Quantcast
Channel: Amharic News – Medrek
Viewing all 2265 articles
Browse latest View live
↧

ለኦዚው አገር  መንገደኛ  ለአቶ ኤፍሬም የምላቸው አለኝ። (ደምሳቸው ንጋቱ)

$
0
0

ከደምሳቸው ንጋቱ

ኤፍሬም ማዴቦ

የመንገደኛው ጋዜጠኛን መሰሉ የአቶ ማዴቦን ጽሁፍ በወርድ በቁመቱ ወረድኩበት።የኦዚን አገር ከእግር እስከራሱ እንደሄዱበት ነገሩን። ያጻጻፋቸው ይትባህልና አጀማመር ሊሰነዝሩልን የፈለጉት መልእክት  ማዋዣነት የተጠቀሙበት ስለመሆኑ ማሳበቁ አልቀረም።  እርግጥ ነው ሊሰብኩን ለተነሱበት ጭብጥም ስለኦዚ የጠቃቀሱት  በማጠናከሪያነት የረዳቸው አይመስልም።  ስለኦዚ መልክአምድርና የትዬለሌነቷን ከሚነግሩን የተሻለ ሊሉት የሚገባውና በፓለቲካውም ሊያግዛቸው ይችል የነበረ ጉዳይ  አለ ። አውስትራሊያ የመድብለ ባህል /MULTICULTURALISM/ የተሳካባት ቁንጮ ምእራባዊ አገር ነች ። የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፤ የሰዎች ባህል ቋንቋና እምነት የተከበረባት የተለያዩ ብሄረሰቦችን ቁጥር ሳይጨምር ከ224 አገሮች በላይ ዜጎች ተከባብረውና በጋራ የሕግ ጥላ ሥር የሚኖሮባት እድልኛ አገር በመባል ትታወቃለች። ብዙም ብዙም በጋራ የመኖርን ፋይዳና አንድነትን ለማጉላት የሚበጅ ታሪክ ያላት አገር ነች። ስለመጀመሪያዎቹ የእንግሊዝ ሰፋሪዎች ከሚያወሱልን ይልቅ  ይሄ ሚዛን ይደፋ ነበር ለማለት ነው። ጽሆፎ ከኦዚ አገር ስለተነሳ እኔም ከዚያው ልጀምር ብዬ ነው።

አቶ ኤፍሬም ለመሆኑ «በመስታወት ቤት ውስጥ የተከበበ ሰው ድንጋይ ለመወርወር የመጀመሪያ መሆን የለበትምን»  ሰምተው አያውቁም። ለመሆኑ የአእምሮ በሽታ ማለት ምን ይሆን? መገለጫዎቹ ምንድናቸው? ደግሞስ « አትግደሉኝ፤ካገሬ አታፈናቅሉኝ» ያለ አማራ እራሱን ሊከላከል ቢደራጅ እርሶን ለምን ሆዶን ቆረጦት። አዩ የእርሶ ድርጅት አሁንም ወረቀት ከመበተን እንኳን አላለፈም። ብዙዎቻችን የእርሶን ድርጅት ተስፋ አድርገን በምንችለው አቅም ረዳን ። የተፈጠረላችሁን መልክማ አጋጣሚ አለመጠመቀማችሁ ብቻ ሳይሆን ስንት የስልት ግድፈት ፈጸማችሁ። የአንድነት ሃይሎች ቢሳካላቸው አማራው ይጠላል የሚል የተዛባ አመለካከት አሎት ብዬ ለመገመት ያዳግተኛል። ለዚህም ሲባል አማራው ከጥንት እስከዛሬ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል። ይሁን እንጂ በእናንተ በኩል እንኳን ቆሞ የሚሄድ ዳዴ የሚል ነገር እንኳን ማየት ህልም ሆነ። ስለሆነም የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ሆነና  አማራው ያልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል ጀመረ። ይሄ ደግሞ እሰየው ያሰኛል እንጂ ለአካኪ ዘራፍ ምክኒያት አይሆንም። ምክኒያቱም አማራው ባንዲራው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አገሩ አንድ ኢትዮጵያ መሆኗን ሙጥኝ ያለ ከዚህ ውጭ በምንም የማይጠረጠር ሕዝብ ነው።

ደጋጎቹና ጨዋዎቹ የአማራ ዘመዶቼ የኑሮ መመሪያ ሲሰጡኝ እንዲህ ነበር ያሉት« ሰውን አልፈህ ተርፈህ መብቱንና ማንነቱን አትጋፋ። ማንም ይሁን ማን አክብር ። ካለህ ላይ ለማካፈል አትቦዝን። ድንበር አልፎ አሻፈረኝ ብሎ እምቦር እምቦር ያለ እንደሆን ግን በለው ነበር።» ያሉኝ። አያይዘውም ከባለጌ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ አትግባ  ምክኒያቱም ወደ እሱ ደረጃ ትወርዳለህና» አስተያየቴ ከዚህ መርህ ጋር እጅና ጓንት እንዲሆን የተቻለኝን ጥንቃቄ ወስጃለሁ።

አቶ ኤፍሬም እናንተ እኮ አማራው ሲፈናቀል ሲጨፈጨፍ አንድ ጠንከር ያለ መግለጫ እንኳን እኮ ነው የነፈጋችሁት። ለምን?« ከቀድሞው ጨቋኝ » ጋር አበራችሁ እንዳትባሉ የፓለቲካ ስልት ብጤ መሆኑ ነው። ከእናንተ ይልቅ የጀነራል ከማል ገልቹ ድርጅት የአማራውን ከጉራፈርዳ መፈናቀል በተመለከተ ለአብነት የሚጠቀስ ጠብሰቅ ያለ መግለጫ አውጥቷል።

ብዙ ጊዜ ድርጅቶዎ ከሚመልሳቸው ጥያቄዎች ይልቅ የሚፈጥረው ጥያቄ ይበልጣል። የምትፈጽሙት ያሰራርና የፓለቲካ ስህተት ደግሞ እጅግ ብዙ ነው። ለመሆኑ ለምታደርጉት ነገር ፓሊሲና መመሪያ የሚባል ነገር አላችሁ ወይንስ እንደመጣላችሁ ነው የምትሰሩት? ይሄን ያልኩት ያለምክኒያት አይደለም። ለምሳሌ የአቶ አንዳርጋቸው ወያኔ እጅ ውስጥ መውደቅና በወቅቱ አድበስብሳችሁ ያለፋችሁት ጉዳይ ምን ያህል እርጥብ ፓለቲከኞች መሆናችሁን የሚያሳብቅ ጉዳይ ነው። የድርጅታችሁን ቁንጮ መሪ በወቅቱ ከሁላችሁም የተሻለ ይንቀሳቀሱ የነበሩትን ሰው በየመን ተጉዘው ለትግሬ ወያኔ ገጸበረከት አደረጋችሃቸው። እራሳችሁን የማትጠብቁ እንዴት ለሌላው ትተርፋላችሁ?አቶ አበበ ገላው በቅርቡ በከተበው የእንጊሊዝኛ መጣጥፉ ላይ በአቶ አበበ ቦጋለና በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መካከል በየመን በኩል መሄድና አለመሄድን አስመልክቶ  ሃሳብ ተለዋውጠው እንደነበር አስነብቦናል። ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘም የወያኔዎች አንዱ ቱባ ባለስልጣንና አሁን የአለም አቀፍየጤና ድርጅት ዳይሬክተር የሆነው ሲሳለቅባችሁ « እንዴት እሳቸው(አቶ አንዳርጋቸውን ማለቱ ነው)የደህንነት መ/ቤታችን እንደሚከታተላቸው እያወቁ አለመጠንቀቃቸው ይገርማል» ማለቱም ይታወሳል። ለመሆኑ የመሪዎቻችሁን ደህንነትና እንቅስቃሴ የሚገዛ ፓሊሲና ለድርድር የማይቀርብ መመሪያ የላችሁም? ወይንስ ግለሰቦች በየፊናቻው ነው ያሻቸውን የሚያደርጉት? አቶ አንዳርጋቸው በተያዙ ሰሞንም እጅ እግር የሌለው መግለጫ የሰጡትም የኦዚው አገር ጎብኚ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ እርሶ ነበሩ።

ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅምና እርሶዎ በተለያየ አጋጣሚ አማራውን ለመተናኮል አለመቦዘኖን የሚያሳይ ብዙ የጽሁፍ መረጃ አስቀርተውልናል። ለነገሩማ ሃጼ ምኒሊክንም ተችተዋል። ሞት ሰውን ሁሉ እኩል ያደርጋል አሉ። ምኒሊክ በአቶ ኤፍሬም አፍ መተቸታቸው  ይገርማል።

ሳይቸግሮት ተናግረው እኔንም አናገሩኝ። የቤት ስራዎንም በደንብ ሳይሰሩ ቀርተው በእርሶ ቤት ጥቂት አማሮች ብቻ ውርውር የሚሉ አስመስለው ለማቅረብም ሞክረዋል። አዩ አማሮች ታጋሾች እንጂ ተላላዎች አይደሉም። እንዴት አብረውት የኖሩትን  ሕዝብ እንኳን በቅጡ አያውቁም። ይታዮት  ነገሮች ምን ያህል እያመለጧችሁ እንደሄዱ? እንኳን ሁኔታዎች ላይ ተጽእኖ ልታሳርፉ ይቅርና ክስተቶችን ለመረዳት እንኳን አቅም እንዳጣችሁ ያሳያል።

እንቆቅልሹ እንገነጠላለን ፤ኢትዮጵያ ለ እኛ ምናችን ነች ወዘተ ከሚሉት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከወያኔ ጋር ህግ ካረቀቁት የነ ሌንጮ ድርጅት ኦነግና ኦብነግ እና መሰል ድርጅቶች  ጋር ግንባር እንፍጠር እያላችሁ እየተፋራረማችሁ ስታበቁ አማራን ማውገዛችሁ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንደተባለላት ሴት ሆናችሁ። አዎ አማራ የእናንተ ባጣ ቆየኝ አይደል።

ነገሬን ከእርሶ ጋር ገና አልቋጨሁም።  በናንተ የስልት ጉድለትና ጉራ ወይም ዲሲፕሊን እጦት በተለይ የድርጅቶ መሪ «ወያኔን የምናሸንፈው እዚያው ጉያው ሥር ሆነን» ነው እያለ ባንድ ወቅት ደጋግሞ መግለጫ በመስጠትና ለወያኔዎች ፍንጭ በመስጠት  በመንግስት ግልበጣ ስም ትግሉን ዛሬ ለማጦዝ ይረዱ የነበሩ የአማራ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እስር ቤት እንዲማቅቁ ያደረጋችሁ እናንተ አይደላችሁም? ወጣቷ ንግስት ይርጋ «አማራ አሸባሪ አይደለም» የሚል ካናቴራ ለብሳ በመውጣቷ በእናንተ ድርጅት ስም አይደል የተከሰሰችው?  እረ ስንቱን ልጥቀስ። ተግባር አልባ በሆነው ስማችሁ ብቻ ስንቱን ለክፉ ቀን የሚሆን ታጋይ በተለይ አማራ አስለቀማችሁት።

ከሁሉ የሚገርመው ለእናቷ ምጥ አስተማረች እንዲሉ አቶ ኤፍሬም ለአማራው ስለአንድነትና ስለኢትዮጵያዊነት ለመስበክ መሞከራቸው ነው። ነገሩ ወዲህ ነው እናንተ በኢትዮጵያ ስም ከላይ ሆናችሁ ልትዘውሩ አማራው የእናንተ ጠመንጃ አንጋች ሊሆንላችሁ ሞኛችሁን ፈልጉ!ከሁሉም ግራ የሚገባው ለጣሊያኖች ወይም ለአረቦች የምትሰብኩ  ይመስል በኢትዮጵያዊነት ነው መሰባሰብ የምትሉት ቋንቋ ነው። ወያኔዎች ኢትዮጵያን በዘር ሸንሽነው አንዱን ባንዱ ላይ እያዘመቱ በተለይም አማራውን ኢላማ አድርገው ሲፈጁት የአንድነት ሀይል የሚባል በሌለበት ምድር እጁን አጣምሮ ይለቅ ብላችሁ ነው ክርክራችሁ። ወይንስ እናንተ ሃይል እስክትፈጥሩ  ጦር እስክታደራጁ ሌላ 26 አመታት ቢፈጅም ጠብቁን ነው ሙግታችሁ። የትኛው ቋንቋ ነው ያልገባችሁ ? አማራው ያልሞት ባይ ተጋዳይነት መብት አለው እራሱን ለመከላከልም ብቃት አለው ስትባሉ ለምን ያዙኝ ልቀቅን ትላላችሁ?

እርሶ መቼም ጉደኛ ኖት! የትልቅነት ትምክህትም ተጠናውቷችሃል ነገር ነው ያሉት? አዩ የገጠጠውን ገሃድ መካድ ነው የጤና ማጣት ምልክት። ለመሆኑ ሕዝብ ብዛት የኢኮኖሚ፤ የመከላከያና የፈጠራ አቅም ሊያዳጉስ እንደሚችል ለመረዳት ልዬ ጠበብት መሆንን ይጠይቃል? በየትኛው ቀመር ሲሰላ ነው 2 ሚሊዮንና 40 ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ የሚያመርቱት እኩል የሚሆነው? ይሄ እኮ የስሜት ጉዳይ ሳይሆን የሚዳሰስ የሚጨበጥ እውነታ ነው።

ምንም ውስጥ የሌሉበት አፈር ገፊ አማሮች በዘረኞች ጥይት ሲታጨዱ። አለም በቃኝ ብለው የመነኑ መነኩሳት አይናቸው እየታሰረ ገደል ሲጣሉ። ለአመታት ያፈሩትን ንብረት ባንድ ሌሊት ተነጥቀው እንዳልባሌ ሲባረሩ  ቆርቁሮን ብንነሳና «እህት ወንድሞቻችን አትንኩ በአገራቸው በሰላም ይኑሩ» ብለን ድምጻችንን ብናሰማ የእእምሮ በሽተኛ ብለው ጸያፍ ስድብ ለምን ይሳደባሉ?   ወያኔ እኮ ያጠቃው ሌላውንም ብሄረሰብ ማለትም አማራውንም ፤ከንባታውንም፤ጉራጌውንም ኦሮሞውንም ነው ይባል ይሆናል። አማራው በተጎዳበት መጠንና አይነት ግን ማንም ላይ አልደረሰም። ይሄ ደግሞ አሉባልታ ሳይሆን በጥናት የተደገፈ በአሃዝና በአይነት የተመዘገበ በዳጎሰ መድብል የተጠረዘ መረጃ ያለው ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያዊነት እንደሚሉን የሚቆረቆሩ ቢሆንማ ኖሮ በአማራው ላይ ወንጀል ሲፈጸም «ወንድም እህቶቻችንን አትንኩ በክፉም በደጉም አብረን የኖርን ነን። ጥቃታቸው ጥቃታችን ነው» ብለው ከፊት ቀድሞው ሌላውን ኢትዮጵያዊ አስተባብረው የበሰለ ስራ አሳይተውን ቢሆን ኖሮ እራስን ለማዳን ወደ ተፈጥሯዊ ትግል ባላመራንም ነበር። ሞታችን ሞታችሁ ካልሆነ ስቃያችን ስቃያችሁ ካልሆነ የራሳችንን ችግር በራሳችን ከመጋፈጥ ውጭ ምን አማራጭ አለን?

ከእርሶ አጻጻፍ ምንም ሊጨበጥልኝ  ያልቻለው ሌላው ሃሳብ «የእኔ የግሌ አስተያየት» የሚለው ሃረግ ነው። አቶ ኤፍሬም አርበኛ ሆነው ወደ ኦዚ አገር ባይሄዱና ቱሪስት ሆነው ሄደው ቢሆን ኖሮ የጻፉት የእኔንም ጊዜና  የብእር ቀለሜን ይቆጥብልኝ ነበር።

የአማራውን መደራጀት ጉዳይ ለአማራው ቢተውለት ለርሶም ስራዎን ያቀልሎታል። በሌላ በኩልም የሚያነቡት መጽሃፍ ቅዱስም «አትፍረድ ይፈረድብሃል» ይል የለ።

↧

ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች! – ስዩም ተሾመ

$
0
0
ስዩም ተሾመ

ስዩም ተሾመ

ሁለት ቴዲዎች ባለፉት ሳምንታት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ሰንብተዋል። በእርግጥ ሁለቱም በየፊናቸው ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል። ከዚያ በስተጀርባ ግን በሁለቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብዙ ነገር ይጠቁማል።

በመጀመሪያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሁለቱም ቴዲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሁለቱም ወገኖች ለድጋፍና ተቃውሟቸው የራሳቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል። ነገር ግን፣ ከሁለቱ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሲነሱ የነበሩት ሃሳቦች በዋናነት “ኢትዮጲያ” በሚለው ጭብጥ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ።

 

እንደ ማንኛውም እውቅ ሙዚቀኛ በተለይ “ኢትዮጲያ” በሚለው ነጠላ ዜማ እንደወጣ ሌላው ቴድሮስ (ፀጋዬ) የሰነዘረው ሂስና ትችት ከዘፈኑና ዘፋኙ አልፎ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን አሳዝኗል፥ አስቆጥቷል። ከዚያ በተረፈ፣ ዘፋኙ የለቀቀው አልበም ተደማጭነት እንዳያገኝ ወይም ለአድማጭ ተደራሽ እንዳይሆን “በገበያ ላይ መቅረብ የለበትም” የሚል ተቃውሞ አልገጠመውም። ከዚያ ይልቅ፣ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ትኩረታቸው “አርቲስቱ ከብዙሃንነት ይልቅ የአህዳዊ አንድነት አቀንቃኝ ነው” የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ከአርቲስቱ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ በኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት – ኢብኮ (EBC) እንዳይቀርብ ታገደ። ስለ “ኢትዮጲያ” በመዝፈኑ አርቲስቱን “የአንድነት አቀንቃኝ ነው” በሚል ቃለ-ምልልሱ የሕዝብ ንብረት በሆነው ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይቀርብ ሲከለከል የፖለቲካችን ሕመም አገረሸ። በውሳኔው የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎች ክፉኛ ሲቆጡ፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ በጣም ተደሰቱ።

የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኢብኮ እንዳይተላለፍ በታገደበት ሳምንት ሌላኛው ቴድሮስ (ዶ/ር) “ኢትዮጲያን” ወክሎ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ሆኖ ለመመረጥ የመጨረሻውን ጥረት እያደረገ ነበር። በአንድ በኩል የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ዶ/ር ቴድሮስን በመደገፍ የዓለም-አቀፉ ድርጅት መሪ ሆኖ እንዲመረጥ ድጋፍና ቅስቀሳቸውን አጠናከረው ቀጠሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ተቃዉሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ከሁለቱም ወገኖች ምርጫው በሚካሄድበት ቦታ በአካል ተገኝተው ያሳዩት ድጋፍና ተቃውሞን እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ደጋፊዎች ለራሳቸው የብዙሃንነት አቀንቃኝ ሆነው የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን “የአንድነት አቀንቃኞች” እያሉ ሲያብጠለጥሏቸው ነበር። ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተርነት የሚደረገው ውድድር ሊጠናቀቅ ሲቃረብና በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የሚካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲሄድ በአብዛኛው “የብዙሃንነት አቀንቃኝ” የነበሩት ደጋፊዎቹ ስለ አንድነት ማቀንቀን ጀመሩ። በዚህም “ዶ/ር ቴድሮስ እየተወዳደረ ያለው እንደ ግለሰብ ወይም መንግስት ሳይሆን ኢትዮጲያ እና አፍሪካን ወክሎ እንደመሆኑ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኢትዮጲያዊ ድጋፉን ሊቸራቸው ይገባል” የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀረቡ። ቀድሞ የአንድነት አቀንቃኝ የነበሩት አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ደግሞ “ስለ አንድነት ሲባል ዶ/ር ቴድሮስ ከፍተኛ አመራር ከሆኑበት የኢህአዴግ መንግስት ጋር ያለንን ቅራኔና ልዩነት መተው አይቻለንም” በሚል ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በዚህም የኢትዮጲያ ፖለቲካ ሕመሙ በጣም እንደፀናበት መገንዘብ ይቻላል።

አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጲያ አንድነት ይልቅ ብዙሃንነትን በማስቀደም የሁላችንም በሆነ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቃለ-ምልልሱ እንዳይተላለፍ አደረጉ። በተመሣሣይ፣ አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ተቃዋሚዎች ከአንድነት ይልቅ የፖለቲካ ልዩነትን በማስቀደም የዓለም-አቀፍ ድርጅት መሪ እንዳይሆን ተቃወሙ። ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ቴዲዎች በየፊናቸው ስኬታማ ሆነዋል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ተነስታ የወደቀችው ኢትዮጲያ ናት። ኢትዮጲያ ውስጥ እየኖረ ስለ ሀገር አንድነት ሲዜም የሚቀፋቸው በአንድ ወገን፣ ስለ ኢትዮጲያ አንድነት እያዜሙ የኢትዮጲያን ተወካይ የሆነ ተወዳዳሪ የሚቃወሙ በሌላ ወገን ሆነው አንዱ ሌላውን ሲጠላና ሲያጥላላ በመሃል ግራ ተጋብታ መሄጃ የጠፋት ኢትዮጲያ ናት።

“ኢትዮጲያ” በሚለው አልበም ዙሪያ ከትችትና ተቃውሞ ባለፈ ቃለ-ምልልሱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ ቢታገድም ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሥራው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። ስለዚህ፣ ቴድሮስ አሸንፏል! ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን ያደረገው ውድድር ምንም ያህል ተቃውሞ ቢገጥመው በምርጫው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። አሁንም ቴድሮስ አሸንፏል። በሁለቱም አጋጣሚዎች የታየው በቂምና ጥላቻ የታጨቀ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ “አንድነት” የሚለውን ቃል ትርጉምና ፋይዳ አሳጥቶታል። በአጠቃላይ፣ ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!!!

↧
↧

ህወሃት የብዓላ ወረዳን ወደ ትግራይ ለማካለል እየተንቀሳቀሰ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ገለጹ

$
0
0

ኢሳት ዜና :- በአፋር ክልል የምትገኘውን የብዓላ ወረዳን ወደ ትግራይ ክልል ለማካለል ሕወሃት የልዩ ወረዳ መብት እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቧል። የወረዳዋ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ነባር ነዋሪ የሆኑትን የአፋር ብሄር ተወላጆች በማግለል የስልጣን እና የሃብት ቅርምቱን በበላይነት ተቆጣጥረዋል።

ባለፉት 26 ዓመታት ውስጥ በክልሉ በተለይም በጨው ምርታቸው በሚታወቁት አፍዴራ፣ ዳሉል፣ ኤርታአሌ፣ ፖታሽ፣ የኮናባ የወርቅና ማእድን ማውጫ ቦታዎች በህወሃት ባለሃብቶች መዳፍ ወድቀዋል።
የንግድ፣ የቱሪዝም ገቢውን በብቸኝነት የያዙት የስርዓቱ ባለሃብቶች ለጉልበት ሥራም የአካባቢውን ተወላጆች ከማሰራት ይልቅ ከትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በማምጣት የሕዝብ ቁጥሩን ሆን ተብሎ እንዲጨምር ተደርጓል። ሁለት የአፋር ክልል ወረዳዎች ከሕዝብ ፈቃድ ውጪ በግዴታ ላለፉት 17 ዓመታት ወደ ትግራይ እንዲካለሉ መደረጉን የአፋር ሕዝብ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ወጣት አካድር ኢብራሂም ተናግሯል።
የብዓላ ወረዳ የልዩ ወረዳ መብት እንዲሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ውድቅ ቢደረግም ፣ የወረዳዋ የትግራይ ተወላጆች ከአፋርኛ እና አማርኛ ውጭ ትግርኛ መማር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። “ካለፍቃዳቸው ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ወልቃይቶች፣ ኩናማዎችና ኢሮቦች በግዴታ ትግርኛ እንዲማሩ እየተደረገ እንዴት በአፋር ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አፋርኛ አንማርም፣ የምንማረው በትግርኛ ነው’ ሊሉ ቻሉ በማለት ነዋሪዎቹ ይጠይቃሉ። የማንነት ጥይያቄዎች በትግራይ በኩል ሲመጡ ፌደሬሽን ምክርቤት በአፋጠኝ የሚያየው መሆኑና ሌሎች ብሄረሰቦች ግን ምክር ቤት በር ላይ እንኳን ለመድረስ አለመቻላቸውን በማስታወስ ምክር ቤቱ የህወሃትን ጥያቄ በሂደት ስልታዊ በሆነ መንገድ እያስተናገደው ነው በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ማንነታችን ይከበር በማለት ለአመታት የጠየቁ የወልቃይት፣ የወለኔ፣ የቁጫ፣ የዶርዜ፣ የዛይ እና ጋሮ ማህበረሰቦች እስካሁን መፍትሔ አላገኙም። የብሄረሰቦቹ ተወካዮች፣ ጥያቄ በማንሳታቸው ከግድያ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓቱትበተለያዩ የአገሪቱ ክልል ለሚነሱት ግጭቶች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን የመስኩ ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ ናቸው።

↧

ዶ/ር ቴድሮስ ያሸነፈባቸው 4 ምክንያቶች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች – ዶ/ር ቴድሮስ ያሸነፈባቸው 4 ምክንያቶች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች

$
0
0

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዳሬክተር ሆኖ የተመረጠበት ምክንያት በዋናነት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ አንፃር ስለሆነ ነው። በዚህ መሰረት፣ ዶ/ር ቴድሮስ አሸናፊ የሆነው በሚከተሉት ከአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡-

1ኛ – አፍሪካ፡- ዶ/ር ቴድሮስ በኢትዮጲያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ የተሰጠው እንደመሆኑ ከሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና በመጠቀም ዶ/ሩ ሙሉ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።

2ኛ – አውሮፓ፡- ሁለተኛው ተወዳዳሪ “Dr. Nabaro” እንግሊዛዊ መሆናቸውና ሀገራቸው እንግሊዝ ደግሞ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣቷ ይታወሳል። በዚህ ምክንያት፣ የእንግሊዙ ተወዳዳሪ ልክ እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ከአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

3ኛ – ኢሲያ፡-  ሦስተኛዋ ተወዳዳሪ ፓኪስታናዊቷ “Nishtar” ከኢሲያ ክፍለ ሀጉር የመጡ ናቸው። ነገር ግን፣ ላለፉት አስር አመታት የዓለም የጤና ድርጅትን የመሩት ዳይሬክተር የዚሁ ክፍለ ሀጉር ተወካይ እንደመሆናቸው እኚህ ተወዳዳሪ ከኢሲያ ሀገራት ሳይቀር ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

4ኛ፡- ላቲን አሜሪካ – “Dr. Nabaro” ከእንግሊዝ ይልቅ ስፔናዊ ወይም ፖርቹጋላዊ ቢሆኑ ኖሮ የላቲን አሜሩካ ሀገራትን ድጋፍ የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ይሆን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሦስተኛ ተራ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው ምክንያት፣ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ሌላ የኢሲያ ተወካይ በድጋሜ እንዲመረጥ ድምፃቸውን ለፓኪስታናዊቷ “Nishtar” አይሰጡም። ስለዚህ፣ በላቲን አሜሪካ ሀገራት ዘንድም ቢሆን ዶ/ር ቴድሮስ የመመረጥ እድላቸው ከሁለቱም ተወዳዳሪዎች የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ዶ/ር ቴድሮስ ከሦስቱም ተወዳዳሪዎች የላቀ የማሸነፍ እድል እንደነበራቸው እሙን ነው። ስለዚህ፣ ለዶ/ሩ ፈታኝ የነበረው የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ማግኘቱ አልነበረም። ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የውድድር ስልት በላይ ለዶ/ር ቴድሮስ ትልቅ ፈተና የነበረው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጋጠማቸው ተቃውሞ ነው።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የድምፅ አሰጣጡ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፐሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ዶ/ር ቴድሮስ በማህበራዊ ሚዲያዊች አማካኝነት የገጠማቸው ተቃውሞ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ውስን ነው። ነገር ግን፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ምን ያህል ጉልህ እየሆነ እንደመጣ በግልፅ ያሳያል። በአጠቃላይ፣ የምርጫ ሂደቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማህብረሰቡን በንቃት በማሳተፍና ንቅናቄ መፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በግልፅ አሳይቶናል።

↧

ፍልሰት፤ ልመናና የጎዳና ህይወት በአዲስ አበባ!

$
0
0
  • “በመንገዶች አምራ በፎቆች ተውባ” የህወሃት/ኢህአዴግ ኩራት የሆነችው አዲስ አበባ
  • “አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ትመስላለች”

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ነች፡፡ ከተማዋ ከፖለቲካ ከተማነቷ ባሻገር የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፎች ማዕከል መሆኗ የብዙዎችን ትኩረት እንድትስብ አድርጓታል፡፡ በክልሎች የሚታየው የሥራ ዕድል ዕጦት፣ ይህን ተከትሎ የተፈጠረው ሥር የሰደደ ድህነት አዲስ አበባን የከተማ ስደት መከማቻ ማዕከል አድርጓታል፡፡

በርግጥ የከተማ ስደት ስረ-መነሻ ከቀደሙት ጊዜያቶች ጀምሮ የተለያየ መንስኤ አለው፡፡ የኢትዮጵያን የከተማ ስደት ከአገሪቱ ማህበረ-ኢኮኖሚና የፖለቲካ መዋቅር ጋር አስተሳስረው የሚያጠኑ ምሁራን  የከተማ ስደትን ከኢትዮጵያ ከተሞች አመሠራረት ጋር አያይዘው የጥናት ውጤታቸውን ያቀርባሉ፡፡

በጥንቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ከገናናው የአክሱም ሥልጣኔ እስከ ዛጉዌ ላስታ ዘመን፣ ከሐረር ሱልጣኔቶች እስከ ሸዋ ነገሥታት፣ ከጎንደር ነገሥታት እስከ ዘመነ መሳፍንት በነበሩ ጊዜያት እንደነገሥታቱ አነሳስና አመጣጥ ከተሞች ተቆርቁረዋል፡፡ የከተሞችን መቆርቆር (መመስረት) ተከትሎ ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ የሥነ-ህዝብ አሰፋፈሩ በጊዜ ሂደት ቅርጽ እየያዘ ቢሄድም ከነገሥታቱ መውድቅና መነሳት ጋር በተያያዘ የከተሞች ዘላቂ ዕድገት ቀጣይነት የሌለው የአንድ ወቅት የሥልጣኔ አሻራ ከመሆን የተሻገረ ሊሆን አልቻለም፡፡ አንዳንድ የነገሥታት ከተሞች ከቶውንም ከነገሥታቱ መኖሪያ (ቤተ መንግሥት) ውጪ ይህ ነው የሚባል የከተማ አሻራ የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ ቀዳሚ ተጠቃሹ የዛጉዌን ዘመነ መንግሥት የሮሃ ላስታ ጉዳይ ተጠቃሽ ምሳሌ ነው፡፡ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር ይህ ነው የሚባል የከተማ አሻራ የለም፡፡ የጁም ተመሳሳይ ይዘት ያለዉ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ጀማሪ የሆነው ዳግማዊ ቴዎድሮስ የንግሥናውን መንበር ሲቆናጠጥ፤ መቀመጫውን መቅደላ ላይ ሲያደርግ፤ የጎንደር የተሟሟቀ ከተማነት እየነጠፈ በአንፃሩ መቅደላ እየከተመች መጥታ ነበር፡፡ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ ህልፈት በኋላ መቅደላ ከቶውንም እንዳልነበረች ስትጠፋ በአንፃሩ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ መናገሻ አንደርታ (መቀሌ) የከተሜነት ቅርጽ ለመያዝ በቃች፡፡

በነዚህ ጊዜያቶች ሁሉ ከነገሥታቱ መውደቅና መነሳት ጋር በተያያዘ ከተሞች ህልውናቸው ሲከስምና ሲነሳ ኖሯል፡፡ ነገሥታቱ መናገሻ ከተማ በሚያደርጓቸው ከተሞች ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ባሉ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አዲሱ ከተማ የመፍለስ ልማድ ነበራቸው፡፡ በወቅቱ ፍልሰቱን የሚያጠናክሩት ደግሞ ወዶ-ገብ ወታደሮች፣ አዝማሪዎች፣ የቤተ ክህነት ሰዎች፣ የዕደ ጥበብ  ባለሙያዎች፣ በአነስተኛ የጉሊት ችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ እና የሲራራ ነጋዴዎችን ተከትሎ የጉልበት ሥራ የሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የምስራቅ ኢትዮጵያ ከተሞች አመሰራረትም ከሱልጣኔቶች አነሳስ እና ከእስልምና ኃይማኖት አስተምህሮታዊ መስተጋብሮች ጋር የተያያዘ ለመሆኑ የጥናት ውጤቶች ይመሰክራሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱ ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው በዋናነት የከተማ ስደት ታሪክ ከዳግማዊ ምኒልክ የአገር ግንባታ ሂደት ጋር በእጅጉ የተሳሰረ መሆኑን በዘርፉ ጥናት የሰሩ ምሁራን የጋራ ምልከታ ነው፡፡ በእምዬ ምኒልክ የአገር ግንባታ ሂደት አዲስ አበባን ጨምሮ አዳዲስ ከተሞች የሚመሰረቱበት ጊዜ ስለነበር፣ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለመቀጠር ብዛት ያለው ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተማ ፈልሷል፡፡

የጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር መስመር ዝርጋታን ተከትሎ የምስራቁ ክፍል ከደቡብ ኢትዮጵያ (አዲስ አበባ) ጋር በተሳለጠ መጓጓዣ መተሳሰሩ ለፍልሰቱ አይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህ የታሪክ ምዕራፍ በኋላ የከተማ ስደት ባህል እየሆነ መጣ፡፡ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት፣ ከተሜነት መስፋፋቱ እና የሥራ ክፍፍል መደባዊነት መፈጠሩ ለከተማ ፍልሰት ሌላ በር ከፋች ሆነ፡፡ በዘመነ ደርግ ጊዜያትም ለገጠሬው ወደ ከተማ መፍለስ በርካት ምክንያቶች ነበሩ፡፡ የባላባቶች መሬት መነጠቅ፣ የንግድ እርሻዎች መዘጋት፣ በከተሞች አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች መከፈት እና አዳዲስ ኬላዎች ሥራ መጀመራቸው ለፍልሰቱ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ድህረ-ደርግን ተከትሎ በህወሓት/ኢህአዴግ ዘረኛ የአፓርታይድ ሥርዓት ላይ የተመሰረተው የክልሎች አከላለል ፍልሰቱን ለጊዜው የገደበው ቢመስልም በክልሎች የሚታየው ኢ-ፍትሃዊ የገቢ ልዩነት ከሥነ-ህዝብ ፖሊሲው አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ ፍልሰቱን በተለየ መልኩ ጨምሮታል፡፡

ህወሓት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ በነበሩት አስራ አምስት አመታት (እስከ ድህረ-ምርጫ 97) ድረስ “ለገጠር ፖሊሲዬ እታመናለሁ” በማለት ከተሞችን ዘንግቶ ቆይቶ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን አንፃራዊ ማህበራዊ ፍትህ ፍለጋ ከገጠር ወደ ከተማ ይደረጉ የነበሩ ፍለስቶች ከዛሬው ጋር በቁጥር ለንፅፅር ባይቀርቡም ቀላል የማይበል ፍልሰት ነበር፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ ገዥው ኃይል ሙሉ ትኩረቱን ከተሞች ላይ በተለይም አዲስ አበባ ላይ በማድረጉ ወትሮውንም በማህበረ-ኢኮኖሚ መስክ ራሱን ያልቻለው የገጠሩ ኢትዮጵያ ክፍል ጥልቅ ችግር ላይ ወደቀ፡፡ የገጠሩን ነዋሪ ለፍልሰት ከሚዳርጉት በርካታ ገፊ ምክንያቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ችጋር፣ ድርቅ እና ረሃብ፣ ትምህርት እና ጤና አገልግሎት፣ ያልተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ፣ የግብርና ምርት ማሽቆልቆል እና የሥራ ዕድል እጦት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ እና ተያያዥ ምክንያቶች ከገጠር ወደ ከተማ በተለይም ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ፍልሰቶች በአሁኑ ጊዜ መቆሚያ አጥተዋል፡፡

አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲን በመከተል ከፋፋይና በታኝ ዘውጋዊ ልዩነቶችን፣ የቀደሙ የታሪክ ቁርሾዎችን በማንሳት፤ ደማቅ የልዩነት መስመር ያስመረው ገዥው ኃይል፣ በክልል ከተሞች ዜጎች  በነፃነት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል – ከትግራይ ተወላጆች በስተቀር፡፡

የአዲስ አበባ የሥራ ነፃነትም ሆነ የሥራ ዕድሎች በጫማ ጠረጋ (ሊስትሮ)፣ እንደ ማስቲካ፣ ሲጋራ፣ ሶፍት፣ የሞባይል ስልክ ካርድ፣ ትንንሽ ሸቀጣ ሸቀጦች ሽያጭ፣ የግንባታ እና የቀን ሥራዎች ላይ፣ በቤት ሰራተኝነት እና በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራት የሚተረጎም የሥራ ነፃነት እና የሥራ ዕድል እንጂ ከዚያ የተሻገረው ትርፋማ የሥራ ዘርፍ ለትግራይ ተወላጆች እና ለገዥ መደቡ ሎሌዎች  በተዋረድ ተከልለው የተቀመጡት ናቸው፡፡

ከምርጫ 97 በኋላ የአዲስ አበባ ሥነ-ህዝብ አስፋፈር (Demography)፣ የኢኮኖሚ አሰላለፍ (Formation of economy)፣ ከፖለቲካ መዋቅሩ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነው፡፡ ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ባስፈነጠረው መለስ አንደበት “የነፍጠኞች  ከተማ” የምትባለዋን አዲስ አበባ መዋቅራዊ ድጋፍ  (state sponsor) በሆነ መልኩ በትግራይ ተወላጆች ብቻ መሙላት ከአናሳነታቸው አኳያ የማይታሰብ ሆኗል፡፡ አማራጩ የትግራይ ሰዎችን በተሻለ ማህበረ-ኢኮኖሚ ልዕልና ቦታ ላይ በማስቀመጥ ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል በዕለት ተዕለት ኑሮ ባተሌ ማድረግ ለህወሓት ተመራጭ  መንገድ ሆኗል፡፡ የትግራ ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ ያላቸው የበላይነት ምንጩ ፖለቲካዊ  ኃይል የመሆኑ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ፖለቲካዊ ኃይሉን ተደግፎ የኢኮኖሚ በዝባዥነት፣ ዝርፊያ፣ ቀማኝነትና ነጣቂነት የትግራይ ሰዎች መገለጫ ሆኗል፡፡

የአዲስ አበባ የቀደመ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ሥሪት በማደብዘዙ ረገድ የደቡብ ኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ከገጠር ወደ ከተማ የሚያድርጉት ስደት (ፍልሰት) ለገዥው መደብ አዋጪ አጋጣሚ  ቢመስልም ማህበራዊ ቀውሱ ግን ከከተማዋ ባሻገር አደጋ ያለው ሁነት ሆኗል፡፡ የእነዚህ ወጣቶች በተለየ መልኩ ወደ አዲስ አበባ የመፍለስ ሁኔታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእጅጉ አየተባባሰ መጥቷል፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “በግብረሰዶማዊያን የተወረረችው አዲስ አበባ!” በሚል ርዕስ ባስነበበው የዜና ሃተታ እነዚህ ወጣቶች በምን ዓይነት መልኩ ወደ ሰዶማዊነት እየገቡ እንደሆነ አስነብቧል፡፡

አዲስ አበባ ማስተናገድ ከምትችለው በላይ የህዝብ ብዛት ተከማችቶባት ይገኛል፡፡ በአንፃሩም ቢሆን ወደ ውጭ አገር የሚደረጉ ስደቶች በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የጠበቀ የሰራተኞች  ፖሊሲ የተነሳ (የሳውዲ አረቢያን፣ ኳታርን፣ ኩዌትን ወዘተ አረብ አገራት እርምጃዎች ያስታውሷል) የአገር ውስጡን ሥራአጥ ቁጥር ማስተንፈሻ መንገድ (safety valve) ዘግቶታል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚሰደዱ ዜጎች ብዙውን ጊዜ ከተማ ውስጥ ሥራ በማጣት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እየታየ ያለው የማህበረ-ኢኮኖሚ ተግዳሮትም የዚህ ችግር አካል ነው፡፡ ቁጥራቸው የበዛ ታዳጊ ወጣቶች ለጎዳና ህይወት ተዳርገው ማየት የዕለት ተዕለት ትዕይንት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ መፈጠርን በሚያስጠላ መልኩ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው፣ የሥጋ-ደዌ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ነዳያን (የሚጭበረብሩ ጥቂቶች መኖራቸውን ሳንዘነጋ) የእግረኛ መንገዶችን አጣብበው ሲለምኑ ይውላሉ፡፡ “ወገን ራበኝ አጉርሱኝ አልብሱኝ”፣ “የቤት ኪራይ የምከፍለው አጣሁ”፣ “ባለቤቴ .. (ቁጥር ያላቸው) ልጆቼን ጥሎብኝ ሞተ”፣ “የማርያም አራስ ነኝ እርዱኝ”፣ “ቤቴ ለልማት በሚል ፈረሰ፤ መጠለያ ያጣሁ ችግረኛ ነኝ”፣ . . . ወዘተ የሚሉ የልመና ድምፆች የአዲስ አበባን ጎዳናዎች ሞልተውት ውለው ያድራሉ፡፡

በየቤተ-እምነቱ ደጃፍ በመኮልኮል በልመና ተግባር ከተሰማሩ ዜጎች ቁጥር በእጥፍ በሚልቅ ደረጃ የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን ያጣበቡ ነዳያን ተበራክተዋል፡፡ ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች በህብረ-ዝማሬ (በእነርሱ ቋንቋ “ቅፈላ”) አላፊ አግዳሚውን ሲለምኑ የሚውሉትም በርካታ ናቸው፡፡ የሌሊቱን ብርድ ለመቋቋም በሚል ቤንዚል በስፖንጅ አድርገው ወደ አፍንጫቸው በማስጠጋት የሚስቡት የጎዳና ልጆች፤ ቤንዚሉ በሚፈጥርላቸው የአዕምሮ መነቃቃት (መደፋፈር) የወንጀል ተሳታፊ ሆነው ሲገኙ ይስተዋላል፡፡

በአዲስ አበባ የኮንደሚኒየም መኖሪያ ቤቶች እና በከተማዋ ዳርቻ አካባቢዎች ተዘግተው የሚውሉ መኖሪያ ቤቶችን በቀን (ቤት) ገልብጠው የሚገቡ ሌቦች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተከታታይ ዘገባዎች አመላካች ናቸው፡፡ በምሽትና በሌሊት ተዝናንቶም ሆነ ማህበራዊ ጉዳይን ከውኖ በሰላም ወደ ቤት መግባት የማይታሰብበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ የሞባይል ንጥቂያና የአካል ማጉደል የወንጀል ተግባራት እየተበረከቱባት ባለችው አዲስ አበባ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት ለከተማዋ ወንጀል መበራከት ጉልህ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡

በህወሓት/ኢህአዴግ አጠራር “አተት” የተባለውን ተላላፊ (የኮሌራ) ወረርሽኝ በሽታ ያህል የዜና ሽፋን እያጣ ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ጉዳይ ከፍልሰቱ ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የከተማዋን ሴተኛ አዳሪዎች መበራከት ተከትሎ ቫይረሱ መዛመቱን እንደቀጠለ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፡፡ የግብረሰዶማዊያን መበራከት ጉዳይም ከፍልሰቱ ጋር የተያያዘ ደጋፊ ምክንያት አለው፡፡

ሩብ ክፍለ ዘመን የተሻገረው የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ የፈጠረው የፖለቲካ ነፃነት እጦት እንደተጠበቀ ሆኖ የትግራይ የኢኮኖሚ ሊሂቃንና የገዥ መደቡን ተለጣፊ ሎሌዎች ከማበልፀግ ባሻገር እንደ አገር ይህ ነው የሚባል የጋራ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ሊያካፍል አልቻለም፡፡

በህገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገራት የሚደረገው ስደት እያስከተለ ያለው ማህበራዊ ቀውስ የሚያባራ አልሆነም፡፡ ከዚህ ችግር ባልተናነሰ መልኩ በአገሪቱ የተለያዩ ገጠራማና የክልል  ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ የሚያድርጉት ፍልሰት ለነባሩ ነዋሪም ሆነ በፍልሰት ከተማዋን ለሚቀላቀሉት ዜጎች የማይመች ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ችግር ሲፈጥር እየታየ ነው፡፡

የሥራ አጥነት መበራከት ወደ ወንጀል ድርጊት እንደሚገፋ አዲስ አበባ ውስጥ በየዕለቱ የሚመዘገቡ የወንጀል ሪከርዶች አስረጅ ምሳሌዎች ይሆናሉ፡፡ የወሲብ ንግድ፣ ልመናና የጎዳና  ህይወት የማህበራዊ ቀውስ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለአንድ ዘር ልዕልና የሚተጋው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ከኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ እስካልተነቀለ ድረስም እነዚህ ችግሮች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ይገመታል፡፡

የሥርዓቱ መክሸፍ ወይም ነውር በማያውቀው ሟቹ መለስ አነጋገር “መበስበስ” የእነዚህ እና የሌሎች ኢኮኖሚያዊ በተለይም ማኅበራዊ ችግሮች መባባስ አስረጅዎች ናቸው፡፡ የኢህአዴግ ውጤቶች ናቸው፤ የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸው፤ … እያለ በየዕለቱ በሚደሰኩረው መግለጫው በህወሓት ሰዎችና ሎሌዎቻቸው ከሕዝብ እየተመዘበሩ የተሰሩ ፎቆችን፤ ተከፍሎ በማያልቅ ብድር ዓመታትን መዝለቅ የማይችለውን መንገድ እና ሌሎች ጥራዝነጠቅ “የልማት ውጤቶችን” በማሳየት “ሁሉ ሰላም ነው” በማለት የግዛት ዘመኑን ለማርዘም ይተጋል፡፡ ማስጠንቀቂያ መስማትም ሆነ አለ ብሎ ማሰብም አይፈልግም፡፡ ማኅበራዊው ሰቆቃ የፖለቲካው ክሽፈት ማሳያ አድርጎ ለመውሰድ ባለመፈለግ ለማንኛውም የዜጎች የጣዕር ጩኸት ምላሹ “ጥሪ አይቀበልም” ሆኗል፡፡

በባራክ ኦባማ አስተዳደር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት ቶም ማሊኖውስኪ ባለፈው ታህሳስ ወር ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የአገሪቱን ሁኔታ ቢዘህ መልኩ ነበር የገለጹት፡፡ “አገሪቱ አሁን ያለችበት ሂደት በእሳት ላይ ተጥዶ እንደሚንተከተክ ማሰሮ ይመስላል። እናም እንዲህ የሚንተከተክ ማሰሮ ለማስተንፈስ ያለው ምርጫ ክዳኑን ማንሳት ብቻ ነው፤ ያ ካልተደረገ መንተከተኩ አያቆምም። በዚያ ከቀጠለ ደግሞ መገንፈሉ አይቀርም። ከዚያ በኋላ የሚሆነው ሁላችንም እናውቀዋለን”፡፡


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

↧
↧

አውቀን እንታረም

$
0
0

ደራሲ፤ አቢይ አበበ (ሌ/ጄኔራል)
 ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ

ዓለም ገና ልጅ ናት አውራጃዋም ደግሞ
አርጅቶ የሚሞተው ሰው ብቻ ነው ቀድሞ
ብዙ አሳልፋለች ብዙዎች ተክታ
የሁሉንም ምግባር በየተራው አይታ።

ሌ/ጄ አቢይ አበበ

 

እንዲህ ሆነ፤

ርዕሱን አነበብኩና ደራሲውን ስመለከት ሌተናንት ጄኔራል ይላል። የህትመት ዘመኑ ደግሞ 1955 ዓ/ም። ባለሁበት ዘመን ውስጥ ሆኜ ሳሰላው እንግዲህ መፅሀፉ ከታተመ ግማሽ ምዕተ ዓመት አልፎታል። ህትመቱስ? አስቀድሞ አሥመራ በ”ኢል ፖሊግራፊኮ ሶ. አ” ማተሚያ ቤት የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር ኤርትራ ዋና ከተማ ሲሆን እርግጥ ከ12 ዓመት በሁዋላ በ1967 ዓ/ም (ዘመነ ፅልመት) አዲስ አበባ በቼምበር ማተሚያ ቤት በድጋሚ ታትሟል። ስለምን ዘመነ ፅልመት አልነው 1967 ዓመተ ምህረትን? አንባቢ ቅኝቱን አስጀምሮ ካስጨረሰህ ምላሹን ታገኘዋለህ።

ይዘቱስ? እዚህ ላይ ነው “ጉድ እዩ!” ያልነው። (እንደ ትግሪኛ ካነበብከው “ጉድ ነው” ማለት ሲሆን፤ እንደ አማርኛው ደግሞ “ጉድ ተመልከቱ” ማለት ይሆናል።) አጀብ ቋንቋችን ማማሩ። “መፅሀፍን በሽፋኑ አትመዝነው” ያለው ማን ነበር? ደራሲንስ በስሙ በማዕረጉ ሳይሆን በድርሰቱ ጭብጥ ብቻ መፈረጅ አይገባምን?

“አውቀን እንታረም”ን ስለምን እንደፃፈው ጄኔራሉ ካወረድልን ቃል የሚከተለውን ያገኟል፤ መተዛዘንን፤ መተሳሰብን፤ ጠንካራ መንፈስን፤ ቅን ባህሪይን፤ ፍቅርን እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል። ይህም በመኻላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም። ወደ መጥፎ መንፈስ የሚመራ ሁሉ መጥፎ ነገሮችን እያራባ ሌላውን ሁሉ ከትቦ እንዳይጎዳ ያስፈልጋልና በኑሮ ውስጥ ምን ምን እንዳሉ ተረድቶ ከአሁኑ መገታት ያስፈልግ ይመስለኛል።

 

     በአጭሩ ከገለጥኩት በሁዋላ አስፋፍቶ ማተቱን የሚመለከተው የአንባቢዎች አእምሮ እንደሚሆን በማመን፤ ለመልካም ሥራ ይውል እንደሆን በማለት ተስፋ ይህን ትንሽ መፅሀፍ ለውድ ሀገሬ ሰዎች አበረክታለሁ – ይላል ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ። ቀልብን ማራኪ፤ አእምሮን ቆንጣጭ ጅማሮ ይሏል እንዲህ ነው።

እና እንግዲህ ሌተናንት ጄኔራሉ በሠይፍ ወይ ደግሞ በጥይት ሳይሆን በሰላ ብዕሩ ማረከኝ፤ ገና በጠዋቱ ከፍልሚያው አምባ ዘልቄ እንኳን ሳልገባ አንዲት ቅጠል እንደቀረደድኩ። ጠሊቅ ሀሳቡ፤ አመራማሪና ኮርኳሪ ምልከታው በዘመን ተወልዶ በዘመን የሚሞት ሳይሆን ዘመን የሚሻገር ትውልዶችን እሚያናግር ሆነና በተለይ ደግሞ አሁን ላይ እምገኝበትን ዘመኔን እንድፈትሽ ቀፍድዶ ያዘኝ። እኔነቴን እንድከልስ እንድጠይቅ እንድመዝን አካባቢዬን እንድቃኝ። አወዳደቄን እንዳስተውለው ወይም ከመውደቅ እንድድን። እና ብዕሬን አነሳሁ። እነሆ የሆነው ይኸው ነው። ከዚህ በሁዋላ ያለው ያው “ታሪክ ነው” አይደል እሚባለው? ደግሞስ ቢሆን ጠቢቡ ወታደር የመፅሀፉን ቃል ‘አስፋፍቶ ማተቱ የአንባቢ ሥራ ነው’ አይደል ያለው? ከሆነ “ራስ ወለድ” በሆኑ ንዑስ ርዕሳን ‘ቅኝቱን’ እንዲህ አደራጅተነዋልና እንግዲህ እንቀባበል . . .

 

ሰው ሆይ!

ፍልስፍናን በተላበሰ አገላለፅ ስለ ሰው ሰብዕና ፤ ስለህሊና ፤ በምድር ቆይታው ሰው ራሱን በመሆንና ራሱን በመሸሸግ ስለሚኖረው ተቃርኖ ጥቂት በማይባሉ ገፆች ቋጥኝ የአስተሳሰብ ዘርፎች አስቀምጧል – ጠቢቡ ወታደር። ጥቅልና ጥልቅ የሆኑትን አገላለፆች ሁሉ የመተንተን የቅኝታችን አቅሙም ሆነ ግቡ አይደለም። እንዲያም ቢሆን ቅሉ፤ የተወሰኑትን ግና እየነቀስን እና ከዘመናችን ጋር እያዋደድን እናወርዳለን።

ጠቢቡ ወታደር እንዲህ ይላል፤ አንዳንድ ጊዜ ሁሉን ሳመዛዝን ሳወጣ ሳወርድ እዚህ ምን አደርጋለሁ እስከመቼስ አለሁበት እቆያለሁ? ጨረቃና ፀሀይ ሲፈራረቁ ማየት የሰው ልጅ ሁሉ ወግ ነው። ዛሬን አስመሽቼ ነገን ማንጋቴን አላውቅም። በዚህ ምክንያት ብተክዝና ያለኝን ጊዜ ንቄ ባሳልፈው አይሻለኝምን? እላለሁ።

     በሌላ ጊዜ ደግሞ ለምን እተክዛለሁ፤ በአለሁበት ዓለም እምኖረው ለአጭር ጊዜ ነው። ስለምን ደስ ብሎኝ አላሳልፈውም? ለምንስ እንደሌላው ሁሉ አልሆንም! . . . ሌላው የሚያደርገውን ሁሉ ለማድረግ እኔም ይቻለኛል። ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም። የኔም ዕድል በግድ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው እያልኩ አስባለሁ –  ይለናል።

እነሆ ይህንን የመሰለ መጨበጫው የረቀቀና በእዝነ ህሊና ምልከታው የመጠቀ ሀሳብ ያሰፈረው ጠቢቡ ወታደር ስለዚህች ዓለም፤ ስለ ሰው ልጅ፤ ስለ ህሊናና ስለ ህይወት ተልዕኮ ከድምሩ ህብረተሰብ ያፈነገጠ ዕይታ እንዳለው በገሀድ ያሳያል። እንዲህ የመሳሰሉትን ረቂቅ እሳቤዎችን የሚያባዝቱ በአብዛኛው በቀድሞው የሩቅ ዘመን ውስጥ የኖሩ ፈላስፎችና ተመራማሪዎች ሲሆኑ፤ በዘመናችን ደግሞ ምናልባት ጥቂት ፈላስፋዊ ነፍስ ያላቸው /ጠቢባዊ አስተሳሰባቸው የተመነደገ – በዊዝደም የተሞላ/ እና ምናልባትም ደግሞ ጥቂት ነፍሳቸው ከጥበብ ህዋ የተጣለ፤ የሰጠመ የጥበብ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ የትኛውን ነፍስ ይሆን ይዞ የነበረው? ጠቢቡ ወታደር በቁሳዊ ህይወቱ የተመነደገ ኑሮን መኖር የሚችል ሆኖ ሳለ በእንዲህ ያሉ ነፍስ ሞጋች መጠይቆች ስለምን ሲብሰለሰል ኖረ? አቢይ አበበን የሚያስጨንቀውና እንቅልፍ የሚነሳው  ምን ነበር? ማለታችን መቼም አይቀርም። ለዚህ ምላሽ የቅኝታችን አንደምታ ሲጠቃለል ፍንትው ይላልና ወደዛው የሚያመራንን ፍተሻ እንቀጥላለን።

የተፈጠርኩት ጨረቃና ፀሀይ ሲፈራረቁ፤ ክረምትና በጋ፤ ፀደይና በልግ ሲወጡና ሲገቡ ለማየት፤ ዕድሜ ለመቁጠር – “ትላንት” ነበር “ዛሬ” ግን የለም ለመባል ነውን? ማለቱ ነው ጠቢቡ ወታደር  – ሲመራመር። ከተፈጠርኩና በምድር መኖሬ ካልቀረ – ትርጉም ያለው ተግባር ከውኜ እና ሰው ሆኜ መኖር ይገባኛል – ነው የሚለው ጠቢቡ ወታደር። ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም – ይላል ጠቢቡ ወታደር። በዚህች ምድር ሰው አልፎ ሂያጅ ነውና ሰው በሰውነቱ ወደ ምድር በመምጣቱና ተለይቶም በመሄዱ መሬት የምታጣው ነገር የለም ነው እሚለው ጠቢቡ ወታደር። ሰው ግን መሬትን ያጣታልና በመሬት ቆይታው  እርሱ ሲያልፍ መሬት ባታጣውም ታስታውሰው ዘንድ ግን መልካም ምግባር ከውኖ አሻራውን አሳርፎ እርሱን ለሚተካው ሰው እርሱ ከኖረበት የተሻለ አድርጎ ማለፍ የሰው ሃላፊነት ነው ማለቱ ነው – ፈላስፋው ወታደር። “ሰው መሬትን ያጣል እንጂ መሬት ሰውን አታጣም” እንደምን ያለ አመራማሪና እንደ ውቅያኖስ የተንጣለለ ባህረ ሀሳብ ነው? እንደምንስ ተተንትኖ ይዘለቃል? አንባቢ በራስህ ጊዜ ቀሪውን ተመራመረው ፤ ባህረ ሀሳቡንም ዋኝተህ ውጣው እንጂ እኛስ ከዚህ በላይ አንሞክረውም። ይልቅ ቀጣዩን ደግሞ ነቅሰንልኻል፤

ሰው ሆኖ መፈጠር ሰውነትን ለማክበርና ምድርን ለመሙላት ብቻ ሳይሆን ትዕዛዛትን ለማክበርና ሕግጋትን ለመፈፀም እንደዚሁም ዕውነትንና ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ ከልብ ለመፈቃቀርም በሆነ ነበር። ግን ሰው ተብሎ እንዲፈጠርና በምድር ላይ እንዲኖር አስፈልጎ ተፈጥሮም መሬትን የሰፈረባት ሰው ደጉንም ክፉውንም ነገሮች አስከትሎ ዓለምን ወረራት። በጊዜያችን የምናየው ሁሉ ምድር ከተፈጠረች ጀምሮ እስካለንበት ጊዜ ድረስ የነበረውን እንጂ ብርቅ አድርገን የምንቆጥረው እምብዛም እንደሌለ እንመን – ይላል ጠቢቡ ወታደር።

ለመሆኑ ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ምን ማለቱ ነው? ብለን እንጠይቅና እንዲህ እንመልስ። የሰው ልጅ ወደ ምድር ሲመጣ ተቃራኒ ባህሪያትንም አጣምሮ ነው የመጣው። በዚህች ምድር ላይ ሲኖርም ለመውለድና ለመብላት ብቻ አይደለም።  ህግጋትን ለማክበር፤ ፍቅርን ለመናኘት፤ በጎና ቅን ሆኖና ቅን አድርጎ መልካም ተግባርን ለመከወንም ጭምር እንጂ። ይህችን አንዴ ተፈጥሮ አንዴ ብቻ የሚኖርባትን ዓለም ጠብቆና አበልፅጎ እንጂ አጥፍቶና አራቁቶ መሄድ የለበትም ማለቱ እንጂ። ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ የሰው ልጅ ታሪክ መስራት ከጀመረ ጀምሮ በዓለም ላይ ዛሬ እኛ በደረስንበት ዘመን ሰው ሲያደርግ የምናየው ህሉ ትላንት እኛ ባልኖርንበትና ባልተፈጠርንበት ዘመንም የነበረው ሰው ሲያደርገው ነበር። ክፋት ደግነቱ፤ መግደል መቀማቱ፤ መጨከን ማዘኑ፤ መግዛት ማሰቃየቱ፤ ጦርነቱ ፤ ጥፋቱ ፤ ድህነቱ፤ ድረቁ ፤ጎርፉ ፤ ወጀቡ . . . ነበር አለ ይኖራል። የሰው ክፋቱ ጥፋቱ ጭካኔው  አውሬነቱ – ስፋትና ጥልቀቱ ወርድና ቁመቱ ፤ እንደዘመኑ እንዳኗኗሩ ቢለያይም ቅሉ ፤ ማለቱ እንጂ ጠቢቡ። ‘አሁን ያለው በፊት ነበር፤ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር’ እንዲል መክብብ በታላቁ መፅሐፍ።

ሰው ሆኖ መፈጠር ሰውነትን ለማክበርም ነው  ይላል ጠቢቡ ወታደር። እንዴት ማለት ነው? ራሱን ያላከበረ ሰው ነው ሌላውን ሰው የማያከብረው ማለቱ ነው። ወይም ስለራሱ በእሱነቱ ውስጥ ኢምንትነት ውስጠቱን የሚንጠው ሰው ነው በሌላው ሰው ላይ የሚታበየው፤ ተራራ አክሎ ለመታየት ተራራ የሚያከል ጭካኔና ግፍ የሚፈፅመው ማለቱ ነው አቢይ አበበ። የኢምንትነት ቫይረስ በደማቸው የሚሯሯጥ ሰዎች ሲሰባሰቡ ህመማቸውን የፈወሱ የሚመስላቸው ወይም የህመማቸው ማስታገሻ ሆኖ የሚያገኙት – በመሰል ዜጎቻቸው ወይም በሌሎች ዜጎች ላይ ዘረኝነትን ፤ ቅኝ ገዢነትን ፤ አምባ ገነንነትን ፤ ፍርደ ገምድልነትን ፤ ጥላቻንና ቂም በቀለኝነትን በመስበክ በማሰራጨትና በማስፈን ወደር የሌለው ብዝበዛና ዝርፊያ ወንጀልና እልቂት አድልዖና ኢሰብዓዊ ግፍ – የዘር ማጥፋትን ወንጀል ጨምሮ – በመፈፀም ወይም በማስፈፀም ወይም ለመፈፀም (በአደረጃጀትም ሆነ ባላሰለሰ ፕሮፓጋንዳ) በመዘጋጀት ነውና።

ማስረጃ ካስፈለገህ የጣሊያንና የስፔን ፋሽስቶችን እንዲሁም የጀርመን ናዚስቶችን ከሩቅ አገር ከሩቅ ዘመን መመልከቱ ይህም ካልበቃህ በአህጉረ አፍሪካ በምድረ ኡጋናዳ በሁርሲና ቱትሲ ጎሳ/ዘር መካከል የተካሄደውን አሰቃቂ እልቂት (የዘር ማጥፋት ዘመቻ) ወይም በጎጠኞች፤ በሃይማኖት አክራሪዎችና የሥልጣን ልክፍተኞች መካከል በሚካሄደው ጦርነት እየተፈጁ ያሉትን ሶሪያውያንንና እየወደመች ወይም እያወደሟት ያለችውን ሀገራቸውን አስተውል። ወደራስህ መመለስ ከቻልክም ከ1983 ዓ/ም ወዲህ በኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የሰፈሩትን ባለተረኞች የኢምንት ሰብዕና ሰዎች ስብስብ ጎጠኛ/ዘረኛ ድርጅቶች ያካሄዱትንና በማካሄድ ላይ ያሉትን ተነግሮ የማያልቅ ምዝበራ ቶርቸር ማፈናቀል ትውልድን (ዘርን) የማጥፋት ዘመቻን መርምር።

 

እነሆ ደግሞም እነሱም በቀየሱት ቦይ በመፍሰስ ‘ማነህ ባለተራ’ ድርሻቸውን ለመረከብ ነባርና አዳዲስ ጎጠኞች/ጎሰኞች በ’ማንነት ፍለጋ’ “ዘመናዊ ጭምብል” የዘመኑን ጎጥ/ጎሳ/ዘር ዜማ የሚያዜሙት “አክቲቪስቶች” የሚያደርጉትን የሚደሰኩሩትንና “የሚገነቡትን” የፉክክር አጥር፤ የፉክክር ክልል፤ የፉክክር ድንበር (በጎሳ በዘር በጎጥ የመሰባሰቡን የመቧደኑን ከእድር እስከ እቁብ እስከ ሰንበት ማህበር እስከ ፖለቲካ) ሽር ጉድ –  ከኢትዮጵያ እስከ አውሮፓ እስከ አሜሪካ እስከ ካናዳ እስከ እስያና አውስትራሊያ የሚሆነውን፤ የሚቦተለከውን፤ የሚታመሰውን መቃኘትም ‘የገደል ሩጫችንን’ ፍጥነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

እነሆ ዛሬ “ኢትዮጵያ” ብሎ የሚነሳው ወይም ስለ ኢትዮጵያ አደባባይ የሚወጣው ዲያስፖራ ስንት ሆኗል? በየጎጡና ዘርማንዘሩ ቆጠራና ደም የተመለመለው ሁሉ ግን በዝግ ስብሰባና በግላጭ ኮንፍረንስ በማስታወቂያ ካገር አገር እየተጠራራ ኢትዮጵያዊነትን አግልሎ በዘር /በጎሳ /በጎጥ አጀንዳ ላይ በአሜሪካ በካናዳ በአውሮፓና በአውስትራሊያ ሲዶልትና ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ ሲሸነሽን – ለመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ጉዳይ (በተለይ በስደት ዓለም) የሚጠራ ኮንፍረንስና የሚገኝ ህዝብ መመናመኑን ወይም እየጠፋ መሄዱን አስተውለሃልን? ይህ እንደ ሰመመን እያማለለ የሚወስድ ወይም እንደ አረንቋ ስቦ የሚያሰምጥ የዘር ቫይረስ ‘ተስቦ’ ባልተጠበቀ ፍጥነት በየአቅጣጫው እየተራባ በመሆኑ – ጠቢቡ ወታደር እንደተነበየው (በተለይም በስደት ዓለም) ዕውነትንና ትክክለኛውን መንገድ ተከትሎ ከልብ ለመፈቃቀር – አልተቻለም ወይም አዳጋች እየሆነ ይገኛል – የአቢይ አበበን አገላለፅ መሬት አውርደን  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በምንገኝበት ነባራዊ ዕውነታ ስንተረጉመው።

 

እንግዲህስ – ንግባዕኬ ሀበ ጥንተ ነገር – እንዲል የቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት – እኛም ወደ ቀደመ ጉዳያችን እንመለስ።  እነሆ የሚከተለውን የጠቢቡን ቃል ደግሞ ልብ ይሏል፤-

በተቀደሰ መንፈስ ለተቀደሰ ሥራ የተፈጠረው ሰው በበኩሉ ክፉ ሥራዎችንና ተንኮልን እራሱ ፈጥሮ ሲጨነቅና ሲንገላታ ፤ ሲያዝንና ሲተክዝ ፤ ሰውነቱን ሲጠላና የተወለደበትን ቀን ሲረግም ፤ በወገኑ ላይ ሲያፌዝና ወንድሙን ሲገድል ፤ በጓደኛው መንገድ ላይ ወጥመድ ሲዘረጋ፤ በጎረቤቶቹ ሲቀና በሌላው ሲመቀኝ ፤ የጊዜውንና የራሱን ጥቅም ብቻ ሲከተል ፤ዝርያውን በሀሰት ሲወነጅል ፤ የራሱን ሥራ ብቻ ሲያመሰግን ፤ ካጠገቡ ራቅ ያለውን ሲያማና ሲነቅፍ ፤ እራሱን እያታለለ ሌላውን ሲያሳስት፤ ተቆጥሮ የማያልቀውን ስንቱን ጉዳጉድ አመርቅዞና ደብቆ የያዘው ሰው እንደናንተም እንደ እኔም ያለ ነው።  

     አንባቢ ሆይ ፍረድ ! እርሱ በማይኖርበት ዘመን ያለህ አንተ አንባቢ አስቀድሞ የዘረዘረልህ ባህሪያት እንደኔም እንደናንተም ባለው ሰው ውስጥ ነው ይልሃል፤ ጠቢቡ ጄኔራል አቢይ አበበ። ታዲያስ? ይህ ዘመን ተሻጋሪ ትውልድን አነጋጋሪ ጠቢበኛ አገላለፅ አይደለምን?

ዛሬ እኔና አንተ በምንኖርበት ዘመን ውስጥ ለምሳሌ . . . በወገኑ ላይ ሲያፌዝና ወንድሙን ሲገድል ፤ የጊዜውንና የራሱን ጥቅም ብቻ ሲከተል ፤ ዝርያውን /ህዝብን/ በሀሰት ሲወነጅል ፤ እራሱን እያታለለ ሌላውን ሲያሳስት . . . የምናውቀው ግለሰብ ቡድን ድርጅት ወይም መንግሥት የለምን? ብዙ ሳትደክም ሀገርህን ኢትዮጵያንና ገዢዎቿን ህወሃት/ኢህአዴግን ተመልከት። ህዝብህን ኢትዮጵያውያንን ተመልከት ። የጠቢቡ ወታደር ቃል በዙሪያ ገባህ በእነ ሆድ አምላኩዎች እና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮች ሲተገበር አይታይህምን?! ይህን ግፍ ፈፃሚውና አስፈፃሚው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ከማታውቀው ዓለም የመጣ የማይታወቅ ፍጡር ሳይሆን እኔና አንተን የሚመስል ሀገር በቀል ሰው ነው።

ህወሃትን እንኮኮ የተሸከሙትና ለህልውናውም ዘብ የቆሙለት ከአማራው፤ ከኦሮሞውና ከሌላውም ብሄረሰብ የተሰባሰቡት “ኢህአዴጋውያንም” በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የተቀረፁ ሀገር በቀል ‘ሰዎች’ ናቸው። ይህ ሀገር በቀል “ሰው” ግን “ሰውቱን” አጥቷል። “ጭራቅ” የሚባል ምናብ ወለድ ጨካኝና “በላኤ ሰብ” ፍጡር ከምናብነት አልፎ “ዕውን” እንደሆነ ማወቅ ከፈለግህ ሩቅ ሳትጓዝ በሀገርህ መዲና እምብርት አዲስ አበባ ላይ በማዕከላዊ የሥቃይ ‘ቀራንዬ’ ብቻ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ህወሃት የሚፈፅመውን (ታዛዥ አገልጋዮቹ በዝምታ አልያም በመተባበር የሚያግዙትን) ጭራቃዊ ግፍና ‘ሰው በላነት’ ከመንጋጋው በተአምራት የተረፉትን የእነ ሀብታሙ አያሌውን የጣዕር ኑዛዜ ስማ!! በዘመነ ትግራይ  ነፃ አውጪ ግንባር አገዛዝ ሥር ያደገውንና ነፍስ ያወቀውን የዚህን ወጣት ትውልድን የኢትዮጵያዊነት ዕምነት ማተብና ፅናት በእነሀብታሙ አያሌው “ስቅላትና ትንሳኤ” ሰቆቃ ወፍዳ ትርከት ውስጥ ታየዋለህና!

የሀገር ፍቅርና የእናት ፍቅር ዐይንና አፍንጫ መሆናቸውን በእነ አንዳርጋቸው በእነ ሀብታሙ በእነ ኒሞና ጫሊ በእነ ሌንጂሳ አለማየሁ በእነ አቡበከር በእነ አህመድ ጀበል በእነ ካሚል ሸምሱ በእነ አህመድ ሙስጠፋ በእነ መሀመድ አባተ በእነ ካሊድ ኢብራሂም በእነ አደም በደዊ በእነ ኩርፊል ጀማል በእነ ብሩክ አጥላዬ በእነ ማስረሻ ሰጤ በእነ አቤል ከበደ በእነ ዳንኤል ሺበሺ በእነ አሸናፊ አካሉ በእነ አበበ ውርጌሳ በእነ ኑረዲን በእነ ናትናኤል በእነ አቤል ዋበላ  በእነ ባህሩ ደጉ በእነ አንጋው ተገኝ በእነ ብሥራት አቢ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው በእነ በላይነህ በእነ ኡጁሉ በእነ እስክንድር በእነ ተመስገን በእነ አናንያ በእነ ዮናታን በእነ በቀለ በእነ መራራ በእነ አንዱዓለም በእነ ደመቀ በእነ ንግሥት በእነ ማህሌት ፋንታሁን በእነ ኤዶም ካሳዬ በእነ ባንቺ በእነ ሺህዎቹ የግፍ ማቃቂዎች ኢትዮጵያውያን ፍዳና ፅናት (ማየት ከፈለግህ) አሻግረህ ታያለህና … ትንታጎቹ የኢትዮጵያ ልቾች ስለ እናታቸው ክብርና ጤና በክፉ ሰዎች እጅ ቢወድቁም ቀንዲላቸው አልጠፋ አልወደቀምና!!

ክፉ ልብ ይዞ የተፈጠረ ክፉ ሰው ሁሌም የራሱን ድኩም ባህሪያት ለማየት አይቶም ለመለወጥ ከቶም አይጥርም። ክፋቱና ግፈኛነቱ ሲብስበት እንጂ ሲሻለው አይታይም። ሀገራችንና ህዝባችን እንዲህ ባሉ ክፉ ሰዎች እጅ ወድቀዋል – በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርና በሶስቱ ጉልቻ ባለሟሎቹ (ብአዴን ኦህዴድ ደህዴግ) ጨጎጎታዊ መዳፍ!! ክፉዎች ደግሞ በመጨረሻ አወዳደቃቸው አያምርም። ጠቢቡ ወታደር – አቢይ አበበ – እንዲህ አስቀምጦታል ፤ ጭነቱ ምንም ባይሰማህና ባይከብድህ ፤ አወዛውዞ የሚጥልህ የማይታይህ የራስህ ምግባር ሸክም እንደሆነ አትዘንጋው።

አንጀት አርስ ቃል! ቃልም ምግብ ሆነ – ይሏል እንዲህ ነው። ጄኔራል አቢይ በዚህ አባባሉ እንደኔና እንዳተ ባሉ ግለሰቦች ምግባር ላይ ያተኮረ እንዳይመስልህ። ይልቁንም የዚህ አባባሉ ቀስት የተወነጨፈው ማህበረሰባዊና መንግሥታዊ ሃላፊነት በጨበጡት ላይ እንጂ። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ሃላፊነቱን በአግባቡና በወጉ ካልተወጣ – ህዝብን ካስለቀሰ ፤ ህዝብን ከረገጠ፤ ህዝብን ከመዘበረ ፤ ህዝብን ከፈጀ ፤ ድህነትን ጉቦኝነትን አድልዖን ዘረኝነትን ከተገበረ ካስፋፋ – እኩይ ምግባሩ በጊዜ ሂደት አወዛውዞ ከሥሩ ይመነግለዋል – ነው የሚለው ጠቢቡ ጄኔራል።

አባባሉን መሬት ላይ ስታኖረው ደግሞ እንዲህ ማለት ነው። የኢትዮጵያን  ህዝብ በግፍ ግፍ የሚገዛው ህወሃት/ኢህአዴግ ክፋቱ አይከብደውም። አይሰማውም። ህወሃት ጥፋቱ አይታየውም። የማይሰማው ፤ የማይታየው ፤ የማይከብደው የጥፋት ፤ የክፋት ፤ የወንጀል ምግባሩ ግን ህወሃት / ኢህአዴግን አውሎ ንፋስ እንዳርገፈገፈው ዛፍ ከሥሩ መንግሎ ይጥለዋል። ይህ ከቶም አይቀሬ ነው። ይህ ይሆን ዘንድ የተፈጥሮም ህግ ነውና።

እነሆ የጀመርነውን ንዑስ ርዕስ በሚከተለው የጠቢቡ ወታደር ቃል ብንሸብበውስ?

ሰው ሰው ሰው የማትበለጠው የማትሸነፈው የማትደመሰሰው ስምህን አክብረህ ለመኖር የምትመኘው፤ ሀብትህን ለምን ወይንም ለማን የምታከማችበትን ምክንያት የማታውቀው፤ ለጓደኛህ ውለታ የማትሰራ፤ ሌላው ላደረገልህ ምሥጋና የሌለህ ፤ ወገንህን ወደወጥመድ የምትመራ፤ ጠባይህን ሳታርም የሌላውን ጠባይ የምትነቅፍ፤ በወንድምህ የምትቀና በሀሰት ጎዳና የምትጓዝ፤ ከዐይንህ ጆሮህን የምታምን፤ የሌላው ስቃይና መከራ ደስ የሚልህ፤ በራስህ ብቻ የምትመካ፤ በዕውቀትህ የምትራቀቅ፤ ያሰኘኝን ሁሉ አደርጋለሁ አደርጋለሁ የምትል ሰው ሆይ መች ይሆን መታረሚያህ ?!

 

      ሀገር እና ህዝብ

አንድ፤

ሀገር ያለ ሰው ምድረ በዳ ሆና ትኖር ይሆናል። ሰው ግን ያለ ሀገር ሊኖር አይችልም። ሀገር ምን እንደሆነች ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን ሀገር የምትኖርበትን ዘዴ ገና አጥርተን ያወቅነው አይመስለኝም።

     የአንድ ሀገር ሰዎች መሆናችንን እንድናውቅና ለአንድነታችን መጠጊያ የሆነችውን እናታችንን ኢትዮጵያን ለማገልገል ለማኖርና ለኑሯችንም ለመሥራት የምንችለው በአንድ መንፈስ ስንሰለፍና በንፁህ ህሊና ፀንተን ስንተባበር ብቻ ስለሆነ ወደዚህም በቅንነት እንድንራመድ ስለሚያሻ የያንዳንዳችን መንፈስ ከደካማነት ወደ ፅኑነት መለወጥ አለበት።

      መተዛዘንን፤ መተሳሰብን፤ ጠንካራ መንፈስን፤ ቅን ባህሪይን፤ ፍቅርን እርስ በርሳችን መተዋወቅንና አለመናናቅን ማወቅ ይገባናል። ይህም በመኻላችን ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም።

ይህ የጠቢቡ ወታደር ቃል ነው። እነሆ ይህ ቃል የተፃፈውም በ1955 ዓ/ም ነው። ይህ የጠቢቡ ወታደር ቃል በዚህ ዘመን እኔንም ሆነ ትውልዴንም ሆነ ሀገሬንም ሆነ አይመለከትም የምትል የዚህ ቅኝት አንባቢ እዚሁ ላይ በጨዋ ደንብ ብንሰነባበት መልካም ይሆናል። ለምን ብትል? እኛና አንተ የምንኖረው በሁለት ዓለማት ውስጥ መሆኑ ነውና።

የጠቢቡ ወታደር ቃል የሰረሰረንና የነዘረን ዙሪያ ገባችንን ደጋግመን እንድንመረምር እኛን እኛ ባደረጉን መሰረቶችና እሴቶች እኛን ዛሬ ላይ ሆነን ለመመዘን ግፊት ለሚሰጠን ግና እነሆ በቅኝታችን አብረን እናዝግም።

ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በመፅሀፉ ያቀረበውን ሀሳብ የማስፋፋቱ ጉዳይ የአንተና የእኔ እንደሆን አስቀድሞ ነግሮናልና እነሆ እኛ በምንኖርበት ዘመን ተርጉመን የተረዳነውን እንዲህ እናወርዳለን።

ለአንድነታችን ማዕቀፍ ፤ ለእኛነታችን መለያ ፤ ለዜግነታችን መታወቂያ የሆነች ሀገራችንን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለመጠበቅ ለማራመድና እኛም አብረናት ለመራመድ አስቀድመን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የአንዲት ሀገር ልጆች መሆናችንን እንወቅ እንመንም – ይላል ጠቢቡ ወታደር በአፅንዖት።

ታዲያስ ?! ዛሬ ዘመን ቅጥ አምባሩ በጠፋ ውስብስብ ‘የማንነት’ ዘር ማንዘር አባዜ ውስጥ ገብተን የምንዳክረው አስቀድመን የአንዲት ሀገር ልጆች ፤ የአንዲት ሀገር ዜጎች – ኢትዮጵያዊ – መሆናችንን አላምን ብለን አይደለምን? እንግዲህ እኛና ሀገራችን በምንገኝበት በዚህ ምስቅልቅል ሁሉም በቅድሚያና በዋናነት ‘ኦሮሟዊ’ ‘አማራዊ’ ‘ትግራዊ’ ‘ሲዳማዊ’ … ነኝ ካለ ኢትዮጵያዊው ማን ነው? ኢትዮጵያዊነትስ ምንድን ነው? ኢትዮጵያስ የማን ናት? ሁሉም በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆኔ ተበድያለሁ እያለ በዋናነት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ጦር የሚሰብቅ ከሆነ፤ ከዘሬና ዘሬ ከሚኖርበት ክልል ውጪ ያለችው ኢትዮጵያ ገደል ትግባ ትፈራርስ ትበታተን ካለ፤ ጎሳዬ ከተበደለባት ኢትዮጵያ ወጥቼ / ተገንጥዬ የራሴን የዘሬን / የጎሳዬን መንግሥት አቆማለሁ ካለ እንግዲህ መጨረሻችን እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ ምን ሊሆን ይችላል?

 

 

ሁለት ፤

 

እነሆ ደግሞ አንባቢ ሆይ የሚከተለውን በፅሞና አንብብ ፤ አስተውልም።

እርስ በርሳችን ባለመስማማትና በመቀናናት አንዱም አንዱን ጥሎ የሚመኘውን ክብር ለመያዝና ለጊዜው ብቻ በጊዜው ለመታየት፤ ወንድምና ወንድም እየተጋጩ በውስጣችን በደረሰው መገዳደልና መዘራረፍ ከዘመን ወደ ዘመን እየተላለፈ የኢትዮጵያ ልጆች ደም ያለምክንያት በከንቱ እየፈሰሰ ህዝቡም እየተቀነሰ መሬቱ ተራቁቶ ይገኛል።

     ያለፈው አለፈ። ደጉም ሆነ ክፉውም ሥራዎች ታሪክ ሆነው ስለሚገኙ ባለፈው ከመፀፀትና ባለፈ ነገር ላይ ከመተቸት ያለፈውን ክፉ ነገር ሁሉ የታረመ ትምህርት አድርጎ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን መጭውን በማመዛዘን የዛሬው ተሻሽሎ ለነገ ሊተካ በሚገባው ላይ መድከም ግዴታችን ነው።

ለመሆኑ አቢይ አበበ ይህንን የፃፈው ለማንነው? እሚል መጠይቅ አእምሮህ ውስጥ አላሰተጋባምን? አዎ ዕውነት ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ለእኔ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ላንተና ላንቺ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ለኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ ነው። ጠቢቡ ወታደር የፃፈው ከአብራኳ ወጥተው በኢትዮጵያ ላይ ሰይፋቸውን ለሳሉት ጦራቸውን ለነቀነቁት ጥርሳቸውን ለሚያፋጩት ሁሉ ነው። እነሆ እንሰማው ዘንድ ሠዐቱ አሁን ነው። መስማት ከተቻላችሁ ህወሃትአውያን ሆይ ስሙ፤ ብአዴንአውያን ሆይ ስሙ፤ ኦህዴድአውያን ሆይ ስሙ፤ ደህዴግአውያን ሆይ ስሙ፤ … በሰፈራችሁት ቁና ትሰፈራላችሁና ከዛ በፊት ህሊና ካላችሁ ከህሊናችሁ ታረቁ! “ውርድ ተራሴ!” እንዲሉ አበው።

እነሆ ደግሞ ከእኒህ ዛሬ የኢትዮጵያን ማንቁርት ካነቁት ጀርባ ተደራጅተው ነገን በተራቸው በዘር ማንዘር  ቅኝት ኢትዮጵያን ሊቃኙዋት ከውስጥና ከውጪ የተነሱባትና “ከድጡ ወደ ማጡ” እየደገሱላት ላሉትም ሁሉ ጆሮ ካላችሁ ስሙ፤ ምክር መቀበያ ህሊና ካላችሁ ተቀበሉ – ይላችዃል አቢይ አበበ ፤ ከመቃብር በላይ በሚያስተጋባው ጥሪው።

 

ያለፈው ዘመን ታሪክ አለፈ። ከመቶ ከሁለት መቶ ከአምስት መቶ ከወዘተርፈ መቶ ዓመት ጀምራችሁ እየቆጠራችሁ በሌላችሁበትና በሌለንበት የታሪክ ኡደት በዚህ ዘመን በቂም በቀል እንድንመታተር ደም እንድንፋሰስና እንድንበታተን የምታደርጉትን ድካም ሁሉ ግቱ። ያለፈውን ደጉንም ሆነ ክፉውን ሥራ የሰሩት ትውልዶች ለታሪክ አስመዝግበው አልፈዋል። እኛም እንደ ‘ዛሬ’ ትውልድነታችን ከትላንቱ ትውልድ መልካሙን እንቀጥልበት፤ ክፉውን እንዳይደገምም እናስወግደው። የትላንቱን የተዛባ አስተሳሰብና ድርጊት በእኛ ዘመን አንድገመው። በእኛ ዘመንና በእኛ ትውልድ ትላንት ከተረከብነው ትላንት ከነበረው በሥነ ምግባር በሥነ ልቡና በፍቅር በመቻቻል በአስተዳደር በአፈራረድ በመተሳሰብ በዕድገትና በብልፅግና ተራምደን እንጂ ብሰን አንገኝ። ይህንንም መሆንና ማድረግ ያለብን ስለማንም ብለን ሳይሆን ስለራሳችን ብለን ስለመቀመጫችን ብለን ስለመኖራችን ብለን ስለልጆቻችን ብለን እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ስለመቀጠላችን ብለን እንጂ!!

 

ሶስት ፤

እነሆ አቢይ አበበ ይህንንም ፅፏል፤-

ስለሀገሩ ተቆርቋሪ ያልሆነ ሰው ለህጓ ተገዢ አይሆንም።  ድንጋጌዋንም የማያከብር አፉ ይዘልፋታል፤ አሳልፎም ለማይገባው ዘላፊ ይሰጣታል። የሀገሩንም ክብር በከንቱ የሚዘልፍ ሰነፍ ብቻ ነው። እርሱም የራሱና የወገኖቹ ጠላት ሆኖ በሚነዛው መጥፎ ምሳሌ ብዙ ደቀመዛሙርትን አስከትሎ የሀገርን ፍቅር መሰረት ለመናድ የተነሳሳ ነው።

ጎበዝ…ጄኔራል አቢይ አበበ ትንቢተኛ ነበር እንዴ? ጠቢቡ ወታደር የፃፈው እንደ ፀሀይ ብርሃን ፏ ብሎ በምድረ ኢትዮጵያ የሚታይ ሀቅ አይደለምን? እነሆ ህግ አውጥቶ ህግ የሚጥስ ፤ በህዝብ ፊት በአደባባይ ሀገርና ትውልድን የሚዘልፍ ፤ ታሪክን ‘ቧልት’ ‘ተረት ተረት’ እያለ የሚሳለቅ፤ ሀገርን አኮራምቶ ቀበሌን የሚያገዝፍ፤ ዘርፎ ለዘራፊ ሰድቦ ለተሳዳቢ አዋርዶ ላዋራጅ፤ አፈናቅሎ ላፈናቃይ የሚሰጥ መሪና መንግሥት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረው የምኒልክን ቤተመንግሥት በ1983 ዓ/ም በርብርብ ወርረው በማረኩት ህወሃት / ኦነግ / ሻእቢያ አስኳልነት አይደለምን? ከዛን ዘመን እስከዚህ በሶስቱ ፅንፈኞችና በዝርያዎቻቸው የተባለውንና የተደረገውን … ዘለፋውን የህዝብ ንቀቱን ድርጅታዊ ስድነትንና ብልግናውን ስንቱንና ስንቱን እንደምን ዘርዝሮ ይዘለቃል?

የኢትዮጵያዊ ሀገር ፍቅር መሰረቱና ፅናቱ በህወሃት / ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ ድውይ ፕሮፓጋንዳና እኩይ ምግባር ተገዝግዞ ተሰርስሮ ተሸንቁሮ ተሸራርፎ ለይቶለት ባይናድም ቅሉ አልተገዘገዘም አልተሸነቆረም አልተሸራረፈም ብሎ የሚደፍር ይኖር ይሆን? “የሀገሩን ክብር በከንቱ የሚዘልፍ የራሱና የወገኖቹ ጠላት ሆኖ በሚነዛው መጥፎ ምሳሌ ብዙ ደቀመዛሙርትን አስከትሎ የሀገርን ፍቅር መሰረት ለመናድ የተነሳሳ ነው – በማለት አቢይ አበበ የተነበየው ዛሬ  በኢትዮጵያ ምድርና አልፎም በመላው ዓለም በተበተኑት ኢትዮጵያውያን መካከል የተከሰተ ክፉ ሰዎች የፈጠሩትና ክፉዎች ደቀመዛሙርትን ያፈሩበት የክፉ ዘመን ጎጣዊ በሽታ አይደለምን?  የደቀመዛሙርቱ ስምና ቀለም ቢለያይም ቅሉ!!

 

አራት ፤

ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ‘አውቀን እንታረም’ በማለት የጎጥንና የጎሳን ጉዳይ አስመልክቶ በአፅንዖት ካሰፈርው ውስጥ የሚከተለውን ደግሞ ያስተውሏል፤

ሰው በራሱ ከተመካና ስለራሱ ብቻ ካሰበ ከሰው ጋር ሊኖር አይችልም። የራሱን ሀሳብ ብቻ ተርጓሚና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ከሆነም የማህበራዊ ዕድገት አይስፋፋም። ስለዚህም ማንኛውንም ሁሉ የጋራ ጉዳይ በማድረግ ተመልክቶ አጣርቶና ተባብሮ ለሚበጀው ነገር ብቻ መጠመድ ፍቅርን ስለሚጠይቅ አንተ ትብስ አንተ ትብስ ተባብሎ መፎካከር ቅን መንገድ ይመራልና በዚህ ዐይነት መጓዝ ግዴታ ነው።

     የሚመሰገኑና የሚነቀፉ ባህሎቻችንን ለይተን አውቀን የምንተወውን ትተን የምንይዘውን ማዳበር አለብን። በየጎራው ፤ በየሸንተረሩ ፤ በየመንደሩና በየጎጡ በየጎሳውና በየክፍሉ በየሃይማኖቱ ከመመካት ለአንዲት ኢትዮጵያ ብለን የምንሰራው ሁሉ የጠቅላላው መደርጃ ጥቅም መሆኑን ብቻ እንመንበትና እንነሳ።

     ሕግ እንዲከበርና እንዲፀና አዋጅም እንዲሰራ አድልዖና ልዩ አስተያየት የሚባሉት ይቁሙ። ሥልጣንም ማዕረግም ለግል ጥቅምና መከበሪያ አይሁን። ማንኛውም የሀገር ሰው በችሎታውና በሥራው ብቻ ይመረጥ እንጂ በወገንና በባለወገንነት አይደገፍ። በጥፋት የተገኘ ባለሥልጣንም ጥፋቱ ለህዝብ ተገልጦ ይነገርበት።

አንባቢ ሆይ! ይህንን ጥልቅና ምጡቅ እንዲሁም ክቡር ሀሳብ አንተው ካገርህና ከመንግሥትህ ከራስህም ተሞክሮና ህይወት ጋር እያሰናሰልክ ተርትረው እንጂ ቃኚው ለማብራራት አይዳዳውም። ነገር ግን ቃኚው ይህን ይላል፤- ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ አርቆ አሳቢና ተመራማሪ የነበረ ፤ መንፈሳዊ ቅንንት ከሀገራዊና ወገናዊ ፍቅር ጋር የሰረፀበት ከዘመኑ አብሪ ትውልድ መካከል አንዱ አንደነበር እስካሁን የነቀስናቸው ፅንሰ ሀሳባዊ ምልከታዎቹ ዋቢ አይሆኑምን? እነሆ በዚህ ከተስማማን ጥቂት አብረን እናዝግም።

 

አምስት ፤

 

እነሆ ደግሞ ቀጣዩን ወደ ውስጥህ እየተመለከትክ ልብ ብለህ አንብበው!

በአሁኑ ጊዜ ህብረት እንጂ የሀሳብ መነጣጠል ለሀገሪቱ አይጠቅምም። ደግሞም በተለዬ ጥቃትና ጭቆና የማይወደው የሀገራችን ህዝብ የሚተባበረው መከራ ሲደርስበት ብቻ ነው። ይህ ለምን ይሆናል? አንድ ክፉ ነገር በሀገሪቱ ላይ ከመድረሱ በፊት የሚደረገው መተባበር እንጂ ከደረሰ በሁዋላ በመቆጨት አይዞህ ወንድሜ መባባሉ ዋጋ የለውም።

     ዛሬ የተያዘውና የሚታሰበው መነቃቀፍ ብቻ ሆኖ ይገኛል። መነቃቀፍም አርቆ ማስተዋል የሌለበት የአለ ይበሉኝና የወሬ ማዳነቂያ መደብር ሆኖ ከመገኘቱ በስተቀር ፍሬ አፍርቶ አልታየም።

አጀብ ነሽ ኢትዮጵያ! ያኔም (በ1950ዎቹ) እንዲህ ነበርሽ? ዛሬስ (በ2ሺህዎቹ መጀመሪያ) እንደ ያኔው ነሽ? ወይስ ትለያለሽ? አንባቢ በያኔውና በአሁን አንድነቱንና ልዩነቱን አንተው ዘርዝረው።  እኛ ግን በዚህ ዘመን ባለው የሀሳብ መነጣጠል መነቃቀፍና ህብረት ማጣት ላይ ጥቂት እንቆዝማለን።

አቢይ አበበ አስቀድሞ ያወረደውን አንቀፅ ተረካቢ ባለቤቶች አሉ። እነርሱም በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ከህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ ፍዳ አገዛዝ እንታደጋለን እሚሉት በተቃዋሚው ጎራ የሚገኙት አያሌ ድርጅቶች ናቸው። እነሆ ከሁለት አስርታት በላይ በአንድ መድረክ ተገናኝተው በጋራ መምከር፤ በአንድ ጥላ ቆመው በጋራ መራመድና የጋራ ክንድ ማንሳት አልቻሉም። ስንት ህብረት ስንት ቅንጅት  ስንት መድረክ  ስንት ውህደት ተፈጥረው ፈረሱ? ለመሆኑ ‘የብሄር’ ነፃ አውጪው ድርጅት ስንት ነው? (ለነገሩ ሃያ ስድስት ዓመት ምኒልክ ቤተ መንግሥትን የተቆጣጠረው ገዢም ዛሬም ድረስ መጠሪያው ‘የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር’ አይደለም?) በኢትዮጵያ ስም የተደራጀውስ ፓርቲ ግንባር ጦር የሲቪክ ማህበር ስንት ነው? መዘርዘሩ ራሱ ያታክታል … አቢይ አበበ እንዳነጠበው – መነቃቀፉም አርቆ ማስተዋል የሌለበት የአለ ይበሉኝና የወሬ ማዳነቂያ ሆኖ ከመገኘቱ በስተቀር ፍሬ አፍርቶ አልታየም! (የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ዛሬ ላይ በየፊናቸው የሚገኙበትን ሀቅ እንደምን በመሰለ ውብ አገላለፅ ነው ያስቀመጠልን?!)  እንግዲህስ በዚህ ነቁጥ እዚህ ላይ ይብቃን። አቢይ አበበ ግን ይቀጥላል ፤-

የሀገሩን እድገትና ሥልጣኔ የህዝቡንም ደህንነትና ስለከፍተኛ ኑሮው ደረጃ ማደግ የማይመኝና የማያስብ በአሁኑ ጊዜ ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን አንዳንድ በጎ አሳቢና ሁሉን ያወቅን ነን ባዮች ሌላውን ወገን ያላወቀና ያልገባው ተመቅኝና ልዩ ሀሳብ ያለው  እንዲያውም የሀገሩ እድገት እንቅፋት ነው በማለት በሚያትቱት አሉባልታ የሚነዛው እድፍ እገባውም አልገባውም ላይ ማረፉ ስለማይቀር ለማንኛውም ወገን ሊበጀው አይችልም። የዚህም ዐይነት ሽሙጥና ማንኛውም ዐይነት አነጋገር ሁሉ ለሀገሪቷ ፈውስ የሚሰጥ መድሃኒት አይደለም።

     ጥንታዊቷንም የዛሬይቱንም ኢትዮጵያችንን የወደፊትም እንድትሆን ካስፈለገ በቅን መንፈስ በፍቅርና በመተሳሰብ ደግፈን እናዘልቃታለን ብለን ካልተነሳን በቀር በአሉባልታና በመነቃቀፍ፤ በሀሰት በመነዳትና በወሬ በመሰልጠን በንፁህና በተባረከው ህዝቧ ተንኮል በመዝራት እንደዚሁም በሰው ሀገር ጉዳይ ውስጥ እየገቡ አሳቢ በመምሰል የህዝቧን መነጣጠል ለሚገፋፉ ባዕዶች ደጋፊና ተባባሪ ሆኖ በመገኘት ጥቅም ይገኛል ብሎ የሚያስብ ቢኖር በተሳሳተ መንገድ መሄዱን ይረዳው። ከእንደዚህም ያሉ ሰባኪያን መራቅ የማንኛውም ሀገሬን እወዳለሁ የሚል ሰው ጥንቃቄ መሆን አለበት።

     ላንዲት ሀገር ከልጆቿ የበለጠ ደጋፊና አሳቢ ሊኖራት አይችልም። አሳቢ መስለው ልጆቿን በመለያየት የሚጠቀሙ እነማን እንደሆኑና የመለያየት ትርጉም ምን እንደሆነ ሀገራቸውን ወዳድ የሆኑ ሰዎች ሁሉ አእምሮ በቀላሉ ሊመዝነው ይችላል። ከሁሉ የባሰ አንድ ሀገርንና ህዝቧንም ወደ ከንቱ ምሣሌ የሚመራው ያልታመነ ተስፋ ነው።

የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊ፤ የኢትዮጵያ ልጅ ኢትዮጵያዊት ሆይ! እነሆ ገና በማለዳ ቅኝታችንን ስንጀምር የጠቢቡ ወታደር መፅሀፍ ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ አነጋጋሪና ልጓም አስጨባጭ ብለን የመነሳታችን አንጓ ነቁጥ አንዱ አስቀድሞ የነቀስነው መልዕክት ነው። እነሆ ደግሞ እኛ ይህንን የአቢይ አበበን መልዕክት በዘመናችን የተረዳነውና የተረጎምነው እንዲህ ነው፤-

በዚህ ዘመንና በዚህ ትውልድ ውስጥ (በዛሬይቷ ኢትዮጵያ) እየኖረ ጥንታዊቷን ለዛሬዋ መሰረት የሆነችውን ኢትዮጵያን (የአፄዎቹ የሚል ቅፅል ሰጥቷት) እንደ ማርያም ጠላት አልያም መስጊድ እንደ ገባች ውሻ በየአቅጣጫው ድንጋይ የሚወረውርባት ሜንጫ የሚያፋጭባት ትበጠስ ትቆረጥ ትበተን ገደል ትግባ እያለ የዘመተባት ሁሉ አደብ ገዝቶ ይህንን የጠቢቡን ወታደር ቃል እንዲመረምር እንዲያበራይና እንዲያጠና በኢትዮጵያዊነታችን እንጋብዛለን። የጠላቶቿ መሳሪያ ፤ የትዕቢተኛና የሥልጣን ናፋቂ አውቀናል ባዮች ጎጠኛ ምሁራንና ባዕዳን ሀይሎች መናጆና መሰላል ፤ የወንበዴና ዘራፊ እኩይና ፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ከለላ ከመሆን ታቅቦ የትላንቷ ኢትዮጵያ ተረካቢ መሆኑን አምኖ ታሪኳን በታሪክነቱ ተቀብሎና አክብሮ እንደ ትውልድ እንደ ዜጋ የበኩሉንና የሚኖርበትን ዘመን ለሚኖርበት ትውልድ መልካምና ቅን ተግብሮ ከትላንቱ ልቆና ዳብሮ ደግሞ በተራው ለነገው ለማስረከብ እንጂ ያልኖረበትንና የትላንቱን “ክፋትና ጥፋት” እያመነዠከ በከንቱ ቅዥትና በቀቢፀ ተስፋ እየዳከረ ለበቀልና ለጥፋት እንዳይኖርም ሰሚ ጆሮ አስተዋይም ልቡና ላለው ወገን ሁሉ “አቤት” እንላለን።

አንድ ሀገርንና ህዝቧንም ወደ ከንቱ ምሣሌ የሚመራው ያልታመነ ተስፋ ነው – ብሏልና ጠቢቡ ወታደር – በቀቢፀ ተስፋ  “ቅዥታዊ ራዕይ” እየሰበክን በከንቱ ተግባር የክቡር ኢትዮጵያውያንን ደም ከማፍሰስ ወይም እንዲፈስ ከማመቻቸት ፤የክቡር ኢትዮጵያውያንን ሠላም ከማናጋትና የአንድነትን ፍቅር ከማደፍረስ መቆጠቡ ከታሪክ ተጠያቂነትና ወንጀለኛነትም ያድናልና አውቀን እንታረም – ይላችዃል ጠቢቡ ጄኔራል።

 

ስድስት ፤

 

እነሆ ትዕግስቱና ማስተዋሉ ላንባቢ ይሁንና በእኛ በኩል ቅኝታችን ይቀጥላል።

 

በየአለንበት ሥፍራ ስንኖር ጥረን ግረን እንድንበላ ታዟል። ይህንንም ስናደርግ እንታያለን። ግን ድካማችንና መታከታችን ሁሉ ለምንድን ነው? ለማንስ ነው? የድካማችንስ ፍሬ ምን ይሆን?

     የተለመደውን ሀተታ በመያዝ ድካማችን ለሀገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል። ነገር ግን ይህን መናገር የሚገባው በአንድ ትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት።

     እንግዲያውስ እንደሚታየው ከሆነ ድካማችን ለየግል ፍላጎታችን ሆኖ የድካማችንም ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው።

     እነሆ አስቀድሞ በተነቀሰው መልዕክት ውስጥ ቃላቱ በአእምሯችን ጓዳና አደባባይ እንደ ክላስተር ቦንብ (ተፈነጣጣሪ) በየአቅጣጫው ሲፈነዱ ይሰማናል። ለምን? ለምሳሌ ከ’ተቃዋሚው ጎራ’ በየመድረኩ በየጋዜጣው በየሬዲዮው በየቴሌቪዥኑ በየወዘተርፈው የሚቀርበው አብዛኛው(?)  የፖለቲካ የሲቪክ የጎጥ /የዘር ድርጅት መሪ ወይም አክቲቪስት ዲስኩሩን ሲሰጥህ – የሚያስረግጠው ቃል – ድካሙና መስዋዕትነቱ ለሀገርና ለመጪው ትውልድ መሆኑን። እና ይህን ‘ተቃዋሚ አካል’ ፤ ይህን ‘በጎጥ የተደራጀ’ – ይሄ መንገድ አያዋጣንም፤ ይህ ራዕይ አያዛልቀንም፤ እልህና ከማን አንሼ ሀገር አይገነባም  ለትውልድ ሠላም አይሰጥምና ታርመንና አደብ ገዝተን መኻል መንገድ ተገናኝተን (ፅንፍ ለፅንፍ ሳንቆም) ተወያይተን መላ መትተን ተያይዘን እንራመድ” ብትለው … ይፈርጅኻል፤ ይወርድብኻል፤ ‘ፔቲሽን’ እየፈረመና እያስፈረም ቢችል ከሥራህና ከምትኖርበት ሀገር እንድትባረር ‘ኡኡ’ ይላል። ለምን? የርሱ መንገድ ብቻ፤ የርሱ ራዕይ ብቻ፤ የርሱ ቀኝ ጌታ (መሪ) ብቻ የርሱ ‘አክቲቪስት’ እንጂ ጎዳናውና የዕውነት መንገዱ። ለሀገርና ለትውልድ መሥዋዕትነቱ በእርሱ ድርጅት በእርሱ መሪ ከእርሱ ጎን መቆም ብቻ እንጂ ዕውነቱ። ካልሆነ “ወይ ከኛ ወይ ከነሱ” ይልኻል – ሶስተኛና አማካይ መንገዱን ዘግቶ።

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ዙሪያዋን ቀስፎ የያዛትና የዘመተባት ጎጠኛ አካል አደገኛነት እጅግ መረን ከመልቀቁ የተነሳ ግማሹ “የአፄዎቹን ኢትዮጵያ አናውቃትም ገደል ትግባ፤ ትበተን” ሲል፤ ሌላኛው ወገን ደግሞ አጥንት እየቆጠረና ቀበሌ እየጠራ “አፄዎቹ” “የኛ ናቸው” እያለ ታሪክንና ኢትዮጵያውያንን ከርሱ ዘር ክልል ከማውጣት አልፎ የሀገር መሪዎቹን የኢትዮጵያን ሠንደቆች አውርዶና አኮስሶ በርሱ ቁመትና በርሱ ቀበሌ ለክቶ ያቆማቸዋል። ዘረኝነት እርከን ካለው እኒህ አዳዲሶቹ የዘመነ መሳፍንት ቀበሌያውያንና ጎጠኞች አክቲቪስቶች የህወሃትን የዘረኝነት መንፈስ በአዲስ ጎዳና ላይ ቀደው ወዳልታወቀ እርከን አሸጋግረውታል።

እናንት የዚህ ዘመን አዳዲስ ዘመነ መሳፍንት አክቲቪስቶችና ማህበርተኞቻቸው ሆይ! የኢትዮጵያን ነገሥታትና መሪዎች ከኢትዮጵያ ማማ ላይ አውርዳችሁ በየጎጥና ቀበሌ ኮንፍረንስና ስብሰባችሁ ግርግዳ ላይ እየሰቀላችሁ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የኢትዮጵያ ዳርቻዎች በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነታችን ብቻ የምናምነውን ከመሪዎቻችንና ከታሪካችን (ከትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር /ህወሃትም በረቀቀ መንገድ) ለመነጠልና ባይተዋር ለማድረግ የምታካሂዱብንን ከፍተኛ የሥነ ልቡና ርብርቦሽ አቁሙ!!! አፄዎቹና ታሪካቸው የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ብቻ ነው። አባትነታቸውም በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነታቸው ለማይደራደሩ መላ ኢትዮጵያውያን እንጂ ለአዳዲሶቹ ዘመነ መሳፍንት ቀበሌያውያን አክቲቪስቶችና ማህበርተኞቻቸው አይደለም!! ጆሮ ካላችሁ ስሙ ልቡና ካላችሁ ተመለሱ መካሪ አዛውንቶች ካሏችሁም ምክር ተቀበሉ!!

 

እንግዲህስ ‘ንግባዕኬ ሃበ ጥንተ ነገር’ እንዲሉ እኛም ወደቀደመ ጉዳያችን እንመለስ።

 

በዛኛው ጎራ ደግሞ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ከነባለሟሎቹ የሚያላዝነው የሚሰብከው የሚምል የሚገዘተው ድካሙና ጥረቱ መሥዋዕትነቱ ሁሉ – ለሀገርና ለመጪው ትውልድ መሆኑን። የሚደንቅና የሚገርመው የህወሃት ኢህአዴጉን ተግባር በራስህ በቤተሰብህ በጎረቤትህ በሰፈርተኛው በሀገሬው ላይ ያደረሰውን ቁስል  ያስከተለውን ሰቆቃ በደልና ኢፍትህ በአይንህ እያየኸው በሰራ አካልህ እየዳሰስከው አሌ ይልኻል፤ ይህን ሁሉ የሚያደርገው – ለሀገርና ለመጪው ትውልድ ከርሱ በላይ ተግባሪ ከርሱ በላይ አሳቢ ከርሱ በላይ ወኪል የሌለ መሆኑ።

እነሆ እንግዲህ ግራና ቀኝህን ስታስተውል ነው የጠቢቡ ወታደር ቃል እንደ ፈንጂ የሚፈነዳብህ። … ድካማችን ለሀገራችንና ለመጪው ትውልድ ነው የሚል ሞልቶ ይሆናል … ይህንን መናገር የሚገባው በአንድ ትውልድ ዘመን አብሮት ላለው ጓደኛው /ህዝብ፤ ትውልድ/ የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው መሆን አለበት፤ ይላልና አቢይ አበበ።

የራሱን ትውልድ አካል እንደ ጉድ እየጠላ እየናቀ እየረገጠ እያሰቃየ እየበደለ እያንጓጠጠ እየፈጀ እየፈረጀ እያስራበ አያፈናቀለ እያሰረ እየገደለ አካል እያጎደለ በጎጥና በወንዝ እየፈረጀና እየተደራጀ ሌላውን ወገኑን እያገለለ … ስለሀገርና ስለነገው ትውልድ ወይም ስለማንነቴ ነው ድካሜና መሥዋዕትነቴ ብሎ ጩኸት አይገባኝም አይዋጥልኝም ነው ያለው ጠቢቡ ወታደር አቢይ አበበ። በአደባባይ የሚታየውና የሚሆነው አቢይ አበበ እንደታዘበው ድካማችን ለየግል ፍላጎታችን ሆኖ የድካማችንም ፍሬ በልቶ መሞት ብቻ ነው።

 

ሰባት ፤

 

ቀጣዩን የጠቢቡን ወታደር ቃል ደግሞ ያጤኗል፤

 

ትንሽም ብትሆን ደግ ነገር ሰርተን ካልተሸኘን እኛን የሚያስታውስ ምንም ምክንያት አይኖርም። ምናልባት እንኳ ወግ ባለው መቃብር ተቀብረን መቃብራችንም በእምነበረድ አጊጦ ስማችን በላዩ ላይ ተቀርፆ ቢታይና ቢነበብ የሚያመለክተው የስም መቃብርነቱን ነው። አለበለዚያ ግን የትም ዋሻ ውስጥ ተወርውረን አንድ ቀን መከረኛው አፅማችን ከአፈር ውስጥ ብቅ ብሎ ሲታይ የሰው አጥንት ተብሎ በተፈጥሮ ስማችን ብቻ ያስነሳን ይሆናል እንጂ የእገሌ አያሰኘንም።

 

     አዎ ሀቅ አንጥቧል አቢይ አበበ። ሠው በዚህች ምድር ላይ በሚቆይበት ዘመኑ መልካም ነገርን ቢያደርግ ማንን ምን ይጎዳል? ፍቅርን መስበክ ፍቅርን ማስተማር በፍቅር ስለመኖርና ስለ ፍቅር ይቅር ማለትን ለወገኑ ቢያስተምርና ወገኑን በፍቅር ቢያንፅ ሀገሩ ሠላም ፤ ህዝቡ ሠላማዊ ዕድገትና ብልፅግናው የጋራ ይሆናሉ። አንድነት ይፀናል። ጥላቻ ይኮሰምናል። መተሳሰብ መተዛዘን መደጋገፍ ይጎለብታል። ይህ ሁሉ ቅን ከመሆን ይመነጫልና። ይህ ሁሉ መልካም ልቦናን ይዞ መልካም ለማድረግ ከመነሳት ዕውን ይሆናል። ኢትዮጵያውያንን በዚህ ዘመን የራቀን ቅንነት ነው። መልካም አስቦ ለመልካም መነሳት ነው የሸሸን፡፤ ከፍቅር ሳይሆን ከጠብ ስለምንጀምር ነው አድባር አውጋሩ የተጣላን። አቢይ አበበ ሊነግረን የፈለገው ይኸው ነው። በከንቱነት ኖረን በእብነበረድ ተቀበርንም አልያም ስም አልባ መቃብር ገባን…ያው አስታዋሽ የሌለው ከንቱ ህይወት ኖረን ነው ያለፍነው ማለቱ ነው ጠቢቡ ወታደር።

 

አቢይ አበበ ለሀገር ዕድገት ጠንቅ፤ ለመልካም አስተዳደር ዕንቅፋት፤ ለህዝብ ብልፅግና ነቀርሳ የሆኑትን ቅልብጭ አድርጎ ሲያስቀምጥና ምክሩንም ሲለግስ ደግሞ እንዲህ ይላል፤-

 

ምቀኝነት፤ ቅናት፤ ተንኮል፤ ሀሰት፤ ጉቦ፤ ዕምነት ማጉደልና አድልዖ እነዚህ ከቀሩ ማንኛውም ነገር ቀጥ ብሎ በንፁህ መንገድ ሊሄድ ይችላል። እነዚህን ደግሞ ለማስቀረት የሚችለው ንፁህ ህሊና ብቻ ስለሆነ ህሊናችንን ለማንፃት እንታገል።

 

ስምንት ፤

እነሆ እንግዲህ የመጀመሪያውን መጨረሻ ያለ ቃኚው ምልከታ እናስከትላለንና አንባቢ ሆይ ተበራቺ ፤ አንባቢ ሆይ ተበራታ።

    ኢትዮጵያ ትላንት ወይም ዛሬ የተፈጠረች ሀገር የተዘረጋች ምድር አይደለችም። ከእኛ በፊት የነበሩባት ሰዎች ኖረውባት አልፈዋል። የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መሠረት ታሪካችን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአሁኑ ትውልድ እስካለነው ድረስ በሀገሪቷና በህዝቡ ላይ የደረሰውን በጥቂቱ በህሊናችን ውስጥ ብናመላልሰው ለአለንበት ሁኔታ ምክንያት ሆኖ ወደ ሁዋላ ያስቀረንን በአጭር መንገድ ልንረዳው እንችላለን።

    እነማን ነበሩ? እነማንስ አሉ? እነማንስ ይኖራሉ? የተወደደችው ሀገራችን ግን ነበረች አለች፤ የምትኖረው ግን እንድትኖር አድርገን ስንይዛትና ስናገለግላት ነው እንጂ እንድትወድቅ ስናንገዳግዳት አይደለም። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ማለትም በአፍአዊ አነጋገር ሳይሆን ከእኛ ከልጆቿ የሚጠበቀው የሆነ ይሁን ማለት ትቶ ሊሆን የሚገባውን መርጦ የሚበጀውን ማድረግ ብቻ ነው።

 

    በሥልጣን ላይ የሚገኝ ሁሉ የገባበትን ቃልኪዳን አክብሮ አስታውሶም ሀገርንና ህዝብን ፤ ማህበራዊ ኑሮን እንጂ ክብሩንና ሥልጣኑን አገልጋይ አይሁን።

    ቀደም ካለው ትውልድ የምመጣ ስለሆንኩ በሀገራችን የሆኑትንና ያለፉትን የደረስኩባቸውን አጥርቼ ስለምረዳው የነበረውንና ያለውንም ሳመዛዝነው እደረስንበት ሥፍራና ደረጃ እንደምን እንደሆነ በበኩሌ ደህና አድርጌ እገነዘበዋለሁ።

 

    ይኸውም የሀገር ፍቅር አቃጥሏቸው ደማቸውን ባፈሰሱት ብዙሃን ትጋትና ዕውነተኛ መሥዋዕትነት መሆኑ አይካድም። ባለታሪክ የሆኑት አባቶቻችን የነበረባቸውን ትግልና ድካም፤ የውስጥ ተቃዋሚ ወገንንና የውጪ ጣልቃ ገብ የባዕድ ፖለቲካ በትዕግሥት አልፈው የገነቧትን ሀገራችንን በቅርቡ ተወልደው ፤ ደርሰው ፤ ያዩዋት እንዲህ ሆና የቆየች ትመስላቸው ይሆናል። የደረሱበትንም እንደ አቅሙ የተደላደለ ጊዜ ከመንቀፍ በፊት እንዴት ኖሯል ብሎ ወደሁዋላ የነበረውን ጠይቆ፤ ተረድቶ ያለውን አመስግኖ ስለመጪው መሻሻል ትጋትን አሳይቶ የአሳብ ተካፋይና የሥራ ረዳት ሆኖ በትጋት ማከናወን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ፈንታ ስለሆነ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ዕውቀትና ጉልበቱን መሥዋዕት ማድረግ ይኖርበታል።

    መሥራት አስቸጋሪ ነው። ማፍረስ ግን በጣም ቀላል ነው። የፈረሰን ደግሞ መልሶ መሥራት ከሁሉ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ያንን የተከፋፈለ አሳብ ያንን የተወሳሰበ መጥፎ ልማድ፤ ያንን የተጨቆነ የህዝብ መብትና ነፃነት ፤ ያንን የተናቀ የገዥነትና የተገዥነት መንፈስ ለማጥፋት ፤ እንደዚሁም ፈርሳና ወድቃ የነበረችወን ውድ አገራችንን እንደገና ለማቋቋምና ከነፃ አህጉሮች ጎን እንድትሰለፍ ያደረጓት ሁሉ ባለውለታዎች ናቸው።

    ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ዓይናችንን ከከፈትነው አንዳንዳችን ያልተደረገውን ወደ ሌላ በመተርጎምና ውለታ ቢሶች ሆነን ከመገኘት እርቀን ለሁላችንም ለሀገራችንም የሚበጀውን ብቻ በፍቅርና በህብረት አስማምተን ተደጋግፈንም እፊታችን የተደቀነውን የትየለሌ ተያይዘን በጊዜያችን ልናደርግ የምንችለውን ያህል እንወጣ።

 

    ስለሀገራችን ክብር የተሰዉትንም አፅማቸውም በያለበት የረገፈውን ጀግኖቻችንን ሁልጊዜ እናስታውሳቸው። ስማቸውም በታሪክ ጎልቶ እንዲኖር እናድርግ። ውለታቸውም ይወሳላቸው። ምንም ጀግናን የሚፈጥረው የጊዜው ሁኔታ ነው ቢባልም አዲሱ ጊዜ የሚፈጥረው ጀግና የቀድሞው ጊዜ ጀግና ስምና ታሪክ መነሻና መቀስቀሻ እንደሚሆነው አያጠራጥርም።

    እንግዲህ ከዚህም ከዚያም ጠቅሼ የደረደርኳቸው እዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሰፈሩት አነጋገሮች ሊነቀፉም ፤ ሊያስነቅፉም ፤ ሊያከራክሩም ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን በማንኛውም ዓይነት ይሁን በንፁህ ህሊና ብቻ በመመራት ወደፊትም የሚጠበቅብንን በመገመት ማንኛችንም ተባብረን ለውድ ሀገራችን  የዕውነት አገልግሎት ማበርከት እንዳለብን ማሳሰቤ ነውና “አውቀን እንታረም”

 

 

 

ማሳረጊያ፤

 

እነሆ የሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበን ታላቅና ክቡር መልዕክት ያዘለውን መፅሀፍ በዘመናችንና በትውልዳችን ካለው ነባራዊ የሀገራችን ፖለቲካዊና ሥነ ማህበራዊ ዕውነታ ጋር እያነፀርን የቃኘንበትን ሥራ ማሳረጊያችን ደረሰ።

የሌ/ጄ አቢይ አበበ “አውቀን እንታረም” ‘መቅድም’ ‘መነሻ’ና ‘መድረሻ’ ይዞ በሶስት ምዕራፍ በ57 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን መፅሀፉ በፖለቲካ፤ በማህበራዊ በአስተዳደርና በለውጥ ላይ ያለው አመለካከት ሰፊ የመሆኑን ያህል ጥቅልና ጥልቅ በሆኑ ንድፈ ሀሳቦችም የተሞላ ነው። አቢይ አበበ መፅሀፉን ለንባብ ያበቃው በብርጌዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይና በወንድሙ ገርማሜ ነዋይ የተጠነሰሰው የ1953 ዓ/ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ (በተለምዶ የታህሳስ ግርግር ይባላል) ከከሸፈ በሁዋላ ነበር። ከጄኔራል አቢይ ‘አውቀን እንታረም’ ሀገራዊና ትውልዳዊ መልዕክትና ተማፅኖ እንደምንረዳው ነውጥን ወይም ደም አፋሳሽ አብዮትን አጥብቆ ይቃወማል።

በኢትዮጵያ የተሞከረው የመጀመሪያው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲከሽፍ ብርጌዴር ጄኔራል መንግሥቱ እና ወንድሙ ገርማሜ ነዋይ በቤተመንግሥቱ ውስጥ አግተዋቸው ከነበሩት የሀገሪቷ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አስራ አምስቱን በጥይት ደብድበው የፈጁዋቸው ሲሆን ከእኒህ ለሀገራቸው ከደከሙ አድባራት አንዱ የጣሊያን ቦንብና መትረየስ ያልጣላቸውና ከነፃነት በሁዋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ክቡር ራስ አበበ አረጋይ ይገኛሉ።

አቢይ አበበ ከሁሉም በላይ በሌሎች ሀገራት ያለን የግራ ፖለቲካና ሥርዐተ መንግሥት እንዳለ ቀድቶ በኢትዮጵያ ላይ ለመጫን መነሳትን ሲቃወም ለኢትዮጵያ ሀገራችን የፖለቲካ፤ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት አማራጭ አይደለም ከሚል ፅኑ ዕምነት መሆኑን በገሀድ ያመለክታል። ለዚህም ይመስላል፤ – የሚበጀንን የውጪ ፖለቲካ ከመከተላችን በፊት የሚበጀንን የውስጥ ፖለቲካችንን ማደራጀት የሚገባን እኛው ነን። የውስጥ ፖለቲካው ያልደረጀ ህዝብ ብዙውን ጊዜ ሊከተለው የሚገባውን የሌላውን ሀገር ፖለቲካ አጥርቶ ሊያውቅና ሊጠቀምበት አይችልም። የአባቶች ምሳሌ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ይላል – ሲል ዘመን ተሻጋሪ ትውልድ አስተማሪ አስተውሎቱንና ምክሩን ያስቀመጠልን።

 

ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥቱ ተሳትፈው የነበሩትና ሁዋላም ስለዚሁ ታሪካዊ መፈንቅለ መንግሥት ሂደትና ክሽፈት መፅሀፍ የፃፉትም ሆኑ ወይም በዘመኑ የኖሩ የርሱ ትውልድ አካላትና ከርሱ ጋር የመስራት ዕድሉን ያገኙ ሁሉ ስሙንና ምግባሩን በአርአያነት የሚጠቅሱት ሲሆን ታላቅ ሰብዕና፤ ቅንነትና ፍፁማዊ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ስለመሆኑም ምሥክርነታቸው በተለያዩ መፃህፍት ላይ ሰፍሮ ይገኛል። አቢይ አበበ ከአድልኦ ፤ ጉቦና ከመሳሰሉት የነፃ – የሀገርና የህዝብ ንብረትን ለግሉ ያላዋለ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ ስለመሆኑም ተመስክሮለታል።

እነ ራስ አበበ አረጋይ ያለ ፍትህና ርትዕ ከተጨፈጨፉ ከ14 ዓመት በሁዋላ በመስከረም 1967 ዓ/ም ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መቀመጫ ቤተ መንግሥት በሁለተኛው ዙር ወታደራዊ ስብስብ ስር ወደቀ። ታህሳስ 14 ቀን 1967 ዓ/ም በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ አባላት ጭብጨባና በመሪው በሻለቃ መንግሥቱ ሃይለማርያም ፊርማ እድሜያቸውን ሙሉ ለውድ ሀገራቸው ደፋ ቀና ሲሉ የኖሩትንና በአብዛኛው ከመጀመሪያው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተረፉት የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ መንግሥት ባለሥልጣናትን ያለ አንዳች ፍትህና ርትዕ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ በታዘዘው መሰረት በጥይት ተደብድበው ህይወታቸው ካለፈው አንጋፋና የሀገር አድባራት ኢትዮጵያውያን አንዱ ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ነው።

ሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ በደርግ ጥይት ተደብድቦ ሲገደል ዕድሜው 56 ዓመት ነበር። በዚህ ዘመነ ፅልመት ቀን በግፍ ግፍ ከተረሸኑት መካከል ክቡር ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ (ጠቅላይ ሚኒስትር)፤ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን (ጠቅላይ ሚኒስትር) ፤ ልዑል ራስ አስራተ ካሳ ፤ ክቡር አቶ አካለ ወርቅ ሃብተ ወልድ እና በድምሩ ሃምሳ ሁለት የግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ የሲቪልና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሲገኙ በዚህ ዕለት በድምሩ ደርግ በጥይት ደብድቦ የፈጃቸው ስልሳ ኢትዮጵውያን ናቸው።

በታህሳስ 14 ቀን 1967 ዓ/ም ያለ አንዳች ፍትህና ርትዕ በኢትዮጵያ ሰማይ የደም ዘመንን የጀመረው ወታደራዊው ደርግ የእኒያን አንጋፋ የኢትዮጵያ አድባራትን ታሪክና ገድል ግን ከሥጋቸው ጋር በጥይት ደብድቦ መቅበር አልቻለም። እነሆ ዛሬ ዘመን በምድረ ኢትዮጵያ ምን እሾሁና አሜኬላው ቢበዛ ከደርግ መንግሥት መሪዎችም ሆነ ከኢህአዴግ እኩይና እርጉም ባለሥልጣናት በትውልዱ እጅግ እየፈኩና እየተከበሩ ስማቸው ከመቃብር በላይ በፍቅርና በክብር የሚነሳው እኒያ ጥንታውያኑ አባቶቻችንና በደርግ ጥይት የወደቁት የጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ሰማዕታት ናቸው።

እነሆ እኛም እድሜ ሰጥቶን ከእኒያ የቀድሞው ትውልድ አባቶቻችን መካከል የሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበን ታላቅና ክቡር የኢትዮጵያዊነት መልዕክት የተላለፈበትን ምጡቅ ስራ ለማንበብ አንብበንም ከምንኖርበት ዘመን አዛምደን ለመመርመርና ለመማር በመብቃታችን ክብር ሞገስና ምሥጋና ለተከበረው አባታችን ለሌተናነት ጄኔራል አቢይ አበበ ይሁን እንላለን!! ስምህ ከመቃብር በላይ በፍቅርና በአክብሮት ከኢትዮጵያ ጋር በትውልድ ሁሉ ሲወሳ ይኖራልና!

 

እንግዲህ ማሳረጊያችንን የምንቀነብበው በጠቢቡ አባታችን በሌተናንት ጄኔራል አቢይ አበበ ቃል ይሆናል።

 

የእኛ ነገር ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንደሆነ ደህና አድርገን እናውቃለን። ስለዚህም ዞረን ዞረን የምንገባባትን ሀገራችንን ቤታችንን፤ ኖረን ኖረን የምንቀበርባትን መሬታችንን እንደዋዛ አንያት። ሁላችንም ነገ ጥለነው ለምንሄደው ነገር አንጓጓ። ሀገራችንን ካልን የሀገራችን ነገር ከሁሉ በፊት ይቅደም። ሀገራችንን ካልን ደግሞ ይዘን እናሻግራት፤ እንጠብቃት፤ ከልብም እንውደዳት፤ አንድነትም ሆነን እናገልግላት፤ ከእኛ በሁዋላ ለሚመጡትም ሀገራቸው ሆና እንድትቆይ እንድትወራረድም አድርገን እንያዛት።

     ሰው በሰው ክፉ መሆን አይገባውም። በተለይም የአንድ ሀገር ሰዎች የአንድ እናት ልጆች ማለት ነንና መተዛዘን መተሳሰብና መፈቃቀርን ማወቅ ግዴታችን አድርገን እንያዘው።

     ወንድም በወንድሙ ላይ በከንቱ አይነሳ። የከንቱ ነገርንም ምንጭ አይቆፍር። እያንዳንዱም ሊቅ አፉን ይክፈት፤ በጎ ምግባርናን የሀገር ፍቅርን ከመናገር ከመስበክ አይቦዝን።

     ሁላችንም እናልፋለን። ይህንን የማያምን ቢኖር የነበሩ እነማን አሉ? ማለፋችንን ካመንን ስለምን በቀና መንገድ አንሄድም? ስለምንስ ቅን ሰርተን አናልፍም?

 

          ——————————– //  ተ ፈ ፀ መ  // —————————–

ተፃፈ፤ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ 26ኛ ዓመት ግንቦት 2009 ዓ/ም (ሜይ 2017)

 

ሲድኒ አውስትራሊያ

 

ለአስተያየት፤- mmtessema@gmail.com

 

*በዚህ ቅኝት ውስጥ በቀረቡት የሌ/ጄ አቢይ አበበ መልዕክቶች ላይ የሚገኙት ሰረዞችና ደማቅ ፅሁፎች  የቃኚው ትኩረት ናቸው።

 

 

 

 

 

   

 

 

 

 

 

 

↧

አይቀሬው የለውጥ ማዕበል በኢትዮጵያ እና የህወሀት/ኢህአዴግ የቁልቁለት መንገድ!!! ( በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት)

$
0
0

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት

ኢትዮጵያ ሐገራችን አሁን ላለችበት ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍትፌው ምን መሆን አለበት በሚለው አስተሳሰብ ላይ በገዥው ቡድንና በለውጥ ኃይሉ ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ችግሮቹ በተጨባጭ መኖራቸውን በመረዳት በኩል ግን በገዥውም ሆነ በለውጥ ፈላጊዎች መካከል ብዙም ልዩነት ስለሌለ ስለሚደርሰው ግፍ፣ ግድያ፣ አፈናና ሌሎች ቀውሶችን መተንተን አሁን ላይ ብዙም አስፈላጊ ሆኖ ስላልታዬኝ በለውጥ አይቀሬነት፣ የለውጥ ስልቶችና ውጤቱ ላይ አተኩራለሁ፡፡

ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው፣ማንኛውም ነገር ይለወጣል፡፡ የሰው ልጅም ይወለዳል ያድጋል ይሞታል፡፡ስልጣኔም ይፈጠራል፣ያብባል ከዚያም ያረጅና በሌላ ስልጣኔ ይተካል፡፡ አገዛዝም የተለያዩ ማደናገሪያዎችንና አስተሳሰቦችን ይዞ በስልጣን ላይ ይቆያል፡፡ ያለውን አመለካከትና አገዛዝ የማይሸከም ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ ሲፈጠር በስብሶ ይወድቃል፣ በሌላ ሰርዓት ይተካል፡፡
ስለዚህም ህወሀት/ኢህአዴግ ወደደም ጠላም እኛ ተንቀረፈፍንም ፈጠንም በራሱ በተፈጥሮ ህግም ቢሆን ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ የእኛ ሚና ሊሆን የሚችለው ለውጡን በራሱ በተፈጥሮ ከሚሆነው ይልቅ እግዚዓብሄር በሰጠን አዕምሮ ተጠቅመን በታቀደና በተጠና መልኩ በአነስተኛ ወጭና ጊዜ ወደ ተሻለና አስቀድሞ ውጤቱ ወደታወቀ መንገድ መምራት ነው፡፡ ይህንን ካለደረግን ተፈጥሮ በራሱ ለውጥ የሚያደርግብን እንጅ በራሳችን ነገሮችን የምንለውጥ ወይም የመጡ ለውጦችን የምንቆጣጠር ሰብዓዊ ፍጡሮች መሆናችን ይቀርና ደመነፍሳዊ እንስሳ ወደ መሆን እንጠጋለን፡፡ ይህንን ካልኩ በኋል አሁን በሃገራች ያለውን የለውጥ ማዕበል በተመለከተ በሶስት ክፍሎች በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

1. የለውጡ ሁኔታና የህወሀት/ኢህአዴግ የሁኔታዎች ትንተና
2. ለውጡ ሊመጣ/ሊፋጠን/ የሚችልባቸው አመራጮች
3. የሚመጣውን ለውጥ እንዴት ወደ ተሻለ ሁኔታ መምራት እንቻላለን በሚሉ መሰረታዊ ሃሳቦች እይታዬን አቀርባለሁ፡፡

1. የለውጡ ሁኔታና የህወሀት/ኢህአዴግ የሁኔታዎች ትንተና
ህወሀት/ኢህአዴግ አሁን ያለውን የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ሲገመግም “የጠባብና የትምክህት አመለካከቶች ለስርዓቱ አደጋ መሆናቸውንና ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር ተጨምሮበት የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ባለማጠናቀቃችን የህዝብ ቅሬታ ተፈጥሯል፡፡በዚህ ቅሬታ ምክንያት ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሮ ሌሎች ሃይሎች ለፖለቲካ መጠቀሚያ አድርገውታል” የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፈራ ተባ እያለም ቢሆን የልማትና የዲሞክራሲ ጥያቄ የብሄራዊ ደህንነት አጀንዳ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ህወሀት/ኢህአዴግ የተፈጠረውን ችግር ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ከተነተነ በኋላ ችግሮቹን ለማስወገድ እንደ መፍትሔ ያቀረበው ሐሳብ “በመጀመሪያ የተፈጠረውን ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ማዋል፤ ለዚህም የእስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ፤ ቀጥሎም በጥልቅ የድርጅት ግምገማ የትምክህትና የጠባብ ሃይሎችን መምታት፣የድርጅትን የማስፈፀም አቅም በማሳደግ ለህዝብ ቅሬታዎች ምላሽ መስጠት ከዚህም በተጨማሪ የፓርላማ ወንበሮችን ሙሉ በሙሉ በማሸነፋችን ተቃዋሚ ሃይሎች ባለመደመጣቸው ስለሆነ የምርጫ አዋጁን ከተቃዋሚዎች ጋር በማሻሻል በቀጣዩ ዙር ምርጫ ተቃዋሚዎች መጠነኛ ወንበር እንዲያገኙ በማድረግ የህወሀት/ኢህአዴግን የተራዘመ የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ” የሚል ነው፡፡
ህወሀት/ኢህአዴግ የወቅቱ የሀገሪቱ ችግሮች እነዚህ ናቸው ይበል እንጅ የነገሮችን እድገትና የችግሮችን ዋና ምንጭ በውል ለመገንዘብ አልቻለም/አልፈለገም፡፡ ህወሀት/ኢህአዴግ እንደ ችግር የተቀበላቸውን ሀሳቦች እንደመነሻ ብንወስድ ትምክህትና ጥበት እንዴት ሊፈጠር ይችላል? ወቅታዊ ችግር ነው ወይስ በየደረጃው እያደገ የመጣ ችግር? ትምክህትና ጠባብነት እንደ ችግር እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላ የችግሩን ምንጭ ሳይገነዘቡ እና የመፍትሄ ሃሳብ ሳያስቀምጡ በድርጅታዊ ግምገማ እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል በግልፅ አላስቀመጠም ወይም ለማስቀመጥ አልፈገም፡፡ በተጨማሪም ዴሞክራሲና ልማት ጥያቄ አለመመለስ የብሔራዊ ደህንነት አደጋዎች ናቸው ብሎ ቢናገርም የዴሞክራሲና የልማት ጥያቄ በኢትዮጵያ እንዴት የህዝቡን ፍላጎት በሚመጥን ሁኔታ እውን ማድረግ እንደሚቻል ሳያሳይ የዴሞክራሲ መሰረታዊ ተቋማት እንዴት እንደሚገነቡ እና የዴሞክራሲና የልማት ጥልቅ ትስስርን ሳይገነዘብ ችግሩን ለማለፍ ብቻ በማድበስበስ እነደ ጊዜ መግዣ መንገድ እየተተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ስለሆነም በሕወሀት/ኢሕአዴግ የተሳሳተ የነባራዊ ሁኔታዎች ግምገማ ላይ ተመርኩዞ የሚሰጥ የመፍትሄ ሀሳብ ውጤታማ ስለማይሆን የለውጡን አይቀሬነት ያመላክታል፡፡
በእኔ እምነት ህወሀት/ኢህአዴግ እንደሚለው ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ችግር መሰረቱ ጠባብነትና ትምክት ያመጣው ነው የሚለውን ብንቀበል እልኳን ጠባብነትና ትምክህት ላለፉት 26 ዓመታት ሕወሀት/ኢህአዴግ ውሃ እያጠጣና እየኮተኮተ በየደረጃው እያሳደጋቸው የመጡ ችግሮች እንጅ በድንገት የተፈጠሩ ስላልሆኑ የተፈጥሮ እድገታቸውን ጨርሰው የሚያደርሱትን ጥፋት አድርሰው ይከስማሉ እንጅ በድርጅት ግምገማ ሊጠፉ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ህወሀት በባህሪውና የተመሰረተበትን የቆመበትን የማነነት ፖለቲካ እስካልቀየረ ድረስ የራሱ የችግር መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህትን መዋጋት አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ለማታለልም ቢሆን በማንነት ላይ ተመርኩዞ ራስን ለማስተዳደር በህገ መንግስት የተፈቀደው መብት በክልሎች ዘንድ እያደገ ስለሚሄድና ከህወሃት ተፈጥሯዊ የጠቅላይነት ባህሪ ጋር በፅኑ ስለሚቃረን የውስጥ ሽኩቻውን ከጊዜ ጋር እያጠናከረው ይሄዳል፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ህወሃት አሁን በያዘወ የችግር አፈታት ዘዴ ከጊዜ ጋር በተቃራኒው መንገድ ስለሚሄድ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የማንነት ጥያቄዎችና ሽኩቻዎች እያደጉ ድርጅቱ እራሱን በራሱ እየበላ ወደማይቀረው ሞት አፋፍ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም ለውጥ አይቀሬ ይሆናል፡፡
ዴሞክራሲ በመሰረቱ ለአብላጫ ድምፅ በመገዛት የአናሳውን መብት ማክበር ሲሆን በዚህ መሰረት ከህዝብ መካከል በህዝብ የተመረጠ እና ለህዝብ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ከዚህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ አንፃር ህወሃት/ኢህአዴግን ስናየው ድርጅቱ እጅግ የጠበቀ ማዕከላዊነት ያለውና ጥቂቶቹ ብዙኃኑን እንደፈለጉ የሚገዙበት ስልጣንና ተዕዛዝ ከላይ ወደ ታች የሚወርድብት ከዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ በተፃራሪ የተፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ህወሃትና ዴሞክራሲ አይተዋወቁ ወይም በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡ የህወሃትና የዴሞክራሲን ዝምድና በጨለማና በብርሃን መመሰል ይቻላል፡፡ ብርሃን ካለ ጨለማ የለም፤ ጨለማ ካለ ብርሃን የለም፡፡ ጨለማና ብርሃን አንዱ ሌላውን ካላጠፋ በስተቀር በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡ ህወሃትና ዴሞክራሲም እንዲሁ ናቸው፡፡ ህወሃት ካለ ዴሞክራሲ የለም፤ ዴሞክራሲ ካለ ህወሃት የለም፡፡ በተፈጥሮ ባህሪያቸው አንዱ ሌላውን ካላጠፋ በስተቀር በአንድ ላይ ሊገኙ አይችሉም፡፡
በአጠቃላይ ህወሃት/ኢህአዴግ አሁን በያዘው የችግር መፍቻ መንገድና ከላይ በተነሱት ትንተናዎች መሰረት ትምክህትንና ጠባብነትን ታግሎ አመጣዋለሁ የሚለው ዴሚክራሲ እንደ ጊዜ መግዣና ማታለያ አድርጎ ስልጣኑን ለማስቀጠል የያዘው የመፍትሔ መንገድ በመሰረቱ የተሳሳተ የችግር ግምገማና መፍትሄ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ የለውጡን ሂደት በእጅጉ ያፋጥነዋል፡፡ ለውጡንም አይቀሬ ያደርገዋል፡፡

2. ለውጡ ሊመጣ/ሊፋጠን/ የሚችልባቸው አማራጮች
ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑን ከላይ ያነሳኋቸው መሰረታዊ ምክንያቶች የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ገዥውም ቡድን ቢሆን ለውጥ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው በማለት ጥገናዊም ቢሆን ለውጥ ሳያደርግ ሊቀጥል እንደማይቻል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ለውጡ በምን ይመጣል በሚለው ላይ ግን የተለያዩ ወገኖች የተለያዩ እይታዎች እንዷላቸው በማሰብ የለውጡን ማዕበል ሊያፋጥኑ ለለውጥም ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ አማራጭ የትግል ስልቶች መካከል፡-
ምርጫ
የትጥቅ ትግል
በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ
በህወሃት/ኢህአዴግ የሚወሰድ የማሻሸያ እርምጃ
መፈንቅለ መንግስት
ህዝባዊ እምቢተኝነት
የእርስ በእርስ ጦርነት እና የሐገር መፍረስ አደጋ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ አማራጭ መንገዶች ለውጡን ለማምጣት ያላቸውን እድል ለመለየት እያንዳንዱን መንገድ ያለውን መልካም ዕድል ወይም ችግር በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡

1ኛ. በምርጫ ለውጥ ማምጣት፡- ምርጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥን ሊያመጣ ይችላል ወይም አይችልም ከማለቴ በፊት ምርጫ በባሕሪው ከምንም አስቀድሞ ነፃነትን የሚሻና መራጩ የሚፈልገውን ለመምረጥ አማራጮች በእኩልነት የሚቀርቡበት መንገድ ነው፡፡ ለኢህአዴግ ምርጫ ማለት ዛሬ የሰው ልጅ ከደረሰበት የአስተሳሰብ ልዕልና አንፃር ቢያንስ ቢያንስ ያለማስመሰያ ምረጫ በገዥነት መቀመጥ ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብና የኢህአዴግ ቁንጮ የሆነው ሕወሃት የአናሳ ቡድን ተወካይ በመሆኑ ብዙሃኑን ሁልጊዜ በኃይል አፍኖ ለመግዛት የማይችል መሆኑን ስለተረዳ የሚጠቀምበት የማታለያ ስልት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድርገው ወደስልጣን ያመጡትን ምዕራባውያን አሁን በደረሱበት የስነ መንግስት አወቃቀር ስልጣንን በምርጫ መለወጥ መርህአቸው እያደረጉት በመምጣታቸው ድጋፍ የሚደርጉላቸው አናሳ ቡድኖች ምርጫ እንዲያደርጉ ስለሚያስገድዱ የእነሱን ፍላጎት ለሟሟላት ብቻ ለይስሙላ የሚጠቀምበት ስልት እንጅ ዜጎች በነፃ ምርጫ የሚፈልጉት የሚያወጡበትና ያልፈለጉትን የሚያወርዱበት መንገድ እንዲሆን ስለሚፈልግ አይደለም፡፡ በነፃ ምርጫ የሚወለድ ዲሞክራሲ መሰረታዊ ባህሪው በብዙሃን ድምፅ መገዛትን እና የአናሳዎችን መብት ማክበር ነው፡፡ ሁለቱም መሰረታዊ ሃሳቦች ማለትም ነፃነትና ዲሞክራሲ ስለሌሉና የሕወሃት አፈጣጠር ከነዚህ በተቃርኖ የቆመ ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ነፃነት ለዲሞክራሲዊ አስተዳደር ቅድመ ሁኔታ ነው፤ነፃነትና ዲሞክራሲ በሌሉባት ኢትዮጵያ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም፡፡

2ኛ. በትጥቅ ትግል ለውጥ ማምጣት፡-
ዓለም በካፒታሊዝምና ኮሚዩኒዝም ርዕዮተ ዓለም ጎራ ተከፍላ ስትናጥበት የነበረው ዘመን የኮሚንይዝሙ ጎራ ተዳክሞ ከተፈረካከሰ በኋላ ዓለም በብቸኝነት በምዕራቡ የካፒታሊዝም ተፅዕኖ ስር ወድቃለች፡፡ የሁለቱ ጎራዎች ፉክክር በተመጣጣኝ ደረጃ በነበረት ወቅት በአንድ ጎራ የተቀመጠን ስርዓት ማውረድ የፈለጉ አካላት ከተቃራኒው ጎራ በሚያገኙት ድጋፍ መንግስታትን በትጥቅ ትግል ሲለዋውጡ አይተናል፡፡ ነገር ግን የኮሚንይዝሙ ጎራ ተዳክሞ ከተፈረካከሰ በኋላና ዓለም በምዕራቡ ዓለም የአስተሳሰብ ዕዝ ስር ከወደቀ በኋላ በስልጣን ላይ የተቀመጡ አምባገነኖችን በትጥቅ ለማውረድ የሚሞክሩ ለውጥ ፈላጊዎች በበቂ ሁኔታ ድጋፍ የሚሰጣቸው ኃይል ባለመኖሩ በዚህ ስልት አምባገነኖችን ለመቀየር እየከበደ እንደመጣ የኮምኒይዝሙ ዓለም ከፈረሰበት ካለፉት 28 ዓመታት ወዲህ በጠመንጃ የተቀየረ አምባገነን ስርዓት ዓለሞኖሩ ግልፅ ማሳያ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኮንጎንና የሊቢያ አምባገነኖች ከኮምኒዝም ጎራ መፈረካከስ በኋላ በጠመንጃ ኃይል የተገረሰሱ አምባገነኖች በመሆናቸው እንደመከራከሪያ ሊቀርቡ ይችሉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በሁለቱ ሐገራት ላይ በትጥቅ ትግል ለውጥ የመጣበትን መንገድ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኮንጎ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት መዝረፍ የፈለጉ ኃይሎች ያለ ኃፍረት የካቢላን ኃይሎች በቀጥታ በማስታቅና በመርዳት ስድስት ወር ባልሞለ ጊዜ ውስጥ ወትሮም ደካማና በሙስና የላሸቀውን የዛየር መንግስት ማውረዳቸው ከጀርባው የሚፈልጉትን ቡድን ወደስልጣን በማውጣት እሱን ተጠግተው የተፈጥሮ ሐብቷን ለመዝረፍ የፈለጉ ሰፍሳፋ የውጭ ኃይሎች የነበራቸውን ሚና በተለዬ ሁኔታ ማየት ይኖርብናል፡፡ የሊቢያውን አምባገነን ኮሌኔል ሞአመር ጋዳፊን ለማውረድ ምዕራባውያን በቀጥታ በዓየርና በምድር ጥቃት በማድረስ የሊቢያ ለውጥ ፈላጊዎች ጋዳፊን ለማውረድ ካደረጉት እንቅስቃሴ ጀርባ ምዕራባውያን የነበራቸው ጣልቃ ገብነት እጅግ ያፈጠጠ ስለነበረ በትጥቅ ትግል ለውጥ መጥቶበታል ለሚባል መከራከሪያ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ በዚህም መሰረት በኮንጎና በሊቢያ በትጥቅ የተደረጉ ለውጦች ምን ያህል በውጭ ኃይሎች ፍላጎት የተመሩ እንደነበሩ በማሰብ ባሁኑ ዘመን በትጥቅ ትግል ከሚደረጉ ትግሎች ጋር በተለዬ ሁኔታ መታየት አለባቸው እላለሁ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በቅርብ ጊዜ የትጥቅ ትግል የጀመሩት ይቅርና ዓለም በሁለት ጎራ በተከፈለችበት ወቅት ጀምረው የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነቡሩት ለአብነት ያህል የኮሎምቢያው ፋርክ፤ የኩርዶቹ ፒኬኬ፣ የስፔኑ ኤታ፤ የዩጋንዳው ሎርድ ሬስታንስ እና ሌሎችም የትጥቅ ትግል አራማጆች እየተዳከሙ እንደመጡና አሁን ለውጥን በድርድና በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ጥረት ላይ እንዳሉ ስናይ አሁን ባለንበት ዘመን በትጥቅ ትግል ለውጥ ለማምጣት እየከበደ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም በትጥቅ ትግል ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ኃይሎች ዓለም ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰለባ በመሆናቸው እስካሁን ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት አልቻሉም፡፡ ወደፊም ቢሆን ለምዕራባውያንም ሆነ ለኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ጥቅም መከበር ተቃዋሚዎች ከገዥው ቡድን የበለጠ ምቹ ሆነው ስለማይገኙ ድጋፍና እርዳታ አግኝተው ገዥውን ቡድን በትጥቅ ትግል የማውረዳቸው እድል እጅግ የመነመነ ይመስለኛል፡፡

3ኛ. በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ለውጥ ማምጣት
በሐገሮች መካከል የሚደረጉ ዲፕሎማሲዊም ይሁን ሌላ ዓይነት ግንኙነት መሰረታዊ መነሻው ሁሉም የየራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በመሆኑ እያንዳንዷ የሚያደርጓት እንቅስቃሴ ከጥቅማቸው መከበር ወይም ማጣት ጋር ያለውን ተፅዕኖ በማስላት ነው፡፡ እንደ መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ዛሬ በመላው ዓለም በስልጣን ላይ የተቀመጡ አምባገነኖች ዜጎቻቸውን ቀጥቅጠው እየገዙ ቢሆንም በመሸጦነታቸው የውጭ ኃይሎችን ጥቅም በማስከበር ለለውጥ ከሚታገሉ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች በላይ እጅግ የተመቹ በመሆኑ አገልጋይነታቸውን በማሳየት ከውጭ ኃይሎች የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ እያሳነሱ መጥተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የውጭ ኃይሎች የራሳቸውን ብሔራዊ ጥቅም እስካስከበሩ ድረስ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀመው በደልና ግፍ ብዙም ግድ ስለማይሰጣቸው በበደል ሰለባዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት ያሳስበናል እያሉ ሲቀልዱ ከመኖር አልፈው የእነሱን ጥቅም ያልነካን አምባገነል እንዲያውም በተቃራኒ በስውርና በግልፅ ድጋፍ ከማድረግ አልፈው ተፅዕኖ በመፍጠር ለለውጥ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ወትሮም ለዲሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት መከበር ደንታ የሌላቸው ራሳቸውም በአምባገነኖች ስር ያሉና የወደቀው የኮሚንስት ርዕዮተ ዓለም ትራፊ የሆኑ የምስራቁ ዓለም ሐገሮች ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚታገሉ ኃይሎችን ትግል ደግፈው ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብሎም አይታሰብም፡፡ እንግዲህ የዲሞክራሲና የነፃነት ኃይሎች መሸጦነታቸው በስልጣን ላይ ካሉት አምባገነኖች በላይ ሆኖ የውጭ ኃይሎች ብሔራዊ ጥቅማቸውን የበለጠ የሚያስጠብቁበትን መንገድ ካላሳዩ በስተቀር የውጭ ኃይሎች በአምባገነኖች ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት ያላቸው ሚና በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ የማይታሰብ ነው፡፡

4ኛ. በህወሃት/ኢህአዴግ በሚወሰዱ የየማሻሸያ እርምጃዎች ለውጥ ማምጣት
ከዲምክራሲያዊ ስርዓት በተቃርኖ የተቀመጠው የሕወሀት/ኢህአዴግ ገዥ ቡድን ህዝባዊ አመፅ ባናወጠው ሰሞን አክራሪ ጠባብ ኃይሎችና የትምክህት ኃይሎች ለስልጣኑ አደጋ እንደሆኑበት በመግለፅ እነዚህን ጠባብና የትምክህት ኃይሎች በጥልቅ ተሃድሶ አጥፍቶ ለውጥ አመጣለሁ በማለት ሲንደፋደፍ ታይቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የመልካም አስተዳደር እጦትና አንዳንድ መሰረታዊ የሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎችን ከተቃዋሚዎች ጋር በመነጋገር አንዳንድ ህጎችንና የህገ መንግስት ማሻሻያ በማድረግ ኢህአዴግ ራሱን ለውጦና አሻሽሎ በገዥነቱ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት ለማሳከት የሄደበትን የምኞት መንገድ ታዝበናል፡፡ ከላይ በመግቢያው እንደተጠቀሰው ኢህአዲግን በህዝባዊ አመፅ ጭንቅ ውስጥ አስገብቶት ዛሬ ሐገራችንን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ ያደረጋት ጠባብነትና ትምክህት ነው የሚለው የሕወሀት/ኢህአዴግ የግምገማ ግንዛቤ እወነት ነው እንኳ ብንል ጠባብነትና ትምክህትን ገዥው ቡድን ላለፉት 26 ዓመታት ውሃ እያጠጣና እየኮተኮተ በየደረጃው እያሳደጋቸው የመጡ ችግሮች እንጅ በድንገት የተፈጠሩ ስላልሆኑ የተፈጥሮ እድገታቸውን ጨርሰው የሚያደርሱትን ጥፋት አድርሰው ይከስማሉ እንጅ በሕወሀት/ኢህአዴግ የድርጅት ግምገማ ሊጠፉ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ህወሀት በባህሪውና የተመሰረተበትን የማነነት ፖለቲካ እስካልቀየረ ድረስ የራሱ የችግር መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህትን መዋጋት አይችልም፡፡ በሌላ አነጋገር ለማታለልም ቢሆን በማንነት ላይ ተመርኩዞ ራስን ለማስተዳደር በህገ መንግስት የተፈቀደው መብት በክልሎች ዘንድ እያደገ ስለሚሄድና ከህወሃት ተፈጥሯዊ የጠቅላይነት ባህሪ ጋር በፅኑ ስለሚቃረን የውስጥ ሽኩቻውን ከጊዜ ጋር እያጠናከረው ይሄዳል፡፡ ጠቅለል ባለ አነጋገር ህወሃት አሁን በያዘወ የችግር አፈታት ዘዴ ከጊዜ ጋር በተቃራኒው መንገድ ስለሚሄድ ጊዜ በጨመረ ቁጥር የማንነት ጥያቄዎችና ሽኩቻዎች እያደጉ ድርጅቱ እራሱን በራሱ እየበላ ወደማይቀረው ሞት አፋፍ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም በህወሃት/ኢህአዴግ በሚወሰዱ የየማሻሸያ እርምጃዎች ለውጥ ማምጣት አይቻላቸውም፡፡

5ኛ. በመፈንቅለ መንግስት ለውጥ ማምጣት
በመሰረቱ መፈንቅለ መንግስት ሊደረግ የሚችለው የፖለቲካውና የወታደራዊ ኃይል አንደኛው ከሌላው ገለልተኛ ሆኖ የተዋቀረ ሲሆንና አምባገነኖች ባሉበት ሐገር ወታደራዊ ኃይሉ የህዝብ ወገንተኝነት ያለው ከሆነ ወይም ወታደራዊ ኃይሉ ከሲቪል አስተዳደሩ የተለየ አመለካከት ሲኖረው ነው፡፡ በግልፅ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተቋማትና የደህንነት ኃይሎች እና ገዥው የሕወሀት/ኢህአዴግ በዘርም ሆነ በአመለካከት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች በመሆናቸው እንደ ሁለት የተለያዩ አካላት ሊታዩ አይችሉም፡፡ አመራሩ መቶ በመቶ በአንድ ሰፈር ልጆች የተያዘው የኢትዮጵያ የወታደራዊ ኃይል የሰፈሩ ልጆችና የጥቅም ተጋሪው የሆኑ የሲቪል አስተዳደሩን መሪዎች አውርዶ በጠላትነትና እንደ ባዕድ በሚቆጥራቸው የዲሞክራሲ ኃይሎች እንዲተካ የራሱን ሚና ይጫወታል ብሎ መጠበቅ ሲበዛ የዋህነት ይሆናል፡፡ ስለዚህም በሕወሀት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ለውጥ በመፈንቅለ መንግስት ይመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡

6ኛ. በህዝባዊ እምቢተኝነት ለውጥ ማምጣት
የሕወሀት/ኢህአዴግ የማስመሰያ የሲቪል አስተዳደር ኢትዮጵያን የማስተዳደር አቅሙ ተዳክሞ ዛሬ ሐገራችንን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡ ለውጥ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ ባለፉት 26 ዓመታት ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት ብዙ ዋጋ የከፈሉና እየከፈሉ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖትና የሞራል ሰዎች፣ የኪነጥበብና የስነ ጥበብ ባለሙያዎች ያደረጉአቸው አስተዋፅዖዎች ስርዓቱ ዛሬ ለወደቀበት የጭንቅ መንገድ የራሰቸውን ሚና አበርክተዋል፡፡ በሕወሀት/ኢህአዴግ አስተሳሰብም ዛሬ ላጋጠመኝ ፈተና መነሻው ጠባብነትና ትምክህት ነው የሚለው አስተሳሰብም ለማታለያነት ታስቦ በሰነድና በሕግ የተቀመጠ የመብትና የአስተሳሰብ መሰረትም እያደገ መጥቶ ጥቂቶች ብዙሃኑን እየገዙ የሚኖሩበት ስርዓት በህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ለውጥ እየተገፋ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዛሬ ሕወሀት/ኢህአዴግ ደረሸበታለሁ በሚለው ግምገማም ሆነ አማካሪዎቹ በአደባባይ የሚሰጡት ምክር ለውጥ ማድረግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አከራካሪነቱ አክትሟል፡፡ ነገር ግን የሕወሀት/ኢህአዲግ የችግር ግምገማና የመፍትሔ መንገድ ችግሮችን የመፍታት አቅም ስለሌላቸው የትንሽ ጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሕዝባዊ ተቃውሞውን አያቆመውም፡፡ ሕወሀት/ኢህአዴግ በጥገናዊ ለውጥ ሊያቆመው የፈለገው ስርዓትም መፈራረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ የታገሉ ዜጎች በፈጠሩት የፖለቱካ ጫና ያስከተለው ህዝባዊ እምቢተኝነትም ሆነ በሕወሀት/ኢህአዴግ የግምገማ ድምዳሜ ጠባብና የትምክህት ኃሎች የፈፀሙት ሕዝባዊ አመፅ ስርዓቱን ወደ ከፍተኛ ጭንቅ በመክተት ባለፉት 25 አመታት ካጋጠሙት ፈተናዎች በላይ ወደ መፍረስ ጫፍ ስላመጣው የሲቪል አስተዳደሩን አፍርሶ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም ሐገራችንን በወታደራዊ አገዛዝ ስር እንድትወድቅ በማድረግ የሲቪል አስተዳደሩን ለመመለስ ፍርሃትና ጥርጣሬ ውስጥ ከቶት ይገኛል፡፡ ከላይ ከተነተንናቸው የትግልና የለውጥ አማራጮች መካከል ሕዝባዊ እምቢተኝነት በስርዓቱ ላይ ተጨበጭ ጫና በመፍጠር ከሌሎች ስልቶች የተሻለ ለውጥ የማምጣትም አቅም ያለው ስልት መሆኑን አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና አሁን ባለው የዓለም የኃይል ሚዛን አሰላለፍ አንፃር ሲታይ በገዥው ቡድን ላይ የመጨረሻውን ለውጥ ለማምጣት የተሻለ እድል ያለው የትግል አማራጭ ስልት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡

7ኛ. የእርስ በእርስ ፍጅት እና የሐገር መፍረስ አደጋ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደምንገነዘበው ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር መልካም አጋጣሚ የነበሩ በርካታ የለውጥ ሙከራዎች በእርስ በእርስ ሽኩቻና በአመራር ድክመት ምክንያት በትክክል ሳንጠቀምባቸው በማለፋችን አሁን ሐገራችን ላለችበት ምስቅቅል አድረሰናታል፡፡ አሁንም ሊመጣ ያለውን ለውጥ በተጠናና በምክንያታዊ አስተሳሰብ ካልገራነው በስተቀር አሁን እያቆጠቆጡ የመጡት የአመለካከት ጫፎች በኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ፍጅትና የሐገር መፍረስ አደጋ ያንዣበበ መሆኑ ብዞዎቻችን ባንወደውም አፍጥጦ እየመጣ ያለ ሐቅ ነው፡፡ ሐገር መፍረስ በዜጎች ላይ የሚያመጣውን ስቃይ፣ በአጎራባች አካባቢዎች የሚፈጥረውን ትርመስ ግምት ውስጥ በማስገባት በሌሎች ሐገሮች የደረሰው መከራ በእኛም ላይ ከመድረሱ በፊት ሁላችንም ለመፍትሔው የበኩላችንን መልካም አስተዋፅዖ ማድረግ ይኖርብናል እላለሁ፡፡

3. የሚመጣውን ለውጥ እንዴት ወደ ተሻለ ሁኔታ መምራት እንቻላለን
በሁለቱ ዋና ርዕሶች ለማሳየት እንደሞከርኩት ሕወሀት/ኢህአዴግ ችግሮችን የሚገመግመው በተሳሰተ መንገድ መሆኑና የሚያቀርባቸው የምፍትሔ ሐሳቦችም ችግሮች አሁን ያሉበትን ደረጃ የማይመጥኑ በእውነትም መፍትሔ የማያመጡ በሙሆኑ በእኔ አስተያዬት በኢትዮጵያ የለውጥ ማዕበል አይቀሬ ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያና አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሕዝባዊ እምቢተኝነት በተግባር ውጤት ያመጣና የወደፊቱንም የሐገራችንን የለውጥ ሂደት በመወሰን ከሌሎች አማራጮች የተሻለ እድል እንዳለው ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ነገር ግን ይህን በህዝባዊ እምቢተኝነት የሚመጣ ለውጥ በአግባቡ ካልያዝነው የእርስ በእርስ ፍጅትና የሐገር መፍረስ አደጋም ሊያመጣ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን አደጋ በመገንዘብና ካለፈ ታሪካችን ትምህርት በመውሰድ ለዉጡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአወንታዊነት የሚቀበሉትና ለውጤታመነቱም የሚሰሩለት የጋራ አጀንዳ መፍጠር ይኖርብናል፡፡
እዚህ ላይ የታሪካችን አካል የሆነውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የመሬት ላራሹ አጀንዳን መጥቀስ አሁን ላለንበት ሁኔታ ትምህርት ሰጭ ይመስለኛል፡፡ የመሬት ላራሹ ጥያቄ በአፈፃፀሙና በውጤታማነቱ ላይ አከራካሪነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በወቅቱ ግን በኢትዮጵያ የለውጥ ኃይሎችን ለማሰባሰብና ለማስተባበር በብዙዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትልቅ የጋራ አጀንዳ ነበር፡፡ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በአሁኑ ጊዜ በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ያለውን ያለመተማመን የሚቀንስ የኢትዮጵያን የሽግግር ወቅት የሚመጥን ሁሉን አቀፍ የሆነና በጊዜ የተገደበ “የባለ አደራ መንግስት መቋቋም አለበት” የሚል አጀንዳ ከፍ ብሎ መውጣትና መሰባሰቢያ የለውጥ ግብ ሆኖ መቀረፅ አለበት፡፡ የባለ አደራ መንግስቱ ይዘት፣ ስልጣንና ኃላፊነት ውክልናና አሳታፊነት በሂደት በዝርዝር በድርድርና በውይይት ቅርፅ ሊይዝ የሚችል ጉዳይ ይሆናል የሚል እምነትም አለኝ፡፡

ከትውልድ ተጠያቂነት ለማምለጥ የተሻለውን ነገር ለመስራት ከአሁን የተሸለ ጊዜ የለንም!!!!
አመሰግናለሁ!!!

↧

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው ዬናታን ተስፋዬ የስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት ተፈረደበት

$
0
0

ዬናታን ተስፋዬ

ነገረ ኢትዮጵያ

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው ዬናታን ተስፋዬ የስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት ተፈረደበት
(በሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ)
ዛሬ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም በከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ እንደተነበበው ዬናታን ተስፋዬ የተፈረደበት ሽብርን በማነሳሳትና በመቀስቀስ ወንጀል እንደሆነ ታውቋል:

↧

“መጀመሪያዉኑ ወንጀለኛ ሊባል የማይገባውን ሰው መቅጣት ‘አሳፋሪ” ነው”- አምነስቲ

$
0
0

ቀድሞውኑ እንደወንጀለኛ ሊቆጠር በማይገባው ተከሳሽ ላይ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር እስር መፍረድ ተገቢ ያልሆነና አሳፋሪ ጭምር መሆኑን ሰማያዊው ፓርቲና ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጹ። እንዲህ ያሉ አፈናዎች በበዙ ቁጥር የሚፈራውን ዐመጽ እንዳይቀሰቅሱ የኢትዮጵያ መንግሥት አፈናውን አሁኑኑ ማቆምና ከዚህ ቀደም የፈፀመውን የመብት ጥሰት ማረም ይገባዋል ብለዋል።

ውሳኔው ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ፌስቡክ ከመለጠፍ እና ሰላምታ ከመለዋወጥ ያለፈ ነገር ለማድረግ ስጋት እንዲያድርባቸው እየተደረጉ ነው ይላል – አምነስቲ።

if(typeof(jQuery)==”function”){(function($){$.fn.fitVids=function(){}})(jQuery)};jwplayer(‘jwplayer-1’).setup({“image”:”http://www.satenaw.com/amharic/wp-content/uploads/2017/05/yonatan.jpg”,”file”:”http://www.satenaw.com/amharic/wp-content/uploads/2017/05/dcbc5966-71f8-4e30-b417-fbb8def25a29_32k.mp3″});

↧
↧

ነገድ ሰፈራና ሰብአዊ መብት – ጌታቸው ኃይሌ

$
0
0
ፕ/ ር ጌታቸው ኃይሌ

ፕ/ ር ጌታቸው ኃይሌ

ወያኔዎች ክልል የሚባል ፖለቲካ አምጥተው የታሪክ ሂደት አንድ ሀገር፥ አንድ ሕዝብ፥ አንድ ኢትዮጵያ ያደረገንን፥ ወደኋላ መልሰው፥ ብዙ ሀገሮች፥ ብዙ ሕዝቦች፥ አልቦ ኢትዮጵያ አደረጉን። መንሥኤያቸው ግልጽ ነው። በነሱ አስተሳሰብ፥ መንግሥቱ የትግሬዎች ነበር፤ አማሮች ወሰዱባቸው። እንደሚመስላቸው፥ የተጐዱት ኢትዮጵያ በአማሮች ትጋት ከትግራይ ውጪ የተስፋፋች ጊዜ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ ኢትዮጵያን ማን እንዳኮማተራት እንጂ ማን እንዳስፋፋት፥ መቸ እንደተስፋፋች የሚያስረዳ ሰነድ የለንም። ያሉት ማስረጃዎች የሚያመለክቱት፥ ከአጼ ዓምደ ጽዮን ጀምሮ የነገሡ ነገሥታት በዛጔዎች ዘመንና በዘመነ መሳፍንት የተዳከመችውን ኢትዮጵያ ሲያጠነክሩ፥ የጠፋውን ሲያገኙ፥ የተቈረጠውን ሲቀጥሉ ነው። ከአማራ ክፍለ ሀገር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንም እንዴት አማራ የሚለውን ስም እንደወረሱ የነገረን የለም። ያለን ጭላንጭል፥ የንጉሡ ወታደሮች አማሮች ስለነበሩ፥ ዘምተው እዚያው ለቀሩበት አገር ሕዝብ ስማቸውን አወረሱት የሚል ነው። አሁን ወያኔዎች የሚያደርጉት ጥረት መኖሩ ገና ያልተረጋገጠውን የትግራይን ክብር ከኢትዮጵያ ነጥቆ ማጎናጸፍና (ትንሣኤ ትግራይ) ኢትዮጵያን አልቦ (የሌለች) ማድረግ ነው። ከኢሐፓ ጋር የነበራቸው ቅራኔ ይህ ነበር። እነሱ ወይ ትግራይ ወይ ሞት ሲሉ፥ ኢሐፓዎች ወይ ኢትዮጵያ ወይ ሞት አሉ።

—-[ሙሉውን  በፒ.ዲ.ኤፍ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ]——

 

———–///—————

Download (PDF, 78KB)

 

 

↧

ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም፡-ጀነራል ተክለብረሀን ወልደአረጋይና የኦሮሚያ ቲቪ – ሰርጸ ደስታ

$
0
0

ሰሞኑን የወያኔው ቡድን መረጃ መረብ ኃላፊ የሆኑት ጀነራለ ተክለብርሀን ወልደአረጋይ ለኦሮምያ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ የጻፉት ደብዳቤ ግራ ገባኝም ገረመኝም፡፡ ሲጀምር 200ሺ ካሬ ሜትር መሬት 20 ሄክታር ማለት ነው ወይም በኢትዮጵያውኛ ግማሽ ጋሻ መሬት ለሰራተኞቼ የሚለው የሚገልጸው የወያኔ ትግሬ ወሮበሎች እንዴት መሬት እየተቀራመቱ እንደሆነ ከዛም በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እንዴት የራሳቸውን ቤትና ንብረት እየገነቡ እንደሆነ ነው፡፡ መቼም ተክለብርሀን የሚመራው የወያኔ ስለላ ቡድን በወያኔ ትግሬ እንደተሞላ አይካድም፡፡ ከሌላ አለ ከተባለም ክፍለሀገር ምናምን ነው፡፡ ሲቀጥል በምን ሂሳብ ነው ለዚህ ድርጅት ሠራተኞች ከሌላው በተለየ የመኖሪያ ቤት የሚሠራው፡፡ ከዛም ሲያልፍ ቤቶቹ ንብረትነታቸው የማን ነው የሚሆነው;  ከዛ በመለስ ግን ለአቶ ለማ የተጻፋው ደብዳቤ ሕገወጥነት ሰውዬውን እጅግ እንድታዘብ አድርጎኛል፡፡ እንደኔ አንደ ጀነራል ማን አለብኝነት ካልሆነ ይህ አካሄድ ይጠፋዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኦሮሚያ ቲቪ ላቀረበው ዘገባ አቶ ለማ ማስተካከያ እንዲሰጥ መጠየቃቸው የሚዲያውን ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከመናቅ አቶ ለማንም እኛ እኛ የምንልህን ሥራ ሠራተኞችህን ታስተካክል እንደሆን አስተካክል አይነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ እርማት እንዲሰጥ ከተፈለገም መጠየቅ ያለበት በቀጥታ ሚዲያው ነው፡፡ ቢሆን እንኳን ማለቴ ነው፡፡ ሚዲያው ግን ለሕዝብ ፍነትው አድርጎ ያሳየው ውንደብድናን ነው እንጂ አንደም ስህተት የለበትም፡፡ አቶ ለማ በዚህ የማያምኑ ሆነው ክልሉን አመራለሁ ካሉ የውሸት ነበር ማለት ነው ብዙ ሊሉን የሞከሩት፡፡ ይልቁንም እንዲህ መስመሩን ያልጠበቀ ደብዳቤ ስለደረሳቸው መልሰው ማስጠንቀቂያ ሊጽፉና በይትኛውም መልክ የሕዝብንና አገርን ጥቅም ለሚጋፉ ወሮበሎች በር እንደማይኖራቸው ሊያሳዩን ይገባል፡፡ ሰውዬው(ተክለብርሀን) ግን መረጃ ሚስጥር ኃላፊ ነኝ እያሉ እንዴት የጻፉትን ደብዳቤ እንኳን ሚስጥራዊ ማረግ አቃታቸው፡፡

ይህን ጉዳይ ወደሌላ እንቅስቃሴ እገፋለሁ ብለው ቢሞክሩ አደጋው ለወያኔ እንደሚሆን ሊያውቁት ይገባል፡፡ ላለፉት 2ዓመታት ህዝብን አገንፍሎ ያሰወጣው የመጀመሪያው ምክነያት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገበሬዎችን አፈናቀለ የሚል አልነበርም እንዴ; ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንደተባለው ይመስላል፡፡ ኦሮምያ ቲቪ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ይመስላል፡፡ እንገዲህ ለማም በዚህ ሊፈተኑ ይሄው ፈተናው ቀርቦላቸዋል፡፡ ነገሩ የሚመርና ሌላ አቅጣጫ ከያዘ እንደባለፈው ሊያቆሙት በሚቹሉበት አቅም አይኖራቸውም፡፡ ጥጋብና ገንዘብ ያወራቸው የወያኔ ባለስልጣናት የታጠቁት የጦር መሳሪያ ያድነናል ብለው ተማምነው ከሆነ አዝናለሁ፡፡ እያንዳንዱን ባለስልጣን እየለቀመ ከምድረገጽ ሊያጠፋ የሚችል ሕዝብ ዙሪያቸው በቁጣ አሰፍስፎ እንዳለ  የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ እንደነ ሳዳም ሁሴንና ጋዳፊ የአውሮፓንና አሜሪካን ድጋፍ አይፈልግም የኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡ ምሬቱን ጫፍ እያወጡት እንደሆነ ምንም ሊማሩ አልቻሉም፡፡ ሰራዊቱን በአንድ ሌሊት ሊበትን የሚቸችል አጋጣሚም ሊኖር እንደሚችል አይገባቸውም፡፡ አሁንም አይታረሙም፡፡ ተክለብረሀን 26 ዓመት የለመዱትን ጋጠወጥ አካሄድ ነው የተጠቀሙት፡፡ ሲሆን ደብዳቤ መጻፍ ላይ ባልፈጠኑ፡፡ በቃል ከሚመለከታቸው አካላት መነጋገር በበጃቸው፡፡ ሲቀጥል በቀጥታ ለሚዲያው ኃላፊዎች መጻፍን ባሰቡ አሰራሩ እንደዛ ስለሆነ፡፡ የሚዲያውን ኃላፊዎችና ሠራተኞችን ከመናቅም በላይ ለማን ሚዲያውን ሥርዓት አስይዝ አይነት ደብዳቤ መጻፍን ባላሰቡት፡፡

አሁንም መሬት ከገበሬዎች እየተነጠቀ ለወያኔ ትግሬዎች እየተሰጠ መሆኑ ብዙ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ እሰጋለሁ፡፡ ወያኔ ሠራዊቷን በሙሉ በትግሬ ባለስልጣን ሙልታ ዛሬ ከተማውን (አዲስ አበባን) ያጨናነቁት እነሱ ናቸው፡፡ ወና ነጋዴዎቹም እነሱ ናቸው፡፡ ቤት በሠራዊት ሥም በየቦታው ቢሠራም እነዚሁ ትግሬ ወያኔዎች ናቸው የያዙት፡፡ ይህን ሁሉ እያየ ነገሮችን ዝም ባለ አሁንም እየታቀቡ አደለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው በትዕቢት እንደልባቸው እያወሩ እድሜ ይኖረናል ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ ብዙዎች ለበርካታ አመታት የወያኔ ትግሬዎች (ከትግራይ ወጥቶ በየ ቦታው ያለው ባብዛኛው) ደጋፊም ባይሆኑ ተቃዋሚ አልነበረም፡፡ ዛሬ ሁሉም በትግሬ ላይ ጥርሱን እንዲነክስ የሚያደርግ ንግግር ነው የሚያወሩት፡፡ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያሉ ወያኔ ትግሬዎች ቀን ከለሌት በሌላው ላይ ስላላቸው ጥላቻና ትዕቢት ሲያሳዩ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ሂደት ግን ብዙ ነገር እያመለጣቸው፣ በአንጻሩ ለራሳቸው መቃብር እየቆፈሩ እንደሆነ ሊያስተውሉ አልቻሉም፡፡ በወያኔ ቡድን ባልስልጣናትም ያለው ይሄው ነው፡፡ ችግሩ ከምን እንደሚመጣ በትክክል ባልረዳውም ከአስተዳደግና ከበታችነት ሥሜት እንደሆነ ይነበባል፡፡ እስካሁን ሕዝብ ተሸውዶም፣ ቀን ከሌሊት የሚያወሩትንም ውሸት ሰልችቶ ደንዝዞ ብል ይሻለኛል፡፡ አሁን ግን ምሬቱ እየከፋ ነው፡፡ ብዙ ሕዝብ ያመነባቸው ትግሬ ሆነው ወያኔ ያልሆኑ የመሰሉ እንኳን ቆይተው ያው ወያኔነታቸው እየተገለጠ ለሌላው ሕዝብ ያላቸው ጥላቻ እየባረቀባቸው ነው፡፡ ዮናታን ተስፋዬ ትግሬ አለመሆኑ ብዙ አመነት ያለአንዳች ጥፋቱ እንደተፈረደበት፣ አብረሃ ደስታ ትግሬ በመሆኑ ለወያኔ ስለላ እንዲያመች ተቃዋሚ በሚል መታሰሩን ስናስብ እጅግ እንታዘባለን፣ እንቆጫለን፡፡ ከወያኔ አፈነገጡ የተባሉ ዛሬ ልዩ እድል አግኝተው ለወያኔ በውጭ አርበኝነት እያገለገሉ እንደሆነ ስናይ፡፡ ትግሬ ያልሆነ ግን አንዳች ስህተት ሳይኖርበት አሸባሪ እየተባለ ሲታሰርና ሲገደል፡፡ እነ መረራ ትግሬ አለመሆናቸው መስሎች 26 ዓመት ሰላማዊ ሂደት ይኑር ሕዝቡን በፍትሀዊነት እንምራው ባሉ ማጎሪያ የገቡት፡፡

ተክለብርሀን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም የኦሮሞ ሕዝብ ይጠየቅሀል ለመሆኑ ለአንተና ሠራተኞችህ መሬት የሚሰጠው ለምንድነው; አሁን እኩል እኩል ሆነናል በመረጃው፣ እሰልላለሁ ሲሉ መሠለልም አለና፡፡ ሥንት የኦሮሞ ልጂ እንዳሰፈጀህ እናውቃለን፡፡ አስካሁን የኦሮሞ ሕዝብ እናንተ በአሰለጠናችኋቸው ሆድ አደሮች ብዙ ውዥንብር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ አሁን በአብዛኛው እየነቃ ነው፡፡ አደለም ገና እጅህ ያልገባውን መሬት ከዚህ በፊት በግፍ የዘረፍከውን ሁሉ ማጣት እንደሚኖር ማሰብ ጥሩ ነበር፡፡ በወያኔ ስሌት ኦሮሞን አምክነንዋል ብላችሁ ስለምታስቡ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ዝም አሉ አንጂ አልመከኑም፡፡ ዛሬ እያፈረሳችኋት ያለችው አገር በኦሮሞ አባቶች መሪ ተዋናይነት እንደተገነባች ታውቃላቸሁ፡፡ የሚኒሊክን ታሪክ ጥላሸት ለመቀባት መሪ መርሀችሁም የነበረው የሚኒሊክን ትክክለኛ ታሪክ ያወቀ ኦሮሞ እድሜያችንን ያሳጥረዋል በሚል ስጋት እንደሆነ እናውቃለን፡፡  26 ዓመት በልዩ ልዩ አዚም ብትሞክሩም፣ ያን የኦሮሞ ጀግኖች ታሪክ የሰሩበትን ዘመን ወላጆቻቸው እየነገሯቸው ያደጉ ልጆች ዛሬ እየበዙ መጠተዋል፡፡  ስግብግብነታችሁና ምቀኝነታችሁ እንዲሁም ሌላውን መጥላትን ከልጅነታችሁ ጀምሮ ያደጋችሁበት በመሆኑ እንጂማ 26 ዓመት ያገኛችሁት እድሜ ስንት ነገር ሰርታችሁ በዘለቄታው የምትወደሱበት በሆነ፡፡

ወያኔ ትግሬዎች መቼም እንደማይማሩ ሕዝብ አውቆ በቁጣ በዙሪያችሁ እንዳለና ቀን እየጠበቀ እንደሆነ እንዴት ማሰብ አትችሉም፡፡ ተክለብርሀንም ይሄ ስለማይባቸው ይመስለል በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ አካሄድን የመረጡት፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኦሮሚያ ቲቪ የሕዝብና አገር ወገንተኝነቱን በሚያሳይ መልኩ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ቀጣይም እንዲህ ሊያጋልጣቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ ሕዝብም በትኩረት እንዲህ እያገለገሉ ያሉ የሚዲያ ሰራተኞችና ሃላፊዎችን ሊከታተል ይገባል፡፡ በእነሱ ላይ ሊሴር የታሰበው ሁሉ የሕዝብ ሊሆን ይገባዋልና፡፡ ሚዲያዲያውም ሆን የመስተዳደሩ ባለስልጣናት ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባው ጉዳይ ብዙ ነው፡፡ በግፍ የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎችን (አነ መረራን)ና የሕዝብ ልጆችም በአስቸኳ እንዲለቀቁ በይፋ መስተዳድሩ አቋም ሊወስድበት የሚገባ ነው፡፡ ዮናታን የተፈረደብት በዘሩ ትግሬ ባለመሆኑ ብቻ እንደሆነ ስናስብ እጅግ እናዝናለን፡፡ መረራና ባልደረቦቹም የኦሮሞ ጀግኖች አባቶቻቸውን የሚያስቡ የኦሮሞን ሕዝብ ወደማንነት ክብሩ ሊመልሱት የሚችሉ መሆናቸውን ታስቦ እንደታሰሩ እናውቃለን፡፡  ሰዎች በዘራቸው ምክነያት ብዙ እንደሞቱ፣ እንደተሰደዱ፣ እንሚታሰሩ ማሰብ እልህ ያጭራል፡፡ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርም እንደተባለው እየሆነ ነው፡፡ ብዙ ቢመከሩም የማይገባቸው፡፡

ማስተዋሉን ይስጠን

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!

 

አሜን!

 

ሰርጸ ደስታ

↧

ሰበር መረጃ ! …..” የሠራተኛ ስምምነቱ ተፈርሟል ” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ ገበየሁ – ነቢዩ ሲራክ

$
0
0

ኢትዮጵያና ሳውዲ አረቢያ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የሠራተኛ ስምሪት ስምምነት መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ ገበየሁ ባሰራጩት መረጃ አረጋግጠዋል ። ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ ስምምነቱን የተፈራረሙት በኢትዮጵያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሳውዲ አረቢያው አቻቸው መሆናቸውን በመጠቆም ስምምነቱ ሀሙስ መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓም በጄዳ ከተማ መሆኑን ባሰራጩት መረጃ አስታውቀዋል ።

እንደ ሚኒስትር ዶር ወርቅነህ በማከል ባሰራጩት ማብራ መረጃ የሚከተለውን አስፍረዋል ” … በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሁለቱም ሀገራት ፈቃድ በተሰጣቸው የስራ ስምሪት ኤጄንሲዎች አማካይነት በሚፈፀም ውል ወደ ሳውዲ አረቢያ ተሠማረተው መሥራት ይችላሉ። በአሠሪዎቻቸው በደል ቢደርስባቸው በሕግ አግባብ መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ ስምምነቱ ስለሚደነግግ በሕገወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው ከፍተኛ ችግር ላይ የሚወድቁት ካሁን በሁዋላ እንደማይኖሩ ይታመናል::” ብለዋል ዶር ወርቅነህ

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስምምነቱ ውስጥ ስለተካተተው የደመወዝና የተለያዩ መብቶችን በሚመለከት ዝርዝር መረጃ እስካሁን ይፋ አልሆነም ። በጉዳዩ ላይ ያነጋገርኳቸው በሳውዲ በኩል ያሉት የመረጃ ምንጮች በስምምነቱ የኢትዮጵያውያኑ ደመወዝ ከ800 ሪያል በላይ እንዳልሆነ ቢጠቁሙም ሊያረጋግጡልኝ ግን አልቻሉም ። ያም ሆኖ በቀጣይ ቀናት ውስጥ በሳውዲ መገናኛ ብዙሃንና በሳውዲ ሠራተኛ ሚኒስተር በኩል ዝርዝር መረጃዎች እንደሚወጡ ይጠበቃል ።

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
ግንቦት 18 ቀን 2009 ዓም

↧

ሕፃናት በጎዳና እና በትምህርት ቤት – ግርማ ሠይፉ ማሩ

$
0
0
ግርማ ሠይፉ ማሩ

ግርማ ሠይፉ ማሩ

ወደፊት አዲስ አበባ እንዴት እንደምትሆን መገመት ከባድ ቢሆንም የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል ብለን ለምናም ሰዎች፤ ሳያገባቸው ገብተው አያገባችሁም የሚሉንን ንቀን በመተው፤ አንድ አንድ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል፡፡ እነዚህ የወደፊት አገር ተረካቢ የምንላቸው ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በየቀኑ በምመላለስበት ለገሐር፣ ብሔራዊ ቲያትር/መከላከያ መብራት ላይ፣ መስቀል አደባባይ፣ ወዘተ የምናያቸው ህፃናት ልጆች በዚህ ሁኔታ መኖራቸው እንዲያበቃና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኝ አንድ ቀን ተነስተው በከተማው ያለውን ህንፃና መኪና በድንጋይ ሲያወድሙ፣ እሳት ጭረው ሲለኩሱ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ በተጨማሪ ከተማው የተስፋፋው ህፃናትን አዝሎ ልመና በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተናገደው፤ የሴቶችና ህፃናት ሚኒሰትር ቢሮ ባለበት ጎዳና ላይ ነው፡፡ በሰማቸው ሚኒሰትርም ይሁን ኤክስፐርት የሆኑ ሰዎች ይህ ጉዳይ እንደሌለ ቆጥረው በተንደላቀቀ መኪና ሲገቡና ሲወጡ ስራቸው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አይችልም፡፡

በአንድ ወቅት የቀደሞዋ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒሰትር በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ስለሄዱት ህፃናት ጉዳይ ለመነጋገር ፈረንሳይ መሄዳቸውን አስታውሳል፡፡ አፍንጫቸው ስር ቤንዚልና ማስተሸ እየሳቡ በጠራራ ፀሀይ ናላቸውን እያዞሩ የሚገኙትን ህፃናት ለመታደግ ግን አንድም የሚደረግ ነገር አይታይም፡፡ በዚህ ፅሁፌ ወቀሳ ብቻ ሳይሆን የመፍትሄ አቅጣጫም ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡

1. በመንገድ ላይ የሚገኙ እድሚያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ በተለይ በቤንዚልና ማስትሽ ናላቸውን የሚያዞሩት ህፃናት እንደዚህ መሆን መብታቸው ሰለአልሆነ፣ በግዳጅ ወደ አንድ ማዕከል ገብተው ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቢ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ህፃናት በማሳደጊያ ወይም በጉዲፈቻ እንዲኖሩ ማመቻቸት በወረቀትም ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አለ (አንቀፅ 36)፤ እነዚህ ሕፃናት ምግብ፣ መጠለያ፣ ትምህርት የማግኘትና ጤናቸው የመጠበቅ መብት አላቸው፡፡ መንግሰት ይህን የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
2. ሕፃናትን ለልመና መጠቀም ወንጀል ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ወላጅ እናትም ሆነ አባት ቢሆኑ ህፃናትን ለልመና ሲጠቀሙ ዝም ብሎ መመልከት፤ ይልቁንም ለእነዚህ ሰዎች ገንዘብ በመስጠት ማበረታታት ገደብ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ልጆቻቸውን መመገብ አልቻልንም ብለው በልመና ላይ የተሰማሩ ሰዎች፤ ልጆቻቸውን ተቀምተው ልጆቹ አስፈላጊው ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ የመንግሰት ግዴታው ይመስለኛል፡፡
የአረጋዊያን መጦሪያ እንደሚያስፈልግ ሁሉ የህፃናት ማሰደጊያ ቦታ መኖር የግድ ነው፡፡ የህፃናት ማሳደጊያ የመጨሻው አማራጭ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ሕፃናት በጎዳና ላይ በዚህ ሁኔታ ከሚኖሩ ግን መቶ በመቶ የተሻለው አማራጭ የህፃናት ማሰደጊያ ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ይህች አገር አቅም የላትም የሚባል ሰንካላ ሰበብ መቅረብ የለበትም፣ ስርዓት ተዘርግቶ ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ህፃናት ማቆያዎች በጉዲፈቻ ልጆች ማሳደግ ለሚፈልጉም ግለሰቦችም ሰርዓት ዘርግቶ ሊያስተናግድ ይችላል፡፡

ለማነኛውም ህፃናት ደህነነታቸው እንዲጠበቅ፣ ሕፃናትን መለመኛ የሚያደርጉ ወላጅ ተብዬዎች ደግሞ አደብ እንዲገዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ሆይ እነዚህ ልጆች ድንጋይ አንስተው፣ እሳት ጭረው ከመነሳታቸው በፊት ሳይቃጠል በቅጠል መባል ያለበት ይመስለኛል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በተለይ አዲስ አበባ ፎቆች እየበቀሉ፣ ከስር ግን ህፃናት ከስብዕና ውጭ እየሆኑባት ያለች መሆኑን ለመረዳት ከላይ በገለፅለኳቸው ቦታዎች መገኘት በቂ ነው፡፡ ወዳጃችን ከበደ ካሣ በቅርቡ እንደተረዳው የባለስልጣኖቻችን መኪና ከውጭ እነርሱን እንዳናይ የሚጋርደ ቢሆንም፤ እነዚህን ልጆች ለማየት የሚጋርዳቸው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በትላንት ምሽት ቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተሰፋዬ የሚመሩት የተማሪዎች መመገቢያ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መድረክ ነበር፡፡ ይህ መድረክ የአድርባይ ማስታወቂያ ስራተኞችን ከማሳየት ባለፈ አንድም ፋይዳ አላገኘሁበት፡፡ በጣት ከሚቆጠሩት የግል ድርጅቶች ውጭ ከፍተኛውን ድጋፍ ያደረጉት ከኢትዮጵያ አየር መንግ፣ ቴለ፣ መብራት ኃይል፣ የክልል መንግስታት፣ ወዘተ በአብዛኛው የመንግሰት ተቋሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ያለምንም ተጨማሪ እዩልኝ ሰሙልኝ ሊያድርጉ የሚችሉት የህዝብ ሀብት ባለቤቶች ናቸው፡፡ መንግሰት የሚያስተዳድራቸው፡፡ ሰለዚህ ኢትዮጵያ አገራችን እነዚህን ልጆች አብልታ ማስተማር ትችላለች የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ የግሎቹ ድጋፍ ሊያደርጉበት የሚችሉበት እድል ሊመቻች ይገባል፡፡ ለማነኛውም ትላንት ለምግብ ገንዘብ የተሰበሰበላቸው ከወላጆች ወይም ከአሰዳጊዎች ጋር ሆነው ምግብ ሳይበሉ በትምህርት ገበታ ለሚገኙት ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ከላይ በመግቢያ ያነሳኋቸው ሕፃናት ልጆች ከዚህ በከፋ ደረጃ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት በበሩ ላይ ያሉትን ልጆች ቢታደግ የበለጠ ያስመሰግነዋል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡ ይህ ሁሉ የምለው መንግስት ካለ ብዬ ነው…….
“የሕፃናት ጉዳይ ሁሉንም ይመለከታል – ከሠይጣን በስተቀር!!!”

↧
↧

ሰበር ዜና !….በማህበራዊ ድረ ገፅ ሐሳብሕን ዉጪ ፤ ከሚኖሩ ተቃዋሚ ሐይሎች ጋር ተለዋዉጠሐል ፣ በሚል የሀሰት ወንጀል በ1 አመት ከ6 ወር የወያኔዉ ካንጋሮ ፍርድ ቤትፈርዶበታል

$
0
0

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው

በማህበራዊ ድረ ገፅ ሐሳብሕን ዉጪ ፤ ከሚኖሩ ተቃዋሚ ሐይሎች ጋር ተለዋዉጠሐል ፣ በሚል የሀሰት ወንጀል ተከስሶ በቅሊንጦ መታጎሪያ ቤት <1 አመት ከ6 ወር > በቀጠሮ መመላለስ ሲማቅቅ የቆየዉ ፤ ጋዜጠኛና አክቲቪስት ጌታቸዉ ሺፈራዉ ዛሬም የወያኔዉ ካንጋሮ ፍርድ ቤት ፥
< በ1 አመት ከ6 ወር > እስራት ፈርዶበታል ፡፡
የህዉሓት ኢትዮጵያ ፍትህን እያስቀጠለች ነዉ ፡፡
ድል የሕዝብ ነዉ !

↧

ለትግሉ የሚበጀው የቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴን ለቀቅ፣ ህወሓት/ኢህአዴግን ጠበቅ ማድረግ ነው!

$
0
0

አበጋዝ ወንድሙ

የኢትዮጵያ ተማሪዎ እንቅስቃሴና ከውስጡ ወጥተው  ፣ ባለፈው ዘመን  ህብረብሔራዊ ትግል ያካሄዱ ወገኖች (ያ ትውልድ ተብሎ የሚጠራው) ላይ የሚካሄደው ያልተቋ ረጠ ወገዛና እርግማን የዘመኑ አንቆቅልሽ ሆኖ ይሰማኛል።

ይህንን ተገቢ ያልሆነ ወቀሳ የሚያካሂዱ ወገኖች ስብሰብ ተደርገው ሲታዩ የሚከተሉትን ይመስላሉ።

  • አሁን አሁን፡ ጀማሪ ፖለቲከኞች የሆኑ፣
  • በንጉሱ ጊዜ ወይንም በደርግ ዘመን የገዥው ቡድን አካልና መሪ ተዋናይ የነበሩና፣

ግን ዛሬ ተገልብጠው ደርሶ ዴሞክራት የሆኑ  የአገርና የህዝብ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ፣

  • ከህብረብሔራዊው እንቅስቃሴ ውጭ በብሄር ተደራጅተው የነበሩ፣
  • ወይንም ጭራሹኑ ምንም ውስጥ ያልነበሩ፣ በግል ኑሮና ትምህርት ተጠምደው ቆይተው የወጣትነትና የትግል አፍላው ጊዜ ያለፈባቸውና፣ አሁን ግን የምሁር ካባ ለብሰናልና ፍርድ ሰጭ ነን ባይ ግለሰቦች

 

በቴክኖሎጂ እድገት አማካይነት፣ ዛሬ ሁሉም በየፊናው ተነስቶ የሚፈነጭበት ድረ ገጽና የመሳሰሉት  መድረክ በመፈጠራቸው፣ (facebook, tweeter, blog, paltalk…) ተማርኩ ተመራመርኩ ባዩ   ፣ “የባእድ አስተሳሰብ እንዳለ በመቀበል” የሌለ ችግር ፈጥረው አገርን ለችግር ዳረጉ ሲል፣አንዳንዱ የፈጠራ ታሪክ በመፈብረክ የተማሪውን አንቅስቃሴ በ”ጸረ አማራነት” ሲከስ ፣ በተቃራኒው ደግሞ በስልጣን አካባቢ ያሉ ጠባብ ብሄርተኝነት ያሰከራቸው ቡድኖች፣ በህብረብሔራዊ ትግል ስም “የአማራውን  የበላይነት ሊያስቀጥሉ የታገሉ” ብለው ሲወነጅሉ ማየት የተለመደ እየሆነ መጥቷል ።

ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መጀመር ምክንያት የሆነው ፣ እንዲሁ የተወሰኑ መሰሪ ወይንም የዋህ  ልጆች (እንደ አውጋዡ ይለያያል!)  አንድ ማለዳ ተነስተው፣ “እስቲ አንድ የተማሪ አንቅስቃሴ እንጀምርና ሀገር እናምስ!”  በሚል የተነሳ ነገር ሳይሆን፣በወቅቱ የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የፈጠረው ጉዳይ አንደነበረ  ማንም መሳት የሌለበት፣  የግዴታም መቀበል ያለብን ሀቅ ነው ።

ምናልባት እነኚህ ግለሰቦች፣ የኢህአዴግ ዘረኝነት፣ ጭካኔና ሀገርን ከፋፍሎ መግዛት እየከፋ መምጣትና፣ ተያይዞም የደርግ አውሬያዊ ስርዓት አየተረሳ መሄድ፣ በንጉሱ ዘመን የነበረውንና መለወጥም የነበረበትን የፈላጭ ቆራጭና የዃላ ቀር አገዛዝ እንዲረሱና የፊውዳል ስርዓቱን እንዲናፍቁ አድርጎዋቸው ይሆናል። በዚህም የተነሳ ስርአቱን ለመቀየር የተነሳውን የተማሪውን አንቅስቃሴ በጭፍን ማውገዝ፣ የትውልዱን በጎም ሆነ የተሳሳተ ታሪኩን በቅጡ አለመረዳት ወቅቱንም  በሚገባ አለመገንዘብም ይሆናል።

የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን  በቅንነት ካየነው ግን የተማሪው እንቅስቃሴ እንዲሁ አንዴ እመር ብሎ ሃገራዊ አጀንዳ አንግቦ የተነሳ  ሳይሆን፣አጀማመሩ  ከራሱ ከተማሪው ጥቅም ጋር የተያያዙ ውሱን ጥያቄዎችን በማንሳት በሂደት እያደገ  ሃገራዊ ጥያቄዎች ወደ ማንሳት የዘለቀ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። መማር ማለት ማወቅና ማገናዘብ ነውና የእውቀት አድማሳቸው  እየሰፋ ሲሄድ ነው፣ ከራስ ውሱን ጥያቄ ባሻገር  የሀገራችንን መሰረታዊ ችግር መገንዝብ የጀመሩት ተማሪዎች ፣  “ድህነት ወንጀል አይደለም !” “ መሬት ለአራሹ !” “ የብሄረሰቦች መብት ይከበር !”  “የዜጎች አኩልነት የሚከበርባትና የበለጸገች ሀገር አንገንባ” ወደሚል ሃገራዊ አጀንዳ የተሸጋገሩት። ይሄንን ተግባራዊ ለማድረግ ክቡር ህይወታቸውን እስከመሰዋት የደረሰ ወኔ የተላበሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ያካሄዱትን ትግል፣  በትግሉ ሂደት የተፈጠሩ አንዳንድ  ስህተቶችን በማጉላት ከነአካቴው እንቅስቃሴውንና ታጋዮቹን በጅምላ መኮነን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፣ ፍትሃዊም አይደለም የምለው።

እስቲ እንደምሳሌ አንዱን፡ “የባእድ አስተሳሰብ አምጥተው” የሚለውን ውንጀላ በአጭሩ እንቃኘው ፣

 

የ”ባእድ አስተሳሰብ” ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው የሚለው በጨለማ ዘመን የተነገረ ቢሆን ተቀባይነት ይኖረው እንደሁ እንጂ  አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ያውም ተማርን ተመራመርን ከሚሉት ወገን ሲሰነዘር የሚያሳፍር ይሆናል። የሰው ልጅ ስለ ህብረተሰብ አረዳድም ሆነ ሌላ የሚያፈልቀው እውቀትና፣ በዛ ላይ ተመስርቶ የሚገኙ ተመክሮዎች፣ በአንድ ሀገር ጂኦግራፋዊ ክልል ብቻ መወሰን አለባቸው የሚል አይነት ክርክር ስለሚሆን ብዙም አንደማያስኬድ አጥተውት ነው ለማለትም  ይከብዳል።

እንደው የሰነፍ ዱላ መሆኑ ነው አንጂ፣ ዛሬ ሁሉም የሚምልበትና የሚገዘትበት የ”ሊበራል ዴሞክራሲ” አስተሳሰብ ውልደቱ ኢትዮጵያ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን። እኒህ ወገኖች ይሄን በወቅቱ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ የበላይነት የነበረውን የፖለቲካ አመለካከት ትክክል ነበር ወይንም የተሳሳተ ነበር ማለቱ ሲበቃ ፣በድፍኑ የባእድ አስተሳሰብ የሚለው ወገዛና ማጥላላት አያዋጣቸውም። ዛሬ በአገራችን አብዛኛው ሕዝብ የሚከተላቸው የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶችም አመጣጣቸው  ከባእድ ነውና ወደ ጥንታዊውና ሃገራዊ እምነት፣ ምንም ይሁን ምንም  እንመለስ የሚል ክርክር ውስጥ እንደማይገቡም ግልጽ ነው።

በወቅቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ባብዛኛው ዓለም ለነጻነትና ለፍትህ የሚታገሉ ኃይሎች  ተቀባይነት የነበረውን  የማርክሲዝም ሌኒንዝም አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና ሌሎች ታጋዮች እንደ ትግል መሳሪያ መጠቀም፣ (ዛሬም ቢሆን የዓለም አንድ አምስተኛ ሕዝብ ያላትና ፣በዓለም በኢኮኖሚ ግዝፈት ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛነትን የያዘችው ቻይና፣ አስካሁን ከዚህ ያደረሰኝ ለቀጣዩም አድገቴ ወሳኙ ይሄው የፖለቲካ አረዳዴ ነዉ ማለቷ አንዳለ ሆኖ )  ምናልባት በቅጡ አልተረዱትም፣ ወይንም ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝበው አለተጠቀሙበትም ይባል እንደሆነ እንጂ፣ እንደው በድፍኑ የ”ባእድ አስተሳሰብ” በሚል ለማጣጣል መሞከሩ አያዛልቅም።

በኢትዮጵያ የነበረውና አሁንም ያለው በብሔረሰቦች መሃል ያለ አድልኦ የተማሪው እንቅስቃሴ የፈጠረው ይመስል፣ ትውልዱ የብሔሮች እኩልነት ይከበር በሚል ያካሄደውን ትግል፣  በሰላም ይኖር የነበረውን ሕዝብ እንደከፋፈለ ተደርጎ የሚነዛ ውንጀላ ከገዥ መደብ አባላት ሲሰነዘርበት፣ ከጠባብ ብሄርተኞች ደግሞ የተማሪው እንቅስቃሴ የብሄርን ትግል የሃገሪቱ ዋነኛ ቅራኔ ነው ብሎ አለመቀበሉ፣ የአማራውን የበላይ ገዥነት ለማስቀጠል የሚደረግ ጥረት  ነበር የሚል ሀሰት ይሰራጭ አንደነበር ይታወቃል። በተቃራኒው ደግሞ አሁን አዲሱ ውንጀላ “ለብሄሮች እኩልነት በሚል የተደረገው ትግል ጸረ አማራ ትግል ነበር” ወደሚል አይን ያፈጠጠ ቅጥፈት ተቀይሯል። ይሄ ውንጀላ በጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ተወልዶና አድጎ አሁን ድረስ የዘለቀው ህወሓት ላይ ቢወሰን ኖሮ  ትርጉም ሊሰጠው ይቻል ነበር።

የቀድሞው የተማሪው እንቅስቃሴ ከሌላ ወገኑ የተለየ ኑሮ ያልነበረውን የአማራ ማህበረሰብን  አስመልክቶ ምንም አይነት ብዥታ ሳይኖረው ፣ ከሌሎች መሰል ወገኖቹ ጋር በመተባብር በስሙ የሚነግዱትን የገዥ መደብ አባላትና አጋሮቻቸውን ከስልጣን አውርዶ የሁሉም ብሄረሰብ አባላት በአኩልነት የሚኖሩባትን ሀገር እንገንባ ብሎ መታገሉ በምንም መመዘኛ ጸረ አማራ ሊያሰኘው አይችልም።

 

ዛሬም ቢሆን ሀገሪቱን በዋናነት በሁሉም ዘርፍ ተቆጣጥሮ ህዝብን መከራ የሚያበላውን ዘረኛ የህወሓት አገዛዝ ስንታገል፣ አብዛኛውን የትግራይ ማህበረሰብ አባላት ለትግል አጋርነት አየጠራን፣ የገዥ መደቡ ላይ አነጣጥረን መሆን ስላለበት በጸረ ትግሬነት ሊወነጅሉ የሚፈልጉ የትግራይ ገዥ መደብ አባላትና ደጋፊዎች አንዳሉ ብንገነዘብም፣ እነሱን ፍራቻ ወይንም ለማስደሰት ሲባል የምናድበሰብሰው አውነታ ሊሆን አይችልም።

ዛሬ አገራችን ላይ የተዘረጋውን አስከፊ የህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት አስወግዶ የዜጎች አኩልነትና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገው ትግል ስኬት አንዲኖረው ከተፈለገ ፣ነጋ ጠባ የቀድሞ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በማውገዝ የሚገኝ ትርፍ የለምና፣ የሚበጀው ሙሉ ትኩረታችንን ህወሓት/ኢህአዴግ ላይ አድርገን ፣ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ የሀገር ፍቅርን፣ ህብረብሄራዊነትን፣ የአላማ ጽናትን ፣ ላመኑበት ደግሞ፣ ክቡር ሕይወትን እስከመሰዋት ድረስ የዘለቀ ቆራጥነትን ተውሶ፣ ከነበሩት ስህተቶችም ትምህርት ቀስሞ ወደ ፊት መራመድን ነው ።

 

አበጋዝ ወንድሙ

↧

 ፀረ ሽብር ህጉ ያመጣው ሽብር! – በቶማስ ሰብሰቤ

$
0
0
ፌስቡክ/Facebook/ በ2016 ሰኔ ወር ባወጣው የአፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚዎች ዝርዝር 5 ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ፌስቡክ ይጠቀማሉ።ከአልጄሪያ ፣ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ ቀጥላ ብዙ ኢትዮጵያ በርካታ አካውንት አላቸው።የፌስቡኩ ማህበረሰብ ከአዲስ አበባ የህዝብ ብዛት ጋር ተቀራራቢ የህዝብ ብዛት አላው። አምስት ሚሊየን ፌስቡክ/Facebook/ ተጠቃሚዎች ዘመኑ ይዞላቸው በመጣው ” መተንፈሻ ” የሚያቁትን እና የመሰላቸውን ይፃፃፋሉ ፣ ሃሳባቸውን በነፃ ያጋራሉ።
ይህ ሀሳብ በነፃነት የመግልፅ አጋጣሚ ደሞ ለሀሳብ ነፃነት የተለያዮ ህጎች ላወጣ መንግስት አይመችም።ለመቆጣጠር ፣ ለመከታታል እና እሱ የማይፈልገው ሀሳብ የለቀቀውን እና ያጋራውን  በቀላሉ ለመልቀም ከባድ ነው።በኢንተርኔ አፈና እና በፌስ ቡክ ገፆች ላይ በሚፅፉት ሃሳቦች ብዙ ተከታይ ያገኙ ግለሰቦች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ ፣ መክስስና ማሰር ቀሪውን ተጠቃሚ እንደ መቆጣጠር የተያዘ ስልት ባለፉት አመታት በሰፊው አይተናል።በዚህ አመት ኢህአዴግ የገባበት የፖለቲካ አለመረጋት ለማርገብ የመጀመሪያ ካደረገባቸው መፍትሄ አንዱ የፌስቡክ Facebook አፈና እና የፌስቡክ ተጠቃሚውን ማስደንበር ፣ ጠንከር ያለ ትችት የሰነዘረ ጫና ፈጣሪ ግለሰብን ማስር አንዱ መንግድ ነው።
አሸባሪውን የረሳ የፀረ ሽብር አዋጅ!
በእነዚህ ባነሳውት ርዕስ እንኳን ብቻ በኢንተርኔት ያለው 5 ሚሊየን ህዝብ እያሸበረ ያለው ማን ነው? ኢህአዴግ የፌስ ቡክ ተጠቃሚን በምን ስልት እያሸበረ ይገኛል? ስልቱ ምን ያህል እዋጭ ነው? እንዚህን ጥያቄ ለመመለስ መጀመሪያ የመንግስተ ሁለት መደበኛ ስልቶች በፌስቡክ ላይ እያደረገ ያለው ምንድ ናቸው የሚለው በዝርዝር እንመልክት።
የኢንተርኔት አፈና
የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ብዙ ሰዓታቸውን በገፃቸው ላይ እንዳያሳልፉ ፣መረጃዎችን ወዲያው ወዲያው እንዳይለዋወጡ ፣ ወቅታው መረጃዎች አጀንዳ እንዳይሆ እና የጋራ መግባባት ላይ እንዳይደርሱ የኢንተርኔት አገልግሎቱን አብዛኛው ቀን መዝጋት ፣የተወሰነ ቀን በከፊል መልቀቅ ፣በክልል ከየሞች ጭራሹኑ ለወራት ማቋረጥ እና ብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ያሉበት ከተማዎች ላይ ኢንተርኔት ቅቤ ለምኔ ማድረግ ነው።ይህም መኪና ስቶ ነዳጅ እንደ መከልከል ይቆጠራል።ይህው ስልትም ሰው ኢንተርኔት ተጠቃሚውን አሰልችቶ በደካማ አገልግሎት ከገፁ ማራቅ እና አዲስ ተጠቃሚም አካውንት ከፍቶ እንዳይመጣ እንዲከለክል የማድረግ ስልት ነው።በተለይ መንግስት ላይ ጥርሱን የነከሰ ከተማ እና ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር ልምድ ባላቸው አካባቢዎች የኢንተርኔት አፈና ይበረታል።
ብዙ ተከታይ ያለቸው እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግልሰቦችን በሽብር መክስ
ይህ ሁለተኛው የኢንተርኔት አብዛኛው ተጠቃሚ ማህበረሰቡን ማስበርገጊያ ዘዴ ነው።ኢህአዴግ የፌስቡክ ተፅዕኖን ለመቆጣጠር የፌስቡክ ሞዴሎችን ላይ እርምጃ መውሰድ ተያይዞታል።”መሪው ከተመታ መንጋው ይደንብራል ወይም ይበተናል ” ብሎ የማመን ፖለቲካ ውጤት ነው።።በፌስቡክ በሚያነሱት ሀሳብ ብዙሃን ተከታይ ያለቸው ግለሰቦች በሚፅፉት ሀሳቦች ላይ መመሰረት በማድረግ የሃስት የሽብር ክስ ማቅረብ ፣ማሰር እና መቅጣት ተከታዮቹን ያስደነብርለታል ፤ አዲሱ ተጠቃሚም በፍርሃት ያሰረረዋል ብሎ እየሰሩ ነው።ዮናታን ታስፋዮን ስድስት አመት ሲቀጣው ልጁን ማሰር ሳይሆን ዋነኛ አላማው ሳይሆን የእሱን መሰሎች እና ተከታዮችን የመተጣውላቹ ደውል ነው።ይህም አምስት ሚሊየን ህዝብን ለማሸብር ፣ ለመቆጣጠር እና ለማስደንበር አይነተኛ ምሳሌ ነው።በዮናት ተስፋዮ እና የሌሎችን ክስ የሰማ የፌስቡክ ተጠቃሚ ምን እንደሚያስብ አስቡ።ፖስተ  ማድረግ 6 አመት ከሆነ ሼር 4 ፣ ኮመንት 2 አመት ብሎ ነው የሚደንብረው።በትንሹ 5 ሚሊየን ህዝቦች በዚህ መልኩ ነው ሽብር የተፈፀመብት።ታዲያ እዚህ ጋር ነው እራሱ ኢህአዴግ ያወጣውመ የፀረ የሽብር ህግ አንቀፅ ሶስት የሚጥሰው።ይህ አንቀፅም ኢህአዴግን ሽብርተኛ ያደርገዋል።
” ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖታዊ ወይም የአይዶሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሰት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራት ወይም  የሃገሪቱን መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ህገመንግስተዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋት ወይም ለማፍረስ፡-
 አዚህ አንቀፅ ስር ያለውን …አይዲዮሎጂ ዓለማ ለማራመድ በማስብ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡ ክፍል ለማስፈራራት  ……የሞከረ የሽብር ድርጊት ነው ይላል።ከላይ እንደገለፅኩት በሁለቱ ዘዴዎች 5 ሚሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚን ለማስፈራራት እና ተፅዕኖ ለማሳደር የራሳቸው አይዴዮሎጂ መሰል ስልት ይዘው አንድ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ፍርሃት የዘራው ኢህአዴግን ማን ይክሰሰው? የፌስቡክ ተጠቃሚው ብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ከፍተኛ ማህበረሰብ አገልግሎት ውስጥ ቢቆጠር ቀዳሚው ቦታ ይይዛል።ታዲያ ይህ ማህበረሰብን ሀሳቡን በነፃነት እንዳያሸራሽር ፣የመሰለውን ፣ያየውን እና የሚሰማውን በነባራዊ እውነታዎች እንዳይገልፅ ተጠቃሚው አርአያ የሚላቸውን ሰው ማሰር ፣መክሰስ እና ማሰቃየት ሽብር አይደለም እንዴ? የዮናታን መታሰር የፖስት መታሰር አይደል እንዴ? ብዙ ተከታዮች ያላቸውን ግለሰቦች በሽብር መክስ እና ማሰር ቀሪው 5 ሚሊየን ህዝብ በፍርሃት ማሰር ፣ አዲስ ተጠቃሚ እንዳይመጣ የሚያደርግ ሽብር አይደለም እንዴ? ማንኛውም ሰው ቦብም የማያዝበት አንደኛው ምክንያት ውጤቱን ሰለሚያውቅ ነው።ለዚህም ቦምብ የዋለበት ጦረኛ እንጂ ንፁሃን የለም።ቦምብ  እና ጦርነት የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው።ዛሬም ፌስቡክ እና ሽብርተኝነት ቤተሰብ ያደረገው ኢህአዴግ ሰው ፌስቡኩን እንደ ቦንብ እንዲፈራው አድርጎታል።ታዲያ አንቀፅ ሶስት የጣሳው ማን ነው? ከጋዜጠኛው እና ከጦማሪው በላይ 5 ሚሊየን ህዝቦችን እያሸበረ ያለውን መንግስት እራሱ ባወጣው ህግ መሰረት አሸባሪው እሱ ያደርገዋል።
ፌስቡክን ከሽብር ጋር በተደጋጋሚነት ማያያዝ እና በፖስት 6 አመት ማሰር የሰው ልጅ የሚያገናዝ   እንስሳ ከሚለው ጋር ይጋጫል።ሀሳቡን በነፃነት መግልፅ አለበት የሚለው ገደል እና እስር ቤት የሚከት ነው።Man is a rational animal! የሰው ልጅ የሚያገናዝብ እንስሳ ነው፡፡ የሚያግናዛበው በአካባቢው ከሚያገኛቸው እውነታዎች አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ስለፈለገው ነገር ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ከፈለው መረጃ ላይ፡፡ ያገኘውን መረጃ አገናዝቦ የፈለገው አቋም የመያዝ መብትም አለው፡፡ መንግሥትን ጨምሮ ማንም ሰው ይህንን ዕወቅ ይህንን አትወቅ እንዲለው አይፈልግም፡፡ የማወቅ፣ የማገናዘብ፣ አቋም የመያዝ ብቻ አይደለም አቋሙን ለፈለገው ሰው ያለምንም ፍርሐት የማሳወቅ መብት አለው፡፡ ምክንያቱም ሰው ነውና፡፡
ኢህአዴግ ሆይ የዮናታን እና መሰሎቹ እጅ ለማያዝ ብትችልም ሚሊየን እጆችን ይዘህ አዘልቀውም! ቢያንስ ቢያንስ አንተህ ላወጣውህ ህጎች እራስህን ተገዛ።የመናገር ነፃነት እስከ መጮህ እና ማልቀስ ድረስ ነውና ታቀብ ወይስ የአሰተሳሰብ  ነፃነት ከሚለው አንቀፅ 29 ስር “ይህ አንቀፅ ለኢትዮጵያን ሳይሆን ለጉረቤት ሀገር ነው ” ብለህ ፃፍበት።
↧

የቴዲ አፍሮ …ተሞክሮ! (ቁጥር አንድ) ከኤርሚያስ ለገሰ

$
0
0

የዛሬ ሁለት አመት በጸደዩ ወራት የኢሳት ስድስተኛ አመት ለማክበር በፍሎሪዳ ግዛት ታምፓ ከተማ ተጉዤ ነበር።-የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በዝግጅቱ ላይ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ጋር አብሮ የሰራ ድምጻዊ አብሮኝ ተጉዟል ። ይህ የሚወዳት አገሩን ተቀምቶ በሰሜን አሜሪካ ቨርጂኒያ የከተመ አርቲስት ጋር በነበረን ወግ መሃል ስለ አርቲስት ቴዲ አፍሮ አንስተን የተጫወትንበት ነበር። ቴዲ አፍሮን በቅርበት የሚያውቀው ይህ የኪነጥበብ ሰው እንዳጫወተኝ ከሆነ የቴዲ አፍሮ የስኬት ምክንያቶች በዘፈቀደ የመጣ አይደለም። ይልቁንስ የቴዲ የስኬት ምክንያቶች የስራ ዲሲፕሊኑ፣ ትጋቱ፣ ለራሱና ለሙያው የሚሰጠው ዋጋ፣ በየጊዜው ብቃቱን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት፣ ትላንት የነበረውን አስተሳሰብ ዕድገት ለማምጣት ያለው ዝግጁነትና የጠለቀ የአሸናፊነት ስሜት ሰንቆ መጓዙ እንደሆነ ያምናል። በህይወቴ ጥንቅቄ የሚያውቅ እንደ ቴዲ አፍሮ አላጋጠመኝም ይላል።

እርግጥም ቴዲ አፍሮ እምቅ የሆነ ችሎታውን ለአለም ማሳየት የቻለው ሙያው ለሚጠይቀው ባህርያትና ክህሎት ጥልቅ ስሜት ያለው መሆኑን ከሩቅ ሆኖ መገመት ይቻላል። አሁንም ከርቀት መታዘብ እንደሚቻለው ቴዲ አፍሮ ወቅታዊውን የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ መከታተል መቻሉና ተራክቦውን አንደበተ ርቱዕ በሆነ መንገድ መግልፅ መቻሉ የማህበረሰቡን ቀልብ ለመግዛት አስችሎታል። እንዲህ አይነት ግለስቦችላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው  ታዋቂው የአመራር ሳይንስ ፅሐፊ John Maxwell “በወርቃማ ቃላትና አንደበት ዕለምን መግዛት ይቻላል” በማለት ይገልጻል። ወርቃማ ቃላትን ሰዎችን ለማሳመን እንደቅድሚያ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን በማስገንዘብ።

በእኔ ዕምነት ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የኪነጥበብ ሙያተኞች የሚጎላድላቸው ከላይ የተገልጸው የቴዲ አፍሮን ባህሪ መላበስ አለመቻላቸው ይመስለኛል። ለነገሩ የዚህ አጭር መጣጥፍ ትኩረት የኪነጥበብ ሰዎች ላይ በመሆኑ እንጂ ችግሩ በተለያዩ ሙያ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጨምር ነው። እንዲያውም የኋለኛው ሳይከፋ አይቀርም። አለማወቅ የራሱ በረከትና ጸጋ ያለው ይመስል አገዛዙ ያነገበውን አገር የማፍረሻ አሳብና መሳሪያ አለማወቃቸው የሚያስኮፍሳቸው ራሳቸውን “ምሁር” ጎራ የከተቱ በርካታ ሰዎች አጋጥመውኛል። ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም እንዲህ አይነት ደካማ አቋም ያላቸው የምሁርነት ካባ ያጠለቁ ኋላቀሮች መኖራቸውን እጠብቃልሁ። ከስራ ዲሲፕሊንና ትጋት ይልቅ ልግምተኛና ተሳዳቢ፣ በየጊዜው የራስ ብቃትን ለማሳደግ ከሚደረግ ጥረት ይልቅ ወደ ዘለፋና አጉል አሽኮለሌ የሚያመራ፤ ከሁኔታዎች ጋር የሚለዋወጥ የስነልቦና ዝግጅትና ለውጥ ከማሰብ ይልቅ በትላንትና የወደቀ አመለካከት ተቸንክሮ መቅረት የሚይታይባቸው ብዙ ናቸው። እጅግ በጣም በዙ።

ብዕሬ ሌላ ቦታ ረግጦ እዚህ ገባሁ እንጂ ልፅፍ ያሰብኩት የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሙያተኞች ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ምን ትምህርት ሊቀስሙይገባል የሚለውን የግል ምልከታ ለማስቀመጥ ነበር። አስተያየቴ ስሜታዊነት አጥቅቶ ከሆነ ምናልባትም የወቅቱ የአገራችን ሁኔታ የፈጠረው ሊሆን ይችላል።ይህ ምልከታየ የሚቀርብበት ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የህልውና አደጋ ያጋጠማት ሁኔታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ አደጋውን በሚያመላክቱ ቃላት የታጀበ ሊሆን ይችላል። አሁን የደረስንበት ደረጃ አካፋን አካፋ የምንልበት እንጂ አንዱ ሌላውን በቃላት ለመሸንገልና ለማቄል የሚሞክርበት አይደለም። ተወደደም ተጠላም “እኛ እና እነሱ” የሚል ነጭና ጥቁር መጋረጃ የተፈጠረበት ዘመን ላይ እንገኛለን። በነጭና ጥቁር መሻሻል ደግሞ ግራጫ የሚባል እራፊ ጨርቅ የለም።

***

ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን “ኢትዮጵያ” በሚለው አልበምም ሆነ በተከታታይ በሰጣቸው ቃለ-መጠይቆች የገለጠው ቀዳሚ ቁም ነገር “ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት አደጋና ፈተና ላይ ወድቋል!! በጎሳና ሐይማኖት መከፋፈል ተፈጥሯል!” የሚለውን ነው  ይሄ የቴዲ አፍሮ አገላለጽ እጅግ የጠለቀና ከየትኛውም አጀንዳ በፊት ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ነው። የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሙያተኞች አደጋ ውስጥ ስለወደቀው ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት በየጊዜው መድረክ አየፈጠሩ መነጋገር አለባቸው:: በአንድ ውቅት  ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም አንደተናገሩት ኢትዮጵያዊነት አንዲቀጥል በመጀመሪያ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር መኖር አለባት ። የዛሪው ወሳኝ ትግል ደግሞ በቅድሚያ ኢትዮጵያን ማዳን ሊሆን ይገባል ። ኢትዮጵያን ለማዳን ደግሞ ማንኛውም ሰው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ፥ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድነቱን ለማምጣት ሲል የሚከተለውን ስትራቴጂና ታክቲክ ከሩቅ ሆኖ መመልከት አይቻልም። ከፍ ካለም ሞራላዊ ወንጀለኝነት ነው::በመሆኑም የህልውና ትግሉን ያለማቅማማት ተቀብሎ የዜግነት ግዴታን መወጣት ፍላጎት የሚያጣ የኪነ-ጥበብ ሰው የቀድሞ ዝናው የትየለሌም ይድረስ አፈር ከድሜ መጋጡ አይቀርም:: በአጠቃላይ መልኩ አሁን አየተደረገ ያለው ትንቅንቅ የሞት ሽረት ትግል መዳረሻ ህልሙ ኢትዮጵያን መታደግ መሆን እንደሚገባው መገንዘብ ያሻል።

ቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ የጣለ ጎሰኝነት ተፈጥሯል “ የሚለው አገላለጡም ወቅታዊ እውነታ ነው ። አርቲስቱ እንዳሰመረበት ዛሬ በሃገራችን የተነሰራፋውን የዘረኝነትና ጎሳዊ  መንፈስ ድል አድርገን ብዙህነትን በሚቀበል አንድነት ውስጥ መኖር የምንችለው ችግሩን በቅጡ ስንገነዘብ ነው ። በሽታውን ያላወቀ መድሃኒቱን ማወቅ ይሳነዋል እንዲሉ የወቅቱ የኢትዮጵያ ችግር መፍቻ ኣብይ ቁልፍ ያለው እዚህ ላይ ነው ። በግልጽ እንደሚታየው ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ህውሃት መንግስታዊ ስልጣኑን በመጠቀም በፈጠረው “ የትግራይ አድሎአዊ ተጠቃሚነት “ ምክንያት ጎሰኛ አመለካከት እየተስፋፋ ሄዷል ። በተለይም ህውሃት በአማራና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ በቀል ለማድረስ ፖሊሲ ነድፎ መንቀሳቀሱ የመገፋት ስሜት ፈጥሯል ። ህውሃቶች ለትግራይ ክልል እንደ ገጸ በረከት ይዘውላቸው የመጡት “ ኤፈርት ትልማ እና ረስት “ የሚባሉ ኩባንያዎችና ማህበራት የፈጠሩት አድሎ እርስ በእርስ በጠላትነት መመልከትን ፈጥሯል ። አርቲስቱ እንደገለጠው ጉዞአችን አንድ ሐገር የመመስረት ከሆነ አንደዚ አይነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በባለቤትነት ስሜት ኣንስተን መነጋገር ይኖርብናል። አሁንም ቢሆን ልሰማው የማልወደውና ለመረዳቴ እንደ ቧልት የምቆጥረው “ትግራይ በህውሃት አልተጠቀመችም “ የሚለውን ነው ።

ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ትልቁ ጥያቄ ብሄራዊ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት መጥፋት ሆኗል ። ይህንን ጠንቅቆ አለማወቅ ተጨባጩንና ትክክለኛውን ሁኔታ አለመረዳት ያስከትላል ። ያየነውና እያየነው ያለነው ነባራዊ ሃቅ ጸረ እኩልነትና የራስን ዘር ለመጥቀም የሚካሄድ ሩጫ እንደ አንድ ሃገር መቀጠል የማያስችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ። በአንድ በኩል ህውሀት በሚከተለው በዘር ላይ የተመረኮዘ አድሎአዊ ፖሊሲ ምክንያት ከኢፍትሃዊነቱ ተጠቃሚ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ተፈጥረዋል ። በሌላ በኩል ከፖለቲካው ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች የተገለለው የሌላው ብሄረሰብ ተወላጅ ከበደሉ ብዛት አንጀቱ እየነፈረና ሌሎች አማራጮችን የሚያማትርበት ሁኔታ ተፈጥሯል ።

እናም ቴዲ አፍሮ በቃለ መጠይቁ “ኢትዮጵያዊነት የሚሻክራቸው ሰዎች ተፈጥረዋል” በማለት የጋረዳቸው ማህበረሰቦች ሊፈጠሩ የቻሉበት መሰረታዊ ምክንያት ይሄ ነው ። ህውሀት ካልተወገደ አልያም የዘረኝነት ፖሊሲውን እስካልቀየረ ድረስ በመገፋት የሚፈጠረው የጎሰኝነት ስሜት የሚስፋፋ እንጂ ሊጠፋ የሚችል አይደለም ። ይህም የበለጸገች ኢትዮጵያ ከመገንባት ይልቅ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና የተባበረ አቅም በመሸርሸር ወደ ዜሮ የሚወስድ ይሆናል ። ለዚህ ሁሉ አደገኛ ሁኔታ መፈጠር ተጠያቂው ሃገሪቱን በብቸኝነት እየመራ ያለው “ የትግራይ ነጻ አውጪ“ እንጂ ሌላው ሊሆን አይችልም ። አሁን ባለችው ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መገለል ምክንያት ኢትዮጵያውነታቸውን ጥያቄ የሚያነሱ ቢኖር ሊገርመን አይገባም ። ጥያቄውን የሚነሱት ሃይሎች አሜሪካ ይኑሩ አውስትራሊያ፥ አውሮፓ ይኑሩ አፍሪካ ፥ ኢስያ ይኑሩ አንታርክቲካ መነሻ ሃቅ አላቸው።  ጎንደር ይኑሩ ሐረር፥ አዲስ አበባ ይኑሩ አላባ ፥ ኮፈሌ ይኑሩ ሰላሌ በመገለሉ ምክንያት ቅሬታ የቋጠረ ህዝብ ነው። የሲዳማ ህዝብ “ ኦላን ይዞ “ እንጂ በሎቄ አዋሳ የደረሰበት ጭፍጨፋ ለማኩረፍና ቂም ለማዘል በቂ ነበር ። የጋምቤላው ጭፍጨፋና የመሬት ንጥቂያ “ አገነ ገትያ! አነ ሚዬጎ! “ በሚሉ የፊቅር ቃላት ባይታጀብ ኖሮ የቂም ቋጠሮው ይፈነዳ ነበር ። “ አረጀች እያሉ ሰዎቹ ሲያሙሽ፥ ሙሽራ ነሽ ጎንደር ይሰፋል ልብስሽ “ የሚለውን አገላለጥ ኢትዮጵያዊያን በሲቃ እየተያዙ የሚዘፍኑት ባለፉት ወራት ጥይት የተርከፈከፈባቸው ኢትዮጵያውያንን በማስብ ነው ። አዲስ አበባ ቀዳማዊ ሐይለስላሴ ያቆሙለትን ባለ 42 ሜትር ርዝማኔ እና 140 ሺህ ሜትር ስኩየር ስፋት አድባር “ ያምራል” እያለ ማድነቅ ያልቻለው “ በአዱገነት አድባር “ ውስጥ ያለው ዘረኝነት አይኑን ስለደፈነው ነው ። ( ይህን በተመለከተ “ ያምራል “፡ ቴዲ አፍሮና  “ የመንዲ አድባር “ በሚል ርእስ ተከታይ መጣጥፍ ለማዘጋጀት እያሰብኩ ነው። )

***

አገራችን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለመውጣት በግለሰብ ደረጃ ቆራጥ ውሳኔ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በኢትዮጵውያን ዘንድ እየተንጸባረቀ ያለው የለውጥ ፍላጎት ጥልቅ ስሜትና እምነት የሚጠይቅበት ደረጃ ላይ ደርሳል። የኪነ-ጥበብ ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት የፖለቲካ ትኩሳትና ቁጭት በሚመጥን መልኩ መንቀሳቀስ ካልቻሉ የህዝቡን መሰረታዊ ድጋፍ ሊያጡ ይችላሉ።ከአሁን በኋላ በግማሽ ጎን የአገዛዙን መድረክ እያደመቁ፣ በግማሽ ጎን “እኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ነኝ” እያሉ፥ በሌላ በኩል ፖለቲካ አላውቅም የሚባለው አካሄድ ቢያንስ ከአጭር ጊዜ አኳያ የሚሰራ አይደለም።አይሰራም:: ይህ ማለት ግን ትናንትም ሆነ ዛሬ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የተለበሰ ቆሻሻ ልብስ ለማጠብ ጊዜው አልፏል ማለት አይደለም። ይልቁንስ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ህዝብ ህልምና ተስፋ በመሰነቅ፣ በኢትዮጵያውያን መሻሻል እንዲጠፋ የሚሞከረውን አንድነትና ፍቅር በመጠበቅ የራስ ሃውልት እንደገና ማቆም የሚቻልበት ሁኔታ የተመቻቸ ይመስላል። ግለሰብ ማንሳት ባይሆንብኝ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ለዚህ አገላለጥ ተስተካካይ ይመስለኛል። እርግጥ አንዳንዶች ራሳቸውን “የይቅርታ ደረጃ መዳቢ የስራ ሂዲት ባለቤት” በማድረግ ቀብተው መቶኛ  ሲያወጡ መመልከቱ የሚያስተዛዝብ ቢሆንም የሚያዛልቅ አይደለም። በህዝብ ወገኖች ጫንቃ ላይ ብዙ የመከራ ሸክም እያለና ብስጭት ባለበት ሁኔታ መወቃቀሱ ደግ ላይሆን ይችላል። የግል ዕምነትን አስቀምጦ ለመሄድ ያህል ግን ኢትዮጵያዊነታችን ዋናና ዘላቂ ፈተና፥ ወደፊትም እንደሃገር መኖር አለምኖራችን የሚወሰነው ከተጋረጠብን የዘረኝነትና ቅስም ሰባሪ ድህነት ስንወጣ ብቻ ነው። እነዚን መቀርቀሪያ መቀርቀሪያ የሚያካክሉ አደጋዎች ተሸክመን በእጭፍጫፊ ጉዳዮች ላይ ማተኮሩ ተገቢ አይመስለኝም። ታደለ ሮባ፣ ደረጀ ደገፋ፣ ነዋይ ደበበ፣ ሰለሞን ተካልኝ፣ ሰራዊት ፍቅሬ፣ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ፣ ሰማኸኝ በለው ይቅርታ ጠየቁ አልጠየቁ ኢትዮጵያን ወደመበተን እየመራ ባለው መሰረታዊ ጉዳይ ላይ የሚጨምሩት፣ ወይም የሚቀንሱት ነገር የለም። በግለሰብ ደረጃ ከታየ ግን ዋነኛ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው የኪነጥበብ ሰዎች ናቸው። ከገዳይና ዘረኛ ጋር ዕቁብ መጠጣት ደም ከመጠጣት የሚተናነስ አይደለም።

***

ቢፈቀድልኝ ቀደም ሲል ወዳነሣሁት እና የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ሊያውቁት ይገባል ወዳልኩት ወቅታዊ የአገራችን ሁኔታ ልመልሳችሁ። አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን እንደገለጠው አገራችን ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቃለች። በኢትዮጵያ አየር ላይ ላለፉት ሩብ ክፍለ-ዘመናት ህወሐት የዘራው የዘር ፓለቲካ በኢትዮጵያውያን መካከል ጥላቻ፣ አለመተማመንና የጠላትነት መንፈስ እንዲሰርፅ አድርጓል። በህወሐት አገዛዝ በታቀደ መልኩ እየተሰራ ያለው እኩይ ተግባር “ኢትዮጵያዊነት” እንዲደበዝዝና ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ምክንያት ሆኗል ።

ኢትዮጵያዊያንን እንደ ድርና ማግ ያስተሳሰሩን ማህበራዊ እሴቶች እየጠፉ በመሄዳቸው በፈንታው ቂምና በቀለኝነት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ እየተስፋፋ ያለው የመጠፋፋት መንፈስ ከግለሰብ አልፎ “ኢትዮጵያዊነት” ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ላይ ነው። የህወሓት አገዛዝ እየተከተለ ያለው ቅጥ ያጣ የዘረኝነት ፓለቲካ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያጠለቀው ገመድ የታነቀች ኢትዮጵያን እንድንመለከት እያደረገ ነው። ፀሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት “ደሃ አደግ” በሚለው ቲአትሩ እንደገለጠው የትላንቱ ጅል ጦርነት ዛሬ በዘር ጦርነት ተቀይሯል። ሠሞኑን በታደምኩበት አንድ የህዝብ ስብሠባ ላይ ተሠብሳቢውን ለማነቃነቅ ወደ መድረክ የወጣው ድምፃዊ ሻምበል በላይነህ በዘፈኑ መጀመሪያና ማሳረጊያ ላይ “ኢትዮጵያ በጎሳ ፓለቲካ አደጋ ውስጥ ገብታለች በዘር መደራጀት ቁምጥና ነው!” እያለ ሲያስጠነቅቅ ሠምቻለሁ። በውስጤም “እንደ ሻምበል በላይነህ የኢትዮጵያ ሁኔታ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ለማየት፣ ለመስማት፣ ለመናገር ስንቱ የኪነት ሰው አቅም አግኝቶ ይሆን?” የሚል ጥያቄ አንስቻለሁ።

መጨቅጨቅ አይሁንብኝና እስቲ እናንተ በቃለ መጠይቅ ውስጥ “የህዝብ ነን!” የምትሉ የኪነ-ጥበብ ሠዎች ራሳችሁን ፈትሹ። ከሙያ ባልደረቦቻችሁ ጋር ልብ ለልብ ሃሳብ ተለዋወጡ። አንዱ የጎደለውን አቅምና ወኔ ሌላው የሚሞላበትን መንገድ ፍጠሩ። ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ስሜት ተነጋገሩ። በህዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ በተግባር ግን ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆኑ የህወሓት አገዛዝ ባለሞሎች ጋር በድብቅ የሚሠሩትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አድርጓል:: አንድ ልትገነዘቡት የሚገባው ነገር መስዋኣትነት የፓለቲከኞች ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ አርቲስቶችም በሞት፣ በእስራት፣ በመንገላታት እና በስደት የሚከፍሉት መስዋእትነት ሊኖር ይገባል። ኢትዮጵያ የታማኝ በየነ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የጅጋየው ሺባባው (ጂጂ) ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የብርሃኑ ተዘራ ብቻ አይደለችም።ኢትዮጵያ የቴዲ አፍሮ ብቻ አይደለችም።ኢትዮጵያ የሻምበል በላይ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የአብነት አጎናፍር ብቻ አይደለችም።

አሁን ያለንበትን የተመሰቃቀለ የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመረዳት፣ በአገሪቱ መጻኢ እጣፋንታ ላይ ያሰፈሰፈውን መአት ለመቋቋምና መፍትሔ ለመስጠት ዘወትር እነ ታማኝ በየነን የመስዋት በግ እያደረግን መቀጠል አንችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ህሊና ለመቀስቀስ ዘወትር የነፍስ ዕዳ ከእነሱ የምንጠብቀው መቆም አለበት። ዛሬም መስቀል አደባባይ ቆሞ ” ባንዲራችን የአያቶቻቸን የደም ውጤት ነው!” የሚልልን የሺ-ኪነጥበብ ሰው እንፈልጋለን። ዛሬም ህዝቡ የማደኸየቱን፣ አገርን ታሪክ አልባ እያደረጉ ያሉትን፣ አሰቃይቶ መግዛትና ማጋጨት የኩራታቸው ምንጭ ያደረጉትን ዘረኞች “ፌዜራሊዝም” በማለት በመረጃና ማስረጃ ተደግፈው የሚያጋልጡትን ዕልፍ አእዕላፍ ጀግና አርቲስቶች እንፈልጋለን። የ “ወርቅ፣ ብርና ነሃስ ዘር” እንዳለ ለገለጡልን ዘረኞች “የትኛው ዕኩልነት?” ብሎ የሚሟገትና ይህ አካሄድ እንዲበቃ የሚጮሁ መጥምቁ ዮናንሶችን እንሻለን። የሻብዕያ ጫማ ጠርገውና መቀመጫ ልሰው ወደ ስልጣን የመጡትን “ማነው ተላላኪው?” በማለት የሃፍረት ካባቸውን እንዲያጠልቁ የሚያደርጉ አርቲስቶች እንዳለ እንደእንጉዳይ መፍላት ይኖርባቸዋል። ይህን ማድረግ ስንችል የህወሃት የፕሮፓጋንዳ ማሽን “አኬልዳማ!”፣ “ጀሃዳዊ ሃረካት”፣ አዲስ አበባ እንደባግዳድ” የሚሉ ትያትሮችን ውጤት አልባ እናደርጋቸዋለን። ተደጋግሞ እንደተገለጸው ይሄን ለማድረግ ግን መስዋዕትነት ይጠይቃል። በህዝብ ላይ የሚፈጸምን ግፍ እንደ ራስ ላይ የተፈጸመ አድርጎ በመውሰድ “አናኛቱ” ማለት ያስፈልጋል።

ከዚህ በፊት በተለያዩ መጣጥፎች ደጋግሜ ብዬዋለሁ። አሁንም እደግመዋለሁ። የኢትዮጵያ አርቲስቶች ለአገራቸው እና ለወገናቸው የነበራቸውን (ያላቸውን) ተቆርቋሪነት አሳንሶ የማሳየት ፍላጎት የለኝም። አምባገነን እና ፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝን ለመታገል በስውርና ግላጭ የከፈሉት መስዋእትነት ለደቂቃም ሊዘነጋ አይገባም። እንደውም የሰሞኑን የፖለቲካ ጡዘት በአርቲስቶች ዙሪያ መሆኑን ስመለከት ዛሬም ሆነ ነገ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ወሳኝ የፖለቲካ ሃይል መሆነቸውን ተረድቻለሁ። የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ይሄን መጣጥፍ እየከተብኩ እዚህ መስመር ላይ ስደርስ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር የስራ ወንበሬ ላይ ቁጭ ብዬ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ሲጨዋወት እያደመጥኩት ነበር። እኔም መፃፌን አቁሜ የውይይቱ ተካፋይ ሆንኩኝ። በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አሻራውን አስቀድሞ ያኖረው ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር በቅርብ ቀን በሚያወጣው የግጥም መድብል ውስጥ ያስቀመጠው ማዕከላዊ መልዕክት “ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ወድቃለች፤ አባቶቻችን ኢትዮጵያ ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ ለማቆይት የከፈሉት መስዋዕትነት ዘወትር ሊታወስ ይገባል” የሚል እንደሆነ አጫወተን። እንግዲህ ለደቂቃም ሊዘነጋ አይገባም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። እርግጥም በክፉ ዘመን “ሴጣን ሲዘምር” ፣ “ተኖረና ተሞተ” የሚል ግጥም ወደ አደባባይ ያዋል የኪነ-ጥበብ ሠው መዘንጋት የህሊና ተጠያቂ ያደርጋል። “ የኋላው ከሌለ የፊቱ የለም “ የተባለው በዚህ ምክንያት ነው ።

ከዚህ እውነት ጎን ደግሞ አንድ መዘንጋት የሌለበት ቁምነገር አለ። አገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ማለፍ የማንችላቸውን የህልውና ጥያቄ ከፊታችን አምጥቶ የደነቀረ ብች አይደለም። ኢትዮጵያ የገባችበት ብሔራዊ ውርደት፣ የህዝብ እልቂት እና የተስፋ መጨለም በቁጭትና አጣዳፊነት መፍታት ካልተቻለ  የዘር ፍጅት ከፊታችን የተገተረ መራር እውነት እንደሆነ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ይህንን መራር እውነት በቁጭትና እውቀት ተኮር በሆነ መንገድ ለመጋፈጥ መድፈር ያስፈሊጋል። አሁንም በኢትዮጵያ መሬት ላይ የተነጠፈው መራር እውነታ የሕዝብ ጠላቶች የሆኑት የህወሓት አመራሮችና ጋሻጃግሬዋቻቸው የግፍ ስርቸውን እንዲያቆሙ አልተከላከልንም። በዘር ማበላለጥ ላይ የተሞረከዘ ፓለቲካቸውን አላስጣልናቸውም። ድምፃዊ ኤደን ገ/ስላሴ (የድምፃዊ አብርሃም ገ/ምድህን ባለቤት) የፓሊስ ማርሽ ባንድ አጅቧት የሙዚቃ ሲዲዋን ስታስመርቅ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት በጣም ግልጥ ነው። አገዛዙ በሚቆጣጠረው የፕሮፖጋንዳ ማሽን አንድ የትግራይ ተወላጅ አንዲት ነጠላ ሲዲ በ50ሺህ ብር እንደገዛ ሲነገር አሁንም እንዲታወቅላቸው የፈለጉት ነገር እጅግ በጣም ግልጥ ነው። በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ አልፎ በአለም ደረጃ አነጋጋሪ የሆነንና ሪከርድ የሠበረን ድምፃዊ እቤቱ ድረስ መጥቶ ቀረፃ ካካሔዱ በኋላ ማገድ የዘር ፓለቲካው የት ጫፍ እንደደረሠ የሚያመላክት ነው። የፓለቲካ ስልጣኑን ከየትኛው ዘር የፈለቁ ሠዎች እንደተቆጣጠሩትና አድራጊና ፈጣሪው እነማን እንደሆነ የተጋለጠበት ነው።

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በመንግስት የፕሮፓጋንዳ ማሽንም ሆነ ብሮድካስቲንግ ፍቃድ ሠጥቶአቸው የሚሰሩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በሙሉ (ኢቢሲ፣ ፋና፣ ኢቢኤስ፣ ዛሚ፣ ሸገር…) የህወሓት ባለስልጣናት ሳይፈቅዱላቸው ቴዲ አፍሮንም ሆነ እንደ አጫሉ ሁንዴሳና ጃንቦ ጆቴን የመሳሰሉ ድምፃውያን ማቅረብ እንደማይችሉ የፀና እምነት አለኝ። የእነዚህ ድምፃውያን መቅረብም ሆነ መቅረት ፓለቲካዊ ነው። እዛው ሳለ የህወሓት መከፋፈልን የሚያሳይ ነው። በተባራሪ እንደሠማሁት ከሆነ የወቅቱን አደጋ መሻገር የሚቻለው “ኢትዮጵያዊ ጭምብል” ካጠለቅን ነው የሚለው የህወሓት ብድን ቴዲ አፍሮን በሚዲያው ላይ በማቅረብ ተቀባይነቱን ከፍ ለማድረግ አስቦ ነበር። ይሄኛው ሀሳብ በገዱ አንዳርጋቸው በሚመራው የብአዴን ክፋይ ተቀባይነት አግኝቶ እንደነበረም ተነግሯል። ባለፉት ወራት የአማራ ራዲዬና ቴሌቪዥን አጼ ቴድሮስን፣ አጼ ሚንሊክን፣ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ ለማሳየት የሄደበት ርቀት የድጋፍ ምልክት ተደርጎ ሊታይ የሚችል ነው። በሌላ በኩል ቴዲ አፍሮ መቅረብ የለበትም የሚለው የህወሓት ብድን የወቅቱን አደጋ መሻገሪያው መንገድ የዘር ፓለቲካ አጡዞ ማስቀጠል እንደሆን አምኖ የሚንቀሳቀሰው ነው። ይሄኛው ሀሣብ ኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራው የኦህዴድ ክፋይ የሚቀበለው ሲሆን “እኛም አጫሉንን ጃምቦ ጆቴን እንድናቀርብ ይፈቀድልን” የሚል አቤቱታ ያቀረቡ እንደሆን ይነገራል። እንግዲህ በሁለቱ ተቃራኒ አመለካከቶች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም። ቴዲ አፍሮም የለም። ለወደፊቱም ተመሳሳይ ነው።

አረረም መረረም፣ ተቀበልነውም አልተቀበልነውም ህወሓት በድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን ላይ የፈፀመው አይን ያወጣ ወንጀል ህዝብን ከመናቅ የሚመነጭ ነው። አደባባይ ወጥተን መቃወምም ፤ ደፈር ብሎ ጩኽት ማሰማትም፤  በየልባችን ያለውንም አውጥተን ለመግለጥም ስለምንፈራ እንጂ ሁላችንም በውስጣችን አልቅሰናል። ተናደናል። አንዳንዶቻችን ልጓም የሌለው የስልጣን በቅሎ ላይ ቁጢጥ ያሉትን እየተሳደብን የጾም ሽለላና ቀረርቶ አሠምተናል። ጥቂቶቻችን ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ ጆሮ ያልፈጠረባቸውንና አፍንጫቸውን ፎንነው የሚገዙንን ህወሓቶች አደብ እንዲያስገዛልን ፈጣሪያችንን ለምነናል። ሠማይ የወደቀባቸው የመሰላቸውና አንጀታቸው የተኮማተረባቸው ደግሞ በፌስቡካቸው ቀጥታ ስርጭት እየተንዘፈዘፍ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ቅሬታ ቂምን፣ ቂም ደግሞ ህዝባዊ አምፅን ሊወልድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ማልቀስ ብቻ ! መናደድ ብቻ ! ቀራርቶ ብቻ ! መንዘፍዘፍ ብቻ !

በሌላ በኩል “አበስሁ ገበርሁ” በሚያስብል መልሱ የአገዛዙ ባለቤቶች፣ የእልፍኝ አስከልካዮችና በጥላቻ ላይ የተሞረኮዙ የዘውግ ፓለቲከኞች በህወሓቶች እርምጃ ጬቤ ሲረግጡ ለመታዘብ ተችሏል። ሀሣብን በሀሣብ ማሸነፍ ያቃታቸው እነዚህ ድውያኖች የበቀል ጅራፋቸውን ባልተቆጠበና ባልተገራ አንደበታቸው ሲያረግፉት ማየት ያሸማቅቃል። በግልፅ ለመናገር እነዚህ አሳዳጊ የበደላቸው የአገዛዙ ግልገል ማጋጣዎች የሚናገሩትንና የሚፅፉተን መመልከት ሠው መሆናቸውን ያጠራጥራል።  የስነ-ህይወት ጠበብቶች ሰው እንደ ሰውና እንደ ሰው ባህርይ መኖር ካልቻለ እንደ እንሰሳ ይቆጠራል። እነዚህ ልባቸው ከድንጋይ የጠጠረ እንስሳዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አይናችሁ ላፈር ብሏቸው እንኳን ከኣኩይ ድርጊታቸው መቆጠብ አልቻሉም። እርግጥ ይህን ፀሐይ የሞቀው ሚስጥራቸውን ሕዝቡ ይበልጥ እየትረዳው በመምጣቱ በፍርሃት ተወጥረዋል። የሚሰነዝሩት ብትረ የፈሪ ዱላ ሆኗል። የፈሪ ዱላ ደግሞ ቦታ አይመርጥም። ይሄ ብቻ አይደለም ። “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” እንደሚባለው በፈሪነታቸው ላይ ድንጉጥንት ስለታከለበት ሁሉንም ሠው በጠላትነት የመፈረጅ ህመም ተጠናውቶአቸውል። በዚህ ምክንያት ያገኙትን ሁሉ ለመጥረግ ይፈልጋሉ።

አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን ላይ ህወሓቶች የወሰዱት እርምጃ ስሩ የሚመዘዘው ከዚህ መሰረታዊ ባህሪያቸው ነው። ህወሓቶች ፈሪዎች ናቸው። ህወሓቶች ድንጉጦች ናቸው። ለህወሓቶች ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላታቸው ነው። ሌላው ቀርቶ እነሱ የፈለቁበት የትግራይ ህዝብ ለቀናቶች ፊቱን ቢያዞርባቸው አፈሙዛቸውን በማዞር ጥይታቸውን ያርከፈክፉበታል። ባለፉት ወራት በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታና የአመራር ለውጥ ፍላጎት ያላስተናገዱበት መንገድ ከላይ የቀረበውን አባባል ትክክለኛንት የሚያረጋግጥ ነው። ተጋዳሊት ፈትለወርቅ ገ/እግዜብሔር (ሞንጆሪኖ) እና የክልሉ ፕሬዝዳንት አባይ ወልዱ እንዴት የለውጥ ጥያቄ ይነሳል በሚል በቁጣና በምሬት እርምጃ መውሰዳቸውን በግላጭ ሰምተናል። የትግራይ ህዝብን አቅጣጫ ልማስቀየር የስፖርት ውድድርን ተገን አድርገው አማራና ትግሬውን እርስ በራስ ለማጨፋጨፍ የጎነጎኑት ሴራ መጋለጡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከአካላቸው ላይ መጥፋት ያልቻለውን ሰምበር ለመሸፈን ያደረጉት እኩይ ተግባር ነው ።

ነገ ከነገ ወዲያ የትግራይ ህዝብ ካንቀላፋበት ሲነቃና ወደ ውስጡ መመልከት ሲጀምር በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የተነሳውን የለውጥ ንፋስ መከላከል ሳይሆን የለውጥ አካል ይሆናል። የትግራይ ህዝብ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን እየተገለለ ያለው የስጋና ደም ልጆቹ በፈጠሩት አፓርታይድ መሠል ፓሊሲ መሆኑን መገንዘብ ሲጀምር መራራውን ትግል ልጆቹ ላይ ማንጣጠሩ አይቀርም። በትግራይ ተወላጆች አዛዝነት የሚመራው ሠራዊት በሕዝቡ ላይ መተኮሱን አቁሞ ጠመንጃውን ወደእነሱ ማዞር የሚጀምርበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። እርግጥ ከአጭር ጊዜ አኳይ አብዛኛው የስርአት ለውጥ ፈላጊ የሆነው ኢትዮጵያዊ ከላይ በቀረበው ሃሣብ እንደማይስማማ ይረዳኛል። ይሁን እንጂ በለውጥ አመራር ሳይንስ ውስጥ እንደተገለፀው የለውጥ ንፋስ አቅጣጫ ካልተጠበቀ ቦታ ሊነሳ ይችላል። ምንአልባትም ከአባይ ወልዱ መኖሪያ ቤት፣ ምንአልባት ከሳሞራ የኑስ እቁባቶች ቤት ፥ ምንአልባትም ከአዜብ መስፍን ቤተሠቦች ቤት። ማን ያውቃል?

 

↧
↧

ህዝባችን በዘረኝነት ከመምራት እንታቀብ !! – ከኣስገደ ገብረስላሴ ወልደሚካኤል

$
0
0

በገራችን ዘረኝነት ግጭት በመፍጠር የአገራችንና የህዝባችን ኣንድነት እንዲላላ ብሎም በመበታተን ፣በማዳማት ፣ የኢህኣደግ ገዥዎች የስልጣን እድሚያቸው እንዲራዘም ዋናው ተዋናኝ ማነው ????
————————-;——————————–
1ኛ የ ኢህኣደግ ኣባል ፓርቲዎች ኣማራር እና ለከፋፍለህ ኣገዛዙ በመሳሪያነት የሚጠቀምባቸው የኣጋር ፓርቲዎች ኣማራር ፣ እንዲሁም ከኢህአደግ የበሰበሱ ኣማራሮች ቡሙሱና ቁርኝት ያላቸው ፣ ይህ ስርኣት ሆንብሎ የሰራቸው ምንጩ የማይታወቅ የሀገራችን ሃብት ጨምድደው የያዙ እና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ባለ ህብቶች ፣ ነጋዴዎች ፣ በነጻ ኢኮኖሚ አሰራር መሰረት የን7ድና የኢንቨስት ስራ እንዳይሰሩ በሞኖፖል ኣፍነው በመያዝ መፋናፈኛ ያሳጡዋቸው ናቸው ። በተጨማሪ ከፈደራል እስከ ቀበሌ የተዘረጉ የገዥ ፓርቲና አጋሮቹ አስተዳዳሪዎች ሰላዮች ፣ ካድሬዎች በህዝብ ሃብት የበለጸጉት እና ተጠቃሚዎች ናቸው ።

2ኛ የህወሓት ፣ የበኣዴን ፣ የኦሆዴድ ፣ የኣጋር ፓርቲዎች ፣ የኢህኣደግ የህትመተና የሚዲያ ልሳኖች ፣ በየቦታው የሚገኙ የትምህርት መሳራጫ ኤፍ ኤሞች በዋናነት የኢትዮጱያ ተለብዥንና ሬድዮ መሳራጫዎች በሚቃኙዋቸው መሰረት ሀገራችን በዘረኝነት ፣ በሀይማኖት ፣ በጎጥ ልዩነት እየናጡ ለመበታተን ያለመታከት የውሼት መርዝ ረጭተዋል ።እየረጩም ይገኛሉ ።

3 ኛ በተቃዋሚ ስም ኢህኣደግ በቡዙ ሚሊዮን ብር ባጀት በመመደብ ገዝቶ ያቋቋማቸው ( ለማሳሪያነት ቅንጅትን ፣ አንድነትን ፣ ኢድዩን ፣ ሚኢኣድን ፣ የኢትዮጲያ ዲሞክራሲያዊ ህብረት ፣ ኢደባ ሌሎችን በውስጣቸው ሰርገው በመግባት ያፈረሱ የቀሙ ፣ገዥ ፓርቲ በነዳቸው የሚነዱ ፣ በኃላቸው ኣንድሰውም እንኳ ተከታይ የሌላቸው ፣ ገዥ ፓርቲ በዜጎች ያደረሰው ግድያ ማሰር መሰቃዬት ምዝበራ እየመረቁና የዘረኝነት ግጭት እንዲስፋፋ ያለመታከት ለሊት ተቀን ይሰራሉ ። እነዚህ ቅጥሮኞች በኦሮሞ በጎንደርና በትግራይ ፣ በጎጃም፣ በቅማንት ፣በደቡብ ህዝቦች ፣ በቤልሻንጎል በኣኝዋክና በጋንቤላ ፣ላለቁ ዜጎች የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝና ከዛ በላይ ሊሄድ እየቻለ በመንግስታችን ጥንቃቄ በተሞላበት የተወሰደ እርምጃ ነው በማለት ባንዳዊ ምስክርነት የሰጡ ።

የሀገራችን ህዝቦች በነዛ ያለፋት የዘውዳዊውና የፋሽሽት ስርአት ደርጊ እንኳን ፣ ለዛውም የሃይማኖት የዘር፣ የቢሄር ፣ የጾታ ፣ ልዩነት ለዛ ለበሰበሰ ስርኣታቸው እድሜ ለመራዘም ታሳቢ በማድረግ ይፈጥሩት ለነበሩ የከፋ ፍለህ ግዛ ስርኣታቸው እድሜ የመራዘም መርዛማ ሴራ ሳይበግረው በመበጣጠስ ሁሉም ኢትዮጱያዊ በመላው የሀገራችን ጠቅላይ ግዛቶች ፣ኣውራጃዎች ፣ ወረዳዎች ፣ እስከ ሩቅ ጠረፎች በመዝለቅ የአካባቢው ቋንቋ ባያውቅም በነበረው የኣማርኛ ቋንቋ በመግባባት ሃኪም ፣ኣስተማሪ ፣ፍርድቤት ፣ የእርሻ ባለሙያ ፣ሌላ ስቢል መስራቤት ሰራተኛ ፣ፖሊስ የሃይማኖት መሪዎች ፣ ሁሉ በእጣ ወይ ቦሙያ ተወዳድረው ፣ ያለኣንዳችን ስጋት ሁሉም ቦታ ኣገሬ ብለው በየተመደቡበት የስራ መስክ ተነጻጻሪ ነጻነት ኑሮዋቸው ይሰሩ ነበር ።

ይህ ስልግን ገዥዎች የሚፈጥሩት ችግር እንቅፋት ኣልነበረም ማለት ኣደለም ። እጅግ ዘርፈ ቡዙ ኣስቀያሚ ስራ ይሰሩ ነበር ። የኣሁኑ ስርኣት መሪዎች ግን በሁሉም ነገር የፈጸሙት እና እየፈጸሙት ያሉ ሴራ በአለም ተወዳዳሪ የለለው ነው ። በፈጠሩት ለከፋፍለህ ስርኣታቸው ይሳካ ዘንዳ ሀገሪቱ በቋንቋና በባህል የአከላለል መዋቅር ዘርግተው የአንድ ክልል ዜጋ ወደሌላ ክል ሄዶ ኣገሬ ነው ብሎ በሃገሩ ነጻ ሆና እንዳይኖር ፣እንዳይ ሰራ በማድረግ በዜጎች መካከል ጥላቻን መቃቃር እንዲፈጠር ኣድረገዋል ። እነዚ ህወሐት ኢህኣደግ የሰራቸው ኣዲስ ምልምለ ሰርጎ ገብ በዱኖች ፣ህወሓት ኢህአደግ ህዝባችንና የኣለም ህብረተሰብ ለመታለልና ለፖለቲካ ፍጆታ ለማግኜት ብሎ በሚያደርገው ድርድርም ከ21 ተቃዋሚ ፓርቲዎች 16ቱ ስሪቶች ናቸው ። ይህን የሚያሳዬን ድርድሩ በምልኣተ ጉባኤ ስለሚሆን የድርድሩ የህወሓት ኢህአደግ ፍሏጎት የሚያሟሏ ይሆናል ።
4ኛ ሀቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚባሉም የትግል ስልትታቸው ምንይሁን ምን ባገር ውስጥና በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ገዥ መንግስትና መዋቅሩ ፣ሸሪኮቹ ፣ሚዲያዎቹ የሚረጩት የዘረኝነት እልቂት ኣውቀውና ተገንዝበው ጥቃቅን ልዩነት ካላቸው በበኩሌ እንካን ውሃ ቀጠነ ልዩነት እንጅ መሰረታዊ ልዩነት የለቸውም ምናልባች በትግል ስልት በሰላም ወይ በትጥቅ ትግል የሚል ሊኖራቸው ይችላል
በተረፈ ሌላ ችግር የላቸውም ።

ሁኔታው ይህ እያለ ግን የኢህኣደግ ተንኮል ወይ ሴራ እያጋለጡ ወደ ህዝብ ዘልቀው በመግባት የህዝብን ኣንድነት ኣጠናክረው ጠላትና ወዳጁ ኣውቆ ሰላማዊ ማእበል እንደመፍጠር ፈንታ የኢህኣደግን እድሜ የሚያራዝሙ የፓርቲ መሪዎች ተብለው በውጭ ሬድዮጣብያዎች የተለያዩ ሚዲያዎች ፣በማህበራዊ ሚዲያዎች በመጽሄትና ጋዜጣ ፣ ራሳቸው በሚፈጥሩት መድረኮች ፣ በተለያዬ ኣህጉር የሚኖሩ ኣባሎቻቸው ኣድርገው ለአንድ ብሄር ያተኮረ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ በህወሓት ኢህኣደግ የጭቆና ፣የእስራት ፣የስደት የመበታተን ሞዴል እያለ ። ከ5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንደ ጨቋኝ ገዢ ፣ከሞቶ ሚሊዮን በላይ የኢትየጱያ ህዝብ የበለጠ ተጠቃሚ ኣድርጎ በማዬት ከህወሓት ኢህአደግ ጎን እንደተሰለፈ ኣድርገውታል ። ይህ ብቻ አይደለም የሌላ ቢሄር ህዝብም በተለይ ንቃተ ህሊናው ዝቅተኛ የሆነና ኃላ ቀር ኢሊቶች በወንድማቸው የትግራይ ህዝብ ጥላቻና መጠራጠር እንዲያሳድሩ አድርገዋል ። ይህ ተግባር ለሀወሓት ኢህአደግ እድሜ መራዘምያና የሀዝባችን እሴታችን የሆነው የኣንድነታችን ታሪካችን የሚንድ ነው ።

የትግራይ ህዝብ ግን ደርግ በሀገር ደረጃ ጠራርጎ ማስወገዱ ፍትሃዊና ለመላው ህዝባች ያስደሰተ ነበር ። የትግራይ ህዝብ ግን ደርግን ለማስወገድ የበለጠ ሂወት ሀብት ከፍያለሁና የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ኣለብኝ ኣላለም ። ይህ ባህል ከጥንት ጀምሮ ለባእድ ወራሪዎችና ለባንዳዎች ሲዋጋም እኔ በጠረፍ ኣጥር ሆኜ የበለጠ መስዋእት ስለከፈልኩ የበለጠ መጠቀም ኣለብኝ ኣላለም ። የእድል ጉዳይ ሆነና ባለፉት ስርኣቶች ይሁኑ የባሰ ደግሞ የኣሁኑ ዘረኛ ስርኣት በስሙ እየነገደ በስሙ የቢሌኖች ባለቤት እንደሆነ እያዳናገረ በ26 ኣመት የኣፈና አገዛዙ ለሂወታች መኖርና ኣለሞኖር ወሳኝ የሆነ ውሃ እንኳን ኣላጠጣንም ። ዋና ከተማችን መቀሌ እስከ ኣሁን የህወሓት ኢህኣደግ ውሃ ኣልቀመስንም ። ሌሎች የአውራጃና የወረዳ ከተሞችም እንደዚሁ ተጠቃሚ ኣልሆኑም ። የፍትህ የመልካም አስተዳደር የዲሞክራሲ የሁሉም መቡቶች መከበር ለሽታውም የለም ። ዜጎች የሚታሰሩበት የሚሳቃዩበትም ድብቅ እሱር ቤቶች የበረሓ 06 እሱር ቤት በትግራይ ነው የሚገኜው ። ኣልምተናል እያሉ የሚኩራሩበት በዘውዳዊው ስርኣት ሉኡል ራስ መንገሻ ስዩም የሰሩዋቸው ፣የጀመሩዋቸው ወይ ያቀዱዋቸው ነው የጠገኑ ሌላ እንደ ዩኒፈርሲቶች ህክምና ት ቤት የሰሩዋቸው ቢኖሩም ትንሽም ቢሆን ካልሰሩ ስርኣታቸው ስለማይኖር ብቻ ነው እንጅ ለትግራይ ህዝብ ደንግጠው ኣይደለም ። እኒህ ሰዎች በኤፈርት በሞቶዎች ቢሌን የሚገመት ሀብት ያለው በህወሓት ጥቂት መሪዎቻቸውና ታማኝ ካድሬቻቸው ባለቤትነት ነው ተይዘው ያሉ ? ታድያ የትግራይ ወጣት በሳሀራ በልቢያ ፣በየመን ፣ በሱማል በሌሎች የኣፍሪካ ኣገሮች ኣቋርጦ ሲሰደድ በባህር ሲበላ በሱዒዲ አረብያ ሲረሸን በኣልሲሲ ሲታረድ ልጆቹ እየታፈኑ ሲሸጡ የትግራይ ህዝብ ኣልፈለታል ያስብላልን ? የህወሓት ኢህኣደግ ተጠቃሚ ከሆነ ለምን ይህ ሁሉ መከራ ለብቻው ይደርሰዋል ( ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሚዲያዎቻቸው የተግራይ ህዝብ በህወሓት ይደርሰው ያለው ሰቆቋ ኣንድ ቃልም ተንፍሰው ያውቃሉን ? ) በፍጹም ።

እስት እማውቀው ሃቅ ልናገር በቅርብ በስማልና በኦሮሞ የተፈጠረ የዘር ግጭት የሞተው ህዝብ የወደመ ሃብት የትግራይ ወታደር ነውን ? በኣጠቃላይ በኦሮሞ የነበረ ህዝባዊ አመጽ የእረቻ በኣል እንደ መንስኤ ያለቁት ወገኖች በትግራይህዝብና የት ግራይ ወታደር ነው ? በወለጋ ፣በደቡብ ህዝብ ያለቁ የአማራ ወገናኖች ፣ በጎንደር ፣በባህርዳር ፣ በጎጃም የነበረ ሀልቂት የትግራይ ህዝብ ነውን ? አግኣዚ ክፍለጦርስ ትግራዋይ ነው ፣? ሁሉም ውሸት ነው ምክንያቱም ኣግኣዚ ድሮ በትግራይ ተወላጆት ተሞልቶ ነበር ይህደግሞ ከበረሃ ይዞት የመጣ ሰራዊት ነበር ።ይህ በኣሁኑ ጊዜ ነበረ ሆኖዋል ። በአግኣዚ የሚባል በኣጠቃላይ በኢትዮጱያ ያለው ሰራዊት እኮ የህወሓት መሪዎች እየነገሩን ያሉ ከሞቶ 1 % የትግራይ ተወላጅ ወታደር የለም ፣ በኦሮሞ ያለቁ ወገኖች የክልሉ ፓሊስና የክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ናቸው የጨረሹዋቸው ። በሌሎች ክልሎችም እንደዚሁ ነው ። የምናልባች ጠንከር ባለ ኣካባቢ ጦር ሃይል ጣልቃ ገብቶ ይሆናል። ግን ደግሞ የትግራዋይ ሰራዊት ኣስተዋጽኦ ባዶ ሆኖዋል ። ምክንያቱም ህወሓት ራሱ እንዲመናመን ኣድርጎታል ። ምክንያቱም ለስልጣኑ ስላሰጋው ። ከሻለቃ በላይ የነበረ የህወሓ የበላይነትም በኣሁኑ ጊዜ ነበረ ነው የሆነው ። በኣሁኑ ጊዜ እቺ ኣገር ጨምድደው ይዘዋት ያሉ የህወሓት መሪዎች የሰሩዋቸው ሰው በላዎች ከኦሆዴድ ፣ከበኣዴን ፣ከደቡብ ህዝቦች ከኣጋር ፓርቲ መሪዎች ብዙ ፋሽሽቶች ተፈጥረዋል ።ታድያ ተቃዋሚዎች ይህን ሀቅ ለምን ኣይታያቸውም ለጥቂት መሪዎች ለመምታት ሲሉ ለትግራዋ ህዝብ ለማጥላላት በጅምለ ይመታሉ ? እንደዚህ ኣካየድ ተቃዋሚዎችና ሚድያዎቻቸው ለህወሓት ኢህኣደግ መደገፍ ኣይደለምን ?

በኣዲስኣበባና በክልሎች ያሉ ህንጻዎች ኩባንያዎች የህወሓት መሪዎች እና የተግራይ ህዝብ ነው ። የሀገራችን ሃብት የተቆጣጠሩት ትግራዎት ናቸው በሚል ቅን ለሆነው የኢትየጱያ ህዝብ በመቀስቀስ የትግራይ ህዝብ እንዲገለል ኣድርገዋል ።

ሃቁ ግን ልናገር አዲስ ኣበባ እንመልከት ኣራት አይነት ሃብታሞች ኣሉ ከነሱም ፣
1ኛ ለረጅም ጊዜ በንግድ ስራ ተሰማርተው ሰርተው ግብር እየከፈሉ የተጋዙ የአማራ የትግራይ የእሮሞ የደቡብበተለይ ውራጌ በንጽህና የናጠጡ ሃብታሞች ኣሉ
2ኛ ከየት ተነሱ የማይባሉ ምንጩ በማይታወቅ ቢሊዮኖሮች ትግራዎት ጎጃሞች ውራጌ ኦሮም ጎንደሬ ሰሜን ሽዋ ኦሮሞዎች ኣሉ የማን ኣካባቢ ይበዛል የሚል ሊለያይ ይችላል ። እነዚህ ሁሉ ግን የህወሓት ፣የበኣዴን ፣ የኦሆዴድ የሌሎች ፓርቲ መሪዎች ሸሪኮች ናቸው ከውጭ ሄደውም መነሻ ሃብት ያልነበራቸው ሸሪኮች ሆነው ሃብት የሰበሰቡ ኣሉ ።

3 ኛ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት የሰበሰቡ የሁሉም ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት እስከቀበሌ ያለው መዋቅራቸው ናቸው ለነዚህ ሆዳሞች መነሻ ሃብት የሚጠይቃቸው ቢመጣ መልሲ የላቸውም ። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ይህን ሀቅ በመገንዘብ ተንትነው ጠላትና ወዳጅ ለይተው እንደማጋለጥ ፈንታ ትግራይ በባዶ ሆዳ ናጠጠች ይሏቷል ። ይህ ደግሞ ባልበላ በላ የሚባለው ያለው ትግራዋይ ሳይወድ በግድ ከሚጠላው የህወሓት ቡዱን ጎን ሆኖ ዘበኛ ይሆናል ።

4ኛ የናጠጡ የሀገራችን ሃብት በመዳፋቸው ያስገቡ ኤፈርት በትግራይ ህዝብ ፣ ጥረት በኣማራ ህዝብ ስም የአማራ ህዝብ ግን ኣ ያውቀውም ፣ ድንሾ በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚነግድ ፣ ወንዶ በደቡብ ህዝቦች የሚነግድ ፣ ሌሎች አጋር ፓርቲዎችም ተመሳሳይ ሃብት ኣላቸው ። በነዚ የፓርቲ ባለስልጣናት የእንድስትሪ ፣ የደረቅና ፈሳሽ ትራንስፓርት በሽ የሚቆጠሩ ካሜኖች ፣ የኮንስትራክሽ ኩባንያዎች ፣ የአስመጭና የላኪ ኩባንያዎች ፣የበንክ እንሹራንስ ፣ ኣክስዮኖች ፣የሚዲያ ማእከላት እና የህትመት ኩባንያዎችየማይኩሮ ፋይናንስ ወይ የብድርና ቁጠባ ባንኮች በቁጥጥራቸው ናቸው ።ከነዚህስ የትግራይ ህዝብ ምን ተጠቀመ ?
የሚገርመው ነገር ግን የትግራይ ህዝብ በሁለት ምድጃ ማኸል እየነደደ መሆኑ ነው ። በኣንድ በኩል በህወሓት መሪዎችና ካድሬዎቻቸው ተሰቃይታለ ፣በኣንድ ለኣንድ የስለላ መረብ ተይዛል ።
በሌላ በኩል በተቃዋሚዎች ና በሌላ ህዝብ ተገልለዋል ፣ ።

የትግራይ ህዝብ ከኢህኣደግ ጋር በመወገን ለመብቱ ኣይታገልም ይላሉ ፣
——;———;;;—————————-//////
የትግራይ ህዝብ በዘር በቢሄር ልዩነት በመፍጠር አንጻር የኢትዮጱያ ህዝብ አይነሳም ። የኃላ ታሪኩም የሚነግረን እሱ ነው ። የኃላ ታሪኩ ይቆይና ባለፈው 25 አመት ለህወሓት መሪዎች በህቡእና በግልጽ እየታገለ ተጉዛል ። ለህወሓት ኣዲስ ኣበባ ካስገባ ጀምሮ ስለየሀገር ሉኣላውነት ክህደት ከሰራዊቱ ጀምሮ የህወሓት ኢህኣደግ ክህደት በሚመለከት አድማ ኣንስቶ እነመለስና ቡዱኖቹ 32 000 ታጋይ ታስረዋል ተባርረዋል ፣በእሱር ቤት ሞተዋል ። በዛን ጊዜ ማንም ዜጋ ተው ኣላላቸውም ። ይህ ታጋይ ሙሱናን ጸረ ዲሞክራሲ ፣ስለጣን በወታደር መያዙ ፣ በወገነ በዘመድ ወደ ስልጣን ቦታ ማስቀመጥ ፣በወቅቱ ለነበሩ የደፈጣ ተዋጊዎች ይወሰድ የነበረ ግድያ ማሰር ወዘተ ተቃውማል ።በትግራይ ክልልም ህወሓት ይወስደው ለነበረ ኣቃም በመቃወማቸው በ06 ገብተው ታስረዋል በከባድ ቅጣት የተቀጡም ኣሉ ።

መቸ ይህ ብቻ ህወሓት ኤርትራ ቀይባህር ይዛ ልትገነጠል ሀገራችን የባህር በር የለላት ማድረጉ የትግራይ ህዝብ በግንባር ቀደምት ተቃውሞ ኣሳዩቷል የተቃወሙ ወገኖች ያለፍርድ ታስራል ተቀጥተዋል ።

የትግራይ ህዝብ ኢህኢደግ ባደረጋቸው ምርጫዎች በመጀመሪያ 1987 ዓ ም ብቻ በርከት ያለ ህዝብ መርጦታል ።ከዛበኃላ በኣራቱ የምርጫ ዘመናት ኣልመረጠም የድምጽ ካርዱ ተቀምቷል ።ህወሓት ግን በትግራይ 100% ተመረጥኩ ነው ያለን ።

ሽኣብያ ሀገራችን ለመውረር ሲዘጋጅ በቅርብ ይከታተለው ስለነበረ ለህወሓት መሪዎች ተናግሮ ሰሚጀሮ ስላጣ በጅማ ኢህኣደግ ጉባኤ ከንመለስና ቡዱኖቹ በኣቋም ተለያይቶ ወጣ ።

በ1997 ዓ ም የፓርላማ ምርጫ ውድድር ቅንጅት ተዋዳዳሪ ያላቀረበበት በቡዙ ወረዳዎች ተመርጧል ። በ2002 / በ2007 / የትግራይ ህዝብ ለዓረና ወይ መድረክ ነው የመረጠ ።

ከትግራይ ህዝብ ኣብራክ የወጡ የአረና ታጋዮች ኣባላቱ በግፍ ተገድለዋል ታስረዋል በከባድ የስቃይ ምርመራ ከባድ የስነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል ፣ ካገር ውጭ ተሰደዋል ፣ ኣሁንም በእሱር ቤት እየተሰቃዩ ይገኛሉ ። የተቃዋሚ ዓረና ወይ ደጋፊዎቹ በማናቸውም ቦታ ሰርቶ ሊኖር አይፈቀድም ።

ባለፈው ኣመት ህወሓት ኢህአደግ ሆን ብሎ የፈጠረው የዘር ግጭት በተለያዩ መድረኮችተቃውሞ አሰምተዋል ።በተለይ የህወሓትና የበኣዴን መሪዎች የወልቃይት ጸገዴ እንደመነሻ አድርገው አመራ ትግራ በሚል ሊፈጥሩት አስበውት የነበረ የዘር እልቂት የትገራይ ህዝብ የሚያደርጉት የነበረ ቅስቀሳ በማክሽፍ ኣደጋው ሊቀንስ ችሏል ። ሃቁ ግን የወልቃይት ጸገዴ ጥያቄ ሁለቱ ፓርቲዎች ኣፍነውት እንጅ በ184 ዐ ም ነበር የተጀመረው ። መፍቲሄውም በሰላምና በዲሞክራሲ መንገድ ነበር ።

ሌላስ የትግራይ ህዝብ ኣርሶ ኣደሩ ሙሁሩ ተማሪ ነጋዴው ባለሃብት ወዘተ ለስብሰባኑ እምቢ ፣ ወደ ወታደር ተሰለፉ እቢ ፣ ኑ የካቲት በኣል ኣክብሩ እቢ ፣ ኑ ተሃድሰናልና እንንገራቹ እምቢ እናንተ ኣትታደሱም እምቢብሎ ከነ አባይ ወሉና ቡዱኖቹ ተፈጥጦ ይገኛል ። ይህ ህዝብ ባደረገው ግልጽና ስውር ተጋድሎ ህወሓት ኢህኣደግ የቀበሌ ሴቶች በስንዴ የተሰበሰቡ እንዲሁም ተጠቃሚ ካድሬዎች ጀሮ ጠቢዎች ብቻ ይዞ እንዲቀር ኣድገዋል ። ታድያ ከዚህ በላይ መታገል ኣለ እንዴ ? በውጭ ሆኖ የህዝቦች ትግል ሳያውቁ በሬድዮ ጣብያዎች እየወጡ ህዝብን መደናገር ።በማህበራዊ ሚድያ አገርን የሚበታትን የዘር መርዝ መርጨት ለህወሓት ኢህኣደግ ደግፎ በጎኑ መቆም ነው ።ሌላ ትርጉም ኣይሰጠውም ።

ይህ ሀሳብ ከነመፍትሄው የሚጠቁም ኣስተያዬት ይቀጥላል ።
ከኣስገደ ገብረስላሴ ወልደሚካኤል

↧

ከመቀሌ አቻው ጋር ጫወኣየባህር ዳር ከነማ ክለብ ጥፋተና ተብሎ ቅጣት ተፈረደበት

$
0
0

ከመቀሌ አቻው ጋር ሲጫወት በትግራይ ደጋፊዎች ተደብድቦ ወደ አማራ ክልል የተመለሰው የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥፋተኛ ተብሎ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት ተጣለበት።

የባህር ዳር ከነማ ክለብ በረኛን ጨምሮ 4 ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ተባርረው በ7ቱ ብቻ ወደ መቀሌ ሄዶ ደጋፊ በሌለበት ዝግ ስታዲየም ጨዋታው ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለው 16 ደቂቃዎች ከመቀሌ አቻው ጋር ውድድር እንዲጨርስ ግዴታ ተጥሎበታል። 4ቱ ተጫዋቾቹ ለ3 ውድድሮች እንዳይጫወቱም እገዳ ተጥሎባቸዋል።

የጣና ሞገድ የሚል ያሜ ያለው የባህር ዳር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾቹ በመቀሌ ደጋፊዎች መደብደባቸው ሳይንሳቸው ክለባቸው የ450ሺ ብር ቅጣትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወስኖበታል። የመቀሌው ከነማ እግር ኳስ ክለብም 1 መቶ ሺ ብር ለይስሙላ ቅጣት እንደተጣለበትም ለማወቅ ተችሏል። የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች በያዝነው ግንቦት መጀመሪያ ከመቀሌ ከነማ ክለብ አቻው ጋር ትግራይ ድረስ ሄደው ሲጫወቱ በብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ስድብ በደጋፊዎች መሰደባቸው አይዘነጋም።

በተለይ በጨዋታው ጊዜ የተጎዳው የባህር ዳር ተጫዋች ከሜዳ ሲወጣ በወጌሻዎች ተወርውሮ ሲጣል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተቋርጦ ነበር። ተጨዋቾቹ ከመቀሌ እንዳይወጡ ታግደው እንደነበርም አይዘነጋም።

ከዚህ በኋላ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ቴሌቪዥና በአማራ ቴሌቪዥኖች እንዳይዘገብ ከተወሰነ በኋላ በመቀሌ ከንቲባ አቶ ዳንዔል አሰፋ የተመራ የልዑካን ቡድን ባህር ዳር ድረስ መጥቶ ሚስጥራዊ ስብሰባ ከአማራ ክልል ባለስልጥናት ጋር ሲያደርግ እንደነበር ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያስረዳል።

በመጨረሻም፣ የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጥፋተኛ ተብሎ የገንዘብ ቅጣትና የተቋረጠውን ውድድር በ8 ተጫዋቾች ብቻ እንዲጨርስ፣ 450 ሺ ብርም እንዲከፍል ግዴታ ተጥሎበታል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ፣ (ኢሳት) የጨዋታውን በረብሻ መቋረጥ ተከትሎ የነበረውን ሂደት ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል። ምን እንኳን ጥፋቱ የመቀሌው ክለው ነው ቢባልም፣ የባህርዳር እግር ኳስ ክለብ የችግሩ መንስዔል ተደርጎ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል መግለጻችንም አይዘነጋም።

↧

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ አምባሳደር ሰየመች

$
0
0

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንጋፋው ዲፕሎማት ማይክል አርተር ሬኖር በኢትዮጵያ ቀጣዩ የሀገራቸው አምባሳደር እንዲሆኑ አጭተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንጋፋው ዲፕሎማት ማይክል አርተር ሬኖር በኢትዮጵያ ቀጣዩ የሀገራቸው አምባሳደር እንዲሆኑ አጭተዋል፡፡ አምባሳደር መታጨቱና መሾሙ በሁለቱ ሃገራት መካከል ላለው ጠንካራ ግንኙነት መቀጠል በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ የዩናይትድ ስቴትስ ኢምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዴቪድ ኬኔዲ አዲሱ አምባሳደር የሚተገበሩትን ፖሊሲ በተመለከተ እንደዚህ ወይንም እንደዚያ ይሆናል ማለት እንደማይችሉ ግን ጠቁመዋል፡፡ ከዋይት ሃውስ የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተለያዩ ሀገራት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት ማይክል አርተር ኔኖር በኢትዮጵያ የሀገራቸው አምባሳዳር እንዲሆኑ አጭተዋል፡፡ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

if(typeof(jQuery)==”function”){(function($){$.fn.fitVids=function(){}})(jQuery)};jwplayer(‘jwplayer-1’).setup({“image”:”http://www.satenaw.com/amharic/wp-content/uploads/2017/05/F85A1938-A48E-4836-9379-0EB0DD258848_w1023_r1_s.gif”,”file”:”http://www.satenaw.com/amharic/wp-content/uploads/2017/05/0119e8bc-f149-49fe-8df0-664594b71a30_32k.mp3″});

 

 

↧
Viewing all 2265 articles
Browse latest View live