ዛሬ ታላላቅ አፍሪካውያን ከተናገሩት መነሳትን መረጥሁ። አንጋፋው ደቡብ አፍሪካዊ ታጋይ ዴዝሞን ቱቱ “When the missionaries came to Africa, they had the Bible and we had the land. They said ‘Let us pray’. We closed our eyes. When we opened them we had the Bible and they had the land”. ተቀራራቢ ትርጉሙ “ሚሲዮናውያን ወደ አፍሪካ ሲመጡ መጽሃፍ ቅዱስ ይዘው ነው። እኛ ደግሞ መሬት ነበረን። ‘እንጸልይ’ አሉን። ለጸሎት ዐይናችንን ጨፈንን። ጸሎቱን ጨርሰን ዐይናችንን ስንከፍት ግን እኛ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ታቅፈን ስንቀር እነሱ ግን መሪታችንን ይዘውት አገኘን” የሚል ነው።
አዎ! ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ዚምባዌ ወዘተ… በቅኝ ግዛትነት ለመውረር የመጡት ነጭ ሚስዮናውያን ቀጥሎም መሳርያ የታጠቁ ናቸው። ከነጮች ወረራ ራሷን ተከላክላ የኖረችውን ኢትዮጵያን ባለፈው ሃያ አምስት ዓመት የወረሯት የእኛ መልክና ደም ያላቸው ወንድሞቻችን ወያኔዎች አገሪቷን ሲቆጣጠሩ አንገታቸው ላይ ኩሺት (መቀበርያ ጨርቅ) ምላሳቸው ላይ የዘረኝነት ከፋፋይ መርዝ ይዘው መጡ። “ሁላችንም በጎሳ እንደራጅ፣ በማንነታችንና በቋንቋችን እናተኩር” ብለው ሰበኩን።
በተቀነበበልን የጎጥ አጥር ገባንላቸው፤ ያለፈና አስከፊ የሆነውን ታሪካችንን እየመረጥን አፅም ቆፈርን፤ የምንበቃቀልበትን ስልት እያዘጋጁ ሲሰጡን ተቀበልን። ካለፈ ስህተት የባሰ ስህተት ውስጥ ገብተን መሳርያቸው ሆንን። አሁን ከእንቅልፋችን ባንነን ዐይናችንን ስንገልጥና ልቦናችንን ስናቀና መሬታችን፣ ቀሪው ሃብታችን፣ አጠቃላዩ ህልውናችን በእጃቸው ውስጥ ሆኖ ሲሳሳቁና ሲዘባበቱብን አገኘናቸው። እኛ እጅ የቀረው ለብሄር ብሄረሰብ መብታችን መከበር ራቁታችንን በየዓመቱ መጨፈርና በርሃብ፣ በስደት፣ በአጋዚ ጥይት ማለቅ ሆነ።
አባቶቻችን መጽሃፍ ቅዱስ ይቅርና መድፍ ይዘው የመጡ የውጭ ጠላቶችን እጃቸውን እየሰበሩ መልሰዋቸዋል። እኛ ልጆቻቸው ግን የኤይድስ ቫይረስ የሰውነት ሴሎችን ተመሳስሎ በማጥቃቱ መከላከል እንደሚያስቸግር ሁሉ የእኛን ደም፣ ቀለምና ቋንቋ የተካኑ የባንዳ ልጆችን ለይቶ ማጥቃት ስላልቻልን ለዚህ ወርደትና ውድቀት በቃን።
የህወሃቶች ብቸኛው መሳርያቸው ህዝብን መለያየትና መከፋፈል ነውና ይህንን ብቸኛ መርዛቸውን መቋቋም ከቻልን ሰላማዊ አገር የመገንባት ተስፋችን እውን መሆኑ የማይቀር ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዐይኑን መግለጥ የጀመረው ኢትዮጵያዊ የተከሰተለት እውነት ቢኖር ይኼው ነው።
አንገታቸው ላይ ኩሺት ብቻ ጠቅልለው የመጡት ወያኔዎች በአንድ ጀንበር ሚሊዮነር፣ የባለብዙ ፎቅ ጌታ፣ የከተማና የእርሻ መሬት ባለቤት፣ በውጭ አገራት የብዙ ካምፓኒዎች ባለድርሻ ሲሆኑ፤ ቀሪው ኢትዮጵያዊ የከተማ መሬቱን ተነጥቆ ዘበኛቸው፣ ከእርሻውን ተፈናቅሎ የቀን ሠራተኛቸው፣ መብራቱን ተቀምቶ ሻማ ይዞ የሚያበላቸው ተደርጓል። ይህ ሁሉ ካስከፋውና ተስፋ ከቆረጠ ደግሞ በስደት የየአገሩ እስር ቤት ታዳሚና ኩላሊት ገባሪነት ይጠብቀዋል።
ዛሬ የወላጆቻቸውን መሬት አይነጠቅም ብለው የተነሱ የኦሮምያ፣ የጎንደር፣ የጋምቤላ፣ ልጆችን የሚጨፈጭፉ ወያኔዎች አገዛዛቸውን ዘለዓለማዊ ለማድረግ የትምህርት ሥርዓቱን ሲገድሉ የእነሱ ልጆች በስዩም መስፍን የበላይ ተቆጣጣሪነት ልጆቻቸው በቻይናና በምዕራቡ ዓለም ትልልቅ ዩኒቨርስቲዎች ተምረው አሁን ያሉትንና ወደፊትም የሚፈጠሩትን የህወሃት ካምፓኒዎች እንዲመሩ፤ እያረጁ ከፖለቲካው የሚገለሉ አባቶቻቸውን የሚተኩ መሳፍንት እንዲሆኑ እየተዘጋጁ ነው። አገር ውስጥም የመለስተኛ ህወሃት ልጆች አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ ሲዳምኛ፣ ጉራጌኛ ወዘተ … እንዲሰለጥኑ ተመቻችቶላቸው በመላ አገሪቱ እንዲሰማሩ ሲደረጉ ሌላው ህዝብ ከራሱ ቋንቋ ውጭ ሌላውን በጥላቻ እንዲያይና ወንዝ በማያሻግር ሁኔታ በመንደሩ ታውሮ እንዲኖር ፈርደውበታል።
ወያኔዎች ይህ አስማታቸው አሁን የያዘላቸው አይመስልም። ዓላማቸው የገባው ኢትዮጵያዊ ከዳር ዳር ተንቀሳቅሷል። ዐይኑን ገልጧል። እየቆየም አጥርቶ ያያል። በተለይም ሁለቱን ታላላቅ ህዝብ ማለትም አማራውንና ኦሮሞውን ለመለያየት ብዙ የደከሙበት ቢሆንም አሁን ህዝቡ የአንድነትን መንገድ በመምረጥ ላይ ነው። ላለፉት ሰላሳ አመታት የተፈጠረው የልዩነት ክፍተት ቀላል ባለመሆኑ የብዙ ቅን ኢትዮጵያውያንን ድካም የሚጠይቅ ሥራ ገና ከፊታችን አለ።
እንደ ህወሃቶች የእንግሊዞች መርዝ ያንገበገባቸው የኬንያውያን የነፃነት አባት ጆሞ ኬንያታ ለወገኖቻቸው የሰጡት ምክር የቆየ ቢሆንም በተመሳሳይ ሁኔታ ላለነው ኢትዮጵያውያን ይጠቅማልና እንዲህ ላቅርበው። “የነበረው የዘር ጥላቻ ማብቃት አለበት። የጎሳ ጥቃትም ሊቆም ይገባል። ባሳለፍነው መራራ ሁኔታ ውስጥ አንኑርበት። ካለፉት የከፉ ታሪኮቻችን ይልቅ የወደፊቷን አዲሷን ኬንያ ማለም እመርጣለሁ። ይህንን ዓይነት ብሄራዊ ስሜትና ማንነት ከፈጠርን የኤኮኖሚ ችግራችንን ለመፍታት ረጅሙን ጉዞ መሄድ እንችላለን” ብለዋል። እኛም ብንሆን ያለፉ አስከፊ ታሪኮቻችንን እያስታወስን ወደ ኋላ ከምንድህ የወደፊቷን የጋራ ኢትዮጵያ እያለምን ወደ ፊት ብንራመድ ይጠቅመናል።
አዎ! ባለፉት ጊዚያት አባቶቻችን ሉአላዊነታችንን ለማስጠበቅ የከፈሉትን ጉልህ አኩሪ መስዋዕት ያህል ብዙ አስከፊና አሳፋሪ ታሪክ አለን። ያንን የሚክዱትም ሆኑ ያንን እየመረጡ የሚቆፍሩና በትናንት የሚኖሩ ዛሬን የማያዩ ጨለምተኞች ናቸው። ከሁሉም በላይ የወያኔ ጥሩ መሳርያዎች ይሆናሉና። የኢትዮጵያ አፈር ትናንት በደርቡሾች፣ በግብፆች፣ በጣልያኖች ጥይት ተደራርበው ከወደቁ ኦሮሞዎች፣ አማሮች፣ ትግሬዎች፣ ወላይታዎች፣ ሶማሌዎች፣ ሲዳማዎች ወዘተ ደምና አጥንት ውህደት የተቀመመ ነው። ዛሬም በወያኔ የአጋዚ ጥይትና ዱላ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባ፣ በአምቦ፣ በወለጋ፣ በሃረር፣ በጎንደር በሚወድቁ ወጣቶች እየታደሰ ያለ አፈር ነው የኢትዮጵያ አፈር።
ወያኔ ለሱዳን “እንካ” ብሎ ቆርሶ የሚሰጠው ዳቦ አይደለም የኢትዮጵያ መሬት። የአፄ ዮሃንስና ከሁሉም ጎሳ የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን አፅም የተቀበረበትን መሬት ነው የጣልያን እንቁላል አቅራቢ ሹምባሽ ልጆች ለማስረከብ በጓዳ የሚስማሙት። የአብዲሳ አጋ፣ የአበበ አረጋይ፣ የበላይ ዘለቀ፣ የገረሱ ዱኪ፣ የአሞራው ውብነህ፣ የአሉላ አባነጋ፣ የጀጋማ ኬሎ፣ የባልቻ አባነፍሶ አገር እንዲህ በቀላሉ ለባዕድ ስትሸጥ ልጆቿ በዝምታ ልንመለከት አይገባም።
ሚሊዮኖች በርሃብ እየረገፉ፣ ሺዎች እየተሰደዱ፣ ሺዎች በእስር እየማቀቁ፣ ሚሊዮኖች የሃፍረት ማቅ ለብሰው በሚኖሩባት፤ ጥቂት ዘረኞች አቅል ባጡባት አገር ላይ ዛሬ እየኖርን ትናንትን ለልዩነታችንና ለድክመታችን ምክንያት ማድረጉን እናቁም። ከዛሬው ተጨባጭ ችግራችን ተነስተን የነገዋን የሁላችን የጋራ አገር የመገንባት ተልዕኮ ላይ እናተኩር። ለነገ ተስፋችን እንቅፋት የሆኑ ጥቂት ዘረኞችን እንታገል። ከራሳችን ወንድሞች ቅኝ አገዛዝ ስር ነፃ እንውጣና ኢትዮጵያንና ህዝቧን ነፃ እናውጣ!
amerid2000@gmail.com
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
<!–
–>