ሰንደቅ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዛሬ 46 ዓመታት በፊት የተመሠረተና በእንቅስቃሴውም አብዛኛውን የኢትዮጵያ አካባቢዎች (ክልሎች) በመሸፈን ላቅ ያለ ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ነው። ኮሚሽኑ ከሚያደርጋቸው መጠነ ሰፊ የልማትና የርዳታ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ፣ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል በቀዳሚ አርአያነት አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል። ከዚህና መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከኮምሽኑ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጋር ባልደረባችን ፍሬው አበበ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለውን አደረጃጀት ቢገልጹልን?
ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ በህግ ክፍል ማስታወቂያ 415/1964 በነጋሪት ጋዜጣ፣ ከታኅሣሥ 26 ቀን 1964 ዓ.ም ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት በመሆን ተቋቁሞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲም ሪፐብሊክ መንግሥት፣ የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጄንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሠረት፣ በኢትዮጵያዊ ነዋሪዎች የበጐ አድራጐት ድርጅትነት በምዝገባ ቁጥር 1560 ተመዝግቦ የማህበራዊና የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኝ የበጐ አድራጐት ድርጅት ነው። ድርጅቱ፣ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ቦርድና የአመራር አባላት ያሉት ኮሚሽን ነው።
በመሆኑም የልማት ኮሚሽን፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የወገን ደራሽ መሆንዋን በማረጋገጥ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የነፍስ አድን ርዳታ በማድረግ ብሎም መልሶ በማቋቋም እና በልማት በማገዝ ፈርጀ ብዙ አገልግሎት ሲስጥ ቆይቶአል፤ አሁንም እየሰጠ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- በአኹኑ ሰዓት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ዋና ትኩረቶች ምንድን ናቸው?
ብፁዕነታቸው፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የገጠር ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የሚስፋፉበትን መንገድ መቀየስ፣ በገጠር የሚኖሩ ዜጐች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ የመቀየስና የመሥራት፣ የኤች.አይቪ/ኤድስ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተቀናጀና የተጠናከረ ሥራ መሥራት፣ በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የበኩሉን የስራ ድርሻ ማበርከት፣ በእናቶች እና ሕፃናት ሥርዓት ምግብ ሥራ ላይ ትርጉም ባለው መንገድ መሳተፍ፣ ስደተኞችን የመቀበልና የማስተናገድ ሥራን አጠናክሮ መቀጠል፣ ችግር ፈቺ የሆኑ የልማት ስራዎችን በማጥናት እና በፕሮጀክት በማካተት የሥራ አጥ ወጣቶችን ና ችግረኛ ሴቶችን ተጠቃሚ በማድረግ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ኑሮአቸው የተሻሻለ እንዲሆን ማገዝ እና የመሳሰሉት ናቸው።
ሰንደቅ፡- በልማት የተለያዩ ዘርፎች በኮሚሽኑ የተከናወኑ ተግባራትና ተጨባጭ ውጤቶች ምን ምንድን ናቸው?
ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከበርካታ አገር አቀፍና የውጭ በጎ አድራጐት ድርጅቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በአገሪቷ በሚገኙ ክልሎች ለሚኖሩ አያሌ ማህበረሰቦች ከአሉባቸው ችግሮች እንዲላቀቁ በማድረግ ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን በመሆን አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ይኸውም በበርካታ ወረዳዎች የገጠር ልማት ፕሮጀክቶችን በመተግበር በመስኖ፤ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የተሻሻሉ ግብርና ዘዴዎችን በማሥረጽ፣ በገቢ ምንጭ ተግባራት፣ በአቅም ግንባታ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ በማህበረሰብ የአደጋ ጊዜ መቋቋሚያና መጠባበቂያ ፈንድ ማህበራትን በመመስረትና በማጠናከር፣ በሥርዐተ ምግብ አጠቃቀም፣ በሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ በኤች አይቪ እና በመሳሰሉት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል በኮሚሽኑ ሥር ባለው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች መምሪያ አማካኝነት ከጐረቤት ሀገራት ተሰደው የሚመጡትን እና ከስደት ተመላሾችን፣ ኮሚሽኑ ባቋቋመው የስደተኛ ካምፖች በመቀበል አስፈላጊውን ሰብአዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አድርጓል። ለዚህም ዐብይ አስረጂ የሚሆነው፣ ልማት ኮሚሽኑ በተገበራቸው በዘላቂነታቸው በተረጋገጡ የልማት ተቋማት እና ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት፣ በክርስቲያን በጎ አድራጎትና ልማት ድርጅት ጥምረት (CCRDA) በተደረገው የምርጥ ተሞክሮ ግምገማ ኮሚሽኑ በአገሪቷ ከሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በቀደምትነት አሸናፊ ሆኖ ለመሸለም በቅቷል። በተጨማሪም የክልል፣ የዞን እና የወረዳ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የልማት ኮሚሽናችን በተገበራቸው የልማት ሥራዎች በተጠቃሚው ሕብረተሰብ ላይ ያመጣውን ተጨባጭ ለውጥ በመመልከት ምስጋናና እውቅና እየቸሩን ይገኛሉ።
ሰንደቅ፡- በክርስቲያናዊ ተራድኦ ረገድ፣ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥና በድርቅ ኮሚሽኑ የፈፀማቸው ጉዳዮች ቢዘረዝሩልን? ለምሳሌ፡-
ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት ለዓለም አስጊ ለሆነው የአየር ለውጥ ችግር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአየር ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በፕሮጀክት ጥናት በማካተት ተግባር ላይ እያዋለ ነው። ይኸውም ለተጠቃሚ አርሶአደሮች የአየር ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝሪያዎችን በማቅረብና በማከፋፈል፣ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ እና ጥበቃ ሥራን በማጠናከር የጎላ ተግባር እያከናወነ ነው።
ልማት ኮሚሽኑ ለቤተ ክርስቲያን ደን ልማትና ጥበቃ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት የቤተክርስቲያ ደን ፕሮጀክት አጥንቶ በአጋርነት የሚሰራ ድርጅት በማግኘቱ በተመረጡ ገዳማት ላይ የደን ጥበቃና ማስፋፋት ሥራን መሠረት በማድረግ የተራቆቱ መሬቶች በደን የሚሸፈኑበትን ሁኔታ ለማስቻል ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል።
በተጨማሪም ኮሚሽኑ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጅ እና የሶላር መብራት ተከላ በ15 ገዳማት ያከናወነ ሲሆን ለወደፊቱም በሰፊው የሚሠራበት የልማት መስክ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።
የልማት ኮሚሽኑ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተቋማትን በመገንባት እና የመስኖ ልማት በማስፋፋት ወደፊት በድርቅ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ለመቋቋም የሚያችል ስራዎችን በአፋር እና በሰሜን ሸዋ የአፋር አዋሳኝ ወረዳዎች እና በሌሎችም ላይ በሰፊው በማከናወን ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች ውስጥ ፣ የሕዝቡ ተሳትፎ ምን ይመስላል?
ብፁዕነታቸው፡- ልማት ኮሚሽኑ ሥራውን እስከ ታች አውርዶ ለመሥራት የሚያስችል የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን በክልል እና በዞን ከተሞች ስላሉት በእነርሱ አማካኝነት ሥራው ማህበረሰቡን መሠረት አድርጎ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በሚንቀሳቀስባቸው የፕሮጀክት ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ሥራውን ለማስተዋወቅም ሆነ ከህዝብ ጋር ለመሥራት ምቹ መንገድ በመኖሩ እና የልማት ኮሚሽኑ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላለው የማህበረሰቡ በልማት ተሳታፊነት በጣም ከፍተኛ ነው። የልማት ሥራዎቻችን በዘለቄታዊነት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት የማህበረሰቡ ተሳትፎ የታከለበት በመሆኑ በግልጽ የሚታይ እውነት ነው።
ሰንደቅ፡- የስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን፣ መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላትና መልሶ ማቋቋም በኩል ኮሚሽኑ ሥራዎች ያገኙትን ውጤቶች ቢያብራሩልን?
ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ስደተኞችና ከስደት ተመላሾችን በመቀበልና አስፈላጊዉን ርዳታ በማድረግ በሀገሪቱ ቀደምት ታሪክ ያላት ስትሆን በዚህም ከአምስት አስርት አመታት በላይ አገልግሎቱን እየሰጠች ትገኛለች። በዚህም ቤተክርስቲያኗ የሀገሪቱ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለስደተኞችና ተመላሾች በተቀናጀ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ሳይጀመሩ እሷ ይህን አገልግሎት በቀደምትነት መስጠቷን ያሳያል። በነበሩት የድጋፍ ጊዜያትም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ የሆኑና መሠረታዊ ፍላጎቶችን ያማከለ ድጋፍና ርዳታ መስጠት ተችሏል።
በሂደትም የቤተክርስቲያኗዋ ክንፍ የሆነዉ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን 1964 በህግ ሲቋቋም የስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ እንደ አንድ የስራ ዘርፍ በማካተት በርካታ ተግባራትን ለመፈፀም በቅቷል።
ስደተኞችና ተመላሾች ጉዳይ መመሪያ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሥር በመሆንና የራሱን አስተዳደር በማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከመንግሥት፤ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና እና ከልሎች አለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን በበአዲስ አበባና ከተማ አካባቢዋ ባሉ ከተሞች እና በአራም ሀገሪቷ አቅጣጫ በሚገኙ 18 የመጠለያ ጣቢያዎች ማካኝነት ቁጥራቸው በየጊዜ የሚለያይ ቢሁንም በአሁኑ ሰዓት ከ801 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የተለያዩ ሀገር ስደተኞች ማለትም ከደቡብ ሱዳን፤ ከሶማሊያ፤ ከየመን፤ ከኤርትራ፤ ከኮንጎ፣ ከሱዳን፣ ወ.ዘተ ለመጡ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ላይ ይገኛል።
ይኽውም፡- ኮሚሽኑ ለስደተኞች የመጠለያ፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የገንዘብ፣ የጤና፣ የማህበራዊና የስነልቦና ምክር፣ የትምህርትና የሙያ ክዕኖት ስልጠና ድጋፍ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶችን ይሰጣል። በተጨማሪም ስደተኞች ቤታቸው እንዳሉ ሆነው እንዲሰማቸው ለማድረግ የሚኖሩበት መጠለያ አካባቢ ምቹ የሆነ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ይኸውም የአካባቢ እክብካቤ፣ የአካባቢና የግል ንጽሕና እንዲጠበቅ እንዲሁም የመጡበትን አዲስ አካባቢ እንዲላመዱ የማስተማርና የማሳወቅ ሥራዎች በሰፊው ይከናወናሉ።
በመሆኑም ስደተኞች በሚሰጣቸው የትምህርት እና የሙያ ክህሎት ድጋፍ የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ሆነው የተለያዩ የገቢ ምንች የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እራሳቸውን ለማቋቋም ላይ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ ስደተኞችን ከቤተሰብ ጋር በማገኛኘት ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ይሰጣል።
ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ስደተኞች የተለየዩ የቁሳቁስ ድጋፍ፤ በኤች አይቪ ኤድስ ድጋፍና እንክብካቤ፤ በግጭት አፈታት በፆታ ጥቃት ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም ይሰራል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ከመሰል አገራዊና የውጭ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅትና መተባበር ምን ይመስላል?
ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በሚተገብራቸው የልማት ሥራዎች እና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጥራት ከሌሎች ልቆ እስከ መሸለም ያበቃው ከሌሎች የልማት አጋሮች ጋር ተናቦ፣ ተቀናጅቶ እና ተባብሮ በመሥራቱ ነው። እንደሚታወቀው ዘላቂ ልማትን ማምጣት የሚቻለው ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ መስራት ሲቻል ነው።
ኮሚሽኑ ይህን መርሆ በዋናነት በመከተል በግልጽነት እና በተጠያቂነት እየተንቀሳቀሰ በአነስተኛ በጀት ታላላቅ የልማት ሥራዎችን በመገንባት እውን እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም ኮሚሽኑ በከፈታቸው የልማት የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችም ሆነ የፕሮጀክት ጽ/ቤቶች በሚሰሩባቸው አካባቢዎች ከሁሉም የልማት ባለድርሻ አካላት ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ በፕሮጀክት ሥራ መልካምድራቸው አስቸጋሪ በሆኑ ሥፍራዎች ሁሉ የተለያዩ የልማት ተግባራትን በማከናወን እና ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የካበተ ልምድ ስላላቸው በየፎረሙም በተምሳሌነት የሚቀርቡ ሆነዋል።
ሰንደቅ፡- የኮሚሽኑ ፕሮጀክቶች እና እንቅስቃሴዎች፣በሀገራዊ ሽፋን ያላቸው ስርጭት የተመጣጠነ ነው?
ብፁዕነታቸው፡- አዎን! በእኛ በኩል ሙሉ በሙሉ ባይሆን እንኳ ፕሮጀክቶች ያላቸው ስርጭት በአብዛኛው የተመጣጠነ እንደሆነ እምነታችን ነው። ኮሚሽኑ በአኹኑ ሰዓት በሚያካሂዳቸው 27 የሚሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች እና በ18 የስደተኞች መቀበያ ካምብ አማካኝነት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የፕሮጀክት ወረዳዎች ላይ እየሠራ ይገኛል። ይኸውም በጋምቤላ ክልል፡ ጋቤላ ዙሪያ ወረዳ፣ ፊኝዶ፣ ተርኪዲ፣ ኩሌ፣ ሆኮቡ፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል፡ በከማሽ፣ በኩርሙክ፣ በሸርቆሌ፣ በባምፓሲ፣ በቶንጎ፣ አፋር ክልል፡ በአርጎባ ልዩ ዞን፣ ሰሙ ሮቢ፣ ዱለቻ፣ በኦሮሚያ ክልል፡ በጉርሱም፣ በጃርሶ፣ በአርሲ ሮቤ፣ በቄለም ወለጋ፣ በሶማሌ ክልል፡ በጂጂጋ፣ በሸደር፣ በቀርቢበያህ፣ በአውበሮ፣ በኮቤ፣ በመልካ ጂዳ፣ በሔለወይኒ፣ በቆልማንዩ፣ አማራ ክልል፡ በሊቦ ከምከም፣ በአንኮበር፣ በጊሼ ራቤል፣ በዳወንት፣ በበርኸት፣ ትግራይ ክልል፡ በክሊተ አውላዐሎ፣ በእንደርታ፣ ሽመልባ፣ አደ አርሹ፣ እፀጽ፣ ደቡብ ክልል፡ ጉራጌ፣ ሙዑር፣ ቡታጀራ፣ ወልቂጤ፣ ሲዳማ፣ ጌዲዮ፣ ይርጋ ዓለም፣ አለታ ወንዶ፣ አላባ፣ አርባ ምንጭ በ10 ወረዳዎች የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች በ150 ወረዳዎች ላይ የኤች/አይቪ እና የስነ-ተዋልዶ ጤና ሥራዎች ያከናውናል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች ሲያከናውናቸው የቆያቸው የልማት ፕሮጀክቶች እየተዘጉ እንደሆነ ይነገራል፣ ፕሮጀክቶቹ የሚዘጉበት አልያም የሚቋረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
ብፁዕነታቸው፡- ፕሮጀክቶች በተፈጥሮአቸው የጊዜ ገደብ አላቸው ይሁንና በኮሚሽኑ የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች እስከ ታች የሚዘልቀውን የልማት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶችን፣ ፕሮጀክት ጽ/ቤቶችን እና የማህበረሰብ ማህበራትን በመጠቀም ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የፕሮጀክት አፈፃፀም ሂደት በመከተል ሕብረተሰቡ የተለያዩ ሕግጋትን እና ደንቦችን እንዲያወጡ በማገዝ ፕሮጀክት በዘለቄታነት የሚቀትልበትን ሁኔታ እያመቻቸ በራሱ በህብረተሰቡ እየተመራ የሚከናወኑ የፕሮጀክት ዓይነቶች ናቸው።
ይህንን ለማድረግ ፕሮጀክቶች ዘላቂ በሆነ መልኩ እንዲቀጥሉ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ተጋባራት ይከናወናሉ። ተጠቃሚው ሕብረተሰብ በፕሮጀክት ጥናት፣ እቅድ፣ ክንውን፣ ክትትልና ግምገማ እንዲሳተፉ ይደረጋሉ። በዕቅድ ዝግጅት ወቅት የሕብረተሰቡ፣ ማህበራዊ ድርጅቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአካባቢ አመራሮች ወዘተ በፕሮጀክት ሂደት ውስጥ ያላቸው ድርሻ በግልጽ እንዲቀመጥ ይደረጋል። የፕሮጀክት መጀመሩን የሚያበስር ዓውደ ጥናት ይዘጋጃል፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ የእያንዳንዱ የሥራ ድርሻ በግልጽ ለውይይት ይቀርባል። የፕሮጀክት ተግባራትም እንደተጠናቀቁ በወቅቱ ለሚመለከተው ባለድረሻ አካላት በሕጋዊ የርክክብ ሰነድ ተረክቦ እንዲያስተዳድራቸው ይደረጋል።
ሰንደቅ፡- አንዳንድ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የበጎ አድራጎት ማህበራት ሕግ አላሰራ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ፣ በዚህ ረገድ ኮምሽኑ የገጠመው ችግር ይኖር ይሆን?
ብፁዕነታቸው፡- ኮምሽናችን ከ46 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየ ነው። በዕድሜው ሶስት መንግሥታት ተፈራርቀዋል። በእነዚህ ዘመናት ሕጎች ተለዋውጠዋል። ኮምሽኑ ሁሉንም እንደአመጣጡ አስተናግዷል። ፈቃድ ሰጪው አካል ቀድሞ በፍትህ ሚኒስቴር ነበር፣ አሁን ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ተቋቁሞ የራሱን ሕግ ይዞ እየሠራ ነው። በእኛ በኩል ቀድሞውንም እንቅስቃሴያችን ተጠቃሚውን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የገጠመን የጎላ ችግር የለም። 70 በ30 የሚለውን ሕግ ቀድመን ተግብረነዋል። ነገር ግን ይህ 10 በ90 (10 ከመቶ በላይ ከውጭ ለጋሾች ገንዘብ መቀበል አይቻልም) የሚለው የውጭ ለጋሽ ድርጅቶች ብዙም አልተቀበሉትም። እሱ ነው ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው። ሕጉ የሀገሪቱን ሁኔታ፣ የረጂዎችን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም። ለእኛ ግን ትልቅ ተጽዕኖ ግን ይህ አይደለም። የእኛ ትልቅ ተጽዕኖ ሕዝባችን ከተረጂነት መላቀቅ አለመቻሉ ነው። የውጭ እጅ ማየት የትም አያደርስም። የጠባቂነት መንፈስ ያሳድራል። ከጠባቂነት መንፈስ ተላቀቅቀን ባለን ሐብት መጠቀም መጀመር አለብን።
የረጂዎችንም ሁኔታ ስንመለከት ቅድሚያ የሚሰጡዋቸው ችግሮች በዓለም ዙሪያ እየበዙ መጥተዋል። ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ ጎረቤቶቻችን ሱዳንና ሶማሊያ በየዕለቱ ሰዎች እየሞቱ፣ እየተሰደዱ ረጂዎች ለእኛ ቅድሚያ ሰጥተው እጃቸውን ሊዘረጉልን አይችሉም። በዚህ ምክንያት ከልመናና ከፈረንጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ መስራት ይኖርብናል። ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ለተወሰነ ጊዜ ከችግር ለመውጣት ሊጠቅመን ይችላል፣ ለሽግግር ጊዜ ሊረዳን ይችላል። በዘላቂነት ግን የሚጠቅመን አይደለም።
ሰንደቅ፡- ለልማትና ለዕርዳታ የሚውል ሀብት ከሀገር ውስጥ ለማሰባሰብ ዕቅድ አላችሁ?
ብፁዕነታቸው፡- በትክክል፣ የውጭ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የሌለበት ሕግና ደንብ አውጥተናል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ምሁራን ጋር በዚህ ጉዳይ ሕግና ደንብ አዘጋጅተናል። በቀጣይ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በሥራ ላይ የሚውል ይሆናል። ይህ ጥናት ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆን ራሳችን እንድንችል የሚረዳን ይሆናል ብለን እናስባለን። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ 10 ሺ የሚጠጉ ሕጻናትን ይንከባከባል። ከእነዚህ ሕጻናት መካከል ወላጅ አልባ የሆኑ አሉ። ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው የሚረዱ አሉ። ለእነዚህ የምናገኘው ዕርዳታ በአሁኑ ሰዓት በግማሽ ቀንሷል። ምን እናድርግ ብለን አይተነዋል። በሃሳብ ደረጃ አንድ ምእመን አንድ ልጅ በፈቃደኝነት ቢይዝ ብለን ብዙ ሕጻናት መርዳትና መደገፍ እንደሚቻል አይተናል። በአሁኑ ወቅት በጉድፈቻ ወደውጭ የሚሄዱ ሕጻናት ምን አሳዛኝ ሁኔታ እየደረሰባቸው እንደሆነ እናውቃለን። ይህ ችግር እንዲቆም እዚሁ በሀገራችን ልንረዳዳ፣ ልንደጋገፍ ይገባናል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሾች ጋር ያለው ግንኙነትና የወደፊት ዕቅዱን ቢጠቁሙን?
ብፁዕነታቸው፡- የልማት ኮሚሽኑ በአኹኑ ወቅት ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር የላው ግንኙነት መላካም እና በተሸለ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ዋናው ጉዳይ ለሚረዱን ድርጅቶች፣ ለመንግሥት እና ለተጠቃሚ ማህበረሰብ ታማኝ ሆኖ በመገኘት የታለመለትን ፕሮጀክት በጥራትና ዘላቂ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በጽናት ማከናወን ነው።
ልማት ኮሚሽኑም ዋነኛ ዓላማ የሕብረተሰቡ ኑሮ ተሻሸሎ ማየትና ለተሻለ እድገት ማብቃት በመሆኑ በዚሁ ረገድ ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል። ግለፀኝነት እና ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በየጊዜው ከለጋሽ ድርጅቶች አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝ ቆይቷል፣ አሁንም እያገኘ ይገኛል።
በተለይ ኮሚሽኑ የህፃናት ፖሊሲን ቀርፆ እና አፀድቆ በሥራ ላይ ማዋሉ እና የማኅበረሰብ ተጠያቂነት አጋርነት (Humanitarian Accountability Partnership) ፍሬም ወርክ አዘጋጅቶ እና አፅድቆ በመተግበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ አጠናክሯል።
ኮሚሽኑ በቅርቡ ሁሉንም የፕሮጀክት አጋሮች ተወካዮችን በመጋበዝ ባለን የጋራ አጀንዳ እና በቀጣይ ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት በተመለከተ ለመወያየት ዕቅድ በመያዝ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ የራሱ የሆነ የገቢ ምንጭ ለማጠናከር ምን እየሠራ ነው?
ብፁዕነታቸው፡- ኮሚሽኑ ከውጪ ከሚያገኘው የርዳታ ድጋፍ በተጨማሪ በገቢ ራስን ለማጠናከር እንዲቻል ዓላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የውጭ ርዳታ በእጅጉ እየቀነሰ የመጣ ስለሆነ የተለያዩ የገቢ ምንጭ ዕቅድ ማዘጋጀትና መሥራት ግዴታ ሆኖአል። በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ ለገቢ ምንጭ መምሪያ አደራጅቶ ሥራ ጀምሯል።
በቃሊቲ አካባቢ ከሚገኘው የኮሚሽኑ ጋራዥ እና መጋዘን እንዲሁም የከርሰ ምድር መቆፈሪያ ሪግ ማሽን ጨምሮ ለዚሁ ተግባር በመዋል የገቢ ምንች ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው።
ኮሚሽኑ በአኹኑ ጊዜ የገቢ ምንጩን በበለጠ ለማጠናከር እንዲያስችለው አንድ የሻማ ማምረቻ ፋብሪካ እና በሁለት ቦታዎች ላይ የታሸገ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም መሠረታዊ ጥናቶች በማድረግ ላይ ይገኛል።
ሰንደቅ፡- ኮሚሽኑ በእንጦጦ አካባቢ የሆስፒታል ግንባታ እቅድ እንዳለው ይታወቃል፣ ሂደቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ ይቻላል?
ብፁዕነታቸው፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ46 ዓመት በፊት የልማት ኮሚሽኑን ሲያቋቁም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ስደተኞችን ለመርዳት፣ አባት እናት የሌላቸውን እና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ምዕመናን ከውጪና ከውስጥ በሚገኝ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ ነው።
ቤተክርስቲያኒቱ በገዳማት፣ በአድባራትና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብዙ በጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት ስላላት መሬቱን በማልማት ገዳማቱና ህብረተሰቡ ከልማቱ ውጤት እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ እንዲሁም በየአካባቢው የትምህርት ቤትና የጤና አገልግሎቶች እንዲሰጡ ከመንግስት ጋር በመተባበር መሠረተ ልማት ማካሄድ አንዱ ተግባፘ ነው።
ይህን የጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና ለማዳበር በቅርቡ በእንጦጦ አካባቢ አንድ ራሱን የቻለ ከፍተኛ ሆስፒታል ተቋቁሞ በአይነትና በጥራት አገልግሎት እንዲሰጥ እቅድ ወጥቷል።
ይህ የተጠቀሰው ሆስፒታል በአይነቱም ሆነ በባህሪው የተለየ ከመሆኑም ባሻገር የግንባታው ወጪ ከ370,000,000 የአሜሪካን ዶላር (ሦስት መቶ ሰባ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ) ሲሆን በኢትዮጵያ ብር ሲተመን ደግሞ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር (ከስምንት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር) በላይ ግምት ተይዞለታል።
ሥራው በሚጀምርበት ጊዜም ለ2100 ቋሚና ለ369 ጊዚያዊ በጥቅሉ ለ2469 ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
በተመሳሳይ ሂደት ሆስፒታሉ የልዩልዩ በሽታዎች መታከሚያና ማገገሚያ ክፍሎችና መሳሪያዎች የሚኖሩት ሲሆን የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን፣ የዲፕሎማቲክና የኤምባሲ ሠራተኞችን እና ከልዩልዩ አካባቢ የሚመጡ በሽተኞችን ለማከም ከ200 በላይ አልጋዎች ይኖረዋል።
ቅድመ ጥናቱ እንደሚያሳየው ይህ በቀጥታ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና ከአሜርካን ሀገር ከሚገኝ ሌዠንደር ኮርፕ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በአጋርነት የሚቋቋመው ሆስፒታል የውጪ ምንዛሪን በማስገኘትና በአገሪቱ ውስጥ የቱሪዝምን አገልግሎት ለማስፋፋት እንደሚረዳ ይታመናል።
የአሜሪካ መንግስትና በአሜሪካ ውስጥ ያሉ አበዳሪ ድርጅቶች ብድሩንም ሆነ ለብድሩ ዋስትና ለመስጠት ኃላፊ እንደሚሆኑ ቃል ገብተዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ግንባታውንና ከውጪ የሚገኘውን መዋዕለነዋይ እውን ለማድረግ በእንጦጦ አካባቢ ያለውና ለዚሁ ጉዳይ የተከለለውን መሬት ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ከሚመለከተው አካል ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ እንገኛለን።
The post በሀብት ማሰባሰብ ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ እየሠራ ያለ ተቋም appeared first on ሳተናው: Ethiopian Amharic News | Breaking News: Your right to know!.