ይህን የጀግና ስም ጠቅሼ ክታቤን ስከትብ በደደቢቶቹ ሹመኞች የግል መገኛ( መገናኛ አይደለማ) የቴሌቪዥን ጣቢያቸው አንድ ሰሞን ኢሳትን ሳይቀር እስኪያደናግር ድረስ ነጋሪት ተጎሽሞለት፤ መለከት ተነፍቶለት እና በፉቹሪዝም ፍልስፍና ቀመር አዲስ ገጸ -ባህሪ ተቀርፆለት በአየር ላይ ስለተንቆለጳጰሰው የወያኔ ምርኮኛ አይደለም፤ ምን ማለቴ ነው የስም መደለዥያ ስለሆነው ውልንፍጥ የወያኔ ታሪክ ሳይሆን ስለእውነተኛው አሞራው ነው። አሞራው ውብነህ ተሰማ(ራስ)!።
ነውጠኞቹ የዘመኑ ገዥዎቻችን በዘመን መካከል ከተዘገቡ መንግስቶቻችን ጋር ማወዳደር ቂል ያሰኛል። አነሳሳቸው ፤ አካሄዳቸው እና አደራረሳቸው( ?) ዘውጉ ሌላ ነውና ። እነርሱ በጭካኔያቸውና በውሸታቸው ፋሽዝምንም አፓርታይድንም ሲልቅም ዲያብሎስን ያስናቁ የሴዖል ጀግኖች ናቸውና ከማን ጋር እናመሳስላቸው?። እንደእኔ እምነት የክፋታቸውን ከፍታ እና ጥልቀት ሰውኛው ቋንቋ ሊገልጠው አቅም ያጥረዋል። ለዚህ ጽሁፌ ማጣቀሻ ይሆነኝ ዘንድ ግን አንድ ወቅት የጣሊያንን ህዝብ በአውሎ እንደተመታች ጀልባ ያናወጠውን የፉቹሪዝምን ዕንቅስቃሴ ላነሳው ወደድኩ።
ፉቹሪዝም በጣሊያናዊው ፊሊፖ ቶማሶ ማሪያንቲ ( Filipo Thomaso Marinetti) የተጀመረ የነውጥ ጽንሰ-ሃሳብ ሲሆን ትርጉሙም “ዘመቻ ጥፋት በታሪክ እና በባህል ላይ” ማለት ነው (ትርጉም የራሴ)። ማሪያንቲ ዕንቅስቃሴውን ያዳቀለው አናርኪዝምንና ፋሽዝምን አዋስቦ ነው። ማኒፌስቶው የሚያተኩረውም ነባር ባህል፤ ታሪክ እና ዕውቀቶችን እንዳይመለሱ አድርጎ መናድ ላይ ነው። ምሳሌ መፃሕፍት ቤት፤ ሙዚየሞች፤ የዕውቀት ተቋማት ሁሉ አያስፈልጉም በሚል የተጠናገረ አስተምህሮ የታጨቀ ግሳንግስ ነው። የጣሊያን ህዝብ በነውጠኞቹና በዱሩጌዎቹ በደረሰበት ናዳ ታሪኩና ባህሉ ፊቱ ላይ ሲፈረካከሱ ሲመለከት ለጊዜው ምንም ማድረግ እንኳን ባይችልም “ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሰብራል እንዲሉ” ሁሉም ግን በደረሰበት ሃዘን ብሶቱን እንደፍም እሳት በየቤቱ ይዞት ተቀምጧል። ነውጠኞቹ አንዳንድ በህዝቡ ልብ ውስጥ አልፋቅ ብለው ያስቸገሯቸውን ሃገራዊ ዕሴቶች ውልንፍጥ ምስሎችን በማቆም የማይሽረውን ይልቁንም የሚያመረቅዘውን የህዝቡን ቁስል ለማከክ ሞካክረዋል። እንደኛው የባንዴራ ቀን እንዲሁም ለዚህ ጽሁፌ መነሻ የሆነኝን የአሞራው ማንነትን እንደምሳሌነት ይጠቅሷል። የፉቹሪዝምን ማኒፌስቶ ከተጠቀሙበት መሃከል ሂትለርና ስታሊን ዋነኞቹ ሲሆኑ የሞሶሎኒ የስልጣን ዘመኑ መሰረትም ይሄው ማኒፌስቶ ነበር። የእኛዎቹም ምስኪኖች በአቅም ድንክዬነት ምክኒያት በአናታቸው ላይ ዘጭ ያለውን እንግዳ እና ሽብልቅ ነገር እየጓጎጡ የመጠጡትን መርዛማ ውሃ ዛሬ ህዝቡ ላይ ሲይስመልሱት ብናይ ልንደነቅ አይገባም አቅማቸው እዚህ ላይ ነዋ ተሸክሞ ካወጣቸው ህዝብ ላይ መጨፈር!። የእንቅስቃሴው የጥፋት ምዕራፍ አኃዙ ሰፊ በመሆኑ በዚሁ ልዝጋውና የባለ ታሪኩን የአሞራውን ታሪክ በማሪያንቲ ያልሰከነ ዛር ተለክፈው ወደ ደለዙበት! ዋናው ሃሳቤ ልመለስ።
ጀግናው ራስ ውብነህ ተሰማ በጎንደር ክ/ሃገር በወገራ አውራጃ ቆላ መረባ በ1884 ተወልደው በአካባቢው ባህልና እምነት መሰረት ተኮትኩተው ያደጉና በኢትዮጵያዊነት ተጠምቀው ለኢትዮጵያውያን የኖሩ ስመ፟-ጥር ጀግና ናቸው። ‘አሞራው’ የሚለውን ስያሜ ያገኙትም በፈጠራ የእውሸት ድርሰት ተጀቡነው ሳይሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ በፋሺስት ወረራ ስር በወደቀችበት በዚያ የጭንቅ ጊዜ እንደወርቅ በእቶን ውስጥ በዕውነት አልፈው ነው። ይህ ማንነታቸው ነው በትውልድ መካከል ሰብሮ የመግባት ብቃት ያጎናጸፋቸው!። ይህ ማንነታቸው ነው እኔም በውስጤ ለጸነስኩት ተውኔት እንዳጫቸው ያደረገኝ!። የእኒህ ጀግና፤ አስተዋይ፤ ጥበበኛና የራሳቸው የሆነ ፍልስፍና የነበራቸው እንደስማቸው ውብ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ለፃፍኩት ሙዚቃዊ ተውኔትም በመሪ ገጸ-ባህሪነት እንደምሰሶ አገለገለኝ።
ተውኔቱን የፃፍኩት ከ1997ቱ ምርጫ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ ነበር። ተውኔቱን ያዘጋጀሁበት ዓቢይ ምክኒያትም በወቅቱ ለተከታታይ ወራት በሬዲዮ ፋና በሚተላለፍ ፕሮግራም የአባቶችን የጀግንነት ታሪክ የማጠልሸት ስራ በሰፊው እየተሰራ ስለነበር ነው። የሬድዮው ዘመቻም ቅስትም ታሪክ የጀመረው ዛሬ ነው ዓይነት ነገር ልክ እንደ ማሪያኒቲ ፍልስፍና የደንበር አልባውን አፄ ትዕቢትን ወናፍ በማናፋት ነበር። ጋዜጠኛ የተባሉቱም ያለምንም መሸማቀቅ ሰንካላውን የውንብድና ፍልስፍና በሰንካላ ቃላት ይቸፈችፉት ይሸፈሽፉት ይዘዋል። የተፈጥሮን ህግ ባለማስተዋል የጨለመው እንደሚነጋ፤ ክረምቱ በበጋ እንደሚተካ፤ ዘመን አልፎ አዲስ ዘመን እንደሚመጣ በመዘንጋት ብሎም እግዚአብሄር የሚባል ፃድቅ ፈራጅ እና እውነተኛ ዳኛ እንዳለ በመርሳት ማለት ነው። በዘመን መካከል በፍርድ የሚገለጥ ዕውነተኛ አምላክ አለና አንሳት።
በዚህ ወቅት ነበር ተውኔቱን ጽፌ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲአትር ያቀረብኩት። ተውኔቱ ለቲአትር ቤቱ የሚመጥን ነው በሚል ለመድረክ ለማቅረብ እንደወሰነ የሚገልጥ ደብዳቤ ከቲአትር ቤቱ ይደርሰኛል። ይሁን እንጅ ቲአትር ቤቱ ተውኔቱን ለማቅረብ ሲታመስ፤ በማይታይ ስውር እጅ ከኋላ ሲጎተት አስተውልኩና ካንድ ዓመት ጥበቃ በኋላ ሙዚቃዊ ድራማውን በግል ለማዘጋጀት ወስኜ ስራውን ጀመርኩት። እርግጥ ነው ሁለት ስዓት ተኩል የሚወስድን ሙዚቃዊ ድራማ በግል ለማዘጋጀት መሞከር ለሙያው ከሚያስፈልጉት ግብዓቶች ሌላ የሚጠይቀው የገንዘብ ዓቅምም ሲታሰብ እንደእብድ ሊያስቆጥር ይችላል ይሁን እንጅ ስራው ቀጠለ። ለመንፈሴ ጥንካሬ የሰጠኝም አባቶቼ በአረር ውስጥ አልፈው ወድቀውና ተዋድቀው ለሰሩት አኩሪ ገድል እኔ ከተማ ለከተማ እያንዛረጥኩ እንዴ ታሪካቸውን እንኳን አልጽፍ? እናም በህሊናዬ ኮርኳሪነት የዝግጅቱን ስራ ተያያዝኩት። ተውኔቱ ከዝግጅት ጊዜው ለመድረክ እስከበቃበት ከዚያም ለመድረክ ከቀረበም በኋላ በገዥው ኃይላት የተደረገው ዘመቻ ራሱን የቻለ ተውኔት ወይም ሲኒማ ይወጣዋልና በዚህች አነስተኛ ጽሁፌ ለመንካት አልሞክርም አዲሱ የአሞራው(የወያኔው ምርኮ) የመደለዣ ታሪክም የዘመቻው አንዱ አካል ነው።
ተውኔቱ ከአንድ ዓመት የዝግጅት ጊዜ በኋላ ወያኔ ካሰማራቸው ሃይላት ጋር ትንቅንቁ ቀጥሎ 1998 ግንቦት 19 ቀን በሃገር ፍቅር ቲአትር ተመረቀ። በዚህ አጋጣሚ በጊዜው የሃገር ፍቅር ቲአትር ዋና ስራ አስኪያጅ ለነበረችው ለአርቲስት መንበረ ታደሰ፤ ለገምጋሚው ቡድንና ለመላው የቲአትር ቤቱ ሰራተኞች አክብሮቴ እጅግ የላቀ ነው። በተለይም የገምጋሚው ቡድን አባላት ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው እያወቁ ለህዝብ መቅረብ እንዳለበት ወሰኑ። ዋጋም ከፈሉ ታሪክ ግን ስራው ነውና እየዘገበ ያልፋል በጊዜውም አስውቦ ይገልጠዋል። አንዳንድ ጊዜ የኪነ፟-ጥበቡ ሰዎች ምን ሰሩ? የሚል የጅምላ ፍረጃ በኢሳት ቴሌቭዥን ሲተላለፍ ሰምቻለሁና ቢስተካከል መልካም ነው እላለሁ። ምክኒያቱም የሃገራቸው እና የሙያቸው ዚቅ መውረድ ውስጣቸውን የቁጭት ረመጥ የሚለበልባቸው አያሌ ናቸውና የጅምላ ፍረጃው የቁስላቸውን ጥዝጣዜ ያብሰዋልና ጥንቃቄ ይደረግ ነው ምክሬ።
በወቅቱ ተውኔቱ ሲመረቅ በክብር እንግድነት የተጋበዙትም ሰፊውና ተምሳሌተ ብዙው ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ ነበሩ እዚህ ላይ ነጥብ ይያዙልኝ!!። የኢህአዲግ አባሎቹና የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ሹሞች አኮረፉ ተቆጡም። እኛ እያለን ነዋ!። በጊዜው በእኔ መመዘኛ ሚዛን ደፍተው የተገኙት አንጋፋውና ተፈትነው የወጡት ጄኔራል ጃጋማ ናቸው። ተውኔቱ ሲመረቅ አስተያየት ከሰጡ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የጥቂቶችን ልጥቀስ።
“ያቀረብክልን ቲአትር ከአንቀላፋንበት የሚያነቃንና ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊነታችንን አደመቅከው…..” ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ።
“ራስ አሞራውን አውቃቸዋለሁ ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነበሩ በዚህ ባለንበት ጊዜ ሆነን የአባቶቻችንን ስራ ስንመለከት ደግሞ የተለየ ትርጉም አለው። ባጭሩ ያባቶችን ስራ ለአዲሱ ትውልድ በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ስራ ተሰርቷል።” የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ።
“ጸጋዬ ሞተ ብዬ አዘንኩ ለምን? ደፋር ጸሃፊዎች አይኖሩንም ብዬ ይህን ተውኔት ስመለከት ግን አሁን ጸጋዬ ቢሞት አይቆጭኝም ለካስ ተተኪ ትውልድ ማስነሳት ችለናል ብዬ ተደሰትኩ..” አርቲስትና ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ
“በተለይማ መዝጊያው መዝሙር የኢትዩጵያ ህዝብ መዝሙር ቢሆን ብዬ ተመኘሁ…” ጸሓፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት
“ለካስ ኢትዮጵያዊነት አልሞተም እኔም በአንተና አብረውኽ በሚሰሩት አርቲስቶች ኮራሁ.” ድምፃዊ ታምራት ሞላ
ከላይ ለመጥቀስ እንድሞከርኩት ከብዙዎች አስተያየቶች ጥቂቶቹን ነበር ለመግለጥ የሞከርኩት ተጨማሪ ከፈለጉ ይህንን ሊንክ ይጫኑ https://www.youtube.com rddQ2lgSc5U /watch?v=
በተውኔቱ አሞራው ውብነህ መሪ ገጸ ባህሪ ይኑራቸው እንጅ ራስ አበበ አረጋይ( ኦሮሞና አማራ) ፤ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፤ (ኦሮሞ) ሻቃ በቀለ ወያ(ኦሮሞና ጉራጌ)፤ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ(አማራ)፤ ደጃዝማች ዓባይ ካሳ(ትግራይ)፤ደጃዝማች ዑመር ሰመተር (ሱማሊ) እነኝህ ገጸ ባህሪያትም በተውኔቱ ውስጥ በኢትዩጵያዊነት መንፈስ ሲንጎማለሉ ማየት ተውኔቱን ልዩ ሞገስ ያላበሰ ትዕይንት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም አያሌ ጀግኖች በተውኔቱ ይወደሳሉ።
አሞራው ውብነህ የግላቸው ፍልስፍናዎች ነበሩዋቸው ስለነፃነት ሲናገሩ “ተዋርዶ ከመኖር ሞት ይሻላል” ይላሉ። ስለጀግንነት ሲናገሩ ደግሞ የጀግንነት ግቡ ከባላንጣ ጋር ታግሎ ማሸነፍ እንጅ መግደል አይደለም ጠላትህ በእጅህ ላይ ሲወድቅ አክብረህ ያዘው” ብለው ይመክራሉ ሲያክሉም በእጅህ የወደቀውን ጠላትህን ወደ ምር ወዳጅነት ያመጣኸው እንደሆነ ያንተ ጀግንነት ይን ጊዜ ፀና ማለት ነው። እነኝህ የህይወት መርሆዎቻቸው ናቸው። ተውኔቱ ሲጀምር አሞራው መድረክ ላይ ለህዝብ ንግግር በማድረግ ላይ እንዳሉ ነው። ከተውኔቱ እንደወረድ ልጥቀስ “ሃገሬ መቼም በዚህ ዘመን የገጠመን ፈተና ይሄ ነው አይባልም ወራሪው ጠላት ክብራችንን ሃይማኖታችንንና ሃገራችንን ለማፍረስ ነው አመጣጡ። ይሁን እንጅ እሱ እንዳሰበው ግን አልሆነለትም። የሃገሬ ህዝብ በስተስሜን በስተደቡብ በስተም ዕራብ በአንድ ቆሞ የሶልዳቶውን ጦር እያስጨነቀው ይገኛል። ለዚህም ተሽዋ እነአበበ አረጋይ፤ ተኦሮሞ እነገረሱ ዱኪ፤ በሶዶ እነበቀለ ወያ ፤ እነ ዑመር ሰመተር ተሱማሊ እረ ስንቱን ( ሁሉንም ጀግኖች በየተራ እየጠሩ ይቀጥላሉ) ….ዛሬ ልነግርህ የፈለግሁት ተዚህ በፊት በአድዋ ዘመቻ ጊዜ በአባቶቻችን ጀግንነት ድል በመነሳቱ ዛሬም በኛ ዘመን አልሆንልህ ቢለው አንዲት መርዝ ነገር ይዞ መጥቶአልና ይህችን መርዝ ነገር እንዳትቀበል ልነግርህ ነውና አድምጠኝ። (ሃገሬው ባንድ ላይ ) ምንድነው እሳ አያ? አሞራው ይቀጥላሉ.. ይኸውም ምንድነው ያልከኝ እንደሆነ? ሶልዳቶው ጦርነት አልሳካልህ ቢለው ወንድም ተወንደሙ ፤ወገንን ተወገኑ ሊያፋጅ ትግሬን በሃማሴን ፤ኦሮሞውን በአማራ ላይ ፤አፋሩን በኢሳው ላይ ከንባታውን በወላይታው ላይ እርስ በርስ የሚያጋጭ ሴራ ይዞ መጥቶአልና ይሄን ሴራ አጠብቀህ እንድትጠብቅ ልነግርህ ነው አመጣጤ። እረ ይገርማል እኮ እናንተ ሌላው ቀርቶ በአማራ እና በቅማንት መሃል እንኳን ሲገባ? እናማ ንቃ በእንቃሽቱ ማርያም ይዥሃለሁ በወገንህ ላይ አንዲት ጥይት ትተኩስና ውርድ ከራሴ (ሃገሬው አሁንም በአንድ ድምጽ ) አንቀበልም! ይላል…….
ሃገሬ ተዚህ በፊት ወደ ሽዋ ዘልቄ እንደነበር ነግሬሃለሁ ዛዲያ አንድ አባ ዶዮ ( የጄኔራል ጃጋማ ኬሎ አጎት) የሚባሉ የኦሮሞ መኳንንት አግኝቼ ነበር። እኒህ መኳንንት ምን እንዳሉኝ ልብ ብለህ አድምጠኝማ አንድ የጥልያን ጂኒናር ወደ ቤታቸው ይሄድና እርሶ ኦሮሞ ነዎት የኦሮሞን ግዛት ይያዙና ይግዙ ከአማራው ፤ከትግሬው ጋራ ምን አለዎት? ለዚህ ደግሞ የጥልያን መንግስት ገንዘብና የጦር መሳሪያ ያቀርባል ይላቸዋል። እርሳቸውም መልሰው አይ አንተ አስበህበት እንደመጣህ እኔም አስቤ እስክመልስልህ ቀን ስጠኛ ይሉታል። ቀን ቆርጠው ይለያያሉ በተቀጠረው ቀን ጂኒናሩ አጃቢዎቹን አስከትሎ ሲመጣ እርሳቸውም እንደሳቸው ያሉ የኦሮሞ መኳንንት ይይዙና አንድ አራት ማድጋ ያህል ጤፍ ተጄንዴው (የከብት ቁርበት) ለቀው ይተውትና ጠበቁታ ጂኒናሩም እንዴት ነው አሰቡበት ይላቸዋል እርሳቸውም አዎ አስቤበታለሁ ዛዲያ ግና የአንተን ጥያቄ የምመልስልህ አንተ የእኔን ጥያቄ የመለስክ እንደሆን ነው ይሉታል እርሱም ምንድነው ይላቸዋል በል ይህን ጤፍ ቀዩን በቀዩ ነጩ በነጩ አርገህ ለይልኝ ይሉታል ያ ሶልዳቶማ ምን ጎፍቶ ብድግ ይልና ይህ እንዴት ይሆናል ? ይላቸዋል እርሳቸውም አየህ ይህን ጤፍ መለየት እንደማይቻል የኢትዩጵያን ህዝብም እንዲሁ መለየት አይቻልም ብለው አሳፈሩታ……..” ተውኔቱ ይቀጥላል።
አባቶቻችን ይህቺን ሃገር ያቆዩአት እንዲህ በጠለቅ አስተዋይነት፤ በረጅም ዘመን በዳጎሰ ባህል እና ፈሪሃ እግዚአብሄር በገሰጠው በተገኘ መቻቻል ነው። የፕሌቶን አባባል እዚህ ላይ ልጠቀም “ ከመቶ ሰዎች መካከል አንድ ጀግና ማግኘት ይቻላል፤ ከሺህ ሰዎች መካከልም አንድ ጥበበኛ ማግኘት ይቻል ይሆናል ወደፍጹማና የመጣ ግን ከመቶ ሺሆች አንድ ማግኘት ይችግራል…” እስኪ እያንዳንዳችን በዚህ መመዘኛ ስር ራሳችንን እንይ የት ነን? በዘመናቸንስ በዚህ መመዘኛ ራሱን ተመልክቶ በልበ ሙሉነት እኔ አለሁ የሚለን እናገኝ ይሆን? በአባቶቻችን ዘመን ግን ነበሩን። በጀግንነቱም በጥበበኝነቱም ወደ ፍጹምነት በመገስገሱም ቢሆን ነበሩን። ያለፈውን ናፋቂ ሆኜ ትውልዴን ወቃሺ ለመሆንም አይደለም ደግሞም ለእየራሳችን ከሰጠነው የቅል ምዘና ገልቱነት አንጻርም ምናልባት ሊያሟግተንም ይችላል። ታላላቅ የትምህርት ተቋማትን ደጆች ረጋግጠናላ!። ካስተዋልን ግን ለእኛ ለኢትዩጵያውያን “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ነው የሆነብን ከዚያም ሲያልፍ የነፍስ እብጠት አመጣብን እንጅ ለህዝባችንም ሆነ ለምድራችን የገሰጠርነው ብስ የፈነገልነው መርገም የለም። ነፍሱን ይማረውና መምህር ሙሉጌታ ሉሌ አንድ ወቅት ላይ “ማዕማር ማዕምራን” በሚል ርዕስ ስር ሊህቃን እነማን ናቸው? ለሚል ቆንጣጭ ጥያቄ መልስ ለመስጠት በዘረዘረው ማዕማር ነፍስን አንዝሮና አንዘራዝሮ በቦታዋ የሚያስቀምጥ ድንቅ ጥሁፍ በጦቢያ ላይ አስነብቦናል።
አሞራውና ቅማንት
ለእኔ አሞራው ውብነህ በፕሌቶ መመዘኛ መሰረት አብዛኛውን ደፍነውታል ባይ ነኝ። ለምን ይህን እንዳልኩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ላስቀምጥ። ዛሬ በጎንደር የተነሱ ሁለት መሰረታዊና ሴራዊ ጥያቄዎች በገዥዎቻችን አባቶች(ጥልያኖች) በኩል በጥል ማቀጣጠያነት ተነስተው ነበር ጣሊያን ጎንደር ሲገባ መጀመሪያ ያደረገው የቅማንትንና የይሁዲውን ማህበረሰብ በአማራው ላይ በማስነሳት ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲጫረስ ለማድረግ ነበር። ይሁን እንጅ አሞራው ውብነህ ጠላትን በጀግንነት ብቻ ሳይሆን በጥበብም አልፈውት ተገኙና በወንድማማቾች መሃከል አንዲትም ጥይት እንኳን ሳትተኮስ ከወገኖቻቸው ጋር በመሆን ወራሪው ያውጠነጠነውን ሴራ አክሽፈውታል ለዚህም ነው በፕሌቶ መመዘኛ አባቶቻችን ልቀውናል ያልኩት። ከቅማንት በኩል ቀኛዥማች አያናዬ ከይሁዲው ማህበረሰብ የተከበሩ አቶ ዮና ቦጋለ ተጠቃሽ ጀግኖች ናቸው። ለዚህ ነው አሞራው በፈላስፋው መመዘኛ ሚዛን የደፉብኝ። እኒህን ጀግና ነው በአዲሱ የወያኔው አሞራው መደለዝ መተካት የተፈለገው!።
በአማራውና በቅማንቱ ማህበረሰብ መሃከል ያለውን አብሮነት እንዴት ላሳያችሁ ይሆን? አይከል፤ ሰራባ፤ጮንጮቅ፤ተንከል፤ ብሆና፤ገለድባ ከዚያም ወደ አርማጭሆ ግቡ ህዝቡ ከፍቅሩ የተነሳ በስማቸሁ አይጠራችሁም የፍቅር ቅጽል ስም ያወጣላችኋል። ታዋቂው ድምጻዊ ይርጋ ዱባለ የሚያቀነቅነው “አንጓባ አንጓባ አንጓባ ተሻገረች ጋባ” የሚለው ታዋቂ ዜማ የቅማንት ብሄረሰብ ዘፈን ነው። ይህ ዘፈን ሰርግ ላይ ሲወርድ ማን ነው? ቅማንት ማን ነው አማራ? መለየት አይቻልም። ዛሬ የዞረባቸው ዕብዶች በረቀቀ ሴራ ቅማንትን ወደ ትግራይ ለማዞር መዳዳታቸው “አንጓባን” ክቅማንቱ ጋር እንዴት ሊዘፍኑት ይሆን? ለነገሩ ምን ችግር አለው ብቻ ወደ እነርሱ የመጠቅለሉን ስራ ይፈጽሙት እንጅ ልክ እንደ ጠገዴ ህዝብ መከራውን እንዳበዙት ቅማንትንም ባህሉንም ይደፈጥጡታል አብሮ አደጌ የቅማንት ህዝብ ሆይ ንቃ። በዚህ በኩል የተከበሩ ፕሮፌሰር ማለደ ማሩ፤ አምባሳደር ዘመነ ካሰኝ፤ አቶ ነጋ ጌጡ በአካማቻችሁት ዕውቀትና በማህረሰቡ ባላችሁ ተደማጭነት በኩል አልፋችሁ ነገ ማለፍ አይቀርምና ታሪካችሁን እንደ አሞራው ውብነህ በወርቅ ብዕር ጽፋችሁ እለፉ!።
አሞራውና የኢትዩጵያ ድንበር በሱዳን በኩል
አንድ ጊዜ ራስ አሞራው በተገኙበት በንጉሱ የዘውድ አማካሪዎች ስብሰባ ላይ የጅቡቲ ጉዳይ ይነሳል። ንጉሱ ሰው ሁሉ ሃሳብ ከሰጠ በኋላ ራስ አሞራውን አንተስ ምን ትላለህ? ብለው ይጠይቋቸዋል አሞራውም ስለጅቡቲ ከእናንተ የተሻለ ዕውቀት ስለሌለኝ የምትሉኝን ማድመጥ ነው እኔን ስለሱዳንና የኢትዩጵያ ድንበር ብትጠይቁኝ የት ላይ እንደሆነ እነግራችኋለሁ በዚያ አካባቢ እንኳን የሃገሬን ድንበር የዛፉን ቁጥርና ስሙን አውቀዋለሁ አሏቸው። የልጆቻቸውን ስም እንኳን እንዴት እንደሰየሙ ተመልከቱ። አቶ አግባው ውብነህ ( ከኃ/ስላሴ ወደ ሃገር ተመልሶ መግባት ጋር ተያይዞ የተሰየመ) ፤ ወይዘሮ ጋዳሪፍ ውብነህ (የድንበራችን ማህተም)፤ ወይዘሮ ኢትዩጵያ ውብነህ( ኢትዩጵያዊነት)!። ጠረናቸውን አሽትቱት የኢትዩጵያዊነት ማዕዛ ያውዳችኋል። ስለ ኢትዩጵያዊነት ማዕዛ ከተነሳ እዚህ ላይ ሰለ ተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜተር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ትንሽ ልበል። አንድ ጊዜ እቤታችው እኔን ታናሹን ሰው ራት ይጋብዙኝና እሄዳለሁ ባየሁት ነገር ግን ተደመምኩ እሳቸው ቤት ራት ተጋበዙ ማለት ምግብ መብላት ብቻ ማለት እንዳልሆነ ይገነዘባሉ። ኢትዩጵያን በኤደን ገነት ውስጥ ማየትና እና ማዕዛዋን መጥገብ ነው ስለእኒህ ዕንቁ ኢትዩጵያዊ በግሌ ያጫወቱኝንና ያየሁትን አንድ ቀን አንድ ነገር እላለሁ። አንዳንድ ሰዎችን እንዲሁ ጠጋ ስትሏቸው የኢትዩጵያዊነት ማዕዛ እንደቤተክርስቲያን ዕጣን ያውዳችኋል እውነተኛው አሞራው እንዲህ ናቸው የምርኮን ታሪክ ገልብጦ በመጻፍ የጀግናው የአሞራውን የገዘፈ ታሪክ ማክሰም አይቻልም። ወያኔ ኢህአዴግ የአሞራው ውብነህን ታሪክ መስማት አይፈልግም ምክኒያቱም ለኢትዩጵያዊነት እና ጎንደርን ሰሞኑን ስለሚያውኳት ዓቢይ ሴራዎች አሞራው ውብነህ ከወርቅ የነጠሩ ቋሚ ምስክር እና መልስም ናቸውና። የአሞራው ስም በወያኔ ሰፈር ተነሳ ማለት በአጋንንት ሰፈር የኢየሱስ ስም ተጠራ ማለት ነው። ለዚህም ነው አንድ ወቅት አንድስ እውነት እንኳን ሳንሰማበት ለሃያ አራት ዓመት ሙሉ ቃና እንደሌለው ቆርቆሮ የሚጮኽውና በደደቢቶቹ ሹሞች የሚዘወረው የገዥዎቻችን ቴሌቪዥን ጣቢያ አንድ ጎልዳማና ውልንፍጥ ታሪክ ይዞ “አሞራው” በሚል ዘጋቢ ፊልም አቅርቦ ለመውተርተር የሞከርው። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ተውኔቱን ከዝግጅት ለህዝብ እስከ ቀረበበት ድረስ የነበረው ትንቅንቅ ሌላ ራሱን የቻለ ሙቪ ይወጣዋል ያልኳችሁም ለዚሁ ነው። የስደቴ ምክኒያትም ይኼው ነው!።
አሞራውና ገረሱ ዱኪ
ሃገር ከወራሪው ነፃ ከወጣችና እንደ ሃገር ከቀጠለች በኋላ የራስ አሞራው ውብነህና የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ግንኙነት በጠነከረ ወዳጅነት ላይ ተመስርቶ ከፍቅራቸው የተነሳ ገረሱ አንዱን ልጃቸውን ውብነህ ብለው እንደሰየሙት አንድ በዕውቀትም በዕድሜም የበሰሉ ኦሮሞ ኢትዩጵያዊ አጫውተውኛል። የሁለቱን አርበኞች የአብሮነት ዘመንም ወደፊት በሰፊው እመጣበታለሁ። ነገርን ነገር ያነሳዋልና አቶ ዋቅጋሪ ጁጌሳ የሚባሉ የጓደኛዬ አባት ጎንደር ለብዙ ዘመን ይኖሩ ነበር በእነዚህ ዓመታት ጭልጋ፤ ዳባት እየተዘዋወሩ ሰርተዋል ከዚያም ጦሮታ ሲወጡ ከጎንደር አዘዞ መግቢያ ላይ ቤት ሰርተው መኖር ጀመሩ። በመሃል ዘረኛው ወያኔ ሲገባ በተደረገባቸው የስነ-ልቦና ጫና ቤታቸውን ሽጠው ዝዋይ ወደ ዘመዶቻቸው ሃገር ይሄዳሉ ትንሽ ህመም እየጀመራቸው ሲመጣ ለቤተሰቦቻቸው አንድ የአደራ ኑዛዜ ይናዘዛሉ ይህ የጠበቀ የኑዛዜ ቃላቸውም እንዲህ የሚል ነበር “አደራ ጎንደር ወስዳችሁ እንድትቀብሩኝ”። የኖርነው እንዲህ ነው! ጋሽ ዋቅጋሪ መግለጥ የፈለጉት በፍቅር ተቻችለን መኖራችንን ለማሳየት ነው። አሞራውን ፤ገረሱንና ዋቅጋሪን እንመልከት ከነፍስ ዕብጠት በጸዳ በአብሮነትና በመቻቻል መኖርን ተግብረው አሳዩን። እኔ አንድ ሰውም ይሁን ማህበረሰብ በዕውቀት ደረጀ የምለው ቅጥያጡና የፈራረሱ ነገሮችን አስተካክሎ በውበት መገንባት ከቻለ ነው የኛ ቀለም ቆጠራ ግን ጋፍኛ ለማፈራረሱ ተግቶ ተገኜ እናም ልሂቃን ወይ ልበል የዕውቀታችንን መነሻና መድረሻ እንመርምረው። ጀግናው ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ እንዲህ በመሰለ አኩሪ ታሪክ በጀግንነት ከጠላት ጋር፤ በጥበብ ከህዝባቸው ጋር በማዳወር ተሳክቶላቸው ያለፉ ጀግና ናቸው። እኛም ከህይወታቸው ተምረን ታሪካችንን በወርቅ ቀለም ጽፈን እንለፍ እንጅ በብልጠት ፕሮፐጋንዳ ታሪክ ደልዞ በሰው ታሪክ ላይ ቁብ አይቻልም። ቸር እንሰንብት!።
The post አሞራው ማን ነው? ( ነጋ አባተ -ከእስራኤል) appeared first on Medrek.