በይርጋ አበበ (ሰንደቅ ጋዜጣ፣ የካቲት 22/2009)
የደርግን መንግስት በትጥቅ ትግል ጥሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠውና አሁንም ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በ1987 ዓ.ም ዘውጌ ተኮር ከበሬታ የተቸረውን ህገ መንግስት አወጣ። ህገ መንግስቱ በመግቢያው ላይ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መርጠው በላኳቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ያጸደቁ መሆናቸውን ሲል ይገልጸዋል። አሁንም ድረስ በስራ ላይ ያለውና ላለፉት 22 ዓመታትና ከዚያ በላይ ዕድሜ አስቆጥሮ አንድም ጊዜ ያልተሻሻለውን ህገ መንግስት ከረቂቅነቱ ጀምሮ እስከ ማጽደቅ ድረስ ያሉትን ሂደቶችና “የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች” ያደረጓቸውን ውይይቶችና ክርክሮች አቶ አስራት አብርሃም “የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች” ሲሉ በመጽሀፍ መልክ ሰሞኑን ለንባብ አብቅተውታል።
የአቶ አስራት አብርሃምን መጽሀፍ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች ካጸደቁት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጾች ጋር በማነጻጸር ከዚህ በታች በተቀመጠው መልኩ ለመዳሰስ ሞክረናል። መልካም ምንባብ።
የህገ መንግስት ታሪክ በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ረጅም የመንግስት ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም ቃለ መንግስት (ህገ መንግስት) ሳይኖራት ቆይታ በ1923 ዓ.ም የመጀመሪያው ህገ መንግስት በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት መውጣቱን ብዙዎቻችን የምናውቀው ሀቅ ነው። አቶ አስራት አብርሃም ግን ከ1923 ዓ.ም በፊት በኢትዮጵያ መንግስታት የሚመሩበት ህገ መንግስት እንደነበረ ይገልጻሉ። ይህም ህገ መንግስት “ክብረ ነገስት” የሚለው መጽሀፍ መሆኑን በምሳሌ ሲያስቀመጡ “የህገ መንግስት ጽንሰ ሀሳብ በኢትዮጵያ ጥንታዊ መሰረት አለው። ከ1270 ዓ.ም ጀምሮ ዘመናዊ ህገ መንግስት እስከተረቀቀበት 1923 ዓ.ም ድረስ ክብረ ነገስት የሚባለው መጽሀፍ እንደ ህገ መንግስት ሆኖ አገልግሏል። ለዚህ ነው አጼ ዮሀንስ ‘ሀገሬና ህዝቤ ያለ እርሱ አይገዛልኝምና ክብረ ነገስት የተባለው መጽሀፍ በማን እጅ እንዳለ አፈላልገው ይላኩልኝ’ የሚል ደብዳቤ በ1872 ዓ.ም ለእንግሊዙ ሎርድ ግራንቪስ የጻፉት” ሲሉ አገርና ህዝብ በህገ መንግስት ብቻ ይተዳደሩ እንደነበረ የአጼ ዮሐንስን ደብዳቤ በመጥቀስ ይገልጻሉ።
ህገ መንግስት ዓላማው ስለ መንግስታት የስልጣን ምንጭ መግለፅ እና የአስተዳደር ጉዳዮችን በተመለከተ አገርና ህዝብ የሚመሩበት የህግ ሰነድ ነው። ለምሳሌ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የመንግስት ስልጣን ስለሚገኝበት መንገድ ሲገልጽ “በዚህ ህገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው” ሲል በአንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ ሶስት ላይ ይገልጻል። የመንግስት ስልጣን ምንጩም በህዝብ ድምጽ ብቻ መሆኑን እንዲሁ በአንቀጽ 50/3 ይደነግጋል። ከዚህ ውጭ በሆነ መንገድ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ መሞከር ወይ መፈንቅለ መንግስት ነው ወይም ደግሞ በዘመኑ አጠራር “ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ የመንግስት ስልጣን መያዝ” ነው። ይህ ደግሞ ተቀባይነት እንደለሌለው ነው ህገ መንግስቱ የሚገልጸው።
ክብረ ነገስት የሚባለው መጽሀፍም የመንግስታት የስልጣን ምንጭ የትና እንዴት እንደሚገኝ ሲገልጽ “የስልጣን ምንጭ መለኮታዊ ኃይል ሲሆን ይህም በነብዩ ሳሙኤል አማካኝነት ለንጉስ ዳዊትና ለዘሮቹ የሰጠው ቅብዓ ንግስና ነው። የኢትዮጵያ ህጋዊ ገዥነትም የንጉስ ዳዊት ልጅ ከሆነው ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስተ ሳባ ለሚወለደው ምኒልክ ቀዳማዊ ዘሮች እንደሚገባ ይደነግጋል። ከዚህ ውጭ ለሆኑ የነጋሲነት ክብር እንደማይገባ ሲገልጽም እስራኤላዊ ሳይሆኑ መንገስ ህግን መተላለፍ ነው በማለት ነው” ሲሉ አቶ አስራት ክብረ ነገስት የህገ መንግስት ሚና ሲጫወት መቆየቱን በማንሳት የኢትዮጵያን የህገ መንግስት ታሪክ ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ከዘመን ዘመነ የተሸጋገሩት አጼዎችም በዚህ ህግ መሰረት ብቻ ወደ ስልጣን ማማ ላይ መውጣታቸውን ያስታወሱት አቶ አስራት “አጼ ቴዎድሮስ” ብቻ ራሳቸውን “የሰለሞን ዘር” ብለው ሳይመፃደቁ የነገሱ ብቸኛ መሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ለ700 ዓመታት ገደማ አገሪቱ እንደ ህገ መንግስት ስትተዳደርበት የቆየችው ክብረ ነገስት ከ1923 ዓ.ም በኋላ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በወጣው የመጀመሪያው ዘመናዊ ህገ መንግስት ተተክቷል። ከዚያ ጊዜ በኋላም ሶስት ህገ መንግስቶች ስራ ላይ የዋሉ ሲሆን (በ1948፣ በ1978 እና በ1987 ዓ.ም የወጡት) አንድ ህገ መንግስት ደግሞ(በ1966 ዓ.ም) ተረግዞ ገና ሳይወለድ ተጨናግፏል።
የህገ መንግስቶቹ ቅቡልነት
የንጉስ ሰለሞን ዘር ነኝ ሳይሉ የነገሱትን አጼ ቴዎድሮስን ጨምሮ ሁሉም ጦራቸውን ሰብቀው አንደኛውን ባለጊዜ ገልብጠው በተራቸው ባለጊዜ በመሆን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ የነበሩ አጼዎች “ክብረ ነገስትን ተቀብለው ነበር የሚነግሱት” ሲሉ አቶ አስራት ከዘመናዊያኑ ህገ መንግስቶች ይልቅ ክብረ ነገስት በህዝቡም ሆነ በአጼዎቹ ተቀባይነት እንደነበረው ገልጸዋል። “ከክብረ ነገሰት ቀጥለው የወጡት ሁሉም ህገ መንግስቶች ምንም አይነት ተቀባይነት ስላልነበራቸው ያወጧቸው መንግስታት ዕድሜ ሲያበቃ የእነርሱም ዕድሜ አብሮ ሲያበቃ ነው የሚታየው” በማለት ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የህገ መንግስቶቹ ስሪት ህዝብን ለመጥቀም ሳይሆን የመንግስት ስልጣን የያዘውን አካል ስልጣን ለመጠበቅ የሚወጡ አሳሪ ህጎች በመሆናቸው እንደሆነ አቶ አስራት ሲገልጹ “ሁሉም በኢትዮጵያ የወጡ ዘመናዊ ህገ መንግስቶች ያላቸው ግብ ተመሳሳይ ነው። በእጅ የገባን ስልጣን ህጋዊና ዘላቂ ማድረግ ነው” ብለዋል።
የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች ማንነት በአቶ አስራት አብርሃም ምልከታ
ቀደም ሲል በተጠቀሱት ሁለት ንዑሳን ርዕሶች የኢትዮጵያንና የህገ መንግስቶቿን ግንኙነት በአጭሩ ተመልክተናል። ከዚህ ቀጥሎ ባሉት ተከታታይ ክፍሎች ደግሞ ስለ ኢፌዴሪ ህገ መንግስት እና ስለ አስራት አብርሃም ምልከታ የሚመለከተውን ሀሳብ ይሆናል።
አቶ አስራት አብርሃም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ጸድቆ በሰነድ መልክ ተዘጋጅቶ ቃለ መንግስት ሆኖ ለህዝብ ይፋ ከመደረጉ በፊት የነበረውን የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት አስቀምጠዋል። በመጽሃፋቸው “ቀዳሚ ገጽ” (መቅድም) ላይ መጽሃፋቸውን ያዘጋጁት ከ800 ገጾች በላይ ያለውን የህገ መንግስት ጉባኤ የተባለውን መዝገብ በማገላበጥ እንደሆነ ተገልጿል። “የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች”ን ማንነት ሲገልጹም በ1986 ዓ.ም የተቋቋመውና 26 አባላት ያሉት የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አባላት ስራቸውን የሚያከናውኑት በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ሳይሆን ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ በሚመራቸው ሀይል አማካኝነት እንደሆነ አቶ አስራት በመጽሀፋቸው አስፍረዋል። እነዚህን ሀይላትም የህገ መንግስቱ ፈረሰኞች ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ጸሀፊው ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም “የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የተረቀቀው በኢህአዴግ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንደነበር የምንረዳው የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ምስክርነት ስንመለከት ነው። በአርቃቂ ኮሚሽኑ ውስጥ ኢህአዴግ የተወከለው በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እና በአቶ ዳዊት ዮሐንስ ቢሆንም ማታ ማታ በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮቸ ስብሰባ ላይ ሁለቱ ተወካዮች በሚያመጡት ሪፖርት ላይ ተመስርቶ የዕለቱ ውሎ ይገመገማል። ጠንካራና ደካማ ጎኑ ተለይቶ በቀጣይ ውይይቶች ላይ በምን አቅጣጫ መሄድ እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣቸው ነበር” በማለት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ “ዳንዲ የነጋሶ መንገድ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሀፍ ላይ የገለጹትን ሀሳብ በማንሳት ህገ መንግስቱ ሲረቀቅ አቶ መለስ የሚመሩት ፈረሰኛ ቡድን እንደነበረ ገለጸዋል።
አቶ አስራት ከዶክተር ነጋሶ ምስክርነት በዘለለ በራሳቸው መላምት ተነስተው ህገ መንግስቱ ነጻ ሆኖ ያልተረቀቀ ሰነድ መሆኑን ሲገልጹም “የአርቃቂ ኮሚሽኑ የህግ ባለሙያ ሆነው የተሰየሙት ዶክተር ፋሲል ናሆም (የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን ጨምሮን ጨምሮ በ1978 የወጣውን የኢህዴሪንና ስራ ላይ ሳይውል ተጨናግፎ የቀረውን የ1966 ህገ መንግስትን ጨምሮ ያረቀቁ ምሁር ናቸው) ህገ መንግስቱን ያዘጋጁት ከኢህአዴግ ቁልፍ ሰዎች ጋር እየተማከሩ ወይም የፓርቲውን የፖለቲካ ፕሮግራም እየተከተሉ መሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም” ሲሉ ያስቀምጣሉ። ህገ መንግስቱም ስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ ፕሮግራሙን ህገ መንግስታዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ ብዙ ርቀት ሂዷል ብሎ ደፍሮ መናገር የሚቻል ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክሩታል።
የኃይል አሰላለፍ በህገ መንግስቱ መጽደቅ ወቅት
ህገ መንግስት እንደሌሎች አዘቦታዊ ህጎች አይደለም። ሌሎች አዘቦታዊ ህጎች ህገ መንግስቱን ምርኩዝ አድርገው የሚነሱበት ሰነድ በመሆኑ ጠንካራ መሰረት ኖሮት ሊጸድቅ የሚገባ የህግ ሰነድ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ህዝብ ይወክሉኛል ያላቸውን ሰዎች መርጦ ወደ ጉባኤው በመላክ የህዝቡን ሀሳብ ወክለው በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት ይደረግበታል። ጠንካራ ውይይት ከተካሄደበት በኋላም የጉባኤው ሀሳብ ለህዝብ ቀርቦ ህዝቡ ይሁንታ ከሰጠው ህገ መንግስት ሆኖ ይጸድቅና የሁሉም የአገሪቱ ህዝብ የቃል ኪዳን ሰነድ ሆኖ ያገለግላል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚጸድቅበት ወቅት 543 ተወካዮች የተሳተፉበት ቢሆንም “ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኢህአዴግ እና አጋር ደርጅቶች አባላት” መሆናቸውን አቶ አስራት አብርሃም የህገ መንግስቱን ጉባኤ ጠቅሰው አስቀምጠዋል። በዚህም ምክንያት የሀይል አሰላለፉ ወደ አንድ አቅጣጫ ያዘነበለ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ አስራት፤ እንደ ሻለቃ አድማሴ ዘገየ እና አቶ ዳንኤል በላይነህ በግል ከአዲስ አበባ ተወክለው ወደ ጉባኤው ከገቡት ሰዎች ውጭ ሌሎቹ ተመሳሳይ አቋም ብቻ ሲያራምዱ እንደነበረ የጉባኤው ቃለ ጉባኤ ያስረዳል ሲሉ አቶ አስራት ገልጸዋል።
ህገ መንግስቱ በሚጸድቅበት ወቅት በተነሱ መሰረታዊ ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን የሚጠቀሱት አቶ አስራት ሆኖም ሁሉም ነጥቦች በአሸናፊው ሀይል (በኢህአዴግ) የበላይነት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን በመጽሀፋቸው ገልጸዋል። ለአብነት ያህልም በሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ላይ በተነሳው ነጥብ በሶስት ጎራ የተከፈለ እንደነበር አቶ አሰራት አብርሃም ገልጸዋል። አንደኛው ጎራ ቀደም ሲል የነበረው (አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለው) እንዳለ ይቀጥል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ጎራ ደግሞ የተወሰነ ማስተካከያ ይደረግበት የሚል (ምናልባት አሁን ያለው ሊሆን ይችላል) ሲሆን ሶስተኛው ጎራ ደግሞ ፈጽሞ ይቀየር የሚል እንደነበረ ነው ከአቶ አስራት መጽሀፍ ላይ የሰፈረው መረጃ የሚገልጸው።
ሻለቃ አድማሴ ዘገዬ እና አቶ ዳንኤል በላይነህ የተባሉ የአዲስ አበባ ተወካዮች “ባንዲራው የአባቶቻችን ተጋድሎ፣ የኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት የሚያሳይ የታሪክ ምልክት ነው። ከባንዲራው ላይ አንድ ነገር ቢጨመር ወይም ቢቀነስ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያዝንና ህገ መንግስቱንም እንደማይቀበል” አፅንኦት ሰጥተው መከራከራቸውን የገለጹት አቶ አስራት በሌላኛው ጎራ የነበረው የኢህአዴግ እና የአጋሮቹ አቋም ደግሞ “ባንዲራው ለህዝቦች ነጻነት የቆመ ሳይሆን ህዝቦች የታረዱበትና የተጨፈጨፉበት፣ የጭቆና፣ የወረራ፣ የግፍና የብዝበዛ ምልክት ሆኖ ለዘመናት ያገለገለ የገዥ መደቦች የጭቆና መሳሪያ ነው” የሚል እንደነበረ ገልጸዋል። በመጨረሻም የሰንደቅ ዓላማው ይዘትና ቅርጽ በህገ መንግስት አንቀጽ ሶስት በተቀመጠው መልኩ ተወስኖ ጸድቋል (አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት በእኩል መስመር ተቀምጠው መሀሉ ላይ ብሔራዊ አርማ ያለው። ዓርማው የብሔር በሔረሰቦች ህዝቦችና የሀይማኖቶች በእኩልነት በአንደነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ነው ይላል)
የሀገር ግዛት ወሰንን በተመለከተም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ ሁለት “የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል ሆኖ በዓለም አቀፍ ሰምምነቶች መሰረት የተወሰነው ነው” በማለት አስቀምጧል። ይህ አንቀጽ የህገ መንግሰቱ አካል ሆኖ ከመጽደቁ በፊት በተደረጉ ውይይቶች ከኢህአዴግ የተለየ ሀሳብ ሲያራምዱ እንደነበር በአቶ አስራት አብርሃም መጽሀፍ የተጠቀሱት ሻለቃ አድማሴ ዘገየ እና አቶ ዳንኤል በላይ ነህ ሲሆኑ እነሱም “የአንድ አገር ህገ መንግስት ሲቀረጽ አብይ ተግባር የአገሪቱን አንድነት ወሰኗንና የህዝቦቿን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ መሆን እንዳለበት፤ በተቃራኒው ይህ ህገ መንግስት ለዚህ እውቅና የማይሰጥ በመሆኑ እንደማይቀበሉት አመልክተው አባቶቻችንና አያቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አያሌ መስዋእትነት ከፍለው አንድነቷን ጠብቀው ያቆዩአትን አገር ይህ ህገ መንግስት ማስጠበቅ እንዳለበት አስገንዘዋል” ሲሉ አቶ አስራት በመጸሀፋቸው ገልጸዋል። በሌላ በኩል ያለው ሀሳብ ደግሞ ኢህአዴግንና አጋሮቹን ወክለው የሚከራከሩት ሰዎች አሰተያየት ነው።
ለምሳሌ አቶ አባይ ጸሀዬ “ባለፉት ስርዓቶች የነበረው የግዛት ወሰን አከላለልና አመለካከት አንድ ንጉስ ወይም ፊታውራሪ ከእነሰራዊቱ ተንቀሳቅሶ ሊደረስ የቻለበት መሬት ሁሉ እንደነበረ ገልጸው የአሁኑ የግዛት አወሳሰን ግን የአገርን አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆም መበታተንን እና መከፋፈልን የሚያስቀር ሲሆን የዓለም አቀፍ ስምምነቶች መደንገጉም ከአጎራባች አገሮች ጋር ያለው ግንኙነትም በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ስለሚያደርገው በጦርነት ከመፈላለግ የሚያድን ነው” ሲሉ መከራከራቸውን የሚገልጹት አቶ አስራት፤ አቶ ግርማ አዱኛ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ የአቶ አባይ ጸሀዬን ሀሳብ ደግፈው ሲናገሩ “ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማታከብር አገር ስለነበረች ህዝቦቿ ከጎረቤት አገሮች ጋር የነበራቸው ግንኙነት የወንድማማች ሳይሆን በጥርጣሬ የመተያየት ነበረ። ከሶማሊያ ጋር በተካሄደው ጦርነት አያሌ ህዝቦች ያለቁትም በዚህ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ የግዛት ወሰንም ቀይ ባህርን የሚያካልል ነው የሚለው አባባልም አሮጌ ታሪክን ይዞ መንገታገት ነው” ሲሉ የኤርትራን መገንጠልም ሆነ የሶሜሊያ ጦርነት ምክንያቱ ኢትዮጵያ በተጠናወታት የድንበር መግፋት ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን መናገራቸውን የአቶ አስራት አብርሃም መጽሀፍ ያስረዳል።
ከእነዚህ ነጥቦች በተጨማሪም የክልሎች አወቃቀርን፣ የፈዴራል መንግስት የስራ ቋንቋን፣ የመሬት ጉዳይና ስለመገንጠል የሚያተኩሩ የህገ መንግስቱ ክፍሎች ከመጽደቃቸው በፊት እንደተለመደው ሰፊ ክርክር የተደረጉ ቢሆንም በኢህአዴግ አሸናፊነት በመጠናቀቃቸው አሁን ያለውን መልክና ቅርጽ ይዘው ሊወጡ ችለዋል። ለምሳሌ አንቀጽ 39 ላይ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል የሚለው ክፍል ‘መገንጠል’ የሚለው ቃል እንዲገነጠል፣ የክልሎች አወቃቀር በማንነት ላይ ያተኮረ መሆኑ ቀርቶ በአስተዳደር አመቺነት እንዲሆን፣ መሬትም የመንግስት መሆኑ ቀርቶ የህዝብ እንዲሆንና ህዝብ እንደፈለገ እንዲሸጥና እንዲለውጥ መብቱ ሊሰጠው ይገባል የሚሉት የክርክር ሀሳቦች በእነ አቶ ዳንኤል በላይነህና ሻለቃ አድማሴ ዘገዬ በኩል የቀረቡ ነበሩ።
አዝናኝ እውነታዎች በአቶ አስራት አብርሃም መጽሃፍ
የአቶ አስራት አብርሃም መጽሀፍ ከላይ በተቀመጠው መልኩ ጠንከር ጠንከር ያሉ ቁምነገሮችን የያዘ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግን አዝናኝ ሀሳቦች አልታጡበትም። ለምሳሌ የመሬትን ጉዳይ አስመልከቶ ከትግራይ ክልል የተወከሉ ቄስ አለፈ ወልደእዝጊ የተባሉ የኢህአዴግ አባል “በአሁኑ ወቅት በህዝብ ትግል መሬት የሁሉም እንድትሆን በመደረጉ ከዚህ በኋላ መሸጥ መለወጥ ማለት ኢየሱስ ክርስቶስን በ30 ብር እንደተሸጠው ያህል ይቆጠራል” ማለታቸው በቃለ ጉባኤው ሰፍሮ እንደሚገኝ አቶ አስራት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የባንዲራን ጉዳይ በተመለከተ አሁን ያለው የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ አርማ (መሀል ላይ ያለው ኮኮብ) በተመለከተ ራሳቸው አቶ አስራት “በዚህ ምልክት ዙሪያ ብዙ ውዥንብር እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። አንዱ የትግሬ አምባሻ ነው ይላል። ነገር ግን ባንዲራው ላይ ያለው አርማ አምባሻ መጋገር የማትችል ሴት የጋገረችው ካልሆነ በቀር አምባሻ አይመስልም” ሲሉ በባንዲራው ምልክት ዙሪያ የሚሰጠውን አሉባለታ የገለጹበት መንገድ አዝናኝነት ይታይበታል።
“የሀገረ መንግስት ስያሜ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ስር በጻፉት ላይ ደግሞ “የፂም መርዘም ሰውን ፈላስፋ አያደርገውም” የሚለውን የጣሊያኖች አባባል ተጠቅመዋል። ይህን አባባል የተጠቀሙት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ አንድ “የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል” የሚለውን ሀሳብ ለመተቸት የተጠቀሙበት ነው። በዚህ ርዕስ ስር ባሰፈሩት ጽሁፍ አብዛኞቹ አምባገነን መንግስታት ስያሜያቸውን “ዴሞክራሲያዊ እና ሪፐብሊክ” የሚል ተቀጥያ መጨመራቸው ፂምን አሳድጎ ፈላስፋ ለመባል ከሚደረግ ከንቱ ሙከራ ጋር አገናኝተውታል። ይህን ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም በአንድ ወቅት አስመራ ውስጥ ከአንድ ጣሊያናዊ ቤት ተቀጥራ ትሰራ የነበረች አንዲት የትግሬ ኮረዳ ጣሊያናዊው ውሻውን “አሉላ” የሚል ስም ስለሰጠው ትበሳጭና አንድ ቀን ትገድለዋለች። ጣሊያኑ መጥቶ ውሻው ምን ሆኖ ሞተ ቢላት “ስሙ ከብዶት” ብላ እንደመለሰችለት ያስታወሱት አቶ አስራት የኢትዮጵያ መንግስትም አሉላ ሳይሆን አሉላ ነኝ ማለቱ (ዴሞክራሲን ሳይላበስ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም መጠራቱ) ስሙ ከብዶት እንዳይሞት ስጋታቸውን የገለጹበት ክፍልም አዝናኝነት ይታይበታል።