Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

ሰማይ የተሰቀለው አንገብጋቢ የኑሮ ውድነቱና ሸፍጠኛ መንስኤው! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

$
0
0

ባለፈው ሳምንት አንድ የመጽሐፈ ገጽ (የፌስ ቡክ) ጓደኛየ ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝን ነገር ተናገረ፡፡ የደርግ ዘመንን መቶ ብር ለጥፎ ይሄንን አለ “”ከ1983ዓ.ም. (ከወረራው በፊት) ይሄ ብር አንድ ኩንታል ጤፍ በ40 ብር ፣ አንድ ፍየል ቆዳ ምላሽ በ15 ብር ፣ ሩብ ኩንታል አተር በ10 ብር ፣ 5 ድርብ ኮከብ ዶሮ በ12.50 ፣ መቶ እንቁላል በ10 ብር ፣ አንድ ኪሎ በርበሬ በ2 ብር ፣ 3 ሊትር ዘይት በ10.50 ይገዛ ነበር፡፡ አሁን የኔዋ ዕድሜም ዕድሜ ሆና የድሮውን ልናፍቅ!!!”” ነበረ ያለው፡፡

እውነቱን አይደለም? እኛ የደርግ ዘመን ሰዎችም እንደ ጃንሆይ ዘመን ሰዎች “እንዲህ ነበር!” ብለን ተረት የሚመስል ነገርን ለማውራት በቃን እኮ! አይገርምም? ምነው እንዲያው ኑሮው እንዲህ ባልተንጫረረና “እንዲህ ነበር እኮ!” እያልን ተረት የሚመስልን ነገር ማውራቱ በቀረብን ነበር! እኔ ግን እንዲያው ሲመስለኝ ወያኔ ብርን ሲቀይረው መቶው ብር ላይ የነበረውን የአርበኛ ሥዕል አስወግዶ አዲሱን ብር በማምጣቱ ይመስለኛል ብር እንደዚህ ጠባቂና ዋጋ አጥቶ አልያዝ ብሎ እየበረረ ባክኖ የቀረው፡፡

እስኪ ተያይዞ የቀረበውን ነባሩን መቶ ብር እዩት፡፡ አርበኛው ሰጥቶት የነበረውን ግርማ ሞገስ አያቹህት? ለመሆኑ ግን ወያኔ የአርበኛውን ሥዕል ከመቶው ብር ላይ ለምንድነው ያስወገደው? ያው ግልጽ ነው ለአርበኞቻችን ተጋድሎ፣ መሥዋዕትና ተግባራት ዋጋና ክብር የማይሰጥ የባንዳ አገዛዝ መሆኑን ለማሳየት ነው ሌላ አይደለም፡፡ የሚገርመው እንደሌላው የውንብድናና የክህደት ተግባሩ ሁሉ ይሄንንም ሲያደርግ ለሕዝብ አለማሳወቁ ወይም አለማስወሰኑ ነው፡፡

ብዙዎቻችን እንኳን በ1983ዓ.ም. የነበረውን የሸቀጦች ዋጋ ልናስታውስ ይቅርና የሸቀጥ ዋጋ እንዲህ እንደዛሬው ሰማየ ሰማያት ሳይወጣ ከአምስትና ዐሥር ዓመታት በፊት የነበረውን እንኳ ምን በምን ያህል ይገዛ ወይም ይሸመት እንደነበር ምንም አናስታውስም፡፡ የዚህ ምክንያቱ የምጣኔ ሀብት (የኢኮኖሚክስ) ባለሞያዎቹ የዋጋ ግሽበትን አስልተው የሚነግሩን ካለፈው ዓመት በመነሣት “ግሽበቱ ሰባት በመቶ፣ ስምንት በመቶ ነው ያደገው!” ይሉናል እንጅ ወያኔ ሥልጣን ሲይዝ የነበረውን የሸቀጦች ዋጋ መነሻ በማድረግ ባለመሆኑ በደፈናው ኑሮ ተወደደ እንድንል እንጅ የየሸቀጡ ዋጋ ከምን ተነሥቶ በምን ያህል ደረጃ እንደናረ ልብ እንዳንለው እንዳናውቀው አድርጎናል፡፡ በሌላ አማርኛ የባለሞያዎቹ የዋጋ ግሽበት ስሌት ሕዝቡ ወያኔን ከደርግ ጋር አነጻጽሮ ኑሮ በየትኛው ዘመን የተሻለ እንደነበርና አሁን የኑሮ ውድነቱ ምን ያህል እንደተወነጨፈበት እንዳያስተውለው እንዳይረዳው በማድረግ ወያኔን አግዟል፡፡ ወይ ደግሞ ከዚህ ስሌታቸው በተጨማሪ 1982ዓ.ምን መነሻ በማድረግ የሚነግሩን ቢሆን መልካም በነበረ፡፡ ወያኔ በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ ማለቴ አይደለም፡፡ በዚያ እማ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከወያኔ ይዞታ ውጪ ባሉ የብዙኃን መገናኛዎች አልኩ እንጅ፡፡

ካላይ በመቶ ብር የተሸመቱትን ምርቶች ዛሬ ላይ እንሸምት ብንል በትንሹ 6,500.00 (ስድስት ሽህ አምስት መቶ) ብር ያስፈልገናል፡፡ ይሄም ማለት በግርድፉ ስናየው ጥቅል ዋጋቸው 65 ጊዜ እጥፍ አሻቅቧል ማለት ነው፡፡ በአንጻሩ ለሠራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ የዚያኑ ያህል በደርግ ዘመን ይከፈለው ከነበረው 65 ጊዜ እጥፍ እንዲያድግለት ተደርጓል ወይ? ካላቹህ እንኳን 65 ጊዜ የብዙዎቹ የሥራ ዓይነቶች አንድ ጊዜ እጥፍ እንኳ አላደገም፡፡ በመሆኑም ጫናው በዚህ መከረኛ ሕዝብ ላይ ከዘመን ወደ ዘመን እየተደራረበ መጥቶ እጅግ በከባዱ ሊጫነውና ወፍ እንደቆመችበት ቀጤማ ባፍ ጢሙ ሊደፋው አጉብጦት ቁጭ ብሏል፡፡
ይሄ ለዚህ ድሀ ሕዝብ ምን ማለት ነው? ሊታመን በማይችል ሁኔታ የወያኔ ዘመን ብር የመግዛት አቅም በጣም አሽቆልቁሏል፡፡ አሁን ላይ የወያኔ 100 ብር ማለት ከደርግ ዘመን 65 ሳንቲም ጋር እኩል ሆኗል፡፡ አንድ በደርግ ዘመን የአንድ ሽህ ብር ደሞዝተኛ የነበረ ሰው በደርግ ዘመን ይኖረው የነበረውን ኑሮ ዛሬ ላይ ለመኖር ካስፈለገው ደሞዙ 65 ሽህ ብር መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ደሞዙ የኑሮ ውድነቱ የማሻቀቡን ያክል በተነጻጸረ መልኩ እንዲያድግለት ተደርጓል ወይ? የደርግ ዘመን የአንድ ሽህ ብር ደሞዝተኛ አሁን ስንት ነው እየተከፈለው ያለው? ለምንድነው የኑሮውን ማሻቀብ ያክል እንዲያድግለት ያልተደረገው? ልዩነቱ የት ደረሰ? ማን በላው? ምርታማነት በሔክታር (በቃዳ መሬት) ከወትሮው በርካታ ጊዜ እጥፍ እንዳደገ ዘወትር ይለፈፋል እውነቱ ይሄ ከሆነ ልዩነቱ የት ደረሰ? ሀገር ተለወጠችበት ወይ? በፍጹም! መሠረተ ልማቱ ቀርቶ የሀገሪቱ ባጀት (የወጪ ገንዘብ ምድብ) እንኳ ሳይቀር በእርዳታና ብድር የሚሸፈን ነው፡፡

ደርግ ከምዕራባውያኑ ጋር በነበረው ችግር ምክንያት በ17 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ያገኘው ብድርና እርዳታ ከጥቂት ሚሊዮን (አእላፋት) የምታልፍ አልነበረችም፡፡ በወያኔ ዘመን ግን ከ40 ቢልዮን ልብ በሉ ሚሊዮን (አእላፋት) አይደለም ያልኩት ቢሊዮን (ብልፍ) በላይ ዶላር ብድርና እርዳታ ተግኝቷል፡፡ ይሄ ገንዘብ የት ደረሰ? ምን ተሠራበት? ከሀገር ውጪ ዜጎች የሚልኩት ገንዘብ (Remittance) በዓመት ከ3 ቢልዮን (ብልፍ) በላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የት ነው የሚገባው? ምን ተሠራበት? ከፍተኛ የጥራት ችግር የሚታይባቸውና ከዚህም የተነሣ ሀገር ላልተጠቀመችበት በትውልደ ትውልድ ተከፍሎ ለማያልቅ እጅግ ከፍተኛ ዕዳና ለድርብርብ ኪሳራ ጉዳት ከምትዳረግ መሠረተ ልማት ተብየዎቹ ከመሠራታቸው አለመሠራታቸው ይሻል እንደነበር ለሚታመንባቸው መሠረተ ልማቶች ሊወጣ የሚችለው ወጪ አነስተኛ በሆነበት ሁኔታ ቀሪው በብድርና እርዳታ፣ በዜጎች በመላክ (remittance) የተገኘው ከፍተኛ ገንዘብ የት ደረሰ? ምን በላው? እነኝህ ሁሉ ቀደም ሲል ያልነበሩ ገቢዎች ሁሉ ካሉ ታዲያ ኑሮው ከሕዝቡ አቅም በተጻራሪ እንዲህ ሊንጫረር የቻለው ልዩነቱ የት ስለገባ ነው? የአሥተዳደር ችሎታ ከማጣት ባክኖ ነው? ተዘርፎ ነው? ምን ሆኖ ነው? መልሱ ሁለቱም ነው፡፡ የሚበዛው ውንብድና ሃይ ባይ አጥቶ ተዘርፎ ሲሆን ቀሪው ደግሞ የአሥተዳደር ችሎታ ከማጣት ባክኖ ነው፡፡ ባልበላበት ዕዳ ከፋዩ ታዲያ ማን ሆነ? ሕዝቡ፡፡ ለዚህ ነው ሕዝቡ ገቢው ወይም ደሞዙ የኑሮ ውድነቱን ያህል ተስተካክሎ እንዲያድግለት ያልተደረገው ወይም የትናንቱ የኑሮ ርካሽነት ዛሬም ላይ ሊያገኘው ያልቻለው፡፡ ለዚህ ነው እድገቱ ሥልጣን የያዘው የዘራፊው ቡድን ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶችና የተሟሳኝ ባለሀብቶች እንጂ የሀገሪቱና የሕዝቧ ሊሆን ያልቻለው፡፡ ሲጀመር ከዓመታት በፊትም እንደተናገርኩት ብድርና እርዳታን ብቸኛ ምንጩ መሠረቱ ያደረገ እድገት እድገት ሊባል አይችልም፡፡ ልማቱንና እድገቱን ልማት ነው እድገት ነው ለማለት ከብድርና እርዳታ ተላቆ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) በመነጨ አቅም መገንባትና መልማት ሲቻል ነው እድገት ነው ለማለት የሚቻለው፡፡
አምና ነው አንድ የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) የመዝናኛ ዝግጅትና የማስታወቂያ ድርጅት ባለቤት የሆነ ሰው በዚያው በአየር ሰዓቱ ምን ሲል ሰማሁት መሰላቹህ “እኛ በልጅነታችን ጫማችን በረባሶ ግፋ ቢል ሸራ ጫማ ነበር የምናደርገው፣ ምግባችን ደግሞ ከሽሮ አታልፍም ነበር፡፡ ዛሬ ግን የኛ ልጆች ከጫማም ጫማ አማርጠው የሚያደርጉና ሳያረጅ የሚጥሉ፣ ምግባቸውም የፈረንጅ ምግብ ነው፡፡ ይሄ፤ ያለንበት ዘመን ከበፊቱ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ የሚያሳይ ይመስለኛል!” ሲል ተናገረ፡፡ እሱ ያየው የራሱን መለወጥ ነው፡፡ የተለወጠው በረባሶ ይጫማና ሽሮ ይመገብ በነበረበት ገቢ መስሎታል፡፡ የእሱ ወላጆች በዚያ ዘመን የነበራቸውን ተመሳሳይ ገቢ ዛሬ ላይ የያዙ ሰዎች ወይም የእሱ ወላጆች በነበሩበት የኑሮ ደረጃ ላይ ዛሬ ያሉ ወላጆች ለልጆቻቸው በረባሶ ወይም ሸራ ጫማ ማስጫማትና ሽሮ መመገብ አቅቷቸው ልጆቻቸውን በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት እየላኩ ልጆች በየትምህርት ቤቱ ራሳቸውን ስተው እየወደቁ እንደሆነ የሰማ አልመሰለኝም፡፡ ያ የሱ የልጅነት ዘመን ግን እንዲህ እንደዛሬው ዘመን ልጆች ከመራባቸው የተነሣ በየትምህርት ቤቱ እራሳቸውን እየሳቱ የሚወድቁበት ዘመን አልነበረም፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሕዝቡ ገቢውና ኑሮ ፈጽሞ ካለመጣጣሙ ወይም ገቢው ወር ለመድረስ አይደለም ለሳምንት እንኳ የማትበቃ ከመሆኗ የተነሣ “እንዴት ነው ግን የምትኖሩት? ከወር ወር የምትደርሱት?” እየተባባለ ለሚጠያየቀው ጥያቄ “እኔ እንጃ! በአስማት ነው መሰል የምንኖረው!” እያለ በመመላለስ ይቀላለድ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ የኑሮ ውድነቱ እንዲህ እንደዛሬው ሳይንጫረር ጥቂት ቀደም ባሉት ዘመናት ነው፡፡ ያኔ በአስማት የተባለ ዛሬ በምን እንበል? በዚህ ሰዓት እኮ ሕዝቡ የምር በቀን አንዴም መመገብ አቅቶታል፡፡

ይሄ ሕዝቡ የግዱን እንዲሸከመው እየተደረገ የመጣውን አግባብ ያልሆነ የኑሮ ጫና ሸክም ከዚህ በኋላ ልሸከም ቢል እንኳ የመሸከም አቅም ይኖረዋል ወይ? ያልን እንደሆን ሕዝቡ የትኛውንም ዓይነት የኑሮ ውድነትን ጫና መሸከም የሚያስችል ገደብ የለሽ አቅም ባለቤት አይደለምና የማንኛውም አካል አቅም የተወሰነ ነውና በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ ሕዝቡ የሚጫንበትን አግባብነት የሌለው ( አግባብነት የሌለው ማለቴ ግሽበቱ ተፈጥሯዊ ያልሆነ በአገዛዙ የሚፈጠር እንደሆነ ስለማምንና ስለማውቅም ነው፡፡ አገዛዙ በራሱ ችግር ምክንያት የሀገሪቱ ምጣኔሀብት ሲቃወስበትና አቅም ሲያጥረው ፍጹም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ወይም ምጣኔሀብት ሊሸከመው ከሚችለው በጣም በዘለለ ደረጃ ገንዘብ በገፍ እያተመ ገበያው ላይ በመርጨት ያጋጠመውን ጫናና ችግር ከራሱ አውርዶ ሕዝብ ትከሻ ላይ በመጫን ሕዝብ እንዲከፍለው፣ ዕዳውን እንዲወጣው ሲያደርግ በተደጋጋሚ አስተውያለሁና ነው አግባብነት የሌለው ማለቴ፡፡ ብር ዋጋ እያጣ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ያው እንደምታውቁት የወያኔ ተፈጥሯዊ አስተሳሰብ “ቻልኩበትም አልቻልኩበት በእኔ ስትገዢ ትኖሪያለሽ፣ ይዠሽ መቀመቀ እወርዳታለሁ እንጅ ሌላ አማራጭ እንድትሞክሪ ቀርቶ እንድታስቢ ፈጽሞ አልፈቅድልሽም!” የሚለው እጅግ ጤናማ ያልሆነ የራስወዳድነት አስተሳሰብና “የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” አስተሳሰብ ነው እንጅ “አይ በቃ! አስተሳሰቤ ሊሠራ አልቻለምና! አላዋጣምና! በእኔ ምክንያትም ሀገርና ሕዝብ መጎዳት ስለሌለባቸው ሌላው ይሆንለት እንደሆን እሱ ደግሞ ይግባና ይሞክረው! ቦታውን ልልቀቅ!” የሚል ቅንና ኃላፊነት የተሞላበት አስተሳሰብ ፈጽሞ የለውምና!) እናም ሕዝቡ ያለው አቅም ከዚህ በኋላ የሚጣልበትን አግባብነት የሌለው የኑሮን ጫና ሸክም መሸከም እንደማያስችለው በተለያየ መንገድ እየገለጸ በመሆኑ ከዚህ በኋላ የሚጨመርበት የኑሮ ጫና ሸክም ሁኔታውን ገለባብጦ የነገሩን መቋጫ ሊፈጥር እንደሚችል መገመት በጣም ቀላል ይመስለኛል፡፡ ወገኖቸ በዚያም ሆነ በዚህ መጨረሻው ደርሷል!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

The post ሰማይ የተሰቀለው አንገብጋቢ የኑሮ ውድነቱና ሸፍጠኛ መንስኤው! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News 24/7: Your right to know!.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 2265

Trending Articles