የፌዴራል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታና በሌሎች ግለሰቦች ላይ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 60/89፣ 368/95፣ 622/2001 እና የወንጀል ሕግን በመጥቀስ፣ በሥልጣን አለአግባብ በመገልገልና በጥቅም በመተሳሰር የቀረጥ ነፃ መብትን ያላግባብ በመገልገል፡ እንዲመረመር አለማድረግ ወይም እንዳይመረመር ማድረግ፣ ገደብና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ዕቃዎች (መድኃኒቶች) በማስገባት ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው፣ ጉዳያቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ እያለ አዲሱ የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 ወጥቷል፡፡
አዲሱ አዋጅ ነባር የጉምሩክ አዋጆችን ሙሉ በሙሉ ሽሯል፡፡ ስለዚህም ከላይ የተጠቀሱት ድርጊቶች በአዲሱ ሕግ ወንጀልነታቸው ቀርቷል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 እና የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 አንድ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ የሚወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፣ ከድርጊቱ በኋላ የወጣው ሕግ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በአዲሱ አዋጅ በአንቀጽ 182 ላይ፣ ‹‹በሌሎች ሕጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ መሠረት ፍፃሜ ያገኛሉ፤›› ሲል ያሰፍራል፡፡
ተከሳሾቹና አቶ መላኩ ጉዳያቸውን በማየት ላይ ለሚገኘው ፍርድ ቤት አንቀጹ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጋጭ ያመለክታሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ይመራዋል፡፡ ጉባዔው ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ባለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚደራጅ ሲሆን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅራቢነት በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የሚሾሙ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ስድስት የሕግ ባለሙያዎችና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ከአባላቱ መካከል የሚወክላቸው ሦስት ሰዎችን በአባልነት ይይዛል፡፡ ጉባዔው ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሐሳብ ያቀርባል እንጂ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ምክር ቤቱ ነው፡፡
ጉባዔው ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ፍርድ ቤቱ በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ያቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ መርምሮ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የአዲሱ አዋጅ አንቀጽ 182 ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭና የተከሳሾችን መበት የሚጋፋ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ የተጠበቀው ጉባዔ፣ ለውሳኔው ጭብጥ ያደረገው አዲሱ አዋጅ ተከሳሾችን ሊጠቅም የሚችል ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በአዲሱ አዋጅ ተከሳሾች እንዲጠቀሙ የተደረገ ባለመሆኑ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 ጋር አይጋጭም፤›› ሲል ውሳኔው ያትታል፡፡
ሕጉ ተከሳሾችን ሊጠቅም ይችላል ወይስ አይችልም በሚል ታሳቢ የተደረገ እንዳልሆነ በአጽንኦት የሚገልጸው የጉባዔው ውሳኔ፣ የአዋጁ ዓላማ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመደገፍና ሕጋዊ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እንጂ፣ ተከሳሾችን ለመጥቀም ታሳቢ ተደርጎ የወጣ ስላልሆነ ጥያቄው የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልገውም በማለት ደምድሟል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ከ20 ዓመት በፊት ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. በሙሉ ኃይሉ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በአወዛጋቢነታቸው ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ፣ እንዲሁም የመደበኛ ፍርድ ቤቶች ግንኙነትና ሥልጣንና ተግባር ነው፡፡ ይህ የጉባዔው ውሳኔም ውዝግቡ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ እንጂ በጊዜ ሒደት በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተደረጋጋና የሰከነ አሠራር ስለመስፈኑ እንደማያሳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዜጎችና የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች ይናገራሉ፡፡
ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫሉ የተባሉ አዋጆች ላይ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጡ አቤቱታ የሚቀርብላቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው፣ የሕግ አውጪውን (ፓርላማውን) ውሳኔ የተቃወሙት በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ ይህም በተመሳሳይ ጉዳይ የእነ አቶ መላኩ ይግባኝ የማለት መብታቸው የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የመጀመርያ ደረጃ የዳኝነት ሥልጣን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚሰጠው አዋጅ ቁጥር 25/88 ተጥሷል በሚል በዚሁ ዓመት በመወሰኑ ነው፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ የተነሳበት ጉዳይ ላይ የተሰጠው የኋለኛው ውሳኔ እንደ መጀመርያው ድጋፍ ያለው አይመስልም፡፡ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት የሆኑት አቶ እንዳልካቸው ገረመው ጉባዔው የአዲሱ የጉምሩክ አዋጅ አንቀጽ 182 ሕግ አውጪው አካል የወንጀል ሕግን የተፈጻሚነት ወሰን ያለ ገደብ እንዲወስን የሚያደርግ በመሆኑ መሠረታዊ ስህተት ያለበት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሦስት ሥር የታቀፉትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ላይ ሕግ አውጪው ገደብ ሊያደርግ የሚችለው ልዩ ሁኔታዎች መፍጠር እንደሚቻል ራሱ ሕገ መንግሥቱ ሲያቅድ መሆኑን ያስታወሱት አቶ እንዳልካቸው፣ አንቀጽ 22 ግን ይህን የማይፈቅድ በመሆኑ ለልዩ ሁኔታ ሌላ ልዩ ሁኔታን በማምጣት ጉባዔው መወሰኑ ስህተት ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
የቀረበለትን የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ በቀጥታ ከማየት ይልቅ፣ ጉባዔው የአዋጁን መግቢያ በመጥቀስ የሕግ አውጪውን ሐሳብ በመመርመር ያቀረበው መከራከሪያም በጣም ደካማና አሳማኝ ያልሆነ፣ እንዲሁም ከዋናው ጉዳይ የሸሸ እንደሆነ አቶ እንዳልካቸው አስረድተዋል፡፡ መሠረታዊ መርሆዎችን የሚፃረሩ አዋጆችን ሕገ መንግሥታዊ ናቸው ብሎ መተርጎም የሕገ መንግሥቱን የበላይነት የሚቃረንና የተወሰኑ ግለሰቦች ላይ አድልኦ ለመፈጸም ሕግን እንደ መሣሪያ ለመጠቀም በር የሚከፍት እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል፡፡
ጉባዔው በጭብጥነት ከመረመራቸው ጉዳዮች መካከል ተከሳሶቹ በአዲሱ አዋጅ ይጠቀማሉ ወይስ አይጠቀሙም የሚለው አንዱ ነው፡፡ አቶ እንዳልካቸው ጭብጡ በፍርድ ቤቱ ከቀረበው ጉዳይ ጋር የማይገናኝና በጉባዔው የዳኝነት ሥልጣን ሥር ያልወደቀ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ አንቀጹ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ፣ ይኼንን ጭብጥ ሊመረምር የሚገባው መደበኛው ፍርድ ቤት ሊሆን እንደሚገባም ተከራክረዋል፡፡ አዋጁ በግልጽ ወንጀል የነበሩ ድርጊቶች በአስተዳደራዊ ጥፋት መቀየራቸውን እየገለጸ ባለበት ሁኔታ፣ ይህ ተከሳሾቹን አይጠቅምም ብሎ በሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ውስጥ ማስፈር ትርጉም የሚሰጥ ነገር እንዳልሆነላቸው አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል፡፡
የጉባዔውን ዝርዝር ውሳኔ እንዳልተመለከቱ የገለጹት ተቀዳሚው የፌዴራሊዝም ተመራማሪ ዶ/ር አሰፋ ፍሰሐና የሰብዓዊ መብት ኤክስፐርት ዶ/ር ታከለ ሰቦቃ፣ በተመሳሳይ በውሳኔው እንዳልተስማሙ አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር አሰፋ ‹‹ጉባዔው ከመብት አንፃር ጉዳዩን ሰፋ አድርጎ ቢተረጉመው መልካም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ሁለቱም ምሁራን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ያሳተሙ ሲሆን ሕግ አውጪው አካል ባወጣቸው ሕጎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት፣ ሁልጊዜም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም ጉባዔው ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብለው አያምኑም፡፡ ፍርድ ቤቶች መቼ ነው ጉዳዩን ለምክር ቤቱ ወይም ለጉባዔው የሚመሩት የሚለው ግን ቁልፍና አወዛጋቢ ጥያቄ መሆኑን ይቀበላሉ፡፡ ዶ/ር ታከለ በሕገ መንግሥቱ ላይ መተማመንና ስምምነት ለመፍጠር ለዚህ ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለምን?
ሕገ መንግሥት ከሚሰጣቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ዋነኛው የመንግሥት ሥልጣን በያዙ ሰዎች ላይ ገደብ የሚያስቀምጥ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን ሥራ ላይ የዋሉት ሕገ መንግሥቶች ይህን ዓላማ በተሳካ ሁኔታ አልፈጸሙም በሚል ይተቻሉ፡፡ የፖለቲካ ኃይሎች ሥልጣን ላይ ገደብ ከማበጀት ይልቅ በሥልጣን ላይ የመቆየት መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል በሚል ይወቀሳሉ፡፡
የኢፌዴሪ ሕገ መንገሥት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሦስት ሕገ መንግሥቶች የሚሻልባቸው በርካታ መለኪያዎች ያሉ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ልሂቃኑን ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ ከማድረግ አኳያ ተመሳሳይ ጉድለት እንዳለበት አስተያየት ሰጪዎች ያመለክታሉ፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፖለቲካ ተንታኝ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ተፈጠረ ማለት ፖለቲካዊ ጠብ፣ የሕዝብ ቅሬታ፣ የአገር ችግርና የእርስ በርስ አለመግባባት ይቀራል ማለት እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ይሁንና ችግሮችን ከጠብመንጃ ይልቅ በሰላማዊ፣ በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ሥርዓቱ አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ ለመግባባት የሚያስችል ከባቢ ባለመፈጠሩ ስለዲዛይን ችግር ጥልቅ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ጊዜ ማጥፋት መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የፖለቲካ ባህሉ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መንገድ ለመግባባት የሚያስችል እንዳልሆነም ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የተለያዩ ፍላጎቶችን በነፃነት ማንሸራሸር የሚያስችል ከባቢ አልፈጠርንም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የመደራጀት መብትን ለማስፋፋት የሚሠራ መንግሥት ሳይሆን፣ በከፍተኛ ሥጋትና ጥርጣሬ ብቻ ነፃነትን የሚጋፋ መንግሥት ነው ያለን፤›› ያሉት ተንታኙ፣ ከመጠን በላይ ፈርጥሟል ያሉት አስፈጻሚው አካል ራሱ ላረቀቀው ሕገ መንግሥት መታመን እንዳልቻለ ይተቻሉ፡፡
ስለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ስለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ሥልጣንና አፈጻጸም ሲጠየቁም ‹‹ዞሮ ዞሮ በአገሪቱ ለመገንባት ያቃተን ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህ ተቋማት ከምርጫ ቦርድ፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከፍርድ ቤትና ከዓቃቤ ሕግ ጋር ተመሳሳይ ችግር አለባቸው፡፡ የሚሰጡት ትርጉም ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆነ ነው? ወይስ ለፖለቲካ ኃይሎች? ከመንግሥት ትዕዛዝ የማይቀበሉ ነፃ ተቋማት ናቸው? ይህንን የሚያረጋግጡት ሕገ መንግሥታዊ ነፃነታቸውን ሲጠቀሙና በውስጥ ደንብ ብቻ መመራት ሲጀምሩ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ የችግሩን ምንጭ ከሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት ጋር የሚያያይዙትም በርካቶች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥትን የመተርጎም ሥልጣን በአብዛኛው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ወይም ለሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከአስፈጻሚውና ከሕግ አውጪ አካላት በተዋቀረው የፖለቲካ ተቋም እንዲተረጎም በማድረግ ያልተለመደ ውሳኔ ወስናለች፡፡ ይህ ዲዛይን የሥልጣን ክፍፍልና የእርስ በርስ ቁጥጥር መርህን አያረጋግጥም በሚል በማርቀቅ ሒደቱ ተቃውሞ ቀርቦ እንደነበር የሚያስታውሱ ጥናቶች፣ በሒደቱ ላይ የበላይነት የነበረው ኢሕአዴግ ስለፈለገው ብቻ የሕገ መንግሥቱ አካል እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህም በማርቀቅ ሒደቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ግብዓት ቢወሰድ ኖሮ ውጤቱ የተለየ ይሆን ነበር በማለት አንዳንዶች እንዲደመድሙ አድርጓል፡፡ የሕግ ባለሙያው ዶ/ር አሰፋ እንደሻው፣ ሕገ መንግሥቱ ወደ ሥራ ከገባ 20 ዓመት መሙላቱን አስመልክተው ለሪፖርተር በላኩት ጽሑፍ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ከኅብረተሰቡ አብራክ የወጣ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኃይሎች የሚደግፉት እስከሆነ ድረስ ተፈጸሚነት ይኖረዋል፡፡ የተጠቀሱት ኃይሎች ሕገ መንግሥቱን የሚሹና መኖሩንም ሆነ መሻሻሉን አበክረው የሚከታተሉት እስከሆነ ድረስ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው ግን እነዚህ ኃይሎች ደካማ ሆነው ወይም ገና ሥር ያልሰደዱ፣ ጭራሽም ያልበቀሉ ከሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ብቻውን ሊያስፈጽመውም ላያስፈጽመውም የሚችለው ሰነድ ሆኖ 20 ዓመታት ዘልቋል፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት የሌለው መሆኑ ቁልፍ ችግር እንደፈጠረ አመልክተዋል፡፡
የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አበራ ደገፋ ችግሩን ከዲዛይንና ከፖለቲካ ባህሉ እንደሚቀዳ ይገልጻሉ፡፡ ዲዛይንና የፖለቲካ ኃይሎች ተግባር አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩም ያስገነዝባሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲተረጉመው የተደረገበት ምክንያት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ለመጠበቅ ቢሆንም በዲዛይንም ሆነ በተግባር ይህን በሚያረጋግጥ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እየተጓዘ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን እንዲተረጉም በመመረጡ ቅሬታ ባይኖራቸውም፣ ውሳኔን በውሳኔ የመሻር ሥልጣንን ጨምሮ ሌሎች ጥበቃዎች የሌለው መሆኑ ደካማ እንዳደረገ ጠቁመዋል፡፡
በአውስትራሊያ የዌስተርን አውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ የሕግ ፕሮፌሰር ዶ/ር ታከለ ሰቦቃ የሕግ አስፈጻሚውና የሕግ አውጪው አካላት የራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም የሚፈልጉ አካላት ከመሆናቸው አኳያ፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጥቅምን የማይሻው የዳኝነት አካል ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም ተመራጭ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ሥልጣን ለምክር ቤቱ ከመስጠትም በላይ አስቸጋሪ ሁኔታ የፈጠረው፣ ምክር ቤቱ ከመደበኛ ፍርድ ቤት ጋር ያለው ግንኙነትና የዳኝነት ሥልጣን ወሰኑ እንደሆነ ዶ/ር ታከለ ያስረዳሉ፡፡
ሳይጠየቅ እጅ የሰጠ ሕግ ተርጓሚ
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 83(2) የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ሲነሳ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚያገኝ ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 79(1) ላይ ደግሞ በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚቀርብ ክርክር ወደ ሕገ መንግሥታዊ ክርክር የሚቀየረው መቼ ነው? የሚለው ጥያቄ ቁልፍ አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ መዝለቁ ተገልጿል፡፡ በአንቀጽ 84(2) ላይም በፌዴራሉም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሊያቀርብ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ከላይ በተገለጸው የእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ላይ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያደረገውም ይህንኑ ነው፡፡ ነገር ግን ለምንና እንዴት አድርጎ ጉዳዩን ለትርጉም ሊያቀርብ ይችላል የሚለው ጥያቄ በጽንሰ ሐሳብም ሆነ በተግባር ደረጃ ግልጽ ሳይሆን ሁለት አሥርት ሞልተውታል፡፡
ዶ/ር አሰፋ ፍሰሐ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ መብትን የሚነኩና ፖለቲካዊ ጠቀሜታቸው የጎሉ ጉዳዮች ላይ ትርጉም የመስጠት ሥልጣን ቢኖረውም፣ በግለሰቦች የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ላይ ምክር ቤት እጁን ሊያስገባ እንደማይገባ ይከራከራሉ፡፡ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ የነበረው አረዳድ ይኼው ቢሆንም፣ ዶ/ር አሰፋ ‹ኢሕገ መንግሥታዊ ናቸው› የሚሏቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤትንና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውን ሥልጣንና ተግባር የሚደነግጉት አዋጅ ቁጥር 250/93 እና 251/93 ከወጡ በኋላ ግን ማንኛውም ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መሄድ እንደጀመረ ይገልጻሉ፡፡
የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ሥልጣን በመጋፋት ሁሉንም ሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰባቸውን ጉዳዮች የሚያየው ምክር ቤት ትልቁ ፈተናው በፖለቲካ ተቋምነቱና በገለልተኛ ተቋምነቱ መካከል የሚዋልል መሆኑ ነው ሲሉም ዶ/ር አሰፋ ይከራከራሉ፡፡ በቀረቡለት ጉዳዮች ላይ የሰጠው ውሳኔ መንግሥትን አትንኩ የሚል አዝማሚያ እንዳልውም አመልክተዋል፡፡ ይሁንና ባለፉት ሦስት ዓመታት ምክር ቤቱ በተሻለ መልኩ ሥራውን ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በቅርብ ዓመት ከፓርቲ ዲሲፕሊን ወጣ ብሎ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሞቅ ያለ ክርክር አድርጎና ሐሳብ አንሸራሽሮ ለመወሰን የፈጠረው ተነሳሽነት ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ በከድጃ በሽር ጉዳይ ላይ ያለፈቃዷ የናይባ (ሼሪአ) ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ብሎ ከወሰነው ውሳኔ በኋላ፣ በእነ አቶ መላኩ የይግባኝ መብት ላይ የሰጠው ውሳኔ ምሥጋና የሚገባው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ክርክር ምንን ያካትታል የሚለው ጥያቄ ምላሽ ግልጽነት የጎደለው መሆን የፈጠረው ችግር እንዳለ የጠቆሙት ዶ/ር አሰፋ፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ግን ሥልጣናቸውን አሳልፈው ለመስጠት ይህን ሁኔታ እንደሰበብ እየተጠቀሙበት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ምዕራፍ ሦስትን ካየን በተለይ ከአንቀጽ 13 አንፃር መደበኛ ፍርድ ቤቶች ትልቅ ሚና እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ፍላጎት ያለ ሲመስላቸው ጉዳዩን ከእጃቸው የማውጣት አቋም ነው ያላቸው፤›› በማለት ዲዛይኑ ከፈጠረው ጫና ይልቅ በገዛ ፈቃዳቸውና ድክመታቸው ሥልጣናቸው እንደተሸረሸረ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ዶ/ር አበራ፣ ‹‹ፍርድ ቤቶች ወይም የዳኝነት አካላት ራሳቸው ሥልጣናቸውን የሚያስከብሩ አይደሉም፡፡ እንኳን ተፈጥሯዊ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሊሟገቱ በግልጽ የተሰጠ ሥልጣናቸውንም የሚጠቀሙ አይመስሉም፡፡ በተለይ ጉዳዩ የፖለቲካ ትኩሳት ያለው በሚሆንበት ጊዜ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምራትን ይመርጣሉ፡፡ ምክር ቤቱም ጉዳዮችን በአግባቡ የመመርመርና ውሳኔውን በተቀላጠፈ ሁኔታ የመስጠት ሪከርዱ ደካማ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ዶ/ር አሰፋም የፖለቲካ ትኩሳት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላለመስጠት ያላቸው ፍላጎት በምክር ቤቱም ተመሳሳይ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ በተለይ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሠራተኞችን ያለ ምንም ዓይነት ምርመራ ማባረር ይችላል በማለት የወጣው ደንብ ላይ ትርጉም የሰጠው ምክር ቤት ደንቡ ላይ ችግር የለበትም በሚል የሰጠው ትርጉም የዚህ አዝማሚያ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት መምህር የሆኑትና ከ1988 ዓ.ም. እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት የሥራ ዘመናት የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው አባል የነበሩት አቶ ጌታሁን ካሳ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በመደበኛ ፍርድ ቤቶች መካከል ያለው የዳኝነት ሥልጣን ግልጽነት መጉደል እንዳለ ሆኖ የክልሎች ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔዎች ሲጨመሩ ጉዳዩ ይበልጥ የተወሳሰበ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ አቶ ጌታሁን በክልልና በፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ግለሰቦች የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት መሆናቸው በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው ውሳኔ እንዲሰጡ እንደሚያደርግ፣ ይህም በሥልጣን ክፍፍልና እርስ በርስ የመቆጣጠር መርህ ላይ ጫና እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማን ቢተረጉመው የተሻለ ሥርዓት ይፈጠራል የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰባሰበውና አደረጃጀቱም ጠንካራ ያልሆነው ምክር ቤት የአቅም ጥያቄ እንደሚነሳበትም አስታውሰዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የምክር ቤቱ አባላት ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ይወክላሉ እንጂ የፖለቲካ ቡድኖችን ይወክላሉ ብሎ እንዳላሰበ ያስታወሱት አቶ ጌታሁን፣ እስካሁን ድረስ አባላቱ የሚመረጡት በክልል ምክር ቤቶች እንጂ በሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ አለመሆኑ ይህን ችግር እንዳመጣ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ታከለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉም ከመጠየቁ በፊት ጥያቄውን በግልጽ ሊያሰፍር እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶች ፍሬ ነገርን በመያዝ የሕግ ጥያቄ ብቻ ሊያቀርቡ እንደሚገባም ተከራክረዋል፡፡ ጥያቄውን በደፈናው ከላኩ ግን ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመስጠት በር እንደሚከፍቱ አስጠንቅቀዋል፡፡ ‹‹መተርጎም እንጂ ዳኝነት የምክር ቤቱ ሥራ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የታችኛው ሕግ ከሕገ መንግሥቱ ከተጋጨ ትርጉም አያሻውም፡፡ ተፈጻሚ ነው መሆን የለበት፤›› ያሉት ዶ/ር ታከለ በተግባር ግን ተቃራኒው እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡ በተለይ ጉዳዩ የፖለቲካ ትኩሳት በሚኖረው ጊዜ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን ሳይጠየቁ ሁሉ ወደ ምክር ቤቱ እንደሚልኩ አመልክተዋል፡፡ ለአብነትም በ1997 ዓ.ም. በቅንጅትና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መካከል በነበረው ጉዳይ ፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ሥልጣን በአግባቡ ሳይጠቀም ጉዳዩን ለምክር ቤቱ እንደመራው ጠቅሰዋል፡፡
ቅንጅት በወቅቱ ዋነኛው ተፎካካሪ ፓርቲ ሲሆን ምርጫው ከመደረጉ ከአንድ ቀን በፊት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአዲስ አበባና በአካባቢው ሕዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ለአንድ ወር ማድረግ እንደማይቻል ማወጃቸው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት፣ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አቤት ይላል፡፡ አቤቱታው በዋነኛነት የተመለከተው የሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ አዋጅ ቁጥር 3/1983 መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ ቅንጅት ጉዳዩን ፍርድ ቤቱ ወደ ምክር ቤቱ ሳይመራ እንዲያየው ቢያመለክትም ፍርድ ቤቱ ጥያቄዎችን እንኳን በአግባቡ ሳይገልጽ ድርጊቱ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ እንዲወስን መጠየቁ፣ ፍርድ ቤቶች ሥልጣናቸውን በቀላሉ ለሌላ አካል አሳልፈው የመስጠት አዝማሚያ እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን ዶ/ር ታከለ ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት መተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 255/1994 የተደነገገውን ለቀድሞው ፕሬዚዳንት የተሰጠ ጥቅማ ጥቅም፣ በምርጫ 97 የግል ተወዳዳሪ መሆናቸው በአዋጁ አንቀጽ 3(7) ላይ ‹‹ፕሬዚዳንቱ በሥራ ዘመኑም ሆነ የሥራ ዘመኑ ካበቃ በኋላ ወገንተኝነት ካላቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የመገለል ኃላፊነት ይኖረዋል፤›› ተብሎ ከተደነገገው ጋር የሚጋጭ ነው በማለት፣ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ አቤቱታ ያቀርባሉ፡፡ ሕጉ የወጣው በፖለቲካ አለመግባባት ምክንያት ፕሬዚዳንቱ በገዛ ፈቃዳቸው ከመልቀቃቸው ከሰዓታት በፊት መሆኑ በራሱ ጥያቄ የሚፈጥር እንደሆነ ዶ/ር ታከለ አመልክተዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብትን የሚፃረር ነው በማለት ተከራክረዋል፡፡
በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ሕጎቹ ከሕገ መንግሥቱ ጋር አይጋጩም ተብሎ መወሰኑ ብቻ ሳይሆን፣ የተጠቀሱትን መብቶችና ሕጎች በአግባቡ መመርመር አለመቻሉ ተቀባይነት እንደሌለው ዶ/ር ታከለ አመልክተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ባሩድ ምክር ቤቱ በተወሰነ መልኩ የአቅም ውስንነት እንዳለበት ተቀብለው፣ ሚዛናዊና ገለልተኛ ሆኖ ጉዳዮችን አያይም በሚል የሚቀርበውን ትችት አጣጥለዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱን ይጥሳል የተባሉ የአስፈጻሚውም ሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በምክር ቤቱ ተሽረዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች ሥራ ጣልቃ አንገባም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ጉዳዩን የሚመሩት ራሳቸው ናቸው፡፡ ከግለሰቦች፣ ከቡድኖችና ከፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት በማትረፋችን ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ 852 ጉዳዮች ቀርበውለት ለ610 ጉዳዮች ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በ1991 ዓ.ም. የቀረቡለት ጉዳዮች አራት ብቻ ሲሆኑ፣ በ2005 ዓ.ም. ብቻ 272 ጉዳዮች መቅረባቸው ለውጡን ያመለክታል፤›› ብለዋል፡፡ አቅሙን ለማጎልበት በተለይ የምርምር ክፍሉን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ባለቤት ያጣ ሕገ መንግሥት?
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(1) ‹‹ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖርም፤›› ይላል፡፡
ዶ/ር አደም ካሴ “A Coustitution without a Guardian: Is the Ethiopian Coustitution Really Supreme?” በሚል ርዕስ ባሳተሙት የምርምር ሥራ፣ የፖለቲካ ኃይሎች ሥልጣን ላይ ገደብ የሚያስቀምጥ ተቋማዊ አሠራር በሌለበት ሁኔታ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ነው ማለት እንደማይቻል ተከርክረዋል፡፡ ዶ/ር አደም ‹ባለቤት ያጣ ሕገ መንግሥት› በሚል የገለጹት የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ቁልፍ ችግር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥርዓት ለፖለቲካ ኃይሎች የሚሰጠው ሥልጣንን እንዳሻቸውና በዘፈቀደ የመጠቀም አዝማሚያ ላይ ለውጥ ካልተደረገ፣ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲው ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተከራክረዋል፡፡
ዶ/ር ታከለም በተመሳሳይ በተግባር የዳበረውና ከዲዛይን የመጣው የሕገ መንግሥት ትርጉም አሰጣጥ ካልተቀየረ በሕገ መንግሥቱ የታቀፉ በርካታ መብቶችን መጠቀም ከዜጎች ተደራሽነት እየራቀ እንደሚሄድ አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ዶ/ር አሰፋ ፍርድ ቤቶችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዜጎች መብትና ነፃነት ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጡት ለገዢው ፓርቲ ፍላጎት ከሆነ፣ ሕገ መንግሥቱ ባለቤት ያጣ ሕገ መንግሥት እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎችም በተመሳሳይ በሕገ መንግሥት ትርጉም ላይ ያለው ግራ መጋባትና ያስከተላቸው ጠባሳዎች የቀጣይ ዓመታት የቤት ሥራ መሆን እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙና አቶ እንዳልካቸውም የእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ መንግሥትን ለመከላከል ተቋማቱ የሚሄዱበትን ርቀት የሚያሳይ በመሆኑ፣ መሰል ውሳኔዎችን ማስወገድ አስፈላጊ ነው ሲሉ መክረዋል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)
<!–
–>
The post ባለቤት ያጣ ሕገ መንግሥት? appeared first on Medrek.