ወለላዬ ከስዊድን
ቅዳሜ ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. (ኦክቶበር 31 ቀን 2015 እ.ኤ.አ.) በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ መርጃ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተደረገ። በዝግጅቱ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ተገኝተዋል። በቦታው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ አበበ ቦጋለ የውጪ እንቢተኝነት ሊቀመንበር እና አቶ ቸኮል ጌታነህ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራር ናቸው።
አቶ አበበ ቦጋለ ንግግር ሲያደርጉ
ዝግጅቱ ረፋዱን 8 ሰዓት (14፡00 ሰዓት) የተጀመረ ሲሆን፣ አቶ ጌታሁን ማሬ የዝጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ የስዊድን የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ዘለሌ ፀጋ ሥላሴን ስለዝግጅቱ ገለጻ እንዲያደርጉና ዝግጅቱንም እንዲመሩ ጋብዘዋል። አቶ ዘለሌ በበኩላቸው የከተማው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ያለበትን ሁኔታ ገልጸው፤ እንግዶቹንም በማስተዋወቅ አቶ አበበ ቦጋለና አቶ ቸኮል ጌታሁን ንግግር እንዲያደሩ ጋብዘዋል።
አቶ ቸኮል ጌታሁን ንግግር ሲያደርጉ
አቶ አበበ በአሁኑ ሰዓት አርበኞች ግንቦት ሰባት እየሠራ ስላለው የሥራ ክንውን እቅድና ዓላማ፣ እንዲሁም ደጋፊዎቹና አባላቶቹ እያደረጉ ስላሉት እንቅስቃሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ቸኮል ጌታሁን በበኩላቸው በኤርትራ ቆይታቸው ወቅት ስለተመለከቱት የአርበኛው ቆራጥነትና የዓላማ ጠንካራነት የገለጹ ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት የድሮ ጀግናችን ስም በመጥራት የምንቀመጥበት ጊዜ ሳይሆን እኛው እነሱን ተክተን በጀግንነት ስማችንን ማስጠራት የሚገባን ጊዜ ነው በማለት ደጋፊውንና አባላትን የሚያበረታታና የሚነሳሳ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለጨረታ የቀረበው ምስል
ከሁለቱ አመራሮች ንግግር በኋላ ተሰብሳቢው ሰው ጥያቄ እንዲያቀርብ ተጋብዞ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቷል። እንዲሁም ንቅናቄውን በተመለከተ ግልጽ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ በመቀጠል «በደል ይረሳል ወይ?» የሚል ግጥም በማራኪና በወለላዬ ከቀረበ በኋላ የገቢ ማሰባሰቢያ ጨረታ ተደርጓል።
ለጨረታ የቀረበው የንቅናቄው ሊቀመንበር የሆኑት የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ቆራጡ አርበኛ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከሚመሯቸው አርበኞች ጋር ሆነው የሚታዩበት «ላንቺ ነው ኢትዮጵያ» የተባለ ምስል ሲሆን፣ ይሄው ምስል በግልና በቡድን ተጫርቶ ከፍተኛ ፉክክር ከተደረገ በኋላ በአንድ መቶ አራት ሺህ የስዊድን ክሮነር (ከ21 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ) የስዊድን የስደተኞች ማኅበር አሸንፎ ምስሉን የግሉ አድርጎታል። ከዚህ ከጨረታ ከተገኘው ገንዘብ ሌላ ሁለት የቃል ኪዳን ቀለበቶች የመግቢያ ገንዘብ ሦስት መቶ ዶላርና ከዕጣ የተሰበሰበ ገቢ ተገኝቷል።
በወቅቱ በስደተኛ ማኅበሩ አባላት ይደረግ የነበረው ተሳትፎ ዝግጅቱን አድምቆት አርፍዷል። በጨረታው ጊዜም በመሃል እረፍት በሚደረግበት ወቅት የወ/ሪት ሙሉቀን አማረ «ኢትዮጵያዊት ነሽ አትበሉኝ» የሚል ግጥምና የወ/ሮ ውቤ ማሞ እንዲሁም የአቶ መብራቱ ፀሐዩ ቀስቃሽ ግጥሞች ቀርበዋል።
የጨረታው አሸናፊዎች ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ጋር
The post በስዊድን ለአርበኞች ግንቦት ሰባት መርጃ ገንዘብ ተሰበሰበ appeared first on Medrek.