የሩስያ ኮሚኒስት አምባገነኖች ሕዝቡን ሰንገው በሚገዙበት ዘመን፤ አንድ ስመጥር ፈረንሳዊ ደራሲ ወደ ሞስኮ ጎራ ይላል፡፡ በጊዜው የመንግሥት ታጣቂዎች ተቃዋሚዎችን በማፈንና በመግደል ተጠምደው በማየቱ አዝኖ ቅሬታውን ላንድ ካድሬ ገለጸ፡፡ ካድሬው ቅሬታውን ከሰማ በኋላ “እንቁላል ፍርፍር ለመሥራት ከፈለግህ እንቁላሉን መስበር አለብህ” ብሎ ተፈላሰፈ፡፡ ደራሲው የዋዛ ስላልነበረ እንዲህ ብሎ መለሰት፤ “እዚህም እዚያም የእንቁላል ስብርባሪ ይታየኛል፡፡ ግን ፍርፍሩ የታል?”
እስከቅርብ ጊዜ ስንሰማው የነበረው፤ “ዲሞክራሲን ቸል ያልነው ቅድሚያ ሕዝቡን ዳቦ ለመመገብ ነው” የሚለው መከራከርያ ውሃ በልቶታል፡፡ ዳቦውም ሆነ ዲሞክራሲውም ገደል ገብቷል፡፡
የምለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ በሀገሪቱ በየቦታው እየተፈጸመ ያለውን ግድያ በጊዜ አቁሙ! ገባሩ ህዝብ የሚላችሁን ስሙ፡፡ ስለ “ዘለቄታዊ ልማት” ለማሰብም እኮ ዘላቂ አገር መኖር አለበት፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ ባንድ ወቅት “ሕዝብ ከሸፈተ ሠራዊት አያቆመውም” ብሎ ተናግሯል፡፡ መለስ በሕይወት ዘመኑ ከተናገራቸው በጣም ጥቂት እውነቶች አንዱ ይህ ይመስለኛል፡፡ እናም፤ የሸፈተን ማኅበረሰብ ከመቆጣጠር ይልቅ ሰላማዊውን ሰልፈኛ በጸጥታ ማስከበር ስም በጠራራ ጸሀይ ፤ባደባባይ የሚደፉ ፖሊሶችን መቆጣጠር ይበጃል እላለሁ፡፡
ሕዝብን ሁሌ በጭራ እንደሚበረግግ ዝንብ ኣድርገው ለሚቆጥሩት ጌቶች፤ ያለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን ግጥም ጋብዤ ልሰናበት፤
“ተርብም ዝንብ ይመስላል የማይናደፍ
እስኪቆሰቁሱት፤ በሌባ ጣት ጫፍ፡፡”
Bewketu Seyoum
<!–
–>
The post “ሕዝብ ከሸፈተ ሠራዊት አያቆመውም” መለስ ዜናዊ appeared first on Medrek.