በ1875 በሰሜን ሸዋ ፍቼ የተወለዱት መገርሳ በዳሳ በእስክንድርያው ፓትርያሪክ አቡነ ጴጥሮስ ተብለው የጵጵስና ማዕረግ ተቀብለዋል ።
መገርሳ በተከተሉት ሀይማኖት የምንኩስና ስርዓት መሰረት አለማዊ ስምን ትቶ በክርስትና ስም መጠራት ግድ በመሆኑም ጵጵስናን እስኪቀበሉ ድረስ አባ ኃይለማርያም በሚል ስም ሲጠሩ ቆይተዋል ።
አቡነ ጴጥሮስ ወይም አባ ኃይለማርያም ብንላቸውም ዞረን ዞረን መገርሳን ማንሳታችን ነው ።መገርሳ አባትና የኃይማኖት መምህር ሆነው የፈፀሙት ከፍ ያለ ስራ ለሌሎች መገርሳዎች፣ለሀይማኖቱ ተከታዮችና ሰማዕት የሆኑለትን አላማ እንጋራለን ለሚሉ ሁሉ አርአያ ይሆናል ።
አቡነ ጴጥሮስ የሞቱት አገሬን፣ህዝቤንና ሐይማኖቴን ብለው ነው ፣ እርግጥ ነው አቡኑ ላይ ሞት ከፈረዱባቸው ሶስት ዳኞች ሁለቱ የአገራቸው ልጆች ነበሩ ።መገርሳ ግን ከሆዳቸው ይልቅ ያስቀደሙት ነገር በመኖሩ በ11 ጥይቶች መደብደብን እንደ ሽልማት ቆጠሩት ።
ዋናው ጉዳይ እንዲህ አይነት መስዋዕትነት በተከፈለላት ምድር የምንገኝ ዜጎች የመገርሳን ደም የምንመልሰው ለወደቁላት አገር በመኖር መሆኑ ነው ።
ለአቡኑ አገሪቱ ቅድስት ፣ሉዓላዊትና ለዜጎቿ ብቻ የምትገባ ነበረች ፣ ይህን ለማጥፋት የሚሰራ ሲመጣ ግን ህይወታቸውን በሞት ለወጡ።
በየራሳችን ዘውግ እየተሰባሰብን የየመንደራችንን ባንዲራ ለመስቀል እየተራወጥን የመገርሳ ወይም የጴጥሮስ ልጆች ነን ማለታችን ቤት ያፈርስ ይሆናል እንጂ አይመታም ።
ለጉልበተኛው እያደላን ፍትህ ላንቲካ ስትሆን ካላገጥን ጴጥሮስን አላወቅነውም ፡ መገርሳ ለትልቅ አገር ክብር ራሱን ሰጥቶ ሳለ በዘውጌ ተሸፍነን ከእኛ ውጪ ያሉትን ካጠቃን የእርሱ ወገን ነን ለማለት ሞራሉን ከወዴት እናገኛለን ?
ባይሆን የጴጥሮስ አገር ለሁሉ የምትበቃ፣ፍትህ የሰፈነባትና ልጆቿ በተከፈለላቸው የህይወት ዋጋ ቀና ብለው የሚሄዱበት ዘመን እንዲመጣ እናዋጣ። መገርሳ ፍቼ ተወልደው የሁላችንም ሆነዋል፣ እኛስ የማን ነን?
አባ ጴጥሮስን ፍቼ ለመመለስ የምንደክም? ወይስ የመገርሳን ጀግንነት በእርገጤ፣በሀጎስ፣በጠንክር፣በጌድሌቦና በወዚር የደም ስር እንዲዘዋወር የምንቃትት?