የጎሕ መመስረት ምክንያቱ ወያኔ ለዘመናት አብሮ በፍቅር የኖረውን የቅማንትና የአማራ ወገናችንን ለእኩይ ተግባሩ ማሳኪያ አመች እንዲሆንለት በቦታ መካለል ምክንያት እራሱ ግፊት በማድረግ እርስበርስ ለማጫረስ የዘረጋው ተንኮል እንደሆነ ማስታወስ እንወዳለን። የጎሕ መመስረት ባስተላለፋቸው ይድረስ ለጎንደር ሕዝብ መግለጫወቹ የወያኔን እኩይ እንቅስቃሴ አክሽፎ ሕዝባችን የኖረ የአንድነት መሰረቱን ለማስከበር እንዲችል አብይ ሚና ተጫውቷል።
ለሱዳን ተቆርሶ ሊሰጥ የታቀደው ሰፊ የኢትዮጵያ መሬት፤ የጎንደር ክ/ሀገር ለም መሬቶች (ሁመራ፤ ቃፍትያ፤ ወልቃይት፤ ጠገዴ) በወያኔ እጅ ስር መውደቃቸው፤ ሕዝቡ በዚህ ምክንያት የደረሰበት ግድያ ስደትና መከራ፤ ወያኔ ከዚህ በበለጠም በስሜን በኩል ታላቁን ራስ ዳሸንን፤ በምዕራብ በኩል እስከ ዐባይ ግድብ ለመስፋፋትና ጎንደርን ከካርታ ውጭ ለማድረግ ልዩ የተንኮል ስልት ይዞ መምጣቱን ስንገነዘብ ዝም ብለን ልንቀመጥ አልቻልንም። ጎሕ የዕነዚህ ሁሉ ግፎች ክምችት የፈጠረው መሆኑና ዓላማውና ተግባሩም የጎንደር ሕዝብ ከነዚህ ሁሉ ችግሮች ተላቆ በግፍ ያጣቸውን እሴቶቹን መልሶ እንዲያገኝ ካለፉት ሶስት አመታት ጀምሮ በሰፊው እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።
የኢትዮጵያን ሕዝብ እያስደመመ የሚገኘውን ህዝባዊ እምቢተኝነት እያፋፋመ ከሚገኘው ጀግናው የጎንደር ወጣት ጎን በመቆም የትግል አጋር እንድትሆኑ በአለም ዙሪያ ለምትገኙ የጎንደሬ ወጣቶችም ሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ሃምሌ 5 2008 ዓ.ም. በጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከተለኮሰው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጀምሮ እስከ ሃምሌ 24 2008 ዓ.ም. የተደገመው አስደማሚ ታላቅ ሰልፍ የኢትዮጵያውያንን የትግል ስሜት እጅጉን እንዳነሳሳው የታወቀ ነው። ከዛ በኋላም ተከታታይ የሁኑ ወያኔን መፈናፈኛ ያሳጡ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። ለዚህ ሁሉ የትግል ፍሬ ያበቁንን መተኪያ የሌላትን ህይወታቸውን ሰውተው ያለፉትን ጀግናዎች እኛ የጎንደር ወጣቶች መቼም አንረሳቸውም። እነሱን በማጣታችን ልባችን በሃዘንና በቁጭት ይቃጠላል። ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ከመቸውም በበለጠ በቆራጥነት ተነሳስተናል። ይህን ክቡር ህይወታቸውን የሰውለትን ዓላማ ለማሳካት ከጠላት ወያኔ ጋር ሌት ተቀን እየተፋለሙ ያሉ ወጣቶችን ሙሉ ድጋፍ ልናደርግላቸው ግድ ይላል።
ስለሆነም ለጎንደሬ ወጣቶች በሙሉ ኑ! በጎንደር ሕብረት ጥላ ስር የወጣቶች ክንፍ ተሰባስበን የትግል አጋርነታችንን እናሳይ። በህዝባችን ላይ ሙሉ ጦርነት የከፈተውን ወያኔን የተጋፈጡትን ወጣቶች አጋር እንሁናቸው። የእኛ ሁለገብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። በዚህ ወቅት ወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብሎ አውጆ በተለይ ደግሞ በጎንደርና በጎጃም አካባቢ ድርብ ቀይ መስመር አስምሮ ወጣቶችን በጅምላ እያሰረ ይገኛል። ብዙ ወጣቶችም ዱር ቤቴ ብለው ከገበሬው ህዝባችን ጎን በመሰለፍ ከጠላት ጋር የመረረ ትግል ውስጥ ገብተዋል።
“አማራ ጠላቴ ነው” ብሎ ኢትዮጵያዊ ወኔ ያለውን የዐማራን ዘር ለማጥፋት የመጣውን ዘረኛ የወያኔ ቡድን አመችና አስፈላጊ በሆነው መልኩ እየተደራጀን ልንመክተው ብሎም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ልናስወግደው ይገባል። በወያኔ ልዮ የግፍ አገዛዝ ሥር የሚገኙትን የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ወገኖቻችንን ልንታደጋቸው የምንችለው የጎንደር ወጣቶች ይበልጥ ተጠናክረን ስንደራጅ ነው። ከዚህም አልፈን ወልቃይት ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ! የወልቃይት መሬት የጎንደር ሕዝቡም አማራ ነው! በማለት እጅግ የሚያስመካ ተጋድሎ እያደረገ ካለው የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ ወገናችን ጋር ይበልጥ አብረን እየተደራጀን ወደ ድል እንጓዛለን።
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረቱም አመራሩም አገር ቤት ያለው ህዝባችን እንደሆነ እያስገነዘበ በውጭ ሃገራት የምንኖር የዚህ ጀግና ልጆችም አጋርነታችንን እስከ ህይወት መስዋእትነት እንደምንቀጥል ወዳጅም ጠላትም ይወቀው። ወያኔ የሽብር አዋጅ ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የጎንደር ወረዳ ከተሞች ላይ ወጣቱ ላይ ያነጣጠረ ተከታታይ የጅምላ እስር እየተካሄደ ነው። ለአብነትም በደባርቅ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ላይና ታች አርማጭሆ፣ በጭልጋ፣ በመተማና ቋራ፣ በደልጊ፣ በበለሳ፣ በደንቢያና በደብረታቦር አካባቢዎች እስርና ወከባው በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል። ይህ ግን የህዝባችንን ቁጣ አባባሰው እንጅ የነፃነቱን ፍላጎት ሊያዳፍነው አልቻለም። ጎንደር ወያኔን አንቅሮ የተፋው ከጥዋቱ ነው። አሁን ደግሞ መቀበሪያውን እየቆፈረለት ነው።
በጠነከረ መሰረት ላይ የተደራጀው የጎንደር ሕብረት የወጣቶች ግብረሃይል በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያና ኒውዝላንድ፣ እስራኤል፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የተቋቋሙትንም ሆነ እየተመሰረቱ ያሉትን አጋር የድጋፍ ማህበራት ይበልጥ አጠናክሮ ለጎንደር ወጣት ላቅ ያለ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል። ስለሆነም በዓለም ዙሪያ ለምትኖሩ የጎንደር ወጣቶች በሙሉ ለህይወታቸው ሳይሳሱ ለነፃነታቸው በክብር መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን ወጣቶች አርማ አንስተን ከጎናቸው እንድንቆም ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ደጉ እና ሰላም ወዳዱ የጎንደር ወገናችን ተገዶ የገባበት ጦርነት እረፍት ይነሳናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ትግል በያለበት እንዲያፋፍም በየግንባሩ ያሉ ወገኖቻችን ጮክ ብለው ጥሪ እያቀረቡ ስለሆነ ለጥሪው ምላሽ ዛሬውኑ መስጠት አለብን።
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት አላማው፦
የክፍለሀገሩን ተወላጆች ያሰባሰበ፤ ለህዝቡ ደህንነትና ታሪካዊ አንድነት ጠበቃ ሆኖ የሚከራከር፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ እና በተለይ በጎንደር ክፍለሀገር፤ የሰፈነው የዘር ሥርዓት ተወግዶ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን አጋር ሆኖ የሚታገል ድርጅት ነው።
የጎንደር ሕብረት ተግባራት መካከል፦
• በመላው አለም የሚገኙ የጎንደር ክፍለሀገር ተወላጆችን ማደራጀት
• የሚሰራውን ግፍ ሰባአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንዲያውቁት ማድረግ።
• በዓለም ደረጃ ዘረኛውንና ተስፋፊውን ምንነት/ማንነት ለማጋለጥ፤የቅስቀሳ ስራዎችን ማካሄድ።
የመረጃ ማሰባሰብና ማሰራጨት ስራዎችን ማከናወን።
በአጠቃላይ በሀገራችን በተለይ በክፍለሀገራችን ለፍትህ የሚደረገውን ትግል ድጋፍ መስጠት።
ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው ወያኔ በህዝብ ትብብር ይወድማል!
ኢትዮጵያ ሃገራችን በክብር ለዘላለሙ ትኑ
የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የወጣቶች ግብረ ሃይል!