንም ሊሰራ ነው ተመልሶ የሄደው። እናም ጋዜጠኛው እንደሰጋው ታሰረ። በቀለ አሜሪካ አለመቅረቱ ይጸጽተው ይሆን? አይመስለኝም። በቀለ፣ አንዷለም፣ እስክንድር፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ኤፍሬም ማዴቦ… ወዘተ የመሳሰሉት የህይወት ግባቸው እና እርካታቸው የሚመነጨው፣ ማደረግ የሚፈልጉትን (ለሌሎች ሰዎች ልዕልና እና ሰላም ሲሉ ጭምር) እያደረጉ መኖር እና ካስፈለገም መስዋዕት መሆን ነው። ማህበረሰብን በመልካም ጉኑ መለወጥ የሚችሉት ደግሞ እንደዚህ አይነት ሰዎች ናቸው።

 

ጃዋርም ራሱን ለመስዋዕትነት ባያዘጋጅም፣ ሌሎቹን ለመሰዋት ዝግጁ ነው። የጃዋር “በሜጫ…”) አባባል ሲተነተን “… እስላም ያልሆኑትን በሜጫ አርዳለሁ…” ነው። ጃዋር እና የአይሲስ ወይም አልቃይዳ አጥፍቶ ጠፊ፣ ሌሎችን ሰዎች በሃይማኖት ልዩነት ብቻ መግደል ይፈልጋሉና፣ ሁለቱን ያመሳስላቸዋል። ልዩነታቸው ደግሞ፣ አጥፍቶ ጠፊው ጀነት ውስጥ የሚጠብቀውን የቅንጦት እና ድሎት ኑሮ እያሰበ ሲሆን (አቤት ስግብግብነት! ለራሱ የሰማይ ቤት ደስታ ሲል፣ አንተን ምንም ባላውቅኸው፣ ባልገባህ ጉዳይ፣ “ራንደምሊ”፣ በተገኘህበት ይገድልሃል፣ ጀነት የሚያስገባው ከሆነ ደግሞ፣ ከገዛ አገሩ ተርቦ፣ ሰላም እና ደስታ አጥቶ ተሰዶ የመጣ መሆኑ ሁሉ ግድ ሳይለው፣ እጅ እግርህን አስሮ ያርድሃል (አይሲስ እንዳረዳቸው ሰላሳዎቹ ኢትዮጵያዊያን)፤ ጃዋር ደግሞ ደስታን የሚያገኛት እዚሁ ምድር ላይ ነው፤ ያውም አሜሪካ። የ”ህልውና” ደራሲ “የፖለቲካ/የደም ነጋዴ!” ያለውን አይነት ይሆን? ይኼ ሰው የሚመራው ድርጅት አለ ይመስለኛል። በአሜሪካ አገር በ“አትራፊ ያልሆነ ድርጅትነት” የተመዘገበ ድርጅት። ምን ችግር አለ! በየአመቱ የአሜሪካ መንግስት፣ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ናቸው ተብሎ እስከታመነበት ድረስ በ“ሰብዓዊ/ኮሚኒቲ ደቨሎፕመንት” ድርጅትነት ስም ገንዘብ ይሰጣል። አሜሪካም ባይሰጥ፣ የትግራይ ጉጅሌውን አላማ፣ በሃይማኖትም ሆነ በጎሳ ፖለቲካ የመከፋፈሉን ዋና ስራ፣ ጃዋር እየሰራለት ሊሆን ይችላል እና፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፣ ጉጅሌው ገንዘብ ቢሰጥ አይገርመኝም። Something smells really bad about this guy’s personality!)። በጣም የገረመኝ በ“ሜጫ…” ንግግሩ ጉዳይ የሰጠው ማስተባበያ ነው። “…ሳይኮ አናሊሲስ እንትን ነው ያለው…ሜጫ ምንድነው?… እኛጋ ኦሮሞ ውስጥ ከሰው የማይለዩ እቃዎች አሉ። ለፋርሚንግ የምትጠቀምባቸው፣ … ለአደጋ የምትከላከልባቸው። …ከተነካ ህዝቡ ይነሳብሃል…” “…ሜጫ ማለት እኛ ጋር ቡጢ እንደ ማለት ነው…” ነበር ያለው። ጉጅሌው ኢትዮጵያዊያንን በመከፋፈል እና እርስ በርስ በማባላት ረገድ ተራቅቆበታልና፣ ለኦሮሞ ነገድ ቆሜያለሁ የሚል ሁሉ እና የኦሮሞ ልሂቃን፣ ከዚህ ሰው ጀርባ ያለውን ማንነት ቢከታተሉ መልካም ይመስለኛል።  የሚገርመው ነገር፣ ኢሳትም ሆነ ኦኤምኤን፣ የሜጫውን ጉዳይ ባደባባይ ይቅርታ ሳይጠይቅ (እኔ ባላየሁት እና ባልሰማሁት ሜዲያ ጠይቆ የነበረ ከሆነ እኔ ራሴ ይቅርታ እየጠየቅሁ)፣ ዛሬም ጃዋርን በየሜዲያው ጊዜ እየሰጡ ያቀርቡታል።

[2] “… የምጣኔ ሃብት ሊቃውንት …. ብሄርን የሚሰራው ካፒታሊዝም ነው፣ እንዴት ቢሉ ሰዎች ለስራ ብለው ጉልበታቸውን ለመሸጥ ብለው ከየትውልዶቻቸው ቀየዎች ወደ ሌሎች ስፍራዎች እየሄዱ እየሰፈሩ… ከሌሎች ቦታዎች ከመጡት በመገናኘት እየተወዳጁ፣ አብረው እየኖሩ… እየተዋለዱ እንዲያ እንዲያ …ከቀድሞ የሰፋ አድማስጋ ይደርሳሉ። አዲስ ብሄር ይፈጥራሉ… ደርጉ ሊመጣ፣ ጃንሆይ ኃይለ ስላሴ ሊወርዱ ግድም ከላይ የጠቀስኩት ዓይነት ብሄር ጥንሥስ፣ ኢትዮጵያዊ የሚል ብሄር ሽል ተፈጥሮ ነበር።… ‘ኩሩው’ የኢትዮጵያ ልጅ እያንዳንዱን ጎሳ፣ ነገድ ወዘተ …ብሄር (nation)  ብሎ ሲል፣ ‘ልክ አይደለህም’ ብሎ ሊሞግት የተነሳ ያለ አይመስለኝም። ‘የእገሌ ብሔር “ሀ” ነው። ምክንያቱም እገሌን ቢወልድ እገሌ፣ እገሌም የእገሌ ልጅ…” … እንዲህ ነው የግለሰብ “ብሔር” ትንተና ሲደረግ የምንሰማ። በርግጥ ግን በደም ዝምድና ላይ የተመሰረተ የህብረተሰብ ስብስብ ዘር፣ ጎሳ፣ ነገድ ይሆን እንደሁ እንጂ ብሔር (nation) አይደለም። … አሁን እስቲ በኢትዮጵያ የትኛው ዘር ወይ ነገድ ነው ከሌላው የሚበልጥ? በመጀመሪያ የተደበላለቅን ነን። ሁላችን ምስኪኖች ነን። ሁላችን የመኖራችን ጉዳይ ከሚያጠያይቅ ደረጃ የደረሰ አሳዛኝ ሰዎች ነን። ያለንበት ጊዜ ችግር (ይህ መጽሃፍ የተጻፈው በ1992 ነው)፣ ያለንበት ሁኔታ፣ የተገፋንበት ማጥ፣ እንኳን ተለያይተን አንድ ሆነንም ከተወጣነው ታላቅ ነገር ነው። (ህልውና፡ ገጽ 92፣ ሰለሞን ይርጋ)።

The post “…የተገፋንበት ማጥ፣ እንኳን ተለያይተን አንድ ሆነንም ከተወጣነው ታላቅ ነገር ነው” appeared first on Medrek.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles