ከልብ በመነጨ፣ ፍጹም በሆነ የወገን ፍቅር በሶማሊያ በውትድርና ላሉ ወገኖች ፈጣሪ መፍትሄ እንዲሰጣቸው እንመኛለን። በማያውቁት ጉዳይ የበረሃ ጥሩር ለሚገርፋቸውና የነፍሳቸው ዋጋ በውል ለማይታወቀው ወገኖቻቸን እንኳን አደረሳችሁ ከማለት በላይ ሁሉም ወገኖች ድምጽ እንዲሆኗቸው እንጠይቃለን። በወር 30 ዶላር አበል ህይወታቸው ላለፈና አሁንም እያለፈ ለሚገኙት ሃዘናችን ትልቅ ነው። ትርጉም በሌለው ጦርነትና ለወደፊት ንጹሃን ዋጋ የሚከፈሉበት የፖለቲካዊ ቁማር ስትራቴጂ የደም ግብር ለመክፈል ሰልፍ ለያዛችሁ ፈጣሪ አሁንም ይድረስላችሁ!!
ለራባችሁም ለጠገባችሁም፡-
እንደ ልማዳችን እንኳን አደረሰን፣ አደረሳችሁ፣ እንቁጣጣሽ!! ስንል ለማለት ብቻ ባንለው ምንኛ ደስ ባለን ነበር። አዲሱን ዓመት ተቀብለን እልፍ ሳንል ባለንበት ቆመን ያረጅብናል። እኛም ያለ አንዳች ለውጥ ጎመን/አረም አሮብን የገንፎ ምንቸት ግባ እያልን በራሳችን እንደቀለድን እናረጃለን!! እኛና ዘመን እንዲህ ባለ ሂደት የጎንዮሽ እየነጎድን ነው። መለስ እንኳን ካለፉ ሦስት ዓመት አለፈ!! የክፋት ውርሳቸው ግን አሁንም አለ!!
ካሮጌውና ከጥንቱ ለመማር አንሞክርም። ያ ልባም አቀንቃኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን “የኋላው ከሌለ የታለ የፊቱ” እንዳለው!! ምን ይህ ብቻ “የመጣንበት መንገድ ያሳዝናል” ሲል አእምሮን በርቅሶ በሚገባ የግጥም ፍሰት እየዘከርን ያለፍናቸውን ዓመታት ያመላክተናል። “አፈር ይዞ ውስጡ አረንጓዴ ለምን ይሆን የራበው ሆዴ?” እያለ “አመመኝ አመመኝ ውስጤን አመመኝ” ሲል የልቡን ስቃይ ያዜምልናል። አይገባንም። ወይም እንዲገባን አንወድም!! እውነትም አመመኝ!!
ነገሩ ሁሉ ተቃራኒ ነው። የመታደስ ፍንጭ አይታይም። ውሸቱ አይሏል። ስርቆቱ ጨምሯዋል። እንደ እንቁጣጣሽ በግና ዶሮ ዋጋ ከህደቱ ለከት አጥቷል። የሚልሱትና የሚቀምሱት አጥትው እንደጨለመባቸው ወገኖች ኅሊና የሚባለው የልቡና መብራት ተቃጥሏል፤ ጠፍቷል። ርሃብ ዘር ሳይለይ ወገኖችን እያራገፈ “የእድገት፣ የብልጽግና” ከበሮ ይደለቃል። ኅሊናቸው የቀረናባቸው “ዝናብን መቆጣጠር የቻለ አገር የለም” እያሉ የተላላኪነት ዕድሜያቸውን ያራዝሙብናል።
የአድርባይነት ተምሳሌት ተደርገው የተወሰዱት ገዢዎች የመከርቸሚያውን ሰንሰለት ከማላላት ይልቅ አደድረውታል። ዳክረው ዳክረው “የደኅንነት አገዛዝ” ትግራይ ላይ ተሰብስበው ቸንክረውብናል፤ የደኅንነት ሹሞች የአገዛዙ ቁንጮዎች ሆነዋል። “ባለ ራዕዩ መሪ” የመለመሏቸው የአፈና ማሽኖች “ውርስ ወይም ሞት” ብለው ተነስተዋል። እነርሱ አውራ ሆነው ሌሎችን ጫጩት በማድረግ ቀጥቅጦ ለመግዛት ተቧድነዋል።
ወግ ነውና በአዲስ ዓመት እንዲህ እንላለን። “አውራዎቹ” እጅግ ጥቂት፣ ጫጩቶቹ እጅግ ብዙ ናችውና ያጨለማችሁትን የልቡናችሁን መብራት አብሩት!! ለዕብሪታችሁ ገደብ አድርጉለት፤ ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ የትክክለኛነታችሁ ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት ሳይሆን ምሬትን በአንድ ተጨማሪ ዓመት ማግዘፋችሁ ይታያችሁ፤ ሌሎችም ለአገራቸው የማሰብና አገራቸውን በራሳቸው የሰላም መንገድ የመውደድ መብት ይኑራቸው፤ ምሬት ጥላቻን፤ ጥላቻም በቀልን አርግዞ የግድ መውለድ የለበትም፤ የእርቅና የሰላም ምንቸት ገብቶ የግጭትና የጥላቻ ምንቸት እንዲወጣ ሁሉም ዓይነት መስዋዕትነት ይከፈል!! ኢትዮጵያችንም ትኑርልን። መጪው ትውልድም አገር አልባ አይሁን። ይመርብን።
ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡
<!–
–>
The post የግጭት ምንቸት ውጣ የእርቅና የሰላም ምንቸት ግባ!! appeared first on Medrek.