አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል ለቡ አካባቢ በሚገኝ መዝናኛ ቤት ውስጥ ሰኞ ምሽት አንዲት ወጣት መግደሉ ተሰማ፡፡ ግለሰቡ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ተርፎ በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡
ሰሎሜ ጉልላት የተባለችው የ20 ዓመት ወጣት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን በለቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ በሚገኝ የጓደኛቸው መዝናኛ ውስጥ በመዝናናት ላይ እያሉ ነው ከተጠርጣሪው ገዳይ ጋር የተገናኙት፡፡
ለጊዜው ስሟን መናገር ካልፈለገችው ጓደኛዋ መረዳት እንደተቻለው፣ የፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰው ግለሰብ ከዚህ ቀደም ሰሎሜን አስቸግሮ ከሚያውቅ ግለሰብ ጋር በሚዝናኑበት ባር ውስጥ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ሁለቱ ሴት ጓደኛሞች መዝናኛ ባሩ ውስጥ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ከመውጣታቸው በፊት፣ ወደ መፀዳጃ ቤት ለመግባት ተስማምተው መሄዳቸውን ታስታውሳለች፡፡ ክፍሉ ራሱን የቻለ መዝጊያ ኖሮት መፀዳጃ ክፍሎቹም ራሳቸውን የቻሉ መሆናቸውን የገለጸችው የዓይን እማኟ፣ አንዱን ክፍል በሚከፍቱበት ወቅት ዩኒፎርም የለበሰው ፖሊስ ውስጥ ሆኖ ስላዩት ይቅርታ መጠየቃቸውን ትገልጻለች፡፡
ይቅርታቸውን ተቀብሎ እንደወጣ እነሱ ወደ መፀዳጃ ክፍሎቹ ገብተው ከደቂቃ በኋላ ሲወጡ የዋና ክፍሉን በር ቆልፎ ፖሊሱ መፀዳጃ ክፍል ውስጥ እንደጠበቃቸው አስረድታለች፡፡ ወደ ሰሎሜ ተጠግቶ “አንቺ ሰው የማታናግሪው ለምንድነው?” ብሎ በጥፊ እንደመታትና እንደወደቀች የገለጸችው የሟች ጓደኛ፣ እሷ በሁኔታው ተደናግጣ ወደ መፀዳጃ ክፍሉ ገብታ መቆለፏን ትናገራለች፡፡ በክፍሉ ውስጥ እንዳለች የተኩስ ድምፅ መሰማቱን፣ የማቃሰት ድምፅ ስትሰማ መውጣቷን ገልጻለች፡፡
ጓደኛዋ ሰሎሜም ሆነች ፖሊሱ ወድቀው እንዳየቻቸው ሰው እንዲደርስላት ብትጮህም፣ ለደቂቃዎች ያህል ማንም እንዳልደረሰ ትናገራለች፡፡
በኋላ ከደረሰችላት አንዲት እንስት ጋር በመሆን እስትንፋሷ የነበረውን ጓደኛዋን ለመርዳት እየሞከረች ሳለ፣ ፖሊሶች እንደደረሱና በሥፍራው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ በፒክ አፕ መኪና ይዘዋት መሄዳቸውን፣ ነገር ግን የጓደኛዋ ሕይወት ማለፉን ገልጻለች፡፡
ተጠርጣሪው የፖሊስ ባልደረባ ጭንቅላቱን በጥይት መትቶ ራሱን ለማጥፋት ቢሞክርም ሕይወቱ ባለማለፉ የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገለት ነው፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው ገና በሕክምና ላይ በመሆኑ ፖሊስ ቃሉን እንዳልተቀበለ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የወጣት ሰሎሜ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማክሰኞ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. በለቡ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ (ምንጭ፡ ሪፖርተር፡፡ ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም በግፍ እየገዛ ያለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የፌዴራል፣ የመንግሥት፣ ወዘተ የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ ፖለቲካው የህወሃት ገንዘቡ የኤፈርት ነው፡፡ ሁለቱ ደግሞ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ርዕሱንም ለዚህ እንዲገጥም አድርገነዋል)
*********************
ወጣት ሰሎሜ ጉልላትን በቅርብ የሚያውቃት አሌክስ አብርሃም ይህንን ይላል (ከራሱ ፌስቡክ ያገኘነው ነው)፡-
“ልጄ ... የበኩሬ … ልጄ ... ከሰፈር ልጅስ አስጣልኩሽ መሳሪያ ከታጠቀ ሰዉ በምን አቅሜ ላስጥልሽ“
የሟች እናት ለቅሶ ነበር … ይሄ ግን የአንዲት እናት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጲያዊ ጥያቄ ነው ለእኔ … ይታያችሁ ይች ትላንት ህልፈቷን የነገርኳችሁ ወጣት ሶሎሜ ጉልላት … ስትገደል አብራት የነበረችው ጓደኛዋ እንደገለፀችው … የታመመ ሰው ለመጠቅ ጆሞ ቁጥር 1 ወደሚባለው ኮንዶሚኒየም ይሄዳሉ … የሄዱበትን ጉዳይ ጨርሰው ወደ አንድ ካፌ ይገቡና ሲወጡ ወደመፀዳጃ ቤት ይሄዳሉ … መፃዳጃ ቤቱ ውስጥ ክላሽንኮቭ የታጠቀ የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ሰው ቁሟል አልፈውት ገብተው ሲመለሱ የመፀዳጃ ቤቱ የውጭ በር ተቀርሮ መታጠቢያ ክፍሉ ውስጥ ሰውየው ቁሟል …
ሟችን ጠርቶ “ሰላም በይኝ” ይላታል … ሰላም ለማለት ፈቃደኛ አልሆነችም … እናም ይህ ሰው በቦክስ ሟችን ይመታትና መሬት ላይ ይጥላታል … ቀጣዩ ጉዳይ ለማመን የሚቸግር ነበር … ጓደኛዋ ወደ አንዱ መፀዳጃ ክፍል ገብታ ከውስጥ ቀረቀረችው … ወዲያው ግን አካባቢው በተኩስ ድምፅ ተናወጠ … አራት ጥይቶች ተተኮሱ ሰውየው በሶስት ጥይት ሶሎሜን ነበር የደበደባት … በመጨረሻም ራሱ ላይ ተኮሰ … ሶሎሜ ህይወቷ ወዲያው ሲያልፍ ገዳይ ይሙት ይትረፍ አልተረጋገጠም!!
እንግዲህ መሳሪያ የታጠቁና የመንግስት እና ህዝብ አደራ የተሸከሙ ሰዎች የግል ስሜታቸውን መቆጣጠርና ሃላፊነትን ከግል ጉዳይ መለየት ካልቻሉ ምን እንላለን! ከዚህ በፊት ባህር ዳር ላይ በተመሳሳይ የወደድኳት ልጅ ተወችኝ በሚል ምክንያት በርካታ ሰዎችን ተኩሶ በመግደል ራሱን ስላጠፋው የፌዴራል ፖሊስ አባል ብዙ ተብሏል … ለመሆኑ ለእንደዚህ አይነት ለህዝብም ህዝብ እጠብቃለሁ ለሚለውም አካል አሳፋሪና አሰቃቂ የሆነ ድርጊት ተጠያቂው ማነው? በቃ የሆነው ሆነ ተብሎ ዝም ማለቱስ እስከመቼ?? (አሌክስ አብርሃም)
<!–
–>
The post ክላሽንኮቭ ያነገበ የህወሃት ታጣቂ የወጣቷን ህይወት አጠፋ appeared first on Medrek.